*አስገራሚና አስተማሪ ታሪክ*
...ማሊክ ኢብኑ ዲናር (ረሒመሁሏህ) እንዲህ ይላል፡- በስራ ከተማ ገባሁ ...አንድ ቀን ሰዎች በታላቁ መስጂድ ከዙሁር ሶላት ጀምረው እስከ ዒሻእ ሶላት በኃላ ድረስ ተሰብስበው አሏህን ሲለምኑ ተመለከትኩ .... "ምን አጋጠማችሁ ?" አልኳቸው።
እነሱም "ሰማይ ውሃ ከማውረድ ተቆጠበ፣ ወንዞቹም ደረቁ፣አሏህ ዝናብ እንዲያወርድልን ዱኣ እያደረግን ነው" አሉ።
ማሊክ እንዲህ ይላል፡- "ከዛም ሁሉም ወደ ቤታቸው ሄዱ፤ ለሀገሪቷ እንግዳ ስለነበርኩ በመስጅድ ውስጥ ተቀምጬ ቆዬሁ። በዚህ ሰኣት አንድ ጥቁር፣ አፍንጫው አጭር፣ ሆዱ የገፋ ፣ ከድህነቱ የተነሳ በአንድ ቁራጭ ልብስ እፍረተ ገላውን የሸፈነ፣ ሌላኛውን ጫንቃው ላይ ያደረገ ሰውዬ ወደ መስጅድ ገብቶ ሁለት ረከዓ ሰገደ፤ ከዛም በመስጅዱ ውስጥ ሰው መኖሩን ለማረጋገጥ ግራ ቀኝ ዞረ... እኔ ያለሁበት ቦታ ትንሽ የተደበቀ ስለነበር ሳያዬኝ ቀርቶ ሰው የለም በማለት ወደ ቂብላ ዞሮ እጆቹን በማንሳት፡- "አሏህ ሆይ! ባሮችህን ስርኣት ለማስያዝ ዝናብ እንዳይወርድ አግደሃል፤ በባሮችህ ኃጢኣት ላይ ታጋሽና ይቅር ባይ የሆንከው ጌታ ሆይ! ባሮችህን ውሃ ታጠጣቸው ዘንድ እማፅንሃለሁ!" አለ።
እጆቹን ከማውረዱ ሰማዩ ጨለመ፣ ደመናም ከየቦታው መጦ ከደመነ በኃላ ዝናቡ ዘነበ። ሰውዬው በጣም ስላስደነቀኝ ከመስጅድ ወጥቶ ወደ ቤቱ ሲሄደ ተከተልኩት... የተወሰነ ከተጓዘ በኃላ አንድ ቤት ውስጥ ገባ፤ ቤቱን በማግስቱ ለማግኘት ብዬ በሩ ላይ በጭቃ ምልክት አደረኩና ተመለስኩ።
በማግስቱ ፀሀይ ስትወጣ መንገዶቹን ተከትዬ ምልክት ያደረኩበትን ቤት ደረስኩ፤ ቤቱ የባሪያ መሸጫ ቤት ነበር ። የባሪያ ነጋዴውን "ባሪያ መግዛት እፈልጋለሁ" አልኩት። ነጋዴውም ረዢምና አጭር የተለያዩ ባሪያዎችን አሳዬኝ... የፈለኩትን ስላላገኘሁ "ከነዚህ ውጪ ሌላ አለህ?" አልኩት።
ባሪያ ነጋዴው፡- "ከነዚህ ውጭ የሚሸጥ ምንም የለኝም" አለ።
ማሊክ፦"ተስፋ ቆርጬ ከባሪያዎች ቤት ውጭ ተቀምጬ ባለሁበት ሰኣት ከበሩ አቅራቢያ ከእንጨት የተሰራ ጎጆ አየሁና..በዚህ ጎጆ ውስጥ ሰው አለ ወይ? " አልኩ።
ባሪያዎቹ " አንተ ባርያ መግዛት ነው የምትፈልገው በዚህ ውስጥ ያለው ባሪያ ግን ላንተ የሚገባ ባሪያ አይደለም አይመጥንህም" አሉ።
ማሊክ ፦"ላየው ፈልጋለሁ ይውጣ ብያቸው ባሪያው ከጎጆው ሲወጣ ያ! ትላንት በመስጅድ ውስጥ ሲሰግድ ያዩሁት ሰውዬ ነበር" አለ።
ማሊክ ለባሪያ ነጋዴው "ልገዛው እፈልጋለሁ" አለ።
ነጋዴው፦ " ይህ ባሪያ ለምንም ነገር ስለማይሆን ከሸጥኩልህ በኃላ ምናልባት አታሎ ነው የሸጠልኝ ብለህ ስሜን ታጠፋ ይሆናል!" አለ።
ማሊክ፦"እንዳሰብከው አይደለም ልገዛው ስለፈለኩ ነው" አለ....ነጋዴውም በርካሽ ዋጋ ሸጠለት ።
ማሊክ እንዲህ ይላል ፦ ይህን ባሪያ ወደ ቤቴ ወስጄው የተወሰነ ከተቀመጠ በኃላ አንገቱን ቀና አደረገና ጌታዬ ሆይ! ጥንካሬን ከፈለግክ ከኔ የሚበረታ አለ፣ ዝናን ከፈለክ ከኔ የበለጠ ቆንጆ አለ፣ ለስራ ከሆነ ደግሞ ከኔ የበለጠ አዋቂ አለና ለምን ገዛኸኝ?" አለ።
ማሊክ፦ "ትላንት የበስራ ከተማ ነዋሪዎች በሙሉ ባጋጠማቸው ድርቅ ምክንያት በመስጅድ ውስጥ ከዙሁር ሶላት እስከ ዒሻእ ሶላት በኃላ ድረስ ዱኣ ሲያደርጉ ቆይተዋል...
ነገር ግን ልምናቸው ተቀባይት አላገኘም ነበር። አንተ ግን መስጅድ ገብተህ እጆችህን አንስተህ አሏህን በለመንክ ሰኣት ልመናህ ተቀባይነትን አግኝቶ ዝናብ ወረደ” አለው።
አገልጋዩ፡-" ምናልባት ሌላ ይሆናል! ምንስ አሳወቀህ ምናልባት ያየኸው ሌላ ሰው ሊሆን ይችላል” አለ።
ማሊክ፦"ይልቁንስ! አንተ ነህ" አልኩት፤ አገልጋዩም፡- "አውቀኸኛል?"አለ፤
ማሊክ፦"አዎ!" አለ፤
አገልጋዩ ፡- "እርግጠኛ ነህ? " አለ፤
ማሊክ "አዎ!"አለ።
ማሊክ እንዲህ ይላል፦ "በአሏህ እምላለሁ! ከዛ በኋላ ወደኔ አልተመለከተም፤ ወዲያውኑ ለአሏህ ሱጁድ ወረደ...ስግደቱንም አራዘመ፤ ወደሱ በደንብ ስቀርብ፦ «የሚስጢሩ ባለቤት ሆይ! ሚስጥሩ ተጋለጠ፣ ይህ ሚስጢር ተስፋፍቶ ህይወትን መቋቋም አልችልም።» ሲል ሰማሁ ... ብዙም ሳይቆይ ነፍሱ ከሱ ተለይታ ይችን ዓለም ተሰናበተ።" #ሱብሐን_አሏህ
አንዳንድ የአሏህ ባሮች መልካም ስራቸውንም ሆነ ከአሏህ ዘንድ ያላቸውን ደረጃ በዚህ ልክ ነበር የሚደብቁ፤ እኛስ በኛና በአሏህ መካከል የቱን ያህል የመልካም ስራ ሚስጢር አለን!።
አሏህ ሆይ! ነውራችን ሸፍንልን፣ ላንተ ያለንን ፍራቻ ከአለት የጠና አድርግልን!
አሏህ ሆይ! ከንፁህ፣ ጨዋ፣ ታማኝ፣ አንተን ሲቀርቡ ከሚጽናኑ፣ መልካም ስራቸው ላንተ ከሆኑ ባሮች ያድርገን!
አሏህ ሆይ! በፍላጎትህና ውሳኔህ ደስተኞች አድርገን፣ቃል በገባህላቸው የዘላለም ደስታ ከሚጠቃቀሙ ባሮችህ አድርገን!።
:¨·.·¨: ❀
`·. ሑሰይን የዐብደሪይ ወዳጅ
T.me/husseyn_y_abdery_wedaj