***
ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለላቀ ፖሊሳዊ አገልግሎት በሚል መሪ ቃል የከተማ አቀፍ የአዲስ አበባ ፖሊስ ስፖርት ፌስቲቫልና ውድድር መክፈቻ ስነ-ሥርዓት ጥር 17 ቀን 2017 ዓ/ም በአዲስ አበባ ስታዲየም በይፋ ተከፍቷል ።
ክቡር አቶ ሞገስ ባልቻ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ኃላፊ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የስፖርት ቢሮ በየደረጃ የሚገኙ አመራርና አባላት፣ የሠላም ሰራዊትና የደንብ ማስከበር አባላት እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በስፖርት ፌስቲቫሉ የመክፈቻ መርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል።
በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የዕለቱ የክብር እንግዳ ክቡር አቶ ሞገስ ባልቻ ባደረጉት ንግግር አዲስ አበባ የተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ኮንፈረንሶች የሚካሄዱባት ከተማ በመሆኗ የሠላምና ደህንነት ተምሳሌት እንድትሆን ፖሊስ ከነዋሪውና ከሌሎች የፀጥታ አካላት በጋራ ባከናወነው ተግባር ሠላምን ማረጋገጥ ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል።
ፖሊስ በሀገራችን የስፖርት እንቅስቃሴ ታሪክ ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረከተና በተለያዩ ስፖርት ዘርፎች ሀገርን ያስጠሩ ስፖርተኞች የተገኙበት ተቋም መሆኑንም ገልፀዋል። በተጨማሪም ፌስቲቫሉ ፖሊስ በስፖርት የዳበረ አካላዊ ብቃትን ተላብሶ ተልዕኮውን በላቀ ሁኔታ እንዲወጣ ያግዘዋል ሲሉ አቶ ሞገስ ባልቻ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን በበኩላቸው ስፖርትና ፖሊስ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ መሆናቸውን ገልፀው ፖሊስ በሀገራችን የስፖርት እድገት ውስጥ ጉልህ ሚና እንዳለው እና በዓለም አቀፍ መድረክ የሀገራችንን ክብር ከፍ ያደረጉ ስፖርተኞች የተገኘበት ተቋም መሆኑን ጠቅሰዋል።
አቶ በላይ ደጀን አያይዘው ፣ መሰል ውድድር የአባላትን ጓዳዊ ትስስር የሚያሳድግ በመሆኑ ለወደፊቱ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ለሚያከናውነው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የከተማው ስፖርት ቢሮ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ በላይ ደጀን ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፣ ባደረጉት ንግግር ለፖሊሳዊ ተልዕኮ ስኬት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ወሳኝ መሆኑን የተረዳው ፖሊስ የሚያበረታታ መነቃቃት ላይ እንደሚገኝ ገልፀው ስፖርት የፖሊስ አባላት ህብረተሰቡን በብቃት እንዲያገለግሉ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ቀላል የሚባል አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።
አዲስ አበባ ፖሊስ በስፖርቱ ዘርፍ በሀገር አቀፍና በዓለማቀፍ መድረክ ተሳታፊ የሆኑ ስፖርተኞችን ከማስመረጥ ባለፈ የበርካታ ሜዳሊያዎችና ዋንጫዎች ባለቤት በመሆን ውጤታማ ነው ያሉት ኮሚሽነር ጌቱ ውጤታማነቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው ከስፖርት ፌስቲቫልና ወድድሩ ጠንካራ፣ አሸናፊና ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት በቀጣይ የሚጠበቅ ነው ብለዋል። አያይዘውም ለዚህ ውድድር መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ኮሚሽነሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ የኮሚሽን ፅ/ቤት ኃላፊና የስታፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ምክትል ኮሚሽነር አህመዲን ጀማል የዕለቱን መርሀ-ግብር ካስተዋወቁ በኃላ " ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለላቀ ፖሊሳዊ አገልግሎት " በሚል መሪ ቃል መካሄድ የጀመረው የአዲስ አበባ ፖሊስ ከተማ አቀፍ የስፖርት ፌስቲቫልና ውድድር በቀጣይ ቀናት በእግር ኳስ፣ በአትሌቲክስ፣ በገመድ ጉተታ፣ በጠረጴዛ ቴኒስ፣ በዳርትና በሌሎች የስፖርት ዓይነቶች በጠንካራ ፉክክር እንደሚቀጥል ገልፀው በቀጣይም ለ19ኛው ሀገር አቀፍ የመላው ፖሊስ ስፖርት ውድድር ከተማ አስተዳደሩን በሁሉም የስፖርት መስኮች የሚወክሉ ስፖርተኞች የሚመረጡበት እንደሚሆንም አክለው ገልፀዋል።
*
ዘገባ፦ ሳጅን ኤርሚያስ ዘውዴ
*
ለፖሊሳዊ መረጃዎቻችን፦
በፌስቡክ :- https://www.facebook.com/Addisababapolice
በቴሌግራም:- https://t.me/addispolice
በዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/AddisAbabaPoliceCommission
በትዊተር፦Twitter https://twitter.com/AddisPolice
ድረ ገጽ፦ web https://www.addispolice.gov.et/
“በጀግንነት መጠበቅ በሰብዓዊነት ማገልገል!”
“Protect with courage, Serve with Compassion!”