የቀጠለ ...
የእግዚአብሔር ቃል እውቀት
የእግዚአብሔር ቃል እውቀት የሌላቸው ሰዎች ትክክለኛው መንገድ (ሃይማኖት) የቱ እንደሆነ መጠየቃቸው የተለመደ ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም የየትኛውም የሃይማኖት ድርጅት ስም ባለመጻፉ የትኛው ሃይማኖት ትክክል እንደሆነ ለማወቅ በመፈለግ ግራ ይጋባሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ጥያቄም ሆነ ግራ መጋባት ሊመጣ የሚችለው የእግዚአብሔርን ቃል በጥልቀት ካለመረዳት ነው፤ ምክንያቱም እንደ እግዚአብሔር ቃል ስናስብ እግዚአብሔር ሰዎችን ሁሉ የሚጠራው ልጁን አምኖ ወደመከተል እንጂ ወደ የትኛውም የሃይማኖት ጎራ አይደለምና፡፡
ሰው ላለመሳሳት ከፈለገ ዛሬም ያለው አማራጭ የእግዚአብሔርን ቃል ማወቅና የተጻፈውን ሁሉ አንድም ሳይቀር አምኖ መቀበል ብቻ ነው፤ ይህ ካልሆነ ግን «መጽሐፍ ቅዱስ አለኝ፤ ከቤቴም አኑሬዋለሁ» ማለቱ ብቻውን ከስህተት አያድንም፤ ክብር ይግባውና ጌታ ኢየሱስም መጻሕፍቱ እያሏቸው በእምነት ነገር የሳቱ ፈሪሳውያንን «መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል አታውቁምና ትስታላችሁ» ብሎአቸው ነበር፤ (ማቴ.22፡29፣ ማር.12፡24)፡፡
በዕለታዊ ኑሮም ቢሆን ከስህተት የምንጠበቀው የእግዚአብሔር ቃል እውቀት ሲኖረን ነው፤ መዝሙረኛው ዳዊት ስለዚህ ሲናገር «ጐልማሳ መንገዱን በምን ያነፃል? ቃልህን በመጠበቅ ነው» (መዝ.118፡9)፣ «አንተን እንዳልበድል ቃልህን በልቤ ሰወርኩ (ቊ.11)፣ «ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው» (ቊ.105) «ከቃልህ የተነሣ አስተዋልሁ፣ ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ»(ቊ.104) ብሏል፡፡
2. ላለመጥፋት ይጠቅማል
በጥንት ዘመን እንደነበረ በመጽሐፍ የተመዘገበለት ነገር ግን በአሁን ጊዜ የሌለ የቀደመው ዓለም የጠፋው የእግዚአብሔር ቃል እውቀት ስላልነበረው ነው፤ ከጥፋት ውኃ በፊት የነበረው ያ ዓለም ከሌሎች ሰባት ጋር ጽድቅን የሚሰብከውን ኖኅን ሊሰማው አልቻለም ነበር (2ጴጥ.2፡5)፤ «በዚህም ምክንያት ያን ጊዜ የነበረው ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ» (2ጴጥ.3፡6)፤ ምክንያቱም አላዋቂነትን ወደው ነበርና (ምሳ.1፡22)፡፡ ግለሰብም ሆነ ሕዝብ እንዲሁም አገር የሚጠፉበት ዋነኛው ምክንያት የእግዚአብሔርን ቃል ካለማወቅ የተነሣ በሚፈጸሙ መንፈሳዊና ሥጋዊ በደሎች ነው፡፡ ሰው የጌታን ቃል ካላወቀ መጥፋቱ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ከበደሉ የተነሣ በእግዚአብሔር ፍርድ የሚጠፋ ሁሉ አስቀድሞውኑ የእግዚአብሔር ቃል እውቀት ማጣቱ ከእግዚአብሔር ፊት ያጠፋው(ያራቀው) መሆኑ ግልጥ ነው፤ ከዚህም አንጻር ስለጠፉት ቤተ እስራኤል «ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአልና» ተብሎ ተነግሯል (ሆሴ.4፡6)፡፡ እዚህ ላይ ሕዝበ እስራኤልን የሚያስተምር ሰው አልነበረምን? ብሎ መጠየቁ መልካም ነው፤ እስራኤል የሚያስተምሯቸው መምህራን፣ መሥዋዕት የሚያቀርቡላቸው ካህናት፣ ትንቢት የሚናገሩላቸው ነቢያት እንደዚሁም የሚያነቧቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ነበሯቸው፡፡ ችግሩ ግን ነቢያት የሚናገሩትንና መጻሕፍት የሚመሰክሩትን የእግዚአብሔርን ቃል አውቀው አለመታዘዛቸው ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም ስለ አንድ ባለጠጋ ሰውና ስለደሃው አልዓዛር የተናገረው ታሪክ ሰው በእጁ ያሉትን መጻሕፍት በመጠቀም ከፍርድ የሚድንበትን የእግዚአብሔር ቃል እውቀት መያዝ እንደሚኖርበት ያስረዳል (ሉቃ.16፡27-31)፡፡ እንግዲህ ላለመጥፋት ከተፈለገ መፍትሔው የእግዚአብሔርን ቃል አውቆ መገኘት ብቻ ነው፡፡
3. ለሚጠይቁን ለመመለስ ይጠቅማል
ብዙውን ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል እውቀት በሚገባ ሳይኖር ሲቀር በእምነት ነገር አላዋቂ ከሆኑ ወይም ከማያምኑ ሰዎች ለሚቀርቡ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ መስጠት አይቻልም፡፡ ማንኛውም አማኝ ስለሚያምነው ነገር በተጠየቀ ጊዜ መልስ መስጠት ይችል ዘንድ የእግዚአብሔር ቃል ዕውቀት በሙላት ሊኖረው ይገባል፤ ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር «የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ» ይላል (ቈላ.3፡16)፤ እንደዚሁም በሌላ ስፍራ «በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያት ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት የተዘጋጃችሁ ሁኑ» ይላል (1ጴጥ.3፡15)፤ ዳግመኛም «ለሚጠይቅህም እውነትን ቃል መመለስ ይቻልህ ዘንድ በምክርና በዕውቀት የከበረን ነገር አልፃፍሁልህምን?» የሚል እናነባለን (ምሳ.22፡21)፡፡
የቃሉ እውቀት አስተማሪ
ብዙዎች እንደሚያስቡትና እንደሚናገሩት መጽሐፍ ቅዱስ የተደበቀና የተሸሸገ ምሥጢር አይደለም፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ «የአፌ ቃላት ሁሉ ጽድቅ ናቸው፤ ጠማማ ዘወርዋራም አይደሉም፤ እነርሱ በሚያስተውሉ ዘንድ የቀኑ ናቸው፤ ዕውቀትንም ካገኙአት ሰዎች ጋር የተስማሙ ናቸው» ተብሎ ተነግሮአል (ምሳ.8፡8)፤ ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው እግዚአብሔርን በሚፈልግ እውነተኛ ልብ ሆኖ ቢያነበው የቃሉን እውቀት በመንፈስ ቅዱስ አስተማሪነት ይማራል (ዮሐ.14፡26)፤ ይህ አስተማሪም ሁሌ ከተማሪው አይለይም፤ በየትኛውም ሰዓትና ጊዜ እንዲሁም ቦታ ይህ አስተማሪ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡትን ሁሉ ሲረዳ ይኖራል፤ እርሱ የሚመጣና የሚሄድ አይደለም፤ ስለእርሱም «አስተማሪህ ከአንተ ከእንግዲህ አይሰወርም ... ጆሮችህ በኋላህ መንገድህ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ» ተብሏል (ኢሳ.30፡21)፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ለጃንደረባው እንዳደረገው መንፈስ ቅዱስ ለአንባቢው መጻሕፍትን በማብራራት የሚመራውን ሰው ይልክለታል (ሐዋ.ሥራ8፡29-35)፡፡
ምንም እንኳ መታዘዝ ስለማንችል አእምሮአችን እንዳይወቅሰን መጽሐፍ ቅዱስን ባናነብ ይሻለናል የሚሉ ሰዎች ቢኖሩም ያለእግዚአብሔር እውቀት መኖራቸው ከተጠያቂነት ስለማያድናቸው መልካም አይሆንላቸውም፤ ምክንያቱም «ነፍስ ዕውቀት የሌላት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም» ተብሎአልና (ምሳ.19፡2)፡፡
ምንጭ:- ewnetone.com
ወደ ቻናሉ ለመ🀄️ላ🀄️ል፦ @Holy_scriptures