በዓል ከሌላ ማህበራዊ ጉዳይ ጋር ተደርቦ ባይመጣ! (ርዕሱ ነው!)
.
(#ፈይሠል_አሚን)
.
እንደሚታወቀው ‹‹መውሊድ›› ታላቁ ነብይ (ዐ.ሰ.ወ) የተወለዱበት ተዓምራዊ ቀን ነው፡፡ በዓለም ላይ ሰዎች እንደየ ባሕላቸውና እንደየ ወጋቸው በዓሉን በተለያዩ መንገዶች ያከብሩታል፡፡ በሐገራችን ‹‹መውሊድ›› በአብዛኛው በድምቀት የሚከበረው በየመስጂዶች ነው፡፡
.
እኔም ታዲያ ትናንት ማታ ነገ በዓሉን አስመልክቶ ከእረፍቴ ጋር አዋህጄ ስለ ነብያችን እያነበብኩ ለመዋል አቅጄ የማነባቸውን መጽሐፍት አዘጋጅቼ ተኛሁ፡፡ መቼም ሰውና የራይድ መኪና ባሰበበት አይውልምና ሌሊት ከሰዓት ላይ ክፉ ሕልም ክው አድርጎ ቀሰቀሰኝ፡፡
.
በሕልሜ የሩቅ ጎረቤቴ የኾት ጋሽ ተዘራ ባዶ ሜዳ ላይ ተዘርረው ሞተው ዐየሁ፡፡በሚገርም ሁኔታ ላለፉት ሦስት ሳምንታት እኚህ ሰውዬ በተከታታይ ሦስት የተለያዩ አደጋዎች ሲደረሱባቸው ዐይቻለሁ፡፡ በሕልሜ የጋሽ ተዘራ መዘረር አዲስ ነገር አይደለም፡፡
.
የመጀመሪያ ሳምንት ላይ ጋሽ ተዘራ ማንም ሳይነካቸው በአናታቸው ሲደፉ ዐየሁ፣ በሳምንቱ ዛፍ ተገንድሶ ሲወድቅባቸው…በሦስተኛው ሳምንት ደሞ የፕራንክ ቪድዮ እሠራለሁ ብለው ባስደነገጡት ሰው ተደብድበው ሲዘረሩ ዐየሁ፡፡ቢጨንቀኝ ጎረቤቴ ያሉትን እማማ ሸንኮሬን አማከርኩ፡፡ እንደምታውቁት ሐበሻ ሕልሙን ማሳካት እንጂ ሕልሙን የማስፈታት ችግር የለበትም፡፡ማንም መንገደኛ ነው ሕልምህን ሚፈታልህ፡፡ እማማ ሸንኮሬ ሦስቱንም ሕልም ከሰሙ በኋላ ‹‹ሲሳይ ነው!›› ብለው ፈተቱት፡፡ ሕልሜን ፈተው ሲያበቁ ግን አመናጨቁኝ፡፡ ሕልም ሣይ እማማ ሸንኮሬ ለምን እንደሚበሳጩና ሳያብራሩ እንደሚፈቱልኝ አይገባኝም፡፡ ሕልም መፍታት አይችሉም እንዳልል የሰፈሩ ሰው የመሰከረላቸው ፈቺ ናቸው፡፡
እንደውም በሕልም ፍቺ ጥበባቸው ሲያሞኳሷቸው ‹‹እሳቸው እኮ የሕልም ጋራዥ ናቸው!›› ይሏቸዋል፡፡ ለተከታታይ ሦስት ሳምንታት ያየኋቸውን ተመሳሳይ ሕልሞች ስነግራቸው ቀንተው ነው መሰለኝ ‹‹ቆይ አንተ ግን ሁሌ እንዲህ እንደ አህያ ፊት አንድ ዓይነት ሕልም ምታየው ሰብስክራይብ አድርገህ ነው እንዴ?›› ብለው አሽሟጠጡብኝ፡፡
.
ይኸው ዛሬ ለሊት ጥሩንባ ተነፍቶ የጋሽ ተዘራ መርዶ ደረሰን፡፡አምሽተው ሲገቡ በማጅራት መቺዎች ተወግተው መገደላቸውን ሰማን፡፡
ያኔ እማማ ሸንኮሬ ሕልሜን ‹‹ሲሳይ ነው!›› ብለው ሲፈቱልኝ አምኜያቸው ነበር፡፡ዛሬ ሌሊት እንደደረሰን መረጃ ከኾነ ግን ጋሽ ተዘራን ‹‹ሲሳይ›› የሚባል የመንደራችን ዕውቅ ማጅራት መቺ እንደወጋቸው ሰማሁ፡፡
.
እነሆ! ከበዓሉ ዋዜማ በፊት የገጠመ የሩቅ ጎረቤት ለቅሶ ላይ ተገኝቻለሁ፡፡ እንደ ሕዝብ ለቅሶ ላይ አጉል አመል እንዳለብን ያስተዋልኩት እዚህ ለቅሶ ላይ ነው፡፡ አንዱ ለቀስተኛ የሟች ልጅ ጋር ጠጋ ብሎ ‹‹ታመው ነበር?›› ይላል፡፡ አባትዬው በማጅራት መቺ ተወግተው መገደላቸውን እያወቀ ነው ይኼን ሚጠይቀው፡፡ ልጁ ተናዶ ‹‹አዎ! የዛሬ ስምንት ዓመት ስኳር ይዞት ነበር!›› አለው፡፡ ልጁ ግን መጠየቁን አላቆመም፡፡ ‹‹ዶክተር ተኮላ ጋር እኮ ብትወስዷቸው አይሞቱም ነበር!››፡፡ እኔም ተናደድኩና ‹‹ዶክተር ተኮላ የማጅራት መቺ መድኃኒት ሠርተዋል?!›› አልኩት፡፡
ደንገጥ ብሎ ‹‹ያው ቢያንስ ከስኳራቸው አገግመው ቢኾን ሮጠው ማምለጥ አያቅታቸውም ለማለት ፈልጌ ነው!!›› ነው ብሎ አድበሰበሰ፡፡
.
ጋሽ ተዘራ በበዓል ቀን ቀብራቸው መፈፀሙ ለብዙዎቻችን ገርሞናል፡፡በዓል ሲነሣ አብረው ሚነሡ ሰው ናቸው፡፡ በዓል እጅግ ከመውደዳቸው የተነሣ ‹‹የበዓል አኒቨርሰሪ›› ሁሉ የሚያክብሩ ሰው ናቸው፡፡ ‹‹ቆንጆ ገና ያሳለፍንበት አራተኛ ዓመት!›› ይሉና ጳጉሜ ላይ ድል ያለ ድግስ ሊያሳናዱ ይችላሉ፡፡ ‹‹ጎረቤቶቼ›› የአረፋ በዓልን ክፍለ ሐገር ሔደው በማክበራቸው አብረናቸው ስላላከብርን ይሉና አረፋን ያለ ወቅቱ በሙክት ያከብሩልን ነበር፡፡
.
አንድ ጊዜ ድንገት ተሥተው ዛሬ በዓል ነው ብለው ዶሮ ገዝተው ሊ,ያርዱ ተሰናዱ፡፡ ዶሮው ግን የዋዛ አልነበረም፡፡ባርከው ሲያርዱት አንገቱን እዚያው ጥሎ ተነሥቶ በደመ-ነፍስ እግሬ አውጪኝ አለ፡፡ ክንፉን ዘርግቶ ያለ አንገት ቀጥ ብሎ ሲሮጥ አንገቱን የቆረጥንበት ሳይኾን ኮፍያ ያወለቅንበት ነበር የሚመስለው፡፡ ሳፋ ያለው ሳፋውን ይዞ፣ ሳፋ የሌለው ሰልፊውን ደግኖ ተከተለው፡፡
ዶሮው በዋዛ ሊያዝ አልቻለም፡፡ከምንም ጋር ሳይጋጭ ቀጥ ብሎ መንገዱን ይዞ ሩጫውን ቀጠለ፡፡ በዚህ ሁኔታ የተጨነቁት ጋሽ ተዘራ ከጭንቀት የመነጨ አስቂኝ ሐሣብ አመነጩ፡፡ ሮጦ የራቀው ዶሮ አንገቱን ግቢው ውስጥ ጥሎ ስለሮጠ ዓይኑ ቢሸፈን ተደናቅፎ ይወድቃል በማለት ‹‹ዓይኑን ያዙልኝ! በሕግ አምላክ ዓይኑን ጋርዱልኝ! ሲሉ ጮኹ፡፡
ይኼን የመሰለ ትዝታ ትተው ዛሬ ራሳቸው ጋሽ ተዘራ ዓይናቸው ለዘላለም ተሸፈነ፡፡
.
እነሆ. . .ዘመድ አዝማዱ መጥቶ ጋሽ ተዘራን ወደ ማይቀረው ቤታቸው ለመሸኘት ተሰብስበን በሐዘን ተቀምጠናል፡፡ እኔም ከቀብር በኋላ የበዓል እቅዴን ለማሳካት እያሰብኩ ነው፡፡ እግረ መንገድ ለቅሶው ላይ ሰዎችን እየታዘብኩ ነው፡፡
አንዱ ቲክቶክ ላይ ላይቭ ገብቶ ስለ ጋሽ ተዘራ መልካም ባሕሪ እያወራ ነው፡፡ ለጎረቤት ያላቸው ቅርበት፣ተጫዋችነታቸው የልጅነት ታሪካቸው ሁሉ አልቀረውም፡፡ በነገራችን ላይ ይኽ ላይቭ የገባው ልጅ ከአራት ቀናት በፊት እዚያ ማዶ ያለው ኮንዶሚኒየም ተከራይቶ የገባ ሰው ነው፡፡ ጋሽ ተዘራን በአካል ቀርቶ በፎቶም ያለዛሬ ያያቸው አይመስለኝም፡፡
.
አንዳንዶች ደግሞ እስኪነጋ ከሚደብረን ብለው አስከሬን ሳይወጣ ካርታ መጫወት ጀምረዋል፡፡ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ጋሽ ተዘራ ቤት ወደ አራት ለቅሶዎች ተከስተዋል፡፡ የባለፈው ለቅሶ ላይ አንዱ ቁማርተኛ ካርታ ሲጫወት ተበልቶ ያለውን ሰምቼ ሳላበቃ ዛሬም ዓይኑን በጨው አጥቦ እየተጫወተ ነው፡፡የባለፈው ለቅሶ ላይ ተሸንፎ ብሩን ሲበላ ጮክ ብሎ ‹‹ኤጭ! የዚህ ቤት ለቅሶ ደሞ አይቀናኝም!›› ማለቱን ነግረውኛል፡፡
.
በበዓሉ ቀን የጋሽ ተዘራ ግብዓተ-መሬት ተፈጽሞ ተመለስን፡፡ ከድንኳኑ ቀስ ብዬ ወጥቼ ቤቴ ሔጄ አረፍ ልል ሳስብ አያቴ ስልክ ደወለች፡፡ ‹‹በዓልም አይደል? ብቅ አትልም እንዴ?›› ብላ ጠየቀችኝ፡፡ በርግጥ ጥያቄ ይመስላል እንጂ ትዕዛዝ ነው፡፡
ወንዱ አያቴ በመውሊድ ቀን ወዳጆቻቸውን እና ቤተ-ዘመዱን ሰብስበው ታላቁ ነብይ ላይ ሰለዋት እያወረዱና እየዘከሩ የማሳለፍ ልምድ አላቸው፡፡ መንዙማው በላይ በላይ ሰለዋቱ ይከተላል፡፡ እኔ የሔድኩ እንደው ግን አያቴ እኔን ጎሸም የሚያደርግ ግጥም ጣል እያደረጉ ይዝናኑብኛል፡፡ስናደድ ደስ እላቸዋለሁ መሰለኝ፡፡ ባለፈው ዓመት የመውሊድ ቀን ተጠርቼ አርፍጄ ብገኝ. . . እኔን እያዩ እንዲህ ሚል ግጥም አወረዱ፡-
‹‹ለሰለዋት ብንጠራው፣ቀረ…ነገር መስሎት፤
የአንጎሉን ሽሆና ድፍን አር´ጎ ፈጥሮት!››
.
ታዲያ በአሽሙር ‹‹የአዕምሮህ ሽሆና ክፍት ነው!›› ማለታቸው ለጨዋታ መኾኑ ገብቶኝ እኔም ለጨዋታ አንድ ግጥም ጣል አደረግኩ፡፡ እንዲህ አልኩ. . .