Latest Posts from ✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠ (@betgubae) on Telegram

✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠ Telegram Posts

✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠
በዚህ ቻናል በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ በሰንበት ትምህርት ቤት የሚሰጠውን ተከታታይ ትምህርት በጉባኤ ተገኝተው መማር ላልቻሉ በሃገር ውስጥም ከሃገራችንም ውጪ ለሚኖሩ ምዕመናን መማማሪያ የተከፈተ ነው።
t.me/betgubae

የፌስቡክ ኣድራሻዬንም ይጎብኙ https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71
8,188 Subscribers
915 Photos
12 Videos
Last Updated 06.03.2025 02:30

The latest content shared by ✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠ on Telegram

✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

17 Jan, 18:58

4,269

✝️ የታቦታቱ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ መውረድ ከክርስቶስ ወደ ባሕር መሄድ ጋር እንዴት ተገናኘ?

👉 “ ያን ጊዜ ጌታ ኢየሱስ በዮሓንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ። (ማቴ ፫÷፲፫) እንደተባለው፦

ጌታችን ከተጸነሰባት ካደገባት ከናዝሬት ገሊላ ለመጠመቅ ወደ ዮርዳኖስ እንደሄ ታቦታትም ከማደሪያቸው ከመንበራቸው ተነስተው ወደባሕረ ጥምቀቱ ይሄዳሉ።

👉 “ ሕዝቡም ዅሉ ከተጠመቁ በዃላ ጌታ ኢየሱስ ደግሞ ተጠመቀ። (ሉቃ ፫÷፳፩) እንደተባለው፦

ጌታችን ከባሕረ ጥምቀቱ እንደደረሰ ኣልተጠመቀም ሕዝቡ ሁሉ ተጠምቀው ከጨረሱ በኋላ ነው የተጠመቀው ታቦታትም ወደ ባሕረ ጥምቀቱ እንደደረሱ ሳይሆን በተዘጋጀላቸው ቦታ ካረፉና ከቆይታ በኋላ ነው ሥርዓተ ጥመቀቱ ይፈጸማል።

👉 “ ባሕር ዓየች ሸሸችም፥ ዮርዳኖስም ወደ ዃላው ተመለሰ። ” (መዝ ፻፲፫፥፫) እንደተባለው፦

ጌታችን ወደ ዮርዳኖስ ለመጠመቅ ሲገባ ባሕረ ዮርዳኖስ እንደሸሸች እና ለሁለትም ተከፍላ እንደ ግድግዳ እንደቆመች (እንደተከተረች) ዛሬም ምዕመናን ከመጠመቃቸው በፊት ውኃ በተዘጋጀው ገንዳ ውስጥ ይከተራል በመቀጠልም ጌታችንም እንደተጠመቀ ምዕመናንም የመታሰቢያ ጥምቀትን ይጠመቃሉ።

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ 

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

17 Jan, 17:59

4,527

✥✥✥ጾመ ጋድ እና ሰንበት✥✥✥

፩፦ ጾመ ጋድ በሰንበት ከዋለ ይጾማልን?
፪፦ ከቅዳሜ 7 ሰዓት ከእሁድ 2 ሰዓት ኣገናኝተን ጾመ ጋድ(ገሓድ) እንጾማለንን?
፫፦ በዕለተ በዓሉ የሚቆርቡ እንዴት ይጾማሉ?
 
መልስ፦

፩፦ ጾመ ጋድ በሰንበት ከዋለ በሰንበት ጾም ስለማይፈቀድ ከፍስክ ምግቦች (ሥጋ ዕንቁላል….) በመከልከል ሌላ ምግብ በመመገብ እንውላለን ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ጾመ ገሓድ(ጋድ) በሰንበት ላይ ሲያርፍ እንደ ሌሎች የአዋጅ አጽዋማት ውስጥ እንዳሉ ሰንበታት ሰንበትነቱን በማይሽር መልኩ ይጾማል እንጂ ከምግብ በመከልከል መጾም አይገባም ለማለት ነው።

➙ የጥር 10 ስንክሳር "ወለእመ ኮነ በዓለ ልደት ወበዓለ ጥምቀት በዕለተ ሰኑይ ኢይትከሃል ከመ ይጹሙ በዕለተ ሰንበት ዳዕሙ ይትዓቀቡ እምነ በሊዕ ጥሉላተ" - "የልደትና የጥምቀት በዓልም ሰኞ ቀን ቢሆን በሰንበት ቀን ይጾሙ ዘንድ ኣይቻልም፤ ነገር ግን ጥሉላትን ከመብላት ይቆጠቡ" የሚለውን ነው። ስለዚህ ሰንበትም ሳይሽሩ ጾመ ጋድን ጠብቀው ያከብሩታል ማለት ነው።


፪፦ ከቅዳሜ 7 ሰዓት ከእሁድ 2 ሰዓት ኣገናኝተን ጾመ ጋድ(ገሓድ) እንጾማለን ለሚለው "ሰላም ዕብል ለጾመ ዕለት ዋሕድ" (የስንክሳሩ አርኬ) ከሚለው ጋር ይጋጫል ጾመ ጋድ ቅዳሜን እስከ 7 ቆተው ከበሉ በኋላ እንደገና የእሁድ 2ሰዓት ኣገናኝተው የሚጾሙት ሳይሆን «ለጾመ ዕለት ዋሕድ/ የኣንድ ዕለት ጾም» እንዳለው በልደት እና በጥምቀት ዋዜማ በኣንድ ዕለት ሊፈጽሙት የሚገባ ጾም እንጂ ሁለት ዕለትን በማገናኘት የምንጾመው አይደለም ። ለምሳሌ ሌሎች የኣዋጅ አጽዋማት ዕለታቱ ከአንድ በላይ ናቸው ጾመ ነነዌን ብንመለከት ሦስት ዕለታት ነው በእነዚህ ሦስት የጾም ዕለታት በየዕለቱ እስከ ዘጠኝ እየጾምን እየበላን ብናሳልፋቸውም አንዱን ጾመ ነነዌን ለመጾም ነው ሦስት ዕለት ይጹሙ ይላልና።

➙ በሰንበት ስለሚሆነው ጾም ሊቃውንት ከቀዳም ስዑር (ከሰሙነ ሕማማት ቅዳሜ) ሳያጠቃልል ስለቀሪው ቅዳሜ እና እሁድ በሃይማኖተ አበው ላይ በእሁድ ሰንበት ቅዳሴው እስከሚፈፀም መጾም እንደሚገባ ሲገልጽ ስለቅዳሜ ግን እጾማለሁ የሚል ቢኖር « አላ ጊዜ ዘይደሉ እስከ ስድስቱ ሰዓት ወእመ አኮ እስከ ሰብዓቱ/ እሰከ ስድስት ሰዓት እስከ ሰባት ሰዓት ድረስ » በማለት ገልጾልናል። (ይህ በቀድሞ ጊዜ የቅዳሜ ቅዳሴ አርፍደው ይጀምሩ ስለነበር ቅዳሴው እስከሚፈጸም ስድስት ሰዓት ይሆን ስለነበር ስድስት ሰባት ሰዓት ድረስ ተባለ እንጂ በቅዳሜ ጾም ይገባል ለማለት አይደለም )
በዚህ መሠረት ቅዳሜና እሁድም ቅዳሴው እስኪፈጸም ከምግብ መከልከል ይገባል እንጂ በሰንበት መጾም አይገባም።

➙ ጥምቀት ሰኞ ቢውል እንደሚታወቀው የጥምቀት ቅዳሴ የሚጀምረው እንደልደት እና ትንሳኤ ሌሊት 6 ሰዓት ሳይሆን ሊነጋጋ ሲል ወደ 10 ሰዓት ላይ የሚጀምር በመሆኑ ይህን ታሳቢ በማድረግ 18 ሰዓት አስልተው ከምግብ መከልከል ይገባል። በዚህም ሰንበትን ሻሩ አይባልም ጠዋት ተመግበዋልና ለመቊረብ ብለው ለ18 ሰዓት ከምግብ ተከለከሉ እንጂ ሰንበትን ሽረው ጾሙ ማለት አይደለም። ይቆየን

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

14 Jan, 02:47

3,817

#በዓለ_ግዝረት ጥር 6

ክብር ምስጋና ይድረሰውና የጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ግዝረት በየዓመቱ ጥር ፮ ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡


ግዝረት ማለት መገረዝ/ከሸለፈት ነጻ መሆን/ ማለት ነው፡፡ የተጀመረውም በአብርሃም ነው፡፡ በዘመነ ብሉይ አማንያን ከአህዛብ የሚለዩበት ከእግዚአብሔር ክብር የሚያገኙበት ሕግ መጽሐፋዊ ነው። ( ዘፍ ፲፯/ ዘሌ ፲፪ )

. ግዝረት በዘመነ ሐዲስ በጥምቀት ቢተካም ጌታ ሰው ሲሆን ሕግ መጽሓፋዊን እንዳላፈረሰ ለማጠየቅ በተወለደ በ8 ቀኑ ሥርዓተ ግዝረትን ፈጽሟል ይኸውም በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈ በስምንተኛው ቀን እንደ ኦሪቱ ሥርዓት ግዝረት ይፈጸምለት ዘንድ ሕፃኑ ጌታችንን ወደ ቤተ መቅደስ ወሰዱት፡፡ ስሙም ገና በሥጋ ሳይፀነስ የእግዚአብሔር መልአክ ባወጣለት ስም ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ /ሉቃ.፪፥፳፩-፳፬/፡፡

ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ጌታ ክርስቶስ በሥጋው ግዝረትን ተቀበለ፡፡ ለአባቶች የተሰጠውን ቃል ኪዳን ይፈጽም ዘንድ›› በማለት እንደ ተናገረው /ሮሜ.፲፭፥፰/፣ የክብር ባለቤት መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ ግዝረት በመግባት የኦሪትን ሕግ ፈጽሟል፡፡

- ነገር ግን በዕለተ ዓርብ በመስቀል ከመስቀሉ በፊት ደሙ አይፈስምና የባለሞያተኛው ሰው እጅ እና ስለት ሳያርፍበት በጌታችን ላይ ግዝረት ተገለጠ (የግዝረት ምልክት ታየ)፡፡ (የሉቃ ወን ፪፥፳፩-፳፬ አንድምታ) በስንክሳር በተአምረ ኢየሱስ ያለው በአንዱ ተገዘረ በአንዱ አልተገዘረም የሚለው አገላለጽ በትርጓሜ ወንጌሉ የታረቀውን ለመናገር ተፈልጎ ነው።
ይኸውም አልተገዘረም የተባለው ስለት እንዳላረፈበት ሲያይ ሲሆን ተገዘረ መባሉ ደግሞ ስለት ባያርፍበትም በአምላካዊ ተአምሩ እንደተገዘረ ሆኖ መገኘቱን ሲያይ ነው በማለት በትርጓሜ ወንጌል ታርቋል ለማለት ነው። ይቆየን

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ 

https://t.me/+VBt2ld_HeykCaELL (ቴሌግራም ቻናል )

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

07 Jan, 16:08

4,757

✥ ልጁን ወለደችው አብን መሰለችው ✥

👉 የተወደዳችሁ አንባብያን እመቤታችን እግዚአብሔር ወልድን የመውለድዋ የእናትነቷ ምሥጢር ከአብ ጋር ያመሳስላታል፡፡ ይህ እንደምንድ ነው ቢሉ ፦

፩– በቀዳማዊ ልደት አብ ያለ እናት ወልድን ወለደው በድኃራዊ (በሁለተኛ) ልደት ደግሞ እመቤታችን ያለ አባት ጌታን ወልዳለችና በዚህ የአብ ምሳሌው ሆነች፡፡ ስለዚህ ነገር አበው ‹‹ ልደት ቀዳማዊ ተዓውቀ በድኃራዊ ልደት ›› ያሉት አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከእመቤታችን ያለአባት መወለዱ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለእናት እንደተወለደ ያስረዳል፡፡ ቅዱስ ዳዊትም ስለዚህ ነገር በዝማሬው ‹‹ እግዚአብሔር በይሁዳ ታወቀ ስሙም በእስራኤል ታላቅ ነው ›› ኣለ ይኸም ከይሁዳ ወገን (በነገድ) ከሆነች ከእመቤታችን ያለኣባት በመወለዱ ከአብ ያለ እናት የመወለዱን ሃይማኖት ተገለጸ ማለት ነው፡፡

፪. አብ የወለደው ወልድን ነው እመቤታችንም ሥግው ቃልን እንጂ የሩቅ ብእሲ እናት ባለመሆኗ አብን መሰለችው፡፡ ስለዚህም እመቤታችንን ወላዲተ አምላክ እንላታለን፡፡

👉 ቅዱስ ያሬድም « ወይቤላ እግዚአብሔር ለማርያም አዝማንየ አዝማንኪ አምጣንየ አምጣንኪ ማርያም ሐቀፍኪዮ ወአነ ዮም ወለድክዎ» ( እግዚአብሔር ማርያምን ዘመኖቼ ዘመኖችሽ መጠኖቼ መጠኖችሽ ናቸው። እኔ ዛሬ ወለድኩት ማርያም ሆይ አንቺ ታቀፍሺው) (ቅ ያሬ ድጓ) « ዘመኖቼ ዘመኖችሽ ናቸው » ማለቱ ዓለም ከመፈጠሩ ዘመን ከመቆጠሩ በፊት በእርሱ ኅሊና መኖሯን የሚያስረዳ ነው። ይህም አዳምን ሳይፈጥረው በፊት እንደሚበድል እና በርስዋም አማካኝነት እንደሚያድነው ያውቅ ነበር ለማለት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ « ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳን፥ ንጹሓንና ያለ ነውር በፍቅር ያደረገን ዘንድ ለእርሱ መረጠን » (ኤፌ ፩፥፬) በማለት ዓለም ሳይፈጠር ፍጥረታት ሁሉ በአምላክ የታወቁ መሆናቸውን ገልጾልናል።

፫. ‹‹ እም ኀበ አብ ወጽአ ቃል ዘእንበለ ድካም ወእም ድንግል ተወልደ ዘእንበለ ሕማም ›› (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ ) እንዲል ከአብ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ ድካም ሳይሰማው እንደተወለደ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከድንግል ሕማም ሳይሰማት እርሱም ሕጻናትን የሚሰማው ሳይሰማው ተወልዷል በዚኽም እመብርሃን አብን መሰለችው፡፡

ዛሬ ሴት ስትወልድ ታምጥ የለምን ቢሉ ይህስ አድፈን ለመንጻታችን ምልክት ነው እንላለን፡፡ ቀድሞ በኦሪት 40 ዕለት በምጥ ተጨንቀው የሚቆዩበት ጊዜ ነበር በዚህም የምጥ ጽናት እና ብዛት በጥፍራቸው በጣታቸው ምድርን እስከመቆፈር ይደርሱ ነበር፡፡ ዛሬ በሐዲስ ኪዳን ግን ይህንን መርገም ጌታችን በቸርነቱ ብዛት በመስቀል በፈጸመው ካሳ ኣርቆልናል፡፡ ዛሬ የተወሰነ ምጥ መኖሩ እንዲህ ያለ መከራ ኣበረብን ጌታ ግን ከዚህ ሁሉ ኣዳነን ብለን ለማመስገን እንዲሆነን ነው፡፡ እመቤታችን ግን በዘር ይተላለፍ የነበረ ይህ መርገም ቀድሞውኑ ያልደረሰባት፤ እንደኛም ኣድፋ ኋላ የነጻች ስላልሆነች ጌታን ስትወልደው ምንም ሕማም ጣር ሳይኖርባት ነውና በዚህ ኣብን መሰለችው፡፡

፬. ወልድ ለአብ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ብቸኛ የበኸር (የበኩር) ልጁ እንደሆነ ለእመቤታችንም ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ብቸኛ የበኸር ልጇ ነውና በዚህም አብን መሰለችው፡፡ ውልድ ለአብ ብቸኛ እና የበኸር ልጁ ለመሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ተገልጧል ለምሳሌ፡-ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ በኩሩን ወደ ዓለም ሲያስገባ›› (ዕብ 1፤6) በማለት የበኸር ልጅነቱን ሲገልጥልን ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌል ‹‹ እግዚአብሔርን ያየው ኣንድስ እንኳ የለም በአባቱ እቅፍ ያለው ኣንድ ልጁ ገለጠልን እንጂ ›› ባለው እና ‹‹ አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን ወዷልና ›› (ዮሐ 1፤18/ 3፤17) በማለቱ ብቸኛ ልጁ መሆኑን ገልጦልናል፡፡
ይህማ በመስቀል ስር ከቅዱስ ዮሓንስ በስተቀር ሌላ ወንድ ሰው ቢያጣ ነው እንጂ ልጆችዋ እነስምኦን ፡ ዮሳ… አሉ የሚል ቢኖር እኛም መልሰን አንተ ሰው ‹‹ አንተን በመስቀል ላይ ቢሰቅሉህ እናትህን እና እውነተኛ ባልንጅራህን በመስቀል ሥር ብታይ ያን ባልንጅራህን እባክህን ያጽናኗት ዘንድ ወደ ልጅዎችዋ እና ወደ ባልዋ (ወደ ወንድሞቼ እና ወደ አባቴ) ወስደህ ስጥልኝ ትለዋለህ እንጂ እነሆ እናትህ ብለህ እርሱ እንዲወስዳት ታዘዋለህን? ›› ይኸስ ከልማድ ውጪ ነው፡፡

👉 ለፍጥረትስ ሁሉ ምግባቸውን የሚሰጥ ጌታ ወተት እየመገቡ ያሳደጉን ክቡር ጡቶቿን ፍጡር እንዴት ሊቀርበው ይቻለዋል ‹‹ ስላጠባኸው ጡቶቿ ›› እያሉ ይማጸኑበታል እንጂ፡፡ ቀድሞ በኦሪት ፈጣሪ ሊቀ ነቢያት ሙሴን ሲያዘው ከሰውም ሆነ ከእንስሳት ወገን የእናቱን ማህጸን አስቀድሞ ከፍቶ የሚወጣውን (የሚወለደውን) የእርሱ እንደሆነና እንዲለይለት ኣዞታል፡፡ ዳግመኛም ከሚያገኙት ከኣሥር ኣንድ (አሥራትን) ለፈጣሪ ብቻ እንደሆነ ለሰውም ሆነ ለተለያዩ ጥቅም እንደማያደርጓቸው ሁሉ እመቤታችንም ለእርሱ ለፈጣሪ እናትነት ብቻ የተለየች በመሆኑዋ ሌላ ልጅንም ባለመውለዷ እግዚአብሔር አብን መሰለችው፡፡ (ዘዳ 1፤31)

👉 ስለዚህ ሁሉ ነገር እመቤታችንን ‹‹ አብን ያየንብሽ ›› እያልን እናመሰግናታለን፡፡ ይህንንም ጌታችን ‹‹ እኔን ያየ አብን አይቷል ›› (ዮሓ፲፬ ) በማለቱ ገልጦልናል፡፡ ‹‹እኔን ያየ›› ሲል በመለኮቱ አይደለም መለኮት በሥጋ ድንግል ተገልጦ ቢታይ ዲዳሰስ ነው እንጂ፡፡ ከድንግል የሚታይ የሚዳሰስ ሥጋን ባይነሳ (ገንዘብ ባያደርግ) ኖሮ ባላየነው ባልዳሰስነውም ነበር፡፡ ወልድ በሥጋ ድንግል ተገልጦ ማየታችን ከእርሱ ጋር በሕልውና አንድ የሆነ አብን እንደማየት ነው፡፡ ስለዚህ ጌታችን ‹‹ እኔን ያየ አብን ዓየ›› አለ፡፡ በዚህ ሁሉ ነገር እመብርሃን አብን መሰለችው ለዚህ ታላቅ ክብር በመብቃትዋ ከፍጡራን በላይ ከፈጣሪ በታች መሆንዋ ተገለጠ፡፡ ስለሁሉም ነገር ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁን የወላዲተ አምላክ ረድኤት ኣይለየን፡፡ ይቆየን
✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ

https://t.me/+VBt2ld_HeykCaELL (ቴሌግራም ቻናል )

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

07 Jan, 15:06

3,387

✥ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኃለሁ ✥

ጥያቄ፡- ይህ ኃይለ ቃል የሚገኘው በየትኛው መጽሓፍ ነው?

መልስ፤- በመጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህ የሚል ኃይለ ቃል የለም እናንተ ኦርቶዶክሳውያን ግን ይህንን ኃይለ ቃል ከራሳችሁ አመጭታችሁ ትናገራላችሁ የሚሉ አሉ፡፡

- እንደምናውቀው እኛ እጅ ላይ ያለው መጽሓፍ ቅዱስ 81(ሰማንያ አሓዱ) ብንለውም 8ቱን የሓዲስ ኪዳን የሥርዓት መጽሓፍን ግን አላካተተም ምክንያቱም እነዚህ ይዘታቸው ትልቅ በመሆኑ ነው፡፡ አንዱ የሥርዓት መጽሓፍ እንኳን ከያዝነው መጽሓፍ ቅዱስ ይበልጣል ስለዚህ በአንድነት መጠረዙ ስለማይመች ለብቻቸው ተደርገዋል ነገር ግን ቁጥራቸው ከ81 መጽሓፍት ነው፡፡ 8ቱ የሓዲስ ኪዳን የሥርዓት መጽሓፍ የምንላቸውም

1. ትዕዛዘ ሲኖዶስ
2. ግጽው ሲኖዶስ
3. አብጥሊስ ሲኖዶስ
4. ሥርዓተ ጽዮን ሲኖዶስ
5. መጽሓፈ ኪዳን ቀዳማዊ
6. መጽሓፈ ኪዳን ካልዕ
7. መጽሓፈ ዲድስቅልያ
8. መጽሓፈ ቀሌምንጦስ ናቸው፡፡

- በዚህ መሠረት ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ የሚለው ኃይለ ቃል ቊጥሩ ከሰማንያ አሓዱ( ከ81 ከመጽሓፍ ቅዱስ ) ከሆነው እና የሥርዓት መጽሓፍ ብለን ከጠቀስናቸው ስምንት መጽሓፍት ውስጥ አንዱ በሆነው በመጽሐፈ ቀሌምንጦስ 2፥23 ላይ ይገኛል፡፡ ቀሌምንጦስ የቅዱስ ጴጥሮስ ደቀመዝሙር የነበረ እና ከቅዱስ ጴጥሮስም በኋላ በሮም ሀገር ላይ ሊቀጳጳስ ሆኖ የመራ አባት ነው፡፡ የዚህ መጽሓፍ ጸሓፊ ርሱ በመሆኑ በስሙ መጽሓፈ ቀሌምንጦስ ይባላል፡፡

- ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ የሚለው ኃይለ ቃል ቃል በቃል በዚህ መጽሓፍ ላይ ነው ያለው ብንልም ጌታችን ግን ከአዳም የልጅ ልጅ መወለዱን የሚገልጥ እኛ እጅ ውስጥ ካለ መጽሓፍ ቅዱስ ወይም 66ቱን መጽሓፍት ከሚቀበሉ ሰዎች ከያዙት መጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጦ እናገኘዋለን፡፡ ለምሳሌ በማቴዎስ ወንጌል በምዕራፍ አንድ ላይ የጌታችንን የዘር ሐረግ ሲገልጥልን ‹‹የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ መጽሓፍ ›› ካለ በኋላ ‹‹አብርሃም ይስሓቅን ወለደ፤ ይስሓቅም ያዕቆብን ወለደ……..›› ይለናል ይህ የሚያሳየን ቅዱስ ቀሌምንጦስ ‹‹ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ›› በማለት በመጠቅለል (ጠቅልሎ) የነገረንን ወንጌላዊው ማቴዎስ ደግሞ አብራርቶ ዘርዝሮ እንደጻፈልን ነው፡፡ ይልቁን ይህ ወንጌላዊ በዚሁ ምዕራፍ ላይ የጌታችን የዘር ሐረግ ዘርዝሮ ሲያበቃ የጌታችንን ልደት ሲገልጥልን ‹‹… የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስም ልደት እንዲህ ነበር ……›› (ማቴ1፤18) ማለቱ የጌታችን ልደት እንደ ውኃ ፈሳሽ እንደ እንግዳ ደራሽ የሆነ ሳይሆን ከላይ እንደገለጥኩላችሁ አብርሃም ይስሓቅን ወልዶት፤ ይስሓቅም ያዕቆብን ወልዶት…. በዚህ የመዋለድ ሂደት ከአዳም የልጅ ልጅ ከሆነች ከድንግል ማርያም መወለዱን ሲገልጥል ነው፡፡ ይህንንም ሃሳብ ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ዘመኑ በተፈጸመ ጊዜ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ላከ ከሴትም ተወለደ›› (ገላ.4፡4) በማለት ያስረዳናል ይኸውም ለአዳም ከልጅ ልጅ ተወልጄ አድሃለሁ ያለው የተስፋ ቃል ዘመኑ (5500) በተፈጸመ (ዘመኑ በደረሰ ) ጊዜ ሴት ከተባለች የአዳምም የልጅ ልጁ ከሆነች ከድንግል ማርያም ተወለደ ሲለን ነው፡፡

- ይህ የቅዱስ ጳውልስ ትምህርት መሰረቱን የምናገኘው ወደ ኦሪት ስንመለስ ነው አባታችን አዳም በድሎ ንስሐ ቢገባ ፈጣሪም ‹‹የሴቲቱ ዘር ራስ ራስህን ይቀጠቅጥሃል አንተም ሰኮና ሰኮናው ትነድፈዋለህ ›› ( ዘፍ.3፤11 ) የሚል ቃለ ተስፋ ሰጥቶት ነበር የዚህ ኃይለ ቃል ምሥጢራዊ ትርጉሙ የሴቲቱ ዘር የተባለው ከላይ እንደገለጥነው እንበለዘር ( ወንድ አጋዥ ሳያስፈልጋት ) ከድንግሊቱ የተወለደውን መድኅን ክርስቶስን የሚያመለክት ሲሆን ‹‹የሴቲቱ ዘር ራስ ራስህን ይቀጠቅጥሃል ›› ማለቱም ጌታችን ከድንግሊቱ ሰው ሆኖ ተወልዶ በፈጸመው የአድኅኖት ሥራ ከዲያቢሎስ አገዛዝ ነፃ እንዳደረገን የሚያስረዳ ነው፡፡ በመቀጠልም ‹‹ አንተም ሰኮና ሰኮናውን ትነድፈዋለህ ›› ማለቱ ዲያቢሎስ በአይሁዳውያን ላይ አድሮ ጌታችንን በመዋዕለ ሥጋዌው ይቃወመው እንደነበር ያስረዳናል፡፡ ስለዚህ ‹‹የሴቲቱ ዘር ራስ ራስህን ይቀጠቅጥሃል አንተም ሰኮና ሰኮናው ትነድፈዋለህ ›› የሚለውም የተፈጸመው የአዳም የልጅ ልጅ ከሆነች ከድንግል ተወልዶ መሆኑን የሚያስረዳ ነው እንግዲህ ‹‹ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ ›› የሚለው ኃይለ ቃል ቅዱስ ቀሌምንጦስ ብቻ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ እየመራቸው ሌሎችም ጸሓፍያን በመጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ በጎላ በተረዳ ነገር እንደገለጡልን በሚገባ ልንረዳው ያስፈልጋል፡፡

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ 

https://t.me/+VBt2ld_HeykCaELL (ቴሌግራም ቻናል )

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

07 Jan, 13:04

3,030

✥ ልደታችን እንደክርስቶስ ነው ✥

➙ የቃል (የወልድ) የባሕርይ ልደቱ ከአብ የተወለደው ነው ፥ የእኛ የባሕርይ ልደታችን ከሥጋዊ እናታችን የተወለድንበት ነው።

➙ ከአብ ዘንድ የሆነውን ልደቱን መርምረን የማንደርስበት እርሱ መርምረን በምንደርስበት በሌላ ልደት ተወለደ ይህም ለጌትነቱ ወሰን ለጸጋው ስጦታውም መጠን የሌለው መሆኑን ያስተምረን ዘንድ ነው።

➙ እኛ በጥምቀት የምንወለደው ወልድ ከአብ በተወለደበት በባሕርይ ልደቱ አምሳል ሳይሆን ከእመቤታችን በተወለደበት ልደት በመሰለ ልደት ነው።

➙ ይኸውም በተፈጥሮኣዊ ልደት(ከሥጋዊ እናት) የተወለድን እኛ ከተፈጥሮኣዊ ውጪ በሆነ ልደት (በጥምቀት ልጅነት) እንወለድ ዘንድ እንዲገባን ሊያስገነዝበን በባሕርይው የእግዚኣብሔር አብ የበኵር ልጅ የሆነ እርሱ ከባሕርይው ውጪ በሆነ ልደት ተወለደ። ሥጋዊ በሆነ ልደት ካልተወለደ በቀር መንፈሳዊ የሆነውን እርሱን ግዙፍ አካል አለው እንደማንለው ሁሉ እንዲሁ እኛም መንፈሳዊ በሆነ ልደት ካልተወለድን በቀር መንፈሳውያን አንባልም።


➙ ዳግመኛም በጥምቀት የምንወለደው ልደት ክርስቶስ ከድንግል መወለድን ይመስላል ክርስቶስ ከማርያም እንደተወለደ ከእርሷም ከተወልደ በኋላ አንቀጸ ሥጋዋ የድንግልናዋ ማኅተም ታትሞ እንደተገኘ እንደዚሁ ከጥምቀት ማህፀን የተወለደ ከውሃ ወጥቶ ወደ መጠበቂያው ውስጥ የመግባቱና የመውጣቱ አሠር አይገኝም በመዝሙር መንገድህ በባሕር ውስጥ ነው ፍለጋህም አይታወቅም እንደተባለ ነው። (መዝ ፸፯፥፲፱. መዝ ፻፵፪፥፲)

➙ በባሕር የሄደ ገብቶም የወጣ የመሄዱና የመግባት መውጣቱ አሠር (ፈለግ ምልክት) እንደማይቀር እንደማይታወቅ ጌታችንም ከእመብርሃብ በኅቱም ድንግልና ተጸንሶ በኅቱም ድንግልና በመወለዱ መንገድህ በባሕር ነው ፍለጋህም አይታወቅም ተብሏል እኛም በጥምቀት ውኃ ስንገባ እና ስንወጣ የመግባታችን የመውጣታችን ፈለግ በውኃው ላይ ሳይኖር መንፈሳዊ ልደት የምንወለድ በመሆኑ ልደታችን እንደክርስቶስ ነው። ይቆየን

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ 

https://t.me/+VBt2ld_HeykCaELL (ቴሌግራም ቻናል )

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

07 Jan, 03:52

2,767

ለብርሃነ ልደቱ ያደረሰን ጌታ ይክበር ይመስገን የበረከት በዐል ያድርግልን
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

07 Jan, 02:48

3,081

✥✥✥ ቤተልሔም ሰማይን መሰለች ✥✥✥

✥ በዕብራይስጥ ማሪሃም የተባልሸ እመቤቴ ድንግል ማርያም ሆይ አንቺም በተድላ በደስታዬ ጊዜ ሽልማት ሆንሽኝ፡፡ በኃሤትም ጊዜ ክብ ዘውዴ ሐቲም ቀለበቴ ነሽ፡፡

✥ በሐሳቤም ሁሉ አንቺን አደንቃለሁ፡፡ እንዲህም እላለሁ፡፡ እግዚኣብሔር ለሰው ልጅ ምን ያህልጸጋ ክብር ሰጠ፡፡

✥ እግዚኣብሔር ከሰው ልጅ የማይተባበሩ ሥስት ልደታትን ተወለደ፡፡ እኔም ዓውቄ አደነቅሁ፡፡ ባራተኛው እንጂ የበጎ ዕረፍት አላገኘሁም፡፡

✥ አዳም ከሕቱም ምድር የተወለደ በተፈጥሮ ነው፡፡ እኔን ግን የጠቀመኝ የለም፡፡ ሔዋንም ከአዳም ግራ ጐን ተወለደች እርሷም በተፈጥሮ ነው፡፡ ለኔ ግን የጠቀመችኝ የለም፡፡

✥ ቃየልም እንደ ሰው ሁሉ በዘር በሩካቤ ተወለደ የጠቀመኝ የረባኝ የለም፡፡ ስንኳን እኔን እራሱንም አልጠቀመም፡፡ እሊህ ሦስቱ ልደታትም ለማንም ለማን አይረቡም አይጠቅሙም፡፡

✥ ክርስቶስ ግን ያለዘር ያለሩካቤ ከድንግል ተወለደ ለሁሉ የሚረባ የሚጠቅም ሆነ፡፡

✥ ለዚህ ልደት መስገድ መገዛት ይገባል፡፡ ክብር ምስጋና ለዚህ ልደት ይገባል ጌትነትና ገናንነት፣ ኀያልነት፣ አዚዝነት፣ እልልታ፣ ግርግታ ለዚህ ልደት ይገባል፡፡

✥ ይህ ጥበብ ፍልስፍና ዕጹብ ድንቅ ነው፡፡ ለዚህ አንክሮ ይገባል ይህም የሥጋዊ ምሥጢር ምን ይረቅ ምን ይጠልቅ፡፡ ለዚህ አንክሮ ይገባል፡፡ ይህም ሰው መሆን ሥጋ መልበስ እጅግ ዕፁብ ድንቅ ነው፡፡

✥ የሔዋን ደኅንነቷ እመቤታችን ሆይ የድንግልናሽ ኃይል እጅግ የሚያስደንቅ ዕጹብ ነው፡፡

✥ የአዳምን መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ያጠፋሽለት እመቤታችን ሆይ የማይመረመር ረቂቅ ምሥጢር ባንቺ ተደረገ፡፡

✥ እሳትና ውሀም ባንድነት ተስማምተው መኖራቸው እጅግ ድንቅ ነው የሚያስፈራውንም ያንበሳ ደቦል ፀዓዳ በግዕት በክንዷ መታቀፍዋ እጅግ ድንቅ ነው፡፡

✥ ከድንግልም ብላቴና ጡቶች ወተት መፍሰስ እጅግ ድንቅ ነው፡፡ በበረትም ለድኆች ልጅ የሰማይ ሠራዊት መስገድ እጅግ ድንቅ ነው፡፡

✥ ዓለምን ሁሉ የመላ ኣምላክም ከበረት ተጥሎ በጨርቅ ተጠቅሎ መገኘቱ እጅግ ድንቅ ነው፡፡ በረት ከጽርሓ አርያም ቁመት ረዘመ ከሰማይም ዳርቻ ሰፋ፡፡

✥ ሕዝቅኤል ካየው ሠረገላ ዳንኤልም ካየው ኪሩባዊ ዙፋን በረት በለጠ፡፡ ይኽውም አደፍ ጉድፍ ሳይኖርባት ንጽሕት የወለደችው ንጹሕ በግ ነው፡፡ በረት ለንጹሑ መሥዋዕት ሽታ መሰብሰቢያ ሆነ፡፡

✥ ሰማይና ምድር የማይወስኑትን በረት ቻለው ወሰነውም፡፡ በረት የተመሰገነ ነው፡፡ የኃያላን ጌታ በውስጡ ተገኝቷልና፡፡

✥ በዕብራይስጥ ማሪሃም የተባለች እመቤታችን የተመረፀች ድንግል የሰማዩን ሠራዊት አሰገደቻቸው፡፡ የዓለም ጌጽ ሽልማት የሁሉ አባት የሚሆን መላእክትን የፈጠረ ጌታ ከርሷ ተወልዷልና፡፡

✥ በረት ተመሰገነ ምድርን በውሃ ላይ ያጸናት እርሱ ስለተጠጋባት ድንግልም የመላእክትን አለቆች ገዛቻቸው በኪሩቤል ላይ የሚቀመጥ እሱ በማኅፀኗ ስላደረ፡፡

✥ በረት ኪሩቤል እንደሚሸከሙት ዙፋን ሆነ ስፍራውም እንደ ጽርሓ አርያም ድንግል እንደ አብ ሆነች አንድ ልጅም በጎል ተጥሎ በጨርቅ ተጠቅሎ ተገኘ፡፡

✥ ዮሴፍና ሰሎሜ በወዲህና በወዲያ ላምና አህያም በወዲህና በወዲያ በበረቱ ጐንና ጐን ባራቱ ማዕዘን በዙፋኑ ቀኝና ግራ በጐንና በጐኑ አራቱ እንስሶች እንዳሉ፡፡

✥ የሰማይ ሥርዓት በምድር ላይ ተሠራ፡፡ ቤተ ልሔም ሰማይን መሰለች ስለ ፀሐይም በቅዱሳን ላይ የሚያበራ ለዘወትርም ጨለማ የማይቃወመው ኅልፈት ጥፋትም የሌለበት ዕውነተኛ ፀሓይ በውስጧ ተገኘ፡፡

✥ የብርሃኑም ክበብ መምላትና መጉደልን ስለሚያፈራርቅ በጨረቃ ፈንታ በዕብራይስጥ ማሪሃም የተባለች የድንግልናዋም ምስጋና በሁሉ የመላ ነው፡፡ ለዘወትርም የማይጐድል እመቤታችን የተመረፀች ድንግል ማርያም ተገኘች ስለ ከዋክብትም መላእክተ ብርሃን ታዩ፡፡

✥ ወደዚህ ማኀበር አንድነት እኖር ዘንድ ማን በከፈለኝ ከመላእክት ጋር እንዳመሰግን ከዋላጅቱም ጋር እንዳደንቅ ከእርኞችም ጋር እንዳገለግል፡፡

✥ በረቱንም እጅ እነሣ ዘንድ ማን በከፈለኝ የሙታን ሕይወት የኃጥኣንም ንጽሕና የቅቡፃን ተስፋ የተጨነቁትንም የሚያድን ጌታ ወደተቀመጠበት፡፡

✥ የዓለም ሁሉ መድኃኒት የምትሆን ብላቴና እግሯ የተመላለሰበቱን ምድር እስም ዘንድ ማን በከፈለኝ፡፡

✥ ይቅርታን የምታሰጥ ብላቴና ጥላዋ ይነካኝ ዘንድ ማን በከፈለኝ፡፡ የብርሃን ልጅ ወደ ሄደችበት እከተላት ዘንድ ማን በከፈለኝ የእግሯንም ጫማ እሸከም ዘንድ ማን በከፈለኝ፡፡

✥ አሁንም ያን ጊዜ በዕብራይስጥ ማሪሃም ከተባለች ከተመረጠች ድንግል ማርያም ጋራ ያን ጊዜ ካሉት አላንስም ሀሳቤን ከዚያ እንዳለሁ አድርጌ አለሁና፡፡

✥ በሥጋ አልነበርሁም በመንፈስ ግን አለሁ፡፡ ባነዋወር አልነበርሁም በሃይማኖት ግን አለሁ በገጽ አልነበርሁም በማመን ግን አለሁ፡፡

✥ ሳልኖር እራሴን እንዳለሁ ያረደረግሁ እኔ የተመሰገንሁ ነኝ ጌታችን በወንጌል እንደተናገረ እንዲህ ሲል ሳያዩኝ የሚያምኑብኝ ግን የተመሰገኑ ናቸው፡፡

✥ እኔ ባሪያህ ስለሃይማኖቴ የተመሰገንሁ ነኝ፡፡ ስለ ዕውነቴ አይደለም ስለ መረዳቴም የተመሰገንሁ ነኝ፡፡ ስለ ንጽህናዬም አይደለም በእግዚአብሔር ስም ስለ ኣመንኩ የተመሰገንሁ ነኝ፡፡ በናቱም ጸሎት ስለ አመንሁ ንዑድ ክቡር ነኝ፡፡
( አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አርጋኖን ዘሰኑይ)
✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ 

https://t.me/+VBt2ld_HeykCaELL (ቴሌግራም ቻናል )

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

31 Dec, 09:01

4,355

#ለአብሳሪነት_ቅዱስ_ገብርኤል_ለምን_ተመረጠ?

ቅዱስ ሚካኤልና ፣ ቅዱስ ሩፋኤል .... አልነበሩምን? ስለምን ቅዱስ ገብርኤልን ላከባት? ቢሉ

1፦ እስመ አብሣሬ ጽንስ ውእቱ” እንዳለ፣ ጥንቱን ቅዱስ ገብርኤል አብሣሬ ጽንስ ነው:: አስቀድሞ ማኑሄንና እንትኩይን ሶምሶንን ትወልዳላችሁ ብሎ፣ ዘካርያስና ኤልሳቤጥን ዮሐንስን ትወልድላችሁ ብሎ፣ ኢያቄምንና ሐናንም ማርያምን ትወልዳላችሁ ብሎ፣ የነገራቸው ገብርኤል ነውና ጥንት በለመደው ግብር ይሁን ሲል ገብርኤልን ላከበት:: “ዓቢይ ውእቱ ክብር ዘተውህበ ለከ ኦ ገብርኤል መልአክ ዜናዌ ፍሡሐ ገጽ ሰበከ ለነ ልደተ እግዚእ ዘመጽአ ኀቤነ ወአብሠርካ ለማርያም ድንግል ዘእንበለ ርስሐት ወትቤላ ተፈሥሒ ፍሥሕት ኦ ምልዕተ ፀጋ እግዚአብሔር ምስሌኪ” እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም (የረቡዕ ውዳሴ ማርያም ) ::

2፦ ጌታ ገብርኤልን በስም ይተባበረዋል ገብርኤል ማለት አምላክ ወሰብእ፣ እግዚእ
ወገብር፣ ፈጣሪ ወልደ እጓለ እመሕያው፣ ወልደ እግዚብሔር የሚሆንበት ቀን ነውና በስመ ትርጓሜው ገብርኤልን ላከባት:: “ወራብዑሰ ይመስል ገጹ ከመ ገጸ ወልደ እግዚአብሔር”
እንዲል “ኮነ ወልደ እጓለ እመሕያው አምላክ ዘበአማን” እንዳለ፡፡
- ቅዱስ ኤፍሬም “ሚካኤል ብሂል ዕፁብ ነገር፣ ገብርኤል ብሂል ወልደ እግዚአብሔር” እንዳለ ቅዱስ ያሬድ:: (ለ 2 ኛው የበለጠ ማብራሪያ ከፈለጉ " ገብርኤል የሚለው ስም ለወልድ ተሰጥቶ መነገሩ ስለምንድን ነው " በሚል ርዕስ ከዚህ ቀደም ያቀረብነውን ጽሑፍ ይመልከቱ።

3፦ ገብርኤል የሥላሴ ባለወሮታ ነውና።

መላእክት በተፈጠሩ ጊዜ “እምአይቴ መጻእነ ወመኑ ፈጠረነ” /ከየት መጣ? ማን ፈጠረን? / ብለው ቢሸበሩ ዛሬ መልካም ጐልማሳ ባጭር ታጥቆ፣ ጋሻ ጦሩን ነጥቆ፣ አይዞህ ባለህ እርጋ፣ ጽና፣ ብሎ ሰልፍ እንዲያረጋጋ ቅዱስ ገብርኤልም ፈጣሪያችንን እስክናውቀው ድረስ በያለንበት እንጽና ብሎ አረጋጋቸው:: “ንቁም በበህላዌነ እስከ ንረክቦ ለአምላክነ ወአኅድዖሙ መልአከ ሰላም በቃሉ” እንዲል (አክሲማሮስ ፶፬)

- ይህን በተናገረበት ቃሉ የጌታችንን ሥጋዌ ለመናገር የእመቤታችንን ባለ ብሥራት ለመሆን
አበቃው:: ወበእንተዝ ደለዎ ለገብርኤል ከመ
ይፁር ዜናሃ ለማርያም” እንዲል፡፡ (መቅድመ ወንጌል)

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተሰፋዬ

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)
✠ቤተ ጉባኤ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ✠

31 Dec, 03:02

3,859

" ደስተኛይቱ ሆይ ደስ ይበልሽ "

በበደል ለኃዘን ተዳርገን ነበር አዳም ምድር ገር አትሁንልህ ፣ እሾህ ታብቅልብህ ፣ በወዝህ ጥረህ ግረህ ብላ ፤ ሔዋን በየወሩ ድሚ ፣ ምጥሽ ይጽናብሽ ተብላ የሰው ልጅ ሁሉ በኀዘን ይኖር ነበር ፤ ድንግል ማርያም ግን ይህ ሁሉ የለባትም እና መልአኩ "ደስተኛይቱ ሆይ " ብሏታል ፥ በእርስዋም ምክንያት በሰው ልጅ ሁሉ የነበረው ኃዘን የሚርቅበትም ዘመን የደረሰ በመሆኑ "ደስ ይበልሽ " አላት ። ቀድሞ በበደላችን አጥተነው የነበርነው እርስዋ ምክንያት ሆና በልጅዋ በኩል የተመለሰልን ደስታ ዘለዓለማዊ ስለመሆኑ ልጇ " ደስታችሁን የሚወስድባችሁ የለም" ዮሐ.16 ብሎ አጸናልን።

-> የዓለም ኃዘን በተሰማበት በሔዋን ጆሮ ፥ በድንግል ማርያም ጆሮ በኩል የዓለም ደስታ የሚሆን ብሥራት ተሰማበት ።
-> ቀድሞ መልአኩ የሶምሶን ልደት ለእንትኩይ፣ የዮሐንስን ልደት ለዘካሪያስ የደስታን ዜና ለማብሠር ይላክ ነበር አሁን ግን የዓለም ሁሉ ድኅነት የሚሆንበት ዘመን መድረሱን ለማብሰር በመላኩ ከደስታው ብዛት ክንፎቹን እያማታ ፈጥኖ እየበረረ ወደ ድንግል መጣ ስለዚህም ዜናዊ ፍሱሐ ገጽ ተባለ ለድንግሊቱም ጆሮ የዓለምን ሁሉ የደስታ ዜና አሰማ ስለዚህ የደስታ መፍሰሻ ሆነች።
ቅዲስ ዳዊትም " የወንዝ ፈሳሽ የእግዚአብሔር ከተማ ደስ ያሰኛል " አለ የወንዝ ፈሳሽ የተበለ ቅ. ገብረኤል ነው የእግዚአብሔር ከተማ የተባለችውን ድንግልን ሲያበስራት ደስ አሰኛት :: ነገር ግን አስቀድመን እንደተናገርነው ሲያበስራት ኀዘንተኛይቱ ሆይ ደስ ይበልሽ አለላትም "ደስተኛይቱ ሆይ ደስ ይበልሽ " ነው ያላት ኃዘንተኝነት የመርገም ምልክት ነው ፥ ደስተኛነት የበረከት ምልክት ነው ስለዚህ የአባቷ እና የናትዋ የመርገም ፍሬ የለባትምና ቀድሞም መርገም የሌለብሽ " የተባረክሽ ነሽ " ስለዚህም " ደስተኛይቱ ሆይ ደስ ይበልሽ " አላት። ቅዱስ ኤፍሬም "ዕፅፍ ድርብ ደስታ ያላት ድንግል አማኑኤልን ወለደቸው " አለ።
ሴቶች ትወልዳላችሁ ሲሏቸው ደስ ይላቸዋል ይልቁንም ወንድ ልጅ ትወልዳላችሁ ሲሏቸው ደስታቸው ዕፅፍ ድርብ ይሆናል ይልቁንም የምትልጂው ነበይ ፣ ጻድቅ .... ቢሏቸው ደስታቸው ወደር የለውም፤ ድንግል ግን የነቢያት ጌታ አምላክ ነው የምትወልጅው መቧልዋ ከዚህ በላይ ምን ደስታ ይኖራል !?
-> ቅዱስ ዳዊት "ኵሬ " ሳይሆን " የወንዝ ፈሳሽ " አለ ይህም በእርስዋ የተሰማው የደስታ ዜና በእርስዋ ብቻ የቀረ ሳይሆን ለሰው ልጆች ሁሉ በመሆኑ ነው::

-> ዛሬም " ናዛዚትነ ወኀዘን ወኃይለ ውርዙትነ እም ርስአን በማህፀንኪ ተጸውረ ብሉየ መዋዕል ሕፃን - ኦ ማርያም ተስፋ ለቅቡፃን በጊዜ ጸሎተ ወዕጣን ወበጊዜ ቅዱስ ቍርባን ለናዘዘኒ ወትር ነንዒ ኀበ ዝ መካን " ፥ ከሀዘን የምታረጋጊን ከእርጅና የምታድሺን በማህፀንሽ በዘመናት የሸመገለ ተብሎ የተነገረለት ቀዳሚው አምላክ በማህፀንሽ ህፃን ሆኖ ተወስኗልና። - ተስፋ ቆርጠው በኀዘን ያሉትን የምታረጋጊያቸው ማርያም ሆይ ዛሬም አዝነን ተክዘን ጸሎት ፣ ዕጣን፣ ቊርባናችን በምናቀርብበት ጊዜ ሁሉ እንድታጽናኚን ወደኛ ነይልን " እንላታለን ::
-> በጎሎጎታም ልመናዋም " በስሜ ያዘነውን ያረጋጋውን ማርልኝ " ነው ያለችው ይህም ያዘነውን አይዞህ እርስዋ አለችልህ ብሎ ያረጋጋውን ማለትዋ ነው። እውነት ነው ጊዜያዊ ሀዘን ይቅርና ከዘላለማዊ ሀዘን እንኳን በርስዋ ድነናል።

- አባ ጊዮርጊስም ያዘናችሁ ወደድንግል ኑ .... ያደፍችሁ ልብሳችሁን ታጥቡ ዘንድ ...ይለናል።

✍️ አምኃ ሥላሴ / መኩሪያ ተስፋዬ

https://t.me/+Vd4rG3DjWHFlDGCo (ቴሌግራም ግሩፕ)

https://m.facebook.com/mekuria.tesfaye.71

https://www.youtube.com/channel/UC8v52_jNY156sxZtplafDtw/about (የዩቱብ አድራሻ)