አሁን ጴንጤ ሆኛለሁ
[ይህን ትምህርታዊ ጽሑፍ እባክዎ ሼር ያድርጉት]
አሁን መስቀል አልስምም!! ነው ምላቸው?? ወይስ ሳያሳልሙኝ ለመጨበጥ እጄን ልዘርጋ??
አመጣጣቸው አይተውኝ እንደሆን ያስታውቃል።የእናቴ ንሰሐ አባት ናቸው። ሁሌ ጠበል ሊረጩ ሲመጡ እኔ ጋ ና እያሉኝ ብዙ ጊዜ ጠፍቻለሁ።ዛሬ ደሞ ጭራሽ ጴንጤ ሆኜ ነው መንገድ ላይ የተገጣጠምነው። እንኳን ቄሱ እናቴም ካኮረፈችኝ ሰነበተች...
ልጅ ሀይለ ሚካኤል እንዴት ሰነበትክ ጎረምሳዬ..(ፎቅ የሚያህል ጥምጣማቸውን ጠምጥመው ወደ ቆምኩበት መስቀላቸውን ለማውጣት እየታገሉ መጡ
ጌታ ይመስገን አባ.. ስሙ ይክበር..አልኳቸው ድምፄን ጎርነን ፊቴን ኮስተር አድርጌ ምናልባት ሁኔታዬ ከገባቸው ብዬ ነበር...
ዛሬ ደሞ አትሳለምም እንዴ?? አሉ መስቀላቸውን አዘጋጅተው እንደቆሙ
አይ አባቴ ጴንጤ ሆንኩኝ እኮ...ጴንጤ....(ጭቅጭቃቸውን እያሰብኩት ተንተባተብኩ
ጎሽሽሽሽ የኔ ልጅ!!! ጎሽ.. ጎሽ... ጎሽ..ደግ አደረክ!! ተባረክየኔ አምበሳ ጎበዝ!!( ብለው ብቻ ፈገግ እያሉ መስቀላቸውን ወደ ካፖርታቸው መልሰው ጥለውኝ ሄዱ።የሠማሁት ነገር ግን ከአባ መሆኑ አጠራጠረኝ።እኔ ገና ለገና ተከራከሩኝ ለምን? እንዴት? እያሉ ዘበዘቡኝ ስል እሳቸው ጭራሽ ጎሽ???
ግራ ገባኝ። አባን ሳውቃቸው ትጉህ አገልጋይ የመንጋ ጠባቂ እንደሆኑ ነው፡፡ እንዲያውም እኔ ወደ ቤተክርስትያን እንድቀርብ.... (ተብከነከንኩ!!) ቆይ አታስፈልግም እያሉ ነው?? ብትኖርም አትጠቅምም ነው?? ንቀውኝ ነው?? በቆምኩበት መንገዱን ተሻግረው ወደ ቤተክርስትያን ሲሄዱ ንዴት እያጦዘኝ ተከተልኳቸው.....
ምን ማለትዎ ነው አባ?? ጴንጤ ሆንኩ እኮ ነው ያልኩት!! ወይስ መጀመርያም አላስፈልግም ነበር....(አባ በሩ ላይ እንደደረሱ አማትበው ሲያበቁ ዞር ብለው አይተውኝ ወደ ግቢው ዘለቁ። አረ....መናናቅ!!!ገነፈልኩኝ።
ያናግሩኝ እንጂ!!! ለምን መልስ አይሰጡኝም!! ወይስ እርሶም ሊሆኑ አስበዋል?? ነገሩ...(የጀማሪ ነገር እንዳይሆንብኝ ወሬዬን ገታ አድርጌ አየኋቸው፡፡እሳቸው ግን ጭራሽ ችግኝ እና ዶማ ይዘው መጥተው
ይልቅ ከመጣህ አይቀር እቺን ትከልልኝ አሉ በልምምጥ ድምፅ(ሳላንገራግር ቆፈር ቆፈር አድርጌ የሰጡኝን ችግኝ ተክዬ ሳበቃ አባ በተራቸው መጥተው የተከልኩትን መልሰው ይነቅሉት ጀመር....
እንዴዴ ምነው እርሶ!? በማስተማር ፈንታ ፀብ ፀብ አልዎትሳ???
አይ እንግዴ!! ታድያ ተክለከው መች በቀለ???
መች ስር ሰደደና???አሁን ተክሎ አሁን ይበቅላል????
ጎሽ ጎበዝ...እንግዲህ መልሴ ይሄ ነው፡፡ተተክሎ ያልቆየ ያልተኮተኮተ ወይ ስር ያልሰደደ ተክል አይፀድቅም!!ይህ ችግኝ ማለት ደሞ አንተ ነህ።ተምረህ እንድታውቅ አውቀህ እንድትኖር ብዙ ብለምነህ እምቢ ብለህ የቆየከው አንተ!!ዛሬ ደሞ ወጣሁ ሄድኩ ከቤተክርስትያን ልጅነት አፀድነት ተነቀልኩ ትላለህ....አብ የተከለውማ አይነቀልም....
አየህ ሀይማኖት መቀየርህን ሳይውል ሳያድር ነበር ከናትህ የሠማሁት። ለዚህ ነው አንተ ስትነግረኝ እንግዳ ያልሆንኩት፡፡ ነገር ግን ፍፁም አዝኛለሁ፡፡ በሰአቱ መንገድ ዳር "እንዴት ሀይማኖት ቀየርክ" ብዬ ብሰድብህ ከመቅረብ ይልቅ ትሸሸኛለህ። በተቃራኒው ግን ደግ አደረክ ብልህ ከኔ የማትጠብቀው አነጋገር በመሆኑ አጥብቀህ ትጠይቃለህ። ባትመጣ እንኳ እኔ መመለሴ አይቀርም ነበር።ብዙ ምእመናንኮ የጠፉብን አቅርበን ከማስተማር ገፍተን ሰድበን በማስወጣታችን ጭምር ነው...
ይልቅ እንደዚህ ችግኝ አትሁን። አለባብሰው ቢተክሉህ ያፀደቁህ እየመሠለህ ሽው ባለ ነፋስ አትንገዳገድ፡፡ ስር ያልሰደደ እውቀት የመሀይም መጫወቻ ያደርጋልና ተጠንቀቅ። ተዋህዶን እንኳ አውቀሀት አይተሀት አትጨርሳትም "ሮጦ መውጣት ለእንቅፋት" እንዲሉ ሰክኖ መርጋት ከድንገተኛ ሞት ያድናል። ቤት ውስጥ ያሉትን መ**** ቅ በማለት ውጪ ያሉትን በማቃለል ሀይማኖታቸውን በማንቋሸሽ ሀይማኖት አትፀናም.. እንዲያውም ቤተክርስትያን አክብሮ መጥራት እንጂ ሰድቦ ማባረርን አታስተምርም ።አንተም ያልተማርክበት ቦታ ብትሔድ በጥባጭ እንጂ አማኝ አትሆንም።
እንግዲህ ያላወቅከው እንዲገባህ ያወቅከው እንዲያፀናህ እኔም ለመጠየቅ ዝግጁ ነኝና ጠዋት እዚሁ ና...ጠፍቶ ከመቅረት ወጥቶ መመለስ ይሻላል። አሁን ግን ግባና እረፍት አድርግ ከቅድሙ ይልቅ አሁን ኮርቼብሀለው... (ብለው ዶማቸውን ሰብስበው ወደቤታቸው ተመለሱ....
መች ነው ነግቶ እንደገና ማወራቸው??? እያልኩ ወደቤቴ ገባሁ።
ጸሐፊው ቻቻ ነው።
© አቤኔዘር ዘተዋሕዶ ገፅ
@Mar_Yisihak