Latest Posts from ✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠ (@betgubae) on Telegram

✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠ Telegram Posts

✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠
በዚህ ቻናል በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በሰንበት ትምህርት ቤት የሚሰጠውን ተከታታይ ትምህርት በጉባኤ ተገኝተው መማር ላልቻሉ በሃገር ውስጥም ከሃገራችንም ውጪ ለሚኖሩ ምዕመናን መማማሪያ የተከፈተ ነው።
t.me/betgubae

የፌስቡክ ኣድራሻዬንም ይጎብኙ https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71
8,188 Subscribers
915 Photos
12 Videos
Last Updated 06.03.2025 02:30

Similar Channels

የአብነት ት/ቤት
18,177 Subscribers
የአባቶች ምክር
7,380 Subscribers
Book club
3,735 Subscribers

The latest content shared by ✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠ on Telegram

✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

28 Dec, 03:25

4,102

✥✥✥ ማዳኑ ይደንቃል ✥✥✥

#እሳትን_አጥፎቶ_ማዳን_ይቻላል_እሳቱ_ሳይጠፋ_በነበልባል_ውስጥ_ግን_ማዳኑ_ይደንቃል!!!

በዚህም « ንጉሡ ናቡከደነጾር ተደነቀ ፈጥኖም ተነሣ፤ አማካሪዎቹንም፦ሦስት ሰዎች አስረን በእሳት ውስጥ ጥለን አልነበረምን ብሎ ተናገራቸው። እነርሱም፦ንጉሥ ሆይ፥ እውነት ነው ብለው ለንጉሡ መለሱለት። ፤ርሱም፦ እንሆ፥ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎች አያለኹ፤ ምንም አላቈሰላቸውም፤ የአራተኛውም መልክ የአማላክን ልጅ ይመስላል ብሎ መለሰ።» (ት ዳን ፫)

➛ በእርግጥም ነው ። ስሙ ድንቅ መካር ፣ ኃያል አምላክ ፣ የዘላለም አባት ፣ የሰላም አለቃ የተባለው አምላካችን የእርሱ የባሕርይ ገንዘቡ የሆነውን ድንቅነት እና "ኤል (አምላክ)" የተባለው ስሙም በስማቸው ሆኖላቸዋልና ዘወትር ድንቅ ያደርጋሉ። { ት.ኢሳ 9 ፥ 6 / ዘጸ 23 ፥ 21 }

ቅዱስ ገብርኤል ሆይ እኛንም ጠብቀን🤲

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

25 Dec, 17:07

4,099

እውነት አርነት ያወጣችኋል

" ጌታ ኢየሱስም ያመኑትን አይሁድ እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀመዛሙርቴ ናችሁ፤ እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል» አላቸው/ዮሐ.8፡31/፡፡ "

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «እውነት አርነት ያወጣችኋል» እያለ የሚናገራቸው አይሁድ «የአብርሃም ዘር ነን ለአንድም ስንኳ ከቶ ባሪያዎች አልሆንም፤ አንተ፡- አርነት ትወጣላችሁ እንዴት ትላለህ?» በማለት በባርነት መኖራቸውን መቀበል አልፈለጉም ነበር።

አይሁዳውያን የአብረሃም ዘር መሆናቸው እውነት ቢሆንም ይህ ግን የሚያሳፍራቸው እንጂ የሚያስመካቸው አልነበረም የአብርሃምን ሥራ በመሥራት ሳይሆን የአብርሃም ዘር በመሆናቸው ብቻ በከንቱ ይመኩ ነበር ። አስቀድሞ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ " የአብርሃም ልጆች ነን በማለት ብቻ የምትመኩ አይምሰላችሁ " (ማቴዎስ 3፥9) በማለት የተመከሩ ቢሆኑም እውነትን ለመቀበል ግን አልፈቀዱም። የሚደንቀው ስለ አብርሃም ከመናገር ውጪ የራሳቸውን የጽድቅ ሥራ በጭራሽ አይጠቅሱም የላቸውምና።
.
-> ጌታችንም " ለማንም ባሪያዎች አልነበርንም " ለሚለው ለአይሁድ ንግግር 215 ዐመት በግብፅ ፣ 70 (80) ዐመት በባቢሎን በመሰለው ጊዜ ሁሉ በባርነት የነበሩ መሆናቸው ሊያስታውሳቸው ይችል ነበር ነገር ግን እርሱ ሁሉን ዐዋቂነቱን በመግለጽ እነርሱ በማሳፈር ለራሱ ክብርን ለማግኘት የሰው ባሪያዎች መሆናቸውን ሊያሳይ ሳይሆን ለመዳናቸው፣ ለጥቅማቸው የሚሆን እውነት ወደማወቅ ሊስባቸው ፈልጎ «እውነት እውነት እላችኋለሁ ኃጢአት የሚያደርግ ሁሉ የኃጢአት ባሪያ ነው» /ዮሐ.8፥30-38/ በማለት የኃጢአት ባሪያዎች መሆናቸውን አሳወቃቸው ይህም ባርነት እግዚአብሔር ብቻ ነፃ የሚያወጣበት እጅግ አስከፊ የሆነ ባርነት ነው።

በእርግጥ ዛሬም እንደ አይሁድ ባርነትን እና ነጻነትን በሥጋ ብቻ የሚመዝኑ ለኃጢአት ባርነት እስራት ምንም የማይሰማቸው የሥጋን ባርነትን እጅግ ከመፍራት፣ ከማፈራቸው፣ ካለመፈለጋቸው የተነሳ ለኃጢአት ባርነት አስር ሺህ ጊዜ ባሪያዎች መባልን የሚመርጡ ብዙ ናቸው። እንዲሁም ክህነት፣ ሊቅነትን፣ ሰባኪነትን፣ ዘማሪነትን፣ አስቀዳሽነትን፣ ገዳም ተሳላሚነትን--- እነዚህን የመሰሉትን ብቻ ገንዘብ በማድረግ መመካታችን ባሪያዎች ከመሆን አያድነንም።

- እነዚህ አይሁድ «ያመኑ አይሁድ» እንደነበሩ ተብለዋል /ቊ.30-31/፡፡ ይሁንና ከነበሩበት የኃጢአት ባርነት ገና አርነት ያልወጡ ስለነበሩ እውነተኛ አማኞች ነበሩ ለማለት አይቻልም/ቊ.34፣44/፡፡

ሰው አርነት የሚያወጣውን እውነት ጌታችን ሲናገር «እናንተ በቃሌ ብትኖሩ በእውነት ደቀመዛሙርቴ ናችሁ እውነትንም ታውቃላችሁ» ብሏል /ዮሐ.8፡31/፡፡ በእርግጥ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት፣ በመማርና፣ በማንበብ ደረጃ ብዙዎች አርነት የወጡ፣ እውነትን ያወቁ ፣ ደቀ መዛሙርቱ የሆኑ ይመስላቸው ይሆናል፤ ጌታችን ግን «እውነትን ታውቃላችሁ ....» የሚላቸው በቃሉ የሚኖሩትን ነው፡፡ ... ይቆየን

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

15 Dec, 10:21

4,813

✥✥✥ ቅድስት አርሴማ ✥✥✥

👉 ጥር 6 ልደቷ፣ መስከረም 29 እረፍቷ፣ ታህሳስ 6 ፍልሰተ አጽሟ ይታሰባል።


✥ እናታችን ከአባቷ ከቅዱስ ቴዎድሮስና ከእናቷ ቅድስት አትናሲያ በስዕለት ተወለደች ። ቤተሰቦቿ እግዚኣብሔርን በቅንነት ያገለግሉ ከነበሩ ከከበሩ ካህናት ወገን እንደነበሩ የገድሏ መጽሓፍ ይነግረናል ። ሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከቤተሰቦቿ በሚገባ የተማረች፤ የተማረችውንም በተግባር የተረጎመች፤ በጸሎት ሕይወት የምትተጋ ከቅዱሳት አንስት አንዷ ናት ።


✥ ቅድስት ኣርሴማ ፣ ሂርፕሲም (አርሜኒያዊት) እንዲሁም ሪሂፕሲም ፣ ሪፕሲም ፣ አርብሲማ ወይም ኣርሴማ ተብላ ትጠራለች። የትውልድ ሃገሯ ሮም ። እርሷ እና ባልደረቦችዋ የሰማዕትነት አክሊል በተቀዳጁበት አርሜንያ የመጀመሪያዎቹ የአርሜንያ ሰማዕታት እንደሆኑ ተደርገው ይታያሉ ።

👉 የሕይወት ታሪኳን ሊቃውንት በቅዳሴ አንድምታ ላይ የመዘገቡትን እነሆ፦

ዲዮቅልጥያኖስ መልከ መልካም ብላቴና ፈልጋችሁ ሥዕሏን ሥላችሁ አምጡልኝ ከዚያ በኋላ እሷን ታመጡልኝአላችሁ ብሎ ሠራዊቱን በያገሩ ሰደደ፤ ይህች አርሴማ ፸፪ (72) ያህል ደናግል ይዛ ከተራራ ላይ ወጥታ ተቀምጣለች፤ ኸያ ዓራቱ ደናግል፤ የቀሩት መዓስባን(ያገቡ) ናቸው፡፡

✥ እመ ምኔቲቱ አጋታ (Agatha(Ghana)) ትባላለች፡፡ እየፈለጉ ካለችበት ደረሱ፡፡ ሥዕሏን ሥለው ወስደው ሰጡት፡፡ መልካም ብላቴና አግኝታችሁልኛል፤ እስዋን አምጡልኝ አላቸው፡፡ እስዋም እንዳስፈለጋት አውቃ አርማንያ ወረደች፡፡

✥ እሱም ከዚያ እንደ ወረደች አውቆ የአርማንያ ንጉሥ ድርጣድስ ይባላል፤ እንዲህ ያለች ብላቴና ወዳገርህ መጥታለችና አስፈልገህ ስደድልኝ ብሎ ላከበት፡፡ ቢያስፈልግ አገኛት፤ ቢያያት እንደ ፀሐይ ስታበራ ዓያት፤ ይህችንማ ለራሴ ምን ይዤ ለሱ እሰድለታለሁ ብሎ እመ ምኔቲቱን/አጋታን/፦ ይህችን ብላቴና ለምኝልኝ ኣላት፡፡ አይሆንም ያልሁ እንደሆነ ነገር አጸናለሁ ብላ ይሁን አለችው፡፡ ኋላ ግን ለሰማያዊ መርዓዊ ለክርስቶስ አጭቸሻለሁና ይህ ርኩስ እዳያረክስሽ እወቂ አለቻት።

✥ ብላቴኖች ሰዶ አስወስዶ መልኳን አይቶ ብታምረው ተራምዶ ያዛት፤ ኃይል መንፈሳዊ ተሰጥቷታልና ጎትታ ከመሬት ወቃችው፡፡ ንጉሥ ነውና ቢያፍር በሰይፍ አስመታት፡፡ ከዚያ አያይዞ መላውን አስፈጅቷቸዋል፡፡ ሰይጣን አስቀድሞ ያልሆነ ስራ ማሰራት ኋላ ማጸጸት ልማዱ ነውና መልኳ ትዝ እያለው እህል ውሃ የማይቀምስ ሆነ፡፡

✥ ብላቴኖቹ ሲሞት እናያለን? ኣደን እንጂ ኃዘን ያስረሳል፤ ኣደን ይዘነው እንሂድ ብለው ይዘውት ሄዱ፡፡ በዚያ ባለበት ዕሪያ ሁኖ ቀርቷል፡፡ ማን ባዳነልን እያሉ ሲጨነቁ መልኣክ ለእኅቱ ከጎርጎርዮስ በቀር የሚያድንላችሁ የለም አላት፡፡ በሃይማኖት ምክንያት ተጻልቶት ከአዘቅተ ኲስሕ አስጥሎት ነበርና የሞተ መስሏቸው ደነገጡ፡፡

✥ /ለቅዱስ ጎርጎርዮስ ግን/ መልኣክ ላንዲት መበለት ነግሮለት አንድ ፥ አንድ እንኩርኩሪት እየጣለችለት ፲፭ (15) ዓመት ያህል ኑሯል፡፡ የኒህ ክርስቲያን አምላክ ጽኑ እንጂ ነው እንዳለ ብለው ገመድ ቢጥሉ መኖሩን ለማስታወቅ ገመዱን ወዘወዘው ሐብሉን ቢስቡት ከሰል መስሎ ወጥቷል፡፡


✥ ወንድሜን አድንልኝ ኣለችው፡፡ ያለበትን ታውቂውአለሽን አላት፡፡ አዎን አለችው፡፡ አስቀድሞ አጽመ ሰማዕታት ያለበትን ኣሳይኝ ብሏት አሳየችው፡፡ አጽመ ሰማዕታትን አስቀብሮ በዪ ውሰጂኝ አላት፡፡ ይዛው ሄደች፡፡ አንተ ባድንህ በፈጣሪዬ ታምናለህን አለው፡፡ ወኣድነነ ርእሶ ወኣንገሥገሠ ርእሶ ከመ ኦሆ ዘይብል ይላል፡፡ ግዕዛኑን(አዕምሮውን) አልነሣውም ነበርና ይሁን አለው፡፡ እንዳይታበይ ከእጁ ከእግሩ የእርያ ምልክት ትቶለት ጸልዮ አድኖታል፡፡ አስተማረው ኦሳመነው አጥምቀኝ አለው፡፡ ማጥመቅስ ሥልጣን ካላቸው ሂደህ ተጠመቅ፤ ለኔ ስልጣን የለኝም ኦለው፡፡ የአንጾኪያውን ሊቀ ጳጳስ አስመጥቶ ተጠምቋል፡፡ [መጽሐፈ ቅዳሴ ከቀድሞ አባቶች ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ንባብና ትርጓሜው፤ ሥርዓተ ቅዳሴ፤ ምዕራፍ ፪፤ ገጽ. 20 -21]::


✥ “ ድንግል እናታችን ቅድስት አርሴማን በምን እንመስላታለን? እርሷ በኣድማስ ላይ ተቀምጦ እንደሚያበራ እንቁ ናትና ክብሯ ብዙ ነው ። መድኃኒታችን ክርስቶስ በወንጌል እንዳለው "በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትምና ።" የሰማዕቷ ሕይወት በፊታችን እንደ ብርሃን ተገልጦ ይታያል ። ቅድስት አርሴማ እንደ ልጅ ወላጆቿን በመታዘዝ ደስ ያሰኘች ቡርክት ናት ። ቅድስት አርሴማ ይሕ ቀረሽ የማይሏት ውብ ናት ። ቅድስት አርሴማ ድንግል ናት ። ቅድስት አርሴማ ባሕታዊት ጻድቅ ናት ። ቅድስት አርሴማ ኃያል ሰማዕት ናት ። ” ( ገድለ ቅድስት አርሴማ )


✥ “ሰላም ለአርሴማ ቅድስት ከመ በቀልት ዘይመስል ቆማ ወዘከለላ ዘመንፈስ ግርማ ዘፈጸመት ገድላ በጻማ ወበመንግሥተ ሰማይ ዐቢይ ስማ”፡፡
(ገድሏን በሥቃይ የፈጸመች፤ የመንፈስ ግርማ የጋረዳትና ቊመቷ እንደ ዘንባባ የሚመስል ለምትኾን ለቅድስት ኣርሴማ ሰላምታ ይገባል፤ በመንግሥተ ሰማይም ስሟ ታላቅ ነው) /ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በተአምኆ ቅዱሳን/


✥ “ እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፥ ጽድቅን አደረጉ፥ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ፤ ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ። ” (ዕብ፲፩÷፴፫-፴፰)

✥ የሰማዕቷ የቅድስት አርሴማ አማላጅነት፤ ቃል ኪዳን ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ 

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

12 Dec, 04:11

4,455

በዐታ ለማርያም

እመቤታችን በኦሪት ወዳለው ቤተመቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ እንድትገባ እንድትኖር የተደረገበት ምክንያት ምንድን ነው?

1 - ለሊቀ ካህናት ክርስቶስ ቅድስተ ቅዱሳን እርስዋ መሆኗን ለማስረዳት ነው ።

- በኦሪት በነበረችው ቤተ መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ መግባት የሚችለው ሊቀካህኑ ብቻ ነበር ሊቀ ካህናት ክርስቶስ አንድ ጊዜ ለሚያቀርበው ዘለዓለማዊ መሥዋዕት ቅድስት ቅዱሳን እርስዋ መሆንዋን ለማስረዳት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን እንድትገባ ሆኗል።

2 - ለሰውነታችን መቅደስነት ቅድስተ ቅዱሳን እርስዋ መሆኗን ለማስረዳት ነው

- በኦሪት መቅደስ ባለች በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ሊቀ ካህናት ብቻ ይገባባት ነበር ፤ በቅዱስ ጳውሎስ አንደበትነት እናንተ የጌታ መቅደስ ናችሁ ለተባልነው ለእኛ ለሰውነታችን መቅደስነት ቅድስተ ቅዱሳን የሆነችልን እመብርሃን ናት ምክንያቱም እኛ ሁለችን የአምላክ ማደሪ ቤተ መቅደሶች ብንሆንም ነገር ግን ሊቀ ካህናት ክርስቶስ ከሰው ልጅ ሁሉ መርጦ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ያደረው በእርስዋ ላይ ነውና የሰውን መቅደስነት ሁሉ ወክላ ሊቀ ካህናት ክርስቶስን የክህነቱን ሥራ ይፈጽም ዘንድ ቅድስተ ቅዱሳን የሆነችልን እርስዋ ናት።

3 - አማናዊቷ ታቦት እርስዋ መሆኗን ለማስረዳት ነው ።

- ልዑል እግዚአብሔር ለሊቀ ነቢያት ሙሴ ታቦት ሠርቶ በቅድስተ ቅዱሳን እንዲያደርግ በዚያ ላይም ዘወትር ለእርሱ እና ለሕዝቡ እንደሚገለጽበት ነግሮት ነበር ነገር ግን ከዘመናት በኋላ ይህ የክብሩ መገለጫ የሆነው ታቦት ከቤተ መቅደሱ ቅድስት ቅዱስን ተለይቶ ቤተ መቅደሱ ያለ ታቦት ይኖር ነበር እግዚአብሔር የሚገለጹበት ታቦት ያስፈልግም ነበር ስለዚህም እንደ ቀድሞ የረድኤት ያይደለ በኵነት ለፍጥረቱ ሁሉ የሚገለጽባት አማናዊቷ ታቦት እርስዋ መሆንዋን ለማስረዳት የታቦት ማደሪያ ወደ ነበረው ቅድስተ ቅዱሳን አማናዊቷ ታቦት እንድትጋባ ሆነ።

✍️አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

29 Nov, 03:01

6,856

✥✥✥ ኅዳር ጽዮን በአክሱም ✥✥✥

➙ አክሱም ማርያም ጽዮን በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ መሠረታቸው ስትሆን ከተማዋም የኢትዮጵያ ሥልጣኔ መነሻ ናት፡፡ አክሱም በሕገ ልቡና የጸናች፣ ሕገ ኦሪትን የፈጸመች፣ በሕገ ወንጌል ያመነች ናት፡፡ ቅዱስ ዳዊት «ሕግ ይወጽእ እምጽዮን፤ ከጽዮን ሕግ ይወጣል» ሲል የተናገረው ቃለ የተገናኘላት ናት፡፡

➙ በዓለ ልደትን በላሊበላ፣ ጥምቀትን በጎንደር፣ ኅዳር ጽዮንን በኣክሱም ጽዮን ሲያከብሩት ልዩ የሆነ ሥርዓት ስለሚቀርብባቸው ምእመናን መንፈሳዊ ደስታ ይሰማቸዋል፡፡

👉 ኅዳር 21 ቀን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል ነው ብለን በተለየ መልኩ የምናከብርበት ምክንያት፡-

1. በብሉይ ኪዳን ታቦተ ጽዮን የፈጸመችውን ልዩ ልዩ ገቢረ ተአምራትን ለማሰብ

2. ቀዳማዊ ምኒልክ ከዓሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል የበኲር ልጆች ጋር ሊቀ ካህናቱን አዛርያስንና ታቦተ ጽዮንን ይዞ አክሱም የደረሰበት ዕለት በመሆኑ

3. በሦስት መቶ ሠላሳ ዓመተ ምሕረት በኣብርሃ ወአጽብሃ ዘመነ መንግሥት ክርስትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሃይማኖት ይሁን ተብሎ ዐዋጅ የታወጀበት

4. ነቢዩ ዘካርያስ በተቅዋመ ወርቅ ምሳሌ ራእይ ያየበት፣ ነቢዩ ሕዝቅኤል የተቆለፈች ቤተ መቅደስን፣ ዕዝራ የቅድስት አገር ምሳሌ ራእይ ያዩበት

5. አብርሃና አጽብሃ በወርቅና በዕንቍ ያሠሩት ባለ አሥራ ሁለት ክፍል ቤተመቅደስ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት

➙ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም እና በቃል ኪዳኑ ታቦት መካከል ጥልቅ የሆነ ምሥጢራዊ ትምህርት አለ፡፡ /ዘፀ. 25÷9-20/፡፡ ይህቺ የቃል ኪዳን ታቦት በደብተራ ኦሪት በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ የኖረች፣ የዮርዳኖስን ባሕር የከፈለች /ኢያ. 3÷14-17/፤ ቅጽረ ኢያሪኮን ያፈረሰች /ኢያ 6÷1-21/፤ ዳጎን የተባለ የፍልስጥኤማውያንን ጣዖት የቆራረጠች /1ሳሙ 5÷1-5/፤ በድፍረት ሊነካ የሞከረውን ኦዛን የቀሰፈች /1ሳሙ 6÷6/፤ በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ተቀምጣ ቤቱን በበረከት የመላች /2ሳሙ 6÷12/፣ ዳዊት የዘመረላት /2ሳሙ 6÷14/፤ ጠቢቡ ሰሎሞን በቤተ መቅደስ በክብር ያኖራት/1ነገ 8÷1/፤ የእግዚኣብሔር የክብር መገለጫ ናት፡፡
በታቦተ ጽዮን እና በዘመነ ሐዲስ በተገለጠችው በቅድስት ድንግል ማርያም መካከል ያለውን ረቂቅ እና ድንቅ ምሥጢራዊ ንጽጽር አስመልክቶ ሦርያዊው ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም፤ «ታቦት በወርቅ ልቡጥ እምኩለሔ ዘግቡር እምዕፅ ዘኢይነቅዝ፤ ከማይነቅዝ እንጨት የተቀረጸ በው ስጥ በአፍአ በወርቅ የተለበጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሐ ጠባይዕ ሳያድፍባትና የቅድስና ባሕርይ ሳይጎድፍባት በማየት፣ በመስማት፣ በመዳሰሰ፣ በማሽተት አንዳችም እድፍ ጉድፍ ሳያገኛት በንጽሕናና በቅድስና ጸንታ በኃጢኣት ሳትለወጥ ኖራለች፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም፤ «አልብኪ ነውር ወኢምንትኒ ላዕሌኪ፤ ምክንያታዊ ነውር ኃጢአት የሌለብሽ የኃጢአት ሸታ ያልደረሰብሽ ንጽሕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና ክብርት በልዕልና ኣንቺ ነሽ» /መኃ 4÷7/ ሲል ተናግሯል፡፡

➙ ታቦተ ጽዮን የቃለ እግዚአብሔር ማደሪያ እንደሆነችው ቅድስት ድንግል ማርያምም ለአካላዊ ቃል ለእግዚአብሔር ወልድ ማደሪያ ሆናለች፡፡ ይኽንንም ቅዱስ ኤፍሬም ሲያስረዳ፤ «ኮንኪ ታቦቶ ለፈጣሬ ሰማያት ወምድር ፆርኪዮ በከርስኪ ተሰዓተ አውርኃ አንቲ ማእምንት ለዘኢያገምርዎ ሰማያት ወምድር፤ ድንግል ማርያም ሆይ ሰማይና ምድርን ለፈጠረ አምላክ ለእርሱ ማደሪያ ሆንሽ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀንሸ ቻልሽው ተሸከምሽው ሰማይና ምድር የማይወስኑትን ለመወሰን የታመንሽ አንቺ ነሽ» ብሎ ተቀኝቶላታል፡፡

➙ ስለሆነም ከብሉይ ኪዳን እስከ ሐዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ራሱን የገለጠበትን የቸርነት በዓል እግዚአብሔር በፈቀደልን ቦታ ሆነን ስናከብር ከእኛ የሚጠበቀውን በጎ ነገር እያሰብን በተግባርም እየገለጥን ከበዓሉ ረድኤትና በረከት ተሳታፊ እንሆን ዘንድ የእግዚአብሔር ቸርነት የእናቱ የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡

የቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እና ምልጃ አክሊልና ጉልላት በሆነው በእናታችን በወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት ሁላችንንም ይማረን፡፡ አሜን።
✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ

https://t.me/+VBt2ld_HeykCaELL (ቴሌግራም ቻናል )

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

27 Nov, 03:59

4,668

✥✥✥ የጽዋ ማኅበር ✥✥✥

➙ ጥያቄ፡- ስለ ጽዋ ማኅበር ትርጉም ማን እንደጀመረውና መቼ እንደተጀመረ በተጨማሪም አባላቱ ብቻ የሚቀምሱት ሰአልናክ የሚባል አለ ብዙዎች ከሥጋወደሙ ጋር አንድ ነው ይላሉ እውነት ነው ወይ ?


➙ መልስ፡- ጽዋዕ የሚለው ሁሉት ትርጉም አለው በቁሙ ኩባያ ዋንጫ የመጠጥ መሣሪያ የሚል ትርጉም አለው፡፡ በጽዋ ተቀድቶ የሚሰጥም መጠጥ ጽዋ ይባላል፡፡ ማኅበር ማለት ደግሞ‹‹ ኀብረ ›› አንድ ሆነ ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ነው፡፡ በአንድ ላይም ጽዋ ማኅበር ማለት በጽዋ ለመጠጣት የሚሰባሰቡ የምእመናን አንድነት ማለት ነው፡፡

- በሌላም በኩል ጸውዓ ተጣራ ተብሎ ይተረጎማል በዚህም የጽዋ ማኅበር በጌታችን እና በቅዱሳን ስም የሚጠራ እና የሚዘከሩበት መሆኑን ያስረዳል

✥ ጽዋ ማኅበር ምእመናን በወር ወር ተራቸውን እየጠበቁ እየደገሱ የሚያበሉበት እንዲሁም ችግረኞችን የሚረዱበት ሥርዓት ነው፡፡ በጽዋ ማኅበር መሳተፍ በረከትን ያሰጣል ( መዝ ፪÷፰ ፥ ምሳ፲÷፯ ) እንዲሁም በማቴ ፲÷ ፵፪ ላይ እንደተገለጸው ዋጋን አያጠፋም፡፡


✥ ማኅበሩ በጌታችን ፣ በእመቤታችን፣ በቅዱሳን፣ መላእክት፣ በጻድቃንና በሰማዕታት ዕለት በቤተክርስቲያን ዙሪያ ወይም በምዕመናኑ ቤት የሚካሄድ ነው፡፡


✥ የአንድ ጽዋ ማኅበር አባላት ብዛት አሥራ ሁለት መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም በዓመት ውስጥ ያሉት ወራት አሥራ ሁለት በመሆናቸው ሁሉም አባል ተራው እንዲደርሰው ነው፡፡ ከአሥራ ሁለት በላይ ከሆኑ ግን ድርብ/ደባል/ በሚባለው አከፋፈል መሰረት በወር ውስጥ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ሆነው በመመደብ ተራቸውን እንዲያወጡ ይደረጋል፡፡

#የጽዋ_ማኅበር_አመሰራረት_ትውፊታዊ_ባህልን_የተከተለ_ነው፡፡


✥ በዘመነ ሥጋዌ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በኣንድነት የፍቅር ማዕድ / አጋፔ / ይመገቡ ነበር፡፡ ኋላም ቅዱሳን ሐዋርያት ከጌታ ዕርገት በኋላ ካመኑና ከተጠመቁ ክርስቲያኖች ጋር በአንድነት ኑሯቸውን እንዳደረጉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ( የሓዋ.ሥራ ፪÷፵፬-፵፯ )

✥ በዘመነ ሰማዕታት ግን ይህ ሁኔታ በአብዛኞቹ ክርስቲያኖች ተረስቶ ነበር፡፡ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ግን ይህ ትውፊት በአባቶታቻችን ጸሎት ብርታት ባህሉ ወጉ ሥርዓቱ ሳይፋለስ ተጠብቆ ለትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ ቆይቷል፡፡

✥ የቤተክርስቲያን ታሪክ እንደሚነግረን በኢትዮጲያ የመጀመሪያው የጽዋ ማኅበር መሥራች ቅዱስ ማቴዎስ ሲሆን በ40 ዓመተ ምህረት ሲሆን ማኅበረ ደጌ ይባላል።
በመቀጠልም በአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን በ330 ዓ.ም በአክሱም ‹‹ማኅበረ ጽዮን›› በማለት ተመሥርቶ የነበረ ሲሆን ቆይቶ ‹‹ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊ›› ተባለ በመጨረሻም ‹‹ጽዮን ማርያም›› በመባል ስሙ ሊለወጥ
ችሏል፡፡


✥ በ14ኛው መ/ክ/ዘ አፄ ዘርዓያዕቆብ ሕዝቡን በሃይማኖቱ የበለጠ ለማጽናት በማሰብ በቅዱሳንና በእመቤታችን ስም ማኅበር እንዲጠጣ ሕግ አወጡ፡፡


✥ ቀጥሎም በ16ኛው መ/ክ/ዘ ማኅበረ ሰላም መድኃኔዓለም የተባለ በአቡነ መብዓጽዮን የተቋቋመ ማኅበር እንደነበር የቤተክርስቲያን ታሪክ ይነግረናል፡፡


✥ ማንኛውም የቤተክርስቲያን ሥርዓት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት ያለው ነው፡፡ ጽዋ ማኅበርም ከነዚህ አንዱ ሲሆን በጽዋ ማኅበር የሚደረጉ ሥርዓቶች በሙሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ናቸው፡፡

ለምሳሌ፡- ማኅበሩን በሊቀ መንበርነት ለመምራት በማኅበሩ አባላት ከማኅበሩ የሚመረጠው/የምትመረጠው/ አባል ሙሴ በመባል ይጠራል/ትጠራለች/ ይህም ምሳሌነት አለው፡፡ሙሴ ለእሥራኤል ዘሥጋ መሪ ነበር የማኅበሩ ሙሴም እሥራኤል ዘነፍስ ለተባሉ ክርስቲያኖች መሪ መጋቢ ነው።

➙ ሙሴ መና አውርዶ ደመና ጋርዶ ውኃ ከድንጋይ አፍልቆ እሥራኤልን እንደመገበ ሁሉ ማኅበረ ሙሴውም በአገልግሎት ዘመኑ የጽዋ ወንድሞቹንና እኅቶቹን መንፈሳዊ ምክር ይመክራቸዋል የፍቅር ምልክት የሚሆን ማዕዱን በክርስቲያናዊ ሥነ-ሥርዓት ይመግባቸዋል።

➙ ሙሴ በእግዚአብሔር ፈቃድ ለማገልገል እንደተሾመ ሁሉ ማኅበረ ሙሴውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ወንድሞቹንና እኅቶቹን ለማገልገል የሚሾም ነው፡፡


✥ ሙሴው/ይቱ በችግር ምክንያት የቀሩ እንደሆነ የእነርሱ ምትክ የሚሆን ግልገል ሙሴ የሚባል የማኅበሩ አባል ተክቶ ሥራውን እንዲሠራ ይደረጋል፡፡ ሙሴውን/ይቱን ለማገዝ ከማኅበሩ በፈቃደኝነት የሚመረጡ ሰዎች/አባላት/ ደርገ ሙሴ ይባላሉ፡፡ ሙሴው/ይቱ ከተመረጠ/ጠች በኋላ የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናሉ ከእነዚህም መካከል አዲስ አባል ወደ ማኅበሩ ለመግባት በጠየቀ ጊዜ ከማኅበሩ ጋር በመማከር ፈቃድ መስጠት ከማኅበሩ አባላት መካከል የታመመ ወይም ሌላ እክል የደረሰበት ካለ ለማኅበሩ ነግሮ እርዳታ መሰብሰብ ኣብረውት/ዋት ከሚሰሩት ጋር በመሆን የማኅበሩን ሥነ-ሥርዓት ማስከበር በሚሰበሰቡበት ቀንም ጠቃሚ ምክር መስጠት ምእመናኑ ወደየቤታቸው ከመመለሳቸው በፊት ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት የባለተራዎቹን ስም በመጥራት ማስተዋወቅ የሚሉት ይገኙበታል፡፡


✥ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በጽዋ ማኅበር የአንድነታቸውና የፍቅራቸው መገለጫ የሆነ ሰአልናክ የሚባል የፍቅር ምግብ/ አጋፔ/ አለ፡፡ ሰአልናክ ከምግብ በፊት የሚቀመስ ሲሆን ለዚህ ሥርዓት መሠረት/ምንጭ/ የሚሆነን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴ ፲፬.÷፲፯-፳ ላይ አምስቱን እንጀራ ሁለቱን ዓሣ ባርኮ ለአምስት ገበያ ሕዝብ መመገቡ ነው፡፡


✥ ሰአልናክም የፍቅር ምግብ ነው ነገር ግን እንደ ቅዱስ ቍርባን ይቆጠራል ማለት ግን ታላቅ ስህተት ነው ምክንያቱም ኅብስቱና ወይኑ አማናዊ የጌታችን ሥጋና ደም ሆኖ የሚለወጠው በሥልጣነ ክህነት በቅዳሴ ጊዜ በሚጸለይ ጸሎት እንጂ በጽዋ ማህበር ላይ በሚጸለይ ጸሎት አይደለምና ነው፡፡


✥ በመጨረሻም ጽዋ ማኅበር መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረገ ሥርዓት እንደመሆኑ የራሱ የሆኑ ዓላማዎች አሉት ከነዚህም ውስጥ በማቴ ፲÷፵፪ ላይ ካለው በረከት ተካፋይ ለመሆን፣ ቅዱስ ቃሉን ለመማማር፣ ስለሃይማኖታቸውና ስለቤተክርስቲያናቸው ለመወያየት፣ በሃገርና በወገን ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ተመካክሮ ለማቃለል እንዲሁም ልባዊ ፍቅርን ለማጽናት እንጂ በልተን ጠጥተን ሥጋዊ ጨዋታ ተጫውተን ብቻ ለመለያየት አይደለም፡፡

➙ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ዓላማውን ተረድተን ሥርዓትና ወጉን ጠብቀን ለቅዱሳን የተገባላቸውን ቃልኪዳን እንድናገኝ በቸርነቱ ይርዳን፡፡ ይቆየን

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

25 Nov, 17:56

3,782

✥✥✥ በዓለ ልደት በዘመነ ዮሓንስ ✥✥✥

ጥያቄ ፩ ፦ በዘመነ ዮሓንስ በዓለ ልደት በታህሳስ 28 መከበሩ ስለምንድን ነው?

ጥያቄ ፪ ፦ በዘመነ ዮሓንስ በዓሉ በታህሳስ 28 ከሆነ የጾሙ ዕለት 43 ስለሚሆን ጾመ ጋድ አለን ?

ጥያቄ ፫ ፦ በዘመነ ዮሓንስ በዓለ ልደትን ታህሳስ 28 ማግሰኞ እና ሐሙስ ላይ አርፎ በዓሉን አክብረን ፥ ታህሳስ 29 የሚውለው ረቡዕ እና አርብ ቢሆን ይጾማልን?

👉 መልስ ፩፦ የምሥጢረ ሥጋዌ ዋናው ትምህርት ምሥጢረ ተዋሕዶ ነው ይህን የማኅፀኑን ምሥጢር ቊጥሩን ለመጠበቅ ነው። መጋቢት29 ቀን ቃል ሥጋ የሆነበትና በድንግል ማኅፀን የተፀነሰበት ዕለት ነው። ከዚህ ከመጋቢት 29 ቀን ጀምሮ ወንድ ልጅ በእናቱ ማኅፀን የሚቆይባቸውን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀናት (275 ቀናት) ስንቆጥር ጳጉሜን ጨምሮ ዕለተ ልደቱ ታኅሣሥ ፳፱ ቀን ላይ ይውላል።

- ኣደማመሩን ከተመለከትን ከመጋቢት 29 ጀምሮ እስከ ነሓሴ 30 ድረስ 151 ዕለት ይሆናል፣ ጳጉሜ 5 ዕለት፣ ከመስከረም እስከ ታህሳስ 29 ድረስ 119 ዕለት ነው ኣንድ ላይ ስንደምረው 151+ 5 + 119= 275 (275 ማለት 9 ወር ከኣምስት ቀን ማለት ነው) ይህ ስሌት በዘመነ ማቴዎስ ፣ በዘመነ ማርቆስ እና በዘመነ ሉቃስ ሲሆን ነው። ስለዚህም መጋቢት 29 ቀን የተፀነሰው ጌታችን ከኃጢአት በቀር የሰውነትን ሥራ ሁሉ ፈጽሟልና ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በእናቱ ማኅፀን ቆይቶ ታኅሣሥ 29 ቀን በቤተልሔም ዘይሁዳ ተወለደ።

👉 በዘመነ ዮሓንስ ግን በ 3 ዓመት ( ማለትም በሉቃስ ዘመን ) ጳጒሜን 6 ስለምትሆን ለቀጣዩ ዓመት ማለትም በዮሓንስ ዘመን ልደት ታኅሳስ 28 ይሆናል :: በዘመነ ዮሐንስ ታኅሣሥ 28 የሆነበት ምክንያት ዘመነ ሉቃስ ጳጉሜን 6 ስለሚሆን ጌታ ደግሞ የተፀነሰው መጋቢት 29 ቀን ነው ከዚያ ከመጋቢት 29 ጀምሮ ያሉትን ቀናት ብንቆጥር እስከ ታኅሣሥ 28 ቀን 275 ቀን (9 ወር ከ 5 ቀን) ስለሚሆን ነው::

- ኣደማመሩን ከተመለከትን ከመጋቢት 29 ጀምሮ እስከ ነሓሴ 30 ድረስ 151 ዕለት ይሆናል፣ ጳጒሜን 6 ዕለት፣ ከመስከረም እስከ ታህሳስ 28 ድረስ 118 ዕለት ነው ኣንድ ላይ ስንደምረው 151+ 6 + 118= 275 (275 ማለት 9 ወር ከ5 ቀን ማለት ነው)
እስከ ታህሳስ 29 ግን ብንቆጥረው 276( 9 ወር ከ6 ቀን ይሆንብናል) ይህም የማኅፀኑን ምሥጢር ያፋልስብናል።

👉 በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ኣስተምሮ የልደት በዓል የሠግር 28 ቀንና የአዘቦቱ 29 ቀን ይውላል በማለት ይገልጹታል።
“ሠግር” ማለት ተሻጋሪ፥ ዘላይ ማለት ነው። ዓመቱ 365 ቀናት መሆኑ ቀርቶ 366 ቀን ሲሆን ወይም ጳጒሜ 5 ቀናት መሆኗ ቀርቶ 6 ቀን ስትሆን ማለት ነው። ይህንን ምዕራባውያን "Leap Year" ( “ዝል” ዘላይ ዓመት) የሚሉት ነው።

ጳጒሜን በዘመነ ሉቃስ 6 ቀናት ስትሆን ዘመነ ዮሓንስ የሚጀምርበትን፥ መስከረም 1ን፥ በኣንድ ቀን ማዘግየቷን ነው። ኣንድ ቀን ታዘልለውና እንደሌሎቹ ዓመታት በ1 መጀመሩን ትቶ መስከረም 2 ሊሆን በሚገባው ቀን ይጀምራል። በኣዘቦት ዓመታት (ዘመነ ማቴዎስ፣መ ማርቆስ፣ ሉቃስ) መስከረም 2 ሊሆን የሚገባውን ቀን በዘመነ ዮሓንስ ግን መስከረም 1 ያደርገዋል። መስከረም ኣንድ በኣንድ ቀን ዘግይቶ ከጀመረ (ከባተ) ፥ ወራቱ ሁሉ (ታኅሣሥን ጨምሮ ማለት ነው) አንድ ቀን እያሳለፉ መጀመር (መባት) ግድ ይሆንባቸዋል። ልደት ግን ኣብሮ ኣይዘገይም ማለትም 9ወር ከ5 ቀን ማለፍ ስለሌለበት ይህንን የማኅፀኑን ቊጥርን ይጠብቃል። ስለዚህ በሠግር ዓመት ቀደም ብሎ በታኅሣሥ 28 ቀን ይውላል። የሠግር 28 ቀንና የአዘቦቱ 29 ቀን ይውላል ማለታቸው ስለዚህ ነው።

👉 መልስ ፪ ፦ በዘመነ ዮሓንስ በዓሉ በ ታህሳስ 28 ከሆነ የጾሙ ዕለት 43 ስለሚሆን ጾመ ጋድ አለን ? ቢሉ አዎ አለ መኖሩም የሚታወቀው በዚህ ዘመን ልደት (ታህሳስ 28) በረቡዕ እና አርብ ቢውል እንደሌሎቹ 3ቱ ዘመናት ፍስክ ሆኖ የሚበላ በመሆኑ አስረጂ ነው።

- በተጨማሪም የዘመነ ዮሓንስን ጾመ ጋድ በ3ቱ ዓመታት (በማቴዎስ በማርቆስ በሉቃስ) ጾመ ጋድ ባሉት ትርፍ ሰዓታት ጾሙን ስለምንጾም ነው። ይህ ማለት የማቴዎስ የማርቆስ የሉቃስ የልደት ጋድን ከጾም መደበኛ ሰዓት (9 ሰዓት) አትርፈን ነው የምንጾመው በዚህ የሦስቱ ዓመታት ያሉት አትርፈን የጾምናቸው ስንደምር ለዘመነ ዮሓንስ ጾመ ጋድ ይሆናሉ ማለት ነው።

👉 መልስ ፫ ፦ የልደት በዓል በየዓመቱ ታህሣሥ 29 ዕለት ሲሆን፤ በዘመነ ዮሓንስ ግን የዘመነ ሉቃስ ጳጉሜን ስድስት ዕለት ስለምትሆን ልደቱን ታህሣሥ 28 ዕለት ይከበራል። ነገር ግን በ29 የጌታችን ልደት መታሰቢያነቱ አይቀርም። ለምሳሌ በዘመነ ዮሓንስ 28 ( ማግሰኞ) ልደቱን ቢከበር በነጋታው በ29(ረቡዕ) የልደቱ መታሰቢያነት እንዳለ ሆኖ ዘመነ ዮሓንስ እና ረቡዕ ስለሆነ ግን እንጾማለን( ይጾማል)።

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተሰፋዬ

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

24 Nov, 13:25

3,539

አርባው ዕለታት የነቢያት ጾም ሲሆን ከቀሩት ከ4ቱ ሦስቱ ዕለታት 2 ምክንያቶች በማሰብ የምንጾማቸው ናቸው፦


  ①  ስምዖን ጫማ ሰፊው (አብርሃም ሶሪያዊ) የጾሙትን ጾም ለማሰብ ነው፡፡ በአገሩ ያሉ አሕዛብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ‹‹ የሠናፍጭ ቅንጣት ታህል እምነት ቢኖራችሁ ይህንን ተራራ ከዚህ ተነቅለህ ወዲያ ሂድ ብትሉት እንዳላችሁት ይሆንላችኋል ›› ይላል እንግዲያውስ ይህንን በተግባር ያሳዩንና እኛም በእነርሱ እምነት እንመን በማለት ከአገሩ ንጉሥ ዘንድ በመቅረብ ሊቀ ጳጰሱን አብርሃምን ጠየቁት አባታችንም ሦስት ዕለታትን እንዲሰጡት ነግሯቸው ወደ እመቤታችን ሥዕል ፊት ቀርቦ ይህንን ተኣምር ታደርግለት ዘንድ ተማጸናት ተለማኝቱም ይህን ድንቅ ተአምር ይፈጸምልህ ዘንድ ምን ማድረግ እንዳለብህ የሚያስረዳህ ስምዖን የሚባል ሰው ኣለ ከመንገድ ዳር ተቀምጦ ጫማ ሲሰፋ ታገኘዋለህ አለችው፡፡ አባታችንም ወደ ርሱ ሄዶ የሆነውን ሁሉ ነገረው ቅዱስ ስምዖን ግን ‹‹ እመቤቴ ሆይ እኔነቴን ስለምን ገለጥሽኝ በዚህ መኖሬን አልፈቀድሽውምን እንግዲያውስ ትዕዛዝሽን እፈጽማለሁ በዓቴን ግን ዕለቃለሁ ›› አለ ይህም ቅዱሳን ውዳሴ ከንቱን ስለማይወዱ ክብራቸው በተገለጠበት ቦታ ስለማይኖሩ ነው፡፡ በመቀጠልም ሊቀ ጳጳሱን ሦስት ቀን ያህል እንጹም ሦስተኛውም ቀን በተፈጸመ ጊዜ ህዝቡን ሰብስበህ በተራራው ሥር እግዚኦታ ታደርሳለህ ተአምሩም ይፈጸምልሃል በማለት ነገረው።

- እንደተነገረውም ከሦስት ቀን ጾም በኋላ ሕዝቡን ሰብስቦ እግዚኦታ ሲያደርስ ቅዱስ ስምዖንም ከመካከላቸው ሆኖ ‹‹ጌታ ሆይ የእነርሱ ክብር እንዲገለጥ ብለው አይደለም የአንተ ክብር እንዲገለጥ፥ አሕዛብም በኣንተ ያመልኩ ዘንድ ነውና እባክህን ስማቸው›› እያለ ይማጸንላቸው ጀመር ተራራው ከሥሩ ተነስቶ ክርስቲያኖችን ያስቸግር የነበረውን ባሕር ደፍኖላቸዋል በዚህም አሕዛብ አምነዋል ፤ በባህሩ ምክንያት ተለያይተው የነበሩ ክርስቲያኖችም ተገናኝተዋል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለ ድንቅ ተአምር የተፈጸመበት ጾም ስለሆነ ከነቢያት ጾም ጋር በአንድነት እንድንጾመው አባቶች አዘዋል፡፡

➁ ሐዋርያው ቅደስ ፊልጶስ ሐዋርያት ዓለምን ዞረው ለማስተማር ዕጣ ሲያወጡ ለፊሊጶስ ከወርቅ የተሠራ አሞራ የሚያመልኩ ሰዎች ያሉበት አገር ደረሰው ገድለ ሐዋርያት ላይ አፍራቅያ ይለዋል የአገሩን ስም ቱርክ አካባቢ የሚገኝ ነው፤ ወደ ከተማው ገብቶ ወንጌለ መንግስተ ሰማያትን ሰበከ ብዙዎችንም አሳመነ አጠመቃቸው፤ አቆረባቸውም፤ ቤተክርስቲያን ሠራላቸው፤ ካህንና ዲያቆንም ሾመላቸው፤ ልቡናን የሚያስደምም ድንቅ ድንቅ ተአምራትንም አደረገ፣ ብዙዎችንም እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ መለሰ። ወደ ሌሎች ብዙ አገሮችም ተዘዋውሮ የከበረ የወንጌልን ቃል በማስተማር ሰዎችን ወደ ሃይማኖት ሲጠራ ኖረ ብዙዎችንም ክብር ይግባውና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አሳመነ።

- ነገር ግን ጥቅማቸው የጎደለባቸው የጣኦት ካህናት ከንጉሡ ጋር ነገር ሠርተው አጣሉት ይዘው አሠሩት ጽኑዕ ሥቃይንም አሠቃዩት። እርሱ ግን ከዘለዓለም ሕይወት ስለ ምን ትርቃላችሁ? የነፍሳችሁንስ ድኅነት ለምን አታስቡም? ይላቸው ነበር። እነርሱም ልቡናቸው ደንድኗልና ብዙ መከራ ካጸኑበትና ካሠቃዩት በኋላ ኅዳር 18 ቀን ዘቅዝቀው ሰቀሉት፤ ነፍሱንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ። ሥጋውን በእሳት ሊያቃጥሉት በወደዱ ጊዜ ከእግዚአብሔር የተላከ መልአክ ከእጆቻቸው መካከል ነጠቃቸው እያዩትም ወስዶ ሠወረው። ይህንንም ተመክተው ስለገደሉት ተጸጽተው ያዘኑና ያመኑ ብዙዎች ቢጾሙና ቢጸልዩ ቢለምኑ ሰውን የሚወድ ቸር ይቅር ባይ ጌታችን ልመናቸውን ተቀብሎ በ፫ ቀን መልሶላቸው በፍጹም ደስታ አሳረፉት። ይህን ያዩ ሁለ ወደ እምነቱ ገቡ። ከሐዋርያው ፊልጶስም ሥጋ ታላላቅ የሆኑ ድንቅ ድንቅ ተኣምራት ተገልጠዋል። ደቀ መዛሙርቱ ግን ጾሙን ጀምረን አንተወውም ብለው እስከ ልደት በዓል ድረስ ጾመውታል። ስለዚህ ነገርም «ጾመ ፊልጶስ» ይባላል። ቁጥሩም 43 ይሆናል፡፡  44ተኛ ሁና የምትቆጠረው ጾመ ጋድ(ገሐድ) ናት።

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተሰፋዬ

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

23 Nov, 15:50

3,751

✥✥✥ አስማቲሁ ለጾም✥✥✥

👉 ጾሙ ከኅዳር እኩሌታ ጀምሮ የሚጾም ሲሆን ፍጻሜው ታህሳስ 29 በልደት በዓል ነው በዘመነ ዮሐንስ ግን ታህሳስ 28 የልደት በዓል ይከበራል። ይህን ጾም በዘመነ ብሉይ እና በዘመነ ሐዲስ ብዙ ቅዱሳን ጾመውታል በቤተክርስቲያናችንም ለጾሙ ከተሰጡት ስያሜዎች የተወሰኑትን እነሆ፦

1— ጾመ አዳም

ለአዳም የተነገረው ትንቢት ስለተፈጸመበት ይህንን ስያሜ አግኝቷል።
አዳም ዕፀ በለስን በልቶ ከገነት ከተባረረ በኋላ በፍጥረቱ ገዢ ኣድርጎ በገነት ያኖረኝን ፈጣሪዬን ትቼ የፍጡሩን ቃል ሰምቼ ትዕዛዝን አፍርሼ አሳዘንኩት ብሎ በፈጸመው በደል አዝኖ ተክዞ ፣ ጾመ ፣ ጸለየ ከልብ የሆነ ጸጸቱንም እንባውን በራሱ መፍረዱንም ዓይቶ እግዚአብሔር ተስፋ ድኅነት ሰጠው “በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድህክ ውስተ መርህብከ ወእትቤዘወከ በመስቀልየ ወበሞትየ - በአምስት ቀን ተኩል (ማለት ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ) ከሰማየ ሰማያት ወርጄ ከድንግል ማርያም ተወልጄ በፈቃዴ ተገፍፌ ተገርፌ በዕለተ ኣርብ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅዬ ሥጋዬን ቆርሼ ደሜን አፍስሼ ሞቼ ተነስቼ አድንሃለሁ” ብሎ ቃል ኪዳን ገባለት
አዳምም ‹‹በሐሙስ ዕለት›› ያለውን እንደ ተለመደው አቆጣጠር መስሎት እስከ ኣምስት ቀን ጠበቀ በኋላ ግን አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም በፈቃዴ ተገርፌ በዕለተ አርብ በመልዕልተ መስቀል ተሰቅዬ ሥጋዬን ቆርሼ ደሜን አፍስሼ ሞቼ ተነስቼ አድንኃለው እንዳለው ተረድቶ ይህን ተስፋ በመትክፍተ ልቡናው ተሸክሞ ይኖር ነበር፡፡

➙ ነጋዴ ስንቁን ይዞ እየበላበት ከዚህ እስከዚያ ያደርሰኛል እያለ እንዲጓዝ በአጸደ ሥጋ በአጸደ ነፍስም ሳለ ጌታ እንዲህ ብሎኛል እና ይምረኛል እያለ ተስፋውን ኣጽንቶ ሲጠባበቅ ኖረ ለልጆቹም ሁሉ ነገረ፡፡ ትንቢት ተነገረ ሱባዬ ተቆጠረ፡፡ ፭ (5) ሺህ ፭፻ (500) ዘመን ሲፈጸምም የማያደርገውን የማይናገር የተናገረውንም የማያስቀር ጌታ‹‹ ቀን ቢደረስ አንባ ይፈርስ›› እንዲሉ ከዘመን ዘመን ከወሩ ወር ከዕለታቱ ዕለት ከሰዓቱ ሰዓት ሳይጎል በጽኑ ቀጠሮ የአዳም የልጅ ልጅ ከምትሆን ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ ገላ ፬፡፬ ስለዚህ ጾሙ ለአዳም የተሰጠው ተስፋ የተቆጠረው ሱባዔ ስለተፈጸመበት ‹‹ጾመ አዳም›› ይባላል፡፡

2— ጾመ ነቢያት

ነቢያት የተናገሩት ትንቢት ስለተፈጸመበት ይህንን ስያሜ ኣግኝቷል፦
በየዘመናቱ የተነሱ ነቢያት እግዚአብሔር ወደፊት ሊያደርግ ያሰበውን በእምነት ዓይን እያዩ ምሥጢር ተገልጦላቸው የራቀው ቀርቦ የረቀቀው ገዝፎ እየተመለከቱ ትንቢት ተናገሩ፤ ያዩትን መልካም ነገር እንዲደርስላቸው ጾሙ ጸለዩ ፡፡

➙ ነቢያት ስለመወለዱ፣ ወደ ግብጽ ስለመሰደዱ፣ በባህረ ዮርዳኖስ ስለመጠመቁ ብርሃን በሆነው ትምህርተ ወንጌል ጨለማን ዓለም ስለማብራቱ ለሰው ልጆች ድኅነት ጸዋትወ መከራ ስለመቀበሉ እና ስለመስቀሉ ስለትንሳኤው ስለ እርገቱ እና ስለዳግም ምጽኣቱ ትንቢት ተናግረው ኣላቆሙም፤ ለአዳም የተሰጠው ተስፋ ተገልጦላቸው ለተናገሩት ትንቢት ፍጻሜ እንዲያደርሳቸው ፈጣሪኣቸውን ተማጽነዋል በየዘመናቸው ‹‹ አንሰእ ኃይለከ ፈኑ እዴከ›› እያሉ ጮኹ በጾምና በጸሎትም ተወስነውም ሰው የሚሆንበትን ጊዜ በቀናት፣ በሳምንታት፣ በወራት እና በዓመታት ቆጠሩ ለምሳሌ ነቢዩ ኤርምያስ ስለ ሥጋዊው ትንቢት በተናገር በ446 ዓመት ጌታችን ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆኖል ነቢያት ተስፋው በዘመናቸው ተፈጽሞ በዓይነ ሥጋ ለማየት ባይችሉም እግዚአብሔር ‹‹ አያደርገው አይናገር የተናገረውንም አያስቀር›› ብለው አምነው ከወዲሁ ተደሰቱ በዘመነ ሥጋዊ ቅርብ የነበሩት እነ ኢሳይያስ ጾሙ እንዴት መፈጸም እንዳለበት ተናግረዋል ትኢሳ 58፡1 በመሆኑ በጌታ ልደት ትንቢተ ነቢያት ስለተፈጸመበት ይህ ጾም ‹‹ጾመ ነቢያት›› ይባላል፡፡ የወልደ እግዚኣብሔርን ሰው መሆን ያስተማሩበት ስለሆነም‹‹ጾመ ስብከት ›› ይባላል፡፡

3— ጾመ ማርያም

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ይህን ጾም ጾማዋለች ፡፡ ይህም ቅዱስ ገብርኤል ወልደ አምላክን ያለ ሰስሎተ ድንግልና (ድንግልና ያለማጣት) በግብረ መንፈስ ቅዱስ ጸንሳ እንደምትወልደው ካበሰራት በኋላ እመቤታችን ትሁት ናትና ምን ሠርቼ እወልደዋለሁ ብላ ጌታን ከመውለዷ አስቀድሞ ጾማዋለችና ‹‹ጾመ ማርያም›› ይባላል፡፡

👉 ይህን ጾም ነቢያት እና ሐዋርያት ጾመውት በረከት አግኝተውበታል በመሆኑም የቤተ ክርስቲያን ኣባቶች ምእመናን በመጾም እንዲጠቀሙበት ሥርዓት ሠርተዋል፡፡ ይቆየን

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ

https://t.me/+VBt2ld_HeykCaELL (ቴሌግራም ቻናል )

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

20 Nov, 09:17

3,827

ኅዳር 11 የእመቤታችን እናት የቅድስት Uና በዐለ ዕረፍት መታሰቢያ ነው፡፡ ከበረከቷ ያሳትፈን🤲
መዝሙር ልጋብዛችሁ

ለልብሽ ተስፋ ናት ለዐይኖችሽ ማረፊያ
የማኅፀንሽ ፍሬ የላትም አምሳያ
በወለድሻት ንግሥት ደስ ይበልሽ ሀና
የልብሽ ፍላጎት መሻትሽ ነውና