Alex Abreham አሌክስ አብረሃም @officialalexabreham Channel on Telegram

Alex Abreham አሌክስ አብረሃም

@officialalexabreham


Alex Abreham አሌክስ አብረሃም (Amharic)

እንኳን ወደ ቴሌግራም አፕ ላይ በደህና መጡ። በዚህ ታሪክ ላይ ያለው የባህል ህክምና እና መረጃ ይህ ነው - Alex Abreham አሌክስ አብረሃም ከሚለው አየር ፕላቶሪያሬት አብረሃም ጋር ሰሄድ። እንዴት እንደምንችል እንችላለን? እርስዎ ማንኛውም ነገር ነህ ማን? ከዚህ እስከ ኢትዮጵያ ብሔራዊ በመጣለው ቆይታ እንዳሉ የባህል ህክምና እና መረጃ የተጠበቁ ሰዎች እና ስለዚህ በሚስጥም ንግግር እንስከፍታለን። Alex Abreham አሌክስ አብረሃም የሚለው ግንብ እውነተኞች ውስጥ ፕላቶሪያሬት እና ትምህርት ስትክስ እና ጠበቆቺዎች አስቀምጠናል። ከዚህ ቻናሌንም በመቀነስ ለማግኘት፣ ለመጽሀፉ እና መተዳደር እንዲሆን አይችልም።

Alex Abreham አሌክስ አብረሃም

23 Nov, 09:45


በነገራችን ላይ የኑሮ ደረጃህን ሁልጊዜ የአለም ባንክ እስኪነግርህ አትጠብቅ። የድህነት ወለል ጣራ እያልክ አትድከም። ድህነትህን ቤት ባፈራው ነገር ለካ። ለምሳሌ ለይሄ ፎቶው ላይ የሚታየው ምንድነው? አየህ! መልስህና አጠቃቀምህ ደረጃህን ይነግርሃል ....ሐብታሞች በብዛት ገዝተው በብዛት ለብር ማስያዣነት ይጠቀሙበታል። ደሀ ሴቶች ለፀጉር ማስያዣ ፣ ደሀና ከይሲ ፈላወች ወስፈንጠር ሰርተው አላፊ አግዳሚ ለመነጀስ ይጠቀሙበታል። አንድ የሀብታም ልጅ በወስፈንጠር ሲጫወት አታገኝም። ይሄን ላስቲክ "ለቁርጥማት ጥሩ ነው" ብሎ እንደብራዝሌት እጁ ላይ የሚያስር ቁርጥማታምም አለ። ምን ላይ ነን ?😀 በነገራችን ላይ ይሄንንም ከቻይና ነው የምናስመጣው አይደል? ቁርጥማቱ እንደአገር ነውኮ!

Alex Abreham አሌክስ አብረሃም

21 Nov, 13:18


ሞት ቅፅበት፣ አለመኖር ግን ዘላለማዊ ነው!

ይሄ እዮብ እዚህ ነበር...አሁን እዚህ የለም። ፎቶውን እዚህና እዛ ባየሁ ቁጥር የሆነ የሚያስደነግጠኝ ነገር አለ። ከአስር ዓመት ባለፈ የፌስቡክ ቆይታየ አንድም ቃል ተነጋግረንም ሆነ ጓደኛ ሆነን አናውቅም። ግን እዚህ ነበር። እዚህ ሰፈር በራሱ ሰፈር ሆኖ ነበር። ልክ ፒያሳ ፣ አራት ኪሎ ፣ሜክሲኮ፣ ቦሌ እንደሚባሉ ሰፈሮች ቤታችን እዛም ሆነ አልሆነ የምናውቀው ሰፈር ነበር። የሆኑ የምናውቃቸው ካፌወች ሱቆች ቢሮወች ሰወች ያሉበት ሰፈር። የምንበሳጭበት የምንስቅበት ነገር ያለበት ሰፈር! ሰወች ብቻ አይደለንም ለካ! እና ጧት ስትነሱ አንድ ሰፈር ቢጠፋ እንደማለት ነው። እንደዛ ነው የሚሰማኝ። ቀስ እያሉ በዙሪያው የነበሩ ሰወች ሲጠፉ ሲበተኑ ታያላችሁ። ከነጨዋታቸው፣ ከነሆነ የአነጋገር የመግባባት፣ ባህላቸው !የሆነ ጣዕም ይጎድላል። ብቻ ሞት የሆነ ቅፅበት ነው ከዛ በኋላ ያለው አለመኖር ርዝመቱ.... እንዲያው እንዲሁ ባየሁት ቁጥር ስለሚያሳዝነኝ ነው።

Alex Abreham አሌክስ አብረሃም

19 Nov, 09:59


አንድ የዱር አጋዘን ኮለራዶ የሚባለው የአሜሪካ ግዛት ወደሚገኝ የምግብ መሸጫ ሱቅ ድንገት ገብቶ ይቆማል። እንግዲህ አጋዘን እንኳን በዚህ ልክ ሰወችን ሊቀርብ የቅጠል ኮሽታ እስከጠረፍ የሚያስሮጠው እንስሳ ነው። በአቅራቢያው ካለ ጫካ ወጥቶ ነው ። እና የሱቁ ባለቤት ይሄ አጋዘን እንደተራበ ስለገባው የታሸገ ለውዝ ይከፍትና ይሰጠዋል። ያችን አጣጥሞ ወጥቶ ወደጫካው ሄደ። ከሰላሳ ደይቃ በኋላ ግን አጋዘኑ ቤተሰቡን ( ሚስቱንና ሁለት ልጆቹን) ይዞ ወደሱቁ ተመለሰና ቁልጭ ቁልጭ። እንግዲህ በአጋዘንኛ "እኔና ደጀኔ ቸግሮናል" ነው😀 ርሀብ የሞራልም የተፈጥሮም ባህሪያችሁ የማይፈቅድበት ቦታ የሚያቆም አሳዛኝ ነገር ነው። በተለይ ቤተሰብ መቸም አይራብ!! እንደአገር እንደህዝብ ራሳችንን ነው ያሳየኝ። ለቤተሰብ ሲሉ ከከብር አጥራቸው ወጥተው ሰው ፊት ለቆሙ ሁሉ እስኪ መልካም ዘመን ይምጣ🙏

Alex Abreham አሌክስ አብረሃም

15 Nov, 11:50


"የከሸፉ ሐይማኖተኞች" ከሚድኑ ዳይኖሰር በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀለዋል!
(አሌክስ አብርሃም)

አንድ ፈጣሪን በጥልቀት ወይም ከነጭራሹ የማያውቅ ፣ ባለማወቁም የማይፈራ ነፍሰ ገዳይ አምላኩን ያወቀ ቀን ፍፁም ከቀደመ ክፋቱ የመመለስ እድሉ ከፍተኛ ነው። ከነክፋቱ ወደፈጣሪ ሲቀርብ ነገሮች ይቀየራሉ። ይሄን ለማረጋገጥ ታላላቅ የሚባሉ የሀይማኖት አባቶችን ታሪክ ተመልሳችሁ ፈትሹ።

በክርስትናው ከብሉይ ኪዳን ጀምራችሁ የኢየሱስ 12 ደቀመዛሙርትን ይዛችሁ እስከአሁን ያሉትን፣ በሌሎቹም እምነቶች በየዘመኑ የተነሱትን ተመልከቱ። አንዳንዶቹ አመንዝራ፣ሌሎቹ ቀራጭ ፣ ሌባ ፣ ሴተኛ አዳሪ፣ ለማህበረሰብ መከራ ወዘተ የነበሩ... ከዛስ? የገባቸው ቀን የእውነት የተቀየሩ የፈጣሪ ባሪያወች ፣የማህበረሰቡም ምሳሌወች ይሆናሉ። ሩቅ ሳንሄድ በዚህ ክፍለ ዘመን ራሱ ዘር ማጥፋትን ጨምሮ ብዙ ዘግናኝ ወንጀል የሰሩ ባለስልጣናት፣ አሸባሪወች ፣ አደንዛዢ እፅ አዘዋዋሪወች ፣ ሴተኛ አዳሪወች ወዘተ እስር ቤት ውስጥ ፈጣሪን አውቀው ተለውጠው ሲወጡ ማየት የተለመደ ነው። ብዙ መዘርዘር ይቻላል። እነሱም አይደብቁም እንዲህ ነበርኩ ፈጣሪ ቀየረኝ ይላሉ በአደባባይ።

አሁን ተመለሱና ከይሁዳ ኧረ ከዛም በፊት ጀምሩ...የተመረጡ የፈጣሪን ታላቅነት፣ ክብር ፣ ያወቁ ተዓምራቱን ያዮ ፣የተመረጡ የተቀደሱ ለአመታት የሰበኩ፣ ያስተማሩ "ሐይማኖተኞች" ሸርተት ብለው ገንዘብና ጥቅማጥቅም ውስጥ ከገቡ፣ ወሲብ ፣ስልጣን፣ የታመመ ፖለቲካ ፣ ዘረኝነት ውስጥ ከተዘፈቁ ከሞት በስተቀር ምንም ከክፋታቸው አይመልሳቸውም። ምንም! የመጨረሻውን ሀያል አምላክ ክደውት ተመልሰዋል ማን ይዳኛቸዋል? ኢየሱስን ራሱን አሰቅለውታልኮ! ችግሩ ደግ ሰወች ፣ ትሁትና ፈጣሪን የሚወዱ ሰወችን ከነፍሳቸው ይጠላሉ። ምክንያቱም ክህደታቸውን፣ ያፈረሱትን መለኮታዊ ቃል ኪዳን ያስታውሷቸዋል። ተቅበዝባዢ ናቸው። የጎደለው ከፍሳቸው ስለሆነ ምንም ምድራዊ ሀብት ስልጣን አይሞላቸውም። እና እንዲህ መሆናቸውን አያምኑም። አሁንም ሊሰብኩ ሊያስተምሩ ይችላሉ። የሚሰብኩት ግን ራሳቸውን ነው። የወደቁለትን ሐብት ፣ዝና ፣ስልጣን ነው።

ንሰሐ መጨረሻ ባይኖረውም በገሀድ እንደምናየው፣ እንዲህ አይነት "ሐይማኖተኞች" ግን በታሪክም በአሁኑ የኑሮ እማኝነታችንም ስጋና ደም የለበሱ የአጥፍቶ ጠፊ ፈንጅወች ናቸው። የጭካኔም የብልግናም መጨረሻወች። አገር ሳይቀር ያፈራርሳሉ። በነገራችን ላይ ሰይጣን ራሱ መለዓክ ነበር ዘጭ ሲል ነው አሁን የሆነውን የሆነው! አሰራሩ አንድ አይነት ነው።

Alex Abreham አሌክስ አብረሃም

13 Nov, 22:12


መፅሐፍ ከማሳተማችሁ በፊት🚫
ለማሳተም ሐሳብ ላላችሁ
(አሌክስ አብርሃም)

ብዙ ወዳጆቸ መፅሐፍ ለማሳተም እንደምትፈልጉና ከህትመት ጋር በተያያዘ አስተያየት እንድሰጣችሁ በየጊዜው ትጠይቁኛላችሁ። ምክንያቱ ባይገባኝም በተለይ ሰሞኑን ደግሞ
ጥያቄው በዛ ብሏል። አንዳንዶቻችሁ መልስ አለመስጠቴ ትንሽ እንዳሳዘናችሁ ፅፋችሁልኛል። ኩራት አልያም ንቄት ነው ያላችሁኝም አላችሁ። እውነታው በዚህ ጉዳይ ምክርም አስተያየትም መስጠት አስቸጋሪ ሆኖብኝ ነው። የግድ አስተያየቴን መስጠት ካለብኝ ግን ቀጣዮቹን 10 ነጥቦች ላካፍል። የተለየ ሐሳብ ካለም በደስታ እቀበላለሁ።

1ኛ. እንኳን ፃፋችሁ፣ መፃፋችሁን ቀጥሉ! ከእናንተ የሚጠበቀው ከባዱ ሀላፊነት ይሄው ነው። የፀሐፊ ስራው ሳይታክት መፃፍ፣መፃፍ አሁንም መፃፍ ነው። ይህ ፅሁፍ ግን ስለመፃፍ ብቻ ሳይሆን ((ስለማሳተም)) ነው።

2.መፅሐፍ ስታሳትሙ ለህትመት ያወጣችሁትን ገንዘብ እንደጠፋ፣ እንደተሰረቀ ወይም ፈፅሞ ከዚህ በኋላ እንደማታገኙት ሐብት ቁጠሩት። ከተመለሰ እሰየው! ካልተመለሰም በሞራልም በገንዘብም ህይወታችሁን እንዳያመሳቅል ብዙ ተስፋ አታድርጉ።

3.🚫በጣም እንዳትሞክሩት የምመክረው ...ንብረት በመሸጥ፣ በማስያዝ፣ ወይም በብዙ ድካም ለሌላ ጉዳይ ያጠራቀማችሁትን ገንዘብ በማውጣት መፅሐፍ አታሳትሙ። እባካችሁ አታሳትሙ። ስፖንሰር ከተገኘ፣ ለማሳተም ብዙም የገንዘብ ችግር ከሌለባችሁና ለስሜታችሁ ስትሉ ማሳተም ከቻላችሁ ችግር የለውም።

4. የግጥም መፅሐፍ ማሳተም አሁን ባለው የመፅሐፍ ገበያ የሚመከር አይደለም።

5. ጥሩ ፅፋችሁ በአመታት ድካምና መስዋዕትነት ያሳተማችሁት መፅሐፍ በቀናት ውስጥ በዮ ቲዮብ፣ በሬዲዮ ጣቢያዎች ፣ በቲክቶክና በቴሌግራም አየር ላይ ተበትኖ የሽያጩ ነገር ከአፈር ሲደባለቅ ማየት የዚህ ዘመን የደራሲያን የልብ ስብራት ነው።

6. እነእንትና እንኳ ፅፈው ተነቦላቸው የለ የሚል ሞኝ ንፅፅር ውስጥ ራሳችሁን አታስገቡ። ሰወች ምንጊዜም እንደባህር አለት ጫፋቸው ብቻ የሚታይ ፍጥረቶች ናቸው ውሀው ውስጥ ያላቸውን መሠረት አናውቅም።

7. ሁልጊዜም ሽፋን ላይ የምታዮት ዋጋ ለደራሲው በቀጥታ የሚደርስ አይደለም። እውነታው ግማሹ እንኳን አይደርሰውም። ስለዚህ ማሳተም ስታስቡ ይሄን ያህል ኮፒ በዚህ ዋጋ ቢሸጥ ከሚል የዋህ "ቀቢፀ ሒሳብ" ውጡ።

8. እንዲህም ሆኖ ብዙ መፅሐፍት ይታተማሉ የሚል ግርታ ውስጥ ከሆናችሁ ከብዙወቹ እንደአንዱ ከመሆናችሁ በፊት በእነዚህ ነጥቦች ላይ የራሳችሁን ጥናት ደግሞ አድርጉ። በማይገባኝ ምክንያት ደራሲያን ትክክለኛውን መረጃ እርስ በእርስ አይለዋወጡም።

9. መሠረታዊ ችግሩ በሁሉም ዘርፍ ያለው የዋጋ መናር ካለን ደካማ የንባብ ባህል ጋር መዳመሩ ሲሆን በተጨማሪም አንባቢው በተደጋጋሚ በሚታተሙ መፅሐፍት ያሰበውን ያህል እርካታ ማግኘት አለመቻሉ ያሳደረው ተፅዕኖም ቀላል የሚባል አይደለም።

10. መፅሐፋችሁ መሸጡ ወይም አለመሸጡ የእናተን ደካማ ደራሲነት ወይም ጥሩ ፀሐፊነት ማረጋገጫ ላይሆን ይችላል። ሊሆን የሚችልበትም አጋጣሚም ይኖራል። የመፅሐፍ ገበያ እብድ ነው። ታዋቂ ሁናችሁ ያጨበጨበው ሁሉ ድራሹ ሊጠፋ በተቃራኒው ድንገት ብቅ ብላችሁ ህዝብ ሊሻማ ጥሩ ሊሸጥና ሊነበብም ይችላል። ግን ከመቶ ሁለትና ሶስት እንኳን ይሄ እድል አይገጥመውም። በበኩሌ ህይወትን ለዕድል መተው ለማንም የምመክረው ነገር አይደለም። ዕድልን በህይወት ውስጥ መጠቀምን እመርጣለሁ። ምክንያቱ ብዙና ውስብስብ ነው። የሆነ ሆኖ የተሻለ ተስፋ ብሰጣችሁ ደስ ይለኝ ነበር፤ ግን እውነታው ቢታደጋችሁ ይሻላል። አውቃችሁ ተጋፈጡት!!

Alex Abreham አሌክስ አብረሃም

13 Nov, 10:55


አሜሪካ ማለትኮ ከአለም አንደኛ ሀብታም የሆነውን ሰውየ ካድሬ አድርጋ የምትሾም ብቸኛ አገር ናት😀

ጓድ ኤለን መስክ
በዮኤስ ኤ /አስ/ የዶ/ት/አስተ/ቢ/ወ/ሙ/የስራ ሒደት ዋና ሀላፊ😀

Alex Abreham አሌክስ አብረሃም

10 Nov, 20:19


የቁም ተስካራችሁን አውጡ!
(አሌክስ አብርሃም)

ዕድሜ ልካቸውን ስለታላላቅ ሰወች ፣ ስለታላላቅ ስራወች በማውራት ትልቅነታቸውን ለማሳየት ፍዳቸውን የሚበሉ ሰወች አሉ። በተለይ በጥበቡ ውስጥ ስለነበሩና ስላሉ ታላላቆች። ዘፋኞች፣ ተዋናዮች፣ ደራሲያን ወዘተ። እንዲህ አይነት ሰወች መቸም ታላቅ አይሆኑም። ወደራሳችሁ ተመለሱ፣ ሰው የተፈጠረው ዕድሜ ልኩን ሌሎችን ሲዘክር ለመኖር አይደለም። ሰው የራሱን የቁም ተስካር እንዲያወጣ እድል የተሰጠው ፍጡር ነው። የራሳችሁ ትንሽነት ዘክሩ። ማድነቅና ማክበር እንደእርሾ ነው። ለራሳችን ስኬት የሚረዳ ቅመም ነገር።

ታላላቆች ምን ሰሩ ብለን እንጠይቅ? ታናናሾችን በጥበባቸው አጎሉ። መንገድ ጠረጉ፣ ድምፅ ሆኑ ። አንብቡ የአለምን ሊትሬቸር...ስለጭቁኖች ማንም ዙሮ ስለማያቸው ጥቃቅኖች የተፃፈው ይበዛል። አንድ ዘፋኝ ታዋቂና ታላቅ ሰው አፈቀርኩ ብሎ ሲዘፍን ሰምታችኋል? ስለተቀደደ ጫማችሁ ፃፉ፣ ባል ስለማጣታችሁ ፃፉ፣ ስለነተበ ሸሚዛችሁ ፃፉ፣ ዘይት ስላነሰው ሹሮ ወጣችሁ ፃፉ ፣ ጠይቃችኋት እምቢ ስላለቻችሁ የቤት ሰራተኛ ፃፉ፣ ስለተንጨባረረ ትዳራችሁ ፃፉ፣ ስለህመማችሁ፣ ስለረሀባችሁ፣ ስለብስጭትና ተስፋችሁ ፣ስላንገሸገሻችሁ ኑሮ ፃፉ። በህመማችሁ ልክ አቃስቱ፣ በሀዘናችሁ ልክ አልቅሱ፣ በደስታችሁም ልክ ሳቁ። ጫማችሁ ሸቷቸው ስላስነጠሳቸው ሰወች ስለተሰማችሁ ሀፍረት ፃፉ! በተለይ ነፍሴ ለጥበብ ተጠርታለች ብላችሁ የምታስቡ ጊዚያችሁን በማጨብጨብ አታባክኑ! የሚያጨበጭቡ እጆች ብእር መጨበጥ አይችሉም። ሚሊየኖች እንደምታጨበጭቡላቸው ሰወች ሳይሆን እንደእናተ ነው የሚኖሩት። እናተ ሚሊየኖች ናችሁ። ታላቅነት በሰው ተስካር አደጋገስን ማሳመር አይደለም፣ የቁም ተስካርን ማውጣት ነው። ወደትንሽነታችሁ ተመለሱ። ከአንቆላባሽነት ውጡ። ጥሩ ነው ታላቆችን ማክበር ግን የእድሜ ልክ ስራ አይደለም። ቢያንስ መሰላሎቹ ላይ ለመውጣት ሞክሩ። መሰላል ተሸክሞ መዞር ከፍ አያደርግም።

Alex Abreham አሌክስ አብረሃም

10 Nov, 10:07


ቸርቿ ልትሸልመኝ ይገባል!

አንዱ የቤተክርስቲያን ኪቦርድ ተጨዋች ትልቅ ስህተት ይሳሳታል። እሱ እንኳን ጥሩ ልጅ ነበር ፣ያ የተረገመ ሰይጣን የሆነ ቀን ኪቦርድ ከሚያስተምራት የፓስተሩ ሚስት ጋር አሳስቶት እንጅ። እሷም ጥሩ ልጅ ነበረች ዕድሜዋ ከባሏ በ22 ዓመት ከማነሱና ጌታ ጭው ካለ ገጠር ካወጣው ፓስተር ጋር የተጋባች የከተማ ልጅ ከመሆኗ ውጭ! እና ከማንኛውም አገልግሎት ይታገዱ በሚሉና ለዛሬ በምክር ይታለፉ በሚል ምእመኑ ለሁለት ተከፈለ። መከፈል ብቻ አይደለም በዓለም እንኳን ተሰምቶ በማይታወቅ ፣ማንም ከዚህ በፊት ባልተሳደበበት ፣ ገና በዛ ዓመት ከጥልቁ ተመርቶ ለገበያ በቀረበ ዜሮ ዜሮ ስድብ ጉባኤው ይሞላለጭ ጀመር። ከቃል አልፎ በጣት ምልክት ሁሉ እንካ እንች ምናምን እየተባባሉ። እና ልጁ በግርምት ስድድቡን ዛቻውን ሲኮመኩም ቆየ። የሱ ድርጊት ከሚያየው ጉድ አነሰበት። ሲወጣላቸው ሲረጋጉ "እሽ አስተያየትህ ምንድነው ይሉታል ንስሀ ትገባለህ ወይስ?"

ወገኖቸ ! የገረመኝ የእኔ መባለግ አይደለም። እኔኮ ስትቅለሰለሱ ስትፀልዩና ስትሰብኩ በትእግስት የጌታን መምጣት የምትጠባበቁ ነበር የመሰለኝ። ለካ እዚህ ተሰብስባችሁ ብልግናችሁን የምትተነፍሱበት አንድ ባለጌ ስትጠብቁ ነው የቆያችሁት። ሰበብ ሆንኳችሁ፣ ለዓመታት በፆሎት ያልተገለጠ አጋንንታችሁ በብልግናየ እየጮኸ ወጣ....ቸርቿ ልትሸልመኝ ይገባል😀

ምን ለማለት ነው? የማንም መባለግ እናንተ ባለጌ እንድትሆኑ ልዮ ፈቃድ ሊሆናችሁ አይችልም። የጨዋነታችሁ መሰረቱና ሚዛኑ የሌላው መቅለል አይደለም። ሰሞኑን አንዱ የጊኒ ባለስልጣን የባለገበትን የወሲብ ቪዲዮ ለማየት የተለየ ፈቃድ የተሰጣችሁ ይመስል ስትራኮቱና ስትኮመኩሙ ፣ ልገስፅ ላስተምር ስትሉ ለከረማችሁ "ሸም ኦን ዩ" 😀 በቀጣይ ብትፆሙ ብትፀልዮ እድሜ ልካችሁን ከአእምሯችሁ ትእይንቱ የማይጠፋ የወሲብ ፊልም ነው ስትጋቱ የከረማችሁት።

🚫 የወሲብ ቪዲዮ /pornography/ ለአንድ ደቂቃ ብትመለከቱ ትዕይንቱ በትንሹ ለ20 ዓመታት ከአእምሯችሁ አይጠፋም። ያውም እንደዕድሜ ደረጃችሁ። ይሄ በጥናት የተረጋገጠ እውነት ነው። ጆሮ ያለው ይስማ።

Alex Abreham አሌክስ አብረሃም

10 Nov, 08:37


ጉተታው
(አሌክስ አብርሃም)

ኤለመንታሪ ተማሪወች እንደነበርን አስማተኛ ነኝ የሚል ሰው በጆሮየ መኪና እጎትታለሁ ሃምሳ ሳንቲም ትኬት ቁረጡ እያለ ወደትምህርት ቤታችን መጣ..ማንም አልቆረጠለትም፤ እንደውም መፈንከት አምሮን ነበር። ከዛ በፊት ተታለን ነበራ! ጅል መሰልነው እንዴ?! ይህን የሰሙ ወላጆች ሁሉ ሳይቀር ተቆጡ። በኋላ እኛ ፈላወቹ የባነንበት ሰውየ ሀይስኩል ሄዶ መኪና በጆሮው እንደሚጎትት እና ትኬቱም አንድ ብር እንደሆነ ሲነግራቸው እንኳን ተማሪ አስተማሪና ወላጆች ሳይቀሩ ትኬት ለመቁረጥ ግድያ ሆነ። የተቆጡ ወላጆች ሁሉ ሐሳባቸውን ቀይረው ይጋፉ ጀመር። ግራ ገባን። እንደውም ቦታ ጠቦ ብዙ ትርኢቱን ሊመለከቱ የሄዱ ሴቶች እያዘኑ ተመለሱ። "በአጥርም ቢሆን ይሄን ጉድ እናያለን" ያሉም ነበሩ።

የገረመን ለመመልከት ከሚጋፉት ሴቶች ይበዙ ነበር። ሰውየው እውነትም አስማተኛ ነው ...ከኋላ ከፍሎ ባሰማራቸው ሰወቹ መኪናውን የሚጎትተው በጆሮው አይደለም ልጅ ፊት እንደዛ ስለማይባል ነው እንጅ በእንትኑ ...ነው የሚጎትተው" ብለው አውርተው ነበር። ህዝቡ ነቅሎ ገባ። ብለው ብለው መኪና ሊጎትቱበት? እየተባባለ። ልጆች እዛች ግድም እንዳንደርስ ተከለከልን። በኋላ ሰውየው አንዲት ታክሲ እንደምንም በጆሮው ትንሽ ጎተተ ። ህዝቡ አልተደነቀም፣ ልቡ የተሰቀለው ሌላው ጉዳይ ላይ ነበር። ቀጣዮን ለማየት አዳሜና ሂዋኔ እንደጓጓ "ትርኢቱ አለቀ" ብሎ ኩም አደረጋቸው አስማተኛው።

እንዴ እንትኑሳ?
ምኑ?
መኪናውን የምትጎትተው በእንትንህ...ነው አልተባለም እንዴ? አሉ ወደእንትኑ እየጠቆሙ።
ፈገግ ብሎ የሱሪውን ዚፕ እየነካ "በዚህማ ይሄን ሁሉ አንድ ከተማ ህዝብ ጎተትኩበት!!"😀

ይሄው እስከዛሬ እንትን ጋር የተያያዘ ወሬ እንደጉድ እየጎተተ ይሰበስበናል። እንዳለ ህዝቡ አስማት ሊያይ ኢኳቶሪያል ጊኒ ጠቅልሎ ገባኮ ጓዶች።😀 ያ የተረገመ ሰውየ በእንትኑ ጎትቶ ጊኒ አጎረን።

Alex Abreham አሌክስ አብረሃም

10 Nov, 08:30


የእለት ‹‹ነገራችንን›› አትንሳን!
(አሌክስ አብርሃም)

እያንዳንዱ ብሔርና ብሔረሰብ "ኢትዮጵያ አገሬ ባህሌን፣ ወጌን ፣ትውፊቴን ታክብር አለበለዚያ ...." ቢልስ? ለምሳሌ ብዙ ጊዜ የሰወችን "አክሰንት" ወይም ሌላ አካላዊ ገፅታ፣ ባህልና አምልኮ በመስማትና በመመልከት ? በጨዋነት ብሔራቸውን ትገምታላችሁ። እና አክሰንታቸው እንደፈለገ ይወለጋገድ ፣ ገፅታቸውም ይሁን አለባበስና ባህላቸው ምንም ይሁን እምነታቸውን አትመኑበት ቢያንስ ፊት ለፊት መጥፎ ነገር አትናገሩም። ብሔር ናታ! እሳት ናታ! ኡፉ ናታ! እንደውም "ኢትስ ኦኬ" ልትኮራበት ነው የሚገባው ብላችሁ ለመመሳሰል ዘጭ እንቦጭ ምናምንን ነው የምትሉት። ኋላ ቀር ጎጅ ምናምን ማለትማ አይታሰብም።

ቦርጫም ወንድ ስታዮ ግን፣ ስፖርት ስሩ፣ ኮሌስትሮል .... ምናምን የምትሉት ለምንድነው? ለቅፅበት እንኳን ፊታችሁ የቆመው ጓድ የቦዲ ማህበረሰብ ያፈራው ኢትዮጵያዊ ሊሆን ይችላል ብላችሁ ለምን አታስቡም? ከተማ ብገባም ወግና ባህሌን ማንነቴን አልጥልም እምቢኝ ያለ ቦዲያዊ የለም ያለው ማነው?! በቅድም አያቴ በምንጅላቴ ቦዲ ነኝ ቢልስ? እንደውም "ቦርጭን ለማጥፋት" የሚል ንግግር የአንድን ብሔር ወግና ባህል ለማጥፋት የሚደረግ ሙከራ በመሆኑ በህግ ሊታገድ ይገባል ቢልስ? በብሔራዊ ቴሌቪዢናችን ሳይቀር ባለሙያ ጋብዛችሁ "እንዴት ቦርጭ ማጥፋት እንደሚቻል" ትሰብካላችሁ። ምንዓይነት ሕዝብን መናቅ ነው ይሔ ወገኖቸ?! የጥላቻ ንግግር ልንለው እንችላለንኮ።

የሆነ ሆኖ የቦዲ ማህበረሰብ ግን በሞጋሳ / ጉዲፈቻ ወዘተ የብሔራቸው አባል የሚያደርጉበት ስርዓት ይኖራቸው ይሆን? ባንዴ በኢትዮጵያ ትልቁ ብሔር ነበር የሚሆኑት። ወይ ደህና መካሪ ማጣት!ከተሜው በሙሉ ቦርጭ የታደለው ነውኮ የሚመስለው። ደግሞ ጅም ሂዱ ማለት ምንድነው የአንድ ብሔረሰብን መገለጫ ለማጥፋት ይሄ ሁሉ ርብርብ ለምን? እንደውም ከለጠጥነው ዘር ማጥፋት ጭምር ነው! ቦርጭ ከሌለ ሚስት የለም! ሚስት ከሌለ ዘር ከየት ይተካል? ዘር ማጥፋት ወይ የተወለደውን መጨፍጨፍ አልያም እንዳይወለድ ማድረግ አይደለምን? ይችንም ብሔር ጋር ካላያያዝናት ማንም እየተነሳ ሊዘልፈን አይደል? በዚህ አጋጣሚ የሐመር ሴቶች ኢቲቪ ፣ፋና ተቀጥረው በባህላዊ አልባሳታቸው ተውበው ዜና ያንብቡ ፕሮግራም ይምሩ ፣ ፖርላማ ይሰየሙ ብየ የጠየኩት ነገር ከምን ደረሰ? ኧረ ለህዝብ ጥያቄ ጆሮ እየሰጣችሁ ጓዶች!

እስኪ ሰላም ያውለን!

Alex Abreham አሌክስ አብረሃም

09 Nov, 22:27


የእውነት ግን ትንሽም ቢሆን ስፖርት ስሩ፣ ኧረ ዱብ ዱብ በሉ ጓዶች። አሁን አጠገቤ ተቀምጦ ስልኩን ሲጎረጉር የነበረው ዘናጭ ወጣት ፣ ድንገት ተነስቶ ሲቆም ጉልበቱ እንዴት እንደተንቋቋ! ቋቋቋቋቋቋ ቅጭጭጭጭ! ከስጋና አጥንት የተሰራ ሰው እንዴት እንዲህ ይንቋቋል? ዲሞፍተር ያቀባበለኮ ነው የሚመስለው😀

Alex Abreham አሌክስ አብረሃም

08 Nov, 12:42


በቃ እንዲሁ ልንቀጥል ነው?
(አሌክስ አብርሃም)

"የዛሬ አምስት ዓመት የምሰራበት የህክምና ተቋም ህንፃ ላይ የተፃፈውን ስምና፣ ዋንጫ ላይ የተጠመጠመ እባብ ከነምላሱ ከዚህ ጋ ሆኘ ቁልጭ አድርጌ ማየት እችል ነበር...አሁን ግን በጣም ካልተጠጋሁ በስተቀር ቀለሙ እንጅ ፊደሎቹም እባቡም አይታየኝም። ብዢዢዢ ይልብኛል። ይህን የታዘብኩት ከወር በፊት ነው በአጋጣሚ" አለኝ። ከሩቅ የሚታየውን ህንፃ እያሳየኝ። እናም " አይኔን ያደከመው ቀን ሌሊት ሳልል የምጎረጉረው ስልክ ነው። መነፀር ያስፈልገሀል ተብያለሁ። ፀሐይ ላይ ስሆን እንባየ ያስቸግረኛል። ካየሁት ሁሉ ምን ተጠቀምኩ? ተዝናናሁ እንበል ለመዝናናት የዓይን ጤናን መክፈል ያዋጣል? እንቅልፍ ያጣሁባቸው ምሽቶች ቁጥር ስፍር የላቸውም፤ ምን አገኘሁ? ምንም። መረጃ እንበል ፣ እንቅልፍ የሚከፈልለት መረጃ የትኛው ነበር ? የት እንዳይሄድ? የቱ ህይወት የሚቀይር መረጃ? " አለም አንድ ሆነች ብለው ከራሳችን ለዮን።

እያወራኝ አሰብኩ ...በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የማይመለከቷችሁን ቪዲዮዎች አያችሁ፣ እንቅልፍ እንደበፊቱ እየተኛችሁ አይደለም በጣም እየተጎዳችሁ ነው፣ ከምትወዷቸው ጋር የምታሳልፉት ጊዜ ተወስዷል፣ ( ልጆቻችሁ ጭምር) ብዙወቻችሁ አይናችሁን ቸክ ተደረጉ እስኪ ወይም ራሳችሁ አድርጉት እይታችሁ እንደበፊቱ ነው? ... ሌላም ውሎ አድሮ የሚከሰት አካላዊም ይሁን አዕምሯዊ ችግር አይቀሬ ነው። ያውም የኢንተርኔት ክፍያው፣ የስነልቦና ጫናው፣ ጥላቻው፣ ስጋቱ፣ ባልተገባ ውድድር የሚፈጠርባችሁ የበታችነት ስሜት፣ ከእምነትና ማንነታችሁ ጋር የሚጋጭ ትእይንትና ነውር ወዘተ ሳይቆጠር። ምንድነው ሳናቋርጥ ስልካችን ላይ የምንፈልገው? ምን? የሆነስ ሆነና ሶሻል ሚዲያው ላይ "ዘና ለማለት" በሚል ይሄን ሁሉ መክፈላችን ያዋጣል? እንደቀልድ ቁጭ ብለን ሰዓቱ እንዴት እንደሚፈተለክ አስባችሁታል? ዕድሜ የሚከፈልለት ምን? በቃ እንደዚህ እየኖርን ልናረጅ ነው? በቃ ህይወታችን ይሄ ሊሆን ነው ?እስከመቸ?

Alex Abreham አሌክስ አብረሃም

07 Nov, 19:08


እየገረመኝ ያለው ነገር በአገራችን ጉዳይ ላይ ሚዲያወች መዋሸት አለመዋሸታቸው አይደለም አሱኔማ አደግንበት አረጀንበት። የሚገርመኝ አድማጭ ተመልካቹ ውሸት መምረጡ ነው። አለ አይደል "በፍላጎቴ ልክ የተወራ ውሸት እውነት ነው" ብሎ መገገም። ለምሳሌ ስለሆነ ጉዳይ መስማት የምትፈልገው ውድቀቱን ነው እንበል፤ ውድቀቱን የሚያወራልህን ሚዲያ ከፍተህ ትሰማለህ። ያንኑ ዜና በተቃራኒው ስኬቱን መስማት ብትፈልግ ስኬቱን የሚያወራልህን ሚዲያ ትከፍታለህ። ሁሉም ዜና እንደቻይና እቃ በመግዛት አቅምህ ፣ በሙድህ ልክ ይሰራል። ምሳሌ ልጥቀስ ወይስ አልገብቷችኋል? 😀

Alex Abreham አሌክስ አብረሃም

07 Nov, 16:21


ሰሞኑን አንድ ስለሳይንስና ቴክኖሎጅ ጉዳዮች በፍቅር የሚያወራ ልጅ ቲክቶክ ላይ ተመለከተኩ። (የዮኒቨርስቲ መምህር ነው አሉኝ) ልጁ ለቴክኖሎጅ ያለው ፍቅር ደስ ይላል ፤ በሚያወራውም ነገር በእርግጥ በጉዳዮ ላይ ደህና መረዳት እንዳለው ያስታውቃል። ብዙሀኑ ግን ልጁ ላይ ሙድ ከመያዝ ባለፈ የሳይንሱ ነገር አልተዋጠለትም። ለምን? የልጁ ድምፅ ቀጭንና አክሰንቱም ወደገጠር ወሰድ የሚያደርገው ነው በሚል። የአይዶል ተፅእኖ ሕዝቤ ላይ አርፏል። አብዝቶ ስለዘፋኞች ከማውራቱና ዘፋኞችን ከመተቸቱ የተነሳ ሳይንስ የሚያወራን ሰው ሳይቀር "ድምፅህ ቀጥኗል እንደገና ሞክር" እያለ ነው😀

ልጁ አንድ ቪዲዮው ላይ "ምን ይሻላል? ብናለቅስ ይሻል ይሆን?" እንዳለው ነው ነገሩ😀

Alex Abreham አሌክስ አብረሃም

05 Nov, 05:21


እንደምን አመሻችሁ በመላው አሜሪካ የምትኖሩ አበሻ አሜሪካንስ መራጮች? እንዲሁ ለሰላምታ ነው😀

Alex Abreham አሌክስ አብረሃም

02 Nov, 18:29


ተከራይ ኪራይ ለመክፈል፣ አከራይ ሌላ የምትከራይ ሰርቪስ ለመቀለስ ሁሉም ቲክቶክ ላይ ይጨፍራሉ😀

Alex Abreham አሌክስ አብረሃም

02 Nov, 07:22


እንደምን አደራችሁ? መልካም ቅዳሜ። ድሮ ድሮኮ ቅዳሜ ቅዳሜ ጠረጴዛውን በጠርሙዝ ሞልታችሁ መጠጥ ትጠጡ ፎቶም ትለጥፉ ነበር አይደል? እንደውም ሰው ትጋብዙ ሁሉ ነበር! እኔም አትጠጡ፣ እናተም አታብዙ እንጅ አትጠጡ አይባልም ምናምን እንባባል ነበር እ? ነበር እንዲህ ቅርብ ነው? አሁን ግን ጠጡ ብላችሁ እንደውም ወንድ ከሆናችሁ አብዝታችሁ ጠጡ ብላችሁ ድሮ ጠጥታችሁ ባልመለሳችሁት ጠርሙዝ ነው የምትፈነክቱኝ😀 በዚህ ኑሮ ጠጡ ይላል እንዴ "ምኑ ጀዝባ ነው" አሉ ያ ሰውየ....😀

Alex Abreham አሌክስ አብረሃም

31 Oct, 12:45


ትራምፕን ምረጡ!!
ይህ አሜሪካ ለሚኖሩ አበሾች የምርጫ ቅስቀሳ ነው!!

የአሜሪካ ምርጫ አንድ ሳምንት ቀረው። ታዲያ እኛ ምናገባን የምትሉ እንዳላችሁ አውቃለሁ። ይህ ፅሁፍ ለእናንተ ስላልሆነ ልክ ናችሁ አያገባችሁም። በአሜሪካ ለሚኖሩና የመምረጥ መብት ላላቸው አበሾች የተፃፈ ነው። በተለይም የአበሻ ወላጆችን ለቅሶ ጭንቀትና መከራ እንዳየ ሰው ይህን እላለሁ።

ምናልባት እስከአሁን ማንን እንደምትመርጡ ካልወሰናችሁ እኔ በግልፅ ትራምፕን እንድትመርጡ ለመቀስቀስ ነው ይህን የምፅፈው። በዘረኝነት እና ወዘተ ስሙ በክፉ እንደሚነሳ ግልፅ ነው። ይህም ቢሆን ባስተዳደረባቸው አመታት ከነጆ ባይደን የባሰ የሚወራውን ያህል የከፋ ነገር አልታየበትም። ለሀብታሞች ያደላል የሚል ቅሬታም ይነሳል። ኮቪድን ጨምሮ በተከሰቱ ሁነቶች ድሆችን ከተራ ምግብ ጀምሮ መክፈል እስካቃታቸው ሞርጌጅ በተለያየ መንገድ የደገፋቸው የትራምፕ አስተዳደር ነበር። እውነታው ትራምፕ አሜሪካን ከልብ ይወዳል፣ ከነጉድለቱ በፈጣሪ መኖር ያምናል። ከምንም በላይ ግን ...

ብዙሀኑ አበሻ የመጨረሻ ህይወቱ ልጆቹ ናቸው። ለልጆቹ እድሜውን፣ ጤናውን ፣ ጉልበቱን ያልከፈለ አበሻ የለም። እንቅልፍና አምሮቱን ሁሉ ለልጆቹ ያልሰዋ ወላጅ አይገኝም። ህልሙም የልጆቹ የነገ ስኬት ነው። ልጆቹ ነፍሱ ናቸው "ሰው አለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጣ ምን ያደርግለታል" እንዲል መፅሐፉ ካሜላና ፓርቲዋ በቀጥታ የአበሻም ይሁን ሌሎች ልጆች እጣ ፋንታ ላይ አደገኛ ካርድ የመዘዙ የጥፋት ደቀመዝሙሮች ናቸው። አሜሪካን ወደአሳዛኝ ገደል እየገፉና በዴሞክራሲ ስም የመጨረሻውን የዴሞክራሲ አስኳል እሱንም "ልጅን በራስ ባህል በራስ እምነትና ማንነት የማሳደግ መብት" ለመንጠቅ እየታገሉ ነው። ቤተሰብን የሚበትን መርገምት። ፅንስ መግደልን እንደትልቅ የዴሞክራሲ ስጦታ እየሰበኩ ነው፣ በአጠቃላይ ኢኮኖሚ ጉዳዮችም ቢሆን እዚህ ግባ የሚባል እቅድ የላቸውም። እንደውም አሜሪካ በታሪኳ አይታው የማታውቀው የኑሮ ውድነት ላይ ጥደዋታል። ቤት ህልም ሁኗል፣ ምግብ ተትረፍርፎ ገንዳዎችን የሚሞላባት አሜሪካ የምግብ ወጭ እስከማሳሰብ ደርሷል።

ትራምፕ ሐብታሞችን መደገፉ ፍፁም ጤነኛ መንገድ ነው። ሁላችንም ወደአሜሪካ የመጣነውና ሚሊየኖችም አሜሪካን የሚመኙት ለፅድቅ አይደለም! ሐብታም አገር ስለሆነች ነው። ሰርቶ ተምሮ ለመለወጥ፣ የተሻለ ኑሮ ለመኖር። የሀብቷ ምንጭ የብዙ ሀብታም ግለሰቦች ድምር አገር መሆኗ ነው። ለማንም አገር ቢሆን ሀብታም ማብዛት ኢንቨስትመንትን ማበረታታት የህልውናው ጉዳይ ነው። የውጭ ፖሊሲያቸው ላይ አገራችንን ጨምሮ የተለያየ ሊሆን ይችላል። ከራሳቸው አንፃር ስለሚያዮት ማንም አገር የራሱን ጥቅም ካላስከበረ ሌላው ለርሱ ብሎ ፖሊሲ ሊቀርፅለት አይችልም።

የሆነ ሆኖ ለልጆቻችሁ እጣ ፋንታ፣ ለሰበአዊነት፣ እንዲሁም ለቆማችሁለት ሞራላዊም ይሁን ሐይማኖታዊ እምነት የሚበጃችሁ ትራምፕ ነው። በነገራችን ላይ መምረጥ መቻላችሁን እንደቀልድ አይታችሁ እንዳታሳልፉት ። ለዚህ መብታችሁ ብዙዎች ነፍሳቸውን ከፍለዋ፣ ፊዳ ሆነዋል። ምረጡ! ፍላጎትና ማንነታችሁን በድምፃችሁ አስከብሩ። ድምፃችሁ ለልጆቻችሁ የምትመዙት የዋስትና ካርድ ነው። ትራምፕ ጥቁር ብሎ ሰደባችሁ የሚሉት ሕይወታችሁን ጨለማ እንዲዘሩበት አትፍቀዱ። ከልጆቻችሁ የሚቀድም አንድ ነገር አስቡ ...አለ?

ድል ለጓድ ዶናልድ ትራምፕ
ሰላም ፣ፍቅር ፣ሰርቶ ልጆችን በራሱ ወግና ባህል ፣ እምነትና ስርዓት ማሳደግ፣ ለቁም ነገር ማብቃት፣ ቤተሰብን መርዳት ለመላው አበሻ፣ ለመላው ቤተሰብ!!