#ቅዱስ_ቴዎድሮስ_ዘሮም
#አንድ_አምላክ_በሆነ_በአብ_በወልድ_በመንፈስ_ቅዱስ_ስም
የካቲት ሃያ ስምንት በዚች ዕለት #ለአርእስተ_አበው_ለቅዱሳን #ለአብርሃም_ለይስሐቅና_ለያዕቆብ የበዓላቸው መታሰቢያና በነገሥታት መክሲሞስና መክስምያኖስ ዘመን ሮማዊ ቅዱስ ቴዎድሮስ በሰማዕትነት አረፈ። እርሱም ከእስያ አውራጃ አስጢር ከሚባል አገር ነው። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ #ከቅዱስ_ቴዎድሮስ_ማኅበር ከሆኑ #ስድስት_ሺህ_ሦስት_መቶ_አራት ሰዎች በሰማዕትነት ከዐረፉ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።
ይህንንም ቅዱስ በነገሥታት ዘንድ አማልክትን በማምለክ እርሱ እንደማይስማማ ወነጀሉት በዚያንም ጊዜ አስጠርተው ለአማልክት ለምን አሉት እርሱም እኔ ክርስቲያን ነኝ ከሕያው #እግዚአብሔር ልጅ ከ #ጌታዬ_ከኢየሱስ_ክርስቶስ በቀር ሌላ አላመልክም ብሎ መለሰላቸው።
የበርብዮስጦስ ልጅ ንጉሡም ለአማልክቶቼ ብትገዛ በጭፍራዎቼና በመኳንንቶቼ ሁሉ ላይ አለቃ አድርጌ እሾምሃለሁ ብዙ ወርቅና ብር የከበሩ ልብሶችንም እሰጥሃለሁ አለው ቅዱስ ቴዎድሮስም ወርቅህና ብርህ ለጥፋት ይሁንህ እኔስ በንጉሤ በሕያው #እግዚአብሔር ልጅ በ #ኢየሱስ_ክርስቶስ ባለጸጋና አለቃ ነኝ አለው።
ንጉሡም ለአምላክህ ልጅ አለውን አለው የከበረ ቴዎድሮስም አዎን ከመለኮቱ ባሕርይ የተገኘ ከእርሱ ጋር ዓለምን የፈጠረ በእውነት ልጅ አለው ብሎ መለሰለት ንጉሡም አምላክህን ብናውቀው ልናገኘው እንችላለን አለው ቅዱስ ቴዎድሮስም ወደርሱ ከተመለስክ እንደ እኔ ጭፍራ ትሆናለህ የተወደደ መሥዋዕትም ያደርግሃል አለው።
ንጉሡም ነገር አታብዛ ብዙ ገንዘብ እሰጥህ ዘንድ ለአማልክቶቼ መሥዋዕትን አቅርብ እንጂ አለው የከበረ ቴዎድሮስም ንጉሡን ረገመው ጣዖታቱንም ሰደበ በዚያንም ጊዜ ንጉሡ ተቆጣ። ልብሱንም እንዲገፉት በትምህርቱም ከአመኑ አሕዛብ ጋር በጨለማ ቤት ያሥሩት ዘንድ አዘዘ። የከበረ ቴዎድሮስም ጸለየ በሌሊትም ወጣ ዕንጨቶችንም ሰብስቦ ጣዖቶችን ሁሉ አመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጠላቸው እንዳይሰሙ በአገልጋዮቻቸው ላይ #እግዚአብሔር ከባድ እንቅልፍ አሳድሮባቸዋልና።
ለንጉሡም በነገሩት ጊዜ አጽንቶ አሠረውና ልዩ ልዩ በሆነ በጽኑ ሥቃይ አብዝቶ ያሠቃየው ዘንድ ለመኰንኑ ሰጠው መኰንኑም እንዲህ አለው ለንጉሥ ለምን አትታዘዘም ለአማልክቶችስ ለምን አትሠዋም የከበረ ቴዎድሮስም እኔስ ለረከሱ አማልክት አልሠዋም ለከሀዲ ንጉሥም አልታዘዝም ብሎ መለሰለት።
መኰንኑም ይህን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቆጣ ከወንበሩም ላይ ተነሥቶ እንደ ነብር ተወርውሮ አንገቱን አነቀውና የከበረ ቴዎድሮስን በምድር ላይ ጥሎ ፊቱን ጸፋው በእግሮቹም ረገጠው #እግዚአብሔርም ትዕግስቱን አይቶ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤልን ላከለት መኰንኑንም ገድሎ ከምድር ዐዘቅት አሠጠመው ለከበረ ቴዎድሮስም በእስያ ሀገር ውስጥ እየተዘዋወረ የ #ጌታ_የኢየሱስ_ክርስቶስን ሃይማኖት እንዲአስተምር መንፈሳዊ ፀዓዳ ፈረስን ሰጠው።
ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ የከበረ ቴዎድሮስን ከነፈረሱ እንዲይዙት በትምህርቱም የአመኑትን ሁሉ እንዲገድሉ መቶ ፈረሰኞች ወታደሮቹን ላከ። ከሴቶችና ከልጆች በቀር ስድስት ሺህ አርባ ስምንት ሰውን ገደሉ። ሊይዙትም ወደ ቅዱስ ቴዎድሮስ በደረሱ ጊዜ ፈረሱ በላያቸው ተወረወረ ከአፉም እሳትን አውጥቶ አመድ እስኪሆኑ አቃጠላቸው ነገር ግን ሌሎች አግኝተው ያዙትና ወደ ንጉሥ ወሰዱት እርሱም ወደ እሥር ቤት እንዲአስገቡት እንዳይበላና እንዳይጠጣም ደጃፎችን እንዲዘጉበት አዘዘ።
ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት #ጌታችን_ኢየሱስ_ክርስቶስ ተገለጸለትና ቃል ኪዳን ሰጠው በዚያንም ጊዜ ከእሥር ቤት አውጥተው ዘቅዝቀው ሰቀሉት ደሙም እንደ ውኃ እስቲፈስ ከላም ቆዳ በተሠራ ጅራፍ ገረፉት ደሙ የነካቸውም ብዙ በሽተኞች ዳኑ ተአምራቱንም ያዩና የሰሙ በ #ጌታችን አመኑ በዚያችም ቀን መቶ አርባ ስምንት ሰዎች ተገደሉ።
እሊህን የተገደሉትንም ሰማዕታት ወደ እሳት ማንደጃ ውስጥ ከእርሱ ጋር ጨመሩአቸው በዚያንም ጊዜ ነፋስ ነፈሰ መብረቅና ነጐድጓድም ሆነ እሳቱንም አቀዝቅዞት የከበረ ቴዎድሮስ ምንም ሳይነካው ከእሳት ውስጥ ወጣ።
ከዚህም በኋላ ንጉሡ የሚያደርግበትን በአጣ ጊዜ ኃምሣ አራት ልጥር የሚመዝን ልጓም አምጥተው አፉን እንዲለጒሙት እግሮቹንና እጆቹንም በችንካር ቸንክረው ለአንበሳ እንዲጥሉት አዘዘ። አንበሳውም ዕንባውን እያንጠባጠበ እንደ ሰው አለቀሰለት እንጂ ምንም አልነካውም። #ጌታችንም ተገለጠለትና ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውንም ለሚያደርግ ገድሉንም ለሚጽፍ ዕድል ፈንታውን ከርሱ ጋር በመንግሥተ ሰማያት ያደርግ ዘንድ ቃል ኪዳንን ሰጠው።
ከዚህም በኋላ የሁለት መቶ ሰው ሸክም ዕንጨት መቶ ልጥር ባሩድ መቶ ልጥር የዶሮማር መቶ ልጥር ነሐስ አመጡ ከማንደጃውም ጨምረው እጅግ እስከሚግል አነደዱት ጸሎቱንም ከፈጸመ በኋላ ቅዱስ ቴዎድሮስን ወደ ነደደው እሳት ወረወሩት ምስክርነቱንም ፈጸመ የመላእክት አለቆች ቅዱሳን ሚካኤልና ገብርኤል ነፍሱን ተቀበሉ በሦስት አክሊላትም አቀዳጁት ሥጋውንም አውሳብያ የተባለች የመኰንኑ ሚስት ወሰደች ዋጋው ብዙ በሆነ ሽቱም ገነዘችውና ወደ ገላትያ ወሰደችው በዕብነ በረድ ሣጥንም አድርጋ በዚያ ቀበረችው ቤተ ክርስቲያንም ሠራችለት ከሥጋውም ታላላቆች ድንቆች ተአምራቶች ተገለጹ።
#ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
#ሰላም_ለክሙ_አምዓት_ስሳ። ወበበዐሠርቱ ሠላሳ #ማኅበራነ_ቴዎድሮስ_ማር_መኵሴ_ቴዎድሮስ ዕጓለ አንበሳ። እምኂሩትክሙ ብየ ኃሠሣ። ታናሕስዩ ሊተ ክቡደ አበሳ"። #ሊቁ_አርከ_ሥሉስ (አርኬ) #የየካቲት_28።
የካቲት 28 ቀን የሚከበሩ #ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)
2."6,304" ሰማዕታት (በቅ/ቴዎድሮስ አምላክ አምነው ሰማዕትነት የተቀበሉ)
#ወርኀዊ በዓላት
1.አማኑኤል ቸር አምላካችን
2.ቅዱሳን አበው (አብርሃም: ይስሐቅና ያዕቆብ)
3.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
4.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ
=>+"+ እግዚአብሔር ለኛ የሰማዕትነትን ሥራ ይሰጠን ዘንድ ቅዱሳን ስለሚሆኑ ሰማዕታት እንማልዳለን:: +"+
(ሥርዓተ ቅዳሴ ቁ. 73)
በግዕዝ➞ #ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ። እምእለ ተጸምዱከ ዘልፈ። ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ። እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውኩፈ። እምእለ አብኡ ብዑላን ዘተርፈ።
ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን። ሰማዕት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን። ደናግል ዓዲ ወመነኰሳት ኄራን። ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን። እስከ አረጋዊ ልሒቅ ወንኡስ ሕፃን።
ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ። ለዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ። ወለዘሰምዐ ቃሎ በዕዝነ መንፈስ። በጸሎተ እሙ #ማርያም ዐራቂተ ኵሉ እምባእስ። ኅቡረ ይምሐረነ #ኢየሱስ_ክርስቶስ።
በአማርኛ➞ #ጌታ_ሆይ ከብልጽግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።
እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።