‹‹ ነገር ይገንብኛል››
---=======------
‹‹ለትንሹም ለትልቁም ነገር አቃቂር ማውጣት ትወጃለሽ›› የሚሉኝ ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡
‹‹ሊያውም ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖሩ ሁሉን ነገር መተቸት…ሁሉ ነገር እንከን የለሽ እንዲሆን መጠበቅ አይከብድም?›› ይሉኛል፡፡
አንድ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ በመኖሩ ብቻ የተርመጠመጠ ነገር በቂው ነው ያለው ማነው?
…በቃ ለራሳችን የምንሰጠው ግምት ይህችን ታህል ነው?
…ለዚህ ይሆን አንድ ስፍራ ፀድቶና አምሮ ሲታይ፣
‹‹…ዋው ኢትዮጵያ አይመስልም›› የምንለው…?
እቅጩን ንገሪን ካላችሁ፤ “እኔን አቃቂር ታበዣለሽ” እያሉ የሚከሱኝ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለን ደህና ነገር አይገባንም በሚል የበታችነት ስሜት የሚሰቃዩ ሰዎች ናቸው፡፡
…እነሱ ለራሳቸው የሚሰጡት ግምት ከደረጃ በታች ስለሆነ፣ ያገኙትን ሁሉ ተስገብግበው ስለሚያነሱ፤ እንኩ የተባሉትን ሁሉ አጎንብሰውና በጀ ብለው ስለሚቀበሉ፣ የከፈሉበትን ነገር እንኳን ተሸቆጥቁጠው ተጠቃሚ ስለሆኑ፣ መራጭ ሳይሆን አግበሽባሾች ስለሆኑ….
እኔ ‹‹አረ ይሄ ነገር ከልክ በታች ነው›› ስል አፋቸውን ለትችት ያሞጠሙጣሉ፡፡
ለሽሙጥ የተሞረደ ምላሳቸውን ዘርግተው, ‹‹እስቲ ክፉ ክፉን ብቻ ማየት ትተሸ አይንሽ ለበጎውም ነገር ይከፈት›› ይላሉ፡፡
ደግሞ እኮ ነገር ይገንብኛል እነጂ ፣ ያን ያህል እንከን ፈላጊ ሰው ሆኜ አይደለም፡፡
ምሳሌ ልስጣችሁ፡፡
ባለፈው አንድ ቄንጠኛ ካፍቴሪያ (ስቀብጥ) ገብቼ ለአንድ ማኪያቶ 140 ብር እንደሚጠይቁ ሚኑውን ሳይ ብረዳም “አንዴ ገብቻለሁ” በሚል (የሃበሻ) ይሉኝታ አዘዝኩ፡፡
ማኪያቶው (ሶስቴ ፉት ብልለት በሚያልቅ መጠን እንስ ባለች ስኒ) ሲመጣ ባሬስታው በማኪያቶው አናት ላይ በአረፋ የሰራው የልብ ቅርፅ ወደ አንድ ጎን መንሻፈፉን ሳይ ተበሳጨሁ፡፡
አንዳንድ ሰው፣ ‹‹አሁን ይሄ ምኑ ያበሳጫል…አርፈሽ አትጠጪውም›› ሊል ይችላል…ግን እስቲ ትንሽ ረጋ ብላችሁ አስቡት፤ 140 ብር የተከፈለበትን ማኪያቶ ላይ ልብ የሚስል ባሬስታ የስእል ችሎታው ከአፈወርቅ ተክሌ ጋር ሊስተካከል አይገባም…?
አለበለዚያ ለዚህች ፉት ሲሏት ጭልጥ ለምትል ተራ ማኪያቶ ይሄ ሁሉ ክፍያ ለምንድነው…ለጠማማ ልብ?
በማኪያቶው ጉዳይ የሆንኩትን ለጓደኛዬ ስነግራት፣
‹‹እዛ ቤት እኮ ማኪያቷቸው ምርጥ ነው፡፡ ዋናው መጣፈጡ ነው፡፡ ልቡን አትበይው›› ብላ ነገሩን አጣጣለችብኝ፡፡
‹‹ ሴትዮ…ያለነው 2017 ላይ ነው…ማኪያቶ መጣፈጥም ማማርም አለበት..በተለይ በዚህ ዋጋ›› ብያት ተነስቼ ሄድኩ፡፡
በዚህ ጠባዬ ሳቢያ የአዲሳባ ምግብ ቤቶች የእኔን ጨጓራ በመላጥ የሚደርስባቸው የለም፡፡
ባለፈው አንዱ ጋር ለቁርስ ገብቼ ፍርፍር አዘዝኩ፡፡ ሲመጣ ምን ሆኖ መጣ…?
ግማሾቹ እንጀራዎች በብረት ዘነዘና የተቀጠቀጡ ያህል ደቀው ቁሌቱ ውስጥ ቦክተዋል፤ ሌሎቹ ደግሞ በረጅሙ እንደተጠቀለሉ ሳይቆራረጡ ከቁሌቱ ሳይደርሳቸው ደረቅ ግንድ መስለው ተጋድመዋል፡፡
‹‹ ይሄንማ ፍርፍር ብዬ አልበላም›› ብዬ የነገርኩት አስተናጋጅ እንዳበድኩ ዓይነት ሲያየኝ መልሼ አፈጠጥኩበት፡፡
ማምረሬ ሲገባው ፍርፍር ብሎ ያመጣውን ነገር በሃፍረት ይዞ ተመለሰ፡፡
አንዴ ደግሞ ስለቸኮልኩ ራይድ ጠራሁ፡፡
ሲደርስ በጣም ፈዛዛ ወይን ጠጅ ቪትዝ ነው፡፡
አፕሊኬሽኑ ላይ ቀለሙ ‹‹ወይን ጠጅ›› ተብሎ ስለተመዘገበ ስጋት ሽው አለኝና ሳልገባ በፊት ጎንበስ ብዬ ለሹፌሩ ይሄንኑ ነገርኩት፡፡
ሳቁ እያፈነው፣ ‹‹ፀሃይ መቷት ነው›› ብሎ አቃለለው፡፡
የታርጋ ቁጥሩን አመሳክሬ ካየሁ በኋላ ስለቸኮልኩ ከነቅሬታዬ ገባሁ፡፡
መኪናዋ ውስጥ እንደገባሁ ከባድ እፍነትና ሙቀት ተቀበለኝ፡፡
ወቅቱ በጋ ነው፣ ሰአቱ ቀትር፡፡
ከስር የሚንቀለቀል እሳት፣ ከላይ የተቃጠለ ኩበት ተደርጎ አክንባሎ እንደተደፋበት ድፎ ዳቦ ሰራኝ፡፡
ዋናው መንገድ ላይ ስንወጣማ ባሰብኝ፡፡
‹‹በጣም ይሞቃል- ኤሲውን ታበራው?›› አልኩኝ ለታሪክ በሚቀመጥ ትህትና፡፡
በታላቅ መገረም፤ ‹‹ኤሲ ነው ያልሽው…እንዴ! ..ኤሲማ አላበራም ነዳጅ ይበላብኛል…ከፈለግሽ መስኮቱን ክፈቺው›› አለኝ፡፡
ሁኔታው ኤሲ እንዲከፍት ሳይሆን የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለውጥ ችግር እንዲፈታ የጠየቅኩት ነው የሚመስለው፡፡
እኔ የምለው…የምከፍለው ለነዳጁም አይደለም እንዴ…?.ደግሞስ መገናኛ መሃል መስኮቴን ከፍቼ “ስልኬን ብሉኝ “ የምል ጅል እመስለዋለሁ?
ሆ! ሰው ማፈር አቆመ እኮ እናንተ፡፡
ለዚህ ለዚህማ ባይመቸኝ እንኳን አንከውክዎ የሚያደርሰኝ ሚኒባሴ ምናለኝ፡፡
ከብሬም ከምቾቴም ሳልሆን ስልኬን ከድሮን ጥቃት እንደምጠብቅ ሁሉ ከልዬ መስኮቱን ከፈትኩና ሄድኩ እላችኋለሁ፡፡
እዚህ ሃገር ከፍለውም፣ መሰረታዊም ቢሆን ደህና ነገር መጠየቅ አበሳ ነው መቼስ፡፡
ብቻ አያችሁ አይደል…እኔ የአመክንዮ ሰው ነኝ..ቀበጥ አይደለሁ፣ ብዙ ነገር አልጠይቅም ግን ትንሽዋን ነገር እንኳን ስጠይቅ ቀይ ባህርን ለሁለት ክፈሉልኝ ብዬ የጠየቅኩ ያህል ይገንብኛል፡፡
ነገሬን ለማሳመን አንድ ሌላ ነገር ልጨምርላችሁና ልልቀቃችሁማ፡፡
ሰሞኑን ሰርግ ተጠርቼ ነበር፡፡ በሰርግ ወረቀት፡፡
ግን ቀረሁ፡፡ የቀረሁት ደግሞ እንዲሁ በትንሽ ጉዳይ አይደለም፡፡
የጥሪውን ወረቀት ከፍቼ ሳነበው የሚዘገንን ነገር አየሁ፡፡
ከሙሽሪት ስም በፊት በ‹‹ወይዘሪት›› ፈንታ ‹‹ወይዘሮ›› ብለው ፅፈዋል፡፡
ይቅርታ ግን…ሙሽራዋ በጋብቻ ላይ ጋብቻ እየፈፀመች ነው ወይስ ነገሩ እንዴት ነው…? በእኔ እይታ፣ ይሄ ትልቅና ይቅር የማይባል በአማርኛችን ላይ የተፈፀመ ወንጀል ነው…
‹‹ይሄንን ስህተት እንደ ዋዛ የሰሩ ሰዎችን ሰርግ ታድሜ ተጋቡ አልልም›› ስል ጓደኞቼ እንደ ንክ ሰው እያዩኝ ነበር፡፡
አልፈርድባቸውም፤ እንዲህ ያለው ስህተት በተጋቢዎቹ ላይ እያደር የሚያመጣውን መዘዝ ስላልተረዱት ነው፡፡
ለማንኛውም ከወረደው ሰው ጋር ሁሉ አልውረድ እንጂ ራሴን ማሻሻል የምጠላ ሰው ስላልሆንኩ ከትላንት በስቲያ ወደ አንዱ (ደህና የምለው) ምግብ ቤት ሄጄ ነበር፡፡
‹‹እስቲ ለ24 ሰአት ምንም እንከን ሳላይ፣ አቃቂር ሳላወጣ እንደ ሌላው ሃበሻ ልዋልና ልደር›› ብዬ ራሴን ልፈትን፡፡
ገባሁ፡፡ ተቀመጥኩ፡፡ የምፈልገውን ምግብ አዘዝኩ፡፡
ከአስር ደቂቃ በላይ ለማይፈጅ ምግብ 11 ደቂቃ አስጠበቁኝ (ቻልኩት)
የምጠጣው ነገር ቀድሞ ይምጣልኝ ብልም አስተናጋጇን ማስታወስ ነበረብኝ (እሱንም ቻልኩት)
ያመጣችልን የሚጠጣ ነገር ካዘዝኩት በተቃራኒ ቀዝቀዛ ነበር፡፡ እኔ የጠየቅኩት " ቀዝቀዝ" እንዲል ነበር። ሎሚ ረስታለች (ይህንንም ቻልኩት)
በመጨረሻ ምግቡ መጣ፡፡
የቀረበውን ነገር ሳየው ግን መቻል አቃተኝ፡፡
ከሩዝ በአትክልት ጋር እንጀራ አጃቢ ሆኖ መጥቶልኛል፡፡
ይሄን ጊዜ ያችኑ ቀልብ የሌላትን አስተናጋጅ ጠራሁና፣
በትህትና- በጣም በትህትና- ሩዜ ከእንጀራ ጋር የመጣበትን ምክንያት ጠየቅኳት፡፡
‹‹አንዳንድ ሰው እንጀራ ስለሚፈልግ ነው፡፡ በዚያ ላይ ዳቦም አምጥተንልሻል እኮ…በዳቦ መብላት ከፈለግሽ›› አለችኝ ዳቦና እንጀራው አጠገብ ለአጠገብ ተሰትሮ የተቀመጠበትን የእንጨት ትሪ እያሳየችኝ፡፡
ልክ እስካሁን ዳቦ መኖሩን እንዳላየሁት ሁሉ፡፡