Amhara Bureau of Agriculture @amharabureauofagriculter Channel on Telegram

Amhara Bureau of Agriculture

@amharabureauofagriculter


BOA

Amhara Bureau of Agriculture (English)

Are you passionate about agriculture and looking for a platform to stay updated on the latest trends, news, and information in the field? Look no further than the Amhara Bureau of Agriculture Telegram channel! With the username @amharabureauofagriculture, BOA is the go-to channel for all things related to agriculture in the Amhara region. The Amhara Bureau of Agriculture is a government organization dedicated to promoting sustainable agriculture practices, supporting farmers, and enhancing food security in the region. By joining this Telegram channel, you will have access to valuable resources, expert advice, and opportunities to connect with like-minded individuals who share your passion for agriculture. Whether you are a seasoned farmer, a student studying agriculture, or simply interested in learning more about this vital industry, the BOA channel has something to offer everyone. From updates on new agricultural technologies to tips for increasing crop yield, you will find a wealth of information that can help you improve your farming practices and stay ahead of the curve. In addition to informative posts, the Amhara Bureau of Agriculture Telegram channel also hosts live Q&A sessions with industry experts, virtual workshops, and networking events to help you expand your knowledge and connect with other agricultural professionals in the region. It's a great opportunity to learn from the best and grow your network within the agricultural community. Join the Amhara Bureau of Agriculture Telegram channel today and take your passion for agriculture to the next level. Whether you are looking to increase your crop yield, improve your livestock management skills, or simply stay informed on the latest industry news, this channel has everything you need to succeed in the world of agriculture. Don't miss out on this valuable resource – join BOA now and start reaping the benefits of being part of a supportive and knowledgeable agricultural community!

Amhara Bureau of Agriculture

19 Nov, 13:58


▬▬▬▬▬▬▬▬▬
*ሠላም እንዴት ናችሁ‼️
➺ወድ የግብርና መምሪያ አመራሮች በተፃፈው ደብዳቤ መሰረት በእዬ ደረጃው ያሉ “የግብርና ኤክስቴንሽን ኮሙዩኒኬሽን ቡድን መሪዎች“የግብርና ቢሮ ህዝብ ግንኙነት ፎካል ፐርሰን ሆነው እንዲሰሩ ደብዳቤ አያይዘን ልከናል። ወደፊት በቢሮው ህዝብ ግንኙነት በተለያዩ መልኩ ሙያዊ መደጋገፍ እናደርጋለን🙏🙏
➺ግብርና ከማምረትም በላይ ነው!!
▬▬▬▬▬▬▬▬▬

Amhara Bureau of Agriculture

31 Oct, 14:20


ምስጥ (Termite)

ምስጥ ባለበት ማሳ ላይ ስንዴ የሚዘራ ከሆነ በከፍተኛ ደረጃ ሰብሉ ሊጠቃ ይችላል፡፡ ስለሆነም ምስጥን የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በመስራትና አሲዳማ የሆኑ አፈሮችን በማሻሻል ጉዳት ማድረስ ከማይችልበት ደረጃ ላይ ማድረስ ይቻላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም በፀረተባይ እና በባህላዊ መከላከያ ዘዴዎችን በመጠቀም ምስጥን መከላከል ይቻላል፡፡ በመስኖ ውሃ የሚለማ የስንዴ ሰብል በምስጥ የሚጠቃ ከሆነ የመስኖ ውሃ በተገቢው መጠን በመስጠት ተባዩ በሰብሉ ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት መቀነስ ይቻላል፡፡

ምስጥ የሚያደርሰውን ጉዳት ውኃ በመስጠት መቆጣጠር ካልተቻለ ዲያዝኖን 60% (Diaznone 60% EC) 2 ሊትር ከ200 ሊትር በሆነ ውኃ ጋር በመበጥበጥ በአንድ ሄክታር ማሳ ላይ ከ 2 እስከ 3 ጊዜ ምስጡ ያለበትን አካባቢ ብቻ ደጋግሞ በመርጨት መቆጣጠር ይቻላል፡፡

የግሪሳ ወፍ (Quela quela) መከላከል

የግሪሳ ወፍ በከፍተኛ ቁጥር በመከሰት የስንዴ ሰብልን በእሸትነት ደረጃ ፍሬውን በመብላትና በማራገፍ ጥፋት የሚያደርስ ተዛማች የጀርባ አጥንት ያለው ተባይ ነው፡፡ በአብዛኛው የሀገራችን ክፍል ስንዴን በስፋት ማልማት ከተጀመረ ወዲህ የግሪሳ ወፍ ክስተት እየተስፋፋ ነው፡፡ መከላከል ካልተቻለ እስከ 100% ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፡፡ በመሆኑም የወፉ መንጋ ቁጥር አነስተኛና ከ 250,000 (ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ) በታች ከሆነ አርሶ አደሩ የተለያዩ የመከላከያ መንገዶችን በመጠቀም መከላከል አለበት፡፡

ለምሳሌ የወፍ ማደሪያ ጎጆ ማፈራረስና እንቁላሎችን መሰባበር፣ በማማ ላይ ሆኖ በወንጨፍ በማባረር መጠበቅ፣ በባህላዊ ማሰፈራሪያዎችን (ሰው መሰል አሻንጉሊት) በማቆም ማስፈራራት፣ የሚረብሽ ድምፅ ያለው ነገር በመጠቀም ጉዳቱን መቀነስ ይቻላል፡፡ ነገር ግን የወፉ ቁጥር ከ 250,000 (ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ) በላይ ከሆነ የአውሮፕላን የፀረ-ወፍ መድሃኒት ርጭት ማከናወን ያስፈልጋል፡፡ የፀረ- ወፍ ኬሚካል ርጭት ባታዮን 640% ULV 1 ሊትር በሄ/ር ሂሳብ በባለሙያ የተደገፈ የአየር ላይ ርጭት በማድረግ መቆጣጠር ይቻላል፡፡

የጎተራ ውስጥ ተባዮች ቁጥጥር ዘዴዎች

የጎተራ ውስጥ ተባዮች

እንደ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ገብስ፣ ማሽላና ሩዝ ያሉትን የሰብል ምርቶች የሚያጠቁ ዋና ዋናዎቹ የመጀመሪያ ደረጃ (Primary pests) የጎተራ ተባዮች፣ የጎተራ እሳት ራት (Angomois grain moth/Sitotroga cerealella)፣ የጎተራ ነቀዝ (Grain Weevil/Sitophilus granarius)፣ የበቆሎ ነቀዝ (Maize weevil/Sitophillus zeamais)፤ የሩዝ ነቀዝ (Rice Weevil/Sitophilus oryzea)፣ ትንሹ እህል ቦርብዋሪ (Lesser grain borer/Rhyzopertha dominica)፣ እና ትልቁ እህል ቦርብዋሪ (Larger grain borer /Prostephanus truncafus) ናቸው፡፡ የጎተራ ውስጥ ተባዮች መነሻቸው ከተባይ ያልፀዳ ዘር ወይንም ጎተራ ሊሆን ይችላል፡፡ የጎተራ ተባዮች በሳይንሳዊ መጠሪያቸውና በስነ-ህይወታዊ ጠባያቸው አንዳንድ ልዩነት ቢኖራቸውም በቅረጽም ሆነ በሚያሰከትሉት የድህረ ምርት ጉዳት በጣም የተቀራረቡ ናቸው፡፡

የአይጥ ቁጥጥር ዘዴ

አይጦችን ለመከላከል ከሚያስችሉ ባህላዊ መንገዶች መካከል ከእርሻ ወደ ጎተራ ውስጥ እንዳይገቡ በተቻለ መጠን የጎተራውን ስፍራ ከእርሻ ስፍራ ማራቅና አካባቢውን ማጽዳት፣ ጎተራዎች አይጦችን እንዳያስገቡ አድርጎ መስራት እንዲሁም ለአይጥ መራቢያ ዋና መሰረት የሆኑ መጠለያ፣ ውሃና ምግብ በማሳጣት አካባቢውን በማፅዳትና የተሻሻሉ ጎተራዎችን በመጠቀምና የጎተራ እግሮች ላይ ቆርቆሮ በማስገባት ለአይጦች ምቹ አለማድረግ ነው፡፡

ክፍል ሰባት ይቀጥላል
አዘጋጅ:- አንተነህ ሰውአገኝ

የመረጃ ምንጭ:- የአትክልት ፍራፍሬና መስኖ ውሃ አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት

Amhara Bureau of Agriculture

31 Oct, 14:20


ክፍል ስድስት
*
የመስኖ ስንዴ የተሻሻለ አመራረት ዘዴ

የስንዴ አረማሞ በሽታ (Smuts)

የስንዴ አረማሞ (Ustilago tritici) በሚባለው በሽታ አምጪ ተህዋስያን አማካኝነት የሚከሰት ነው፡፡ ብትን አረማሞ (loose smut) በሃገራችን የስንዴ አብቃይ አካባቢዎች በብዛት የተለመደ ነው፡፡ የበሽታ አምጭ ተህዋስ የሚከሰተው በወበቃማ ወቅት ሲሆን በአማካይ 16 - 230C የአየር ሙቀትና ከ60-85% የአካባቢው የአየር ርጥበት ተስማሚ የእድገት ሁኔታን ይፈጥርለታል፡፡ በሽታው የሚተላለፈው በዘር አማካኝነት ሲሆን የተበከለው የስንዴ ዘር መብቀል እንደጀመረ የበሽታው የዘር ፍሬ አብሮ በመብቀል ሳይታይ በተክሉ ውስጥ ለውስጥ (systemic) ማደግ ይጀምራል፡፡

በመጨረሻም ስንዴው ማዘርዘርና ፍሬ መያዝ በሚጀምርበት ወቅት ዘሩን ተክቶ አረማሞው ያድጋል፡፡ በዚህ መልኩ እራሱን በስንዴው ዘር የተካው የአረማሞ ዘር በንፋስና በዝናብ አማካኝነት እየቦነነ በጤነኞቹ የስንዴ ማሳዎችና ተክሎች አበባ ላይ በመጣበቅ ለመጪው የሰብል ዘመን በአዲሱ የስንዴ ሰብል ውስጥ የብከላ ህይወት ውህደቱን ይቀጥላል፡፡ ይህ በሽታ ዘር ወለድ በመሆኑ የሰብል በሽታ ስርጭት ቁጥጥር (quarantine) ስራን አጠናክሮ በመሥራት በፀረ-በሽታ ኬሚካል ያልታሸ የዘር ስርጭትን መቆጣጠር ሊተኮርበት የሚገባው ተግባር ነው፡፡ በሽታውን በብቃት ለመከላከል ዘርን ካርቦክሲል (carboxyl) እና ቤኖማይል (benomyl) በሚባሉ ሲስተሚክ ፀረ-በሽታ ኬሚካሎች ማሸት ያስፈልጋል፡፡

የሴፕቶሪያ በሽታ (Septoria spp.)

የስንዴ ቅጠል ሴፕቶሪያ በሽታ አምጪ ተህዋስ Septoria tritici blotch የሚባል ሲሆን የስንዴ ዛላ ምች በሽታን የሚያስከትለው ደግሞ Septoria nodorum blotch በመባል ይታወቃል፡፡ የበሽታ አምጭ ተህዋሶች የሚከሰቱት በወበቃማ ወቅት ሲሆን በአማካይ ከ20-250 ሴልሼስ የአየር ሙቀትና ከ35-100% የአካባቢው የአየር ርጥበት ተስማሚ የእድገት ሁኔታን ይፈጥርላቸዋል፡፡ የበሽታው ልዩ ምልክት በመጀመሪያ የታችኞቹ ቅጠሎች ላይ በመከሰት ጊዜው እየቆየ በሄደ ቁጥር ወደ ላይ በመስፋፋት የስንዴ ዛላው ላይ ይደርሳል፡፡

የተራዘመ ደመናማ የአየር ሁኔታና ዝናብ በሚፈጠርበት ወቅት በሽታ አምጭ ተህዋስያን በፍጥነት ለመስፋፋት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ለተደጋጋሚ ጊዜያት ስንዴን በአንድ ማሳ ላይ ደጋግሞ የሚዘራ (mono cropping) ከሆነ በሽታ አስተላላፊ ተህዋስያኖቹ በሰብል ቅሪት ላይ በመቆየት በተከታዩ አዲስ ሰብል ላይ ክስተቱ የጎላ ይሆናል፡፡ ይህ በሽታ ተጠቂ የሆኑ ዝርያዎች ላይ ከ25-60% የምርት ቅነሳ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ለበሽታው ተጋላጭነት የሌላቸውንና የመቋቋም ባህሪ ያላቸውን ዝርያዎች መጠቀም እና ሰብልን አፈራርቆ መዝራት በዝቅተኛ ወጪ በሽታውን የመከላከያ ዘዴ መሆናቸው ከግንዛቤ በመውሰድ ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡

የአፈር ወለድ በሽታዎች (soil borne diseases)

የስንዴን ሥርና ከአፈሩ አካባቢ የሚገኘውን የታችኛውን የአገዳውን ክፍል የሚያጠቁ በዓይን የማይታዩ ጥቃቅን በሽታ አምጪ ተህዋስያን በአፈር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ጥቃቅን በሽታ አስተላላፊ ተህዋስያን የተለየ ባህሪ የህይወታቸውን ግማሽ ዘመን የሚያሳልፉት ከአፈር ጋር በቀጥታ በመነካካት በመሆኑ ነው፡፡ እነዚህ በሽታ አስተላላፊ ተህዋስያን በሚከተለው አኳኋን በሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ፣ 1) የስንዴ ሰብል በሌለበት ጊዜ ሁሉ በአፈር ውስጥ ለብዙ ዓመታት ሊኖሩ የሚችሉ እና 2) ከሌላ አካባቢ በመምጣት በስንዴ ማሳ ውስጥ የሚኖሩ ሆነው አመጣጣቸው ከሌላ የሰብል ዓይነት ወይም በአካባቢው ከሚገኝ የስንዴ ማሳ ሆኖ በንፋስ፣ በእርሻ መሳሪያዎች፣ በሰው፣ በጎርፍና በእንስሳት አማካኝነት የሚሰራጩ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ በሥር አበስብስ የበሽታ ተህዋስያን የተጠቁ ተክሎች የመቀጨጭ፣ ደካማ ቅጥያዎች ወይም ጭራሽ ያለማውጣት፣ የመቃጠል (chlorotic)፣ ቅጥያዎች ሳይደርሱ መሞት እና የተጨማደደ (በደንብ ያልሞላ) የስንዴ ዘር እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ በዚህ በሽታ የተጠቁ ተክሎች አብዛኛውን ጊዜ በማሳው ውስጥ አንድ ቦታ ችምችም በማለት እዚህም እዛም ተበታትነው በግልፅ ይታያሉ፡፡ በደረሱ ሰብሎች መካከል የአገዳቸው ቀለም የመቀየርና የመበስበስ ምልክት ይታያል፡፡ የበሽታ አምጭ ተህዋስያኑን ምንነት ለይቶ ለማወቅ የላብራቶሪ ምርመራ በማካሄድ ማረጋገጥ ተገቢ ይሆናል፡፡ በሥሮችና የታችኛው የአገዳ ክፍል ላይ የሚከሰተው የመበስበስ በሽታ በሻጋታ (fungi) አምጭ ተህዋስያን አማካኝነት ሊከሰት የሚችል ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ Phytium spp, Rhizoctonia spp, Cephalosporium spp, Fusarium spp and nematodes ዋነኞቹ ናቸው፡፡
በመሆኑም በሽታውን መቋቋም የሚችሉ ዝርያዎችን መጠቀም፣ ዘርን በፀረ-ሻጋታ ኬሚካል ማሸትና የሰብል ፈረቃን መጠቀም ተገቢ ነው፡፡

የነፍሳት ተባዮች መከላከልና ቁጥጥር ዘዴዎች

የመስክ ላይ ነፍሳት ተባዮች መከላከልና ቁጥጥር

የስንዴ ሰብልን በማሳ ላይ ከሚያጠቁ ዋና ዋና ነፍሳት ተባዮች መካከል የሩሲያ ክሽክሽ (Russian Wheat Aphid) ፣ ባለአረንጓዴ መስመር ክሽክሽ (Green bug Aphid) እና ምስጥ (Termite) ናቸው፡፡ የእነዚህን ተባዮች ክስተትና ጉዳት ለመቀነስ የተቀናጀ የተባይ መከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

የሩሲያ ክሽክሽ (Russian Wheat Aphid)

የሩሲያ ክሽክሽ የውሃ እጥረት ባጋጠመው እና ከባህር ጠለል በላይ 1000 ሜ እና ከዛ በላይ በተዘራ የስንዴ ሰብል ላይ ይበዛል፡፡ ወረራ የሚጀምረው ሰብሉ ሦስት እስከ አምስት የቅጠል እድሜ ሲኖረው ነው፡፡ ስለሆነም ርጥበትን ለማቆር በመስመር ሲዘራ መከተር፣ የመስኖ ውሃ ስርጭትን የተስተካከለ ማድረግ እና እንደ ዝርያው ዓይነት እንዲዘራ የሚመከረውን የዘር መጠን (እስከ 150 ኪሎ ግራም ለ አንድ ሄክታር) አስቀድሞ መዝራት ተገቢ ነው፡፡ በኬሚካል ለመቆጣጠር ዘርን በቲዮሜቶክሳም 20 + ሜታላክሲል 20 (Apron star 42 WS 250 ግራም በ 1 ሊትር ውሃ ለ100 ኪሎ ግራም ዘር)፣(ቲዮሜቶክሳም 35 FS፣ 350 ግራም ለ100 ኪሎ ግራም ዘር) አሽቶ መዝራት እንደ ቅድመ-መከላከያ ያገለግላል፡፡

እንዲሁም ናሙና ተወስዶ ከ 10 እስከ 20 በመቶ የሚሆኑት የስንዴ ተክሎች ላይ የሩሲያ ክሽክሽ ከተገኘ የተመረጡ ኬሚካሎችን ዳይሜቶይት (dimethoate 40 EC 1 ሊትር ከ200 ሊትር ውኃ ጋር)፣ በመጠቀም ጊዜውን የጠበቀ አንድ ጊዜ ርጭት በማካሄድ መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ስንዴው ካዘረዘረ በኋላ ግን ምንም ዓይነት ፀረ-ተባይ መጠቀም አያስፈልግም፡፡

ባለአረንጓዴ መስመር ክሽክሽ (Green bug)

ባለ አረንጓዴ መስመር ክሽክሽ (greenbug) ከባህር ጠለል በላይ 1000 ሜትር በታች በሆኑ ስንዴ አብቃይ አካባቢዎች በብዛት ይከሰታል፡፡ የተባዩ ክስተት የሚጀምርበት ጊዜ ከሩሲያ ክሽክሽ ጋር ተመሳሳይ ሲሆን የመቆጣጠሪ መንገዶችም አንድ ዓይነት ናቸው፡፡፡

Amhara Bureau of Agriculture

31 Oct, 12:24


የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ መስኖ ልማት በተመለከት አሁናዊ መረጃ

ጥቅምት 21 2017ዓ.ም
የመስኖ ልማት በክልላችን በሁሉም ዞን በሚባል ደረጃ ከአመት አመት በስፋትና ክላሰተርን መሰረት ያደረገ የመስኖ ልማት ስራ እየተሰራ ነው፤ በምርትና ምረታማነት ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ ይገኛል። ክልላችን በርካታ ወንዞች የሚፈሱበት፣ የከርሰ ምድር ዉሃ የሚገኝበት፣ በክረምት የሚገኘዉን ከፍተኛ የዝናብ ዉሃ በማሰባሰብና በመያዝ ለመስኖ ልማት ማዋል የሚቻልበትና በበጋ ወቅት ያለዉን ሰፊ የሰዉ ጉልበት በመጠቀም የአትክልትና ፍራፍሬ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ ያለው በመሆኑ መስኖ ላይ መረባረብ አለብን፡፡

የምግብ ዋስትናን የምናረጋግጥበትና ለገበያና ኢንዱስትሪ የሚሆን የተሻለ ምርት የምናገኝበት መሆኑ ግንዛቤ ተይዞ ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነዉ፡፡ ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች አርሶ አደሩ በአመለካካት ከመኸር የበለጠ ምርት በመሰኖ ማማረት እንደሚችል የግብርና ኤክስቴንሽን ምክር አገልግሎት በመጠቀም ፤ግንዛቤው እያደገ በመምጣቱ በአካባቢዉ ያለዉ የዉሃ አማራጮችን የመለየት፤ የተሻሻሉ ቴክኖሎችዎችንና አሰራሮችና የመጠቀም ልምዱ በመዳበሩ የመስኖ ልማት ስራችን እያደገ መጥቷል፡፡

ካለው የመስኖ የመልማት አቅም አንፃር ሲታይ ግን ገና ብዙ መስራት እንደሚገባን መረጃወች ያሳያሉ፡፡ በተለይ የዝናብ መቆራረጥ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች በክረምት የሚገኘውን አነስተኛ ዝናብ በማቆር በደጋፊ መስኖነት መጠቀም ይገባል።

ሀገራችን የተያያዘቸውን የረጅም ጊዜ የልማት ዕቅድ ለማሳካት የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የመሪነት ሚና አለው፤ የሰብል ልማት ዘርፍ ለአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ጉልህ ሚና ያለው ሲሆን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተየያዘ የሚከሰተውን ችግር ለመቅረፍ የመኸር የሰብል ልማት ሥራችን ዉጤታማ ከማድረግ ጎን ለጎን የመስኖ ልማት በተለይም አትክልትንና ፍራፍሬ ልማት ስራዎች የበለጠ ማስፋፋት ይገባል።

ግብርና ቢሮ በ2017 ዓ.ም በስፋት ፤ በክላሰተርና ፤ ዘላቂነት ያለው፤በጊዜ የለኝም መንፈስና በተጠቃሚው ማህበረሰብ ተመሰካሪነትን ባረጋገጠ መልኩ እንደሌላው ተግባራት የመስኖ ስራችን በታቀደው ልክ ለመፈጸም መረባረብ አለብን መልክታችን ነው፡፡
አዘጋጅ አሻግረው ፈረደ

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ

ድረ-ገጽ
http://www.amhboard.gov.et/
ቴሌግራም https://t.me/AmharaBureauofAgriculter
ፌስቡክ https://www.facebook.com/profile.php?id=100064357704820
ዩትዩብ https://www.youtube.com/@amharaagriculturebureau6055
ቲክቶክ https://tiktok.com/@amhara.agricultur

Amhara Bureau of Agriculture

31 Oct, 12:24


ክፍል አምስት
*
የመስኖ ስንዴ የተሻሻለ አመራረት ዘዴ

የመስኖ ስንዴ ሰብል ጥበቃ

የአረም መከላከል እና ቁጥጥር ዘዴዎች

በአጠቃላይ ሲታይ አረም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ላላቸው ሰብሎች የሚያስፈልገውን ምግብ (plant nutrients)፣ የፀሐይ ብርሃንና (Sunlight) እርጥበትን (Moisture) ስለሚሻማ የሰብሎቹን ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ በቆላማ አካባቢዎች የማንኛውም አረም ዕድገት እጅግ ፈጣን በመሆኑ በወቅቱ ካልታረመ ለስንዴ ሰብል የሚሰጠውን ማዳበሪያና የመስኖ ውሃ በእጅጉ ስለሚሻማ ከ63-90 ፐርሰንት የምርት መቀነስ ሊያስከትል እንደሚችል የቀደሙ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በቆላማ፣ ወይና ደጋና ደጋማ አካባቢዎች እጅግ በርካታ የሣርና ቅጠለ ሰፋፊ አረሞች ይገኛሉ፡፡

እስካሁን በዛ ያሉ የአረም ቁጥጥር ዘዴዎች የስንዴ ማሳን አረም ለመቀነስና የሰብሉን ምርታማነት ለመጨመር እንደሚያግዙ ተረጋግጧል፡፡ እነሱም የመከላከል ተግባራት፣ ባህላዊ የቁጥጥር ዘዴዎች፣ የፀረ-አረም ኬሚካል ርጭት እና የተቀናጀ አረም ቁጥጥር ዘዴዎች ናቸው፡፡

በእጅ ማረም

በቆላና ወይናደጋ አከባቢዎች ስንዴ ከተዘረ በኋላ ከ20 እስከ 30 ቀናት እንዲሁም በደጋማ አካባቢዎች ከ30 እስከ 40 ቀናት ባሉት መካከል በእጅ ማረም በአግባቡ አረምን ለመቆጣጠር ያስችላል። ነገር ግን የስንዴ እና የሳር አረም ቡቃያዎች በሚመሳሰሉበት ወቅት እንዲሁም ሰፊ ማሳ ላይ በእጅ ማረም ተመራጭ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ፀረ-አረም መድሃኒት መርጨት ከተቻለ ከ20ኛው ቀን በኋላ በእጅ በማረም በርጭት ወቅት ያመለጡትን አረሞች ለማስወገድ ስለሚረዳ ርጭቱን ማገዝ ያስፈልጋል፡፡

የእጅ አረም እንደየ ማሳውና የአከባቢው ሁኔታ እስከ ሁለት ጊዜ ሊከናወን ይችላል። የአረም ሥራ በሚካሄድበት ወቅት አረሞቹ እንዳይጎራረዱና ሰብሉ እንዳይሰባበር በጥንቃቄ ማረም ያስፈልጋል፡፡ ስንዴ በመስኖ በሚለማባቸው አከባቢዎች በአረም ወቅት የሰብሉ ስሮች ለፀሐይ ብርሐን ሊጋለጡ ከመቻላቸውም ባሻገር በአፈሩ ውስጥ የነበረው እርጥበት በፍጥነት ስለሚተን እርጥበቱን መተካት አስፈላጊ በመሆኑ ወዲያው የመስኖ ውሃ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

ባህላዊ የአረም መቆጣጠሪያ ዘዴዎች

የማሳ ዝግጅት፡- ማሳው ላይ የነበረ ሰብል እንደተሰበሰበ ማሳውን ጠለቅ አድርጎ ማረስ/መገልበጥ እና ዘር ከመዘራቱ በፊት እንደ አፈሩ ሁኔታ እስከ ሶስት (3) ጊዜ ማረስ ያሰፈልጋል፡፡ የመጀመሪያው እርሻ በደረቅ ወቅት የሚተገበረው ከሁለት ዓመት በላይ ማሳ ላይ የመቆየት አቅም ያላቸው አረሞችን (perennial weeds) ለመቀነስ ነው፣ ሁለተኛው እርሻ ከዘር በፊት የበቀሉ አረሞችን ለመገልበጥ እና ሦስተኛ እርሻ በዘር ወቅት የለሰለሰ ማሳ ለማዘጋጀት ነው።

በተጨማሪ በደረቅ/በጋ ማረስ፣ አረሙን ለፀሀይ እና ዘር አዳኞች በማጋለጥ በአፈር ውስጥ ያሉ የአረም ዘር ክምችቶች እንዲቀነሱ ይረዳል፡፡
በመስመር መዝራት፡- በመስመር መዝራት የሚመከር የአሰራር ዘዴ ሲሆን ይህም ሰብሉን የበለጠ ብቁ በማድረግ የአረሞቹን እድገት ያቀጭጫል።

የዘር መጠን፡- ትክክለኛ የዘር መጠን መጠቀም ዘርን ከመቆጠብ እና መሬትን በአግባቡ ከመጠቀም በተጨማሪ ለሰብሉ የበለጠ አመቺ የእድገት ሁኔታን በመፍጠርና የአረምን እድገት በመግታት ላይ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
የዘር ጥልቀት፡- ተገቢውን የዘር ጥልቀት መጠበቅ ሰብሉ የተስተካከለ ብቅለትና አቋም እንዲኖረው ይረዳል፡፡

በዚህ መሠረት ሰብሉ ወደ መጀመሪያ የእድገት ደረጃ ወቅት የመሻማት አቅሙ ደካማ ስለሆነ ተገቢውን ጥልቀት መጠቀም ፋይደው የጎላ ነው፡፡
ሰብል ፈረቃ፡- ስንዴን ከአትክልት ሰብሎች (ሽንኩረት፣ ቲማቲም፣ ድንች፣ ጥቅል ጎመን፣ ቃሪያ ወዘተ)፣ ከቅባትና ጭረት ሰብሎች (ጥጥ፣ ለውዝ፣ ሰሊጥ፣ ሱፍ፣ ጎመን፣ ኑግ ወዘተ) እና ከጥራጥሬ ሰብሎች (ባቄላ፣ አተር፣ አኩሪ አተር፣ ሽምብራ፣ ማሾ፣ ቦለቄ፣ ወዘተ) ጋር እያፈራረቁ መዝራት ተገቢ ነው፡፡

ስለዚህ ሰብልን አፈራርቆ መዝራት የአስቸጋሪ አረሞችን ክስተት እና ጥቃት ይቀንሳል፡፡ በመሆኑም ስንዴን በአንድ ማሳ ላይ አከታትሎ መዝራት የአፈር ለምነትን ከመቀነሱም በተጨማሪ የአረም ክስተትን ያስከትላል፡፡ ስለዚህ ማፈራረቅ የአረሞችን የሕይወት ኡደትን በማዛባት ምርትን በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራል፡፡

ፀረ-አረም መድሃኒትን መጠቀም

የስንዴን አረም ለመቆጣጠር አዋጭነታቸው የተረጋገጠላቸውና በገበያ ላይ በስፋት የሚገኙትን የተለያዩ ፀረ-አረም መድሃኒቶችን መጠቀም ተገቢ ይሆናል። የፀረ-አረም መድሃኒቶቹ የሚረጩት ሰብሉ ከ2-3 ቅጠል እና አረሙ ከ2-4 ቅጠል ሲያወጣ ነው። በመሆኑም ፀረ-አረም መድሃኒቶቹ የቅጠለ ሰፋፊ እና የሳር አረሞችን በመቆጣጠር ይታወቃሉ። መድሃኒቶቹ የአረም ዕድገትን ስለሚገቱ ከርጭቱ በኋላ ስንዴው በፍጥነት አድጎ መሬቱን ስለሚሸፍን አዳዲስ አረሞች የመብቀል ዕድላቸውን በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ የርጭት ጊዜው የሚዘገይ ከሆነ ግን መድሃኒቱ አረምን የመቆጣጠር አቅሙ ይቀንሳል፡፡

ቅንጅታዊ የአረም መከላከልና የመቆጣጠር ዘዴ (IWM)

ጥሩ የማሳ ዝግጀት ማድረግ፣ ንጹህ ዘር መዝራት፣ ኩትኳቶ እና ዘግይቶ የሚበቅሉ አረሞችን በእጅ መንቀል አንዱ የተቀናጀ የአረም ቁጥጥር ዘዴ ማሳያ ነው፡፡ ፀረ-አረም መድሃኒቶችን በጥሩ ሁኔታ በተዘጋጀው የስንዴ ማሳ ላይ በመርጨት እና በመድሓኒቱ ያልሞቱትን ቀድሞ መንቀል ሌላኛው የተቀነጀ የአረም ቁጥጥር ዘዴ ማሳያ ነው፡፡

ክፍል ስድስት ይቀጥላል
አዘጋጅ:- አንተነህ ሰውአገኝ

የመረጃ ምንጭ:- የአትክልት ፍራፍሬና መስኖ ውሃ አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት

Amhara Bureau of Agriculture

31 Oct, 12:23


ክፍል አራት
*
የመስኖ ስንዴ የተሻሻለ አመራረት ዘዴ

የማዳበሪያ አጠቃቀም

ሰው ሰራሽ (Inorganic Fertilizers) ማዳበሪያ አጠቃቀም

በአብዛኛው የሀገራችን አካባቢዎች በስፋት የተለመዱት ሰው ሰራሽ የማዳበሪያ ዓይነቶች ኤን.ፒ. ኤስ (NPS) እና ዩሪያ (UREA) ናቸው፡፡ የኤን.ፒ. ኤስ ማዳበሪያ በተፈጥሮው በአፈር ውስጥ ለረጅም ጊዜ የመቆየት ባህሪ ስላለው ከስንዴ ሰብል ጋር አብሮ ይዘራል፡፡ ለስንዴ ስብል የሚሰጠው የኤን.ፒ.ኤስ ማዳበሪያ መጠን እንደየአካባቢው ሁኔታ ይለያያል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ግን በሁሉም ስነ-ምህዳሮች በሄክታር 100 ኪ.ግ. መስጠት በቂ ነው፡፡ ሰብሉ በመስመር ከተዘራ የማዳበሪያው አሰጣጥ ከዘሩ 5 ሳ. ሜትር ርቀት ላይ መስመር በማውጣት ከተጨመረ በኋላ በአፈር በመሸፈን ውሃ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

ሰብሉ በብተና የሚዘራ ከሆነ በምክረ-ሃሳቡ የተቀመጠው የኤን.ፒ.ኤስ ማዳበሪያ መጠን በተስተካከለው ማሳ ላይ በብተና በዘር ወቅት በመበተን የውሃ ማጠጫ ትልም (furrow) አውጥቶ ወዲያው ውሃ መስጠት ያስፈልጋል፡፡
የስንዴ ሰብል ጤናማ ዕድገት ኖሮት ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችለው በቂ የናይትሪጂን ንጥረ-ነገር ሲያገኝ በመሆኑ ስንዴው በሚዋለድበት (Tillering Stage) እና ሊያብብ ሲል (Booting stage) በቂ የናይትሮጂን ንጥረ-ነገርን ማግኘት አለበት፡፡

ለስንዴ ሰብል የሚያስፈልገው የዩሪያ ማዳበሪያ መጠን እንደአፈሩ ዓይነት ከቦታ ቦታ የሚለያይ ቢሆንም በሄክታር 150 ኪ.ግ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ለቆላማ አካባቢዎች የዩሪያ ማዳበሪያ ለሰብሉ የሚሰጠው ሁለት ጊዜ ሲሆን በአብዛኛው የመጀመሪያው 75 ኪ.ግ በሰብሉ ውስጥ የበቀለው ዓረም ከተወገደ በኋላ ስንዴው መዋለድ (Tillering) ሲጀምር ይሆናል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ቀሪው 75 ኪ. ግ. ዩሪያ መጠን የስንዴው ሰብል ሊያብብ ሲል (Booting Stage) ይሰጣል፡፡

በሌላ በኩል ለወይና ደጋና ደጋማ አካባቢዎች ደግሞ የዩሪያ ማዳበሪያ ለሰብሉ የሚሰጠው ሁለት ጊዜ ሲሆን በአብዛኛው የመጀመሪያው 1/3ኛው (50 ኪ.ግ) በዘር ወቅት ሲሆን ቀሪው 2/3ኛው (100 ኪ.ግ.) በሰብሉ ውስጥ የበቀለው ዓረም ከተወገደ በኋላ ስንዴው መዋለድ (Tillering) ሲጀምር ነው፡፡ በአጠቃላይ የዩሪያ ማደበሪያ ለሰብሉ የሚሰጠው ሰብሉ ውሃ ከጠጣ በኋላ በዕለቱ የአየር ሙቀት በሚቀንስበት ሠዓት መሆን አለበት፡፡

የተፈጥሮ ማዳበሪያ አጠቃቀም

የተፈጥሮ ማዳበሪያ በሌሎች የሰው ሰራሽ ማዳበሪያዎች የማይተካውን የአፈር ብስባሽ መጠን (Humus) ለመጠበቅ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ እንደየአከባቢው ሁኔታ ኮምፖስት ፤ ቨርሚኮምፖስትና ባዮስለሪ ኮምፖስት በማዘጋጀት እንደዬ አቅርቦቱ በማሳ ውስጥ ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንት ቀድም ብሎ መጨመርና የሰብል ቅሪትን በማሳ ውስጥ መተው አስፈላጊ ነው፡፡

የተፈጥሮ ማዳበሪያዎች ብዙ ጊዜ ብቻዉን መጠቀም መጠኑ በጣም ከፍተኛ ሰለሆነ ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያዎች ጋር አቀናጅቶ መጠቀም ለመስኖ ስንደ ምርታማነት ይመከራል፡፡ ስለሆነም ለአንድ ሄክታር 8 ቶን በደንብ የተብላላ ፍግ ወይም 5 ቶን ኮምፖስት ከ50% የሰው ሰራሽ ማዳበሪያዎች ጋር አቀናጅቶ መጠቀም ለመስኖ ስንደ ምርታማነት ይመከራል፡፡

የሰው ሰራሽ ማዳበሪያዎችን ከተፈጥሮ ማዳበሪያዎች ጋር አቀናጅቶ መጠቀም በሂደት የአፈር ንጥሬ ነገርን ለሰብሉ እድገት በዘላቂነት በመስጠት የአፈር ሁለንተናዊ ጤንነትን እና ምርታማነትን በዘላቂነት ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስላለዉ በተገብ መጠንና ይዘት መጠቀም ለመስኖ ስንደ ምርታማነት ይመከራል።

ክፍል አምስት ይቀጥላል
አዘጋጅ:- አንተነህ ሰውአገኝ

የመረጃ ምንጭ:- የአትክልት ፍራፍሬና መስኖ ውሃ አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት

Amhara Bureau of Agriculture

31 Oct, 12:22


ስለሆነም በአካባቢው በቂ የመስኖ ውሃ ካለ አርሶ አደሮች መሬታቸውን አርሰውና ለመስኖ ውሃ ስርጭት እንዲያመች አድርገው በማዘጋጀት ያለምንም ችግር ስንዴን ማምረት ይችላሉ፡፡ በእነዚህ አካባቢውች የዘር ወቅቱ ከጥቅምት እስከ ታህሳስ መጨረሻ ድረስ መሆን ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን የበልግ ዝናብ ባለባቸው አካባቢዎች ምርቱ በዝናብ እንዳይበላሽ የሰብሉን የመድረሻ ጊዜ ከግምት ውስጥ በማስገባት የዘር ወቅቱን መወሰን ያስፈልጋል፡፡

በመስኖ ለሚለሙ ደጋማ አካባቢዎች፡- በደጋ አካባቢዎች የሙቀቱ መጠን አነስተኛ በመሆኑ የሰብሉ የመድረሻ ጊዜ በአንፃራዊ ረጅም ስለሆነ የዘር ወቅቱ በዋናው የመኸር የዘር ወቅት ላይ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም በደጋ አካባቢ የመስኖ ስንዴ የዘር ወቅት እስከ ታህሳስ አጋማሽ ድረስ መሆን ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም በአካባቢው በቂ የመስኖ ውሃ ካለ አርሶ አደሮች መሬታቸውን አርሰውና ለመስኖ ውሃ ስርጭት እንዲያመች አድርገው በማዘጋጀት ያለምንም ችግር ስንዴን ማምረት ይችላሉ፡፡

የዘር መጠንና አዘራር

በመስኖ በሚለሙ ዝቅተኛ ቦታዎችም ሆነ በወይናደጋ አካባቢዎች ስንዴ በመስመር ቢዘራ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ ይታወቃል፡፡ ከዚህም ባሻገር ስንዴን በመስመር መዝራት በሄክታር የሚያስፈልገውን የዘር መጠን ከመቀነሱም በላይ የሰው ሰራሽ ማዳበሪያን ከተክሉ ትክክለኛ እርቀት ጠብቆ ለሰብሉ ለመስጠት እንዲሁም አረምንና ተባይን ለመቆጣጠር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በመስመር የሚዘራ ስንዴ ብዙ ቅጥያዎች (Tillers) ስለሚያወጣ ምርታማነቱ በእጅጉ ይጨምራል፡፡

በመስመር ለመዝራት የሚያስፈልገው የዘር መጠን በሄክታር በሁሉም ስነ-ምህዳሮች ከ125-150 ኪግ ሲሆን የዘሩ የብቅለት ደረጃ ከ95 ፐርሰንት በላይ መሆን አለበት፡፡ በሌላ በኩል በብተና የሚዘራ ከሆነ በሁሉም ስነ-ምህዳሮች የዘር መጠኑ በሄክታር ከ150-175 ኪ.ግ. ሲሆን ዘሩ ከተዘራ በኋላ በትራክተር በሚገጠም ሪጀር ወይም በበሬ በሚጎተት ማረሻ ትልም (Furrow) ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን የምንጠቀመው ዘር የብቅለት ደረጃው ከ95 ፐርሰንት በታች ከሆነ በሄክታር የሚያስፈልገው የዘር መጠን ሊጨምር ይችላል፡፡

ክፍል አራት ይቀጥላል
አዘጋጅ:- አንተነህ ሰውአገኝ

የመረጃ ምንጭ:- የአትክልት ፍራፍሬና መስኖ ውሃ አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት

Amhara Bureau of Agriculture

31 Oct, 12:22


ክፍል ሶስት
*
የመስኖ ስንዴ የተሻሻለ አመራረት ዘዴ

የማሳ መረጣ

ከአካባቢው የእርሻ መሬት ውስጥ ለመስኖ ልማት ይበልጥ ተስማሚ የሚሆነው መሬት ሜዳማነት ጠባይ ያለውና ወጣ ገባ ያልሆነ ተዳፋትነቱ ከ3% ያልበለጠ አነስተኛ ተዳፋትነት ያለው ሆኖ ውሃ በተመጣጠነ ሁኔታ ሊፈስ የሚችልበት ማሣ ተመራጭነት ይኖረዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ለመስኖ የሚለቀቀው ውሃ በረባዳማ ቦታዎች ላይ በመተኛት ረግረጋማ ቦታን የሚፈጥር ሲሆን ከፍተኛ ቦታዎች ደግሞ በቂ ውሃ ስለማይደርሳቸው ሰብሎች የተመጣጠነ ውሃ እንዳያገኙ ተጽእኖ ያሳድራል።

ሰብሎች የተመጣጠነ ውሃ ማግኘት ካልቻሉ ደግሞ እድገታቸው ወጥነት ባህሪይ የማይኖረው ሲሆን በረባዳማ ቦታዎች ላይ የሚከማቸው ትርፍ ውሃም የሰብል ሥሮችን በውሃ እንዲታፈኑ በማድረግ የአየር ዝውውርን በመግታትና እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ እድገታቸው እንዲቀጭጭና እንዲገታ ያደርጋል። ይህም ሁኔታ የውሃና የማዳበሪያ ብክነትን ከማስከተሉም በላይ በሰብሎች እድገት ላይ ተጽዕኖ በማሳደር የሰብል ምርት ይቀንሳል።
የስንዴ ሰብልን በመስኖ ለሚያመርቱ አርሶ አደሮች ከገጸ ምድር የመስኖ ውሃ አጠቃቀም ዘዴዎች ውስጥ የሚጠቀሙበት የቦይ መስኖ ዘዴን ነው፡፡

ስለሆነም ለመስኖ እርሻ የሚውለው መሬት የተመጣጠነ የውሃ ሥርጭትና ብቃት/efficiency/ ያለው የመስኖ አጠቃቀም ሥርዓትን ለማስፈን ማሣው በተገቢው ሁኔታ መስተካከል ይኖርበታል፡፡ የመስኖ ማሣ በሚስተካከልበት ወቅት መነሻ መደረግ ያለባቸው ነጥቦች የአፈሩ ቅንጣትና ጥልቀት፣ የመሬቱ ተዳፋትነት፣ የመስኖ ውሃ አጠቃቀም ዘዴና የመሳሰሉት ሁኔታዎች በቅድሚያ መጠናትና መታወቅ ይኖርባቸዋል። ከፍተኛ ተዳፋትነት ያላቸውን ቦታዎች ለመስኖ በምንጠቀምበት ወቅት ለአፈር መሸርሸር የተጋለጡ ስለሚሆኑ ከፍተኛ የአፈር ክለት ያስከትላል።

የማሳ ዝግጅት

አነስተኛ የመሬት ይዞታ ላላቸው አርሶ/ አርብቶ አደሮች
ለስንዴ ሰብል ልማት የታሰበው ማሳ በበሬ፣ በፈረስ ወይም በግመል የሚታረስ ከሆነ እንደ አመራረት ዘይቤውና አፈሩ ዓይነት በአማካይ ከ2-3 ጊዜ ሊታረስ ይችላል፡፡
በመስኖ ለሚለሙ ወይናደጋና ደጋማ አካባቢዎች፡- የመጀመሪያው እርሻ የመኸሩ ሰብል እንደተሰበሰበ በአፈሩ ውስጥ ያለው እርጥበት ሙሉ በሙሉ ከማሳው ውስጥ ተሟጦ ከማለቁ በፊት የሚከናወን ሲሆን ሁለተኛውና ሦስተኛው የእርሻ ሥራ የሚተገበረው መሬቱን ለማስተካከያው መሣሪያ ምቹ ለማድረግ ታስቦ ነው፡፡

በመስኖ የሚለሙ ቆላማ አካባቢዎች አመቱን ሙሉ የሚፈስ ውሃ ስላለ ቢያንስ በአመት ሁለት ጊዜ ሰብል ማምረት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በአፋር፣ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ ሁለት ዋና ዋና የዘር ወቅቶች አሉ፡፡ አንደኛው ወቅት ሙቀት ወዳድ የሆኑ (ጥጥ፣ ሰሊጥ፣ ለውዝ፣ ወዘተ) ሰብሎች የሚዘሩበት ወቅት (ከግንቦት እስከ ሰኔ ወር ባሉት ጊዚያት) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እንደ ስንዴ የመሳሰሉ ቅዝቃዜ የሚወዱ ሰብሎች የሚዘሩበት ወቅት (ከጥቅምት እስከ ህዳር ወር መጨረሻ ድረስ) ያለው ጊዜ ነው፡፡ ስለሆነም ለስንዴ ሰብል የሚዘጋጀው ማሳ በበሬ ወይም በግመል ከሆነ ቀደም ሲል የተዘራው ሰብል ከተሰበሰበ ከ15 ቀናት በኋላ በመሬቱ ውስጥ ያለው እርጥበት ሲቀንስ የመጀመሪያው እርሻ ይታረሳል፡፡

በመጀመሪያ የታረሰው ማሳ ለ10 ቀናት በፀሐይ ከደረቀ በኋላ ሁለተኛው የእርሻ ሥራ ይከናወናል፡፡ ሦስተኛው የእርሻ ሥራ የሚከናወነው ዘሩ በሚዘራበት ወቅት ይሆናል፡፡ እንደየአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ በበሬ፣ በፈረስ እና በግመል እንዲሁም በአነስተኛ ትራክተር በሚሳብ የመሬት ማስተካከያ መሣሪያ ማሳውን በማስተካከል ሰብሉ የተመጣጠነ የውሃ ስርጭት እንዲያገኝ ይረዳል፡፡

ሰፋፊ መሬት ባላቸው አካባቢዎች

ሰፋፊ የእርሻ ማሳዎች ባለባቸው ቆላማ አካባቢዎች የእርሻ ሥራው የሚከናወነው በትራክተር በመሆኑ ቀድመው የተዘሩ ሰብሎች ከማሳው ላይ ከተሰበሰቡ በኋላ ማሳው ለ15 ቀናት በፀሐይ ብርሃን እንዲደርቅ ይደረጋል፡፡ በመቀጠል በሞልድ ቦርድ ወይም ገልባጭ ማረሻ ይታረሳል፡፡ ከዚያም የታረሰው ማሳ ከ5-10 ባሉት ቀናት ውስጥ በትራክተር በሚጎተት የመከስከሻ መሣሪያ ተከስክሶ በመሬት ማስተካከያ መሣሪያ መስተካከል ይኖርበታል፡፡

የማሳ ድልደላ/ማስተካከል /Land leveling/

በመስኖ ለሚለማ የስንዴ ሰብል የሚዘጋጀው ማሳ በሚገባ የለሰለሰና የተደላደለ ወይም የተስተካከለ/levelled/ መሆን ይኖርበታል፡፡ በትልም (Furrow) ለሚለማ የስንዴ ሰብል ዘር ከመዘራቱ በፊት የእርሻ ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ የማሳ ማስተካከሉ (Land leveling) ሥራ በአግባቡ መከናወን አለበት፡፡ ይህም ሰብሉ የተስተካከለ የውኃ መጠን ስርጭት እንዲያገኝ ይረዳዋል፡፡ የማሳ ማስተካከሉ ስራ በደንብ ያልተከናወነና ወጣገባ ከሆነ የመሰኖ ውሃ ስርጭቱ በአግባቡ በሚፈለገው ቦታ አይደርስም፡፡ ለምሳሌ በዝቅተኛ ቦታዎች ላይ ውሃ ስለሚከማች ለሰብሉ ዕድገት ተስማሚ ሁኔታ አይፈጥርም፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከፍተኛና ወጣገባ የሆኑት ቦታዎች ውሃ በደንብ ስለማያገኙ ለሰብሉ የሚፈለገውን የውሃ መጠን እንዳያገኝ ከማድረጉ ባሻገር የመስኖ ውሃ ስርጭቱን ይገታዋል፡፡ ስለሆነም የመስኖ እርሻ ሲታሰብ ከምንጣሮ ቀጥሎ ሁለተኛው ተግባር የመሬት ማስተካከል ሥራ ይሆናል፡፡ የመሬት ማስተካከል ሥራ (Land leveling) የሚከናወነው በትራክተር ላይ በሚገጠም የመሬት ማስተካከያ ተቀጣይ መሣሪያ (Land leveler) ነው፡፡

የቅየሳ ሥራ

ለስንዴ ሰብል አገልግሎት የሚውለው መሬት በጥንቃቄ ከተመረጠ በኋላ ትክክለኛ የመስኖ ውሃ ስርጭት እንዲኖር በተገቢው መንገድ ማረስ፣ መከስከሰና መሬቱን ማስተካከል ስራ መከናወን አለበት፡፡ ከመሬቱ አቀማምጥና ተዳፋትነት ጋር በማገናዘብ የመጀመሪያ ደረጃና ዋናው የውሃ ማሰራጫ ቦይ (Primary canal) የአፈር መሸርሸር እንዳይፈጠር አግድመቱን ጠብቆ ወደ ማሳው እንዲገባ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ከዋናው የውሃ ማሰራጫ ቦይ ተቀብሎ ወደ ማሳው ሰብሉን ለማጠጣት የሚሰሩ ቦዮች (secondary canal) የአፈሩን ዓይነትና የመሬቱን ተዳፋትነት ግምት ውስጥ በማስገባት የቦዩን ተዳፋትነትና ርዝመት መወሰን እና ስራውን ማከናወን ይቻላል፡፡ የመስኖ ቦዩ መጨረሻ አካባቢ ደግሞ ትርፍ ውሃን ከመስኖ ቦይ ተቀብሎ የሚያንጣፍፍ ቦይ ያስፈልጋል፡፡

የዘር ወቅት

በመስኖ የሚለሙ ቆላማ አካባቢዎች፡- በቆላማ አካባቢዎች የስንዴ የዘር ወቅት የሚወሰነው በሙቀት መጠን ነው፡፡ እንደሚታወቀው በምስራቅ ሰሜን የሀገራችን አካባቢዎች የሚገኙት ዝቅተኛ ቦታዎች አንፃራዊ የቅዝቃዜ ወቅታቸው ከጥቅምት እስከ የካቲት ወር መጨረሻ ያለው ጊዜ ነው፡፡

ስለሆነም ስንዴ በተፈጥሮው ቅዝቃዜ የሚወድ ሰብል በመሆኑ በእነዚህ አካባቢዎች ከጥቅምት ወር መጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ እስከ ህዳር ወር መጨረሻ ድረስ ያለው ጊዜ ትክክለኛው የስንዴ የዘር ወቅት ነው፡፡ ምክንያቱም በእነዚህ ወራት ውስጥ ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች አማካይ የሙቀት መጠን ከ24-27 ዲግሪ ሰልሽየስ በመሆኑ ከፍተኛ የስንዴ ምርት ማግኘት ይቻላል፡፡ ከዚህ የግዜ ገደብ ውጭ የስንዴ ሰብል የሚዘራ ከሆነ የምርት መጠኑም ሆነ የዘር ጥራቱ በከፍተኛ ደረጃ በሙቀት ሊጎዳ ይችላል፡፡
በመስኖ ለሚለሙ ወይናደጋ አካባቢዎች፡- በወይናደጋና አካባቢዎች የሙቀቱ መጠን አነስተኛ በመሆኑ በበጋው ወቅት ስንዴን በመስኖ ማልማት ይቻላል፡፡