የክርስትና ሕይወት ምስክርነት
ጌታ ኢየሱስን መከተል ከጀመርኩ 17 ዓመታትን አስቆጠርኩ ይገርመኛል ሳስበው የዛሬ አስራ ሠባት ዓመት በአንድ ድርጅት ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ ተቀጥሬ ለመስራት ከቤተሠቦቼ ቤት የወጣሁበት ጊዜ ነበር። ለመስራት የወሰንኩት ደሞ አባቴ በወቅቱ በነበረው መንግስት ስደት ላይ ስለነበረ እና ለቤቱ ደግሞ የመጀመሪያልጅ ስለሆንኩ ሀላፊነቴን ለቤተሠቦቼ ለመወጣት ነበር ። ከእኔ ታናናሾች 4 ወርቅ የሆኑ እህቶች እና አንድ እንቁ ጀግና ወንድም ነበረኝ ።
ለእህቶቼ ያለኝ ፍቅር እንዲህ ነው ብዬ መግለጥ አልችልም ይሄንን የበኩር ልጅ የሆናችሁ ታውቁታላችሁ 😍 ።
እናማ ተቀጥሬ ስራ የጀመርኩበት ድርጅት ከባለቤቷ ጀምሮ በዛው ድርጅት ተቀጥረው የሚሠሩት በአብዛኛው ክርስቲያኖች ነበሩ ። እኔ ደሞ በወቅቱ ፍንዳታ ነበርኩ። 🤣😂 ስቄ ልለፈው እንጂ ጉዱ ብዙ ነው።
ለማንኛውም የምሠራበት ቦታ ሁለት የተባረኩ እህቶች የሕይወት ምልልስ ያስገርመኝ ነበር እናም ትኩረቴን ሳቡት ከኢየሱስ ውጪ ወሬ የሌላቸው በጣም ቅን የፍቅር ሰዎች ነበሩ እናማ እነሱን አተኩሬ እከታተል ነበር ። በህይወታቸው እማረክ ጀመር ፤ ቀስ እያልኩ ተጠጋዋቸው ቀስ በቀስ እንዲጸልዩልኝ ፍቃደኛ ሆንኩ ቀጠል አድርጌ በሞባይሌ መዝሙር እንዲጭኑልኝ አደረኩ ወደ ክለብም እሄዳለሁ መዝሙሯም ውስጥ ውስጤን ትሠረስረው ጀመረ ዘፈን እየጠላሁ ወደ መዝሙሩ እየተሳብኩ ሄድኩኝ።
በዚህ መካከል ታዲያ በሕይወቴ ከባድ ነገር ሆነ እዚህ ላይ አሁን መናገር የማልችለው የእግዚአብሔርን እጅ በብርቱ አየሁኝ በዚህ መካከል የእነዚህ እህቶች ጸሎት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።
በዚሁ ነገር ምክንያት ስራዬን ትቼ ለሦስት ቀናት ያህል እቤቴ እግዚአብሔርን በማመስገን በልቅሶ እና በታላቅ ጥያቄ ተሞልቼ በቤቴ ተቀመጥኩ በዚህ መካከል ታዲያ በቤተሰቦቼ ቤት ውስጥ ያገኝሁትን መጽሐፍ ቅዱስ አንስቼ ከዘፍጥረት ጀምሬ ማንበብ ጀመርኩ የማያቋርጥ ጥያቄ ውስጥ ገባሁ፤ እናቴን ቤት ውስጥ እየተከተልኩ በጥያቄ ጨቀጨኳት የእኔ ደግ እናት ለጥያቄ መልስ ልትሠጠኝ አልቻለችም ።
የእኔ ማንበብ እና ጥያቄ ግን ማቆሚያ አጣ ስራውንም እርግፍ አድርጌ ትቼ ማንበቤን ማቆም እስኪያቅተኝ ቀጠልኩ ጭራሺ በለሊት ተኘስቼ ተንበርክኬ መጸለይ ጀመርኩ።🙏
"እግዚአብሔር የት ነው ያለኸው? እኔ መማር ነኝ ታውቀኛለህ? እኔ እፈልግሀለሁ ብዙ ዝምታ..................😭 እፈልግሀለሁ" ቀጠልኩ አንድ ሳምንት ሆነኝ ከዛ በኋላ ከላይ ያነሳሁላችሁ እህቶች በአንዷ ቤት ለማደር በሳምንቱ መጨረሻ አካባቢ ተቀጣጥረን ስለነበር ሄድኩኝ። በመሸም ግዜ እራት ልንበላ ተሰብስበን እያለ ለባለቤቱ አንድ ስልክ ተደወለ ሠላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ይህ ወንድም እባክህ ቅርብ ነውኮ ያለኸው ሠላም ብለኸን እለፍ እያለ በስልክ ውስጥ ለሚያወራው ሰው ይለምነው ጀመር ከጥቂት ምልልሶች በኋላ ስልኩን ዘግቶ ቆይ እንግዶች እየመጡ ነው እንጠብቃቸው አለ።
ተስማምተን ቁጭ እንዳልን ወዲያው የቤቱ በር ተንኳኳ በሩ ሲከፈት ሁለት ሰዎች ተከታትለው ገቡ ከወንበራችን ተነሳን ሠላም ተባባልን ገብተው ቁጭ አሉ ቤቱ ሞቅ አለ ሠላምታ ተለዋወጡ እና እራት እንዲበሉ የእጅ ውሃ ቀረበ ትንሺ ተግደረደሩና ልመናው ሲበዛ እሺ ብለው ታጠቡ ።
ለምግቡ እንዲጸልይ ሁለተኛ ሁኖ የመጣው እንግዳው ሰው ተጋበዘ እሺ አለና ተነስቶ መጸለይ እንደጀመረ ቆይ እስቲ ከምግቡ በፊት እንጸልይ በደንብ ብሎ ጸሎት ጀመረ ። ይሄ ሰው ከበሩ እንደገቡ ለቤቱ ባለቤት እንግዳ ሰው እንደነበረ አውቂያለሁ ስሙን አስተዋወቀ ቀጠል አድርጎ ጓደኛው አገልጋይ ነው ወንጌላዊ እከሌ ይባላል ብሎ ስለሱ ሲናገር ሰምቺያለሁ።
እኔ ወደ ጴንጤዎች ቸርች ከዛን በፊት የሄድኩት ሁለት ቀን ነው ሁለቱም ቀን የሄድኩት ለማሾፍ ነበር የተሠበከውንም አላስታውስም በጭራሺ። ጴንጤ ጓደኞች ነበሩኝ ሁሉም በተቻላቸው መጠን ሊነግሩኝ ሞክረዋል እኔ ግን ከባድ ተከራካሪ ነበርኩ በእውቀት ሳይሆን🤣 በአልሸነፍ ባይነት ላለመረታት ግን ምንም ነገር አላውቅም ነበር ከእውቀት ነጻ ኃጢያተኛ ነበርኩ🤣🤣🤣 ።
ወደ ዋናው ሀሳቤ ስመለስ ይሄ ሰው ለምግቡ ሊጸልይ ተነስቶ አቅጣጫውን ቀይሮ ሞቅ ያለ ጸሎት ውስጥ ገባ በልቤ እግዚአብሔርን መፈለግ ከፍተኛ ጥማት ውስጥ ብሆንም ጴንጤ የመሆን ፍላጎት የለኝም ነበር። እንደውም እረስቼው ያልነገርኳችሁ ነገር በየትኛው ቀን እንደሆን እንጃ እንጂ ወደ ቦሌ መድሃኒያለም አዲስ ነጭ ነጠላ ገዝቼ ሂጄ ውስጥ መቅደሱ በር ላይ ተንበርክኬ አይኔ ሊወጣ እስኪደርስ ድረስ እያለቀስኩ እግዚአብሔር ይቅር እንዲለኝ ከጸለይኩ በኋላ ከዛው ከቤተክርስቲያኑ ግቢ ሳልወጣ መጀመሪያ ለእናቴ ደውዬ ስላጠፋሁት ጥፋት ዘርዝሬ ተናግሬ ይቅርታ ጠይቄ በመቀጠል አሁን እነማን እንደሆኑ ለማላስታውሳቸውም ሰዎች ደውዬ ይቅርታ መጠየቄን አስታውሳለሁ። የሚገርማችሁ በህይወቴ ምን እየተከናወነ እንደሆነ አላውቅም ነበር። ወይ ጌታ ሆይ በዚህ ሠዓት ይሄንን ለመጻፍ ምን እንዳነሳሳኝ አላውቅም ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ግን
ፍቅሩ ነው የማረከኝ እያልኩ እየዘመርኩ ነበር።
እናላችሁ ይሄ ወንጌላዊ እየጸለየ በመሃል ስለእኔ ጌታ የሚለውን ማለት ጀመረ ቀና ብዬ አየሁት በልቤ የማዋል እንዴ? አልኩ። ጭራሺ እግዚአብሔርን አናግረዋለሁ? ነገረኝ ይላል እንዴ ? ደፋር እላለሁ እሱ ግን ቀጠለ ግራ ገባኝ ማን ነው የነገረው? ግራ ገባኝ ሁለቱን እህቶች ተጠራጠርኳቸው አስጠሉኝ እኔ በበኩሌ ጴንጤ አልሆንም ሙግት ውስጥ ገባሁ ወዲያው ጣራ ቀደው ገንዘብ ያዘንባሉ የሚባለው ነገር ትዝ አለኝ🤣🤣🤣🤣
ቀጠለ ከልጅነቴ ጀምሮ እስከዛች ቀን ድረስ ልክደው ልደራደርበት ያመልችላቸውን ነገሮች ይገልጥ ጀመረ ግራ ገባኝ እየደጋገመ "በህይወት ኑሪ አልኩሺ " ይለኝ ነበር የሆነ ነገር ልቤ ውስጥ ገብቶ ፍንቅል አደረገኝ ልቤ ቀለጠች "እግዚአብሔር ይወድሻል" " እወድሻለሁ" ይልሻል አለኝ እኔን? ማወቁ ሲገርመኝ መወደዴ ይድነቃችሁ። 😭😭😭
በዚህ ሁሉ ግዜ ውስጥ ግን ይሄ አገልጋይ የሚናገረኝ እንደ ጴንጤ አድርጎ ነበር በውስጤ እኔኮ ጴንጤ አይደለሁም እላለሁ "ነፍስሺ የተወደደች ናት" አለኝ አንዳንዱ ነገር በውስጤ ለምጠይቀው ጥያቄ እዛው መልስ ነበረው እስካሁን ይገርመኛል።
የሚገርማችሁ ነገር እስከዛሬዋ ቀን ድረስ የሚፈጸመው ነገር ሁሉ በዛች ቀን የተነገረኝ ነገር ነው የሚቀሩ ነገሮች አሉ በእርግጥ የሚገርመኝ ለእኔ አንድ ወመኔ እግዚአብሔር ለ1:30 ያህል መናገሩ እና በወቅቱ ስለማይገቡኝ ነገሮች መናገሩ ይደንቀኛል ።
ከሰዓታት ጸሎት በኋላ ጸሎቱን ጨረሰና ቁጭ ሊል ሲል እነዚህ የተወደዱ እህቶች ፈራ ተባ እያሉ ጌታን አታውቅምኮ አሉት በዚህ መካከልም አንድ ነገር ተከናውኖ ነበር አሁን ማንሳት አልችልም ምክንያቱም እሱን ነገር ለማውራት ሰፋ ያለ ገለጣ ስለሚያስፈልገው ነው በወቅቱ እነሱንም አደናግጦ ስለነበረ የመንፈስ ቅዱስ ስራ ነው በዓካል ለሚጠይቀኝ ግን አሁን መልስ አለኝ ብቻ እግዚአብሔር ትልቅ ነው እኛም አናውቀውም!!!!