ነገር ግን ፤ በ20ና በ25 ሺ ብር ደሞዝ የ70 ሺ ብር ኮትና ሱሪ ለብሰው፣ የ15 ሺ ብር ሸሚዝ አድርገው ፣ የ30 ሺ ብር ጫማ ተጫምተው፣ የ15 ሺ ብር ሰዓት አስረው የ7 ሚሊየን ብር ተሽከርካሪ እያሽከረከሩና የ30 እና የ40 ሚሊየን ብር ቤት ውስጥ የሚምነሸነሹ ተሿሚዋች፣
ሴቶቹ ከሆኑ ደግሞ የ50 ሺህ ብር ሒውማን ሔይር ተላብሰው፣ የ60 ሺ ብር ካፓርት ደርበው፣ የ20 ሺህ ብር መነጽር አንጽረው፣ የ30 ሺህ ብር ጫማ ተጫምተው፣ የ36 ሺ ብር ቦርሳ አንግተው መድረክ ላይ እየተውረገረጉ ምንጩ ያልታወቀ ሐብት በዝቷል እንወርሳለን፣ ነጋዴውና ባለሀብቱ ሙሰኛ ነው፣ ኦዲት እናደርገዋለን፣ ሕዝቡ በቂ ግብር ስለማይከፍል ላቡን አንጠፍጥፎ በሰራው ቤት ላይ በነጻ ስለሚኖር ግብር መክፈል አለበት የሚሉ ሰዎችን ማዳመጥ የሚሰቀጥጥና የሚያሸማቅቅ ነገር ነው ።
ይሉሽን በሰማሽ ገበያም ባልወጣሽ እንዲሉ መጀመርያ ማን ማንን ነው የሚወቅሰው? ኦዲት የሚያደርገው ? እራሱ ግብር ሳይከፍል ግብር የሚያስከፍለው ? ምንጩ ባልታወቀ ሐብት የሚንፈላሰሰው፣ በሙስና ስለተገኘና ምንጩ ባልታወቀ ሐብት መጠርጠር፣ መመርመርና ኦዲት መደረግ ያለበትስ ማን ነው ?!
በኑሮ፣ ውድነት የሚፈተነው ሕዝብ፣ ነጋዴውና ባለሐብቱ፣ እድሜ ልኩን ጥሮ ግሮ ባፈራው ጥሪት መኖርያ የቀለሰው ታታሪ ደሞዝተኛ ወይስ በ20 እና በ30 ሺ ብር ደሞዝ በውድ ሸቀጣ ሸቀጥ የሚንቆጠቆጠው፣ ውድ ሽቶ የሚርከፈከፍው፣ በቅንጡ ተሽከርካሪ ከነቤተሰቡ የሚምነሸነሸውና በመንግሰት ደሞዝ ልጆቹን ውጭ ሀገር እያስተማረ በዓመት ሁለቴ ዱባይ ካናዳና አሜሪካ የሚመላለሰው !!??»
ሙሼ ሰሙ