Ethiopia Insider @ethiopiainsidernews Channel on Telegram

Ethiopia Insider

@ethiopiainsidernews


Ethiopia Insider is a digital media that provides news, updates, analysis and features.

Ethiopia Insider (English)

Welcome to Ethiopia Insider, your go-to source for all things related to Ethiopia! Our Telegram channel, @ethiopiainsidernews, is your digital media hub for news, updates, analysis, and features on all things Ethiopia. Whether you're a local resident, expat, or simply interested in learning more about this beautiful country, Ethiopia Insider has got you covered. From breaking news to in-depth analysis of current events, our team of dedicated journalists and experts work tirelessly to bring you the most up-to-date and relevant information. Stay informed with our daily updates on politics, culture, business, and more. Join our growing community of followers and be the first to know what's happening in Ethiopia and beyond. Don't miss out on the latest insights and stories - follow Ethiopia Insider on Telegram today!

Ethiopia Insider

26 Jan, 14:11


ጤፍ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ከመደበኛው ገበያ በ40 ብር ልዩነት እየተሸጠ ነው

ቪዲዮ፦ በአዲስ አበባ ከተማ ጎዳናዎች የአትክልት እና ፍራፍሬ ሽያጭ መመልከት እንግዳ አይደለም። ጤፍን በብትኑ መንገድ ዳር ዘርግቶ መሸጥ ግን እምብዛም አይስተዋልም።

ትላንት ቅዳሜ ጥር 17 በልደታ ቤተክርስቲያን አቅራቢያ ምርቶቻቸውን ሲሸጡ ከነበሩ ነጋዴዎች መካከል በአንደኛው ድንኳን የነበረው ይኸው የጤፍ ንግድ ነበር። ነጋዴዎቹ በመንገድ ዳር ድንኳን ዘርግተው ጤፍ መሸጥ ከጀመሩ ሶስት ወራት ሞልቷቸዋል።

ጤፍ በቀጥታ ከገበሬው እንደሚገዙ የሚናገሩት የጎዳና ነጋዴዎቹ፤ ምርቱን የሚሸጡት በኪሎ 120 ብር ነው። በአሁኑ ወቅት በመርካቶ፣ በእህል በረንዳ እና በወፍጮ ቤቶች፤ አንድ ኪሎ ጤፍ ከ150 ብር እስከ 160 ብር ዋጋ ይጠይቅበታል።

የጎዳና ነጋዴዎቹ አንደኛ ደረጃ የምንጃር ማኛ ጤፍ “በቅናሽ” የሚያቀርቡት፤ የየአካባቢው አስተዳደሮች በሚያደርጉላቸው ትብብር እንደሆነ ይናገራሉ። ሽያጭ የሚያከናወኑበትን ቦታ ያለምንም ክፍያ በነጻ ማግኘታቸውንም ለዚህ በማሳያነት ያነሳሉ።

“በዋጋው መቀነስ” እና “ያልተቀላቀለ ጤፍ” በማቅረባቸው ምክንያት “በርካታ ገዢ” እንዳላቸው ነጋዴዎቹ ያስረዳሉ። ከታች የተያያዘውን ቪድዮ ተጭነው፤ የጎዳና ላይ የጤፍ ሽያጩን ይመልከቱ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

25 Jan, 15:32


በጅማ ከተማ “በትንሹ 15 ሺህ ቤቶች መፍረሳቸውን” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከባለቤታቸው፣ ከሚኒስትሮች እና ከሌሎችም እንግዶች ጋር በመሆን፤ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ከተማ እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን በትላንትናው ዕለት ተዘዋውረው ጉብኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ጉብኝት በኋላ በሰጡት ገለጻ፤ በጅማ ከተማ ለተከናወኑ “የገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክቶች “በትንሹ 15 ሺህ ቤቶች መፍረሳቸውን” ተናግረዋል።

በከተማይቱ የነበረ መስጂድ እና ከአንድ ሺህ በላይ የመቃብር ቦታ ቀድሞ ከነበሩባቸው ቦታዎች መነሳታቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የጅማ ከተማ ነዋሪዎች “ቤቶቻቸውን ሲያፈርሱም” ሆነ ቦታዎችን ለፕሮጀክቶቹ ሲያስረክቡ “ካሳ አለመጠየቃቸውን” አብይ በአድናቆት አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተወለዱበት በሻሻ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው የጅማ ከተማ ህዝብ፤ ካሳ ከመጠየቅ ይልቅ “ ‘እስቲ ሃሳባችሁን አፍሱት፤ ልየው ነው’ ያለው” ሲሉም በገለጻቸው ላይ ጠቅሰዋል።

“የጅማ አካባቢ ማህበረሰብ ለእነዚህ ህልሞች፣ ለእነዚህ ሃሳቦች መወለድ የነበረው ሚና፤ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ትምህርት መሆን ያለበት ነው” ሲሉም አብይ በገለጻቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከአዲስ አበባ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 350 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የምትገኘው ጅማ፤ ከሌሎች ቦታዎች በተለየ መንግስት ለሚያፈልቀው ሃሳብ “የተከታይነት” (followership) አመለካከት እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

🔴ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/14902/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

23 Jan, 18:29


በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የግብጽ ተሳትፎ፤ “የትኛውንም ሀገር የማስፈራራት ዓላማ” እንደሌለው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ተናገሩ

የግብጽ በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ ውስጥ መሳተፍ “የትኛውንም ሀገር የማስፈራራት ዓላማ” እንደሌለው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ተናገሩ።

ፕሬዝዳንቱ “የሶማሊያን ደህንነት እና መረጋጋት ለማስፈን” ያለመ ባሉት አዲሱ ሰላም አስከባሪ ውስጥ፤ የግብጽ “ተሳትፎ አዎንታዊ” እንደሆነ ገልጸዋል።

አል ሲሲ በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት ዛሬ ሐሙስ ጥር 15 ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ጋር በካይሮ ተገናኝተው ከተወያዩ በኋላ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

ሐሰን ሼክ ወደ ካይሮ ያቀኑት በአዲስ አበባ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተገናኝተው፤ የሶማሊያ እና የኢትዮጵያን ግንኙነት ወደ ነበረበት ለመመለስ በተስማሙ በ12ኛው ቀን ነው።

ግብጽ እና ሶማሊያ ያላቸውን ግንኙነት ወደ “ስልታዊ አጋርነት (strategic partnership) ለማሳደግ የጋራ ፖለቲካዊ ቃል ኪዳን” እንደተፈራረሙ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይፋ ተደርጓል።

በሶማሊያ ያለው ሁኔታ ግብጽን ከ30 ዓመታት በላይ ሲያሳስብ የቆየ እንደሆነ በዚሁ መግለጫ ላይ የጠቀሱት ፕሬዝዳንት አልሲሲ፤ ሀገራቸው በሰላም አስከባሪው ተልዕኮ ውስጥ የሚኖራት ተሳትፎ በዋናነት “ለሶማሊያ ህዝብ ያላትን አጋርነት ለማሳየት ያለመ” እንደሆነ አስረድተዋል።

🔴 ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/14893/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

23 Jan, 17:19


በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምክንያት የአምራች ኢንዱስትሪዎች የብር ፍላጎት “በእጥፍ መጨመሩን” የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ተናገሩ

የኢትዮጵያ መንግስት ከስድስት ወራት በፊት ተግባራዊ ባደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምክንያት፤ የሀገሪቱ የአምራች ኢንዱስትሪዎች “የብር ፍላጎት” “በእጥፍ እንደጨመረ” የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናገሩ።

ሚኒስትሩ ባለፉት ስድስት ወራት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የቀረበው ብድር “አጥጋቢ” እንዳልሆነ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስረድተዋል።

አቶ መላኩ የመስሪያ ቤታቸውን የስራ አፈጻጸም ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ባለፈው መንፈቅ ዓመት ለአነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የስራ ማስኬጃ ብድር እና የሊዝ ፋይናንስ ለማቅረብ ታቅዶ የነበረው የገንዘብ መጠን 3.4 ቢሊዮን ብር ነው።

ሆኖም በዚህ ጊዜ ውስጥ ለኢንዱስትሪዎቹ የቀረበው 7.8 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የገንዘብ መጠኑ ከ2016 ተመሳሳይ ወቅት ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ4.4 ቢሊዮን ብር ገደማ ከፍ ያለ ነው።

ለከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች 28.7 ቢሊዮን ብር ለማቅረብ ታቅዶ እንደነበር ለፓርላማ አባላት ቤቱ ያስረዱት አቶ መላኩ፤ የተሳካው 24.87 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ተናግረዋል።

ለከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች የተሰጠው ብድር ከዕቅዱ አኳያ ዝቅ ቢልም፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ግን 4.9 በመቶ ብልጫ እንዳሳየ ሚኒስትሩ አመልክተዋል።

🔴 ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/14887/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

23 Jan, 16:28


የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አመራሮች ሹመት፤ የፓለቲካ ገለልተኝነትን “ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው” የሚል ትችት ቀረበበት

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ሹመታቸውን ያጸደቀላቸው የኢትዮጵያ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አመራሮች የአመራረጥ ሂደት፤ “ከፓለቲካ ገለልተኝነት” ነጻ መሆን የሚለውን መስፈርት “ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው” የሚል ትችት በፓርላማ አባል ቀረበበት።

ተሿሚዎቹ ለፓርላማ የቀረቡት፤ የፖለቲካ ገለልተኝነትን ጨምሮ እያንዳንዱ ጉዳይ “በደንብ” እና “በዝርዝር” ታይቶ መሆኑን የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ገልጸዋል።

ለህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ሶስት የኃላፊነት ቦታዎች 345 ግለሰቦች ተጠቁመው እንደነበር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ተናግረዋል። ለዋና ዕንባ ጠባቂነት በዕጩነት የተጠቆሙ ሰዎች ብዛት 60 እንደሆነም የዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አፈ ጉባኤው አስረድተዋል።

ዛሬ በፓርላማ ከጸደቀው የተቋሙ ሶስት አመራሮች ሹመት አስቀድሞ፤ የዕጩዎቹ አመራረጥ በአዋጅ የተቀመጠውን መስፈርት የተከተለ መሆኑ ላይ ጥያቄ ተነስቶበታል።

አንድ ግለሰብ በዋና ዕንባ ጠባቂነት በዕጩነት ለመወዳደር ከፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ መሆን እንዲሁም በህግ ወይም በተዛማጅ የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪ ሊኖረው እንደሚገባ በአዋጅ ተደንግጓል።

የአብን የፓርላማ ተወካይ ዶ/ር አበባው ደሳለው፤ “ሶስቱም ኃላፊዎች ከፍተኛ የመንግስት ተሿሚዎች ሆነው የሰሩ ናቸው። በተለመደው አሰራር ደግሞ ከፍተኛ የመንግስት ተሿሚዎች፤ ከገዢው ፓርቲ ነው የሚሆኑት። ስለዚህ ገለልተኝነት የሚለው ነገር ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ሆኖ አግኝተነዋል” ብለዋል።

🔴 ለዝርዝሩ ▶️ https://ethiopiainsider.com/2025/14876/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

22 Jan, 16:39


በትግራይ ክልል “አስቸኳይ ምርጫ” እንዲደረግ አሊያም “የመማክርት ምክር ቤት” እንዲቋቋም ኢህአፓ ጠየቀ

በትግራይ ክልል “አስቸኳይ ምርጫ” እንዲደረግ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፖርቲ (ኢህአፓ) ጠየቀ። የትግራይ ህዝብ “በመረጣቸው እንደራሴዎች እስኪወከል ድረስ “፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሁሉንም “ህጋዊ” የፖለቲካ ፓርቲዎች ያካተተ “የመማክርት ምክር ቤት” እንዲቋቋም ፓርቲው ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።

ፓርቲው ይህን ያስታወቀው ዛሬ ረቡዕ ጥር 14፤ 2017 አዲስ አበባ ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። በኢህአፓ የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የተጠራው የዛሬው መግለጫ፤ በክልሉ በቅርቡ በተከሰቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።

የትግራይ ክልል በፌደራል ምክር ቤቶች ያለው የውክልና ጉዳይም በዛሬው መግለጫ ላይ ተነስቷል። ከጥቅምት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ዓመት የቆየው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከመካሄዱ አስቀድሞ ካሉት ወራት ወዲህ፤ ክልሉ በህዝብ ተወካዮችም እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ያለው ውክልና ተቋርጧል።

“የትግራይ ህዝብ እንደ ፌዴሬሽን አባልነቱ በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 38 ወንበሮች ያሉት ቢሆንም፤ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ተወክሎ አያውቅም” ሲል ኢህአፓ በዛሬው መግለጫው አስታውሷል። ፓርቲው በዚሁ መግለጫው “ባለፉት አራት ዓመታት በፓርላማው እና በፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የሚተላለፉ ውሳኔዎች፤ የትግራይ ህዝብን ፍላጎቶች ያካተቱ አልነበሩም” ብሏል።

🔴 ዝርዝሩን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/14869/

🔴 የኢህአፓን መግለጫ እና ለጥያቄዎች የተሰጡትን ምላሾች በቪዲዮ ለመመልከት ➡️ https://youtu.be/3gxeQtoadn4

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

22 Jan, 14:21


ለኢትዮጵያ የወጪ እና ገቢ ንግድ ቁልፍ የሆነው የቀይ ባህር የጸጥታ ሁኔታ በቅርቡ ይሻሻላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዶራሌህ ወደብ አስተዳዳሪ ገለጹ 

በቀይ ባህር ላይ ያለው የጸጥታ ቀውስ ለመርከብ ጭነቶች ፍሰት “ትልቅ ተግዳሮት” መፍጠሩን የጅቡቲ የዶራሌህ ኮንቴነር ተርሚናል አስተዳደር ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አብዲላሂ አዳዌህ ተናገሩ። የጸጥታ ችግሩ እንደሚሻሻል የሚያመላክቱ “አዎንታዊ ምልክቶች” በቅርቡ መታየታቸውንም ገልጸዋል።

ከ95 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ የገቢ እና የወጭ ንግድ ጭነት የሚጓጓዝባቸው የጅቡቲ ወደቦች የቀይ ባህርን ተንተርሰው የሚገኙ ናቸው። ከዓለም አቀፍ ንግድ 12 በመቶውን ያህል የሚሸፍኑ ጭነቶች በየዓመቱ የሚጓጓዙበት የቀይ ባህር መስመር፤ ከህዳር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ በየመን የሁቲ አማጽያን ተደጋጋሚ ጥቃት ሲሰነዘርበት ቆይቷል።

ጅቡቲ ካሏት ወደቦች አንዱ የሆነውን የዶራሌህ ኮንቴነር ተርሚናል የሚያስተዳድረው ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ፤ የቀይ ባህር የጸጥታ ችግር ለሀገራቸውም ሆነ ለኢትዮጵያ የንግዱ ማህበረሰብ “እጅግ አስቸጋሪ ነው” ይላሉ። ዋና ስራ አስፈጻሚው ይህን ያሉት፤ ትላንት ማክሰኞ ጥር 13፤ 2017 በአዲስ አበባው ሸራተን ሆቴል በተካሄደ ኮንፍረንስ ላይ በተካፈሉበት ወቅት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ነው።

በቀይ ባህር በሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት የመርከቦች የመድረሻ ጊዜ “አስተማማኝ አለመሆኑን” የጠቆሙት አብዲላሂ አዳዌህ፤ ይህም በንግድ ማህበረሰቡ እና በወደቡ የስራ ክንዋኔ ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩን ተናግረዋል።

🔴 ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2025/14862/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

21 Jan, 17:33


ለአዲስ አበባ የነዋሪነት ምዝገባ የቀረቡ ከ25 ሺህ በላይ የመሸኛ ሰነዶች፤ ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ክልሎች ተላኩ

 
ለአዲስ አበባ የነዋሪነት ምዝገባ የቀረቡ ከ25 ሺህ በላይ የመሸኛ ሰነዶች፤ ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ክልሎች ተላኩ

ተለያዩ ክልሎች መሸኛ በመያዝ በአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት ምዝገባ ለማግኘት ከጠየቁ አመልካቾች ውስጥ፤ ከ25 ሺህ በላይ የሚሆኑት ያቀረቧቸው ሰነዶች ለተጨማሪ ምርመራ ለሚመለከታቸው አካላት እንደተላኩ የከተማይቱ የሲቪል እና የነዋሪነት ምዝገባ አገልግሎት ኤጀንሲ ገለጸ።

የመሸኛ ማስረጃዎች የተላኩላቸው ክልሎች፤ ምርመራቸውን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አጠናቅቀው ምላሻቸውን ያሳውቃሉ ተብሏል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኘው የሲቪል እና የነዋሪነት ምዝገባ አገልግሎት ኤጀንሲ ይህን የገለጸው፤ የዘንድሮውን በጀት ዓመት የመንፈቅ የስራ አፈጻጸም በተመለከተ በዛሬው ዕለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

መግለጫውን የሰጡት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ በመግለጫው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል “የመሸኛ አገልግሎት” እንደገና መጀመር ይገኝበታል።

ተቋሙ ከሌሎች ክልሎች ወደ አዲስ አበባ መጥተው በከተማ ነዋሪነት ለመመዘገብ ጥያቄ ካቀረቡ አመልካቾች ውስጥ በአንድ ሶስተኛው ላይ “የመሸኛ አገልግሎትን” አግዶ መቆየቱን አቶ ዮናስ በዛሬው መግለጫ ላይ አስታውሰዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ለተቋሙ የመሸኛ ሰነዳቸውን አስገብተው፤ የነዋሪነት ምዝገባ ለማከናወን ጥያቄ ያቀረቡ ሰዎች ብዛት 57,214 መሆናቸውን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

🔴ዝርዝሩን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/14856/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

21 Jan, 15:08


የአዲስ አበባ የግማሽ ዓመት የፍቺ መጠን፤ ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ በ34 በመቶ መጨመሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ ከተማ ባለፈው መንፈቅ ዓመት በይፋ የተመዘገበው የፍቺ መጠን፤ አምና በተመሳሳይ ጊዜ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ34 በመቶ መጨመሩን የከተማይቱ የሲቪል እና የነዋሪነት ምዝገባ አገልግሎት ኤጀንሲ አስታወቀ።

በዚሁ ጊዜ የተመዘገበው የጋብቻ መጠን፤ ባለፈው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከተመዘገበው በሰባት በመቶ መቀነሱንም ኤጀንሲው ገልጿል።

ተቋሙ ይህን የገለጸው የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸሙን አስመልክቶ፤ ዛሬ ማክሰኞ ጥር 13 በዋና መስሪያ ቤቱ በሰጠው መግለጫ ነው።

የመታወቂያ ስርጭት፣ የልደት እና የሞት ምዝገባ፣ ያላገባ የምስክር ወረቀት፣ የማስረጃ የማረጋገጥ ስራን ለመዲናይቱ ነዋሪዎች የሚሰጠው ኤጀንሲው፤ በከተማይቱ የተከናወኑ ጋብቻ እና ፍቺዎችንም ያከናውናል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ፤ መስሪያ ቤታቸው ባለፉት ስድስት ወራት የመዘገበው ፍቺ 3,769 መሆኑን በዛሬው መግለጫ ላይ አመልክተዋል።

ኤጀንሲው ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የመዘገበው ፍቺ 2,832 እንደነበር የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የዘንድሮው የፍቺ መጠን በ34 በመቶ ጭማሪ ያሳየ እንደሆነ አስገንዘበዋል።

🔴ዝርዝሩን ለማንበብ ▶️ https://ethiopiainsider.com/2025/14849/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

15 Jan, 11:53


የሚንተከተክ ውሃ፣ የሚጋረፍ እንፋሎት፣ የሚሰነፍጥ ሽታ

ቪዲዮ፦ ባለፉት ሳምንታት በአፋር ክልል የመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ ተከስቷል። በዛሬው ዕለት ንጋት ላይ የደረሰውን ጨምሮ፤ በክልሉ ባለፉት ቀናት የተለያየ መጠን ያላቸው ርዕደ መሬቶች ተመዝግበዋል።

በፈንታሌ እና ዶፈን ተራራዎች መካከል ባሉ ስፍራዎች በደረሱ የመሬት መንቀጥቀጦች፤ ከፍተኛ ግፊት ያላቸውን ፍልውሃዎች በተለያዩ ቦታዎች እንዲፈልቁ አድርገዋል። ክስተቱ በብዛት ወደታየበት ወደ ሳገንቶ ቀበሌ በቅርቡ ተጉዞ የነበረው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ፤ አንዳንዶቹ ፍልውሃዎች የፈለቁት በሰዎች መኖሪያ አቅራቢያ መሆኑን ተመልክቷል።

በእነዚህ ስፍራዎች የሚገኙ የእርሻ ቦታዎች፤ ጭቃ በተቀላቀለበት ውሃ ተሸፍነዋል። ከመሬት ተስፈንጥሮ የሚወጣው የፈላ ውሃ፤ በአካባቢው ያሉ ዛፎችን እና ሜዳዎችን ጭምር ጭቃ አልብሷቸዋል። ከፍልውሃዎቹ ዙሪያ ያለው ቦታም፤ በረግረጋማ ደለል የተሞላ ነው።

በተለያዩ አካባቢዎች የፈለቁት ፍልውሃዎች፤ ከፍተኛ ሙቀት ያላቸው እንፋሎቶችንም አብረው ያመነጫሉ። የሚጋረፈው እንፋሎት ተቋቋሞ ወደ ፍልሃዎቹ የሚጠጋ ሰው፤ የሚሰነፍጥ ጠረን ያውደዋል።

እንዲህ አይነት ክስተቶችን ከዚህ ቀደም ተመልክተው እንደማያውቁ የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፤ በሆነው ነገር ሁሉ ከጎብኚዎች እኩል ሲደመሙ ይታያሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

🔴 የነዋሪዎችን እና የአካባቢውን ሁኔታ ለመመልከት፤ ይህን ሊንክ ይጫኑ ▶️ https://youtu.be/jOx77kWjRqw?feature=shared

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

14 Jan, 15:52


አከራካሪው የንብረት ታክስ አዋጅ፤ በረቂቅ ደረጃ ከነበረበት የተሻሻሉ ጉዳዮች ምንድናቸው?

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ ጥር 6፤ 2017 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው፤ የንብረት ታክስ አዋጅን በአራት ተቃውሞ እና በ10 ድምጸ ተዐቅቦ አጽድቆታል።

የአስረጂ እና ይፋዊ የህዝብ መድረክን ጨምሮ ለአራት ጊዜ ያህል ውይይት የተደረገበት ይህ አዋጅ፤ በፓርላማ አባላት እና በሌሎች ተሳታፊዎች ብዙ አከራካሪ ነጥቦች የተነሱበት ነበር።

የአዋጅ ረቂቁ ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ ለዝርዝር እይታ የተመራለት የተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ በዛሬው ዕለት የውሳኔ ሃሳቡን ባቀረበበት ወቅትም ተመሳሳይ ሃሳቦች ተደምጠዋል።

በማክሰኞው መደበኛ ስብሰባ አስተያየታቸውን ያቀረቡ አንድ የፓርላማ አባል፤ የንብረት ታክስ መጣሉ የዋጋ ንረትን ሊያባብስ እና ተደራራቢ ጫና ሊያስከትል እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በአብላጫ ድምጽ የጸደቀው የንብረት ታክስ አዋጅ፤ በረቂቅ ደረጃ ከነበረበት ጥቂት ማሻሻያዎች ተደርገውበታል።

ማሻሻያ ከተደረገባቸው ድንጋጌዎች መካከል የንብረት ታክስ በመቶኛ የሚከፈልበት ዋጋ መሰረት፣ በየዓመቱ የሚደረገው የንብረት ታክስ ጭማሪ እና በታክስ ነጻ ስለተደረጉ የቦታ እና የህንጻ አገልግሎቶች የሚመለከቱት ይገኙበታል።

🔴 በአዋጁ ከተካተቱ ማሻሻያዎች እና አዳዲስ አንቀጾች መካከል በ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተጠናቀሩትን ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/14839/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

14 Jan, 11:10


በጠለምት ወረዳ በመሬት መንሸራተት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች፤ እርዳታ እና ዘላቂ የሰፈራ ቦታ ባለማግኘታቸው መቸገራቸውን ገለጹ

የአማራ እና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ ከሚያነሱባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው ጠለምት ወረዳ በመሬት መንሸራተት የተፈናቀሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች፤ ከአራት ወራት በኋላም “በጊዜያዊ መጠለያ እንዲቆዩ በመገደዳቸው” ለችግር መጋለጣቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ።

የአካባቢው ባለስልጣናት ለተፈናቃዮቹ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ቢያመቻቹም፤ በበጀት እጥረት ምክንያት ለግንባታ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወዲህ በአማራ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ጎንደር ዞን ስር እየተዳደረ የሚገኘው የጠለምት ወረዳ፤ የመሬት መንሸራተት አደጋ ያጋጠመው ባለፈው ነሐሴ ወር አጋማሽ ገደማ ነበር።

በአደጋው 10 ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ፤ 35 የቤት እንስሳት ሞተዋል። የመሬት መንሸራተቱ ከ30 ሄክታር በላይ በሰብል የተሸፈነ መሬት ላይም ጉዳት አድርሷል።

በአደጋው ከቀያቸው የተፈናቀሉ 2,400 የጠለምት ወረዳ ነዋሪዎች፤ በመጀመሪያ በትምህርት ቤት በስተኋላ ደግሞ በወረዳው ጽህፈት ቤቶች ውስጥ ተጠልለው ቆይተዋል።

ከእነዚህ ተፈናቃዮች አንዱ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ፍስሃ፤ እርሳቸውን ጨምሮ 100 የሚሆኑ አባወራዎች በአሁኑ ወቅት ተጠልለው የሚገኙት የጠለምት ወረዳ አስተዳደር እና የወረዳው የግብርና ቢሮ በጽህፈት ቤትነት ይገለገሉባቸው በነበሩ ክፍሎች ውስጥ እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አቶ ተስፋዬ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ የሚገኙት ከሰባት ልጆቻቸው ጋር ነው።

🔴 ዝርዝሩን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/14831/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

13 Jan, 15:57


የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን አዲስ ዋና ዳይሬክተር ሊሾምለት ነው 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ካሉት ሰባት ምክትል ፕሬዝዳንቶች መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር ሳምሶን መኮንን፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣንን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ በዕጩነት ቀረቡ። የአዲሱ ዋና ዳይሬክተር ሹመት ነገ ማክሰኞ ጥር 6፤ 2017 በሚካሄደው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ላይ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዋና ዳይሬክተሩን ሹመት እንዲያጸድቅ፤ ጥያቄውን ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ጥር 1 በጽህፈት ቤታቸው አማካኝነት ለፓርላማ በላኩት ደብዳቤ፤ የዶ/ር ሳምሶን ሹመት በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ አማካኝነት እንዲከናወን ጠይቀዋል።

በመጋቢት 2013 ዓ.ም የወጣው ይኸው አዋጅ፤ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሰየም ይደነግጋል። ምክር ቤቱ ዋና ዳይሬከተሩን የሚሰይመው፤ በመንግስት አቅራቢነት እንደሆነ በአዋጁ ተቀምጧል። በባለስልጣኑ ቦርድ አማካኝነት የሚመለመለው ዋና ዳይሬክተር፤ “ከማንኛውም ፓርቲ አባልነት ነጻ መሆን” እንደሚኖርበትም በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።

ዋና ዳይሬክተሩ፤ መገናኛ ብዙኃን ተግባራቸውን በሕግ መሰረት ማከናወናቸውን ለማረጋገጥ ክትትል እና ቁጥጥር የማድረግ ስልጣን በአዋጅ የተሰጠውን መስሪያ ቤት ስራዎች የመምራት እና የማስተዳደር ኃላፊነት በአዋጅ ተጥሎበታል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የ12 ዓመታት የማስተማር እና የአመራርነት ልምድ እንዳላቸው የተናገረላቸው አዲሱ ተሿሚ፤ በአዋጁ መሰረት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ “ዋና ስራ አስፈጻሚ ይሆናሉ”።

🔴 ለዝርዝሩ ▶️ https://ethiopiainsider.com/2025/14823/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

11 Jan, 20:34


ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ “ግንኙነታቸውን ወደነበረበት ለመመለስ” ተስማሙ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ፤ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያን “ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ” ተስማሙ።

ሁለቱ መሪዎች በአዲስ አበባ እና በሞቃዲሾ “የተሟላ ዲፕሎማሲያዊ ውክልና” እንዲኖር በማድረግ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት “ለማጠናከር” መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

ሁለቱ ሀገራት ለአንድ ዓመት ገደማ ሻክሮ የቆየውን ግንኙነታቸውን ለማደስ የተስማሙት፤ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ዛሬ ቅዳሜ ጥር 3፤ 2017 ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ነው።

አብይ እና ሐሰን ሼክ “በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ መለዋወጣቸውን” የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከውይይቱ በኋላ ያወጣው የጋራ መግለጫ ይጠቁማል።

በመግለጫው መሰረት መሪዎቹ “በሁለቱ ሀገራት ወንድማማች ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ገንቢ ውይይት” አድርገዋል።

የመሪዎቹ ውሳኔ ከአስር ወራት ገደማ በኋላ በሶማሊያ የኢትዮጵያን አምባሳደር ወደ ሞቃዲሾ እንዲመለሱ መንገድ ይጠርጋል። ሶማሊያ ተቀማጭነታቸው በሞቃዲሾ የነበረውን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር መሐመድን ያባረረችው በመጋቢት 2016 ዓ.ም. ነው።

🔴ዝርዝሩን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/14810/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

07 Jan, 20:21


በአፋር ክልል በመሬት መንቀጥቀጥ ለተፈናቀሉ ሰዎች እርዳታ እየተከፋፈለ ነው

ቪዲዮ:- በአፋር ክልል፣ ገቢ ረሱ ዞን፣ ዱለሳ ወረዳ በመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ ለተፈናቀሉ በሺህዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች፤ ከትላንት በስቲያ እሁድ ታህሳስ 27 ጀምሮ እርዳታ እየተከፋፈለ መሆኑን በወረዳው የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ መሐመድ አስኪር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የምግብ እና የቁሳቁስ እርዳታው እየተሰጠ የሚገኘው፤ በሶስት ጣቢያዎች እንዲሰፍሩ ለተደረጉ በሺህዎች ለሚቆጠሩ ተፈናቃዮች መሆኑንም ገልጸዋል።

የፌደራል የአደጋ ስጋት እና አመራር ኮሚሽን ባለፈው ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ፤ የዱለሳ ወረዳ 20 ሺህ ነዋሪዎች ለርዕደ መሬት አደጋ ተጋላጭ መሆናቸውን ገልጾ ነበር። በሁለት ቀበሌዎች ውስጥ ከሚኖሩት ከእነዚህ ዜጎች ውስጥ ስድስት ሺህ ገደማ የሚሆኑቱ፤ ከስጋት ቀጠና ውጭ ወዳሉ ስፍራዎች እንዲዘዋወሩ መደረጋቸውንም ኮሚሽኑ በወቅቱ አስታውቋል።

አካባቢያቸውን ከለቀቁ የዱለሳ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል የተወሰኑቱ የሰፈሩት፤ ከዶሆ ሎጅ አቅራቢያ በሚገኝ “ዳይኢዶ” ተብሎ በሚጠራ ሜዳማ ቦታ ላይ ነው። በዚህ ገለጣ ስፍራ ላይ እንዲሰባሰቡ የተደረጉ ተፈናቃዮች ምዝገባ ከተከናወነ በኋላ፤ ትላንት ሰኞ ታህሳስ 28 የምግብ እና የቁሳቁስ እርዳታ ሲሰጣቸው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል።

በዳይኢዶ የተፈናቃዮች ማቆያ ጣቢያ ከሰፈሩት ውስጥ አንዷ የሆነችው መዲና ገነቶ፤ ከክልሉ መንግስት 50 ኪሎ ግራም ስንዴ ዱቄት እርዳታ ማግኘቷን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግራለች። የስንዴ ዱቄቱ የሚሰጠው በ2 ሰው ኮታ መሆኑን አመልክታለች።

🔴ተጨማሪ ለማንበብ:- https://ethiopiainsider.com/202/14804/

🔴ቪዲዮውን ለመመልከት:- https://youtu.be/9gdAwcSV0nA?feature=shared

Ethiopia Insider

06 Jan, 19:37


በቀበና ከተማ የቀሩ የከሰም ስኳር ፋብሪካ ሰራተኞች መንግስት በአፋጣኝ እንዲደርስላቸው ተማጸኑ 

ቪዲዮ:- ላለፉት ሁለት ሳምንታት በአፋር ክልል ያለ ማቋረጥ የቀጠለው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ብርቱ ሆኖ ከሚሰማባቸው ስፍራዎች አንዱ የቀበና ከተማ ናት። የቀበና ከተማ አብዛኞቹ ነዋሪዎች የከሰም ስኳር ፋብሪካ ሰራተኞች ናቸው። 

አርባ ሁለት ሺህ ገደማ ለሆኑ ሰራተኞች የስራ ዕድል የፈጠረው የከሰም ስኳር ፋብሪካ፤ ባለፉት ቀናት በአካባቢው በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከፍተኛ ጉዳት አጋጥሞታል። የመሬት መንቀጥቀጡ ከፋብሪካው በተጨማሪ በቀበና ከተማ ያሉ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶችን አፈራርሷል። 

ከዚህ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስባቸው የሰጉ የተወሰኑ የከተማይቱ ነዋሪዎች፤ የጭነት መኪናዎችን በመከራየት በአቅራቢያው ወደሚገኙ ከተሞች ሲሸሹ ቆይተዋል። ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ በርካታ የከተማይቱ ነዋሪዎች፤ የመከላከያ ሰራዊት ባቀረባቸው ወታደራዊ ካሚዮኖች ተጓጉዘዋል። 

የከሰም ስኳር ፋብሪካ የመደበው አንድ ግዙፍ የጭነት ተሽከርካሪም፤ የፋብሪካውን ሰራተኞች ከአደጋ ወደ ራቁ ቦታዎች ዛሬን ጨምሮ በየቀኑ እያጓጓዘ ነው። እንዲያም ሆኖ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፋብሪካው ሰራተኞች፤ አሁንም በቀበና ከተማ ሆነው የሚደርስላቸውን እየተጠባበቁ ይገኛሉ። 

🔴 ተጨማሪ ለማንበብ ▶️https://ethiopiainsider.com/2025/14801/

🔴 ቪዲዮውን ለመመልከት ▶️ https://youtu.be/RhwW29TWv5g?feature=shared

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

05 Jan, 14:19


በአዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ ትላንት ምሽት ብቻ 30 ገደማ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረቶች ተሰምተዋል

በመላው ዓለም የሚከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦችን ከስር ከስር እየተከታተሉ በሚመዘግቡ የምርምር ተቋማት ዘንድ ከሰሞኑ ተደጋግሞ የሚጠቀስ አንድ የኢትዮጵያ አካባቢ አለ - አዋሽ። “አዋሽ” በአፋር ክልል የሁለት ከተሞችም መጠሪያ ነው። አዋሽ ሰባት እና አዋሽ አርባ።

ለሰሞኑ የመሬት መንቀጥቀጥ መነሻ ናቸው በሚባሉት የፈንታሌ እና ዶፋን ተራሮች አቅራቢያ የሚገኙት ሁለቱ ከተሞች፤ በሰዓታት አንዳንዴም በደቂቃዎች ልዩነት ውስጥ ንዝረቶችን ያስተናግዳሉ። በቤትም ውስጥ ሆነ በውጭ የተቀመጠ ሰው፤ የሞባይል ስልክ በኪስ ውስጥ ተይዞ ሲጠራ የሚሰማው አይነት “ቫይብሬት” የማድረግ ስሜት ይሰማዋል።

በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች የሚሰማው አንስተኛ ንዝረት፤ በአዋሽ ሰባት እና በአዋሽ አርባ በተደጋጋሚ መልኩ ጠንከር ብሎ ይሰማል። በሬክተር ስኬል ወደ አምስት የተጠጋ አሊያም ከአምስት ያለፈ የመሬት መንቀጥቀጥ በአቅራቢያው ሲከሰት፤ የህንጻ መስታወቶች ይርገፈገፋሉ። ግድግዳዎች ይንቃቃሉ። አልጋዎች የሚያረግዱ ይመስላሉ። ውሾች ይጮኻሉ። አውራ ዶሮዎች አለ ሰዓታቸው ደጋግመው ጥሪ ያሰማሉ።

ይህ ሁኔታ በተለይ በምሽት እና በለሊት ጎልቶ ይደመጣል። በዚህ መልኩ የሚሰሙ እያንዳንዳቸውን ንዝረቶች መጠናቸው ምን ያህል እንደሆነ፤ በዓለም አቀፍ የመረጃ ቋቶች ውስጥ ለማግኘት መሞከር ትርፉ መድከም ነው።

በአሜሪካው የጂኦሎጂ ሰርቬይ ተቋም በትላንትናው ዕለት ምሽት የተመዘገቡ ርዕደ መሬቶች ብዛት ሶስት ብቻ ነው። የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ትላንት ቅዳሜ ምሽት ብቻ፤ በአዋሽ ሰባት ከተማ 30 ገደማ የተለያየ መጠን ያላቸውን የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረቶችን ቆጥሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

05 Jan, 11:20


የአስፋልት መንገዶች ላይ ስንጥቃት የፈጠረው የመሬት መንቀጥቀጥ

ቪዲዮ (3)፦ በአፋር ክልል በመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ መንገዶች እና ድልድዮች የመሰንጠቅ አደጋ አጋጥሟቸዋል። በተለያዩ አካባቢዎች ባሉ መሬቶች ላይም፤ ባለፉት ቀናት የተፈጠሩ እና መጠናቸው የተለያዩ ስንጥቃቶች እና ገደሎች ይታያሉ።

ይህ በተለይ ጎላ ብሎ የሚታየው፤ በፈንታሌ እና ዶፈን ተራራዎች መካከል ባሉ ስፍራዎች ላይ ነው። በዶሆ ቀበሌ አካባቢ እና ወደ ከሰም ስኳር ፋብሪካ በሚወስደው የአስፋልት መንገድ ላይ ይኸው ይስተዋላል።

ትላንት ቅዳሜ አመሻሹን ወደ ስፍራው የተጓዘው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ፤ በቦታው የተመለከተውን በቪዲዮ ይዞታል።

🔴 ይህን ሊንክ ተጭነው ቪድዮውን ይመልከቱ:- https://youtu.be/vE1y2nCKn8A?feature=shared

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

05 Jan, 06:51


በአፋር ክልል ሳገንቶ ቀበሌ በመንቀጥቀጥ የፈለቀ እሳት ያዘለ ፈሳሽ “ብዙ ቤቶችን አቃጥሏል”- ነዋሪ

ቪዲዮ (2)፦ በአፋር ክልል፣ ዱለሳ ወረዳ፣ ሳገንቶ ቀበሌ ባለፉት ቀናት በተከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦች ሳቢያ የፈለቀ እሳት ያዘለ ፈሳሽ “ ብዙ ቤቶችን ማቃጠሉን” አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ።

ባለፉት ሁለት ቀናት፤ ሶስት ሺህ ገደማ የአካባቢው ነዋሪዎች ስፍራውን ለቅቀው መውጣታቸውን እና እስካሁን ድረስ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ነዋሪው አስረድተዋል።

ካሉአለ ከተባለ ስፍራ የመጡት እኚሁ የአካባቢው ነዋሪ፤ ከሰሞኑ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን ርዕደ መሬት የሚገልጹት “አስፈሪ” በሚል ቃል ነው።

“መሬት መንቀጥቀጥ ነበር። እንደገና ደግሞ እሳት ወጣ። የአካባቢው የመሬት መንቀጥቀጥ ራሱ የተለየ ነው። የቆመ ሰው ይወድቃል፤ ግመልም ይወድቃል፤ ከብትም ይወድቃል” ይላሉ ነዋሪው የሰሞኑን ሁኔታ ሲገልጹ።

“ውሃ የወጣበት አካባቢ ከሶስት ኪሎ ሜትር [ዙሪያ] የሚሆንበት ቦታ ላይ መሬት ስለሚንቀጠቀጥ ሰው በጣም ይፈራል” ሲሉም ነዋሪው ያክላሉ።

የሳገንቶ ቀበሌ ነዋሪው በእርሳቸው የመኖሪያ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጡ ባስከተለው ፍንዳታ የፈለቀ፤ “ውሃ የመሰለ ፈሳሽ” ለቤቶች መቃጠል ምክንያት መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

“ብዙ ቤቶች ተቃጥለዋል። ከግቢ ውስጥ በሚወጣ ውሃ፤ ቤት ይቃጠላል። ውሃ ይባላል እንጂ እሳት ነው” ሲሉ ነዋሪው የፈሳሹን ምንነት ያስረዳሉ።

🔴 ተጨማሪ ለማንበብ:- https://ethiopiainsider.com/2025/14786/

🔴 ቪድዮውን ለመመልከት:- https://youtu.be/l7MkqLwhWRI?feature=shared

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

04 Jan, 20:58


በመሬት መንቀጥቀጥ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች፤ አስቸኳይ እርዳታ እንዲደረግላቸው ጠየቁ

ቪዲዮ(1):- በአፋር ክልል የመሬት መንቀጥቀጥ በተደጋጋሚ በተከሰተባቸው ስፍራዎች የሚኖሩ ነዋሪዎችን፤ የአደጋ ስጋት ወደሌለባቸው ቦታዎች የማጓጓዝ ስራ ዛሬ ቅዳሜ ታህሳስ 26፤ 2017 በስፋት ሲከናወን ውሏል።

ከከሰም የስኳር ፋብሪካ አቅራቢያ በሚገኘው እና በተለምዶ “ቀበና” ተብሎ በሚጠራው አነስተኛ ከተማ ያሉ ነዋሪዎች፤ በዛሬው ዕለት አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡ ተደርገዋል። 

ዛሬ ረፋዱን በስፍራው የነበረ አንድ የዓይን እማኝ፤ የተወሰኑ የከተማይቱ ነዋሪዎች በስድስት ወታደራዊ ካሚዮን ተጭነው ሲጓጓዙ መመልከታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ጥቂት ንብረቶቻቸውን ይዘው አካባቢውን የለቀቁ እነዚህ ነዋሪዎች፤ ለጭነት ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች የሚያውሉት ገንዘብ የሌላቸው ናቸው።

በተሻለ የገቢ ደረጃ ላይ የሚገኙ ጥቂት ነዋሪዎች፤ የጭነት መኪናዎችን በመከራየት ወደ አዋሽ አርባ፣ ወደ አዋሽ ሰባት እና ሌሎችም ከተሞች ንብረቶቻቸውን ሸክፈው ሲጓዙ በስፍራው የነበረው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል።

ነዋሪዎቹ እንደ “አይሱዙ” ያሉ የጭነት መኪናዎችን ለመከራየት ከ10 ሺህ እስከ 15 ሺህ ብር እንደሚጠየቁም ዘጋቢው ተረድቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

🔴 ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ እና ያቀረቡትን ተማጽኖ በቪዲዮ ለመመልከት ▶️ https://youtu.be/QPiMGGunsm0?feature=shared

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

04 Jan, 01:07


በሬክተር ስኬል 5.8 የደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ ዛሬ ለሊት በአፋር ክልል ተከሰተ

በኢትዮጵያ በሬክተር ስኬል 5.8 የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ከለሊቱ 9:52 መድረሱን የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት አስታወቀ። ሰሞኑን ሲከሰቱ ከነበሩት የመሬት መንቀጥቀጦች ዘለግ ላሉ ሰከንዶች የቆየው ርዕደ መሬት፤ ንዝረቱ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ተሰምቷል።

የለሊቱ የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተው በአፋር ክልል መሆኑን የአውሮፓ ሜዲትራንያን ሴይስሞሎጂ ማዕከል (EMSC) ተቋም መረጃ ያሳያል። ርዕደ መሬቱ የተከሰተበት ቦታ ከአቦምሳ ከተማ 56 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከአዳማ ከተማ 146 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ መሆኑን የአሜሪካ እና የአውሮፓ ተቋማት ገልጸዋል።

የአውሮፓው የምርምር ማዕከል የለሊቱን የመሬት መንቀጥቀጥ የልኬት መጠን 5.6 እንደሆነ በመጀመሪያ ገልጾ የነበረ ቢሆንም ከቆይታ በኋላ ወደ 5.8 ከፍ አድርጎታል። የመሬት መንቀጥቀጡ መጠን ከሰሞኑ ከደረሱት ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል።

ከዚህ ክስተት ስምንት ሰዓት አስቀድሞ በሬክተር ስኬል 5.5 የደረሰ ርዕደ መሬት ተከስቶ ነበር። አርብ አመሻሽ 11 ሰዓት ተኩል ገደማ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥም እንደዚሁ በሬክተር ስኬል ልኬት አምስትን የተሻገረ ነበር። በዚህ ጊዜ የተመዘገበው የርዕደ መሬት መጠን 5.2 ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

03 Jan, 17:31


ዛሬ ምሽት በሬክተር ስኬል 5.5 የተመዘገበ ርዕደ መሬት ተከሰተ

በኢትዮጵያ ከሰሞኑ ከተከሰቱት የመሬት መንቀጥቀጦች ከፍተኛ የሆነው እና በሬክተር ስኬል 5.5 የተመዘገበ ርዕደ መሬት ዛሬ አርብ ምሽት መከሰቱን የአሜሪካ እና የአውሮፓ ተቋማት አስታወቁ። የመሬት መንቀጥቀጡ በአፋር ክልል አዋሽ አካባቢ የተከሰተው ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ገደማ ነው።

ይህ ርዕደ መሬት ከአዋሽ ከተማ 44 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለ ስፍራ የደረሰ መሆኑን የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት አስታውቋል። የአውሮፓ ሜዴትራኒያን ሴይስሞሎጂ ማዕከል (EMSC) በበኩሉ የመሬት መንቀጥቀጡ ከጭሮ ከተማ 54 ኪሎ ሜትር፣ ከአዳማ ከተማ ደግሞ በ152 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ የደረሰ መሆኑን ገልጿል።

የጀርመን የጂኦሳይንስ የምርምር ማዕከል በበኩሉ ምሽቱን የተከሰተውን የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 5.0 የሚለካ እንደሆነ በመረጃ ቋቱ ላይ በመጀመሪያ ቢያስፍርም፤ ሰዓታት ዘግይቶ መጠኑን ወደ 5.4 አስተካክሎታል። ይህ የምርምር ማዕከል ከሁለቱ ተቋማት በተለየ፤ ትላንት ሐሙስ ለሊት በአፋር አካባቢ በሬክተር ስኬል 5.3 የደረሰ ርዕደ መሬት መከሰቱን አስታውቆ ነበር።

ሶስቱም ተቋማት ዛሬ አርብ አመሻሽ 11 ሰዓት ተኩል ገደማ የደረሰውን የመሬት መንቀጥቀጥ ግን የመዘገቡት በተመሳሳይ መጠን ነው። በዚህ ጊዜ የተመዘገበው ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል 5.2 የተለካ ነው። ከ2.5 እስከ 5.4 በሬክተር ስኬል የመለኪያ መሳሪያ የሚመዘገቡ የመሬት መንቀጥቀጦች ንዝረታቸው ሊሰማ የሚችል ነገር ግን አነስተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ መሆናቸውን በክስተቶቹ ላይ ምርምር የሚያደርጉ ተቋማት ይገልጻሉ።

🔴 ለተጨማሪ ▶️ https://ethiopiainsider.com/2025/14762/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

03 Jan, 16:44


የመሬት መንቀጥቀጥ እየተከሰተባቸው ካሉ ስፍራዎች ነዋሪዎችን ማዘዋወር ተጀመረ

በአፋር ክልል ገቢ ረሱ ዞን ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ እየደረሰባቸው ባሉ ሁለት ቀበሌዎች የሚኖሩ አራት ሺህ ገደማ አባወራዎችን፤ “የአደጋ ስጋት ወዳልሆነ ስፍራ” የማዘዋወር ስራ መጀመሩን አንድ የአካባቢው ባለስልጣን ተናገሩ። አደጋውን ሸሽተው ወደ አዋሽ አርባ ከተማ የገቡ ነዋሪዎችን በአንድ ማዕከል ለማሰባሰብ ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል።

በክልሉ በድግግሞሽም ሆነ በመጠን ባለፈው አንድ ሳምንት ይበልጥ በበረታው የመሬት መንቀጥቀጥ ይበልጡኑ የተጠቁ ስፍራዎች፤ በገቢ ረሱ ዞን፣ ዱለሳ ወረዳ ስር የሚገኙት የዱሩፍሊ እና ሳገንቶ የተባሉት ቀበሌዎች ናቸው።

በቀበሌዎቹ እየደረሰ ያለውን የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ “የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ” እና በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ ድንገት ውሃ መፍለቅ መከሰቱን የዱለሳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አሊ ደስታ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በአካባቢው ወደፊት ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ታሳቢ በማድረግ፤ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ታህሳስ 23፤ 2017 ጀምሮ የሁለቱን ቀበሌ ነዋሪዎች በአቅራቢያው ወደሚገኘው አዋሽ አርባ ከተማ የማጓጓዝ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ አሊ ገልጸዋል።

“የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ የቱ ጋር ሊከሰት እንደሚችል ትክክለኛ ቦታዎችን እያወቅን አይደለም። የመሬት መንቀጥቀጥ አናሳ ወደ ሆነበት አካባቢ ነው [ነዋሪዎችን] እያዘዋወርን ያለነው” ሲሉ የወረዳው አስተዳዳሪ አስረድተዋል።

🔴 ዝርዝሩን ለማንበብ ▶️
https://ethiopiainsider.com/2025/14744/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

01 Jan, 17:13


ኢትዮ ቴሌኮም በሚሰጣቸው አገልግሎቶቹ ላይ ያደረገው የዋጋ ጭማሪ፤ በህዝብ ዘንድ “ቁጣን ቀስቅሷል” ተባለ

መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎቶች አቅራቢ ኩባንያ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ በአገልግሎቶቹ ላይ ያደረገው የዋጋ ጭማሪ፤ በህዝብ ዘንድ “ቁጣ ጭምር የቀሰቀሰ” እና “አስደንጋጭ ነው” ሲሉ አንድ የገዢው ፓርቲ የፓርላማ አባል ተቹ። የዋጋ ማሻሻያ የተደረገው፤ “ዝቅተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን ባልነካ መልኩ ነው” ሲል ኢትዮ ቴሌኮም ምላሽ ሰጥቷል።

የኢትዮ ቴሌኮም የዋጋ ጭማሪ ጉዳይ መነጋገሪያ የሆነው፤ ዛሬ ረቡዕ ታህሳስ 23፤ 2017 በተካሄደ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፊት ለፊት የውይይት መድረክ ላይ ነው።

በምክር ቤቱ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተጠራው በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ከህዝብ የተሰበሰቡ እና የፓርላማ አባላት በግላቸው ያነሷቸው ጥያቄዎች ቀርበዋል።

የወላይታ ዞን፣ ኦፋ ምርጫ ክልል የፓርላማ ተወካይ የሆኑት አቶ መለሰ መና ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል፤ ኢትዮ ቴሌኮም የዛሬ 3 ወር ገደማ ያደረገውን የዋጋ ጭማሪ የተመለከተው ይገኝበታል።

“በሁሉም product ላይ በአንድ ጊዜ ነው የዋጋ ጭማሪ የተደረገው። ይሄ ደግሞ ትንሽ ህዝብ ውስጥ ቁጣም ጭምር እየቀሰቀሰ ነው” ብለዋል የፓርላማ አባሉ።

“[ለኢትዮ ቴሌኮም] በእርግጥ በጀት ያስፈልጋል። በራሳቸው አቅም እንደሚሄዱ ይታወቃል። ልንደግፋቸው ይገባል ብዬ አስባለሁ። ግን በሁሉም ‘ፕሮዳክቶች ላይ፣ በአንድ ቤት ውስጥ ከአንድ ሪሶርስ ከሚያገኝ ሰው ላይ የመጣበት ሁኔታ ትንሽ አስደንጋጭ [ነው]” ሲሉ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

🔴 ዝርዝሩን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/14728/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

31 Dec, 11:21


ትላንት ለሊት በአፋር ክልል በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ ከ20 በላይ ቤቶች እና ሱቆች ፈረሱ  
በአፋር ክልል በትላንትናው ዕለት በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ በገቢ ረሱ ዞን፤ ዱለሳ ወረዳ፣ ድሩፉሊ ቀበሌ የሚገኙ ከ20 በላይ ቤቶች እና ሱቆች መፍረሳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የወረዳው አስተዳዳሪ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። የመሬት መንቀጥቀጡ ዛሬም አለመቆሙን የገለጹት ነዋሪዎች፤ “ከፍተኛ ስጋት” ውስጥ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአዋሽ አካባቢ ትላንት ሰኞ ታህሳስ 21፤ 2017 ከደረሱ 8 የመሬት መንቀጥቀጦች ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው እና በሬክተር ስኬል 5.1 የተለካው ርዕደ መሬት የተከሰተው ከለሊቱ 7 ሰዓት ገደማ እንደሆነ ከጀርመን የጂኦሳይንስ የምርምር ማዕከል የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በአፋር ክልል በዱለሳ ወረዳ፣ ድሩፉሊ ቀበሌ በተለምዶ ቀበና ተብሎ በሚጠራው አነስተኛ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዳውድ አደም፤ ትላንት ለሊት 7 ሰዓት ገደማ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ለሰከንዶች የቆየ ቢሆንም፤ በቤታቸው ያለውን ቴሌቪዥን፣ ቁምሳጥን እና ብፌ መሰባበሩን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በመሬት መንቀጥቀጡ ሳቢያ እርሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ ሰባት ያህል ቤቶች “ሙሉ ለሙሉ መውደቃቸውን” እና ፍየሎች ሞተው መመልከታቸውንም አስረድተዋል።

ቤታቸው ከፈረሰባቸው የቀበና ከተማ ነዋሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ዳንኤል ደርሳ፤ በትላንቱ የመሬት መንቀጥቀጥ 8 ክፍል ያለው ቤታቸው እንደፈረሰባቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የመሬት መንቀጥቀጡ የሚያደርሰውን ጉዳት በመፍራት፤ ከልጆቻቸው እና ከባለቤታቸው ጋር አስፓልት መንገድ ዳር ማደራቸውንም አክለዋል።

🔴 ለዝርዝሩ ▶️ https://ethiopiainsider.com/2024/14702/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

29 Dec, 17:52


በአዋሽ አካባቢ ዛሬ ምሽት በሬክተር ስኬል 5.0 የደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ

🔴በዛሬው ዕለት ብቻ ሰባት የመሬት መንቀጥቀጦች ተመዝግበዋል

በአፋር ክልል አዋሽ አካባቢ ከሰሞኑ ከደረሱት የመሬት መንቀጥቀጥ ክሰተቶች በመጠኑ ከፍተኛ የሆነ ርዕደ መሬት ዛሬ እሁድ ምሽት መከሰቱን የጀርመን የጂኦሳይንስ የምርምር ማዕከል አስታወቀ።

በአካባቢው ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ10 ላይ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ በሬክተር ስኬል 5.0 የደረሰ እንደሆነ የማዕከሉ መረጃ አመልክቷል።

በሬክተር ስኬል የመለኪያ መሳሪያ ከ2.5 እስከ 5.4 መጠን ያላቸው የመሬት መንቀጥቀጦች አነስተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ እንደሆኑ በዘርፉ ምርምር የሚያደርጉ ተቋማት ይገልጻሉ።

በዚህ መጠን የሚከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦች ንዝረታቸው በበርካታ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባሉ ከተሞች ጭምር የሚሰማ እንደሆነም የተቋማቱ መረጃ ያሳያል። የምሽቱ የመሬት መንቀጥቀጥ በአዲስ አበባ ጭምር ዘለግ ላሉ ሰከንዶች የቆየ ንዝረት አስከትሏል።

ከአዋሽ ከተማ 14 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለ ስፍራ የተከሰተው የምሽቱ ርዕደ መሬት፤ በዛሬው ዕለት ብቻ በአካባቢው የተመዘገቡ መሬት መንቀጥቀጦችን ቁጥር ሰባት አድርሶታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

🔴 ዝርዝሩን ለማንበብ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14694/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

26 Dec, 15:23


በ84 ኮሌጆች የሚማሩ ተማሪዎች፤ እስከ ጥር ወር መጀመሪያ ወደ ሌሎች የትምህርት ተቋማት እንዲዘዋወሩ ትዕዛዝ ተሰጠ

የፌደራል የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን፤ 84 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እስከ መጪው ጥር ወር መጀመሪያ ድረስ  ተማሪዎቻቸውን ፈቃድ ወዳላቸው ተቋማት እንዲያዘዋውሩ ትዕዛዝ አስተላለፈ።

ባለስልጣኑ ይህንን ትዕዛዝ የሰጠው፤ በድጋሚ ሳይመዘገቡ ለቀሩ እና በገዛ ፈቃዳቸው ስራቸውን ለማቋረጥ ለወሰኑ ኮሌጆች ነው።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባወጣው “አዲስ ስታንዳርድ” መሰረት፤ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዳግም እንዲመዘገቡ ጥሪ አቅርቦ የነበረው ባለፈው መስከረም ወር መጀመሪያ ነበር።

በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚንቀሳቀስ ማንኛውም የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ፈቃድ የመስጠት፣ የማደስ እና ቁጥጥር የማድረግ ስልጣን ለመስሪያ ቤቱ የሰጠው በ2014 ዓ.ም. የተሻሻለው የባለስልጣኑ ማቋቋሚያ ደንብ ነው።

መስሪያ ቤቱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ፈቃድ ወይም እድሳት የመሰረዝ ስልጣንም በዚሁ ደንብ አግኝቷል።

በዚሁ መሰረት 84 የሚሆኑ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት “ከከፍተኛ ትምህርት የፈቃድ ስርአት እንዲወጡ” የሚያደርጋቸውን ውሳኔ ባለስልጣኑ ከሁለት ሳምንት በፊት አስተላልፏል።
ዘጠኝ
በሚሆኑ የትምህርት ተቋማት ላይም ተመሳሳይ ውሳኔ በቅርቡ እንደሚተላለፍ ከባለስልጣኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

🔴 ዝርዝሩን ለማንበብ ▶️
https://ethiopiainsider.com/2024/14683/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

26 Dec, 11:49


በኢትዮጵያ የታገዱ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ቁጥር አራት ደረሰ 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን “ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ ተንቀሳቅሰዋል” ያላቸውን፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከልን (EHRDC) ከማንኛውም የስራ እንቅስቃሴ አገደ። ባለስልጣኑ ባለፈው አንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ያገዳቸው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ቁጥር አራት ደርሰዋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሁለቱን ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ያገደው፤ ከትላንት ረቡዕ ታህሳስ 16፤ 2017 ጀምሮ እንደሆነ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተመዘገቡበት ዓላማ መሰረት ስራቸውን ማከናወናቸውን የመከታተል እና የመቆጣጠር ኃላፊነት በአዋጅ የተሰጠው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፤ ለድርጅቶቹ በትላንትናው ዕለት በላከው ደብዳቤ ለእግድ ያበቃቸውን ምክንያት ዘርዝሯል። 

ሁለቱም ድርጅቶች “ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ” እና “ኃላፊነት በጎደለው መልኩ” በመንቀሳቀስ እንዲሁም “ገለልተኛ ባለመሆን” በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ውንጀላ ቀርቦባቸዋል።

እነዚህ ውንጀላዎች ባለፈው ሳምንት በድጋሚ እንዲታገዱ በተደረጉት፤ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች (LHR) በተባሉት ድርጅቶች ላይም በምክንያትነት ተጠቅሷል።

🔴 ዝርዝሩን ለማንበብ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14668/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

24 Dec, 16:36


ምስላዊ መረጃ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ ታህሳስ 15 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው፤ የአረንጓዴ አሻራ እና የተጎሳቆለ መሬት ማገገሚያ ልዩ ፈንድ ማቋቋሚያ እና አስተዳደር አዋጅን በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

አዲሱ አዋጅ፤ የፌዴራል መንግስት ከሀገር ውስጥ ገቢ ምንጭ ከሚመድበው ዓመታዊ በጀት ውስጥ ከ0.5 እስከ 1.0 በመቶ ያህል የሚሆነውን ለልዩ ፈንዱ እንዲመድብ ግዴታ ጥሎበታል።

የልዩ ፈንዱ ዓላማዎች በሚል በአዋጁ ከተዘረዘሩ ጉዳዮች መካከል፤ “የተጎሳቆለ መሬት በተፈጥሮና በመልሶ ማልማት መርህ በመታገዝ እንዲያገግም በማድረግ የደን ልማት እና የደን መልሶ ማልማትን መደገፍ” የሚለው ይገኝበታል።

በኢትዮጵያ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የቆዳ ስፋት ወይም 54 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው መሬት “የተጎሳቆለ” እንደሆነ የወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩት ከቀድሞው የአካባቢ፣ የአየር ንብረት ለውጥና ደን ኮሚሽን ጋር በመሆን ያካሄዱት ጥናት ያመለክታል።

ከዚህ የመሬት መጠን ውስጥ 11 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው “በፍጥነት እንዲያገግም” ካልተደረገ “ተመልሶ ማገገም ወደ ማይችልበት ደረጃ ሊወርድ እንደሚችል” ይኸው ጥናት ተንብይዋል።

የተጎሳቆለ መሬት እንዲያገግም ከሚደረግባቸው መንገዶች መካከል “ለደን ልማት እና ለጥምር ደን ግብርና እንዲውል ማድረግ” አንዱ መሆኑ በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።

የልዩ ፈንዱ መቋቋም፤ እነዚህን መሰል ጥረቶች “በቋሚነት ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል” የፋይናንስ አማራጭ ስርዓት የሚዘረጋ እንደሆነ በአዋጅ ማብራሪያው ላይ ተቀምጧል።

የልዩ ፈንዱ የገንዘብ ምንጮች በዋናነት የፌዴራል መንግስት እና የልማት አጋሮች ቢሆኑም፤ ልዩ ፈንዱን ለመጠቀም የክልል መንግስታት እና የከተማ አስተዳደሮች “ተጓዳኝ በጀት” መመደብ ይጠበቅባቸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

23 Dec, 20:42


ከመተሐራ ከተማ አቅራቢያ ዛሬ ምሽት የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ

ከመተሐራ ከተማ አቅራቢያ 13 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ ዛሬ ሰኞ ምሽት የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት አስታወቀ። ንዝረቱ አዲስ አበባ ድረስ የተሰማው የዛሬው ምሽት ርዕደ መሬት፤ በሬክተር ስኬል 4.9 የተመዘገበ መሆኑን መስሪያ ቤቱ ገልጿል።

የዛሬው የመሬት መንቀጥቀጥ ሃያ አራት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአካባቢው ለሁለተኛ ጊዜ የተከሰተ ነው። ትላንት ለሊት 10 ሰዓት ከ13 ደቂቃ አካባቢ፤ ከአዋሽ ከተማ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለ ስፍራ ተመሳሳይ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ እንደነበር በመላው ዓለም የደረሱ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶችን የሚመዘግቡ ተቋማት ያወጧቸው መረጃዎች አመልክተው ነበር።

የትላንት ለሊቱን የመሬት መንቀጥቀጥ የመዘገቡ እነዚሁ ተቋማት፤ መጠኑ መጠነኛ የሚባል እና በሬክተር ስኬል 4.6 የሚለካ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል። ዛሬ ሰኞ ታህሳስ 14፤ 2017 ምሽት 4 ሰዓት ከ40 ገደማ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ በአዋሽ አካባቢ ከተመዘገበው ርዕደ መሬት ጋር በመጠን እኩል ነው።

በአፋር ክልል የሚገኘው የአዋሽ አካባቢ፤ ባለፈው መስከረም እና ጥቅምት ብቻ 10 የመሬት መንቀጥቀጦችን አስተናግዷል። በአካባቢው እስካሁን የተመዘገበው ከፍተኛ የርዕደ መሬት መጠን፤ በሬክተር ስኬል 4.9 የተለካ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

21 Dec, 10:06


ምስላዊ መረጃ፦ ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጪው ጥር አጋማሽ ገደማ የስልጣን መንበራቸውን ሲረከቡ በሀገሪቱ ጊዜያዊ ጥበቃ የተሰጣቸውን ጨምሮ በህገ ወጥ መንገድ የሚኖሩ ናቸው የተባሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ስደተኞችን በገፍ ለማስወጣት እቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል።

አሜሪካ ካለፈው ዓመት ጥር እስከ መስከረም ባሉት ወራት ብቻ፤ 271,000 ገደማ ስደተኞችን ወደ 192 ሀገራት በግዳጅ መልሳለች። ከእነዚህ መካከል 27ቱ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ መሆናቸውን የአሜሪካ የኢሚግሬሽን እና የጉምሩክ አስፈጻሚ መስሪያ ቤት ዓመታዊ ሪፖርት ያሳያል።

በተቋሙ መረጃ መሰረት፤ በ2024 ወደ ኢትዮጵያ የተጠረዙ ሰዎች ቁጥር ባለፉት ሶስት ዓመታት ከተመዘገቡት ከፍተኛው ነው። በ2019 አሜሪካ 32 ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ የመለሰች ሲሆን አሃዙ በቀጣዩ ዓመት ወደ 43 ከፍ ብሎ ነበር።

ከኢትዮጵያ ጎረቤቶች በ2024 ብዛት ያላቸው ዜጎቿን ከአሜሪካ የተቀበለችው ሶማሊያ ነች። ሶማሊያ በተጠቀሰው ዓመት ከአሜሪካ በግዳጅ የተመለሱ 64 ሰዎች ተቀብላለች።

ከኢትዮጵያውያን እና ሶማሊያውያን በተጨማሪ 48 ኬንያውያን፣ 34 ኤርትራውያን እና 5 ሱዳናውያን በዓመቱ ወደ ሀገራቸው በግዳጅ እንደተመለሱ የተቋሙ ዓመታዊ ሪፖርት ይጠቁማል።

በ2024 አሜሪካ በግዳጅ ወደ ተለያዩ ሀገሮች የላከቻቸው ሰዎች ቁጥር ባለፉት አስር ዓመታት ከነበረው ሁሉ ከፍተኛው ነው። በአሜሪካ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ወይም በጊዜያዊ ጥበቃ የሚኖሩ 11 ሚሊዮን ገደማ ስደተኞች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚገመት የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ይጠቁማሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

20 Dec, 13:05


በሐረር ከተማ የታሸጉ 35 የባንክ ቅርንጫፎች አገልግሎት ወደ መስጠት እንዲመለሱ ለሀረሪ ክልል አቤቱታ ቀረበ

የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር በሐረር ከተማ የታሸጉ 35 የባንክ ቅርንጫፎች ተከፍተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ እንዲደረግ ለሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቤቱታ አቀረበ።

የክልሉ መንግስት ቅርንጫፎቹ የታሸጉት “ግንባታቸው ባላለቁ ህንጻዎች አገልግሎት እየሰጡ በመሆኑ ነው” ቢልም፤ ማህበሩ ግን ከሌሎች የንግድ ድርጅቶች በተለየ መልኩ እርምጃው በእነርሱ ላይ መወሰዱ ለክልሉ የኮሪደር ልማት የተጠየቀው መዋጮ ተግባራዊ ባለመደረጉ ምክንያት የተፈጸመ እንደሆነ “ከድምዳሜ ላይ እንዲደርስ” እንዳደረገው ገልጿል።

በሀረሪ ክልል የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ባንኮች የሁለት ሚሊዮን ብር “ድጋፍ” እንዲያደርጉ በደብዳቤ የተጠየቁት የዛሬ ሶስት ሳምንት ገደማ ነው።

ደብዳቤውን ለባንክ ቅርንጫፎች የጻፈው የሀረሪ ክልል የገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ፤ የገንዘብ መጠኑን በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ገቢ እንዲያደርጉ ቀነ ገደብ ሰጥቷቸው ነበር።

ሃያ ስድስት ባንኮችን በአባልነት ያቀፈው የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር፤ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ታህሳስ 9፤ 2017 ለሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በጻፈው ደብዳቤ፤ የባንክ ቅርንጫፎች የተጠየቁትን ያህል የገንዘብ መጠን በመዋጮ መልክ ለመክፈል “ስልጣን እንደሌላቸው” ገልጿል።

የገንዘብ መዋጮ ጥያቄው በባንኮቹ “ዋና መስሪያ ቤት ታይቶ” እንዲሁም “በቂ በጀት የተመደበለት መሆኑ ተረጋግጦ” የሚፈቀድ መሆኑንም ማህበሩ አመልክቷል።

🔴ዝርዝሩን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2024/14648/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

18 Dec, 14:55


የኦሮሚያ ክልል ተወካዮች ለሀገር አቀፍ ምክክር እንዲቀርቡ የጠቆሟቸው አጀንዳዎች የትኞቹ ናቸው? 

የኦሮሚያ ክልል የማህበረሰብ ክፍል ተወካዮቹ በመጪው ሀገር አቀፍ የምክክር አጀንዳነት እንዲያዙ ተደጋጋሚ ጥቆማ ካቀረቡባቸው ጉዳዮች ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ የባለቤትነት ጉዳይ ይገኝበታል።

የፌደራል የስራ ቋንቋ፣ የሰንደቅ አላማ፣ የክልላዊ አስተዳደር ወሰን እንዲሁም ሰላም እና ጸጥታን የተመለከቱት ጉዳዮችም እንዲሁ በተወካዮቹ በተደጋጋሚ የተነሱ አጀንዳዎች ናቸው።

ከምስራቅ ወለጋ ዞን፣ ጎቢሰዩ ወረዳ ወጣቶችን በመወከል በአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኩ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው አቶ ቡሻ ጎተታ “አዲስ አበባ ከተማ ባለቤትነቷ የኦሮሞ ህዝብ መሆኑ በህግ እንዲደነገግ፣ አፋን ኦሮሞ የፌደራል የስራ ቋንቋ እንዲሆን፣ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው የሸኔ ታጣቂ ቡድን አባላት እጃቸውን እንዲሰጡ” የሚጠይቁ አጀንዳዎች በትላንትናው የምክክር ውሎ ጎልተው መውጣታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የመንግስት ሰራተኞችን በመወከል ከአርሲ ዞን፣ በሌ ገስካር ወረዳ በምክክር ሂደቱ እየተሳተፉ የሚገኙት አቶ መለሰ ተፈራ የተባሉ ተወካይ፤ እርሳቸው በሚገኙበት ቡድን ጎልቶ የወጣው የታሪክ ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል።

የማህበረሰብ መሪዎችን በመወከል ከጅማ ዞን፣ ሸቤ ሶንቦ ወረዳ የመጡት አቶ ኢብራሂም አባጅሀድ “በሌሎች ክልሎች ስር ያሉ የኦሮሞ መሬቶች እንዲመለሱ፣ በጫካ ያሉ ኃይሎች ወደ ምክክሩ እንዲመጡ” የሚጠይቁ አጀንዳዎች መቅረባቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

🔴 ዝርዝሩን ለማንበብ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14640/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

17 Dec, 18:30


የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል የተሰኘው ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት በድጋሚ ታገደ

በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የተጣለበት እገዳ ባለፈው ሳምንት ተነስቶለት የነበረው የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) በድጋሚ ታገደ።

ሀገር በቀሉ የሰብአዊ መብት ድርጅት የታገደው፤ በተሰጠው ማስጠንቀቂያ መሰረት “አሰራሩን ባለማስተካከሉ” እና “ከዚህ ቀደም የፈጸማቸውን ጥፋቶች በመቀጠሉ ነው” ሲል ባለስልጣኑ ወንጅሏል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፤ እነዚህን እና ሌሎችን ውንጀላዎችን ለድርጅቱ በጻፈው ደብዳቤ ላይ መግለጹን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ፊርማ ያረፈበት ይህ ደብዳቤ የተጻፈው በትላንትናው ዕለት ቢሆንም፤ ለካርድ አመራሮች የደረሰው ዛሬ ማክሰኞ ታህሳስ 8፤ 2017 መሆኑን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጮች ገልጸዋል።

ደብዳቤው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በካርድ ላይ ባደረገው “የክትትል እና “የግምገማ ስራዎች”፤ ድርጅቱ ፈጽሟቸዋል ያላቸውን “የህግ ጥሰቶች” በመዘርዝር ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ እንደነበር አስታውሷል። በዚህ መሰረት ድርጅቱ “በተቋቋመበት ዓላማ መሰረት”፤ “ህጋዊ ሂደትን ጠብቆ እንዲሰራ” “በጥብቅ ማሳሰቡንም” ጠቅሷል።

🔴 ዝርዝሩን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2024/14634/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

17 Dec, 14:02


አዲሱ የባንክ ስራ አዋጅ ያካተታቸው ተጨማሪ ድንጋጌዎች የትኞቹ ናቸው?

ዛሬ ማክሰኞ ታህሳስ 8፤ 2017 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው የባንክ ስራ አዋጅ፤ በረቂቅ ደረጃ ከነበረው ይዘት የተወሰኑ ማሻሻያዎች ተደርገውበታል።

በሶስት የፓርላማ አባላት ተቃውሞ በአብላጫ ድምጽ የጸደቀው ይህ አዋጅ፤ በረቅቁ ላይ ተካትተው በነበሩ ትርጓሜዎች እና ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ላይ ማሻሻያ አድርጓል።

ማሻሻያ ከተደረገባቸው ድንጋጌዎች መካከል የባንክ ቅርንጫፎች እና የውጭ ባንኮችን የተመለከቱት ይገኙበታል። የውጭ ዜጎች በባንክ ስራ የሚሳተፉበትን አካሄድ በሚዘረዝረው የአዋጅ ክፍል ላይ አዲስ አንቀጽ እንዲካተት ተደርጓል።

በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆነ የውጭ ዜጋ በባንክ ስራ ስለሚሰማራበት ሁኔታ በረቂቁ ላይ ከተቀመጠው በተጨማሪም አዲስ ድንጋጌ በጸደቀው አዋጅ ላይ ተካትቷል።

ከማሻሻያዎቹ እና ከአዳዲስ አንቀጾች ውስጥ የተወሰኑት በ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተጠናቅረዋል። ዝርዝሩን ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14627/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

17 Dec, 09:42


ኢትዮጵያ ክሪፕቶ ከረንሲን ለመገበያያነት ለመጠቀም የሚያስችል መመሪያ ልታወጣ እንደምትችል የብሔራዊ ባንክ ገዢ ጥቆማ ሰጡ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ “የክሪፕቶ አሴትን”  እና የዲጂታል ገንዘብን በኢትዮጵያ መጠቀም የሚያስችል መመሪያ ወደፊት ሊያወጣ እንደሚችል የተቋሙ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።

ብሔራዊ ባንክ መመሪያውን የሚያወጣው በማዕከላዊ ባንኪንግ፣ በገንዘብ ፖሊሲ እና በገንዘብ አስተዳደር  ያሉ ዓለም አቀፍ “ለውጦችን” እና “እድገቶችን” እያየ መሆኑን አቶ ማሞ ተናግረዋል። 

አቶ ማሞ ይህን ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የአዋጅ ማሻሻያ ዛሬ ማክሰኞ ታህሳስ 8፤ 2017 በተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀበት ወቅት ከፓርላማ አባል ለቀረበ ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያ ነው። 

የአሁኑ አዋጅ ካካተታቸው አዳዲስ ድንጋጌዎች መካከል ክሪፕቶ ከረንሲ እና የዲጂታል ገንዘብን መጠቀም የተመለከተው አንዱ ነው።

አዋጁ “አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ብሔራዊ ባንክ ካልፈቀደ በስተቀር፤ ክሪፕቶ ከረንሲ ወይም ሌላ ማንኛውንም ዲጂታል ወይም የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ በመጠቀም ክፍያ መፈጸም አይችልም” ሲል ክልከላ ያስቀምጣል። 

አዋጁን በመተላለፍ በእነዚህ መንገዶች ክፍያ የፈጸመ ማንኛውም ሰው፤ ከሶስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት እና ከአስር ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣም ተደንግጓል።

🔴 ዝርዝሩን ያንብቡ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2024/14617/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

15 Dec, 10:14


ከኦሮሚያ ክልል ለሀገራዊ ምክክር የሚቀርቡ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ሂደት ከነገ ጀምሮ ሊካሄድ ነው

ከኦሮሚያ ክልል በሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ሂደት ከነገ ሰኞ ታህሳስ 7፤ 2017 ጀምሮ ለተከታታይ ስምንት ቀናት ሊካሄድ ነው።

በዚሁ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ላይ ስምንት ሺህ የሚጠጉ የማህበረሰብ ክፍል ወኪሎች እና የክልል ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስታውቋል።

በአዳማ ከተማ የሚካሄደው ይህ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት፤ በሀገራዊ ምክክር የተዘጋጁ ተመሳሳይ መድረኮችን ቁጥር 12 ያደርሰዋል። የኦሮሚያ ክልል በወረዳ እና በዞን ብዛቱ “ከፍተኛ ቁጥር” ያለው መሆኑ፤ የአሁኑን የምክክር መድረክ ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት የተለየ እንደሚያደርገው ተገልጿል።

በአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኩ ላይ በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ 356 ወረዳዎች በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ዛሬ እሁድ በአዳማ ከተማ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

🔵 ዝርዝሩን ይህን ሊንክ ተጭነው ያንበቡ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14606/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

18 Nov, 15:37


በአዲስ አበባ መርካቶ ገበያ ተደጋጋሚ የእሳት አደጋ ያጋጠመው አካባቢ፤ “በመልሶ ማልማት እንዲለማ” ምክረ ሃሳብ ቀረበ

ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በትላንትናው ዕለት ለሁለተኛ ጊዜ የእሳት አደጋ ያጋጠመው በአዲስ አበባ ከተማ መርካቶ ገበያ የሚገኝ አካባቢ፤ “የአደጋ ደህንነት መስፈርትን ቧሟላ” መልኩ “በመልሶ ማልማት እንዲለማ” ምክረ ሃሳብ ቀረበ። ምክረ ሃሳቡን ያቀረበው የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ነው።

ትላንት እሁድ ህዳር 8፤ 2017 እኩለ ቀን ገደማ የእሳት አደጋ የደረሰበት የመርካቶ ገበያ ስፍራ፤ በተለምዶ “ድንች ተራ” የሚል ስያሜ ያለው ነው። ስፍራው ከሁለት ሳምንት በፊት በተመሳሳይ አደጋ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ከነበረው “ነባር የገበያ ማዕከል” በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ነው።

የእሁዱ ቃጠሎ የደረሰበት ስፍራ፤ “በነባር የገበያ ማዕከል” ላይ የሚነግዱ ነጋዴዎች ንብረቶቻቸውን የሚያስቀምጡበት መጋዘን እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የእሳት አደጋው “ጌሾ ግቢ” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ከሚገኘው መጋዘን በተጨማሪ በአቅራቢያው የሚገኙ መደብሮች እና መኖሪያ ቤቶች ላይ ውድመት አድርሷል። 

በትላንቱ የእሳት አደጋ ሶስት የአካባቢው ነዋሪዎች እና ሁለት የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ሰራተኞች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14595/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

15 Nov, 15:34


የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አዲስ የአመራር ምርጫ ሊያካሄድ ነው 

አባል በሆኑ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ ሲቀርብበት የቆየው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ አዲስ የአመራር ምርጫ ሊያካሄድ ነው። ምክር ቤቱ ነገ እና ከነገ በስቲያ በሚያደርገው ጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢውን እና የስራ አስፈጻሚ አባላቱን ይመርጣል።

በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና በመንግስት መካከል ጠንካራ ግንኙነት እንዲፈጠር ለማድረግ በመጋቢት 2011 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፤ በአሁኑ ወቅት ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ 59 አባል ፓርቲዎች የታቀፉበት ነው። የጋራ ምክር ቤቱ በጠቅላላ ጉባኤ በወሰነው መሰረት ሰብሳቢውን እና ምክትል ሰብሳቢውን ጨምሮ አምስት የስራ አስፈጻሚ አባላትን በየዓመቱ ይመርጣል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄድ ያለበት ባለፈው ነሐሴ ወር ነበር። ሁለት ወር የዘገየው የጋራ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ፤ ከነገ ቅዳሜ ህዳር 7፤ 2017 ጀምሮ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በዚሁ ጉባኤ ላይ እርሳቸው የሚመሩት ስራ አስፈጻሚ በ2016 ዓ.ም ያከናወናቸውን ተግባራት ሪፖርት ለተሳታፊዎች እንደሚያቀርብ ገልጸዋል። 

🔴 ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14592/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

15 Nov, 14:09


በ2017 ሩብ ዓመት ምን ያህል ኢትዮጵያውያን ለስራ ወደ ውጭ ሀገራት ተልከዋል?

የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ካለፈው ሐምሌ እስከ መስከረም ባሉት ወራት በውጭ ሀገራት ለስራ ሊያሰማራቸው ከነበሩ 140 ሺህ ዜጎች ውስጥ ማሳካት የቻለው የእቅዱን 62 በመቶ ብቻ መሆኑን አስታወቀ። በሊባኖስ ለስራ የተሰማሩ ዜጎችን ከጉዳት ለመታደግ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማብራሪያ እንዲሰጥ በፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ጥያቄ ቢቀርብለትም፤ አጥጋቢ ምላሽ ሳይሰጥ ቀርቷል።

ጥያቄውን ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ህዳር 4፤ 2017 በተካሄደ ስብሰባ ላይ ያቀረበው፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነው። ቋሚ ኮሚቴው የትላንት በስቲያውን ስብሰባ የጠራው፤ የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴርን የ2017 እቅድ እና የሩብ አመት የስራ አፈጻጸምን ለመገምገም ነበር። 

በዚሁ ስብሰባ ላይ የሚመሩትን መስሪያ ቤት የሶስት ወራት አፈጻጸም ያቀረቡት የስራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል፤ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን በተመለከተ ጥቅል አሃዞችን በሪፖርታቸው አካትተዋል። ወደ ውጭ ለስራ የሚላኩ ዜጎችን በተመለከተ ከቋሚ ኮሚቴው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዘንድሮ በጀት ዓመት ሩብ ዓመት፤ ሚኒስቴሩ በውጭ ሀገራት ለስራ ያሰማራቸው ኢትዮጵያውያን 87,067 እንደሆኑ ሙፈሪያት ለፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተናግረዋል። ኢትዮጵያውያን ሰራተኞችን በህጋዊ መንገድ ለመቀበል፤ ከስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየሰሩ ያሉ ስድስት የመካከለኛው ምስራቅ እና ሁለት የአውሮፓ ሀገራት መሆናቸውን ሚኒስትሯ አመልክተዋል። 

🔵 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14579/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

13 Nov, 14:07


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “ትኩረት የሚያሻው” “የገቢ እጥረት” እንደገጠመው ገለጸ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በዘንድሮ በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ የሰበሰበው ገቢ፤ በእቅድ ይዞት ከነበረው በ10 ቢሊየን ብር ያነሰ መሆኑን ገለጸ። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከውጭ እርዳታ እና ብድር የተገኘው ገቢም፤ ከታቀደው ከግማሽ በታች መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል።

➡️ በከተማይቱ እየተተገበሩ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቁ ሆነው ሳለ፤ በበጀት ዓመቱ ሶስት ወራት የተሰበሰበው ገቢ መቀነሱ “ትኩረት የሚያሻው” መሆኑ ተገልጿል።

➡️ ይህ የተገለጸው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ2017 በጀት አመት አንደኛ የሩብ አመት የስራ አፈጻጸሙን ትላንት ማክሰኞ ህዳር 3፤ 2017 ዓ.ም በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የመሰብሰቢያ አዳራሽ በገመገመበት ወቅት ነው።  

➡️ በዚህ የግምገማ መድረክ ላይ የአስፈጻሚ አካላት የሶስት ወራት የስራ አፈጻጸም፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕላን እና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ አጠር ባለ መልኩ ቀርቧል። በስራ አፈጻጸም ሪፖርቱ ላይ ከቀረቡ ጉዳዮች መካከል የዕለቱ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ የነበረው፤ የአዲስ አበባ ከተማ ገቢ ሁኔታ ነው።

➡️ በዘንድሮ በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመሰብሰብ ያቀደው ገቢ 54.9 ቢሊየን ብር እንደነበር በትላንቱ የግምገማ መድረክ ላይ ተጠቅሷል። ሆኖም የከተማ አስተዳደሩ በዚህ ጊዜያት ውስጥ ማሳካት የቻለው የእቅዱን 83.3 በመቶ እንደሆነ አቶ አደም ተናግረዋል። 

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14568/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

13 Nov, 11:42


ለቀድሞዋ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የምስጋና መርሃ ግብር ሊደረግ ነው 

ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ከፕሬዝዳንትነታቸው ለተሰናበቱት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፤ በኃላፊነታቸው ላይ ሳሉ ላከናወኗቸው ስራዎች የምስጋና መርሃ ግብር ሊደረግላቸው ነው። ከነገ በስቲያ አርብ ህዳር 6፤ 2017 የሚደረገውን ይህን መርሃ ግብር ያዘጋጁት በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ሰባት ሀገር በቀል እና አለም አቀፍ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መሆናቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

የቀድሞዋ ፕሬዝዳንት ስልጣናቸውን ለተተኪያቸው ታዬ አጽቀ ስላሴ ያስረከቡት፤ የስድስት ዓመት የስልጣን ዘመናቸው ከመገባደዱ ሁለት ሳምንት አስቀድሞ ነበር። የቀድሟዋ ፕሬዝዳንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ፤ የመክፈቻ ንግግር እንዲያቀርቡ አስቀድሞ ተይዞ የነበረው መርሃ ግብር ተሰርዞ በምትኩ አምባሳደር ታዬ ንግግር ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። 

በፌደራል መንግስት ደረጃ ይፋዊ የሽኝት ስነ ስርዓት ላልተደረገላቸው ሳህለ ወርቅ፤ የምስጋና መርሃ ግብር የተዘጋጀው በአዲስ አበባው ሸራተን አዲስ ሆቴል ነው። የምስጋና መርሃ ግብሩ ዋና አላማ የቀድሞዋ ፕሬዝዳንት በሴቶች አመራር ረገድ ላከናወኗቸው ስራዎች በሴቶች አማካኝነት ምስጋና ለማቅረብ መሆኑን ፕሮግራሙን የማዘጋጀት ኃላፊነት የወሰደው የመቅዲ ፕሮዳክሽን ኦፕሬሽን ማናጀር አቶ በሃይሉ ተከተል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

🔵 ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14559/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

12 Nov, 12:14


በአዲሱ የባንክ ስራ አዋጅ ላይ የትውልደ ኢትዮጵያውያን መብት በግልጽ አለመቀመጡ በፓርላማ ጥያቄ አስነሳ 

አዲሱ የባንክ ስራ አዋጅ ጸድቆ ስራ ላይ ሲውል፤ በባንክ ስራ ላይ ለመሰማራት የሚፈልጉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሀገር ውስጥ ወይም ከውጭ ሀገር ኢንቨስተርነት አንዱን መምረጥ እንደሚኖርባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለጸ።

▶️ በ2000 እና በ2011 ዓ.ም. የወጡትን የባንክ ስራ አዋጆችን የሚሽረው አዲሱ የባንክ ስራ አዋጅ፤ ለፓርላማ የቀረበው ባለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ ነበር።

▶️ በተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ትላንት ሰኞ ህዳር 2፤ 2017 በጠራው የውይይት መድረክ ላይ፤ የትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ ጨምሮ በአዲሱ “የባንክ ስራ አዋጅ” የሰፈሩ ድንጋጌዎችን የተመለከቱ ጥያቄዎች ቀርበዋል።

▶️ በፓርላማ ውይይት እየተደረገበት ያለው አዲሱ የአዋጅ ረቂቅ፤ የባንክ ስራን በተመለከተ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ የወጡ አዋጆችን ቁጥር አራት ያደረሰ ነው።

▶️ የኢትዮጵያ መንግስት የባንክ አገልግሎትን ለውጭ ኢንቨስተሮች የሚከፍት ፖሊሲ በነሐሴ 2014 ዓ.ም. ተግባራዊ ማድረጉን ተከትሎ የተዘጋጀው አዲሱ አዋጅ፤ “ለትውልደ ኢትዮጵያውያን የሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነው” የሚል ጥያቄ ተነስቶበታል።

▶️ ጥያቄውን በትላንትናው ዕለት በተካሄደው የፓርላማ የአስረጂ የውይይት መድረክ ላይ ያቀረበው፤ በተወካዮች ምክር ቤት የህግ ጉዳዮች ጥናት ዳይሬክቶሬት ነው። አዲሱ አዋጅ በዋናነት ትኩረት ያደረገው “የውጭ ሀገር ዜጎች በባንክ የስራ መስክ” መሰማራት እንደሚችሉ መሆኑን ዳይሬክቶሬቱ በጥያቄው ላይ ጠቅሷል።

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14555/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

05 Nov, 16:42


የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምን ለመምራት ዕጩ የሚሆኑ ግለሰቦችን የሚያቀርብ ኮሚቴ ተቋቋመ

የስራ ዘመናቸውን ከአራት ወራት ገደማ በፊት አጠናቅቀው የተሰናበቱትን የህዝብ ዋና ዕንባ ጠባቂ የሚተኩ ዕጩዎችን የሚያቀርብ ኮሚቴ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቋቋመ።

▶️ በኮሚቴው ውስጥ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የጌዲኦ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ጌህዴድ) የፓርላማ ተመራጮች እንዲካተቱ ተደርጓል። 

▶️ ተጠሪነቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፤ በህግ የተደነገጉ የሰዎች መብቶች እና ጥቅሞች በአስፈጻሚ አካላት መከበራቸውን በማረጋገጥ፤ የህግ የበላይነትን መሰረት ያደረገ መልካም የመንግስት አስተዳደር እንዲሰፍን የማድረግ ዋና ዓላማ ያለው ነው። ተቋሙ የቀረቡለትን የአስተዳደር በደል አቤቱታዎች መሰረት በማድረግ፤ “ስልታዊ ምርመራ” የማካሄድ ኃላፊነትም በአዋጅ ተሰጥቶታል። 

▶️ይህን ተቋም ላለፉት ስድስት ዓመታት በኃላፊነት ሲመሩ የቆዩት ዶ/ር እንዳለ ኃይሌ ናቸው። ዶ/ር እንዳለ በድጋሚ ተሹመው፤ ለተጨማሪ ስድስት ዓመታት በኃላፊነት መቀጠል የሚችሉበትን ዕድል የተቋሙ ማቋቋሚያ አዋጅ ቢሰጣቸውም፤ ከዋና እንባ ጠባቂነታቸው መሰናበትን መርጠዋል።

▶️ ያገለገሉበት የስራ ዘመን “ከበቂ በላይ” መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት ዶ/ር እንዳለ፤ “አሁን ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ ምቹ ባለመሆኑ እና ነጻ እና ገለልተኛ ሆኖ ለመስራት አስቸጋሪ” ስለሆነ በኃላፊነት ላለመቀጠል መወሰናቸውን አስረድተዋል።

▶️ ለስራቸው ይከፈላቸው የነበረው ደመወዝ አነስተኛ መሆን፤ በዋና እንባ ጠባቂነት ለሁለተኛ ዙር ላለመሾም ካስወሰኗቸው ምክንያቶች መካከል እንደሚገኝበትም ገልጸዋል።

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14549/

Ethiopia Insider

05 Nov, 14:59


ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የምታበድረውን ገንዘብ፤ በድፍድፍ ነዳጅ ለማስከፈል የሚያስችል አማራጭ የያዘ ስምምነት በፓርላማ ጸደቀ 

ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ለምትበደረው 738.26 ሚሊዮን ዶላር፤ ወደፊት የምትፈጽመውን ክፍያ በድፍድፍ ነዳጅ እንድትመልስ አማራጭ የሚሰጥ የብድር ስምምነት በፓርላማ ጸደቀ።

➡️ በብድር ስምምነቱ የሚገኘው ገንዘብ፤ በደቡብ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ድንበር ከምትገኘው ፓጋክ ከተማ በመነሳት እስከ ፓሎች ከተማ ድረስ ያለውን 220 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት የሚያስችል ነው።

➡️ በሁለቱ ጎረቤት ሀገራት መካከል የተደረገው የብድር ስምምነት ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 26፤ 2017 በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በቀረበበት ወቅት፤ ማብራሪያውን በንባብ ያሰሙት በፓርላማ የመንግስት ዋና ተጠሪው ዶ/ር ተስፋዬ በልጅጌ ናቸው።

➡️ ዶ/ር ተስፋዬ የብድር ስምምነቱ የሁለቱ ሀገራትን ፍላጎት መሰረት ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለተግባራዊነቱም የተለያዩ የዝግጅት እና የትብብር ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል። 

➡️ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ብድር የምትሰጥበት የስምምነት ሰነድ በዛሬው ዕለት ለፓርላማ ይቀርብ እንጂ፤ ሁለቱ ሀገራት ስምምነቱን የተፈራረሙት በግንቦት 2015 ዓ.ም ነበር።

➡️ ደቡብ ሱዳን በብድር የምታገኘው ገንዘብ፤ በጋምቤላ በኩል ካለው የኢትዮጵያ ድንበር በመነሳት በነዳጅ ሀብት ወደ በለጸገው ፓሎች አካባቢ የሚዘረጋውን መንገድ ወደ አስፋልት ለማሳደግ የሚውል ነው።

➡️ የመንገድ ፕሮጀክቱ የሲቪል እና የአማካሪ ስራዎች የሚከናወኑት በኢትዮጵያውያን ኮንትራክተሮች እንደሆነ በስምምነቱ ላይ ተጠቅሷል።

🔵 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14540/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

05 Nov, 06:29


ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕዳ መክፈያ እና ካፒታል ማሳደጊያ የሚውል 900 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ቦንድ ለሽያጭ ሊቀርብ ነው

የገንዘብ ሚኒስቴር 900 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው የመንግስት ዕዳ ሰነድ (ቦንድ) እንዲያወጣ የሚፈቅድ የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ቀረበ። ገንዘቡ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድረው ያልከፈሉትን ዕዳ ለመክፈል እና ለባንኩ ካፒታል ማሳደጊያ የሚውል ነው።

ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 26፤ 2017 በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ የቀረበው ይህ አዋጅ፤ “የመንግስት እዳ ሰነድ” የሚል ስያሜን የያዘ ነው። አዋጁን ማውጣት ያስፈለገው፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለበት “ከፍተኛ ዕዳ” በባንኩ የፋይናንስ ገጽታ ላይ “ከፍተኛ ተጽዕኖ ስላስከተለ” መሆኑ በረቂቅ ህጉ ላይ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለመንግስት ለልማት ድርጅቶች ካበደረው ውስጥ እስካሁን ያልተሰበሰበው የገንዘብ መጠን፤ ከ845.3 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል። የልማት ድርጅቶቹ ብድሩን ከመንግስታዊው ባንክ የወሰዱት፤ ለተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ነው።

መንግስት የልማት ድርጅቶቹ ውስጥ ያልተከፈለ ከፍተኛ ብድር ያለበት፤ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኮርፖሬሽን ነው። ኮርፖሬሽኑ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መክፈል ይገባው የነበረው ብድር ከእነ ወለዱ 191.79 ቢሊዮን ብር እንደሆነ አዋጁን ለማብራራት በቀረበ ሰነድ ላይ ተጠቅሷል።

ከመንግስት ተቋሟት መካከል ባልተከፈለ ከፍተኛ የብድር መጠን ሁለተኛውን ቦታ የያዘው፤ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ነው።

🔴 ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14532/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

03 Nov, 15:59


በወላይታ ሶዶ ነዳጅ ማደያዎች የማይገኘው ቤንዚን፤ በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ እንዴት እንደ ልብ ሊገኝ ቻለ?

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፖለቲካ እና የርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ የሆነችው የወላይታ ሶዶ ከተማ፤ በሰባት በሮች እንግዶቿን ትቀበላለች። የህዝብ ትራንስፖርት እና የግል ተሽከርካሪዎችን የሚጠቀሙ ተጓዦች፤ በአረካ፣ ቦዲቲ፣ ኡምቦ እና ገሱባ ከተሞች አድርገው ወደ ወላይታ ሶዶ መግባት ይችላሉ። በጭዳ፣ ሆቢቻ፣ በዴሳ ከተሞች በኩል ያሉ መንገዶችን ለተጓዦች በአማራጭነት ያገለግላሉ።  

ከአዲስ አበባ ከተማ 332 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው በወላይታ ሶዶ፤ ነዋሪዎች ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ በዋናነት የሚጠቀሙት በተለምዶ ባጃጅ ተብለው የሚጠሩትን ባለ ሶስት እግር ታክሲዎችን ሲሆን ሞተር ሳይክልም በነዋሪዎቹ ዘንድ ይዘወተራል። በከተማይቱ ከ12 ሺህ በላይ ባጃጆች እና ሞተር ብስክሌቶች  እንደሚንቀሳቀሱ ከወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

የወላይታ ሶዶ ከተማ ደም ስር የሆኑት እነዚህ መጓጓዣዎች በዋነኛነት የሚጠቀሙት ቤንዚን ቢሆንም፤ በአቅርቦት ረገድ ያለው ችግር የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን ለከፍተኛ ምሬት ዳርጓል። ላለፈው አንድ ሳምንት በሶዶ ቆይታ ያደረገው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ፤ በከተማይቱ ውስጥ ባሉ የነዳጅ ማደያዎች ውስጥ ከፍተኛ የቤንዚን እጥረት መኖሩን አስተውሏል። 

ካለፈው ረቡዕ ጥቅምት 20 ጀምሮ ደግሞ፤ የከተማይቱ ነዳጅ ማደያዎች “ቤንዚን የለም” የሚሉ ጉልህ ማስታወቂያዎችን መለጠፋቸውን ታዝቧል። የወላይታ ሶዶ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት፤ በከተማዋ የነዳጅ ማደያዎች ቤንዚን አለመኖሩን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጧል።

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14522/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

03 Nov, 13:42


የፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ስምምነት ሁለተኛ ዓመት ሲታሰብ፤ ማን ምን አለ?

አቶ ሬድዋን ሁሴን የፌደራል መንግስትን እና አቶ ጌታቸው ረዳ ደግሞ ህወሓትን ወክለው፤ ግጭት የማቆም ስምምነት ተፈራርመው፣ እጅ ለእጅ ከተጨባበጡ፤ ትላንት ቅዳሜ ጥቅምት 23፤ 2017 ድፍን ሁለት ዓመት ሞላቸው። ስምምነቱ ለሁለት ዓመታት በትግራይ ክልል ያጓሩትን ጠመንጃዎች ጸጥ በማሰኘቱ፤ በአቶ ጌታቸው አገላለጽ “ስኬታማ” ነው። 

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሲቀሰቀስ ለአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ በመሾም ውጊያው እንዲቆም ከፍተኛ ግፊት ስታደርግ የቆየችው አሜሪካ፤ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ትላንት ምሽት ባወጣችው መግለጫ ተመሳሳይ ሀሳብ አንጸባርቃለች። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈረመው ስምምነት ተግባራዊነት ያመጣቸውን “ጠቃሚ መሻሻሎች” አሜሪካ በአዎንታ እንድምትመለከት ገልጸዋል።

ብሊንከን በዚሁ መግለጫቸው “ከምንም በላይ በትግራይ የአፈሙዝ ላንቃ ዝም ብሎ መቆየቱን” አድንቀዋል። በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጡ መሰረታዊ አገልግሎቶች እና ሰብአዊ እርዳታ መጀመራቸው፣ የተወሰኑ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውንም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአዎንታዊ ለውጥነት ጠቅሰዋል። 

ታጣቂዎችን ትጥቅ አስፈትቶ በመበተን መልሶ ከማህበረሰቡ ለማዋሃድ የተያዘው ዕቅድ በዚህ ወር ተግባራዊ እንደሚሆን የጠቆሙት ብሊንከን፤ ይህ እርምጃ “ሰላምን ለማጠናከር” “ወሳኝ” እንደሆነ ገልጸዋል። የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ የኢትዮጵያ መንግስት ይፋ ያደረጋቸው የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ እና የትግበራ ፍኖተ-ካርታ፤ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና እርቅ ለማውረድ መሰረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውንም አስገንዘበዋል።

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14517/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

02 Nov, 10:24


የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ እና የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር የቀረቡባቸውን ክሶች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

የማይገባ ጥቅም በመቀበል የሙስና ወንጀል በመፈጸም እና በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ በማቅረብ የተከሰሱት የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጸጋዬ ቱኬ፤ በቀረቡባቸው ሁለት ክሶች ላይ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ። በቀድሞው ከንቲባ እና አብረዋቸው በተከሰሱ ሁለት ተከሳሾች ላይ ባለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 19፣ 2017 ብይኑን የሰጠው፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሀዋሳ ማዕከል ነው።

የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ፤ በአቶ ጸጋዬ እና ሁለት ተከሳሾች ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ የመሰረተው፤ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ ነበር። በአንድ መዝገብ ክስ ከቀረበባቸው ተከሳሾች መካከል፤ የሲዳማ ክልል የቀድሞ የፖሊስ ኮሚሽነር አቶ አበራ አሬራ ይገኙበታል።

የክልሉ ዐቃቤ ህግ በአቶ አበራ እና በአቶ ጸጋዬ ላይ የመሰረተው የመጀመሪያ ክስ፤ በሙስና ወንጀሎች አዋጅ የተቀመጠን ድንጋጌ በመተላለፍ “የማይገባ ጥቅም በመቀበል የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል” የሚል ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የመጀመሪያው ክስ፤ በሀዋሳ ከተማ ሳውዝ ስታር ኢንተርናሽናል ሆቴል ጎን የተወሰደ ቦታ ምትክ መሬት እንዲሰጥ ከቀረበ ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው።

የምትክ ቦታ ጥያቄ ቀርቦ የነበረው፤ ከአቶ ጸጋዬ አስቀድሞ በነበሩት የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ የአመራር ጊዜ እንደነበር በክሱ ተመላክቷል። አቶ ጥራቱ የምትክ ቦታ እንዲሰጥ ውሳኔ ቢያስተላልፉም፤ የመሬት ርክክብ ከመፈጸሙ በፊት ከኃላፊነታቸው በመነሳታቸው ጉዳዩ ለተተኪያቸው ተላልፏል።

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14503/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

31 Oct, 13:17


ኢትዮጵያ ከተነካች “ለማንም የማትመለስ” መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስጠነቀቁ

ኢትዮጵያ ጦርነት ባትፈልግም፤ ከተነካች ግን “ለማንም የማትመለስ” መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስጠነቀቁ። በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣን ወረራ ለመመከት የሚያስችል “በቂ አቅም አለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሀገሪቱ በውጊያ ላይ የገጠሟትን ክፍተቶች የሚያሟሉ “ነገሮች” ማምረት መጀመሯን ገልጸዋል።

ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 21፤ 2017 በተካሄደው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስደመጡት ማብራሪያ፤ “ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ወደ ጦርነት ልትገባ ትችላለች” በሚል “አልፎ አልፎ” ስለሚቀርቡ ስጋቶች ምላሽ ሰጥተዋል። አንዳንድ ሰዎች ይህን ጉዳይ ከኤርትራ ጋር እንደሚያያዙት፤ ሌሎች ደግሞ “ሀገራት ኢትዮጵያን ሊወሩ ይችላሉ” የሚል ስጋት እንዳላቸው ጠቁመዋል። 

ከኤርትራም ይሁን ከጅቡቲ፣ ከሶማሊያም ይሁን ከኬንያ፤ ለኢትዮጵያ የሚያዋጣት “ሰላማዊ ጉርብትና” እንደሆነ አብይ በማብራሪያቸው አስገንዘበዋል። ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስም ላልጠቀሷቸው ሀገራት፤ ከእንግዲህ ወዲያ ኢትዮጵያን “እየመዘበሩ” እና “በሰፈር እያባሉ መኖር” እንደማይቻል ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል።  

“እኛ ቅጥረኞች አይደለንም። ለሆነ ቡድን ተቀጥረን፣ በስሙ ተገዝተን፣ የሆነ ቡድን አጀንዳ የምናራግብ ቅጥረኞች ሳንሆን፤ አርበኞች ነን። ይሄን አምኖ ካከበረ ማንኛውም ሀገር [ጋር] በከፍተኛ ደስታ አብረን መስራት እንፈልጋለን” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ለዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የፓርላማ አባላት በጭብጨባ ድጋፋቸውን ገልጸዋል። 

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14492/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

31 Oct, 11:48


ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ ሐሙስ በፓርላማ በነበራቸው ቆይታ፤ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ካብሯሯቸው ጉዳዮች ሰላም እና ጸጥታን የተመለከቱት ይገኙበታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ማብራሪያቸው፤ “ሰላምን የማይመርጡ” ስላሏቸው ሰዎች አንስተዋል።

“መቶ ፐርሰንት ሰው አመዛዛኝ ስለሆነ ሰላም ይፈልጋል ማለት አይደለም” ያሉት አብይ፤ በዚህም ሳቢያ በአለም ላይ ያሉ መንግስታት፤ ለዜጎቻቸው መኖሪያ ቤት እንደሚገነቡ ሁሉ ማረሚያ ቤት እንደሚገነቡ ጠቅሰዋል። ሆኖም መኖሪያ ቤት መገንባት ብቻውን “ሰላምን አያረጋግጥም” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለደሃ ዜጎች የሚሆኑ 248 ሺህ ቤቶች መገንባቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚያው ልክ ማረሚያ ቤት አለመገንባቱን ተናግረዋል። “ቁጥሩ ቢያንስም” ማረሚያ ቤት መገንባት እንደሚያስፈልግም ማብራሪያቸውን ለተከታተሉት የፓርላማ አባላት አስገንዝበዋል።

“አብዛኛው መኖሪያ ቤት፣ አብዛኛው የንግድ ቦታ፣ አብዛኛው ለውጥ የሚያመጣ [ቢገነባም]፤ ትንሽም ቢሆን ግን ማረሚያ ቤት ደግሞ ያስፈልጋል። ይሄንን balance መጠበቅ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ‘ሰው ሁሉ ሰላም ይፈልጋል፤ ሰው ሁሉ ለሰላም ይሰራል’ ብሎ በጥቅሉ ማየት ያስቸግራል። ባለፉት አመታት ያየነው ልምድም የሚያሳየው እንደዚያ አይደለም” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

31 Oct, 09:01


“አንዳንድ ሀገራት ኢትዮጵያን መዝረፍ መብት እንደሆነ የሚያስቡ አሉ”- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ 

ኢትዮጵያን “መዝረፍ”፤ “መብት እንደሆነ” የሚያስቡ “አንዳንድ ሀገራት አሉ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሰሱ። የኢትዮጵያን ሀብት “የመዝረፍ” እና “የውጭ ምንዛሬ ቢዝነስ የሚሰሩ” ኤምባሲዎች አሉ ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወንጅለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 21፤ 2017 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው፤ ከፓርላማ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው። በሁለት ክፍል በተከፈለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ቅድሚያውን ያገኙት፤ ከኢኮኖሚ ጉዳዮች ጋር በተያያዙ ለተነሱ ጥያቄዎች የተሰጡ ምላሾች ናቸው። 

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዘርፍ፤ በገቢ፣ በሬሚታንስ፣ በውጭ ኢንቨስትመንት፣ በወርቅ እና በቡና የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) “እድገት ማስመዘገቡን” በቁጥር በማስደገፍ ገለጻ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ “ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች” ያሏቸውን ጉዳዮችንም ለፓርላማ አባላት ዘርዝረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አብይ በተለይ በአጽንኦት ያነሱት፤ በባንኮች፣ በኤምባሲዎች እና በኩባንያዎች ይፈጸማሉ ያሉትን “የጥቁር ገበያ” ንግድ ነው። 

በሀገሪቱ ያሉ ባንኮች በህጋዊ መንገድ ከሚሰራው ይልቅ፤ “በትይዩ” የውጭ ምንዛሬ ገበያ በመሳተፍ “ኮሚሽን ማግኘት” እንደለመዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። “ባንክ በህጋዊ መንገድ የሚወዳደሩበት እንጂ በህገ ወጥ መንገድ በኮሚሽን ሀብት የሚሰበስቡበት መሆን የለበትም” ሲሉም ተደምጠዋል።  

🔴ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14474/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

28 Oct, 17:10


የከተማ መሬትን በድርድር በሊዝ ማስተላለፍ የሚፈቅድ የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ሊቀርብ ነው

የከተማ መሬትን ከጨረታ እና ከምደባ በተጨማሪ በድርድር በሊዝ ማስተላለፍ የሚፈቅድ የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ሊቀርብ ነው።

አዲሱ የአዋጅ ረቂቅ፤ ከተሞች በምደባ ለማቅረብ ካዘጋጁት መሬት መጠን ውስጥ፤ ቢያንስ 20 በመቶውን ለቤት ግንባታ አገልግሎት መዋል እንዳለባቸው ግዴታ ይጥላል። 

“የከተማ መሬትን በሊዝ ስለመያዝ” እንደወጣ የተገለጸው ይህ አዋጅ፤ ነገ ማክሰኞ ጥቅምት 19፤ 2017 በሚካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ እንዲቀርብ አጀንዳ ተይዞለታል።

በ2004 ዓ.ም የጸደቀውን “የከተማ ቦታን ስለመያዝ የወጣ አዋጅን” የሚተካው አዲሱ የህግ ረቂቅ፤ በስድስት ክፍሎች እና በ49 አንቀጾች የተከፋፈለ ነው።

በአዋጅ ረቂቁ ከተካተቱ አዳዲስ ጉዳዮች መካከል “መሬትን በድርድር በሊዝ ለማስተላለፍ” የሚፈቅደው ድንጋጌ ይገኝበታል።

አስራ ሶስት ዓመት ያስቆጠረው ነባሩ አዋጁ፤ የከተማ ቦታ በሊዝ እንዲያዝ የሚፈቀደው በጨረታ ወይም በምደባ ስልት ብቻ ነበር።

በአዲሱ አዋጅ የተካተተው “የድርድር” ስልት፤ “በጨረታ እና በምደባ አግባብ” ለተጠቃሚ ሊተላለፉ በማይችሉ የከተማ መሬቶች ላይ፤ አንድ አልሚ “ለተለዩ ሀገራዊ ፋይዳ ላላቸው አገልግሎቶች” መሬት በሊዝ ይዞ ማልማት የሚፈቀድበት ነው። 

በፌደራል መንግስት ለሚተዳደሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ለኢንዱስትሪ ልማት፣ ለከፍተኛ የትምህርት እና የጤና ተቋማት እንዲሁም ለምርምር ዘርፍ ፕሮጀክቶች የከተማ መሬት በድርድር ሊተላለፍ እንደሚችል በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተዘርዝሯል።   

🔵ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14466/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

28 Oct, 13:38


የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው መጠለያዎች “የታጠቁ አካላት ሰርገው በመግባት” ጥቃት እንደሚፈጽሙ ኢሰመኮ አስታወቀ

የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚኖሩባቸው ጣቢያዎች “ተገቢ ጥበቃ ስለማይደረግላቸው”፤ የታጠቁ አካላት “ሰርገው በመግባት ጥቃት እንደሚፈጽሙ” የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። በዚህ ሳቢያ ተፈናቃዮች “አስጊ በሆነ የደህንነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ” ኮሚሽኑ ገልጿል።

➡️ ብሔራዊው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋም ይህን ያስታወቀው፤ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን በተመለከተ ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 18፤ 2017 ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት ነው።

➡️ ኮሚሽኑ ለሶስተኛ ጊዜ ያዘጋጀው ዓመታዊ ሪፖርት፤ ከሰኔ 2015 እስከ ሰኔ  2016 ዓ.ም. ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍን ነው። 

➡️ በስምንት ክልሎች የተፈናቃዮቹን ሰብአዊ መብቶች አያያዝን የተመለከተ ክትትል እና ምርመራ ማድረጉን በሪፖርቱ የገለጸው ኢሰመኮ፤ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የታጠቁ ቡድኖች በየጊዜው በሚያደርሱት ማንነትን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች ዜጎች እንደሚፈናቀሉ አመልክቷል። በመንግስት እና በታጠቁ ቡድኖች መካከል የሚደረጉ ግጭቶች ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ኮሚሽኑ ጠቁሟል።

➡️ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ያለው የጸጥታ ችግር፤ ዜጎችን እንዲፈናቀሉ ከማድረግ ባሻገር ለተፈናቃዮች ሊደረግ የሚገባውን ሰብአዊ ድጋፍ እና ጥበቃ “አስቸጋሪ” እንዳደረገው በኮሚሽኑ ሪፖርት ላይ ተገልጿል። 

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14460/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

28 Oct, 12:29


የፎቶ ዘገባ፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አስረኛ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኩን፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በወላይታ ሶዶ ከተማ በዛሬው ዕለት ማካሄድ ጀምሯል።

በዚሁ የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ፤ በክልሉ ከሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ቁጥራቸው ሁለት ሺህ የሚጠጉ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት በሚደረገው በዚሁ የአጀንዳ ማሰባሰቢያ ምክክር መድረክ ላይ፤ የ32 ብሔረሰብ ተወካዮች ይሳተፋሉ ተብሏል። ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተወከሉት ተሳታፊዎች የተውጣጡት ከ96 ወረዳዎች መሆኑን በዛሬው መርሃ ግብር ላይ ተገልጿል።

የክልሉ የፖለቲካ እና የርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ የሆነችው የወላይታ ሶዶ ከተማ፤ የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረኩን ለማስተናገድ እንግዶችን መቀበል የጀመረችው ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ጀምሮ ነበር።

በወላይታ ሶዶ ከተማ፤ የሀገራዊ ምክክሩን የተመለከቱ ግዙፍ “ቢልቦርዶች” በየቦታው ተሰቅለው ሁነቱን ለማስተዋወቅ ሞክረዋል። ሆኖም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተሳታፊዎች ምክክር በሚደርጉበት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ያለው ድባብ ግን ከከተማይቱ የተለየ ነው።

በግቢው ውስጥ ዛሬ ስለተጀመረው የምክክር መድረክ የሚያስረዳ አንዳችም ነገር የለም። የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብም እንደ ወትሮ ሁሉ የዕለት ተዕለት ስራውን በመስራት ተጠምዷል።

በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ “ምን እየተከናወነ እንደሆነ” ያውቁ እንደሆነ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አራት ተማሪዎች፤ የመርሃ ግብሩን ምንነት እንደማያውቁ ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

🔵 ለተጨማሪ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14451/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

28 Oct, 11:26


የአምስት ሚኒስትሮች ሹመት በነገው ዕለት በፓርላማ ሊጸድቅ ነው

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነገው ዕለት በሚያካሄደው መደበኛ ስብሰባው፤ ከአንድ ሳምንት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሾሙትን ጨምሮ የአምስት ሚኒስትሮችን ሹመት መርምሮ ሊያያጸድቅ ነው። ፓርላማው በዚሁ ስብሰባው፤ የከተማ መሬትን የተመለከቱትን ሁለት የአዋጅ ረቂቆችን ጨምሮ አራት አዋጆችን ለሚመለከታቸው የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ይመራል።

መደበኛ ስብሰባዎቹን ማክሰኞ እና ሐሙስ የሚያካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት፤ ለነገ ጥቅምት 19፤ 2017 ሰባት አጀንዳዎችን ይዟል። በህዝብ ተወካዮች እና በፌደሬሽን ምክር ቤቶች የመክፈቻ የጋራ ስብሰባ ላይ፤ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ የሚቀርብ “የድጋፍ ሞሽን” ማድመጥ የሚለው ከአጀንዳዎቹ መካከል አንዱ ነው።

አቶ ታዬ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት፤ በመስከረም ወር መጨረሻ በተካሄደው በዚሁ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ እንደነበር ይታወሳል። ከዚህ ስነ ስርዓት አንድ ሳምንት በኋላ፤ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞትዮስ አቶ ታዬን በመተካት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።

በነገው የፓርላማ ስብሰባ፤ የዶ/ር ጌዲዮን፤ በፍትህ ሚኒስትርነት እርሳቸውን የተኳቸው የወ/ሮ ሃና አርአያ ስላሴ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር የሆኑት ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ ሹመት ይጸድቃል። ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር መጨረሻ የተሾሙት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ ዶ/ር ካሳሁን ጎፌ እና የባህል እና ስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሸዊት ሻንካም፤ በነገው ዕለት በፓርላማ በመገኘት ቃለ መሃላ እንደሚፈጽሙ ተገልጿል።

🔵 ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14448/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

28 Oct, 08:54


በምርጫ ቦርድ የታገዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በሀገራዊ የምክክር ሂደት ላይ መሳተፋቸው ይቀጥላል ተባለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “ማናቸውንም ህጋዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ” ያገዳቸውን ፓርቲዎች፤ በምክክሩ ሂደት ማሳተፉን እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ። ፓርቲዎቹ በመጪው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ላይም በተወካዮቻቸው በኩል እንዲሳተፉ እንደሚያደርግም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ይህን ያስታወቀው ከዛሬ ጀምሮ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚደረገውን የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ አስመልክቶ፤ ትላንት እሁድ ጥቅምት 17 በወላይታ ሶዶ ከተማ በሰጠው መግለጫ ነው። በዚሁ የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ፤ በክልሉ ከሚገኙ 96 ወረዳዎች በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ካሉት 11 ኮሚሽነሮች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ዮናስ አዳዬ ተናግረዋል።

ተሳታፊዎቹ የወከሏቸው የህብረተሰብ ክፍሎች፤ የመንግስት ሰራተኞች፣ መምህራን፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ተፈናቃዮች፣ የተገለሉ ማህበረሰቦች፣ እድሮች፣ አርሶ አደሮች እና የማህበረሰብ መሪዎችን መሆኑን ዶ/ር ዮናስ ገልጸዋል። ቁጥራቸው 2 ሺህ የሚጠጋው እነዚህ ተሳታፊዎች፤ በቀጣይ 3 ቀናት ለሀገር አቀፍ ጉባኤ የሚሆኑ የአጀንዳ ሃሳቦች ላይ ምክክር እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል።

ባለፈው ሳምንት በብሔራዊው ምርጫ ቦርድ እግድ የተጣለባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በምክክር ሂደቱ ላይ ያላቸው ተሳትፎ እንደሚቀጥል ዶ/ር ዮናስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ቦርዱ ከሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ጥሰቶችን ፈጽመዋል በሚል የታገዱ ፓርቲዎች 11 ናቸው።

🔴 ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14444/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

26 Oct, 08:18


ምርጫ ቦርድ የአገልግሎት ተመን ማሻሻያ ያደረገው “ድጎማን መሰረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን ለማስቆም” መሆኑን ገለጸ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፓለቲካ ፓርቲዎች ምዘገባ እና ለመሰረታዊ ሰነዶች ምዝገባ የሚጠይቀውን ክፍያ የጨመረው፤  “ድጎማን መሰረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን ለማስቆም” መሆኑን ገለጸ። በክፍያ ተመኑ ላይ የተደረገው ማሻሻያ፤ “ወደፊት የሚመጡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን” የሚመለከት መሆኑንም ቦርዱ አስታውቋል።

ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ይህን የገለጸው፤ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ይፋ ያደረገውን የክፍያ ተመን ማሻሻያ በተመለከተ ዛሬ ቅዳሜ ጥቅምት 16፤ 2017 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። በማሻሻያው መሰረት፤ ቦርዱ ጊዜያዊ የዕውቅና ሰርተፍኬት ለማግኘት ጥያቄ ከሚያቀርቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይጠይቅ የነበረውን የ100 ብር ክፍያ ወደ 15 ሺህ ብር አሳድጓል። 

በሀገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ የተመዘገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሙሉ የዕውቅና ሰርተፍኬት ለማግኘት ይከፍሉት የነበረው 200 ብርም፤ በአዲሱ የአገልግሎት ተመን ማሻሻያ ወደ 30 ሺህ ብር አሻቅቧል። ምዝገባቸውን በቦርዱ ያከናወኑ ፓርቲዎች፤ ለምርጫ ቦርድ የሚያቀርቧቸውን ሰነዶቻቸውን በሚያሻሽሉበት ወቅት የሚከፍሉት ተመንም ከ30 ብር ወደ አምስት ሺህ ብር ጨምሯል።

መንግስት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያከፋፈለው ገንዘብ መኖሩን ለጋዜጠኞች የተናገሩት የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ፤ “ይሄንን ጥቅም ብቻ ለማግኘት ብቻ እየታሰበ የሚሰራ ስራ በየጊዜው እየመጣ ነው” ሲሉ በምዝገባ ሂደት የሚሰተዋለውን ችግር አስረድተዋል።  

🔴 ለዝርዝሩ:-
https://ethiopiainsider.com/2024/14433/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

25 Oct, 14:54


ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ወራት ወደ ውጭ ከላከቻቸው ምርቶች፤ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ተነገረ

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ የሶስት ወራት አፈጻጸም፤ ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ83 በመቶ በመጨመሩ፤ 1.5 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ ጭማሪ ቢታይም፤ ወደ ውጭ ከተላኩ የጫት እና የጥራጥሬ ምርቶች የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር መቀነሱን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ይህ የተገለጸው፤ የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጭ ሀገር ከሚልኩ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ጋር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትላንት ሐሙስ ጥቅምት 14፤ 2017 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ላይ ነው።

በዚሁ ስብሰባ ላይ የዘንድሮ በጀት ዓመት የሶስት ወራት የወጪ ንግድ እቅድ አፈጻጸም ለተሰብሳቢዎች ቀርቧል። በአዲሱ የጥራጣሬ እና የቅባት እህሎች የቀጥታ ግዢ መመሪያ ላይም ውይይት ተደርጓል።

በንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የወጪ ንግድ ዘርፍ ስራ አስፈጻሚ አቶ በረከት መሰረት፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት ሶስት ወራት ከወጪ ንግድ ሊገኝ ታቅዶ የነበረው አጠቃላይ ገቢ 1.12 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ለተሰብሳቢዎች ገልጸዋል።

በሩብ ዓመቱ ሀገሪቱ ከዘርፉ ያገኘችው ገቢ በእቅድ ከታየዘው በ385 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ብልጫ ያለው እንደሆነም አመልክተዋል።

🔵 ዝርዝሩን ለማንበብ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14419/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

23 Oct, 14:52


ከመደበኛ እስር ቤቶች ውጭ የሚታሰሩ ሰዎች ሁኔታ “አሳሳቢ” ሆኖ መቀጠሉን ኢሰመኮ ገለጸ

ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ “በተራዘመ እስር”፣ “መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ቦታዎች”፣ እንዲሁም “በአስገድዶ መሰወር ሁኔታ“ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሁኔታ፤ “አሳሳቢ” ሆኖ መቀጠሉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ። የድርጊቱ ተጎጂዎች፤ ሲቪል እና የደንብ ልብስ በለበሱ የታጠቁ የጸጥታ አካላት “የህግ ስነ ስርዓት ባልተከተለ ሁኔታ” “በግዳጅ እንደሚያዙም” ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ብሔራዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ይህን ያስታወቀው፤ “የአስገድዶ መሰወር ሁኔታን” በተመለከተ ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 13፤ 2017 ባወጣው መግለጫ ነው። ኮሚሽኑ በዚሁ መግለጫው፤ ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ከ52 በላይ የሆኑ ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ተወስደው ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ መቆየታቸውን ይፋ አድርጓል።

የዛሬው መግለጫ እስከወጣበት ቀን ድረስ፤ 44 ሰዎች በተለያዩ መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች ከአንድ ወር እስከ ዘጠኝ ወር ድረስ እንዲቆዩ ከተደረገ በኋላ መለቀቃቸውን ኢሰመኮ አስታውቋል። በእነዚህ ቦታዎች እንዲቆዩ ከተደረጉ ግለሰቦች መካከል “ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የነበሩ ግለሰቦች” ጭምር እንደሚገኙበት ባደረገው ምርመራ ማረጋገጥ መቻሉን ኮሚሽኑ ገልጿል።

ሆኖም የሀገር መከላከያ ሰራዊት በሚያስተዳድራቸው ተቋማት ስር ባሉ “መደበኛ ያልሆኑ ማቆያ ቦታዎች “ተይዘው የሚገኙ ግለሰቦችን ሁኔታ ለማጣራት አለመቻሉን ኢሰመኮ አመልክቷል።

🔴 ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14413/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

23 Oct, 13:12


“የንጋት ኮከብ ለኢትዮጵያ” የተሰኘ አዲስ ፓርቲ ዛሬ ሊሰጥ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ተከለከለ

“የንጋት ኮከብ ለኢትዮጵያ” የተሰኘ አዲስ ተቃዋሚ ፓርቲ፤ ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 13 በአዲስ አበባው ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ለጋዜጠኞች ሊሰጥ የነበረውን መግለጫ “በመንግስት የደህንነት ኃይሎች ተከልክሏል” በመባሉ ሳይከናወን ቀረ። ፓርቲው መግለጫውን የጠራው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመንቀሳቀስ ቅድመ እውቅና ማግኘቱን ተመልክቶ ወደ ትግበራ መግባቱን ለማሳወቅ ነበር።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ(ኢዜማ)የቀድሞ አመራር የነበሩት አቶ ሀብታሙ ኪታባን ጨምሮ ዘጠኝ አደራጅ ኮሚቴ አባላት ያሉት አዲሱ ፓርቲ፤ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቅድመ እውቅና ፈቃድ ያገኘው ባለፈው ዓመት ነሐሴ መጀመሪያ ላይ ነበር። የመስራች ጉባኤውን ለማድረግ የድርጅት ስራዎችን በመስራት ላይ የሚገኘው ፓርቲው፤ በአሁኑ ወቅት እያከናወናቸው ያላቸውን እንቅስቃሴዎች አስመልክቶ መግለጫ ለመስጠት ለጋዜጠኞች ጥሪ ያደረገው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ነው።

ይህንኑ መግለጫ ለመዘገብ ዛሬ ረፋዱን 10 ጋዜጠኞች በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ቢገኙም፤ መርሃ ግብሩ ከተያዘለት ጊዜ በግማሽ ሰዓት ያህል በመዘግየቱ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎቹ ለአደራጅ ኮሚቴ አባላቱ ተደጋጋሚ ጥያቄ እንዲያቀርቡ አስገድዷቸዋል። የፓርቲው አደራጅ ኮሚቴ አባላት፤ ለጋዜጠኞቹ “ትንሽ ጠብቁን። ለሁላችሁም በጋራ መረጃ እንሰጣችኋለን” የሚል ምላሽ ሲሰጡ ከቆዩ በኋላ፤ የዛሬው መግለጫ “መከልከሉን” አሳውቀዋል።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የፓርቲው አደራጅ ኮሚቴ አባል ግን የዛሬው ክልከላ የተደረገው በመንግስት “የደህንነት አባላት” እንደሆነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

🔴 ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14407/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

22 Oct, 14:53


🔴 ቪዲዮ:- ከትላንቱ የእሳት አደጋ በኋላ፤ የመርካቶው “ሸማ ተራ” እንዴት ዋለ?

በአዲስ አበባ፤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ፤ መርካቶ ገበያ በተለምዶ “ሸማ ተራ” በተባለው አካባቢ ትላንት ሰኞ ምሽት የደረሰውን የእሳት አደጋ ተከትሎ፤ በዛሬው ዕለት በአቅራቢያው ባሉ ህንጻዎች እና መደብሮች የንግድ እንቅስቃሴ ቆሞ ውሏል። በእሳት አደጋው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት "ነባር የገበያ ማዕከል" በተሰኘ ህንጻ፤ ዛሬም ጭስ ይታይ እንደነበር በስፍራው የተገኘው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተመልክቷል። 

የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊሶች አደጋው የደረሰበትን ስፍራ ዙሪያውን በገመድ ማጠር፤ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ነጋዴዎች ወደ ቦታው እንዳይጠጉ ሲከለክሉ ተስተውለዋል። የተወሰኑ ነጋዴዎች ከቃጠሎ የተረፉ ንብረቶቻቸውን እንዲያወጡ ተፈቅዶላቸው፤ ጉዳት ወደ ደረሰበት ህንጻ ሲገቡም ዘጋቢው ታዝቧል። 

ትላንት ሰኞ ጥቅምት 11 ከምሽቱ 1 ሰዓት ገደማ በደረሰው እና ለ4 ሰዓታት ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ባልተቻለው በዚህ የእሳት ቃጠሎ፤ በገበያ ማዕከሉ ስር ያሉ የንግድ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል። ከቃጠሎው ለማምለጥ ከገበያ ማዕከሉ ህንጻ ላይ ዘልለው የወረዱ 2 ግለሰቦችን መመልከታቸውን ነዋሪዎቹ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በዚህ ሳቢያ አንደኛው ግለሰብ “ህይወቱ ወዲያው ማለፉን”የሚገልጹት ነዋሪዎቹ፤ ከህንጻው ላይ የዘለለው ሌላኛው ግለሰብ ግን ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ደርሶበት ወደ ህክምና ተቋም መወሰዱን አስረድተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ንጋቱ ማሞ ፤ በእሳት አደጋው ቀላልና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ህክምና ተቋማት የተወሰዱ ሰዎች እንዳሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

22 Oct, 14:00


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ11 የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ እገዳ ጣለ

●ሶስት ፓርቲዎች እግዱን በመቃወም ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአቤቱታ ደብዳቤ አስገብተዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ 11 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማናቸውንም ህጋዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ አገደ። ቦርዱ ያስተላለፈው የእግድ ውሳኔ፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሚያዘጋጃቸው ጉባኤዎች ላይ እንዳይገኙ እና በምክር ቤቱ ምርጫ ላይ እንዳይሳተፉም ይከለክላል።

ምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲዎቹ ላይ እገዳ የጣለው፤ ትላንት ሰኞ ጥቅምት 11፤ 2017 ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ ነው። ቦርዱ ለእገዳው በምክንያትነት የጠቀሰው “በጠቅላላ ጉባኤ”፣ “በኦዲት” እና “በሴት አባላት” ብዛት በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ምክንያት ፓርቲዎቹ ፈጽመዋቸዋል ያላቸውን ጥሰቶች ነው። 

ቦርዱ የእግድ ውሳኔ ካስተላለፈባቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል፤ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ህብረት፣ የወላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ፣ የገዳ ስርአት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ እና የአገው ለፍትህ እና ዲሞክራሲ ፓርቲ ይገኙበታል። እገዳ ከተጣለባቸው ፓርቲዎቹ አንዱ የሆነው የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ሰለሞን ፍሰሃ፤ በፓርቲያቸው ላይ ውሳኔው የተላለፈው “የሴቶች እና የአካል ጉዳተኞች አባላትን መረጃ አላቀረበም” በሚል ምክንያት መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

🔴 ለዝርዝሩ:https://ethiopiainsider.com/2024/14399/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

21 Oct, 16:36


በትግራይ ክልል ከጦርነት አስቀድሞ ለተሰጡ ብድሮች “ፖለቲካዊ መፍትሔ” እንዲሰጥ የሚጠይቅ የፊርማ ማሰባሰብ እየተካሄደ ነው

በትግራይ ክልል ከተካሄደው ጦርነት በፊት ለንግዱ ማህበረሰብ ተሰጥተው መመለስ ያልቻሉ ብድሮች እና ወለድን በተመለከተ፤ የፌደራል መንግስት “ፖለቲካዊ መፍትሔ” እንዲሰጥ የሚጠይቅ የፊርማ ማሰባሰብ በክልሉ ባሉ 52 ከተሞች እየተካሄደ ነው።

አርብ የተጀመረው የፊርማ ማሰባሰብ በነገው ዕለት ተጠናቅቆ “ወደ ክልሉ ማዕከል ይላካል” ተብሎ እንደሚጠበቅ የትግራይ ክልል የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል።

በጥቅምት 2013 ዓ.ም. በትግራይ ከተቀሰቀሰው ጦርነት አስቀድሞ፤ በክልሉ የፋይናንስ ተቋማት ተሰጥቶ የነበረው ብድር 31 ቢሊየን ብር እንደነበር ምክር ቤቱ አመልክቷል። ይህ ብድር ወለዱን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት 70 ቢሊዮን ብር ገደማ መድረሱን ምክር ቤቱ አመልክቷል።

በትግራይ ክልል ከተሞች በሚገኙ የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት እና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች አማካኝነት እየተካሄደ ያለው የፊርማ ማሰባሰብ፤ የፌደራል መንግስት ወለዱን እንዲሰርዝ አና ለተሰጡት ብድሮች ጦርነቱ እንዳስከተለው ጉዳት መጠን “ተመጣጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ” የሚጠይቅ ነው።

ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ “ፖለቲካዊ መፍትሄ ለማምጣት” ያለመ መድረክ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በመቐለ ከተማ ተካሄዷል። የትግራይ ክልል የንግድ እና ዘርፍ ማህበራት እንዲሁም የክልሉ የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች በጋራ በካሄዱት በዚህ ስብሰባ ላይ፤ በየከተሞቹ ከሚገኙ ነጋዴዎች የፊርማ ማሰባሰብ እንዲካሄድ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።

➡️ ዝርዝር ዘገባውን ለማንበብ :- https://ethiopiainsider.com/2024/14391/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

17 Oct, 10:35


በአዋሽ አካባቢ በ13 ሰዓት ልዩነት ውስጥ፤ ለሁለተኛ ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ 

አፋር ክልል አዋሽ አካባቢ በ13 ሰዓት ልዩነት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ። ዛሬ ሐሙስ እኩለ ቀን ገደማ የተከሰተው ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል ሲለካ 4.7 የተመዘገበበት እንደሆነ የጀርመን የጂኦሳይንስ የምርምር ማዕከል ገልጿል።

ዛሬ ሐሙስ ጥቅምት 7፤ 2017 የተከሰተው ከመተሐራ ከተማ በሰሜን ምስራቅ አቅጣጫ 34 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ የደረሰ እንደሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦችን በሚመዝግበው “ቮልካኖ ዲስከቨሪ” ድረ ገጽ ላይ ሰፍሯል።  የመሬት መንቀጥቀጡ በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ንዝረት ማስከተሉን ነዋሪዎች በማህበራዊ የትስስር ገጾች ሲገልጹ ተስተውለዋል።  

በትላንትናው ዕለት ምሽት እኩለ ለሊት አቅራቢያ በሬክተር ስኬል 4.6 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ በዚሁ አካባቢ ተከስቶ እንደነበር የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት መረጃ አመልክቶ ነበር። ርዕደ መሬቱ የደረሰበት ቦታ ከአዋሽ በስተሰሜን 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ መሆኑም በመረጃው ተጠቅሷል።   

🔴 ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14379/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

17 Oct, 07:45


ቪዲዮ፦ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስታቸው የጀመረውን የከተማ ኮሪደር ልማት “ሳያቋርጥ” እንደሚቀጥል ገለጹ። የኮሪደር ልማቱ “የሚቋረጥ ነገር መስሎት የሚያስብ ሰው ካለ፤ ደጋግሞ ማሰብ ይኖርበታል” ሲሉም ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ኢትዮ ቴሌኮም፤ 10 በመቶ የሚሆነውን አክሲዮኑን ለሽያጭ ማቅረቡን ይፋ ባደረገበት መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። አብይ በትላንቱ ንግግራቸው፤ “በአፍሪካ በስንዴ፣ በቡና እና በአንዳንድ ምርቶች የተሻለ ውጤት ማምጣት”መቻሉን አመልክተዋል።

በእርሳቸው አነሳሽነት ባለፈው ዓመት የካቲት ወር በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት “የተሻለ ውጤት ማሳየት ችለናል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። የኮሪደር ልማትን በተመለከተ “በጣም ብዙ ውዥንብሮች እንዳሉ አውቃለሁ” ያሉት አብይ፤ አዲስ አበባን በተመለከተ የተከናወኑ ስራዎች በሙሉ “ሰው ተኮር” መሆናቸውን አስገንዘበዋል።

“ሰው እንዳይጎዳ ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን ስራችን ግን አይቋረጥም። ገና እናፈርሳለን፤ ገና እንገነባለን። የሚቋረጥ ነገር መስሎት የሚያስብ ሰው ካለ ደጋግሞ ማሰብ ይኖርበታል” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል። “አዲስ አበባ አፍሪካ ላይ ካሉ ከተሞች ገና ነች። አሁንም፤ እንኳን ከአለም ከአፍሪካ ገና ነች። ገና ሲጀመር የሚቆም ስራ መኖር የለበትም” ሲሉም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

16 Oct, 20:57


በአዋሽ አካባቢ በ11 ቀናት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ

ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 6 ፤ 2017 ምሽት፤ በአዋሽ አካባቢ በሬክተር ስኬል 4.6 የተመዘገበ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት አስታወቀ። የመሬት መንቀጥቀጡ ያስከተለው ንዝረት፤ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች መሰማቱን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ከአዋሽ ከተማ 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተከሰተው የዛሬው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ከምሽቱ 5 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ላይ የተመዘገበ እንደነበር መስሪያ ቤቱ ጠቁሟል። በዚሁ አካባቢ ባለፈው አንድ ወር ጊዜ ብቻ ሰባት ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን መረጃዎች ያሳያሉ።

ባለፈው እሁድ በተመሳሳይ አካባቢ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4.6 የተመዘገበ ነበር። ከዚህ ክስተት አንድ ሳምንት አስቀድሞ መስከረም 26፤ 2017 ምሽት በዚያው ስፍራ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4.9 የደረሰ ነበር።

መስከረም 16፤ 2017 ለአርብ አጥቢያ ከሌሊቱ 6:36 አካባቢ በአዋሽ፣ ፈንታሌ እና ዶፈን አካባቢ ተመሳሳይ መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ተመዝግቧል። በዚሁ ዕለት ከሁለት ሰዓታት ቆይታ በኋላ የተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 4.5 ገደማ የተመዘገበ እንደነበር የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የዘርፉ ባለሙያዎች በወቅቱ መግለጻቸው አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

16 Oct, 15:27


ኢትዮ ቴሌኮም “ለመጀመሪያ ዙር” 100 ሚሊዮን አክሲዮኖችን ለሽያጭ ማቅረቡን አስታወቀ

መንግስታዊ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢው ኢትዮ ቴሌኮም፤ “ለመጀመሪያ ዙር” እያንዳንዳቸው 300 ብር ዋጋ ያላቸውን 100 ሚሊዮን መደበኛ አክሲዮኖች ለሽያጭ አቀረበ።

▶️ ተቋሙ ይህንን የገለጸው 10 በመቶ የባለቤትነት ድርሻውን በይፋ ለህዝብ መሸጥ መጀመሩን ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 6፤ 2017 ባስታወቀበት መርሃ ግብር ላይ ነው።

▶️ በካፒታል ገበያ በኩል ለሽያጭ የቀረበውን የኢትዮ ቴሌኮምን አክሲዮን መግዛት የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ፤ እስከ 3,333 አክስዮን ድረስ መግዛት እንደሚችል ተገልጿል።

▶️ ይህ ከፍተኛ የአክሲዮን መጠን ለገበያ የቀረበው፤  1.5 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ እና ተጨማሪ እሴት ታክስን ሳይጨምር በ999,000 ብር ነው።

▶️ አንድ “ግለሰብ ወይም ባለሀብት” የኢትዮ ቴሌኮምን ዝቅተኛ አክሲዮኖችን ለመግዛት 9,900 ብር ያስፈልገዋል። ይህ የገንዘብ መጠን ለ33 አክሲዮኖችን የቀረበ ሲሆን፣ የአገልግሎት ክፍያ እና ተጨማሪ እሴት ታክስን አያካትትም።

▶️ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ታህሳስ 25፤2017 በሚቆየው የአክሲዮን ሽያጭ የሚከናወነው፤ “ቴሌብር” በተሰኘው የኢትዮ ቴሌኮም ሞባይል ገንዘብ አገልግሎት መተግበሪያ መሆኑን ተቋሙ ጨምሮ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

🔵 ተጨማሪ ለማንበብ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14363/

[በዚህ ዘገባ ላይ ስለ አክሲዮኖች ዋጋ የተጠቀሰው ማስተካከያ ተደርጎበታል]

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

16 Oct, 15:10


በኢትዮጵያ ያሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ቋንቋዎችን ብዛት “በሳይንሳዊ መንገድ” የሚለይ ጥናት ሊካሄድ ነው 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፤ በኢትዮጵያ ያሉ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ቋንቋዎችን ብዛት “በሳይንሳዊ መንገድ” የሚሰነድ ጥናት በጋራ ሊያካሄዱ ነው። ሁለቱ ተቋማት ስራውን ለመጀመር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት በመጪዎቹ ሳምንታት ይፈራረማሉ ተብሏል።

➡️ የፌደራሉ መንግስት አባል በሆኑ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ፤ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የሚወከሉት በፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው።

➡️ በአሁኑ ወቅት 76 ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ ያላቸው ቢሆንም፤ የውክልና እና የማንነት ማስከበር ጥያቄዎችን ያያዙ አቤቱታዎች በየጊዜው ለምክር ቤቱ እየቀረቡ ይገኛሉ።

➡️ ይህ ጉዳይ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በተካሄደው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስብሰባ ላይም ተነስቶ ነበር። በዚሁ ስብሰባ ላይ የቀረበ ሪፖርት፤ ለጥያቄዎቹ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ተግዳሮት ከፈጠሩ ጉዳዮች አንዱ “በሀገር ደረጃ ብሔር፣ ብሔረሰቦችን በተገቢው መልኩ የሚገልጽ ፕሮፋይል አለመኖሩ” መሆኑን ገልጿል።

➡️ ችግሩን ለመፍታት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የማንነት መገለጫ የሆነ “አትላስ ወይም ፕሮፋይል” ጥናት ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ቋሚ ኮሚቴው በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል።

➡️ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጥናቱን ለማካሄድ የሚረዳ የመግባቢያ ሰነድ፤ በቀጣይ ሳምንታት እንደሚፈራረሙ በዩኒቨርስቲው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እና ባህሎች አካዳሚ ዳይሬክተር ዶ/ር ዮሀንስ አድገህ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

🔵 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14359/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

16 Oct, 10:58


ቪዲዮ፦ በአዲስ አበባ ከተማ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የታሪፍ ጭማሪ ተደርጓል። ከዛሬ ጥቅምት 6፤2017 ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገው አዲሱ ታሪፍ “ወቅታዊ የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ” እና “ሌሎች አስተዳደራዊ ወጪዎችን” ያማከለ መሆኑን የከተማይቱ ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል።

መንግስት በነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ ላይ የዋጋ ጭማሪ ያደረገው ከአንድ ሳምንት በፊት ነበር። የዓለም የነዳጅ ዋጋን መነሻን በማድረግ የነዳጅ ችርቻሮ ዋጋ ላይ የተደረገው የዋጋ ማስተካከያ፤ በየሶስት ወሩ የዋጋ ጭማሪ እንደሚደረግበት ተገልጿል። ይህን የዋጋ ማስተካከያ ተከትሎ በከተማይቱ የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጡ ሚኒባስ ታክሲዎች ላይ ከዛሬ ጀምሮ እስከ 13 ብር ከ 50 ሳንቲም የሚደርስ የዋጋ ጭማሪ ተደርጓል።

በከተማይቱ ትራንስፖርት ቢሮ እስከ 10 ብር የሚደርስ የዋጋ ማሻሻያ የተደረገላቸው ደግሞ የሚዲ ባስ ተሽካርካሪዎች ናቸው። በአዲሱ የትራንስፖርት ታሪፍ ማሻሻያ፤ በከተማይቱ አገልግሎት የሚሰጡ አውቶብሶች 5 ብር ጭማሪ አድርገዋል።

🔴 አዲሱን የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የታሪፍ ማሻሻያ ጭማሪ ለመመልከት፤ ከላይ የተያያዘውን ቪዲዮ ይጫኑ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Ethiopia Insider

15 Oct, 10:17


የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቀድሞ ታጣቂዎችን እና ተፈናቃዮችን ለማቋቋም፤ ለዚህ ዓመት ብቻ ከ“130 ሚሊዮን ብር በላይ ያስፈልገኛል” አለ

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሰላማዊ ኑሮ የተመለሱ የቀድሞ ታጣቂዎችን እና በጸጥታ መደፍረስ ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ለማቋቋም፤ በዚህ ዓመት ከ130 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ማቀዱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጸ።

▶️ ክልሉ ለመልሶ ማቋቋም ስራው የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን የሚያፈላልግ የሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ማቋቋሙን አስታውቋል።

▶️ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካቢኔ ከትላንት በስቲያ እሁድ ጥቅምት 3፤ 2017 ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፤ ኮሚቴው “በአጭር ጊዜ ወደ ስራ እንዲገባ” ውሳኔ አስተላልፏል።

▶️ የገቢዎች፣ የፋይናንስ፣ የንግድ፣ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊዎችን በውስጡ ያካተተው ኮሚቴው፤ የክልሉ ማህበረሰብ እና የተለያዩ ድርጅቶችን አስተባብሮ የሚፈለገውን የገንዘብ መጠን የማሰባሰብ ስራን በበላይነት የመምራት ኃላፊነት የተጣለበት መሆኑም ተነግሯል።

▶️ የሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴውን ማደራጀት ያስፈለገው፤ የክልሉ መንግስት ካለው የበጀት ውስንነት አንጻር ስራውን በራሱ አቅም ብቻ ለማከናወን የማይቻል በመሆኑ ምክንያት መሆኑን የክልሉ የካቢኔ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሻሪፍ ሃጂ አኑር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

▶️ ክልሉ ለመልሶ ማቋቋም በዚህ ዓመት ለመሰብሰብ ያቀደው ከ130 ሚሊየን ብር በላይ መሆኑን የገለጹት አቶ አሻሪፍ፤ ሆኖም ለአጠቃላይ ስራው ከዚህም በላይ በጀት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።


🔴 ለዝርዝር ዘገባው፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14356/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

14 Oct, 13:51


የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት “የህዝባዊ ቁጣ መገንፈል እና ተዛማጅ ጉዳዮችን” ሊያስከትል እንደሚችል ኢህአፓ አስጠነቀቀ

በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለው እና ወደ ሁለተኛ ምዕራፍ የተሸጋገረው የኮሪደር ልማት፤ የከተማይቱን ነዋሪዎች “ሰብአዊ መብቶች የጣሰ ነው” ሲል የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ዛሬ በሰጠው መግለጫ ወቀሰ።

➡️ በኮሪደር ልማቱ ሳቢያ“እያየለ የመጣው የህዝብ ብሶት እና ምሬት” በቸልታ ከታለፈ፤ “የህዝባዊ ቁጣ መገንፈል እና ተዛማጅ ጉዳዮችን” ሊያስከትል እንደሚችልም ፓርቲው አስጠንቅቋል።
   
➡️ አዲስ አበባ “ዓለም አቀፍ ደረጃዋን ጠብቃ የመልማቷ ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ” እንዳልሆነ በዛሬው መግለጫው የጠቀሰው ፓርቲው፤ ይሁን እንጂ የከተማዋ ልማት እና እድገት “ከኗሪው ህዝብ መብት መከበር” እና “ከጥቅሞቹ መጠበቅ” ተነጥሎ ሊታይ እንደማይገባ አሳስቧል።

➡️ ልማቱ “ከዜጎች አጠቃላይ የኑሮ መስተጋብር እና የኢኮኖሚ እድገት ጋር የተጣጣመ” መሆን እንደሚኖርበትም ፓርቲው በአጽንኦት አንስቷል።
 
➡️ የዛሬውን መግለጫ የሰጡት የኢህአፓ የአዲስ አበባ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አበበ አካሉ፤ በከተማይቱ እየተካሄደ ባለው የኮሪደር ልማት “የበርካታ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች፣ አነስተኛ እና ከፍተኛ የንግድ ድርጅቶች” መፍረሳቸውን ገልጸዋል።

➡️ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እየወሰዳቸው ያላቸው እርምጃዎች “የነዋሪዎች ሁኔታ ያላገነዘቡ፣ ምቹ ጊዜን ያልጠበቁ እና ከግምት ያላስገቡ” መሆናቸውንም አመልክተዋል። 

🔴 ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14349/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

11 Oct, 09:11


የኢትዮጵያ መንግስት በከተማ የሚሰራው የኮሪደር ልማት “በቂ ስላልሆነ”  በገጠር  የኮሪደር ልማት በቅርቡ እንደሚጀምር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያስታወቁት፤ ለ“ታማኝ ግብር ከፋዮች” በተዘጋጀ የእውቅና እና ሽልማት መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

🔴 ዝርዝር ዘገባውን በጹሁፍ ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14339/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

11 Oct, 07:51


የኢትዮጵያ የእቃ አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማህበር፤ መንግስት የሎጀስቲክ ዘርፍን “ለጊዜው”  ለውጭ ባለሃብቶች “ክፍት እንዳያደርግ” ጠየቀ። ማህበሩ ይህን ጥያቄ ለመንግስት ማቅረቡን ያስታወቀው፤ ትላንት ሐሙስ መስከረም 30 በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል በሰጠው መግለጫ ነው።

ለጋዜጠኞች መግለጫውን የሰጡት የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊት ውብሸት፤ ኢትዮጵያ ከ3 አመት በኋላ የሚካሄደውን ዓለም አቀፉን የሎጀስቲክ ጉባኤ እንድታዘጋጅ መመረጧን አስታውቋል። እስከ 2 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች እንደሚሳተፉበት በሚጠበቀው በዚሁ ጉባኤ ላይ፤ የሎጀስቲክስ ኢንዱስትሪው ላይ ትኩረት  ያደረገ ምክክር ይደረጋል። 

ማህበሩ የኢትዮጵያ የሎጀስቲክ ዘርፍን በተመለከተ ለመንግስት ጥያቄ ያቀረበው፤ ከትላንት በስቲያ ረቡዕ በተካሄደ ውይይት ላይ እንደነበር አቶ ዳዊት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “የሎጅስቲክ ዘርፍን እንዴት ማዘመን ይቻላል?” በሚል ርዕስ በተካሄደው ውይይት፤ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር፣  ንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የጉምሩክ ኮሚሽን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ነው።

የኢትዮጵያ የእቃ አስተላላፊዎችና የመርከብ ወኪሎች ማህበር የሎጀስቲክ ዘርፉ “ለጊዜው ለውጭ ባለሃብቶች ክፍት እንዳይደረግ” የጠየቀው፤ የሀገር ውስጥ ድርጅቶች ከውጭ አቻዎቻቸው ጋር ለመወዳደር “የመዘጋጃ ጊዜ ስለሚያስፈልጋቸው” እንደሆነ አቶ ዳዊት አስረድተዋል። የውጭ ባለሀብቶች በባንክ እና በቴሌኮም ዘርፍ እንዲሳተፉ መንግስት ሲፈቅድ፤ ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች የመዘጋጃ ጊዜ መስጠቱን ያስታወሱት አቶ ዳዊት፤ “እኛም [ዘርፉ] ሙሉ ለሙሉ ለውጭ ከመከፈቱ በፊት የጎደለንን እንድናሟላ ድጋፍ እንዲደረግልን ጥያቄ አቅርበናል” ሲሉ አብራርተዋል።(ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

10 Oct, 16:43


የሪል ስቴት አልሚዎች የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ እንዲያወጡ የሚያስገድድ የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ቀረበ

በሪል ስቴት ልማት ላይ ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሃብቶች “የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ”እንዲያወጡ የሚያስገድድ የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ቀረበ። አግባብ ባለው አካል፤ የሪል ስቴት ወቅታዊ ዋጋ አመላካች የሆነ “መነሻ እና መድረሻ ጣሪያ” በየጊዜው እንደሚወጣም በአዲሱ የአዋጅ ረቂቁ ተደንግጓል።

“የሪል ስቴት ልማት እና የማይንቀሳቀስ ንብረት ግብይትና ግመታ” በሚል ርእስ የተዘጋጀው የአዋጅ ረቂቅ፤ በሰባት ክፍሎች የተከፋፈለ ሲሆን በውስጡ 36 አንቀጾች ይዟል። አዋጁ ከተዘጋጀባቸው ምክንያቶች አንዱ “የቤት ፈላጊዎች በእጥረት እና በገበያ ግልጽነት መጓደል ምክንያት የሚደርስባቸውን ጫና ለመታደግ” መሆኑ በሰነዱ ላይ ተመልክቷል።

ዛሬ ሐሙስ መስከረም 30፣ 2017 ለፓርላማ የቀረበው የአዋጅ ረቂቅ፤ መንግስት ለሪል ስቴት አልሚዎች “መሬት በስፋት እንዲቀርብላቸው” የሚያደርግበትን የድጋፍ አሰራር አብራርቷል።

የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪ የሪል ስቴት አልሚዎች የእዚህ እድል ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት፤ በአዋጅ ረቂቁ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን ሲያሟሉ ነው።

የሪል ስቴት አልሚዎች እንደከተሞች ደረጃ “በአንድ ጊዜ “ከ500 እስከ አምስት ሺህ የሚሆኑ ቤቶች የሚገነቡ” ከሆነ እና ከዚህ ውስጥም “40 በመቶ የሚሆነውን” ለዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ላላቸው የማህበረሰብ ክፍል “ተደራሽ” የሚያደርጉ ከሆነ መሬት በስፋት ሊቀርብላቸው እንደሚችል በአዋጅ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል።

🔴 ለዝርዝሩ :- https://ethiopiainsider.com/2024/14332/

Ethiopia Insider

08 Oct, 17:57


የዓለም የነዳጅ ዋጋን መነሻን በማድረግ፤ የነዳጅ ችርቻሮ ዋጋ በየሶስት ወሩ እንደሚጨምር መንግስት አስታወቀ

 ዛሬ ቤንዚን በ9 ብር ገደማ፣ ነጭ ናፍጣ በ7 ብር ገደማ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎባቸዋል

የዓለም የነዳጅ ዋጋን መነሻን በማድረግ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ ላይ በየሶስት ወሩ ጭማሪ ሊያደርግ ነው። መንግስት በነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ላይ ከአንድ ዓመት በኋላ“የተሟላ ማስተካከያ” እንደሚያደረግም ተገልጿል። 

ይህ የተገለጸው የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 28፤ 2017 ባወጣው መግለጫ ነው። የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መግለጫ ከዛሬ ምሽት 12 ሰአት ጀምሮ በስራ ላይ የሚውል የነዳጅ ምርቶች ችርቻሮ መሸጫ ዋጋን ይፋ ያደረገ ነው።

በዛሬው የዋጋ ማስተካከያ፤ አንድ ሊትር ቤንዚን በ9 ብር ገደማ የጨመረ ሲሆን ነጭ ናፍጣ በበኩሉ በሊትር 7 ብር ገደማ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎበታል። በዚህ መሰረት እስከ ዛሬው ዕለት ድረስ በሊትር 82 ብር ከ60 ሳንቲም ይሸጥ የነበረው ቤንዚን፤ ከዛሬ ምሽት ጀምሮ በ91 ብር 14 ብር እንዲሸጥ ተወስኗል። 

ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ ይፋ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ፤ በነዳጅ ዋጋ ላይ “ከፍ ያለ ጭማሪ” ማስከተሉ ለዋጋ ጭማሪው አንደኛው መሰረታዊ ምክንያት መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል። የነዳጅ ምርቶች ዋጋ የፖሊሲ ማሻሻያው ይፋ ከመሆኑ በፊት በነበረበት መጠን እንዲቀጥል ለማድረግ፤ የኢትዮጵያ መንግስት “በሁለት ወራት ብቻ ከ35.8 ቢሊዮን ብር በላይ ለድጎማ ማውጣቱን” ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14326/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

07 Oct, 19:14


የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፤ በህወሓት አንድ ጎራ የመንግስት “ግልበጣ ታውጆብኛል” ሲል ከሰሰ

በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፤ “የጥፋት ኃይል” ሲል የጠራው ቡድን የመንግስት “ግልበጣ አውጆብኛል” ሲል ከሰሰ። በዚህ ኃይል ላይ “ህጋዊ እርምጃ” እንደሚወስድ ያስታወቀው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ በዚህ ሂደት ለሚፈጠር ማንኛውም አይነት ጥፋት “ብቸኛ ተጠያቂው”ይኸው ቡድን እና አመራሩ መሆኑን ገልጿል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ይህን ያስታወቀው፤ ዛሬ ሰኞ መስከረም 27፤ 2017 ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው። በትግራይ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ይፋዊ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ የወጣው ይህ መግለጫ፤ የህወሓት አመራር “ለሁለት ከተሰነጠቀ በኋላ” የተከሰቱ ጉዳዮችን መለስ ብሎ ቃኝቷል።

በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ጎራ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳን ከስልጣን ማንሳቱን አስታውቋል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫ፤ “የቡድኑ” አካሄድ የመንግስት “ግልበጣ እወጃ” እንደሆነ ገልጿል።

“የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የህዝብ አንድነትን ላለማደፍረስ በሚል የተከተለውን ትግስት እንደ ድክመት በመውሰድ፤ ይህ ቡድን ከመስከረም 27፤ 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ስርዓት አልበኝነትን ለማስፈን ያለውን ፍላጎት በይፋ አውጇል። ቡድኑ መንግስትነት እንዴት እና በምን ሁኔታ እንደሚያዝ ጠፍቶት ሳይሆን፤ በትግራይ ውስጥ ሁከት እና ግርግርን ለመፍጠር እያደረገ ያለው ኃላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው” ሲል አስተዳደሩ በመግለጫው ወንጅሏል።

🔴 ዝርዝር ዘገባውን ለማንበብ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14313/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

07 Oct, 11:35


አቶ ታዬ አጽቀሥላሴ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾሙ

ላለፉት 8 ወራት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሲያገለግሉ የነበሩት አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ፤ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾሙ። የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ሰኞ መስከረም 27፤ 2017 ባካሄዱት የጋራ ስብሰባ፤ የአቶ ታዬን ሹመት በአምስት ድምጸ ተዐቅቦ አጽድቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

🔴 ዝርዝር ዘገባውን ለማንበብ ይህን ሊንክ ይጫኑ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14309/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

07 Oct, 10:19


በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን፤ አቶ ጌታቸው ረዳን ከጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነት ማንሳቱን አስታወቀ

በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ቡድን፤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ከስልጣን ማንሳቱን አስታወቀ።  የጊዜያዊ አስተዳደሩ አራት የካቢኔ አባላትን ጨምሮ 13 ኃላፊዎችን በተመሳሳይ መልኩ ከኃላፊነት ማውረዱን የገለጸው ቡድኑ፤ በምትኩ ተተኪ አመራሮችን መሾሙን ይፋ አድርጓል።

የእነ ዶ/ር ደብረጽዮን ቡድን ይህን የገለጸው፤ ዛሬ ሰኞ መስከረም 27፤ 2017 በይፋዊ የህወሓት የፌስቡክ ገጽ ባሰራጨው መግለጫ ነው። ህወሓትን ወክለው በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እና በክልሉ ዞኖች በአመራርነት የተመደቡ ኃላፊዎች እንዲነሱ ውሳኔ የተላለፈው፤ በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ባለፈው አርብ ባካሄደው ስብሰባ መሆኑን መግለጫው ጠቅሷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

🔴  ዝርዝር ዘገባውን ለማንበብ:-https://ethiopiainsider.com/2024/14290/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

06 Oct, 12:05


በአማራ ክልል “ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ” የሚፈጸሙ እስሮች በአፋጣኝ እንዲቆሙ ኢሰመኮ አሳሰበ

በአማራ ክልል በበባህር ዳር፣ ጎንደር ከተሞች እና በተለያዩ አካባቢዎች ከመስከረም ወር አጋማሽ ጀምሮ “በአዲስ መልክ” በርካታ ሰዎች “ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ” እየታሰሩ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። በክልሉ እየተካሄዱ ያሉት የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን እና መርሆችን “ያልተከተሉ” እስሮች በአፋጣኝ እንዲቆሙም አሳስቧል።

ብሔራዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ይህን ያስታወቀው ዛሬ እሁድ መስከረም 26፤ 2017 ባወጣው መግለጫ ነው። ኢሰመኮ በዚህ መግለጫው፤ “ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ” እስር ተፈጽሞባቸዋል ካላቸው ውስጥ የመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ፣ የሚዲያ እና የሲቪክ ማህበረሰብ አባላት ይገኙባቸዋል።

ለእስራት ከተዳረጉት ሰዎች መካከል “ቋሚ የሕክምና ክትትል የሚያስፈልጋቸው” እንደሚገኙበት ኮሚሽኑ ገልጿል። እስረኞቹ የዛሬው መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ “ፍርድ ቤት ያልቀረቡ” መሆናቸውንም አመልክቷል።

የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፤ በትጥቅ ግጭት እና በጸጥታ መደፍረስ ወቅትም ቢሆን ሲቪል ሰዎችን ለመያዝ እና በወንጀል ለመጠርጠር የሚያበቃ “በቂ ህጋዊ ምክንያት መኖሩን ማረጋገጥ” እንደሚገባ ተናግረዋል። “የተወሰኑ ልዩ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ በፍርድ ቤት የተሰጠ የመያዣ እና የብርበራ ትእዛዝ” ሊኖር እንደሚገባም ራኬብ አስገዝንበዋል።

🔴 ለዝርዝሩ:- https://ethiopiainsider.com/2024/14285/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

04 Oct, 11:29


ቪዲዮ፦ አምስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አመራር “የህግ ጥሰት ፈጽሟል” ሲሉ ከሰሱ። የጋራ ምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጠይቀዋል።

ጥያቄውን ያቀረቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ (ዎብን)፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) እና ህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ህብር- ኢትዮጵያ) ናቸው። ፓርቲዎቹ ዛሬ አርብ መስከረም 24፤ 2017 በአዲስ አበባ ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው በኢህአፓ ጽህፈት ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በወቅቱ የጋራ ምክር ቤቱ አመራር ተፈጽመዋል ያሏቸውን ጥሰቶች ዘርዝረዋል።

የአምስቱን ፓርቲዎች የጋራ መግለጫ በንባብ ያሰሙት የዎብን ሊቀ መንበር አቶ አማኑኤል ሞጊሶ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የአመራር ዘመን ነሐሴ 13፤ 2016 መጠናቀቁን ገልጸዋል። ሆኖም የምክር ቤቱ አመራር የስራ ዘመኑን ወደ ሁለት ዓመት ለማራዘም፤  አባላቱ “የማያውቁትን የማሻሻያ ጥያቄ” ለምርጫ ቦርድ ማቅረቡን አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

🔴 የአምስቱ ፓርቲዎችን የጋራ መግለጫ ለመመልከት ከታች የተያያዘውን ቪዲዮ ይጫኑ። የፓርቲዎቹ ተወካዮች ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጧቸውን ምላሾች፤ ይህን ሊንክ https://youtu.be/7-dC1g6Q5Ys ተጭነው ይመልከቱ።

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

03 Oct, 15:32


ከመስከረም ወር ጀምሮ ታሳቢ የሚደረግ የደመወዝ ጭማሪ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁን የገንዘብ ሚኒስትሩ ገለጹ

ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ለሆኑ የመንግስት ሰራተኞች ከመስከረም ወር ጀምሮ ታሳቢ የሚደረግ የደመወዝ ጭማሪ፤ ከትላንት በስቲያ በተካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ መጽደቁን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናገሩ። የደመወዝ ጭማሪው 92 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት መጠየቁንም የገንዘብ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት፤ ከሁለት ወራት በፊት መተግበር የጀመረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎች አስመልክቶ በትላንትናው ዕለት ለመንግስት ቅርበት ላለው ፋና ቴሌቪዥን በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነው። አቶ አህመድ በዚሁ ገለጻቸው፤ የፖሊሲ ማሻሻያው “በጎላ መልኩ ማህበራዊ ጫና እንዳያስከትል” በወጣው እቅድ መሰረት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል። 

ፌደራል መንግስት “በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ማህበረሰብ የመደገፉ ወይም የመደጎሙን ስራ አጠናክሮ መቀጠል አለበት” የሚለው ከእቅዱ መካከል አንዱ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው ይፋ በተደረገበት ወቅት፤ ለዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ የመንግስት ሰራተኞች “አስፈላጊ የደመወዝ ድጎማ እና ማሻሻያዎች” “ለተወሰኑ ጊዜያት” እንደሚደረግ መገለጹ ይታወሳል።

ይህ የደመወዝ ጭማሪ ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ መስከረም 21፤ 2017 ዓ.ም በተካሄደው “የካቢኔ” ስብሰባ ላይ መጽደቁን አቶ አህመድ ተናግረዋል። ከመስከረም ወር ጀምሮ ታሳቢ የሚደረገው የደመወዝ ጭማሪ፤ “ለኑሮ ድጎማ ጭምር እንዲሆን” በማሰብ የተተገበረ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።  

🔴 ዝርዝሩን ለማንበብ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14278/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

03 Oct, 13:50


በባህር ዳር ከተማ በጸጥታ ኃይሎች ታስረው የነበሩት ሁለት የምክር ቤት አባላት ተለቀቁ

በባህር ዳር ከተማ ከትላንት በስቲያ በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የዋሉት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ አባል አቶ ዘመነ ኃይሉ እና በአማራ ክልል ምክር ቤት የብልጽግና ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ መልካሙ ተሾመ ከእስር ተለቀቁ። ሁለቱ የምክር ቤት አባላት ዛሬ ሐሙስ እኩለ ቀን ገደማ መፈታታቸውን አቶ ዘመነ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። 

አቶ ዘመነ እና አቶ መልካሙ ከመስሪያ ቤታቸው በጸጥታ ኃይሎች የተወሰዱት ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ መስከረም 21፤ 2017 ነበር። የፓርላማ አባሉ በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት አንድ ቀን አስቀድሞ፤ በሚኖሩበት ቀበሌ ያሉ ኃላፊ እና ሰራተኛ ወደ ቤታቸው በመምጣት አድራሻቸውን እና በመታወቂያቸው ያሉ መረጃዎችን አጣርተው መሄዳቸውን ተናግረዋል። 

ይህ የተደረገበት ምክንያት ለምን እንደሆነ ለቀበሌ ሰራተኞቹ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር አቶ ዘመነ ገልጸዋል። በባህር ዳር ከተማ የአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ የጠይማ ቀበሌ ኃላፊ “አንዳንድ ነገር ማጣራት ፈልገን ነው። ስንፈልግ እንደውላለን” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸውም አብራርተዋል። 

🔴 ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14275/

@EthiopiaInsiderNews

Ethiopia Insider

02 Oct, 17:15


የአብን የፓርላማ አባል እና የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ምክር ቤት ተመራጭ ታሰሩ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ አባል አቶ ዘመነ ኃይሉ እና በአማራ ክልል ምክር ቤት የብልጽግና ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ መልካሙ ተሾመ በትላንትናው ዕለት በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ቤተሰቦቻቸው እና ባልደረቦቻቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። ሁለቱ የምክር ቤት አባላት በአሁኑ ወቅት በባህር ዳር ከተማ በሚገኘው ዘጠነኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙም ተናግረዋል።

አቶ ዘመኑ በሰኔ 2013 ዓ.ም በተካሄደው ሀገር አቀፍ ምርጫ፤ በጢስ አባይ ዘንዘልማ ምርጫ ክልል ተቃዋሚ ፓርቲ የሆነውን አብንን በመወከል ለፓርላማ የተመረጡ ናቸው። በባህር ዳር ከተማ በሚገኘው የአማራ መልሶ መቋቋም እና ልማት ድርጅት (አመልድ) የሚሰሩት አቶ ዘመኑ፤ ከመስሪያ ቤታቸው በጸጥታ ኃይሎች የተወሰዱት ትላንት ማክሰኞ መስከረም 21፤ 2017  እኩለ ቀን ገደማ መሆኑን አንድ የቤተሰባቸው አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።  

የፓርላማ አባሉ ከመታሰራቸው ግማሽ ሰዓት አስቀድሞ እርሳቸው በሌሉበት በመኖሪያ ቤታቸው ፍተሻ ተካሄዶ እንደነበር እኚሁ የቤተሰብ አባል አመልክተዋል። ፍተሻውን ያካሄዱት “የመከላከያ ኃይሎች፣ የአማራ ክልል አድማ በታኝ አባላት እና ሚሊሺያዎች” እንደነበሩ የገለጹት የቤተሰብ አባሉ፤ በወቅቱ የፍርድ ቤት የብርበራ ትዕዛዝ አለመያዛቸውንም አብራርተዋል።

ለዝርዝሩ፦ https://ethiopiainsider.com/2024/14264/

@EthiopiaInsiderNews