መጥፎ የአፍ ጠረን የአለማችንን 25% የሚሆን ማህበረሰብ ያጠቃል። ለችግሩ ብዙ መነሻ ምክንያቶች ቢኖሩም አብዛኛውን ግዜ መነሻው ከአፋችን ነው።
ስለ መጥፎ የአፎ ጠረን (ሐሊቶሲስ/ halitosis) እውነታዎች
-መጥፎ የአፍ ጠረን ከ4 ሰዎች በአንዱ ላይ ይከሰታል
-አብዛኛው መነሻ ምክንያቱ የጥርስ እና የአፋችንን ንፅህና (oral hygiene) በደንብ ባለመጠበቅ የሚመጣ ነው።
-የበላነው ምግብ አፋችን ውስጥ ይቀእና ሰልፈር ወደሚባለው ንጥረ ነገር በባክቴሪያ ምክንያት ተከፋፍሎ መጥፍ የአፍ ጠረን ያመጣል
-ዋናው በቤት ውስጥ ማድረግ የምንችለው ህክምናም ጥርሳችንን ማፅዳት፣ ፍሎስ ማድረግ እና በቂ የሆነ ውሀ መጠጣት ናቸው።
መጥፎ የአፍ ጠረን (halitosis) ምንድን ነው?
መጥፎ የአፍ ጠረን በጣም የተለመደ እና በራስ መተማመንን የሚቀንስ በሽታ ነው። በጣም ብዙ መነሻ ምክንያቶች እና መፍትሄዎችም አሉት። ማንኛውም ሰው መጥፎ የአፍ ጠረን ሊያጋጥመው ይችላል። ከ4 አንድ ሰው ላይም ያጋጥማል። ወደ ጥርስ ሀኪም ከሚያስኬዱ መነሻ ምክንያቶችም 3ኛ ነው። ከጥርስ መቦርቦር እና ከድድ ችግር ቀጥሎ
አንዳንድ በቤት ውስጥ ልናደርጋቸው የምንችላቸው ነገሮች ለምሳሌ ጥርሳችንን እና አፋችንን ማፅዳት ፣ ሲጋራ ማጨስ እንዲሁም ጫት መቃም ማቆም ችግሩን እስከነአካቴው ያቆሙልናል ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን ወደ ጥርስ ሀኪም መሄድ ያስፈልጋል።
ህክምናው
- ለመጥፎ የአፍ ጠረን ዋናው ህክምና ጥሩ የሆነ የጥርስ እና የአፍ ማፅዳት ልማድን (good oral hygiene) ማዳበር ነው። ተያይዞም ጥርሳችን እንዳይቦረቦር እና ድዳችን እንዳይጎዳ ይረዳናል።
- በአመት ቢቻል አንድ ግዜ የጥርስ ቼክ አፕ ማድረግ
- የጥርስ ሀኪምዎ ባክቴሪያን የሚቀንሱ መጉመጥመጫዎች ሊያዝሎት ይችላል እንዲሁም የጥርስ እጥበት እንዲያደርጉ ሊመክሮት ይችላል።
መነሻ ምክንያቶች
- ሲጋራ
- ምግብ ፦ የበላነው ምግብ ጥርሳችን ላይ ተጣብቆ መጥፎ የአፍ ጠረን ሊያመጣብን ይችላል። በተለይ ቀይ እና ነጭ ሽንኩርት ከተፈጨ በኋላ እንኳን በደም ስራችን አልፎ ወደ ሳንባችን ደርሶ ስንተነፍስ ሊሸት ይችላል።
- ደረቅ አፍ (dry mouth)፦ በተፈጥሮ ምራቃችን አፋችንን ያጥብልናል። አፋችንን ደረቅ ከሆነ ግን መጥፎ የአፍ ጠረን ይከሰታል።
- ጥርሳችንን እና አፋችንን የማፅዳት ልማድ፦ ጥርሳችንን በምንቦርሽበት እና ፍሎስ በምናደርግበት ግዜ አፋችን ውስጥ ያለው ምግብ ተፀድቶ ይወጣል ካልወጣ ግን በባክቴሪያዎች አማካኝነት ተከፋፍሎ ችግሩ እንዲከሰት ያደርጋል።
- የምግብ ሰዓትን ጠብቆ አለመብላት፦ መፆም እና ካርቦሀይድሬት ያነሳቸውን ምግቦችን መመገብ መጥፎ የአፍ ጠረን እንዲኖረን ያደርጋል ምክንያቱ ደግሞ ሰውነታችን ያጠራቀመውን ስብሰባብሮ ሲጠቀም ኬቶን (ketones) የሚባል ኬሚካል ያመነጫል ይህም ከፍተኛ ሽታ የመጣል።
- መድሀኒቶች፦ አንዳንድ መድሀኒቶች አፋችን እንዲደርቅ ያደርጋሉ ሌሎች ደግሞ ሲሰባበሩ የራሳቸው የሆነ ሽታ ይፈጥራሉ።
- የአፍ የአፍንጫና የጉሮሮ ችግር፦ አንዳንድ ግዜ ትንንሽ ባክቴሪያዎች ከቶንሲላችን ጀርባ እንደ ድንጋይ ተሰባስበው ይገኙና መጥፎ ጠረን ይፈጥራሉ። በተጨማሪም የአፍንጫ የጉሮሮ ወይም የሳይነስ ኢንፌክሽን እና መቆጣት የአፍ ጠረን ሊያመጣ ይችላል።
- የውስጥ በሽታ፦ አንዳንድ ካንሰር ፣ የጉበት ስራ ማቆም (liver failure) እና ሌሎች ከምግብ መፈጨት ጋር የተገናኙ በሽታዎች የአፍ ጠረን ሊያመጡ ይችላሉ ምክንያቱ ደግሞ የሚፈጥሩት ኬሚካሎች ናቸው። እንዲሁም የጨጓራ ህመም Gastroesophageal Reflux Disease (GERD) በሚለቀው የጨጓራ አሲድ ምክንያት መነሻ ሊሆን ይችላል።
ከስንት አንድ መነሻ ምክንያቶች
አብዛኛው መጥፎ የአፍ ጠረን መነሻ ምክንያት የአፋችንን ንፅህና በደንብ አለመጠበቅ ቢሆንም ሌሎች መነሻ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላሉ።
1- Ketoacidosis (ኬቶአሲዶሲስ)፦ አንድ ስኳር ህመም ያለበት ሰው ኢንሱሊኑ ዝቅ ሲል ሰውነታቸው ውስጥ ያለውን ስኳር መጠቀም ያቆምና የተጠራቀመውን ስብ ይጠቀማል። ስቡም ሲሰባበር ኬቶን (ketones) ይመረታል ይህም ሲበዛ መጥፎ የአፍ ጠረን ያመጣል እንዲሁም ለህይወት አስጊ የሆነ ጉዳይ ነው።
2- Bowl obstruction (የአንጀት መደፈን)፦ ትንፋሻቸው ሰገራ ሰገራ ሊል ይችላል በተለይ በተደጋጋሚ ማስመለስ ካለ እና የአንጀት መደፈን ካለ።
3- Bronchiectasis (ብሮንካይተስ)፦ የአየር ቧንቧችን ለረጅም ግዜ ኢንፌክሽን ካጋጠመው ሊሰፋና ሙከስ ተጠራቅሞ ለመጥፎ የአፍ ጠረን ሊዳርገን ይችላል።
ምልክቶች
×የአፍ ጠረን ሽታው እንደመነሻ ምክንያቱ ይለያያል። እርግጠኛ ለመሆኖ ጥሩ የሚሆነው ጓደኛችንን ወይም ቅርብ የምንለውን ሰው መጠየቅ ነው ምክንያቱም በራሳችን ለማወቅ እና እርግገኛ ለመሆን ከባድ ስለሆነ።
× ማንም ሰው አጠገባችን ከሌለ በእጃችን በደንብ ተንፍሰን ደረቅ እስኪል ጠብቀን ማሽተት ነው።
× አንዳንድ ሰዎች ግን ምንም አይነት መጥፎ የአፍ ጠረን ሳይኖርባቸው እንዳለባቸው ይሰማቸዋል ይህም halitophobia (ሀሊቶፎቢያ) ይባላል ይህም በከፍተኛ ሁኔታ ጥርሳቸውን የሚያፀዱ ሰዎች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።
እቤት ውስጥ ምን እናድርግ?
፩- ጥርሳችንን ማፅዳት፦ በቀን ቢያንስ 2 ግዜ ለ2 ደቂቃ ተገቢ በሆነ ሁኔታ ጥርሳችንን ማፅዳት
፪- ፍሎስ ማድረግ፦ ፍሎስ ማድረግ በጥርሶቻችን መሀከል የሚጠራቀመውን ምግብ እና ፕላክ ያወጣልናል። በብሩሽ ስናፀዳ የምናገኘው 60% የሚሆነውን የጥርሳችንን ክፍል ነው።
፫- ወጪ ገቢ ጥርስ ፣ አርቴፊሻል፣ ማውዝ ጋርድ፣ ሪቴነር ካለን በየእለቱ ማፅዳት
፬- የጥርስ ብሩሻችንን በየ3 ወሩ መቀየር
፭- ስስ(soft) የጥርስ ብሩሽ መጠቀም
፮- ምላሳችንን ማፅዳት፦ ምላሳችንን ሳሙና በሌለው ብሩሽ በአፍንጫችን እየተነፈስን ማፅዳት ለራሱም የተዘጋጀውን ማፅጃ ካገኘን መጠቀም በተለይ ደግሞ ሲጋራ የሚያጨሱ ፣ ጫት የሚቅሙ እና የአፍ መድረቅ ችግር ያለባቸው ሰዎች ምላስን በደንብ ማፅዳት ያስፈልጋል።
፯- አፋችን እንዳይደርቅ ማድረግ፦ ውሀ በተገቢው መንገድ በደንብ መጠጣት። የአልኮል መጠጥ ሲጋራ እና ጫት ማስወገድ ምክንያቱምየአፍ መድረቅ ስለሚያመጡ። ማስቲካ ማላመጥም ምራቅ እንዲመረት ስለሚረዳ ይመከራል ከተገኘ ስኳር የሌለው።
፰- አመጋገብ፦ ቀይ ሽንኩርት ነጭ ሽንኩርት እና ቅመም የበዛባቸውን ምግቦች ማስወገድ። ጣፋጭ ምግቦችም ከመጥፎ የአፍ ጠረን ጋር ይያያዛሉ። ቡና እና የአልኮል መጠጦችን መቀነስ። ቁርስ ላይ ጠንከር ያለ ምግብ መመገብ የምላሳችን ጀርባ እንዲያፀዳ ይረዳዋል።
ምርመራ
አብዛኛውን ግዜ መጥፎ የአፍ ጠረን አለብኝ ብሎ የመጣን ታካሚ በማሽተት እና ከምላስ ጀርባ ፍቆ በማሽተት ሊታወቅ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ሌሎች የተወሳሰቡ ምርመራዎች አሉ።
የጥርስ ሐኪማችን የመጥፎ አፍ ጠረን መነሻ ምክንያቱን ያገኝልናል። መፍትሄም ይኖረዋል።
አብዛኛውን ግዜ መጥፎ የአፍ ጠረን ከተከሰተብን በኋላ ከላይ ያሉትን ነጥቦች ከተከተልን በቤት ውስጥ ጥንቃቄ ራሱ የሚጠፋ ይሆናል ይህ ካልሆነም የጥርስ ሐኪሞን ማማከር ያስፈልጋል።