#የካቲት_13 ቀን እንኳን #መልካም_ስም_አጠራርና ጣፋጭ ዜና ላለው ለሶርያ መስፍን ልጁ ለሆነ በሰማዕትነት ካረፈ በኋላ #ቅዱስ_ሚካኤልና_ቅዱስ_ገብርኤል ከሞት አስነሥተውት፤ #ቅዱስ_ዑራኤልም ነጥቆ ወደ ሰማይ አሳርጎት በዚያው በሰማይ 14 ዓመት ለኖረ፤ ተመልሶ ወደ ምድር መጥቶ 40 ዓመት ለኖረ በተአምራቱና በትምህርቱ 85ሺህ አረማውያንን አሳምኖ ላጠመቀ #ለተመሰገነ_ለሁለተኛው_ለቅዱስ_አውሳብዮስ ለምስክርነቱና ለዕረፍቱ በዓል፣ ለከበረ #ለቅዱስ_ሰርግዮስ ከአባቱና እናቱ ከወድሞቹም ከሌሎችም ብዙ ሰዎች ጋር ሰማዕትነት ለተቀበሉበት ለዕረፍታቸው በዓልና ለኅርማኖስ ልጅ ለታላቁ ሰማዕት #ለቅዱስ_ፊቅጦር ለልደቱ መታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከከበረ አባት ከእስክድርያ አገር ሠላሳ ሁለተኛ ሊቀ ጳጳስ #ከአባ_ጢሞቴዎስ ዕረፍት፣ #ከቅዱስ_ፋሲለደስ ልጅ #ከቅዱስ_ቴዎድሮስ ከምስክርነቱ መታሰቢያ፣ #ከአባ_ክፍላና_ከአባ_ኅብስት ከመታሰቢያቸው #እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
#ሰማዕቱ_ቅዱስ_ፊቅጦር፦ ለዚህ ቅዱስ የአባቱ ስም ኅርማኖስ ነው እርሱም ለዲዮቅልጥያኖስ የአማካሪዎቹና የሠራዊቱ አለቃ ነው ስለ አምልኮ ጣዖት ሥራ ምክሩና ንግግሩ ሁሉ ከእርሱ ጋራ ነበር የእናቱም ስም ማርታ ይባላል በክርስትናዋ የጸናች ብፅዕት ናት።
ቅዱስ ፊቅጦርም በአደገ ጊዜ አባቱ ወደ ንጉሥ አቀረበው ንጉሡም በመንግሥቱ ውስጥ ሦስተኛ ማዕርግ አድርጎ ሾመው በዚያን ጊዜ ዕድሜው ሃያ ዓመት ነበረ። እርሱም የዚህን ዓለም ክብር ናቀ ሥጋ አይባላም ወይን አይጠጣም ዘወትርም ይጾማል ጸሎትንም ባለማቋረጥ በቀንና በሌሊት ይጸልያል። በክብር ባለቤት #ክርስቶስ ስም የታሠሩትን ይጐበኛቸዋል ለድኆችና ለምስኪኖችም ይመጸውታል።
የቅዱስ ቆዝሞስና ድምያኖስ እናት ቅድስት ቴዎዳዳን በገደሉዋት ጊዜ ንጉሡም ስለ መፍራት ሊቀብራት ማንም አልደፈረም። ይህ ቅዱስ ፊቅጦርም መጥቶ ሥጋዋን ወሰደ ከንጉሥ ስለሚመጣው ቅጣት ሳይፈራ ቀበራት። ጣዖት ስለ ማምለኩ አባቱን ዘወትር የሚገሥጸውና ብዙ ጊዜም የሚመክረው ሆነ አባቱም ወደ ንጉሥ ከሰሰው እንጂ አልሰማውም። ተከሶም ወደ ንጉሥ በአቀረቡት ጊዜ "አማልክት ያልሆኑ ርኲሳን ጣዖታትን ለሚያመልክ ሰነፍ ዝንጉ ልብ የለሽ ለሆነ ንጉሥ አላገለግልም። ከዛሬ ጀምሮ ለሕያው ንጉሥ #ክርስቶስ እገዛለሁ የሰጠኸኝንም ገንዘብህን ንሣ" ብሎ በፊቱ ትጥቁን ፈትቶ ጣለለት።
አባቱ ኅርማኖስም ወደ እስክንድርያ እንዲልከውና በኄርሜኔዎስ መኰንን ዘንድ በዚያ ፊቅጦር እንዲቀጣ ንጉሡን መከረው። በዚያን ጊዜም ከአደባባይ አወጡት እናቱም በብዙ ልቅሶ ልትሸኘው መጣች። እርሱም ሲመግባቸው ስለ ነበረ የታሠሩ ምዕመናን ስለ ድኆችና ምስኪኖች ስለ ሙት ልጆችና ስለ ባልቴቶች የሚሹትን በመስጠት እንድትጐበኛቸው አዘዛት ከዚያም አፉን ለጉመው ወሰዱት።
በእስክንድርያ አገር ወደ መኰንኑ ኄርሜኔዎስ ዘንድ በደረሰ ጊዜ ታላቅ ሥቃይን አሠቃዩት የ #እግዚአብሔርም መልአክ ወደ ሰማያት አውጥቶ ስለ ክብራቸው ለመናገር የሚያስጨንቁ የብርሃን ማደሪያዎችን አሳይቶ ወደ መኖሪያው መለሰው። መኰንኑም በእሳት በአፈሉት በዝፍት፣ በዲን ደግሞ አሠቃየው ከዚያም በብረት አልጋ ላይ አስተኝተው ከበታቹ እሳትን አነደዱ። ደግመው ከውሽባ ማንደጃ ውስጥ ጨመሩት በየአይነቱ በሆነ ሥቃይም አሠቃዩት የክብር ባለቤት #ጌታችንም ያጸናውና ከሥቃዩ ያስታግሠው መልአኩንም ልኮ ከቊስሉ ይፈውሰው ነበር።
ከዚህም በኋላ ወደ እንዴናው ከተማ ላከው በዚያም ታላቅ ሥቃይን አሠቃዩት ምላሱን ቆረጡ። በእሳት ያጋሉዋቸውን ችንካሮች በጐኖቹ ውስጥ ጨመሩ #እግዚአብሔር ግን አጽንቶ አስታግሦ ያለ ጉዳት በደኅና ያነሣዋል። ከዚህም በኋላ በዚያ በረኃብ እንዲሞት ከዱር ባለ ግምብ ውስጥ አሠሩት። እርሱ ግን መጥረብ የሚያውቅ ስለሆነ ላይዳዎችን በመጥረብና በመሸጥ በየጥቂቱ እየተመገበ የቀረውን ለድኆች እየሰጠ ኖረ። አንድ መኰንንም መጥቶ በዚያ ግምብ አቅራቢያ አደረ ስለ ቅዱስ ፊቅጦርም እርሱ የንጉሥ የሠራዊት አለቃ የሆነ የኅርማኖስ ልጅ እንደሆነ ነገሩት። መኰንኑም ወደርሱ አቅርቦ ብዙ ሸነገለው ባልሰማውም ጊዜ ያሠቃዩት ዘንድ አዘዘ ጅማቶቹን መዘዙ አፋን መቱት ቊልቊል ሰቀሉት በእጆቹ ላይ ከባድ ደንጊያ አንጠልጠሉ። ከዚያም ከሚነድ እሳት ውስጥ ጨመሩት ሙጫ፣ አደሮ፣ ማርና ዘይትን አፍልተው በላዩ ደፉበት በማበራያም አበራዩት አፉንም በአሞትና በእሬት አመረሩት ዐይኖቹንም አወለቁት ደግመውም ዘቅዝቀው ሰቀሉት። የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ተገልጾለት አጸናው አረጋጋው። ሥሮቹንም ሕዋሳቶቹን በቦታቸው መለሰለትና አዳነው።
አንዲት ዓሥራ አምስት ዓመት የሆናት ብላቴና ነበረች ቅዱስ ፊቅጦርን ሲአሠቃዩት በቤቷ መስኮት ታየው ነበር። መላእክትም በእጆቻቸው አክሊሎችን ይዘው እነርሱም በቅዱስ ፊቅጦር ራስ ላይ ሲያኖሩአቸው አይታ እንዴት እንዳየች ለአሕዛብ ነገረቻቸው እጅግም አደነቁ ከእርሳቸውም ብዙዎች በክብር ባለቤት በ #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት ዐረፉ። ያቺም ብላቴና በ #ጌታችን አመነች መኰንኑም ራሷን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ። የሕይወት አክሊልንም ተቀበለች ሁለተኛም የአመኑትን ሁሉ ራሳቸውን እንዲቆርጡአቸው አዘዘ የሕይወትንም አክሊል ተቀበሉ።
ከዚህም በኋላ የከበረች የቅዱስ ፊቅጦርን ራስ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ ተጋድሎውንም ሚያዝያ 27 ፈጽሞ የሕይወትና የድል አክሊል ተቀበለ። ምዕመናን ሰዎችም ሥጋውን ወስደው በከበሩ ልብሶች በድርብ በፍታ ገነዙት። እናቱ ማርታም ከአንጾኪያ እስክትመጣ በንጹሕ ቦታ አኖሩት በመጣችም ጊዜ ከዚያ ወሰደችው። ውብ ቤተ ክርስቲያንም ሠርታ ሥጋውን በውስጥዋ አኖረች ከእርሱም ታላላቅ ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ።
ለ #እግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን የቅዱስ ፊቅጦር በረከቱም ከእኛ ጋራ ለዘላለም ትኑር አሜን። ምንጭ፦ የሚያዝያ 27 ስንክሳር።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ሰማዕቱ_ቅዱስ_አውሳብዮስ_ዘሀገረ_ሶርያ፦ ይኽም ቅዱስ የሶርያው መስፍን ልጅ ነው፡፡ ለርሱም #መንፈስ_ቅዱስን የተመላች ስሟ አውሎፊያ የምትባ እኅት አለችው ይህንንም በተግሣጽና በጥበብ በማስተማር ካሳደጉት በኋላ የሮሜውን ንጉሥ ልጅ በታላቅ ክብር አጋቡት፡፡ በሠርጉም ዕለት ወደ ቅድስት ወደሆነችው ወደ እኅቱ ዘንድ ገብቶ "እስቲ ምከሪኝ ልቤ ይህን ጋብቻ አይሻውም ዓለምን ንቆ መተውን እንጂ" አላት፡፡እኅቱም "የዚህ የኃላፊው ዓለም ጣዕም ምን ይጠቅምሃል?እንደ ሊቀጳጳሳት ድሜጥሮስ በድንግልና መኖር ይሻልሃል" አለችው፡፡ ምሽትም በሆነ ወደ ሙሽራይቱ ጫጉላ ቤት ገብቶ የእነርሱ ውበትና ደምግባት እንደሚጠፋ ከዚህም ይበልጥ የሚጠቅማቸውን የጽድቅ ሥራ በመሥራት ድንግልናቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው ሙሽራይቱን አዋያት፡፡ ሙሽራይቱም በሀሳቡ ተስማምታ ድንግልናቸውን በመጠበቅ በጾም በጸሎት እየዋሉ ሌሊትም ከባሕር ውስጥ፡ገብተው፡ቆመው ሲጸልዩ ያድሩ ጀመር፡፡ አትራ ወደምትባል ቤተ ክርስቲያን ሄደው አራት እልፍ ይሰግዳሉ፡፡