**
የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ የክ/ከተማውን ፀጥታ ከማስጠበቅ ባሻገር የሪፎርሙ ውጤቶች የሆኑ በርካታ የለውጥና የልማት ሥራዎችን ማከናወኑ የሚታወቅ ነው። የካቲት 2 ቀን 2017 ዓ/ም በተጨማሪነት ያከናወናቸውን የልማትና የለውጥ ሥራዎች የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው የክ/ከተማው አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ሚጀና የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የአስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተጎብኝቶ ተመርቋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ባስተላለፉት መልዕክት የክ/ከተማው ፖሊስ መምሪያ ከተቀበለው ተልዕኮ ባሻገር ያከናወናቸው የልማትና የሌማት ትሩፋት ሥራዎች በአርዓያነት የሚታይ መሆኑን አስታውሰው ተግባሩን አጠናክሮ ማስቀጠሉ ያስመሰግነዋል ብለዋል። አያይዘውም ተግባሩን ከቴክኖሎጅ ጋር ማስተሳሰሩ ውጤታማ እያደረገው እንደመጣ ገልጸው ለፖሊሳዊ አገልግሎት ስራው አስፈላጊ የሆኑ ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በበለጠ ለማስፋፋት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ሥራዎችን በቴክኖሎጂ የማገዝ ተግባር የማስፋፋት ስራው በአስራ አንዱም ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች እየተሰራበት መሆኑን ያስታወሱት ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊሰ መምሪያም በአይሲቲ ስራዎች፣ ምቹ የስራ ቦታን በመፍጠር እንዲሁም በሌማት ትሩፋት ዙሪያ የሰራቸው ስራዎች አበረታችና ለሌሎች በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑንም ተናግረው ፖሊስ መምሪያው የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ጨምረው ገልጸዋል።
የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረ/ኮሚሽነር መስፍን ሰብስቤ በበኩላቸው በክ/ከተማው ህዝብ በስፋት የታደመባቸውን ልዩ ልዩ ኩነቶች ካለምንም የፀጥታ ችግር በሠላም ማጠናቀቅ የተቻለው እና እንደ ክፍለ ከተማ የወንጀል ድርጊትን መቀነስ የተቻለው በአጋጣሚ ሳይሆን የክ/ከተማው ፖሊስ አባላትና አመራሮች ደከመን ሰለችን ሳይሉ ሌትና ቀን ተግባራታቸው በቴክኖሎጂ በማስደገፍ በተሰራ ሥራ የተገኘ ውጤት ነው ብለዋል፡፡
ፖሊስ መምሪያው ከዋና የወንጀልና ትራፊክ አደጋ መከላከልና ምርመራ ተልኮው ጉን ለጎን ልዩ ልዩ የልማት ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀው ቀደም ሲል ካከናወናቸው የልማት ስራዎች በተጨማሪ በ200ካሬ ላይ ያረፈ 4 የተለያየ ክፍሎች ያሏቸው 2 የእህል ወፍጮዎች፣ በቀን እስከ 5ሺ እንጀራ መጋገር የሚያስችል ዘመናዊ የእንጀራ ማቀነባበሪያ ፕሮጀክት ስራ ማስጀመሩንም ተናግረዋል።
በፕሮግራሙ ላይ ለፖሊስ መምሪያው ስራ ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋፆኦ ላደረጉ አካላት የገንዘብ፣ የሰርተፍኬት እና ጥሩ አፈጻጸም ላሳዩ ፖሊስ ጣቢያዎችም የኮምፒተር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
*
ዘገባ፦ ረ/ሳጅን አባይነህ እኔምአየሁ
*
ለፖሊሳዊ መረጃዎቻችን፦
በፌስቡክ :- https://www.facebook.com/Addisababapolice
በቴሌግራም:- https://t.me/addispolice
በዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/AddisAbabaPoliceCommission
በትዊተር፦Twitter https://twitter.com/AddisPolice
ድረ ገጽ፦ web https://www.addispolice.gov.et/
“በጀግንነት መጠበቅ በሰብዓዊነት ማገልገል!”
“Protect with courage, Serve with Compassion!”