Tsegaye Demeke - Lawyer @consultancy2012 Channel on Telegram

Tsegaye Demeke - Lawyer

@consultancy2012


Legal Service

Tsegaye Demeke - Lawyer (English)

Are you in need of legal advice from a trusted professional? Look no further than the Telegram channel 'Tsegaye Demeke - Lawyer' run by the esteemed lawyer himself. Tsegaye Demeke is well-known for his expertise in various areas of law and has been offering top-notch legal services to clients for years. In this channel, you will find valuable resources, updates on legal matters, and the opportunity to ask questions directly to Tsegaye Demeke. Whether you are dealing with a personal injury case, need help with family law matters, or require assistance with business contracts, Tsegaye Demeke is here to provide you with the guidance you need. Tsegaye Demeke's dedication to his clients and passion for the law shines through in every interaction. His commitment to providing accurate, timely, and reliable legal advice has earned him a stellar reputation in the legal community. By joining this channel, you will have access to a wealth of knowledge and experience that can help you navigate even the most complex legal issues. Don't let legal challenges overwhelm you. With Tsegaye Demeke by your side, you can rest assured that you are in good hands. Join the 'Tsegaye Demeke - Lawyer' Telegram channel today and take the first step towards resolving your legal concerns with confidence.

Tsegaye Demeke - Lawyer

19 May, 17:22


https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=pfbid02Kz6juaTQEmpQirTKnbY6nb4uYfsLxDSSLTNdbFfFL1ZhQZWrbZCywE6Bsquiypk5l&id=100069902955141&mibextid=ZbWKwL

Tsegaye Demeke - Lawyer

20 Apr, 13:43


የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ሥነ -ሥርዓት መመሪያ ቁጥር 17-2015.pdf

Tsegaye Demeke - Lawyer

06 Feb, 19:51


ለ) የኣቀራረቡ ፎርም ሲታይ ደግሞ በቁ.130 (1) ወይም (2) መሰረት የሚቀርበው መቃወሚያም ሆነ ዓቃቤ ሕጉ ለመቃወሚያው የሚሰጠው መልስ ሁሉ በቃል መቅረብ እንዳለበት ከቁ.131 (1) መረዳት ይቻላል፡፡ ተደጋጋሚ ስልጠናዎች እየተሰጡ ኣሁን ኣሁን እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም በተግባር ሲሰራበት የነበረና ኣሁንም ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል ብሎ በኣስተማማኝ መናገር የማይቻለው፤ መቃወሚያ ለማቅረብ ጊዜ መስጠት ፣ መቃወሚያው በፅሑፍ ማቅረብ ፣ ዓ/ሕግ የመቃወሚያው ግልባጭ እንዲደርሰው ማድረግ ፣ ዓ/ሕግ በሚሰጠው ቀነ ቀጠሮ መልሱ በፅሑፍ ያቀርባል ፣ ተከሳሹ በበኩሉ የመልስ መልስ በፅሑፍ ለማቅረብ ጊዜ ይሰጠዋል ፣ በመጨረሻ ፍ/ቤቱ የተከሳሽ መቃወሚያና የዓ/ሕግ መልስ ከሕጉ ጋር ኣገናዝቦ ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ይሰጣል፤ ምናልባት ምርመራው ያላለቀ ከሆነ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠት እንደተጠበቀ ሆኖ ፍ/ቤቱ ብይን ይሰጣል፡፡ ይህ የተንዛዛ ኣካሄድ ሕጉ ከሚያዘው ውጭ መሆኑን ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡

ሐ) ከመቃወሚያ ጋር ተያይዞ ሌላ መታየት ያለበት ነጥብ በመቃወሚያነት መቅረብ ያለበት በወ/መ/ሕ/ስ/ስ/ቁ.130 ላይ ከተዘተዘሩት ምክንያቶች ሲገኝ ብቻ ነው ወይስ ከዚያ ውጭ የሆኑ ምክንያቶች ሲገኙም ማቅረብ ይፈቀደል የሚለው ነው፡፡ በዚህ ዙርያ ሁለት ኣስተሳሰቦች ይራመዳሉ፡፡ በአንድ በኩል በወ/መ/ሕ/ስ/ስ/ቁ.130 ላይ ባይሸፈንም የክሱ መሰማት ሂደት እንዳይቀጥል የሚያደርጉ ሌሎቸ ምክንያቶች በተገኙ ጊዜም ተከሳሽ እንዲያነሳ ሊፈቀድለት ይገባል የሚሉ ኣሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቁ.130 ሌላ የመቃወሚያ ነጥብ በማይጨምር ሁኔታ (exclusively) ዘርዝሮ ያስቀመጠ በመሆኑ ከዚያ ውጭ የሚቀር ተቃውሞ ተቀባይነት ሊያገኝ ኣይገባም የሚል ሓሳብ የሚያራምዱ አሉ ብቻ ሳይሆን ኣብዛኛው ጊዜ በተግባር የሚሰራበትም ይህ ኣቋም ነው ፡፡ እንደ የሞጁሉ ኣዘጋጅ እምነትም በወ/መ/ሕ/ስ/ስ/ቁ. 130 ስር የማይሸፈን የተቃውሞ ነጥብ በሚነሳበት ጊዜ ተቀባይነት ሊያገኝ ኣይገባውም፤ ምክንያቱም በዛ ስር ያልተጠቀሰ ነጥብ በማያካትት እና በተሟላ ሁኔታ (exclusively and exhaustively) የተቀረፀ ነው፡፡

2. መቃወሚያውን ስለመመርመርና ስለመወሰን

በቁ. 13. (2) መሰረት የሚቀርበውን ማንኛውንም መቃወሚያ ፍርድ ቤቱ በመዝገቡ ከፃፈ በላ ዓ/ሕጉ መልስ እንዳለው ይጠይቃል፡፡ የቀረበውን መቃወሚያ ሕግን በመጥቀስ ለመወሰን የሚቻል ከሆነ ወይም ዓ/ሕጉ መቃወሚያውን ካልተቃወመ ፍ/ቤቱ ወድያው ይወስናል (ቁ. 131 (1)) ፡፡ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ለማጣራት ማስረጃ መቅረቡ ኣስፈላጊ ሆኖ ካገኘውና ማስረጃ ሳይቀርብ ወድያው ውሳኔ (ብይን) መስጠት የማይቻል በሆነ ጊዜ ኣስፈላጊው ማስረጃ እንዲቀርብ ማዘዝ ይችላል (ቁ. 131 (3)) ፡፡ የተፈለገው ማስረጃ አስቀርቦ ከመረመረ በላ ፍ/ቤቱ ወዲያው ውሳኔ መስጠት እንዳለበት ቁጥር 131 (4) ይደነግጋል፡፡

ፍርድ ቤቱ በመቃወሚያው ላይ የሚሰጠው ውሳኔ /ብይን/ እንደየ መቃወሚያው ዓይነት ሊለያይ ይችላል፡፡ ይኸዉም፡-

ሀ) የቀረበው መቃወሚያ የሕግ ድጋፍ የሌለው ከሆነ ወይም በማስጃ ካልተደገፈ መቃወሚያውን ውድቅ ያደርጋል ፣
ለ) በቁ. 130/ 2/ለ/፣ /ሐ/፣ ወይም/ሰ/ መሰረት የቀረበው መቃወሚያ ተቀባይነት ካገኘ ክሱን ዘግቶ ተከሳሹን ያሰናብታል ፣
ሐ) በቁ.130/2/ሀ/ መሰረት የቀረበ መቃወሚያ ከሆነ ጉዳዩ በተጀመረበት ፍ/ቤት እንዲቀጥል በማዘዝ መዝገቡን ይዘጋል ፣
መ) በቁ. 130(2) (መ) መሰረት የቀረበው መቃወሚያ ተቀባይነት ካገኘ ክሱ ተነጥሎ እንዲታይ ያዝዛል ፣
ሠ) በቁ. 130 /2/ሠ/ የቀረበ መቃወሚያ ከሆነ ኣስፈላጊው ፈቃድ እስኪሰጥ መዝገቡን ለጊዜው ይዘጋዋል ፣
ረ) በቁ. 130/2/ረ/ የቀረበ ከሆነ ደግሞ ኣስቀድሞ መፈፀም ያለበት ስርዓት እስኪፈፀም መዝገቡን ለጊዜው ይዘጋዋል፡፡

ከዚህ በላይ በፊደል “ለ” የተጠቀሰውን እንዳለ ሆኖ ተከሳሹ ሙሉ በሙሉ ሃላፊ ባለመሆኑ ክሱ በተዘጋ ጊዜ የተከሳሹ ሁኔታ በፀጥታ ወይም በህዝብ ሰላማዊ ኑሮ ላይ ሁከት ወይም ኣደጋ የሚያደርስ መስሎ ከታየው ተከሳሹ ተገቢ በሆነ ስፍራ ወይም ሕክምና በሚያገኝበት ቦታ ተወስኖ እንዲቀመጥ ፍ/ቤቱ ያዝዛል ( የወ/መ/ሕ/ስ/ስ/ቁ. 208 እና የወ/ሕግ ዓንቀፅ 130 እስከ 132 ) ፡፡
©®
#Join_our_telegram_channel
https://t.me/Consultancy2012
Call us for #Legal_Service
©Tsegaye Demeke - Lawyer

Tsegaye Demeke - Lawyer

06 Feb, 19:51


በወንጀል ክርክር የመጀመርያ ደረጃ መቃወሚያ አቀራረብና በፍ/ቤቱ የሚሰጥ ብይን/ትእዛዝ
=========================
1. የመጀመርያ መቃወሚያ

ተከሳሹ ማንነቱ ካረጋገጠ በላ ፍ/ቤቱ ክሱን ለተከሳሹ ያነብለታል፡፡ ክሱ ግልፅ ስለመሆኑም ይጠይቀዋል፡፡ ተከሳሹ ክሱ ግልፅ መሆኑን ካረጋገጠ በላ የመጀመሪያ መቃወሚያ ካለው ይጠይቃዋል፡፡ የመጀመርያ መቃወሚያ ያለው መሆኑን ኣለመሆኑን ሳያረጋገጥ ፍ/ቤቱ የእምነት ክህደት ቃል ወደ መቀበል መሄድ የለበትም፡፡

በተከሳሹ ሊቀርብ የሚችል መቃወሚያ በሁለት መልኩ ሊታይ ይችልል፡፡ ኣንዳኛ በቁ.130 (1) እንደተመለከተው ተከሳሹ በክሱ ማመልከቻ ፎርም ወይም ይዘት ላይ የሚቀርብ መቃወሚያ ነው፡፡ይህ ዓይነቱ መቃወሚያ በወ/መ/ሕ/ስ/ስ/ቁ.111 እና 112 የተዘረዘሩትን ነገሮች የሚመለከት ነው፡፡

(1) በቁ. 111 ላይ የተመለከቱት ነገሮች ስናይ፤ ማንኛውም የክስ ማመልከቻ፡-

ቀንና ዓመተ ምህረት የተፃፈበትና የተፈረመበት ፣
የተከሳሹ ስም የያዘ ፣
ተከሳሹ የተከሰሰበት እና የወንጀሉ መሰረታዊ ነገር ያካተተ ፣
ወንጀሉ የተፈፀመበት ጊዜና ስፍራ ያመላከተ ፣
የተበደለው ሰው ስም ወይም ወንጀሉ የተፈፀመበት ንብረት (ተገቢ በሆነ ጊዜ) የሚያመለክት፣
ተከሳሹ ወንጀሉን በመፈፀም ተላልፏል የተባለበት የሕግ ዓንቀፅ የያዘ መሆነ አለበት፡፡

(2) በቁ.112 የተመለከተው ደግሞ ተከሳሹ የተከሰሰበትን ወንጀል ለይቶ ኣውቆ መልስ ለመስጠት እንዲችል እያንዳንዱ ክስ ወንጀሉንና ሆኔታውን በዝርዝር መግለፅ እንዳለበት ነው፡፡

ስለዚህ በቁ.111 ወይም 112 ላይ ከተመለከቱት ሁኔታዎች (ነገሮች) ኣንዳንዶቹ በክሱ ማመልከቻ ላይ ያልተካተቱ ሆኖው ያገኛቸው እንደሆነ ተከሳሹ በመቃወሚያ መልክ ሊያነሳቸው እንዲሚችል ነው፡፡

ሁለተኛውና በተግባርም በተደጋጋሚ ሲነሳ የሚስተዋለው መቃወሚያ በቁ.130 (2) ላይ የተደነገገውን ነው፡፡ በዚህ ንኡስ ዓንቀፅ ስር በመቃወሚያነት ሊነሱ የሚችሉ በርከት ያሉ ምክንያቶች ተዘርዝረው የሚገኙ ሲሆን፤ ኣብዛኛዎቹ የመቃወሚያ ነጥቦች በተከሳሹ ወይም በጠበቃው ብቻ ሊነሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ በቁ.130(2) (ሐ) መሰረት የይርጋ ጊዜን ኣስመልክቶ የሚቀርብ ተቃውሞ ግን ተከሳሹ ባያነሳወም ዓቃቤ ሕጉ ሊያነሳው ይችላላ ወይም ፍ/ቤቱ በራሱ ውሳኔ ክሱን መዝጋት ኣለበት (የወ/ሕግ ዓንቀፅ 216 (2)) ፍ/ቤቱ ሌላ ማድረግ ያለበት የተከሳሹ ፍፁም ወይም ከፊል ሃላፊነት ኣጠራጣሪ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ሁሉ ተከሳሹ ተቃውሞ ባያቀርብም ስለዚሁ ነገር ልዩ እውቀት ያለውን የአዋቂ ኣሳብ መጠየቅ ነው፡፡ ቢያስፈልግም በተከሳሹ ጠባይ ፣ ባለፈ ህይወት ታሪኩና በሁኔታዎቹ ላይ ምርመራ እንዲደረግ ትዝዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡

በተለይ ተከሳሹ የኣእምሮ በሽታ ያለበት ወይም በሚጥል በሽታ የሚታወክ ለመሆኑ፤ ወይም መስማትና መናገር የሚሳነው ለመሆኑ ወይም ኣእምሮን በሚያደነዝዝ ነገር ወይም በመጠጥ አዘዉታሪነት በሽታ የተለከፈ ለመሆኑ የሚያመለክቱ ሁኔታዎች በተገኙ ጊዜ ፍ/በቱ ለዚሁ ልዩ እውቀት ያለውን ሰው ኣሳብ የመጠቅ ግዴታ ኣለበት ፡፡
(የወ/ሕግ ዓንቀፅ 51)

በመቃወሚያነት መቅረብ የሚችል ምን እንደሆነና መቃወሚያው ማንሳት ያለበት ማን እንደሆነ ካየን ዘንድ የሚቀርብበት ጊዜ መቼ ነው? የኣቀራረቡ ፎርምስ ምን መሆን ኣለበት የሚለውን ማየት ኣስፈላጊነቱ ኣጠያያቂ ኣይደለም፡፡

ተከሳሹ መቃወሚያ ካለው ማቅረብ ያለበት ክሱ ከተነበበለት በላ መሆኑን ከላይ ተገልፆዋል፡፡ ክሱ ከተነበበለት በላ ብቻ ሳይሆን መቃወሚያ ካለው ወድያው ማቅረብ አለበት፡፡ ይህ ኣባባል ታሳቢ የሚያደርገው ተከሳሹ ክሱ ከሚሰማበት ቀን ኣስቀድሞ እንዲደርሰው ስለሚደረግ ኣንብቦ ሊነሳ የሚችል መቃወሚያ ለማቅረብ ተዘጋጅቶ ይመጣል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው፡፡ ክሱን ወዲያው ካልተቃወመ መቃወሚያውን በላ ማንሳት እንደማይችልም በመርህ ደረጃ በስነ ስርዓት ሕጉ ተደንግጓል (ቁ.130 (3)) ፡፡ ሆኖም ይህ ንኦስ ቁጥር መርህ ብቻ ሳይሆን የመርሁን ልዩ ሁኔታም ደንግጓል፡፡ ይኸዉም፤

“… ፍርድ ቤቱ ሲጠይቀው ተከሳሹ የክሱን ማመልከቻ ወድያው ካልተቃወመ በቀር ቆይቶ እንዲህ ያለውን መቃወሚያ ነገሩ በሚሰማበት በሌላ ጊዜ ሊያነሳ ኣይችልም፡፡ ስለሆነም መቃወም የሚችለው መቃወሚያው የሚፀና ፍርድ ከመስጠት የሚያግድ በሆነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡” የሚል ነው፡፡

እዚህ ላይ መነሳት የሚገባው ጥያቄ “የሚፀና ፍርድ ከመስጠት የሚያግድ” እና ዘግይተውም ቢሆን ሊቀርቡ የሚችሉ መቃወሚያዎች የተኞቹ ናቸው? የሚል ነው፡፡ ለዚህ ጥያቂ መልስ ሊሆኑ የሚችሉ ሶስት ምሳሌዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡
ቁ.130 (2) (ለ) ተከሳሹ በዚሁ ክስ ከዚህ ቀደም ተከሶ ነፃ የወጣ ወይም የጥፋተኝነት ውሳኔ የተሰጠበት መሆኑ ወይም
ቁ.130 (2) (ሐ) ክስ የቀረበበት ወንጀል በይርጋ ሕግ የታገደ ወይም ምሕረት ወይም የኣዋጅ ምሕረት (ይቅርታ) የተደረገለት መሆኑን ወይም
ቁ.130 (2) (ሰ) ለፈፀማቸው ተግባሮች ሃላፊ ያለመሆኑን ባመለከተ ጊዜ ነው፡፡

የመጀመሪያው ምሳሌ ብንመለከት በስነ ስርዓት ሕጉ ብቻ የተቀመጠ ሳይሆን በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት ዓንቀፅ 23 ላይም “ማንኛዉም ሰው በወንጀል ሕግና ስነ ስርዓት መሰረት ተከሶ የመጨረሻ በሆነ ውሰኔ ጥፋተኛነቱ በተረጋገጠበት ወይም በነፃ በተለቀቀበት ወንጀል እንደገና ኣይከሰስም ወይም ኣይቀጣም” በሚል መልኩ ተገልፆ ይገኛል፡፡ በሁለተኛው ምሳሌ የተጠቀሰ ይቅርታን በተመለከተም ሕገ መንግስተዊ እውቅና ያገኘ ነው (ዓንቀፅ 71 (7)) ፡፡ እንዲሁም የይርጋ ጉዳይ በፍርድ ቤት ሳይቀር መነሳት ያለበት መቃወሚያ በመሆኑና ሃላፊ ያለመሆን ጥያቄም ኣስገዳጅ ድንጋጌ ሆኖ በወንጀል ሕግ የሰፈረ በመሆኑ ክሱ እንደተነበበ ወድያው ባይቀርቡም የሚፀና ፍርድ ከመስጠት የሚያግዱ በመሆናቸው በማንኛውም ጊዜ ሊነሱ የሚችሉ መቃወሚያዎች ናቸው፡፡

የሚፀና ፍርድ ከመስጠት የሚያግድ መቃወሚያ ሲገኝ ጊዜ ዘግይቶም ቢሆን ሊነሳ ይችላል ብሎ ሕጉ ሲያስቀምጥ ይህን ተከትሎ የሚነሳ ጥያቄ በስር ፍርድ ቤት ሳይነሳ ቀርቶ በይግባኝ ፍርድ ቤት ይግባኙ በሚታይበት ጊዜ ቢነሳስ ተቀባይነት ኣለው ወይ የሚል ይሆናል፡፡ እንግዲህ ይህ ልዩ ሁኔታ ከኣጠቃላይ የሕገ መንግስቱ መርሆዎችና ከቅጣት ዓላማ ኣንፃር መታየት ስላለበት በይግባኝ ፍርድ ቤት በሚሰማበት ወቅት የተነሳ መቃወሚያ ቢሆንም እንኳ ተቀባይነት ሊያገኝ ይገባል፡፡ የመዝገብ ቁጥሩ ማስታወስ ባልችልም በ1967 ዓ.ም አንድ ሰው የግድያ ወንጀል ፈፅሟል በሚል በትግራይ ክልል ምስራቃዊ ዞን ማእከላዊ /ከፍተኛ/ ፍርድ ቤት ክስ ቀርቦበት ጥፋተኛ ሆኖ ስለተገኘ በ25 ዓመት ፅኑ እስራት ይፈረድበታል፡፡ ፍርዱን በመቃወም ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባይ ያቀረበ ሲሆን የጠ/ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎትም መዝገቡ ከመረመረ በላ ክሱ በይርጋ ጊዜ የታገደ ሆኖ ስላገኘው በዞኑ ፍ/ቤት የተሰጠን የጥፋተኛነትና የቅጣት ውሳኔ ውድቅ በማድረግ ይግባይኝ ባይን በነፃ እንዲለቀቅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

Tsegaye Demeke - Lawyer

17 Jan, 16:31


ስለተከራካሪ ወገኖች አለመቅረብ
===========================
1. ክርክሩን ለመስማት በተቀጠረበት ቀን ግራ ቀኙ ወገኖች ካልቀረቡ የክስ መዝገቡ ይዘጋል (69(2)) ፡፡
2. በቁ.69 (2) መሠረት የክስ መዝገብ ከተዘጋ ከሳሹ በቁ.71 መሰረት ተገቢውን ዳኝነት (በድጋሚ) እና ኪሳራ ከፍሎ መዝገቡን ለማስከፈት ይችላል፡፡ ከሳሹ የቀረው በቂ በሆነ ምክንያት መሆኑን ካስረዳ ድጋሚ ዳኝነት ወይንም ኪሳራ ላይከፍል ይችላል፡፡
3. ከሳሽ ቀርቦ ተከሳሽ ካልቀረበ በቁ.70 መሠረት እንደ ሁኔታው ተከሳሹ በሌለበት እንዲቀጥል ወይም ሁለተኛ መጥሪያ እንዲላክ ማዘዝ ወይም ክርክሩን ለሌላ ቀጠሮ ማስተላለፍ ይቻላል፡፡
4. መጥሪያው ለተከሳሹ(ሾቹ) ያልደረሰው በከሳሽ ጥፋት ከሆነ ባልደረሳቸው ተከሳሾች ላይ የክስ መዝገቡ ይዘጋል (70(መ)፡፡
5. በቁ.70 (መ) መሠረት የክስ መዝገቡ ከተዘጋ ከሳሹ የቁ.71ን ሁኔታዎች በማሟላት መዝገቡ እንዲከፈትለት ለመጠየቅ ይችላል፡፡ ቁጥር 74 ለይግባኝ መዝገብ እንጂ ለቀጥታ ክስ ተፈፃሚ አይሆንም፡፡ (በ70 (መ) ለተዘጋ መዝገብ)፡፡
6. በቁ.70 (ሀ) መሠረት ተከሳሹ በሌለበት ጉዳዩ እንዲታይ ከታዘዘ በኃላ በሚቀጥለው ቀጠሮ ቀርቦ በመጀመሪያ ቀጠሮ ያልቀረበው በቂ በሆነ እክል መሆኑን ካስረዳ መከላከያውን አቅርቦ እንዲከራከር ሊፈቀድለት ይችላል (ቁ. 72) ፡፡
7. ተከሳሽ ቀርቦ ከሳሽ ባይቀርብ፤
ሀ. ተከሳሹ የተከሰሰበትን ነገር በሙሉ ወይም በከፊል ያመነ ከሆነ ፍርድ ቤቱ በታመነው መጠን ውሳኔ መስጠት ይችላል (ቁ.73)፡፡
ለ. ሆኖም ግን ተከሳሽ ስለመነ ብቻ ለከሳሹ የሚወሰን ሳይሆን ተከሳሹ ቢያምንም ከሳሽ ያቀረበው ክስ ሕጋዊ መሆኑንና ከሳሹ የጠየቀው ዳኝነት በሕግ የሚገባው መሆኑን ፍርድ ቤቱ ማጣራት አለበት፡፡
ሐ. ተከሳሹ ከካደ መዝገቡ ይዘጋል፡፡
መ. ሆኖም ከሳሹ በቁጥር 74 በተደነገገው መሠረት የተዘጋው መዝገብ እንዲከፈትለት መጠየቅ ይችላል፡፡ ጥያቄው ተቀባይነት የሚያገኘው ከሳሹ በመጀመሪያው ቀጠሮ የቀረው በቂ በሆነ ችግር መሆኑን ካስረዳ ነው፡፡ ፍረድ ቤቱ ጥያቄውን ከተቀበለ ስለኪሣራውና ስለማናቸውም ወጪ አከፋፈል ተስማሚ መስሎ የታየውን ውሳኔ ከሰጠ በኃላ የተዘጋው መዝገብ እንደገና ተከፍቶ ነገሩ እንዲቀጥል ትዕዛዝ ሰጥቶ ጉዳዩ የሚሰማበትን ቀጠሮ ይወስናል፡፡ ትዕዛዙ የሚሰጥው የከሳሹ ማመልከቻ ለመልስ ሰጪው ከደረሰው በኃላ ነው፡፡ (በቁጥር 73 መሠረት ለተዘጋ መዝገብ ቁጥር 69 ተፈፃሚ አይሆንም)፡፡
========================
ስለ ተከራካሪ ወገኖች መቅረብ
========================
1. ባለጉዳዩ እራሱ መቅረቡ ግዴታ አይደለም፡፡ ስለዚህ ባለጉዳዩ እራሱ መቅረብ ካልፈለገ ወይም ካልቻለ እንደሁኔታው ከቁጥር 57-64 በተደነገገው መሰረት ነገረ ፈጁ ፣ ወኪሉ ወይንም ጠበቃው ቀርቦ መከራከር ይችላል፡፡ እነዚህም በሕግ ወይም በውል የተሰጣቸው የውክልና ማስረጃ ሊኖራቸው ይገባል፡፡
2. ሆኖም ግን ውስን በሆኑና አስፈላጊ በሆኑ ሁኔታዎች ባለጉዳዩ እራሱ እንዲቀርብ ማዘዝ ይቻላል (ቁጥር 65፣ 68ና 241(3))፡፡
3. ባለጉዳዩ እራሱ እንዲቀርብ ታዞ በቂ ባልሆነ ምክንያት የቀረ እነደሆነ ወኪሉ ቢቀርብም ስለከሳሽ ወይም ተከሳሽ ያለማቅረብ የተነገሩት ድንጋጌዎች ተፈፃሚ ይሆናሉ (ቁጥር 77) ፡፡
4. ክርክሩን ለመስማት በተቀጠረው ቀን ባለጉዳዮች እራሳቸው ከቀረቡ ማንነታቸው ከተረጋገጠ ወኪሎቻቸው ከቀረቡ ደግሞ ሕጋዊ ውክልና እንዳላቸው ከተረጋገጠ በኃላ የክስ መሰማት ሂደት ይቀጥላል (ቁጥር 69(1)እና 241(1)) ፡፡

Tsegaye Demeke - Lawyer

23 Aug, 18:56


#ሀ) በሸሪዓና በፍትሐብሔር ህጉ መሰረታዊ የፖሊሲ ሐሳብ ልዩነቶች የሸሪዓም ሆነ የፍትሐብሔር ህጉ የውርስ ደንቦች መሰረታዊ ግብ የሟችን ውርስ ለወራሾቹ ማስተላለፍ ቢሆኑም በይዘታቸው አንድ አንድ መሰረታዊ ልዩነቶች አሏቸው፡፡ ይህም ልዩነት ሁለቱ ህግጋት መካከል የተካተቱ የፖሊሲ ሀሳብ ልዩነት ነፀብራቅ ነው፡፡ ከልዩነቶቹ ጥቂቶቹን ስንመለከት፣
የፍትሐብሔር ሕጉ የሟች ወራሾች ከሟች በሀይማኖትና በእምነት መለየታቸው የወራሽነት መብታቸውን አያሳጣቸውም፡፡ በሌላ በኩል ሟች ሙስሊም ከሆነ የእስልምና ኃይማኖት ተከታይ ያልሆኑ ወራሻቹ በሟች ውርስ እንዳይሳተፉ የሸሪዓ የውርስ ደንቦች ይከለክላሉ፡፡
የፍትሐብሔር ህጉ የሟች ሴትና ወንድ ወራሾች በጾታቸው ምክንያት የተለያየ ድርሻ እንዲወስዱ አያስገድድም፡፡ በእኩል የዝምድና ደረጃ እስካላቸው ድረስ እኩል ድርሻ ያገኛሉ፡፡ በሸሪዓ የሟች ሴት ልጆች ከሟች ውርስ አንድ ሶስተኛ የሚሰጣቸው ሲሆን ወንዶች ሁለት ሶስተኛ ይወስዳሉ፡፡
በሸሪዓ ሚስት ባሏን የመውረስ መብት ያላትና ከባሏ ውርስ አንድ ስምንተኛ የማግኘት መብት ያላት ሲሆን በፍትሐብሔር ህግ መሰረት ሚስት ባሏን የመውረስ መብት የላትም፡፡
የኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ህግ ሟች ከወራሾቹ አንዱን በኑዛዜ የመንቀል መብት ያለው መሆኑን የሚደነግግ ሲሆን በሸሪዓ ሟች ወራሾቹን በኑዛዜ የመንቀል መብት የለውም፡፡
በፍትሐብሔር ህጉ ሟች በኑዛዜ ንብረቱን ለሶስተኛ ወገን የማስተላለፍ መብት ያለው ሲሆን በሸሪዓ አንድ ሰው በኑዛዜ ሊያስተላልፍ የሚችለው የንብረቱን አንድ ሶስተኛ ብቻ ነው፡፡

#ለ) በአፈፃፀም የሚታዩ ችግሮች
በሁለቱ ህጐች መካከል ያሉት እነዚህ እና ሌሎች መሰረታዊ ልዩነቶች ሟች ሙስሊም በሆነ ጊዜና የሟች ወራሾች የሌላ ኃይማኖት ተከታይ ወይም ከጋብቻ ውጭ የተወለዱ በሆኑ ጊዜ ወይም ሟች በጠቅላላ የኑዛዜ ስጦታና ነጠላ የኑዛዜ ስጦታ ንብረቱን ባከፋፈለ ጊዜ በሸሪአ ተጠቃሚ የሚሆኑት ወራሾቹ በሸሪዓ መሠረት ውርሱ እንዲፈፀም ሌሎች ደግሞ በፍትሐብሔር ህጉ መሰረት ታይቶ እንዲወሰን በየበኩላቸው የወራሽነት ማረጋገጫ ለማግኘትና ውርሱን ለመካፈል ክስ የሚያቀርቡበትና የአንድ ሰው ውርስ ጎን በጎን በሁለት ፍርድ ቤቶች የሚታይበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት አንቀፅ 34 ንዑስ አንቀፅ 5 ይህንን ችግር ዘለቄታ መፍትሔ ለመስጠት ታስቦ የተደነገገ ሲሆን፣ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ይቻል ዘንድ የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን ለማጠናከር አዋጅ ቁጥር 188/1992 ታውጇል፡፡ በተለያዩ ክልሎችም የክልል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ማጠናከሪያ አዋጆች ታውጀዋል፡፡ እነዚህ የህግ ማዕቀፎች ከመውጣታቸው በፊት የነበሩ በርካታ ችግሮችን ለመፍታት እንዲረዱ የሚስተባበል ባይሆንም አሁንም ቢሆን፣
በህግ ማዕቀፎቹ ድንጋጌዎች ግልፅ አለመሆንና በአንድ አንድ ጉዳዮች ክፍተት ያለባቸው በመሆኑ የተነሳና
መደበኛው ፍርድ ቤት እና የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ህግን በመተርጎምና በማስፈፀም ሒደት የየራሳቸው ችግር ያለባቸው በመሆኑ
ሁለቱን የውርስ ህግጋት በማስፈፀም በኩል በርካታ ችግሮች እንደሚፈጠሩና ችግሮቹ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አልፈው የህገመንግስት አጣሪ ጉባኤና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመነጋገሪያ አጀንዳ እየሆኑ መሆኑን አንድ አንድ ጉዳዮችን አንስቶ ማየት ይቻላል፡፡


በአጠቃላይ በአገራችን እየተሰራባቸው ያሉ በርካታ ባህላዊና ኃይማኖታዊ የአወራረስ ሥርዓቶች ከፍትሐብሔር ህጉ የአወራረስ ደንቦች ጋር ጎን በጎን ሥራ ላይ በሚውሉበት ጊዜ የሚከሰቱትን ችግሮች መሰረታዊ ባህሪ ችግሮቹ የሚፈቱበትን የህግ አግባብ በመረዳት ለተግባራዊ እንቅስቃሴ ዝግጁ ለመሆን ስልጠናዎች በአካባቢያችን ያሉትን ባህላዊ ኃይማኖታዊ የአወራረስ ሥርዓቶች መሰረታዊ ደንቦች እና የአፈፃፀም ሥርዓት ላይ ስልጣኖቹ በየአካባቢያቸው የዳሰሳ ጥናት በማድረግ በጥናቱ ግኝት ላይ የጋራ ውይይት እንዲያደርጉ ማድረግ የላቀ ጠቀሜታ ስላለው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነጥብ ነው፡፡

በአሁኑ ግዜ በተጨባጭ ቢያንስ ሁለት ዓይነት የአወራረስ ስርአት (መደበኛና ሸሪዓ) በመኖሩ አንዳንድ ግዜ አንድ ጉዳይ በሁለቱም ስርአቶች የሚስተናገድበትና ግጭት የሚፈጠርበት ሁኔታ ይከሰታል። የሽሪዓ ፍርድ ቤቶችን ስልጣን የሚሰጠው አዋጅ ክፍተት ያለበት መሆኑን ከላይ ተመልክተናል። በመሆኑም ህጉ ዘርዘር ባለ ሁኔታ ተሻሽሎ ሊወጣ ይገባዋል። ህጉ እስኪሻሻል ግን የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ምንግዜም ግጭት ሊከሰት የሚችል መሆኑን በጠረጠሩ ጊዜ ጉዳዩን የማጣራትና በተከራካሪ ወገኖች መካከል ፈቃድ በሌለ ግዜ ጉዳዩን ወደ መደበኛው ፍርድ ቤት የመምራት ሃላፊነት ይኖርባቸዋል።

Tsegaye Demeke - Lawyer

23 Aug, 18:56


ስለውርስ ህግ በጠቅላላውና የአወራረስ ስርዓት በኢትዮጵያ
========================

1. ስለ ውርስ ህግ በጠቅላላው
በዓለማችን እየተሠራባቸው ያሉ ዘመናዊ የውርስ ህግጋት በመሠረታዊነት ሶስት አይነት የአወራረስ ሥርዓቶችን የሚዘረዝሩ የውርስ ደንቦችን የያዙ ናቸው፡፡ እነርሡም፣
የሟች ውርስ ያለኑዛዜ ለሟች የሥጋና የጋብቻ ዘመዶች የሚፈፀሙበትን የአወራረስ ሥርዓት በዝርዝር የሚደነግጉ፣ ደንቦችን የያዙ (Rules of Intestate Succession)
የሟች ውርስ በሟች ኑዛዜ መሠረት የሚፈፀምበትን ሥርዓት የሚደነግጉ ደንቦች የያዙ (Rules of testate Succession)
የሟች ውርስ በሟች በክፊል ኑዛዜና በከፊል ያለኑዛዜ የሚፈፀምበትን ደንቦች የያዙ (Rules of partially intestate and partially Testate secession) ናቸው፡፡
በአጠቃላይ አሁን እየተሠራባቸው ያሉ የውርስ ህግጋት የሟች የሚንቀሣቀሥ እና የማይንቀሣቀሥ ንብረት ገንዘብና ከሌሎች ሰዎች የሚሰበሰብ ብድር ወይም ተከፋይ ገንዘብ የአክስዮን ድርሻና ሌሎች በሟች መሞት ምክንያት የማይቋረጡ የሟች መብትና ግዴታዎች ለሟች ወራሾች ቀልጣፋና ውጤታማ በሆነ መንገድ የሚተላለፍበትን የአወራረስ ሥርዓት የሚደነግጉ ናቸው፡፡


2. የአወራረስ ሥርዓት በኢትዮጵያ

ስለ ኢትዮጵያ የአወራረስ ስርዓትና ህግ ስናነሳ በአሁኑ ጊዜ የሚታየው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት ፀድቆ ስራ ላይ ከዋለ በኋላ ያለውን የአወራረስ ስርዓት ነው፡፡
ህገ መንግስቱ የግል መብቶችን በተመለከተ የሚነሱ ክርክሮች በተከራካሪዎቹ ፈቃድ በባህላዊ ወይም ኃይማኖታዊ ፍርድ ቤት የመዳኘት መብትን በአንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ 5 ደንግጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የክልል ምክር ቤት በህገ መንግስቱ አንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ 5 መሠረት የሀይማኖት እና የባህል ፍርድ ቤቶችን ሊያቋቁሙ ወይም ዕውቅና ሊሰጡ እንደሚችሉ ከመደንገጉም በላይ ህገመንግስቱ ከመጽደቁ በፊት ዕውቅና አግኝተው ሲሰራባቸው የነበሩ የኃይማኖትና የባህል ፍርድ ቤቶች በህገመንግስቱ መሰረት በአንቀጽ 78 ንዑስ አንቀጽ 5 በግልጽ ደንግጓል፡፡ በዚህ መሰረት፣ የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤት በአዋጅ ቁጥር 188/1992 መሠረት ተጠናክሮ ስራውን የቀጠለ ሲሆን ክልሎችን የክልል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን የማጠናከሪያ አዋጆችን በማወጅ ስራቸውን እንዲቀጥሉ አድርገዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ስንመዝነው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት ፀድቆ ሥራ ላይ ከዋለበት ነሐሴ 1 ቀን 1987 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ባህላዊና ልማዳዊ የአወራረስ ደንቦች፣ ሀይማኖታዊ የአወራረስ ደንቦች ህገ መንግስታዊ ዕውቅናና ጥበቃ አግኝተው ከፍታብሔር ህጉ የውርስ ህግ ድንጋጌዎች ጐን በጐን እየተተገበሩ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ አሁን ያለው የአወራረስ ስርዓቶች ስንመለከት ሁለት መሠረታዊ እና ልዩ ባህሪያት ያሉት ነው፡፡
የመጀመሪያው በእኩል ደረጃ ህገመንግስታዊ ዕውቅናና ጥበቃ በተሰጣቸው፣ 1)ባሕላዊና ልማዳዊ የውርስ አወራረስ ደንቦች 2)ሀይማኖታዊ የውርስ አወራረስ ደንቦች እና 3) በፍታብሔር ህጉ የተመለከቱት የተለያዩ አይነት ባህሪ እና ውጤት ያላቸው የአወራረስ ሥርአቶች በአገሪቱ ውስጥ ተግባራዊ እየሆኑ መሆናቸው ሲሆን፣
ሁለተኛው በሟች የውርስ አወራረስ ሒደት ሥርዓት ሲፈፀም የሚነሱ ክርክሮች ተፈፃሚነት ያላቸውን የአወራረስ ደንቦች የመምረጥ መብት ሙሉ በሙሉ የተከራካሪዎች መሆኑ ነው፡፡

እዚህ ላይ መታየት ያለበት ከተከራካሪዎቹ አንደኛው በልማዳዊ ወይም ሀይማኖታዊ የአወራረስ ደንቦች መሰረት ለመዳኘት ፈቃደኛ ካልሆነ ጉዳዩ በፍታብሔር ህጉ የውርስ ህግ ድንጋጌዎች መሰረት የሚፈፀም መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡- ስለሆነም ዜጐች የፍታብሔር ህጉን የውርስ ደንቦች ተፈፃሚነት የሚያስቀሩት ጉዳዩ በባህላዊ ወይም ኃይማኖታዊ የአወራረስ ደንብ እንዲፈፀም ሙሉ በሙሉ ሲስማሙና ፈቃደኛ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡

የተለያየ አይነትና ባሕሪያት ውጤት ያላቸው የውርስ አወራረስ ደንቦች መኖራቸው ያለው ጠንካራና ደካማ ጐን
ከላይ እንደተገለፀው በአገሪቱ አንድ ወጥ የሆነ የአወራረስ ሥርዓት ኖሮ የማያውቅ ሲሆን አንድና ወጥነት ያለው የአወራረስ ሥርዓት ለመዘርጋት የተደረገው ሙከራም ተግባራዊ ውጤት አላስገኘም፡፡ ይህም በመሆኑና ህገመንግስቱ ባህልን፣ ሃይማኖትን መሰረት ለሚያደርጉ የአወራረስ ደንቦች ዕውቅናና ጥበቃ ሰጥቷል፡፡ ይህም ዜጐች በፈቃዳቸውና በፍላጎታቸው የህብረተሰባቸው ባህላዊ የውርስ ደንቦች ወይም ኃይማኖታዊ የውርስ ድንጋጌዎች መሰረት የሟች ውርስ የሚያስፈፅሙበት እድል የሚሰጥ በመሆኑ፣ ዜጐች የግል ጉዳያቸው በመረጡት መንገድ የመጠየቅና የመዳኘት መብታቸውን ያረጋግጣል፡፡ ይህም ሊመሰገን የሚገባው ጠንካራ ጎን እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል ከአንድ በላይ የሆኑ የውርስ አወራረስ ስርዓቶች በአንዲት አገር ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ሲሞከር የአንዱ የአወራረስ ሥርዓት ደንቦች ከሌላው የሚለያዩበት ሰፊ ሁኔታ ስለሚኖርና ከሚች ወራሾች መካከል የተወሰኑትን በአንደኛው የአወራረስ ስርዓት ሌሎቹ ደግሞ በሌላ የአወራረስ ሥርዓት መሰረት የሟች ውርስ እንዲፈፀም ለማድረግ የየበኩላቸውን ጥያቄ ስለሚያቀርቡና በሌሎች ምክንያቶች የሚፈጠረው የተለያዩ የውርስ ደንቦችና የአፈፃፀም ግጭት ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ተፈፃሚነት ያላቸው ባህላዊ የአወራረስ ሥርዓቶች ብዛታቸውን፣ ይዘታቸውን የሚያሳይ ወጥ ጥናት ባለመደረጉ በእርግጠኘነት ብዛታቸውን፣ ይዘታቸውንና የአፈፃፀም ሒደታቸውን ከሌሎች ኃይማኖታዊና የፍታብሔር ህግ የውርስ ድንጋጌዎች ጋር በማነፃፀር ለመግለጽ አይቻልም፡፡ ሆኖም የተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦች ጎሳዎችና ማህበረሰቦች የየራሳቸው ባህላዊ የውርስ አወራረስ ደንቦች እንዳላቸውና እነዚህም በይዘትም ሆነ በአፈፃፀም የተለያየ ይዘትና ባህሪ እንዳላቸው በተለያየ ጊዜ ከተደረጉ አጫጭር የዳሰሳ ጥናቶች ለመረዳት ይቻላል፡፡

ስለሆነም በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየሆኑ ባሉ የባህል አወራረስ ደንቦች መካከል ያለው ልዩነትና አንድነት እንደዚሁም እያንዳንዱ ባህላዊ የውርስ አወራረስ ሥርዓት እየተሰራባቸው ካሉት የፍትሐብሔር ህጉ እና የሸሪዓ የውርስ ድንጋጌዎች ያላቸውን አንድነት እና ልዩነት በንጽጽር ለማቅረብ አይቻልም፡፡ በአንጻሩ ጐን በጎን የሚተረጉሟቸው እና የሚያስፈጽሟቸው ፍርድ ቤቶች ተቋቁመው እየተሰራባቸው ባሉት የፍትሐብሔር ሕግ የውርስ ደንቦችና በሸሪዓ የውርስ ደንቦች መካከል ያለውን መሰረታዊ የይዘት ልዩነትም በአፈፃፀም ሒደት እየተከሰቱ ያሉ መሠረታዊ ችግሮች ማየት በአገራችን የተለያዩ ባህላዊ ኃይማኖታዊና የፍትሐብሔር ህግ የተደነገገውን የአወራረስ ሥርዓት ተግባራዊ በማድረግ ሒደት ጥንቃቄ ሊደረግባቸው የሚገቡ መሰረታዊ ጉዳዮች ለመረዳት ጠቀሜታ ስለሚኖረው በአጭሩ ማየት ይጠይቃል፡፡

የሸሪዓና የፍትሐብሔር የውርስ ደንቦች መካከል የሚታየው መሠረታዊ ልዩነትና በአፈፃፀም የሚታዩ ችግሮች

Tsegaye Demeke - Lawyer

23 Aug, 18:56


ባንኮችም የዋስትና ሰነድን ለደንበኞች በመስጠት የሚያገኙት ገቢ በወለድ መልክ ገንዘብን መቀበልንና የዋስትና ጊዜው ሲያልቅ የሚመለስ ገንዘብም በዋስትና ተጠቃሚው በኩል እንዲከፈል አይጠበቅም። በመሆኑም የዋስትና ሰነድ መጻፍ በተለምዶ የሚታወቀውን የአበዳሪና ተበዳሪ የብድር ግንኙነትን አይፈጥርም። ይልቁንም ባንኮቹ ለሚሰጡት የዋስትና ሰነድ የሚቀበሉት ተመጣጣኝ የሆነ ኮሚሽን ብቻ ነው። ይህ ሁኔታ ታዲያ በተለይ የዋስትና ሰነድ እንደ ብድር አገልግሎት የሚታይ አይደለም ለሚሉት ወገኖች እንደ አንድ መከራከሪያ ሀሳብ ይነሳል። ምክንያቱም የባንክ የብድር ግንኙነት የአበዳሪና የተበዳሪ ግንኙነትን ለመፍጠር አበዳሪው ለተበዳሪው በገንዘብ የሆነ ብድር የመስጠትንና ተበዳሪውም ይህንኑ የብድር ገንዘብ በዓይነትም ሆነ በጥሬው የመመለስ ግዴታን የሚጥል መሆኑ ግልጽ ነው።ይሁንና ግን የዋስትና ደብዳቤ ለዋስትና ተጠቃሚው ሲጻፍ ባንኮቹ የዋስትና ደብዳቤ እንዲጻፍለት የጠየቀውን ደንበኛቸው የገባውን ግዴታ እንዲፈጽም መተማመኛ ከመስጠት ባለፈ ለደንበኛቸው የሚሰጡት የብድር ገንዘብ የለም።

ሌላው መነሳት ያለበት ጉዳይ ባንኮች በሚያዘጋጂዋቸው የዋስትና ደብዳቤዎች ላይ የሚጠቀሱ የሰነዱን ይዘቶች የተመለከቱት ነጥቦቸ ናቸው። በተግባር በባንኮች የሚዘጋጁት የዋስትና ሰነዶች የተለያዩ ቢሆኑም የሰነዶቹ ይዘት ግን አንዳንድ የሕግ ክርክሮችን ሲያስነሱ ይታያሉ።የአንዳንድ የዋስትና ደብዳቤዎች ይዘቶች በተለይም ዋስትና ሰጪውን ተቋም ሳይቀር ባለገንዘቡ የዋስትና ሰጪው እና ወራሾቹ በጋራም ሆነ በተናጠል በደብዳቤው በተቀመጡት ግዴታዎች መሠረት ራሳቸውን ህጋዊ ግዴታዎች ውስጥ ገብተዋል፤ የዋስትና ቦንዱም ለተጠቀሰው የገንዘብ መጠን በቦንዱ ውስጥ በሰፈሩት ህጋዊ ስምምነቶች እና ድንጋጌዎች መሠረት ሆኖ ይህንን ቦንድ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሊቀርብበት የማይችል የሚያደርጉ ናቸው፤ ማንኛውም ድርጊት ወይም ሳይፈጸም የቀረ ነገር በመኖሩ ሳቢያ ኪሳራ የሚደርስ መሆኑን ዋስትና የተሰጠው ባለገንዘብ ከደረሰበት ይህንኑ በዋስትና ጊዜው ውስጥ ለዋሱ ማሳወቅ አለበት የሚሉና የመሳሰሉት ይገኙበታል። በመሠረቱ አንዳንዶቹ ግዴታዎች በልማድ የተጻፉ ከመሆናቸው ውጪ በተለይ የዋሱን ወራሾች ሁሉ ተጠያቂ የሚያደርጉት የዋስትና ግዴታዎች ባንኮችን በተመለከተ ሊፈጸሙ የሚችሉም ስላልሆኑ በአብዛኛው በሰነዶቹ ይዘት ላይም ጥንቃቄን ማድረግ ያስፈልጋል። የዋስትና ደብዳቤም በጊዜ ገደብ የተወሰነ ግዴታ ሲሆን ደብዳቤውም በግልጽ ዋስትና የተገባለትን የገንዘብ መጠን ማመልከት ይገባዋል።

እንደማጠቃለያም የዋስትና ውል ማለት ሁለት ሰዎች ባደረጉት የባለገንዘብነትና የባለእዳነት ግዴታ ግንኙነት ውስጥ ከእነዚህ ተዋዋዮች ውጪ የሆነ ሌላ ሦስተኛው ባለእዳው እዳውን በሙሉ ወይም በከፊል ያልተከፈለ መሆኑ ከተረጋገጠ ወይም ግዴታውን በውሉ በተመለከተው አኳኋን በአግባቡ ያልተወጣ ከሆነ እኔ በባለእዳው ስፍራና አቋም ሆኘ እዳውን እከፍላለሁ ወይም ግዴታውን እወጣለሁ ሲል ለባለገንዘቡ ማረጋገጫ የሚሰጥበት በሕግ አግባብ ከተረጋገጠ ከበስተጀርባው ለአፈጻጸሙ የሕግ ጥበቃ የሚያገኝ ውል ነው በማለት የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት ማብራሪያ ሰጥቷል። ይሁንና ግን የዋስትና ሰነዶች ከአገልግሎታቸው አንጻር በህጋችን ላይ ግልጽና ሰፊ ሽፋን የተሰጣቸው አይደሉም። በተለይም በንግድ ሕጉን ውስጥ እነዚህ ሰነዶች እንደ ብድር አገልግሎት የሚቆጠሩ መሆንና አለመሆናቸውን በሚገልጽ መልኩ እንዲሁም የተለያዩ ዓይነት የዋስትና ደብዳቤዎችን አገልግሎት እና በምን ሁኔታ ሊጻፉ እንደሚችሉ በሚገልጽ መንገድ የተቀመጠ ግልጽ ድንጋጌ ያስፈልገናል። በመሆኑም የንግድ ሕጉ የዋስትና ደብዳቤዎችን የተመለከተ ሰፊ የሕግ ሽፋን መስጠትና ማካተት ይጠበቅበታል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የዋስትና ሰነዶችን ልዩ ባህሪያትና በተግባር ያሉትን የባንኮችን አሰራሮች በመፈተሽ ዝርዝር የሕግ ድንጋጌ ማስቀመጡ አስፈላጊ ነው።
By Abyssinia Law

Tsegaye Demeke - Lawyer

23 Aug, 18:56


መሠረት የዋስትና ደብዳቤን ለማዘጋጀት በአብዛኛው የሚቀርበው የመያዣ ንብረት በመሆኑና የሰው ዋስትና በፍትሐብሔር ሕጉ በተቀመጠው መሠረት የዋስትና ደብዳቤ ለመጻፍ እንደመያዣ የማይቀርብ በመሆኑ በሰው ዋስትናና በሰነዶች ዋስትና መካከል መሠረታዊና ሰፊ ልዩነት እንዳለ መገንዘብ ያስፈልጋል ማለት ነው። በመሆኑም ይህ የዋስትና አገልግሎት በዋናነት ሰውን እንደዋስትና ወይም እንደ መያዣ ማቅረብን የሚመለከት አይደለም። ለዚህም ይመስላል የፍትሐብሔር ሕጉ ራሱ የሰው ዋስትናን እንደ አንድ የዋስትና ዓይነት በዘረዘረበት የሕጉ ድንጋጌዎች አሁን ባንኮች የሚጠቀሙባቸውን የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትና፣ የውል ማስከበሪያ ዋስትና፣ የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና ደብዳቤዎችንና ሌሎችንም የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን መሠረት አድርገው እና ለተለያዩ ዓላማ የሚውሉትን የዋስትና ዓይነቶችም ቢሆን ለመዘርዘር ያልቻለው።

በሀገራችን በተለይም እነዚህ የዋስትና ዓይነቶች በአለም አቀፍ ደረጃም በተገባር ላይ መዋል የጀመሩትና ይህ ልማድም ወደ ሀገራችን ገብቶ በባንኮች መተግበር የጀመረውም የንግድ ሕጉና የፍትሐብሔር ሕጉ ከወጡ በኋላ በመሆኑ የዋስትና ሰነዶን በተመለከተ የፍትሐብሔር ሕጉን መሠረት በማድረግ የሚሰጡ የፍርድ ቤት ውሳኔዎችም ሆነ የሕግ ትርጉሞች በመሠረታዊነት እነዚህ በባንኮች በአገልግሎት ላይ የሚውሉ የዋስትና ሰነድ ዓይነቶችን የማይወክሉ የሚሆኑት። በአለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን የዋስትና ሰነዶችን በተለይም (Independent Letter of Guarantees) በተመለከተ በኮድ መልክ የወጣውና በአብዛኛው ሀገሮችና ተቋማት አገልግሎት ላይ የሚውለው URDG 458 የሚባለው ሰነድ ሲሆን ሰነዱም ከጥቂት አመታት በኋላ URDG 758 በሚል ተሻሻሎ ቀርቧል። ስለዚህም የዋስትና ሰነዶች ታሪካዊ አመጣጥና በተግባር አገልግሎት ላይ መዋል የጀመሩትም የኢትዮጵያ የፍትሐብሔርና የንግድ ሕግ ከወጡ በኋላ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ 47004 በተሰጠ አስገዳጅ የሕግ ውሳኔ መሠረት የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትና ውል በፍትሐብሔር ሕግ ድንጋጌዎች መሠረት የሚገዛ መሆኑን ገልጿል። ሰበር ችሎቱ በርካታ ትንታኔዎችን በጉዳዩ ላይ ለመስጠት የተጓዘበት ርቀት ጥሩ የሚባል ቢሆንም በመሠረታዊነት ግን ውሳኔው ሁሉንም የሕግ ባለሙያ ሊያስማማ የሚችል አይመስልም። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ በውሳኔው ላይ የዋስትና ሰነድን የዋስትና ውል ሲል የገለጸው ሲሆን ከላይ በተመለከትነው መሠረት ግን ሰነዱ በባንኮች ተዘጋጅቶ የዋስትና ተጠቃሚውም ሆነ አበዳሪው በዚህ ሰነድ ላይ ምንም ዓይነት የስምምነት ፊርማ ሳያስቀምጡ፤ እንደሌሎች ውሎችም ምስክሮች መኖርም ሆነ መፈረም ሳያስፈልጋቸው በባንኮቹ ብቻ ተፈርመው ለዋስትና ተጠቃሚው የሚሰጡ ሰነዶች ናቸው።

በመሆኑም በዚህ ሰነድ ላይ እንደውል ለመቆጠር ቢያንስ ሁለት ወገኖች በውሉ ስለመስማማታቸው በጽሑፍ በሆነ ሰነድ ላይ መፈረምና ምስክሮችም ስማቸውንና ፊርማቸውን ማስቀመጥ እንደሚገባቸው የውል ሕግ እያስገደደ እነዚህ ነጥቦች ባልተሟሉበት ሁኔታ ሰነዱን ውል ማለት መሠረታዊ የውል መርህን የሚጥስ ነው። ሌላው የሰበር ትንታኔው የዋስትና ውል ብሎ የጠራውን ሰነድ በፍትሐብሔር ሕጋችን አንቀጽ 1920 እስከ 1951 የተቀመጠ መሆኑን በመጥቀስ የዋስትና ውል በችሮታ ላይ የተመሠረተ ግዴታ መሆኑን በመግለጽ ዋሱ ዋስ በመሆኑ የሚያገኘው ጥቅም የሌለ በመሆኑ አንድ ሰው ባለእዳው ሳይጠይቅ ወይም ሳያውቅ ዋስ መሆን እንደሚችል መመልከቱ ግንኙነቱ የግድ ጥቅም ላይ ያልተመሠረተ መሆኑን የሚያሳይ ነው በሚል ያስቀመጠው ነው። (የፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 921ን ይመልከቱ) ይህ ትንታኔም በአንድ በኩል የሰው ዋስትናን ከሰነድ ዋስትና ጋር ለማመሳሰል የተደረገ ይመስላል። ይሁንና ስለሰው ዋስትና የተቀመጠው ይህ ትንታኔ በምንም መልኩ የሰነድ ዋስትናን የሚወክል አይደለም። ምክንያቱ ደግሞ በባንኮችም ሆነ በኢንሹራንስ ድርጅቶች የሚሰጡ የሰነድ ዋስትናዎች እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በችሮታ የሚሰጡ ሳይሆን በተለይ ባንኮች የሰነድ ዋስትናዎችን ለመጻፍ ከተጠቃሚው ጋር የንብረት ወይም የገንዘብ መያዣ ውል የሚገቡ ሲሆን የዋስትና ሰነዶቹንም ለተጠቃሚው የሚጽፉት የዋሰትና መጠኑን መሠረት አድርገው በሚቀበሉት የገንዘብ ኮሚሽን እንጂ በችሮታ አለመሆኑ ነው።

ችሮታም የሰው ዋስትና መሠረታዊ መለያ ባህሪ እንጂ ለሰነዶች ዋስትና የሚሰራ ጉዳይ አይደለም። የሰነድ ዋስትና ለመጻፍም ባለእዳው ሳያውቅ መጻፍ የማይቻል ሲሆን የሰነድ ዋስትናን ለመጻፍ የግዴታ ባለእዳው በአካል ቀርቦ ለባንኩ ማመልቻ ማስገባትና ለሰነዱ መጻፍ መሠረት የሆነውን የመያዣ ውል መዋዋል ግድ የሚል ነው። በመሆኑም የሰነድ ዋስትና ለመስጠት የባለእዳው መቅረብና ስለዋስትናው ማወቅ የግድ ነው። በሌላ በኩል ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የዋስትና ሰነድ የፍትሐብሔር ሕጉ ከወጣ በኋላ የመጣ ጽንሰ ሀሳብ በመሆኑ ይህንን ግዴታ ወደፍትሐብሔር ሕጉ ወስደን ትርጉም ለመስጠት መሞከሩ አግባብ ያልሆነ መሆኑ ነው። በመሆኑም የሰበር ችሎቱ የሰነድ ዋስትናን ከሰው ዋስትና ጋር ለማዛመድ የሞከረበት ትንታኔው ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ተቀባይነት ያለው አይመስልም።ይህ የሚያመለክተንም በመሠረቱ እነዚህ የዋስትና ዓይነቶች በልማድ ባንኮች በተግባር በሰፊው ይጠቀሙባቸው እንጂ አገልግሎታቸው ተለይቶ እንዴት እንደሚዘጋጁ እና በምን ሕግ እንደሚገዙም የሚገልጽ ግልጽ የሕግ ደንጋጌ አሁን ባሉት የንግድ ሕግም ሆነ በፍትሐብሔር ሕግ ውስጥ የሌለ መሆኑን ነው።

የዋስትና ሰነዶች በሁኔታ ላይ የተመሠረቱና በሁኔታ ላይ ያልተመሠረቱ ሊሆኑ ይችላሉ። በሁኔታ ላይ የተመሠረተ ዋስትና የሚባለው ዋሱ ባለዕዳው ግዴታውን በማንኛውም ሁኔታ ሳይወጣ ቢቀር ግዴታውን ያልተወጣው በምንም ምክንያት ይሁን ምክንያቱን መጠየቅ ሳይጠበቅበት የተባለው ግዴታ እንዳልተፈጸመ በአበዳሪው ሲገለጽለት በዋስትና ደብዳቤው የጊዜ ገደብ ውስጥ መሆኑን በማረጋገጥ የሚከፈሉ የዋስትና ደብዳቤዎች ናቸው። በሁኔታ ላይ የተመሠረቱ የዋስትና ደብዳቤዎች ደግሞ ዋሱ ለአበዳሪው የዋስትና ግዴታውን ለመወጣት እንዲያስችለው ባለአዳው (ዋስትና የተገባለት ሰው) ግዴታውን ያልተወጣው በማን ጥፋት ነው የሚለውን ካረጋገጠ በኋላ እና ጥፋቱ የባለእዳው መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ የሚወጣው ግዴታ ነው።

ባንኮች በአሁኑ ወቅት እየሰጡዋቸው ካሉ የዋስትና ሰነድ ዓይነቶች ውስጥ የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትና፣ የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና፣ የውል ማስከበሪያ ዋስትና፣ የቅድመ ክፍያ ዋስትና፣ የአቅራቢነት ዋስትና ሰነዶች (ደብዳቤዎች) ናቸው። እነዚህ የዋስትና ሰነዶች በአብዛኛው ባንኮች ለደንበኞች የሚያዘጋጁላቸው ደንበኞች ለባንኮች በሚያቀርቡት የመያዣ ንብረቶች መሠረት የመያዣ ውል ከተዋዋሉ በኋላ ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን የዋስትና ደብዳቤ እንዲጻፍለት የጠየቀ የባንክ ደንበኛን ባንኮቹ ተመጣጣኝ የሆነ ገንዘብ በዝግ ሂሳብ እንዲያስቀምጡ በማድረግ በምትኩ ግዴታቸውን ለመወጣት መተማመኛ የሚሆኑ ሰነዶችን ይሰጣሉ። ይህ ዓይነቱ ዋስትና የገንዘብ ዋስትና ይባላል። በብሔራዊ ባንክ መመሪያ ቁጥር sib/24/2004 መሠረት የገንዘብ ዋስትና ሰነድ አንድ ሰው አንድን የተለየና የተወሰነ ሥራ ለሌላ ሰው ለመሥራት ግዴታ ከገባ ይኸው ሰው በውሉ መሠረት የገባውን ግዴታ መፈጸም የሚችል መሆኑን ለማረጋገጥ ሌላው ሰው የሚያቀርበው ውል ነው።

Tsegaye Demeke - Lawyer

23 Aug, 18:56


የባንክ ዋስትና ሰነዶች (Letter of Guarantees) በኢትዮጵያ ሕግ ያላቸው ሽፋን
=====================
የዋስትና ሰነዶች ባንኮች በተለይም ለደንበኞቻቸው ከሚሰጧቸው የብድር አገልግሎቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው። የዋስትና ሰነዶች በተለያዩ ስያሜዎች የሚጠሩ ሲሆን በዚህም መሠረት በእንግሊዝኛ ‘independent undertakings’, ‘performance bonds/guarantees’, ‘tender bonds/guarantees’, ‘independent (bank) guarantees’, ‘demand guarantees’, ‘first demand guarantees’, ‘bank guarantees’, and ‘default undertakings’ በሚሉ ስሞች ሊጠሩ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪም እነዚሁ ሰነዶች ‘standby Letters of Credit’ ተብለው ሊጠሩ እንደሚችሉ የተለያዩ ጽሑፎች ያሳያሉ። በዚህ መጽሐፍ ውስጥም የዋስትና ሰነዶች የሚለው ጥቅል ስያሜን ለመጠቀም የተሞከረ ሲሆን አንዳንዶቹ ስያሜዎችም የዋስትና ዓይነቶችን የሚያመለክቱ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የዋስትና ሰነዶች በባንኮች የሚሰጡት ደንበኞች የተለያዩ ስምምነቶችን ከሌሎች ሦስተኛ ወገኞች ጋር ፈጽመው ያለባቸውን ግዴታ በአግባቡ ለመወጣታቸው ከባንኮች ዋስትና እንዲሰጥላቸው በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት ነው። የዋስትና ደብዳቤ የሚሰጠውም አንድን ሰው የብድር አገልግሎት ወይም እቃዎቸንና አገልግሎቶችን ለሌላ ሦስተኛ ወገን በብቃት እንዲያቀርብ መተማመኛ በመሆን ነው። ዋስትና ሰነድም አንድ ሰው አንድን የተለየና የተወሰነ ሥራ ለሌላ ሰው ለመሥራት ግዴታ ከገባ ይኸው ሰው በውሉ መሠረት የገባውን ግዴታ መፈጸም የሚችል መሆኑን ለማረጋገጥ ሌላው ሰው የሚያቀርበው ውል ነው። (የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር መዝገብ ቁጥር 47004 ተመልከቱ) የዋስትና ሰነዶች የባንክ የብድር ዓይነቶች ወይም የብድር አገልግሎት መሆናቸውን ከማየታችን በፊት ግን የዋስትና ሰነዶች ምን ማለት እንደሆኑ ማየቱ ተገቢነት ይኖረዋል።
የዋስትና ደብዳቤ አንድ ደንበኛ የፈለገውን የንግድ እንቅስቃሴዎችና ግንኙነቶችን እንዲፈጽም ለማስቻል ደንበኛው ለአቅራቢው ወይም የአገልግሎት ተግባር ለመፈጸም የተዋዋለውን ደንበኛ ሥራውን እንዲያከናውን ለማስቻል የሚሰጥ ደብዳቤ ሲሆን የዋስትና ደብዳቤውን የሚያዘጋጀው ባንክም ሰነዱ የተዘጋጀለት ደንበኛ ግዴታውን መወጣት ባይችል ለተጠቃሚው በቀጥታ ግዴታውን እንደሚወጣ በማረጋገጥ የሚዘጋጅ ነው። የዋስትና ሰነዶችን በተመለከተ የሕግ ሽፋን የሰጠው የተባበሩት መንግስታት ኮንቬንሽን (UN Convention on Independent Guarantees and Standby Letters of Credit) የዋስትና ደብዳቤ ምን ማለት እንደሆነ እና የዋስትና ደብዳቤ ዓይነቶችንም ለመዘርዘር ሞክሯል። በዚሁ አለም አቀፍ ሕግ መሠረትም የዋስትና ደብዳቤ በአዘጋጁ (በብዛት ባንኮች ሲሆኑ) ደብዳቤው ለተዘጋጀለት ተጠቃሚ ዋስትና የተገባለት ግዴታ በባለዕዳው የማይከፈል ቢሆን የዋስትና ደብዳቤውን የጻፉት ባንኮች ባለዕዳውን ተክተው ክፍያውን (ዕዳውን) ለመክፈል ዋስትና እንደሚሆኑ በመግለጽ የሚሰጥ ደብዳቤ ነው። ይሁንና ይህ ኮንቬንሽን የሚያገለግለው አለም አቀፍ የሆኑ ግብይቶችን በተመለከተ እንደሆነ ተገልጿል። ኮንቬንሽኑንም የፈረሙት ሀገሮች ጥቂት በመሆናቸው ሁሉም ሀገሮች በዚህ ስምምነት መሠረት ይዳኛሉ ባይባልም አብዛኛው ሀገራት ግን የዋስትና ሰነዶችን በተመለከተ በሚያወጧቸው ሕጎች የዚህን ስምምነት አንቀጾች ከግንዛቤ በመክተት ሊሆን ይችላል። ኮንቬንሽኑ በተለይም የተለያዩ ዓይነት የዋስትና ደብዳቤ ዓይነቶች እንዳሉ ደንግጓል።

በኢትዮጵያ ሕግ ከዋስትና ሰነዶች ጋር በተያያዘ መነሳትና መዳሰስ ካለበት ዋና ነጥቦች መካከል የዋስትና ደብዳቤ ምን ማለት እንደሆነ፤ የዋስትና ደብዳቤ ምን ምን ነገሮችን ማካተት እንዳለበት፤ የዋስትና ደብዳቤዎች ያላቸው ሕጋዊ አስገዳጅነት፤ የዋስትና ሰነዶች ከሌሎች የዋስትና ዓይነቶች (እንደ ሰው ዋስትና እና የንብረት ዋስትና) ጋር ያላቸው አንድነት እና ልዩነት፤ እንዲሁም የዋስትና ሰነዶች እየተሰራባቸው ካለው ልማዳዊ አሰራር መነሻ ያደረገ ሌላ ሕግ አስፈላጊነት እና የመሳሰሉት ነጥቦች መብራራት ያለባቸው ናቸው።


ዋስትና የገንዘብ፣ የሰው እንዲሁም የንብረት እና የሰነድ ዋስትና ሊሆን ይችላል። እነዚህ የዋስትና ዓይነቶች ግን በየራሳቸው ልዩነት ያላቸው ሲሆን ሁሉንም በተመሳሳይ መልኩ ትርጉም በመስጠት ወይም አንዱን በአንዱ እያቀያየርን መጠቀም በመደረታዊነት ያሉትን የተለያዩ የዋስትና ዓይነቶች እና ያላቸውን ጠቀሜታ የሚያጠፋ ይሆናል። በዋናነት በንብረት፤ በሰው እና በሰነድ ዋስትና መካከል ያለውን ልዩነት ለመገንዘብ የፍትሐብሔር ሕጉን ድንጋጌዎች መመልከት ያስፈልጋል።

የፍትሐብሔር ሕጉ የሰው ዋስትናን (Suretyships or Guaranteership) በተመለከተ ከአንቀጽ 1920 እስከ 1951 ድረስ ባሉት ድንጋጌዎች ሰፊ ሽፋን ሰጥቷል። እነዚህ የሕጉ ድንጋጌዎች ግን የሚገለጹት ስለ ሰው ዋስትና ሲሆን በዚህም መሠረት ግለሰቦች ራሳቸውን ለአንድ ብድር ዋስትና አከፋፈል ባለዕዳው በገባው ውል መሠረት ግዴታውን መፈጸም እንዲችል ለማረጋገጥ የሚሰጡት ዋስትና ነው። በፍትሐብሔር ሕጉ ላይ የተገለጹት ዋስትናን የተመለከቱት ድንጋጌዎች ከውል ሕግ ጋር የሚያያዙ በመሆናቸው የባንክ የብድር ግንኙነቶችን አስመልክቶ በባንክ የሚዘጋጁትን የዋስትና ደብዳቤዎችን የማይወክሉና የማይመለከቱ ናቸው። በባንክ የሚዘጋጁት የዋስትና ደብዳቤዎች በባንኮች ከመዘጋጀታቸው በፊት ዋስትና ደብዳቤው እንዲዘጋጅለት የጠየቀው ደንበኛ የዋስትና ደብዳቤውን ከማግኘቱ በፊት ለደብዳቤው መሠረት የሆኑ ሁለት ዓይነት የተለያዩ እና በራሳቸው የቆሙ ውሎችን ይዋዋላል። አንደኛው ውል የዋስትና ደብዳቤው እንዲዘጋጅለት የጠየቀው ሰው ሊፈጽመው የገባው የአገልግሎት ወይም የአቅርቦት ወይም ሌላ ግዴታን የተመለከተና ከሦስተኛ ወገን ጋር የሚገባው ውል ነው። ሁለተኛው ውል ደግሞ የዋስትና ደብዳቤውን ከባንክ እንዲፈቀድለት የሚጠይቀው ሰው ከባንኩ ጋር የሚገባው ውል ነው። ይህ ውል የዋስትና ደብዳቤ እንዲጻፍለት ጥያቄ ያቀረበው ሰው ደብዳቤው በባንኩ እንዲጻፍለት ባንኩ የሚጠይቀውን ዓይነት ዋስትና ማለትም የንብረት ወይም የጥሬ ገንዘብ ዋስትና በማቅረብ የሚዋዋለው የመያዣ ውል ነው። እነዚህ ሁለት ውሎችም እርስ በእርሳቸው የማይገናኙ እና በራሳቸው የቆሙ ናቸው ማለት ይቻላል። የዋስትና ደብዳቤው ደግሞ ከእነዚህ ውሎች በኋላ በባንኮች የሚሰጥ የዋስትና ሰነድ ሲሆን ይህንን በባንኮች ተዘጋጅቶ ለባለእዳው የሚሰጠውን ደብዳቤ ግን እንደ ውል ልንቆጥረው የምንችለው ሳይሆን በቅድሚያ ባንኮች እና የዋስትና ሰነዱን የጠየቀው ሰው በገቡት የመያዣ ውል አማካኝነት የሚዘጋጅ ደብዳቤ እንደሆነ የሚቆጠር ነው።

በመሆኑም የዋስትና ደብዳቤው የሚዘጋጀው በባንኮች በመሆኑና በደብዳቤው ላይ የሚፈርመውም የሚያዘጋጀው ባንክ ብቻ በመሆኑና የዋስትና ደብዳቤው ላይ ዋስትና የተገባለት ሰውም ፊርማውን የማያኖር ሲሆን በደብዳቤው ላይም የምስክሮች ፊርማም ሆነ ስም በአብዛኛው አይቀመጥም። በመሆኑም ይህ ሁኔታ የሚያሳየው ደብዳቤውን ውል ለማለት የውል መሠረታዊ ሁኔታዎችን ያላሟላ መሆኑን ሲሆን ውል ነው የምንል ቢሆን እንኳን ከራስ ጋር የተደረገ ውል እንደሆነ ከመቆጠር ውጪ ሌሎች ውሎች የሚያሟሉትን ነጥቦች የሚያሟላ አይደለም። በዚህም

Tsegaye Demeke - Lawyer

30 Jul, 18:42


የወንጀል ህግ ምንነት፣ ዓላማውና ህገ መንግስቱ
====================
የሰው ልጅ ሠላማዊ ህይወትን ለመምራት ከወንጀል የፀዳ ህብረተሠብ መፍጠር አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ያለው አማራጭ የወንጀል ፍትህ አስተዳደርን መዘርጋት ነው፡፡ ይህ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር እንዲኖር ህግ አውጭ፣ ህግ ተርጓሚና አስፈፃሚ አካላት መኖር አለባቸው፡፡ በዚሁ መሠረት ህግ አውጪው እንደ ወንጀል አድርጐ የሚቆጥራቸው ድርጊቶች እና ተገቢ ብሎ ያመነባቸውን ቅጣቶች ዘርዝሮ በህግ ያወጣል፤ ህግ ተርጓሚው ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው የተከሰሱ ሠዎችን ሲቀርቡለት ማስረጃውን አዳምጦ ተገቢውን ውሣኔ ይሰጣል፡፡ አስፈፃሚው አካል በፖሊስ አማካኝነት ወንጀል እንዳይፈፀም ይከላከላል ተፈፅሞም ከሆነ ተጠርጣሪዎች ይዞ ለፍርድ ያቀርባል፡፡ ዓቃቤ ህግ መንግስትን በመወከል ክስ ያቀርባል፡፡ ማረሚያ ቤቶች ቅጣት የተወሰነባቸውን ጥፋተኞች ተቀብለው ያሰራሉ ሌሎች ቅጣቶችም ተወስነው ከሆነ ያስፈፅማሉ፡፡
ስለሆነም የወንጀል ህግና የወንጀል የፍትህ አስተዳደር መሠረታዊ አላማዎች የወንጀል አይነቶችን አስቀድሞ በማሣወቅ የአንድ ህብረተሠብ አባላት ይህንን አውቀው ከጥፋት እንዲታቀቡ ማድረግና ይህን ማስጠንቀቂያ በማይከተሉ ላይ ቅጣት መፈፀም ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት የወንጀል ህግ የተለያዩ የህብረተሠብ አባላት ማለትም ሰዎች ከሠዎች ወይም ከቡድኖች ወይም ከመንግስት ጋር ያላው ግንኙነት ይወስናል፡፡ በህግ እውቅና በተሠጠው ግንኙነት መሠረት ድርጊታቸውን ማስተካከል የሚችሉ ህጉ ተፈፃሚ የማይሆንባቸው ሲሆን ይህን ማድረግ የማይቻላቻው በህጉ መሠረት ይዳኛሉ፡፡
ኢትዮጵያ ከላይ የተጠቀሰውን አላማ ለማሣካት በተለያዩ ጊዜያት የወንጀል ህጐች ድንግጋ በተግባር ላይ አውላለች፡፡ በ1923 ዓ.ም የተደነገገው ለመጀመሪያ ጊዜ በስራ ላይ የዋለው የወንጀል ህግ ነው፡፡ 1949 ዓ.ም የወጣው ደግሞ ሁለተኛውና ከ40 ዓመት በላይ በስራ ላይ የነበረ የወንጀል ህግ ነው፡፡ በየመሃሉም ተጨማሪና ያለውን ከፍተት ሊሞሉ የሚችሉ ህጐች በስራ ላይ ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ህግ ከ1949 ዓ.ም ጀሞሮ በስራ ላይ የነበረውን የወንጀለኛ መቅጫ ህግ በመተካት ከግንቦት 1 ቀን 1997 ዓ. ም ጀምሮ በተግባር ላይ ውሏል፡፡ በኢፌድሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 52(5) ላይ በተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት መሠረት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣ ነው፡፡ ይህ የወንጀል ህግ ህብረተሠቡን በጉዳት ለመጠበቅ የወጣና እንደ ወንጀል የሚቆጠሩ ድርጊቶችና ለነዚህ የተከለከሉ ድርጊቶች ተገቢ ተብለው የተዘረዘሩ ቅጣቶችን የሚዘረዝር ህግ ነው፡፡ ስለሆነም ቅጣት እና ወንጀል ሁለቱ የወንጀል ህግ መሠረታዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡
ወንጀል ምን ማለት ነው?

ወንጀል ምን ምን አይነት ባህሪያትን ያካትታል ብሎ ቋሚና አለም አቀፋዊ ትርጉም ለመስጠት ያስቸግራል፡፡ ወንጀል የሚባሉት ባህሪያት ከማህበረሠብ ማህበረሰብ ይለያያሉ፡፡ ማህበረሠቡ ሲያድግ ይለወጣሉ፡፡ ስለሆነም በዛሬ ጊዜ ወንጀል ተብሎ የተደነገገ ድርጊት ወይም ያለማድረግ ከዚህ በፊት ወንጀል ላይሆን ይችላል፡፡ ወይም ከዚህ በፊት ወንጀል ተብሎ የተደነገገ ጉዳይ ዛሬ ወንጀል ላይሆን ይችላል፡፡
የወንጀል ህግ ህግ እና ቅጣቶቹ በአብዛኛው የአለማችን ሃገሮች በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ተመሣሣይነት ቢኖራቸውም በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ እንዲህ አይነት ልዩነት ሊፈጠር የሚችለው የተለያዩ ሃገሮች ህዝቦች በተወሰኑ ጉዳዮች ያላቸው የአመለካከት ልዩነት ነው፡፡ ይህ ልዩነት ሃይማኖት ከባህል በስልጣኔ እድገት በሰው ልጆች መብት አጠባበቅ ብለው አስተሣሠብ ሊመነጨ ይችላል፡፡ በዚሁም መሠረት የአልኮል መጠጦችን ማዘዋወር፣ ዝሙት አዳሪዎች፣ ግብረሰዶም፣ ፅንስ ማስወረድ የመሣሠሉት ድርጊቶች በአንዳንድ ሃገሮች የወንጀል ድርጌት ተብለው ክልከላ ተደርጐባቸው ግርፋት ወይም የሞት ቅጣት የመሣሠሉትን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ በሌሎች ሃገሮች ግን ይሄንኑ ተመሣሣይ ድርጊቶች ያልተከተሉ ወይንም በወንጀል ህግ የማያስጠይቁ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ሆኖም ግን በሠፊው ተቀባይነት ያገኘው ትርጉም የሚከተለውን ይመስላል
ወንጀል ማለት ፡- በወንጀል ህግ የተከለከሉ ድትጊቶችን መፈፀም ወይም እንዲፈፀሙ ትዕዛዝ ወይም ግዴታ የተጣለበቸውን ድርጊቶች አለመፈፀም ነው፡፡
በዚህ መሠረት የወንጀል ህጉ ኃላፊነትን የማያስከትል ተግባር የፈፀሙ ሠዎች በወንጀል እንዳይጠቁ ማድረጊያና ወንጀል የፈፀሙ ቢሆንም እንኳን በህጉ ላይ ከተመለከተው ቅጣት ውጪ በዘፈቀደና ኢ-ሰብአዊ በሆነ መንግድ እንዳይቀጡ መከላከያ መሣራያ ነው፡፡
የወንጀል ህግ አላማና ግብ

የወንጀል ህጉ አንቀፅ 1 ሁለት ፓራግራፎች ያሉት ሲሆን በመጀመሪያው አላማውን ሲገልፅ ሁለተኛው ግቡን ያብራራል፡፡
አንቀፅ 1
የወንጀል ሕግ ዓላማ፣ ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል የአገሪቱን መንግሥት፣ የሕዝቦቹን፣ የነዋሪዎቹን፣ ሰላም፣ ደህንነት፣ ሥርዓት፣ መብትና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ ነው፡፡
የወንጀል ሕግ ግብ ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከል ሲሆን ይህንን የሚያደርገው ስለወንጀሎችና፣ ስለቅጣታቸው በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በመስጠት፣ ማስጠንቀቂያነቱ በቂ ባልሆነበት ጊዜ ወንጀል አድራጊዎቹ ተቀጥተው ሌላ ወንጀል ከመፈፀም እንዲቆጠቡና ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆኑ ወይም እንዲታረሙ በማድረግ ወይም ተጨማሪ ወንጀሎች እንዳይፈፅሙ እርምጃዎች እንዲወሰድባቸው በማድረግ ነው፡፡


የወንጀል ህግ አላማ

የወንጀል ህግ አላማ ከፍ ብሎ በተቀመጠው አንቀፅ 1 የመጀመሪያው ፓራግራፍ እንደተመለከተው የሃገሪቱ መንግስት፣ የህዝቦቹን፣ የነዋሪዎቹን፣ ሰላም ደህንነት ስርዓት መብትና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ ነው ይላል፡፡ ይህ ህጉ በመጨረሻ ሊደረስበት ያስበውን አላማ ያመለክታል ስለዚህም የወንጀል ህጉ አላማ አጠቃላይ ህብረተሠቡን ከወንጀል ድርጊቶች መጠበቅና ሰላምን ማረጋገጥ ነው፡፡
በአንቀፁ የተገለፀው “ህዝቦች” የሚለው ቃል የሚያመለክተው ህገ መንግስቱ ለብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ከፍተኛ ጥበቃ ያደረገላቸው በመሆኑ የወንጀል ህጉ ይህንን ሊያንፀባርቅና ህጉ ነዋሪዎቹ በግለሰብነታቸው ብቻ ሣይሆን በልዩ ልዩ ህብረት በተቋቋሙበት ሁኔታ ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ነው፡፡ በተጨማሪም ዜጐቹንም ሆነ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙትን የውጭ ሃገር ሰዎች ስለሚያጠቃልልና ወንጀል ህግ ጥብቃ የሚያደርገው ለሰዎች ሁሉ ስለሆነ “ዜጐች” ተብሎ በቅድሞው ህግ ተገልፆ የነበረው ነዋሪዎች በሚለው ተተክቷል፡፡
የወንጀል ህጉ አላማ የነዋሪዎቹን ሰላም ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህ በግልፅ የሚያመለክተው ከግለሰቦች መብት ይልቅ የህዝቦች መብት ቅድሚያ እንደተሠጠው ነው፡፡ ስለሆነም አንድ የወንጀል ድርጊት ሲፈፀም በህብረተሠቡ አጠቃላይ ጥቅም ላይ ጉዳት ደርሷል ተብሎ ይገመታል፡፡ በዚህም መሠረት የህዝብ ስርዓት ፣ ሰላምና ፀጥታ ሊጠበቅ የሚችለው የግለሰቦች መብት ሲጠበቅ በመሆኑ በእነዚህ መብቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት በህዝብ ጥቅም ወይም መብት ላይ እንደተፈፀመ ወንጀል ይቆጠራል፡፡

Tsegaye Demeke - Lawyer

26 Jul, 12:49


Channel photo updated

Tsegaye Demeke - Lawyer

23 Jul, 19:47


ካርታ ማምከን/የይዞታ ማረጋገጫ መሰረዝ/
====================
የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት ማረጋገጫ ማስረጃ /ደብተር ወይም ካርታ/ በመሰረዝ ዋጋ ማሳጣት
አንድ የአስተዳደር አካል የቤት ባለቤትነት ማስረጃ በፈለገው ጊዜ ከሕግ ውጪ እንዲሰረዝ ማስቻል በኢ.ፌ.ዲ. ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 40/1/ እና /2/ ድንጋጌ ሥር የተከበረውን የንብረት ባለቤትነት መብት ዋጋ የሚያሣጣው ነው፡፡ የፍ/ብ/ሕ/ቁጥር 1195 እና 1196 ድንጋጌዎች አንድ ላይ ሲነበቡም የአስተዳደር አካል በባለቤት ማረጋገጫ ማስረጃ አሰጣጥ ላይ ፍጽም የሆነ አስተዳደራዊ ስልጣን ያለው ስለመሆኑ አያሣዩም፡፡ ይልቁንም ድንጋጌዎች እርስ በእርሣቸውም ሆነ ከፍ/ሕ/ቁጥር 1198 ድንጋጌ ጋር ተዛምደው ሲታዩ የባለቤት ማረጋገጫ ደብተር የሚሰረዘው በሕጉ በተመለከቱት ምክንያቶች ብቻ መሆኑን ከሕጉ ውጪ ተግባሩ ተከናውኖ ከተገኘም መብቱ የተነካው ሠው በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 37፣78 እና 79 ድንጋጌዎች መሠረት ጉዳዩን ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት አቅርቦ አቤቱታው እንዲታይለት የሚያርግበት ጉዳይ እንጂ አስተዳደር አካሉ የሰጠው ውሣኔ በፍርድ ቤት እንዳይታይ የሚገደብበት ስርዓት የሌለ መሆኑን የምንገነዘበው ነው፡፡
ሰ/መ/ቁ. 42501 ቅጽ 15፣ ኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 37፣ 38፣ 79፣ ፍ/ህ/ቁ. 1195፣ 1196፣ 1198
አስተዳደራዊ ተቋማት በሕግ ተለይቶ በተሰጣቸው ጉዳይ የመወሰን ሥልጣን እንዳላቸው የታወቀ ነው፡፡ ይሁንና ለአንድ ባለ ጉዳይ የተሰጠው ካርታ የተሰጠበት እና የተሻረበት አግባብ በሕግ አግባብ መሆን ያለመሆኑን አጣርቶ የመወሰን ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ነው፡፡ በዚህ ረገድ አንድ ፍርድ ቤት የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታን የመሰረዝ ሥልጣን የአስተዳደር ክፍል ነው፣ ፍርድ ቤት ጉዳዩን አይቶ የመወሰን ሥልጣን የለውም በማለት የሚደርስበት ድምዳሜ የጉዳዩን የክርክር ባህሪ እና ይዘት ያላገናዘበ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች በአስተዳደር ክፍል የተሰጠው ካርታ የተሰጠበት ወይም የተሻረበት ሥርዓት እና አስተዳደራዊ ውሳኔው ሕግና መመሪያ ያገናዘበ መሆን ያለመሆኑን በማጣራት ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን እንዳላቸው ከፍ/ህ/ቁ. 1196 እና በህገ መንግስቱ ስለ ንብረት መብት ከአደረገው ድንጋጌና በፍርድ የሚያልቁ ጉዳዮችን በተመለከተ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 37 ከተመለከቱት ድንጋጌዎች ይዘት የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡
ሰ/መ/ቁ 99071 ቅጽ 18፣ ኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት አንቀጽ 37፣ ፍ/ህ/ቁ. 1196

Tsegaye Demeke - Lawyer

22 Feb, 16:26


https://youtube.com/channel/UCU9osTZjo6yLL8C6yqVbRhA

Tsegaye Demeke - Lawyer

01 Jan, 08:56


ለመንግሥት ሠራተኞች የሚሰጥ የወሊድ ፈቃድ
==================
ለአንድ የመንግስት ሰራተኛ የተለያዩ ዕረፍት ዓይነቶች ያሉ ስሆን በፌደራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010” አንቀጽ 43 ላይ የተደነገገው የወሊድ ፈቃድ ነው።
ነፍሰጡር የሆነች የመንግሥት ሠራተኛ፣ ከእርግዝናዋ ጋር የተያያዘ ምርመራ ለማድረግ ሐኪም በሚያዘው መሠረት ደመወዝ የሚከፈልበት ፈቃድ ይሰጣታል፤
1. ከመውለዷ በፊት ዕረፍት እንድታደርግ ሐኪም ካዘዘ ደመወዝ የሚከፈልበት ዕረፍት ይሰጣታል፡፡
2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (1) የተመለከተው ፈቃድ እንደ ህመም ፈቃድ አይቆጠርም፡፡
3. ነፍሰጡር የሆነች የመንግሥት ሠራተኛ መውለጃዋ ሲደርስ እወልዳለሁ ብላ ከገመተችበት ቀን በፊት 30 ተከታታይ ቀናት የቅድመ ወሊድ ፈቃድ፣ እንዲሁም ስትወልድ ከወለደችበት ቀን ጀምሮ 90 ተከታታይ ቀናት፣ በአጠቃላይ 120 ተከታታይ ቀናት ደመወዝ የሚከፈልበት የወሊድ ፈቃድ ይሰጣታል፡፡
4. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (3) መሠረት ሠራተኛዋ የተሰጣት የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ከማለቁ በፊት ከወለደች ያልተጠቀመችበትን ቀሪ የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ከወለደች በኋላ እንድትጠቀምበት ይደረጋል፡፡
5. ሠራተኛዋ የወሰደችው የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ሲያልቅ ያልወለደች እንደሆነ እስከምትወልድበት ቀን ድረስ ባሉት የሥራ ቀናት የምትቆይበት ዕረፍት በበጀት ዓመቱ ካላት የዓመት ዕረፍት ፈቃድ ወይም በበጀት ዓመቱ የዓመት ፈቃድ የሌላት እንደሆነ ከሚቀጥለው የበጀት ዓመት የዕረፍት ፈቃዷ ይተካል፡፡
6. ሠራተኛዋ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (3) የተወሰነውን የወሊድ ፈቃድ ከጨረሰች በኋላ ብትታመምና ተጨማሪ ፈቃድ የሚያስፈልጋት መሆኑ በሀኪም ከተረጋገጠ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 43(1) በተደነገገው መሠረት የሕመም ፈቃድ መውሰድ ትችላለች፡፡
7. ማንኛዋም ስድስት ወር የሞላት ነፍሰጡር የሆነች የመንግስት ሠራተኛ የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ከመውሰዷ በፊት ጽንሱ የተቋረጠባት ከሆነ ይህንኑ የሚያረጋግጥ የህክምና ማስረጃ ስታቀርብ የ60 ቀን የድህረ ወሊድ ፈቃድ ይሰጣታል፡፡
8. የቅድመ ወሊድ ፈቃድ ከወሰደች በኋላ የጽንስ መቋረጥ ካጋጠማት የወሰደችው የቅድመ ወሊድ ፈቃዷ ተቋርጦ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (3) የተመለከተው የ90 ቀን የድህረ ወሊድ ፈቃድ ይሰጣታል፡፡
9. ከሦስት እስከ ስድስት ወር ባለው የእርግዝና ጊዜ ውስጥ የፅንስ መቋረጥ ያጋጠማት የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ የሚከፈልበት 30 ተከታታይ ቀን ፈቃድ ይሰጣታል፡፡
10. ማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ የትዳር ጓደኛው ስትወልድ ደመወዝ የሚከፈልበት 10 የሥራ ቀን ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡

Tsegaye Demeke - Lawyer

02 Nov, 15:50


5. የሽብር ወንጀል እና የሚያስከትለው ተጠያቂነት በኢትዮጵያ ህግ ስርዓት
በአገራችን በተለያየ ወቅት የሽብር ድርጊቶች የተፈፀሙ ሲሆን በ1970 ዎቹ ሲፈጸም የነበረው የቀይ ሽብርና የነጭ ሽብር ድርጊት በአገራችን በዜጎች ላይ ከፍተኛ ስጋትን ከፈጠሩ ሁኔታዎች ውስጥ የሚመደብ ነዉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ 1990 ዎቹ በትግራይ ሆቴል፣ በአክሱም ሆቴል፣ በጊዎን ሆቴል እና በድሬ ደዋ በራስ ሆቴል እንዲሁም በ2000 ዓ.ም በታክሲ ላይ በተፈጸመ ጥቃት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

በሀገራችን በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ህግ የሽብር ወንጀልን መከላከል እና ለመቅጣት ጥረት የተደረገ ሲሆን ወንጀሉ ካለዉ አስከፊ ባህሪ በ2001ዓ.ም ራሱን የቻለ አዋጅ ቁጥር 652/2001 ሊወጣ ችሏል፡፡ ነገር ግን አዋጅ ቁጥር 652/2001 መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶችን የሚገድብ ሆኖ በመገኘቱ በአዋጅ ቁጥር 1176/2012 እንዲተካ ተደርጓል፡፡

የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ 1176/2012 አንቀጽ 3 መሰረት የሽብር ድርጊት ማለት፡-
1) ማንኛውም ሰው የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማራመድ በማሰብ ህዝብን ወይም የተወሰነ የህብረተሰብን ክፍል ለማሸበር ወይም መንግስትን፣ የውጭ አገር መንግስትን ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅትን ለማስገደድ፡- ሀ) በሰው አካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ፤ ለ) የሰውን ሕይወት ለአደጋ ያጋለጠ፤ ሐ) ሰውን ያገተ ወይም የጠለፈ፤ መ) በንብረት፣ በተፈጥሮ ሐብት ወይም አካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ፤ ወይም ሠ) የሕዝብ ወይም ማህበራዊ አገልግሎት እንዳይሰጥ በከፍተኛ ሁኔታ ያስተጓጎለ እንደሆነ ከአስር ዓመት እስከ አስራ ስምንት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡

2) በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) የተጠቀሰውን አላማ ለማስፈጸም የተፈጸመው ተግባር ሰውን መግደል ወይም በታሪካዊ ወይም የባሕል ቅርስ ወይም የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ እንደሆነ ከአስራ አምስት ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ ጽኑ እስራት ወይም በሞት የሚያስቀጣ መሆኑን ደንግጓል፡፡

በአዋጁ ከአንቀጽ 3 ውጭ ያሉ የሽብር ወንጀሎች፡-
1. መዛት፡- በአዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 5 መሰረት ከላይ በአንቀፅ 3 ስር የተገለፀውን የሽብር ወንጀል ለመፈፀም መዛት ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ሊደርስ በሚችል ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ተግባር ተደርጎ ተደንግጓል፡፡ ዛቻ የፈጸመው ሰው አደርገዋለሁ ያለውን ድርጊት ለማድረግ ለመፈጸም ያለው አቅም፣ ዕድል ወይም በሌላ ሰው የሚያስደርግ ከሆነ ይህንን ለማድረግ አቅም ያለው መሆኑ ወይም በመዛቱ ምክንያት ህብረተሰቡ ወይም የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል የተሸበረ ወይም ሽብር ሊፈጥር የሚችል መሆኑን በመመዘን ነው፡፡
2. ማቀድና መሰናዳት- የሽብር ድርጊትን ለመፈጸም ማቀድና ማሰናዳት በራሱ የሚያስቀጣ ተግባር ሲሆን በሁለቱ መካከል ግልጽ ወሰን ማስቀመጥ ያስቸግራል፡፡ የአዋጅ ቁጥር 1176 አንቀጽ 6 በአዋጁ አንቀጽ 3 የተመለከተውን ድርጊት ለመፈጸም ማቀድና መሰናዳት የሚያስቀጣ እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ ድንጋጌው ለማቀድ ከሶስት እስከ ሰባት ዓመት እንዲሁም ለመሰናዳት ከአምስት እስከ አስራ ሁለት ዓመት የሚያስቀጣ ስለመሆኑ ያስቀምጣል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 2 ንኡስ አንቀጽ 6 ማቀድ ማለት በአዋጁ አንቀጽ 3 የተመለከተውን የሽብር ድርጊት ለመፈጸም ከሀሳብ ባለፈ ወንጀሉን ለመፈጸም የሚፈጸምበትን ሁኔታ፣ ቦታ፣ ጊዜ ወይም መሰል ጉዳዮችን የመለየት ወይም የመወሰን ጉዳይ እንደሆነ ትርጉም ያስቀምጣል፡፡ ኢትዮጵያ የፈረመችው የአፍሪካ ህብረት የሽብር መከላከልና መቆጣጠር ኮንቬንሽን ማቀድ የሚያስቀጣ ተግባር ሆኖ እንዲካተት የሚያስቀምጥ ከመሆኑ አንጻር ማቀድ በአዋጁ ውስጥ ተካቷል፡፡

3. ማደም ማለት ሁለትና ከዛ በላይ የሆኑ ሰዎች የወንጀል ድርጊት ለመፈጸም የተስማሙ እንደሆነ ስለመሆኑ ከወንጀል ህጉ አንቀጽ 38 ይዘት ለመረዳት ይቻላል፡፡ በአዋጁ የሽብር ወንጀልን ለመፈጸም ማደም ከአምስት ዓመት እስከ አስራ ሁለት ዓመት ድረስ ሊያስቀጣ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ማደም ከማቀድ እና መሰናዳት ለየት የሚያደርገው የድርጊቱ ፈጻሚዎች ሁለትና ከዛ በላይ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን እነዚህ ሰዎች ድርጊቱን ለመፈጸም የተስማሙ መሆኑን የሚጠይቅ ነው፡፡ ስምምነት መኖሩ በማስረጃ መረጋገጥ ያለበት ሲሆን በግልጽ ወይም በተዘዋዋሪ በሰዎቹ መካከል ስምምነት ለመኖሩ የሚያስረዳ ሁኔታ ካለ አድማ ስለመኖሩ ለማረጋገጥ በቂ ይሆናል፡፡

4. በሐሰት ማስፈራራት- በሽብር ድርጊት በሀሰት ማስፈራራት በቀላል እስራት ወይም ጉዳት ያስከተለ እንደሆነ ከሶስት ዓመት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 8 ላይ ተደንግጓል፡፡ በሀሰት ማስፈራራት በሽብር ህግ ውስጥ እንዲካተት የተደረገበት ዋና ምክንያት ሰዎች በዘፈቀደ የሽብር ጥቃት እንደሚያደርሱ በመግለጽም ሆነ በማስመሰል ዜጎችን ለአደጋ እንዳያጋልጡ ማድረግ ነው፡፡
5. ድጋፍ ማድረግ፡- ወንጀሉን የሚፈፅም ሰው መርዳት ከሰባት እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ድርጊት ሆኖ በአዋጁ አንቀጽ 9 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡ የድጋፍ ዓይነቶችን ስንመለከት የሽብር ወንጀል አፈጻጸምን ለመርዳት በማሰብ ሰነድ ወይም መረጃ ማዘጋጀት፣ ማቅረብ፣ መስጠት፣ የምክር አገልግሎት፣ የሙያ ድጋፍ፣ ጉዳት ማድረስ የሚችሉ መሳሪያ፣ ኬሚካሎች ወይም ንጥረ-ነገሮች ያዘጋጀ፣ ያቀረበ የሰጠ ወይም የሸጠ ድጋፍ እንዳደረገ ይወሰዳል፡፡

6. ማነሳሳት፡- አንድ ሰው ሌላው ሰው የሽብር ድርጊት እንዲፈጽም ለማድረግ በመጎትጎት፣ ተስፋ በመስጠት፣ በገንዘብ፣ በስጦታ፣ በማስፈራራት ወይም በማናቸውም ሌላ መሰል ዘዴ ያነሳሳ እንደሆነ ለድርጊቱ በአንቀጽ 3 ላይ በተቀመጠው ቅጣት እንደሚቀጣ በአንቀጽ 10(1) ተደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ ድጋፍ ከማድረግ የሚለየው ድርጊቱን የሚፈጽመው ሰው በራሱ ፍላጎት የሚፈጽመው ሳይሆን ማነሳሳት በፈጸመው ሰው ምክንያት ሲሆን ድጋፍ ማድረግ ደግሞ ወንጀል አድራጊው ሀሳብ ያለው ሆኖ ድጋፍ የሚያደርገው ሰው የድርጊቱ ፈጻሚ ሀሳቡን እንዲያሳካ ማመቻቸት ወይም አስተዋጽዎ ማበርከትን የሚመለከት ነው፡፡

በአጠቃላይ የሽብር ወንጀል ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል አስከፊነት ድርጊት ነው፡፡ ድርጊቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሀገራችን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል፣ በመወሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይበልጥ ወንጀሉን ለመከላከልና ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ እንዲሁም ወንጀሉ ተፈፅሞ ከተገኘ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በተለይ የህግ አስፈፃሚ የተቋማትና የባለሙያዎችን አቅም ማጎልበት ወሳኝ ጉዳይ ነዉ፡፡ ህብረተሰቡም ወንጀልን በመከላከልና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለህግ እንዲቀርቡ ከማድረግ አንፃር እገዛ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡
Ministry of Justice

Tsegaye Demeke - Lawyer

02 Nov, 15:50


የሽብር ወንጀልና የሚያስከትለው ተጠያቂነት

1. መግቢያ
የሽብር ድርጊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኘ አንድ ወጥ ትርጉም የሌለው በመሆኑ በተለያዩ ሀገራት የድርጊቱ አረዳድ ላይ ልዩነት ይስተዋላል፡፡ በአንዱ አገር የሽብር ተግባር የሆነው ድርጊት በሌላው እንደ የነፃነት ትግል ሆኖ ይቆጠራል፤ በአንዱ የነፃነት ትግል ተደርጎ የሚታየው ተግባር በሌላው የሽብር ተግባር ሆኖ ይታያል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በዓለም ሰላም እና ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ስጋት ከሆኑ እና ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ ከሚገኙ ወንጀሎች ውስጥ አንዱ ስለመሆኑ ተቀባይነት ያገኘ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ወንጀሉን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ሀገራት በተናጠል እና በጋራ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

ሀገራችንም በተለያዩ ጊዜያት የወንጀሉ ሰለባ የነበረች ሲሆን ወንጀሉን ለመከላከል ህግ ማዕቀፍ ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዳለች፡፡ ከዚህ አንፃር የፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ማውጣት አንዱ እርምጃ ሲሆን በአዋጁ የሚስተዋለውን ክፍተት ለመቅረፍ አዋጁ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ ቁጥር 1176/2012 ሆኖ ተሻሽሎ ወጥቷል፡፡ በዚህ ጽሁፍ ስለ ሽብር ምንነት፣ የሚያስከትለዉ ጉዳት፣ ወንጀሉን ለመከላከል ያለዉ ዓለም ዐቀፍና ሀገር አቀፍ ህጎች እና የወንጀሉ የሚያስከትለው ተጠያቂነት ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡

2. የሽብር ወንጀል ምንነት፣ የሚፈፀምበት ዓላማ እና የሚያስከትለው ጉዳት
ሽብር የሚለው ቃል የተሰጠ ወጥ ትርጉም ባይኖርም ከብዙ ሀገራት ህጎች መረዳት የሚቻለዉ አንድን ርዕዮት ዓለም፣ የፖለቲካ ወይም የሃይማኖት አስተሳሰብ በሕዝብ ወይም በመንግሥት ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ወይም ለማሳካት ኃይልን በመጠቀም በዜጎች ላይ ፍርሃትን በመፍጠር የማይፈልጉትን እንዲቀበሉ የማድረግ ተግባር ነዉ፡፡ ከዚህ የምንረዳው ከሌሎቹ ወንጀሎች በተለየ መልኩ የድርጊቱ ፈጻሚ ድርጊቱን ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በሌላቸው ንጹሃን ሰዎች፣ የመንግሥት ተቋማት፣ ባለሥልጣኖች፣ ጦርነት በሌለበት ሁኔታ ወታደራዊ ተቋማት ወዘተ ላይ በመፈጸም ሌላኛው ወገን መንግሥትና ሕዝብ እንዲገደድና ሃሳቡን ወይም አስተሳሰቡን እንዲቀበል ለማድረግ የሚፈጸም ተግባር መሆኑን ነው፡፡ ሌሎች ወንጀሎች ግን የሚፈፀሙት ቀጥታ ግንኙነት ባለው አካል ላይ ነው፡፡
የሽብር ወንጀል መሠረታዊ ዓላማ ሲታይ ወንጀሉ የሚፈፀመው የፖለቲካ፤ የሐይማኖት ወይም የአይዲዮሎጂ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ ነው። ከዚህ አንፃር በሀገራችን ህግ መሰረት የሽብር ድርጊት ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማራመድ በማሰብ ህዝብን ወይም የተወሰነ የህብረተሰብን ክፍል ለማሸበር ወይም መንግስትን፣ የውጭ አገር መንግስትን ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅትን ለማስገደድ በሚል በሰው ወይም በንብረት ላይ ጉዳት ማድረስ መሆኑ ተገልፆል፡፡ ይህም በአዋጅ ቁጥር 1176/2012 በአንቀፅ 3 ላይ እንደተገለጸው ለሁለት ዓላማ ማለትም የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማራመድ በማሰብ እና ህዝብን ወይም የተወሰነ የህብረተሰብን ክፍል ለማሸበር ወይም መንግስትን፣ የውጭ አገር መንግስትን ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅትን የማስገደድ አላማ ነው።

የሽብር ወንጀል የተለያዩ ጉዳቶችን የሚያስከትል ሲሆን በአብዛኛዉ በንብረት ወይም አገልግሎት ጉዳት የሚያድርስ፣ የሰውን ህይወትን የሚያጠፋ፣ በታሪካዊ ወይም የባሕል ቅርስ ወይም የመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ ነው፡፡ እንዲሁም የህዝብ አገልግሎትን ያስተጓጉላል፡፡

3. የሽብር ወንጀል ታሪካዊ ዳራ
የሽብር ወንጀል ጽንሰ ሃሳቡ ሲታይ በአብዛኛዉ ቃሉ ሽብርተኝነት (terrorism) በሚለው ቃል ቢገለፅ ይታያል፡፡ ይህ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በ18ኛው ክፍለ ዘመን በፈረንሳይ አብዮት ወቅት (እ.ኤ.አ መስከረም 1793- ሐምሌ 1794) የተገኘ ቃል እንደሆነ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ወቅት የፈረንሳይ የአብዮታዊ አስተዳደሩ የአብዮቱ ጠላት ናቸው በሚል በሚጠረጠሩ ዜጎች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዙን እና ንጉስ ናፖሊዮን የስፔንን መውረር ተከትሎ ሕዝባዊ አመጽ መቀስቀሱንና የሽምቅ ተዋጊዎች መስፋፋትን መሰረት በማድረግ ሽብርተኝነት የ18ኛው ክፍለ ዘመን ክስተት አድርገው ያስቀምጣሉ፡፡

ወንጀሉ በተለያዩ ሀገራት ቅርጽና ይዘቱን እየቀያየረ በዜጎች ላይ ከፍተኛ ቁሳዊ፤ ማህበራዊ እንዲሁም ሀይማኖታዊ ጉዳቶችን እያስከተለ እስካሁን የቀጠለ ጉዳይ ነዉ፡፡ በቅርቡ እንኳ እ.ኤ.አ ከ1990 ጀምሮ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የተለያዩ የውሳኔ ሀሳቦችን ከማሳለፍ ባለፈ፤ ሊብያ፣ ሱዳን እና አፍጋንስታንን ሽብረተኛን ይደግፋሉ በሚል የውሳኔ ሀሳብ በማስተላለፍ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ጥሎባቸዋል፡፡

ሌላዉ በዓለም ላይ አስደንጋጭ ክስተት የነበረው የአሜሪክ መንትዮች ህንጻ ላይ ከተፈጸመበት ከ2001 ጀምሮ ያለው ጊዜን ይመለከታል፡፡ በ2001 ዓ.ም በአሜሪካው ላይ የተፈጸመው ጥቃት ዓለም አቀፍ ተቋማትም ሆኑ አገራት በሽብርተኝነት ላይ ያላቸውን አቋም እንዲፈትሹ ከማድረጉ ባለፈ ጠንካራ የህግ ማስፈጸም ስራ እንዲያከናውኑ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ክስተት አገራት ድርጊቱን ለመቆጣጠር ቀድሞ የነበራቸውን አጠፋዊ ምላሽ ስትራቴጂ ወደ ቀድሞ መከላከል እንዲቀይሩ አስገድዷቸዋል፡፡ የጸጥታው ምክር ቤትም አልቃይዳን ትኩረት ያደረገ የሽብር መከላከል ትኩረትን በመተው ሁሉን አቀፍ የሽብር ወንጀል መካለከል ላይ እንዲያተኮር፣ ሽብር የዓለም አቀፍ ደህንነትና ሰላምና ደህንነት ስጋት እንደሆነ በመቀበል ሁሉም አባል አገራት ድርጊቱን ወንጀል በማድረግ እንዲደነግጉ እና የህግ ማስፈጸም ስርዓታቸውን እንዲያጠናክሩ አቅጣጫ በማስቀመጡ በተለይ አባል ሀገራት ሽብር ህግ እንዲያወጡ አስገድዷቸዋል፡፡

4. ወንጀሉን ለመከላከል የሚያስችል አለም አቀፍ የህግ ማዕቀፍ
የሽብር ወንጀል በየትኛዉም ሀገርና ዜጎች ላይ ሊፈጸም የሚችል ወይም የሚፈጸም ዉስብስብንና አስከፊ ወንጀል ነው፡፡ ይህ ማለት የሽብር ወንጀል ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች (Transnational Organized Crime) ከሚባሉት ዉስጥ አንዱ ነዉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሽብር ድርጊትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በተለያዩ ጊዜ የውሳኔ ሃሳብን አስተላልፏል፡፡ ድርጅቱ እራሱን የቻለ ሁሉን አቀፍ የሽብር ድርጊት መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል ዓለም አቀፍ ስምምነት ከማውጣት ይልቅ በጉዳይ የተነጣጠለ የውሳኔ ሃሳብ ሲያስተላልፍና ስምምነቶች እንዲወጡ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህ ወጥ የሆነ የህግ ማዕቀፍ አለመኖር በወንጀሉ ዙሪያ ያለው አረዳድ የተለያየ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ እነዚህ ስምምነቶች ሀገራት የሽብር ድርጊትን ለመከላከልና ለመቅጣት ህግ ማውጣት እንዳለባቸዉ፣ ለአፈጻጸሙም ትብብር ሊኖር እንደሚገባ እና ልዩ ትኩረት የመስጠት ግዴታ እንደተጣለባቸው ያስረዳሉ፡፡