********
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለተገልጋዮች ቅሬታ እና አስተያየት ማቅረቢያ የቴክኖሎጂ መተግበሪያ በውስጥ አቅም በማልማት ከየካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
ይህን መተግበሪያ ለመጠቀም ተገልጋዮች ወደ ተቋሙ በሚመጡበት ወቅት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ያላቸውን ቅሬታ በድምፅ አሊያም በፅሁፍ የሚያሰፍሩበት ሲስተም ሲሆን ወደ ተቋሙ ለአገልግሎት በሚመጡበት ወቅት ተቋሙ ውስጥ በሚገኘው የወንጀል ይግባኝ ጉዳዮች የአንድ ማዕከል ሬጅስትራር አገልግሎት መስጫ ማዕከል ውስጥ የዳኝነት ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ክፍል በመቅረብ በስራ ክፍሉ በሚገኙ ባለሙያዎች በመታገዝ አሊያም በእጅ ስልኮ በተቋሙ ኢንተርኔት/ዋይፋይ በመጠቀም የተቋሙን QR ኮድ ስካን በማድረግ የዳኝነት ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ፅ/ቤት የሚለውን በመጫን በድምፅ ወይንም በፅሁፍ ቅሬታዎን/አስተያየቶን ያቅርቡ ከሚሉ አማራጮች የሚፈልጉትን በመምረጥ ቅሬታዎን ማቅረብ ይችላሉ፡፡
ቅሬታው/አስተያየቱ የሚቀርበው በድምፅ ከሆነ የድምፅ ምልክቷን በመጫን መልእክቱን ማስተላለፍ የሚቻል ሲሆን በፅሁፍ የሚቀርብ ሲሆን ከተዘረዘሩት አስተያየት መስጫ ነጥቦች (እጅግ ከፍተኛ፣ ከፍተኛ፣ መካከለኛ ወይም ዝቅተኛ) አንዱን በመምረጥ አስተያየቶን መስጠት ይችላሉ፡፡
የተገልጋይ ቅሬታም ወደ ሰርቨር ገብቶ ደህንነቱን በጠበቀ ሁኔታ ለኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት የሚላክ መሆኑን በትህትና እንገልጻለን፡፡
የአጠቃቀሙን ቅደም ተከተል ከስር ባለው ምስል ይመልከቱ፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽንና ስትራቴጂያዊ አጋርነት ዳይሬክቶሬት