Veronica Melaku

@veronicateleg


ይህ የቴሌግራም ቻናል ነሐሴ 18/2013 ተከፈተ!

Veronica Melaku

18 Oct, 18:55


እምቢ በል!

የአማራ ህዝብ ጥቃት የሚያንገበግብህ ከሆነ፣ የአማራ ህዝብ የሕልውና አደጋ እንዲቀለበስና ህዝባችን ነፃነቱን አረጋግጦ በሰላም እንዲኖር ቁርጠኛ እምነት ያለህ ከሆነ “እምቢ!” ማለት ያለበህ ጉዳዮች አሉ፡፡

1/ ቅርጫት ውስጥ እንድትገባ የሚፈልጉ ብዙ አካላት ስላሉ እምቢ በል፡፡ አንዱን ታጋይ ደግፈህ ሌላውን እንድትቃወም፣ አንዱን ቡድን ደግፈህ ሌላውን እንድትቃወም፣ የአንዱ ጎራ አባል እንድትሆን የሚፈልጉ አሉ፡፡ በዚህና በዚያ ሆነው ይወጉሃል፡፡ ያዋክቡሃል፡፡ እንዲህ ነህ፣ እንዲያ ነህ ይሉሃል፡፡ የእከሌ ደጋፊ ነህ፣ የእከሌ ተቃዋሚ ነህ ይሉሃል፡፡ ከአንተ የሚጠበቀው እምቢ ማለት ነው፡፡ ቅርጫት ውስጥ አለመግባት ነው፡፡ ሁልጊዜም ወገናዊነትክን ከአማራ ህዝብ ጋር ብቻ ማድረግ ነው፡፡ አማራ ክልል የሚገኘው ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያ የተሰራጨውና በውጭም የሚኖረው አማራ ሁሉ ወገንህ ነውና በእኩል መንፈስ እየው፡፡ ቀጭኗን መንገድ መራመድ ይገባሃል፡፡ በሂደት መንገዷ ትሰፋለች፡፡ ትግል ያሳፋታል፡፡ ብዙ ልባሞች መምጣታቸው አይቀርምና፡፡

2/ ብሄርተኝነትን ከዘረኝነት ጋር እያያዙ የሚያጣጥሉ ሰዎች ይገጥሙሃል፡፡ ብሄርተኝነትን ካለመዘመን ጋር እያያዙ የሚተነትኑ ያልገባቸው ሰዎች ይገጥሙሃል፡፡ “አማራ ብሄርተኛ ሊሆን አይችልም፣ የአካባቢ ማንነቶች ጠንካራ ናቸው፣ የአማራ ብሄርተኝነት አይነሳም” ወዘተ ወዘተ ይሉሃል፡፡ እንዲህ የሚሉህ ስለ ብሄርተኝነት አንድም መጽሃፍ አንብበው የማያውቁ ናቸው፡፡ አንተ ግን ብሄርተኝነት የከተማ/ዘመናዊት ክስተት መሆኑን እወቅ፡፡ በጎሳ ያልተደራጀ በመሆኑ እንደ አማራ ለብሄርተኝነት የተመቸ ህዝብ እንደሌለ ይግባህ፡፡ ዛሬ የሰልጣኔ ጣሪያ ላይ የደረሱት ከእንግሊዝ እስከ ጃፓን፣ ከአሜሪካ እስከ ጀርመን ሁሉም ብሄርተኞች መሆናቸውን እወቅ፡፡ ስለሆነም የአማራ አባቶች ስህተት ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ማለታቸው እንዳልሆነ፣ ስህተታቸው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚሉት አማራነታቸውን ጥለው እንደሆነና ስህተቱም እሱን እንደሆነ ይግባህ፡፡ ብሄርተኝነት መቼም የማይሸነፍ መሆኑንም በደንብ ማወቅ ይገባሃል፡፡ በአንደኛው ትውልድ ድክመት ድሉ ሊዘገይ ይችል ይሆናል እንጅ ብሄርተኝነት አይሸነፍም፡፡ ደካማው ትውልድ ለልጆቹ የቤት ስራ ሲያስቀምጥ ልባሙ ትውልድ ግን ነፃነትን ያወርሳቸዋል፡፡

3/ የአማራ ብሄርተኝነት ዣንጥላ መዋቅር መሆኑን አጥብቀህ ያዝ፡፡ ሌሎች የፖለቲካ፣ ወታደራዊ፣ የሲቪክ፣ የሚዲያ ወዘተ ድርጅቶች በብሄርተኝነቱ ስር ያሉ እንጅ ብሄርተኝነቱን የሚተኩ አለመሆናቸውን ጠንቅቀህ እወቅ፡፡ አንድ የአማራ ድርጅት ሊዳከም ይችላል፡፡ ሊፈርስም ይችላል፡፡ ያ ድርጅት ተዳከመ ወይም ፈረሰ ማለት ግን የአማራ ብሄርተኝነት አለቀለት ማለት እንዳልሆነ ይግባህ፡፡

4/ የአማራ ብሄርተኝነትን ከሃይማኖት ጋር አታቀላቅል፡፡ ሁሉም የየራሱ ቦታ አለው፡፡ የራስክን ሃይማኖት ያዝ፡፡ ነገር ግን መታገል ያለብህ ለሁሉም ሃይማኖቶች እኩልነት መሆን ይገባዋል፡፡

5/ በተሸነፈ ማህበረሰብ ውስጥ አሸናፊ ግለሰብ ሊኖር እንደማይችል ተረዳ፡፡ ችግር ውስጥ ካለ ማህበረሰብ ወጥተህ ተመችቶህና የሕሊና እረፍት አግኝተህ ልትኖር እንደማትችል ይግባህ። ስለሆነም ሁልጊዜም የህዝብህ ጉዳይ እንቅልፍ ይንሳህ፡፡ በሚገነባ እንጅ በአፍራሽ ተግባር ላይ አትገኝ፡፡ የተግባር ሰው ሁን! የስራ ሰው ሁኚ!!!

የአማራ ብሄርተኝነት ይለምልም!!!

Veronica Melaku

18 Oct, 07:03


ከአንድነት ሃይሉ ጋር መስራት ይቻላል?

ከአንድነት ሃይሉ ጋር መስራት ይቻላል? መልሱ "ይቻላል ብቻ ሳይሆን መቻልም አለበት" የሚል ነው፡፡ ወሳኙ ጥያቄ "በምን አግባብ?" የሚለው ነው፡፡ መልሱ “አማራነታችን ይዘን!” የሚል ነው፡፡ እንደከዚህ ቀደሙ ማንነታችን ጥለን ሊሆን አይችልም፡፡ አማራነትን በሁለተኛ ደረጃ አስቀምጠን ሊሆን አይችልም፡፡ ይህን ወሳኝ መርህ እስከያዝን ድረስ በሚያግባቡን ጉዳዮች ላይ ለኢትዮጵያ አንድነት ከሚታገሉ ወገኖች ጋር መስራት ይቻላል፡፡ ይገባልም፡፡ ከአንድነቱ ጎራ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ብሄረሰቦች ሃቀኛ ታጋዮች ጋርም መስራት ይቻላል፡፡ ይገባልም፡፡ አቋማችንን ይዘን፡፡ ጥቅማችን አሳልፈን ሳንሰጥ!

ጨፍጫፊው ቡድን ራሱን ለማጠናከር ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ አጋሮችን ይፈልጋል፡፡ ሃይል ለማሰባሰብ ይታትራል፡፡ እኛም ከጨፍጫፊው ቡድን በላይ መስራት ይጠበቅብናል፡፡

ከሌሎች ሃይሎች ጋር በሚያግባቡን የጋራ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት ግን መጀመሪያ እኛው ራሳችን እንደ ብረት የጠነከረ አንድነትና ህብረት ሊኖረን ይገባል፡፡ ከሌሎች ጋር መስራት የሚገባን “በእነዚህ፣ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ነው” ብሎ ለመነጋገር መጀመሪያ የራስን ጎራ እውነትም “አንድ ጎራ” ማደረግ ያስፈልጋል፡፡ ሰንበሌጥ ሌሎችን ልደገፍ ይላል እንጅ የሚደገፈው የለም፡፡ ዋርካ መሆን ያስፈልጋል!

በትንሽ ፖለቲካ መርመጥመጡን ትተን ሁልጊዜም አማራን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ እናተኩር፡፡ ሁልጊዜም ህብረታችን በሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ እንሰማራ፡፡ ሌሎችን መግፋት መገፋትን ያስከትላል፡፡ መጠቃቃትን ያመጣል፡፡ የጋራ ውድቀትን ይጋብዛል፡፡ በሚገነባ ተግባር ላይ ብቻ እናተኩር!

ለድል እንታገል!

የአማራ ብሄርተኝነት ይለምልም!!!

Veronica Melaku

18 Oct, 03:50


ዳንኤል ብርሃኔ እና እኔ

ዳንኤል ብርሃኔ ወንበርተኛዬ (batch) ነው፡፡ ሃሳባችን ባይገጥምም ከመወያየትና ከመከራከር ተቆጥበን አናውቅም ነበር፡፡ መቼም አምባገነኖች የራሳቸውን ቅዠት ካመኑ አደገኛ እንደሚሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ዳኒ የዚህ በሽታ ሰለባ ነበር፡፡ ወያኔ እስከ 100 አመት ሊገዛ ይችላል ብለው ከሚያምኑት ወገን ነበር፡፡ በረከት ስምኦን ከዚያ አነስ በማድረግ ቢያንስ 60 አመት ይል ነበር፡፡

ባህር ዳር ላይ ወጣቶች በኢህአዴግ አልሞ ተኳሾች የተገደሉ ሰሞን ነው፡፡ ዳኒ ሚካኤል በሚገኘው ታፍ ህንጻ እልል ያለ ስቱዲዮ ግንብቶ “ሆርን አፌዬርስ” የተሰኘ ሚዲያ ጀምሮ አለሁ አለሁ ማለት ጀምሮ ነበር፡፡ የጫት ቅንጣቢውን በኪሱ ይዞ ቡናውን ማግ እያደረገ ያወራኛል፡፡ “ምን ይታይሃል? እስኪ አስተያየትክን እንስማው” ይለኛል፡፡ “ስርአቱ አልቆለታል፡፡ በተለይ አማራ አምርሯል፡፡ ሃቁ ባይዋጥላችሁም ከዚህ በኋላ ኢህአዴግ ተመልሶ አማራን በሃይል ማስገበር የሚችል አይመስለኝም” ወዘተ ወዘተ እለዋለሁ፡፡ ከት ከት ብሎ ይስቃል፡፡ የተለመደ ነው፡፡ አማራው ተመቷል፣ አይነሳም ብለው ነው የሚያምኑት፡፡ “ህወሃትን አታውቀውም፡፡ ለነገሩ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ትምህርት እኮ በፖለቲካና በህግ ዙሪያ አትድረስ የተባለ ነው የሚመስለው” እያለ የፖለቲካ ትንታኔ አቅሜን ያጣጥላል፡፡ ይቀጥልና “ክፉዎች ናቸው፡፡ ተቀጣቅጠው አፈር ቅመው ይነሳሉ እንጅ ይወድቃሉ ብለህ እንዳታስብ፡፡ ደግሞ አደራህን እየወደቁ ነው ብለህ ከማይሆኑ ሰዎች ጋር እንዳትነካካ” ይለኛል፡፡ ምክርም ማስፈራሪያም ነው፡፡ እኔም በሃሳቤ አጠንክሬ አልገፋበትም፡፡

መጨረሻ ላይ የሆነውን ሁላችንም ስለምናውቀው አንሄድበትም፡፡ ወዳጄ ዳኒም ያን የመሰለ በአቶ ተክለብርሃን አምባዬ ህንጻ ላይ የተሰራ የተንጣለለ ስቱዲዮ ሳይጠቀምበት መቀሌ ከተመ፡፡ የቀረው ታሪክ ነው፡፡

አምባገነኖች ህዝብን ዋጋ የሚያስከፍሉት የራሳቸውን ቅዠት ስለሚያምኑ ነው፡፡ ጋዳፊ “አረንጓዴው መጽሃፍ” የሚባል መጽሃፍ ነበረው፡፡ ነገርዬው ከማኦ “ቀዩ መጽሃፍ” መኮረጁ ነው፡፡ ታዲያ ጋዳፊ የፈጠረውን ቅዠት በማመን ራሱን ማሻሻል ባለመቻሉ መጨረሻ ላይ የገጠመውን የምናውቀው ነው፡፡ መንግስቱ ሃይለማርያምም “ተው የአለም ሁኔታ ተቀይሯል፣ ሶሻሊዝምም አደጋ ላይ ነው” እየተባለ በራሳቸው በነ ጎርቫቼቭ ጭምር ሲነገረው ጭራሽ እነሱን “ከላሽ! በራዥ!” እያለ የሶሻሊዝም ታማኝ ነኝ ብሎ ክችች አለ፡፡ መጨረሻ ላይ የገጠመውን እናውቀዋለን፡፡ የወያኔ አምባገነኖች ሁኔታም ተመሳሳይ ነው፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚባለውን ንድፈ ሃሳብ እያነበነቡ ከእሱ ውጪ ፍቱን መድሃኒት የለም አሉ፡፡ ራሳቸውን መለውጥ ተሳናቸው፡፡ መጨረሻቸው አላማረም፡፡ ሀገርንም ጨምረው ዋጋ አስከፈሉ፡፡

የዛሬዎቹም የራሳቸውን ቅዠት አምነው እያዛጉን ይገኛሉ፡፡ ፍቱን መድሃኒቱ እኛ የጻፍነው ነው እያሉ ነው፡፡ ትልቁ አደጋ ይህን የፈጠሩትን ቅዠት እንደ ፍቱን መድሃኒት ማመናቸው ነው፡፡ ስለዚህም እነሱ የያዙትን ሃሳብ የሚቃወመው በሙሉ ጠላት ነው፡፡ መታሰር አለበት፡፡ መሳደድ አለበት፡፡ መጥፋት አለበት፡፡ ዛሬም እንዲህ አይነት በራሳቸው ቅዠት የሰከሩ ገዥዎች አሉ፡፡ ዛሬም በገዥዎች ቅዠት የሰከሩ እና ልክ እንደ ዳንኤል በእውነት ላይ የሚሳለቁ ጭፋራዎች አሉ፡፡

ታዲያ መፍትሄው ምንድን ነው? መፍትሄው ትግል ብቻ ነው፡፡ ወያኔዎች ከነቡትቶ ሃሳባቸው እንደወደቁት፣ ሌሎችም አምባገነኖች እንደተንኮታኮቱት እነዚህም በትግል ይሸነፋሉ፡፡ በፅኑ ትግል የማይሸነፍ አምባገነን የለም!

ለድል እንታገል!

የአማራ ብሄርተኝነት ይለምልም!!!!

Veronica Melaku

17 Oct, 16:10


የሚያኮራ እና መጠናከር ያለበት ጅምር!

የአማራ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ትዊተር (X) ላይ የጀመሩት እንቅስቃሴ በጣም የሚያኮራና ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው፡፡ ሁሉንም የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች በሚገባ አሟጠን በመጠቀም ለህዝባችን ድምጽ መሆን መቻል አለብን፡፡ በተለይ ትዊተር ላይ የሚካሄዱት ዘመቻዎች የጊዜ ሰሌዳ ወጥቶላቸው መልእክቶች በደንብ እየተቀረፁ ሳይቋረጡ መቀጠል ይገባቸዋል፡፡ ያለ ጥርጥር ተስፋ ሳንቆርጥ የምንሰራ ከሆነ ድምጻችን ሰሚ ያገኛል፡፡

ስለሆነም በተለይ ትዊተር ላይ የሚከሄዱት ዘመቻዎች በተቀናጀና በጥሩ ጥሩ ግራፊክሶችና መልእክቶች በታጀበ መልኩ እንዲቀጥሉ ዘመቻውን የጀመሩትን እህቶችና ወንድሞች ማበረታታት ይገባል፡፡
ውጤት እስክናመጣ እንታገል!

ያዝ ለቀቅ አያስፈልግም!
ፅናት!!!

የአማራ ብሄርተኝነት ይለምልም!!!

Veronica Melaku

17 Oct, 12:19


አማራ ከዲሞክራሲ የሚያጣው ምንም ነገር የለም!

የአማራ ህዝብ ከዲሞክራሲ የሚያገኘው እንጅ የሚያጣው አንዳች ነገር የለም፡፡ ግንባር ቀደም ቁጥር ያለው ህዝብ ዲሞክራሲን ሊፈራ አይችልም፡፡ አይፈራምም፡፡ ዲሞክራሲን መርሃችን ማድረግ ያለብን ግን ብዙ ቁጥር ስላለን አይደለም። ዲሞክራሲ ለሕልውና ትግሉ ቁልፍ ስለሆነ ነው።

ስለ ዲሞክራሲ ሲነሳ አንዳንድ ሰዎች “አሁን ስለ ዲሞክራሲ የምናወራበት ጊዜ አይደለም፣ መጀመሪያ ሕልውናችን እናረጋግጥ፣ ሕልውናችን ሳይረጋገጥ ስለ ዲሞክራሲ ማሰብ ቅንጦት ነው” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ትልቁ ስህተት ይህ ነው፡፡ ምናልባት እንዲህ አይነት አስተያየት የሚሰጡት ዲሞክራሲን ከልቅ ህግ አልባነት ጋር እያያዙት ይመስላል፡፡

ዲሞክራሲን ግን ያለ ህግ ማሰብ አይቻልም፡፡ ያለ ስርአት የሚታሰብ ዲሞክራሲ የለም፡፡ ዲሞክራሲ ለአማራ ሕልውናውን ካረጋገጠ በኋላ እውን የሚያደርገው ጉዳይ ሳይሆን ራሱን ሕልናውን እውን ለማድረግ የሚጠቅመው መሣሪያ ነው፡፡ የምናቋቋማቸው ተቋማት/ድርጅቶች ጠንካራና ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉት በዲሞክራሲያዊ አግባብ ሲቋቋሙና ሲመሩ ነው፡፡ ውሳኔዎች ከተቻለ በሙሉ ስምምነት፣ ካልሆነ በድምፅ ብልጫ መወሰን አለባቸው፡፡ የብዙሃኑ ውሳኔ ተግባራዊ ይሆናል፣ አነስተኛ ቁጥር ያገኙት (የአናሳው ወገን) መብት የከበራል፡፡ እንዲህ አይነቱ አሰራር በትጥቅ ትግል ውስጥ ላሉት ሃይሎችም ሆነ በሲቪል ተቋማት ዘንድ ወሳኝ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የአማራ ተቋማት ዲሞክራሲዊ መሆን በሌሎች ብሄረሰቦችና በአለም አቀፉ ማህበረሰም ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን የሚያስገኝ ትልቅ ጸጋ ነው፡፡ እንዲህ ሲሆን ነው የአማራው ሃይል ገና ወደ ስልጣን ሳይመጣ የሞራልና የሃሳብ መሪነት (moral and intellectual leadership/hegemony) የሚኖረው፡፡ በመጡልን መባል ትልቅ ነገር ነው፡፡ እነሱ ስልጣን ቢይዙ በጎ ለውጥ ይመጣል መባል ትልቅ ፀጋ ነው፡፡

የአማራ ብሄርተኝነት ይለምልም!!!

Veronica Melaku

16 Oct, 17:40


ድሮን እና ትግላችን!

ፋሽስታዊው ቡድን የፋኖን ውጊያ መቋቋም አልቻለም፡፡ ከሶስት ቀናት ወደ ሶስት ወራት፣ ከሶስት ወራት ወደ ስድስት ወር እያስረዘሙ አርበኛነቱን ለማሸነፍ ባለ በሌለ አቅማቸው ዘመቱ፡፡ ሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አወጁ፡፡ በመላው ኢትዮጵያ ያሉ አማራዎችን ማሰር፣ መዝረፍና ማሸማቀቅ ስራቸው ሆነ፡፡ ይህ ሁሉ ተደርጎም ፋኖን ማሸነፍ አልተቻለም፡፡ ማሸነፍም ፈፅሞ አይቻልም፡፡ የፋኖ ትግል የመላው አማራ ትግል ነውና፡፡ ትግላችን የእውነትና የፍትህ ነውና፡፡

ያሰበው ያልተሳካለት ፋሽስታዊ ቡድን የድሮን ጭፍጨፋው ቀጥሎበታል፡፡ ንጹሃንን እየጨፈጨፈ ነው፡፡ የአማራን መሰረተ ልማት እያወደመ ነው፡፡ አላማው አማራን ማደህየት ነው፡፡ አማራን ማንበርከክ ነው፡፡ አላማው አማራን መበቀል ነው፡፡

ጠላት ጠላት ነውና ስራውን እየሰራ ነው፡፡ የእኛን ትግል የሚጠቅም ስራ የሚጠበቀው ከእኛው ከራሳችን ነው፡፡ ልብ እንበል፤ አንድ ችግር በአንድ ምክንያት እንደማይመጣው ሁሉ መፍትሄውም አንድ አይደለም፡፡ ስለሆነም የተለያዩና ተመጋጋቢ ስትራቴጂዎችን ነድፈን መንቀሳቀስ ይገባናል፡-

1/ የቴክኖሎጂና የኢንጅነሪንግ ምሩቃንና ባለሙያዎች ትግሉን እንዲቀላቀሉ ሰፊ ስራ እንስራ፡፡ በፀረ ድሮን ረገድ ከፍተኛ የሆነ ስራ መስራት ይጠበቅብናል፡፡ ሌሎች የነፃነት ታጋዮች እንዴት እንዲህ አይነቱን ጥቃት መቋቋም እንደቻሉ ልምድ እንቅሰም፡፡ ጊዜውና ሁኔታው የሚጠይቀውን የቴክኖሎጂ አቅም እንገንባ፡፡

2/ አላስፈላጊ መሰባሰብን እናስወግድ፡፡ በተለይ ከሞባይል ስልክ ጋር የተያያዘ ሁኔታችን መልክ መያዝ ያለበት ነው፡፡ “ሳይደግስ አይጣላም” ነውና ይህ ፈተና አርበኛውን ከስልክ የሚያላቅቀው ይሆናል፡፡ መላቀቅም ይገባዋል፡፡ የመገናኛ ሬዲዮ መያዝ የሚገባቸው በስርአት ተለይተውና የእነሱ ደህንነት ተጠብቆ ሌላው ታጋይ ከስልክ መላቀቅ ይገባዋል፡፡ ስልክ በመያዙ የሚያጣው እንጅ የሚያገኘው ነገር የለም፡፡

3/ እንደተሳካላቸው ሌሎች የሽምቅ ተዋጊ ድርጅቶች እኛም ጠላት በማይችለው ሁኔታና ጊዜ እንንቀሳቀስ፡፡ ብዙዎቹ የሽምቅ ተዋጊ ድርጅቶች በማታ፣ በክረምት እና ጠላት በማያስበው ጊዜና ሁኔታ የሚያጠቁት ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል ጭምር ነው፡፡ ይህን እውነታ ሃቅ የፋኖ አርበኞቻችን ያጡታል ብለን አናምንም፡፡ ለማስታወስ ያክል ብቻ ነው፡፡

4/ በዲያስፖራ ያሉ አማራዎች የፋሽቱን በድሮን የታገዘ ጭፍጨፋ ሳንሰላች ሁልጊዜም በሰልፍና በሌላውም የተቃውሞ መንገድ ጠላትን የማጋለጥ ስራ መስራት ይገባቸዋል፡፡ የአብይን በደም የጨቀዬ ማንነት በአለም አደባባይ እናጋልጠው፡፡ ተስፋ ሳንቆርጥ ሁልጊዜም ለውጥ እስከምናመጣ እንታገል፡፡ በዚህ ረገድ የትግራይ ዲያስፖራ የሰራውን ተአምራዊ ስራ ማስታወስ ይገባል፡፡

5/ ማህበራዊ ሚዲያውን (በተለይም ትዊተር ወዘተ) በድንብ በመጠቀም የፋሽስቱን ቡድን ገፅታ እርቃኑን እናስቀረው፡፡ ሁልጊዜም የተቀናጀ ዘመቻ እናካሂድ፡፡ ይህን ዘመቻ በተለይ ጋዜጠኞች በደንብ ሊመሩት ይችላሉ፡፡ ይገባልም፡፡

እነዚህንና ሌሎችንም የተቀናጁ ስትራቴጂዎች ተመጋጋቢ በሆነ መንገድ በመተግበር አገዛዙን እርቃኑን ማስቀረትና ባለድል መሆን ይገባናል፡፡ ይህን ጦርነት ማሸነፍ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው!

ጊዜው የስራ ነው!

የአማራ ብሄርተኝነት ይለምልም!!!

Veronica Melaku

16 Oct, 07:13


ብሄርተኝነት እና ፊውዳሊዝም ምንና ምን ናቸው?

ብሄርተኝነት የዘመናዊነት ውጤት ነው፡፡ ከከተሜነት፣ ከትምህርት መስፋፋት፣ ከማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እድገት ወዘተ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለሆነም ፊውዳላዊ አስተሳሰብና ብሄርተኝነት አብረው አይሄዱም፡፡

ፊውዳላዊ አስተሳሰብ እኩልነትን አይቀበልም፡፡ የማእረግ ጋጋታ ያበዛል፡፡ ጀኖሳይደሩን “ሙአዘ ጥበባት” ይለዋል፡፡ የሚሰይመው ነገር ቢያጣ “እጩ ዶክተር” የሚባል ማእረግ ይፈልጋል፡፡ ሶሻሊስቶች አባላትን በእኩልነት ስሜት ለማየት እንዲቻል ጓድ (comrade) ይባባላሉ፡፡ ከፊውዳላዊ አስተሳሰብ ያልፀዳውን ህብረተሰብ ግን ይህ ሊያሳምነው አልቻለም፡፡ ስለሆነም “ጓድ ሊቀመንበር”፣ “ጓድ ፕሬዚዳንት” ወዘተ እያለ ቅጽል በቅጽል አደረገው፡፡ ዛሬም “ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ምንትስ” እየተባለ ነው፡፡ ወደፊት የሚጨመር ሌላ ቅጽል እንደሚኖር ግልጽ ነው፡፡

እኛ እንደ ብሄርተኛ እንዲህ አይነቱን ርካሽ የማእረግ ጋጋታ ማስወገድ አለብን፡፡ የፋኖ አርበኞችም ቢሆኑ “አርበኛ” ከተባሉ በቂ ነው፡፡ ለነገሩማ ከአርበኛ ላይ የምን ቅጽል ማንጋጋት ያስፈልጋል? እሱ ራሱ ከበቂ በላይ አይደለምን?

ሌላው የፊውዳላዊ አስተሳሰብ በሽታ በግለሰብ ላይ መንጠልጠሉ ነው፡፡ አንድን ግለሰብ ሰማዬ ሰማያት ይሰቅላል፡፡ ያ ግለሰብ ከሌላ ሁሉም ነገር ያበቃለታል ይባላል፡፡ እንዲህ አይነት አስተሳሰብ የብሄርተኝነት ፀር ነው፡፡ ብሄርተኝነት ግን የአንድን ብሄር አባላት ድሃ/ሀብታም፣ አርሶ አደር/ከተሜ፣ የተማረ/ያልተማረ፣ ሴት/ወንድ፣ ክርስቲያን/ሙስሊም ወዘተ ሳይል በእኩል አይን የሚመለከት ነው፡፡ ሁሉም በየሚናው አስተዋፅኦ ካደረገ የማይጠቅም ሰው የለም ብሎ ያምናል፡፡ ሁሉም ይፈለጋል፤ ሁሉም ያስፈልጋል ይላል፡፡ ግለሰቦች ደግሞ የማህበረሰብ/የመዋቅር ውጤቶች መሆናቸውን በጽኑ ያምናል፡፡ ከታች እንደቀረበው ጽሁፍ!👇

"Community is the bond resulting from the process of common interactions whereby the characteristics and identity of the numbers is the result of the process of interaction. In this sense the individual national subject does not pre-exist the national community; he or she is constructed by it. The national identity and culture of each member of the nation is the result of his/her socialized existence.

For us, society is not a mere addition of individuals, but each individual is the product of society. In the same way, the nation is not a mere addition of individuals that interact through a common language. The individual himself is the product of the nation, his (her) individual character does not emerge in other forms but through his (her) interaction with other individuals." - Otto Bauer

የአማራ ብሄርተኝነት ይለምልም!!!

Veronica Melaku

16 Oct, 03:45


እናሸንፋለን? መቼ?

ሳንወድ ተገደን የገባንበትን የሕልውና ትግል በአሸናፊነት እንወጣዋለን ወይ? መልሱ “በእርግጠኝነት!” የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም ትግላችን የሕልውና ነውና ነው፡፡ ምክንያቱም ትግላችን የእውነትና የፍትህ ነውና ነው፡፡ ምክንያቱም ትግላችን ራስን ሆኖ ለመኖር የሚደረግ ትግል ነውና ነው፡፡ የራስን እድል በራስ ለመወሰን የመደረግ ክቡር ትግል ነውና ነው፡፡ ስለዚህ በትግላችን አሸናፊነት ላይ ብዥታ ሊኖረን አይገባም፡፡ በብዙ ሀገሮች ብሄርተኞች ትግል ውስጥ ሲገቡ “ትግሉ መራራ ነው፤ ድሉን እኛ ላናየው እንችላለን፤ ትግሉ አሸናፊ መሆኑ ግን እርግጥ ነው!” ይላሉ፡፡

ጥያቄው “መቼ ነው የምናሸነፈው?” የሚለው ነው፡፡ የዚህ መልስም ቀላል ነው፡፡ መልሱ “በታገልነው መጠን፣ በፈጠርነው እንደ ብረት የጠነከረ አንድነትና ህብረት መጠን፣ በገነባናቸው ተቋማት/ድርጅቶች እና በፈጠርነው ሃይል መጠን” የሚል ነው፡፡

ብሄርተኝነታችን ከዚህ ወይም ከዚያ ሃይማኖት ጋር ሳይጣበቅ፣ ከዚህ ወይም ከዚያ አካባቢ ሳይጣበቅ፣ ከዚህ ወይም ከዚያ ግለሰብ/ቦች ጋር ሳይጣበቅ ሁሉንም አማራ በምልኣት ይዞ ከተገነባ ድሉ ቅርብ ነው። ከሁሉም በላይ ትግሉ በብሄርተኝነት ርእዮት ከተመራ ድሉ በጣም ቅርብ ነው፡፡ ሁሉንም አማራ ያሳተፈ ነውና፡፡ የሎጅስቲክስ ችግር አይገጥመውና፡፡ የሰው ሃይል ሀብታም ይሆናልና፡፡

ስለዚህ የትግሉ አሸናፊነት የተረጋገጠ ቢሆንም፣ መቼ የሚለውን የሚወስነው በየእለቱ የምንሰራው ስራ ነው፡፡ ብሄርተኝነቱን በፅኑ መሰረት ላይ ከገነባነው ሁሉም ነገር የሰመረ ይሆናል፡፡ የብሄርተኝነት ትልቁ ፀጋው ሀብታም/ድሃ፣ ሴት/ወንድ፣ ሙስሊም/ክርስቲያን፣ የሀገር ቤት ነዋሪ/ዲያስፖራ ወዘተ ሳይባል ሁሉንም በእኩልነት የሚያሳትፍ መሆኑ ነው፡፡

በየእለቱ ብሄርተኝነቱን በሚጠቅምና በሚገነባ ተግባር ላይ እንሰማራ፡፡ እንንቃ፣ እናንቃ፣ እናደራጅ!

ለድል እንታገል!

የአማራ ብሄርተኝነት ይለምልም!!!

Veronica Melaku

15 Oct, 18:38



Veronica Melaku

15 Oct, 10:05


መንግስት ከወሰነ ምን ይደረጋል?

እንደ ህዝብ መንግስት የሚባለውን አካል የምናይበት መነፀር የተበላሸ ሆኖ ኖሯል፡፡ በመሰረቱ መንግስት ኖሮን አያውቅም፡፡ የነበሩንና አሁንም ያለው አገዛዞች ናቸው፡፡ ያልመረጥናቸው፣ በሃይል የተጫኑብን አገዛዞች፡፡ ስለሆነም አገዛዝ ከወሰነ ምን ይደረጋል ብሎ ነገር አይሰራም፡፡ አደገኛ የባርነት መንገድ ነው፡፡ እንኳን ያልመረጥነው አገዛዝ ይቅርና የመረጥነው መንግስትም ቢሆን የሚወስነውን ሁሉንም ነገር በፀጋ መቀበል አይኖርብንም።

የአማራ ብሄርተኝነት በአጭር ጊዜ መገርሰስ የጀመረው እንዲህ አይነቱን ለዘመናት ተጭኖን የኖረውን አመለካከት ነው፡፡ አገዛዝ የወሰነውን ማንኛውንም አይነት ህዝብን የማይጠቅም ስምምነትም ሆነ የሰየመውን ስያሜ አንቀበልም ብሎ አሽቅንጥሮ መጣል ጀመረ፡፡ ህዳር 11 እና ግንቦት 20 እየተባሉ የተሰየሙ የጠላት ስያሜዎችን ጠራርጎ መቀየርና ማስቀጠር ቻለ፡፡ ስማቸው እንዳይጠራ ተከልክለው የነበሩትን የእነ እምዬ ምኒልክን ስም በክብር ተቋም ሰየመላቸው፤ አሰየመላቸው፡፡ አገዛዙ ራሱ ባመነው መሰረት ሲገፋው የኖረውን የወልቃይት-ጠገዴ፣ ራያና የሌሎችንም አካባቢዎች ጉዳይ ቁልፍ አጀንዳ እንዲሆን አደረገው፡፡ ባህር ዳር ላይ አንገቱን ደፍቶ የቆመውን ወራዳ ሃውልት አስፈርሶና ስያሜውን ጭምር አስቀይሮ በሌላ ሃውልት አስተካው፡፡ ሌላም ሌላም ብዙ ነገር ተደርጓል፡፡ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ይህ ሁሉ በችሮታ የሆነ ነገር አይደለም፡፡ የትግል ውጤት ነው! የመስዋእትነት ውጤት ነው!

ከሁሉም በላይ ደግሞ የአብይ ፋሽስታዊ አገዛዝ አማራን ትጥቅ ለማስፈታት ሲመጣና ምስለኔዎቹ “መንግስት ከወሰነ ምን ይደረጋል?” ብለው የጠላትን አላማ ለማስፈፀም ሽር ጉድ ሲሉ ጀግኖቹ የፋኖ አርበኞች “እምቢ!” ብለው ታሪክ ሰርተዋል፡፡ ዛሬም ታሪክ እየሰሩ ነው፡፡ አገዛዝ መንግስት አይደለም፡፡ ከህዝብ የተረከበረው አንዳችም አደራ ወይም ስልጣን የለውም፡፡ ስለሆነም በዚህ አገዛዝ የሚወሰን የትኛውም ውሳኔ አይገዛንም፤ አንገዛበትም፡፡ በዚህ አገዛዝ የሚካሄድ የትኛውም ህዝበ-ውሳኔም ይባል ሌላ ስምምነት አይገዛንም፡፡

ዛሬም አንዳንድ የእኛው ወገኖች “መንግስት ከወሰነ እንግዲህ ምን ይደረጋል? ምንም ቢሆን መንግስት መሃሪ ነው፡፡ መንግስት አባት ነው፡፡ መንግስት ከሌለበት ሀገር ደካማም ቢሆን መንግስት ይሻላል” ወዘተ ወዘተ እያሉ የባርነት ስብከት ሲሰብኩ ይሰማሉ፡፡ በፋሽስት ጣልያን ጊዜ አርበኞችን ለፋሽስት ለማስገበር በሃይማኖት አባትነትና በሽምግሌነት ሲላላኩ እንደነበሩት ተላላከዎች መሆናቸው ነው፡፡
መንግስት የለንም፡፡ አንዱ የትግላችን አላማም ይኸው ነው፡፡ የራሳችን የመረጥነው መንግስት እንዲኖረን ማደረግ፡፡ የራሳችን እድል በራሳችን መወሰን፡፡

ያልመረጥነው ሃይል ሊወስንልንም ሊወስንብንም አይችልም፡፡ "መንግስት ከወሰነ ምን ይደረጋል?" ብሎ ነገር አይሰራም። በተለይ “አገዛዝ ከወሰነ ምን ይደረጋል?” ብሎ ነገርማ የሞት ሞት ነው፡፡ አገዛዝ ከወሰነብንማ የምናደርገው ግልፅ ነው፦ እምቢ! አሁን እያደረግን እንዳለነው!

የአማራ ብሄርተኝነት ይለምልም!!!

Veronica Melaku

15 Oct, 06:07


ጥርትና ኩልል እያለ ይመጣል!

ስለ ብሄርተኝነት ያነበበና የገባው ሰው ቀስቃሽ አያስፈልገውም፡፡ ሁልጊዜም ስለ ህዝቡ ሰላምና ደህንነት፣ ሁልጊዜም ስለ ህዝቡ ነጻነት፣ ህልውናና ክብር ይጨነቃል፡፡ መፍትሄ ይፈልጋል፡፡ ከመሰሎቹ ጋር ይወያያል፡፡ ይደራጃል፡፡ ያደራጃል፡፡ ህዝቡን በሚጠቅሙ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ይሰማራል፡፡ አንዱ መንገድ ባይሳካ ሌላ መንገድ ይቀይሳል እንጅ ፈፅሞ ተስፋ አይቆርጥም፡፡ አይቷቸው ለማያውቀው ግን ደግሞ ወገኔ ለሚላቸው የብሄሩ አባላት ሁሉ ያስባል፡፡ ለዚያ ህዝብ ህልውናና ክብር ይጨነቃል፡፡ የወገኖቹ በደል እንቅልፍ ይነሳዋል፡፡ ስኬታቸውና ደስታቸው ያስፈነድቀዋል፡፡ በተቋማት መስረታና ግንባታ ውስጥ ንቁ ተዋናይ ይሆናል፡፡ የግድ እኔ ካልመራሁት ብሎ የሚመሰረተውን ተቋም በሚያውክ ተግባር ላይ አይሰማራም፡፡ ይልቁንም ስልጣንና ማእረግ ሳይኖረው በምግባሩ መሪ ሆኖ የትግሉ ተዋናይ ይሆናል፡፡

የእንዲህ አይነት ብሄርተኞች ቁጥር እየበረከተ ሲሄድ ነው ያ ህዝብ ነፃነቱ የተረጋገጠ የሚሆነው፡፡ በሁሉም የተሳካላቸው ብሄርተኝነቶች ውስጥ እንዲህ አይነት ሁለመናቸውን ለህዝባቸው የሰጡ (selfless) ሰዎች አሉ፡፡ እነዚያ ጀግኖች ናቸው የዚያ ብሄርተኝነት መስራች አባቶች የሚባሉት፤ አብሪ ከዋክብት የሚባሉት፡፡

አንድ ጊዜ በፖለቲካ የተነደፈ ሰው ከፖለቲካ ለመውጣት ይከብደዋል፡፡ አንድ ጊዜ ብሄርተኛ የሆነ ሰው ደግሞ ከዚያ በላይ ነው፡፡ ሳይፈልግ ራሱን የሆነ ቦታ ውስጥ ያገኘዋል፡፡ ካልተሳተፈ እረፍት አያገኝም፡፡ ልሸሸው ቢልም የወገኖቹ መጠቃት ያቃጭልበታል፡፡ ስለዚህም ያለ ቀስቃሽ በሚችለው መንገድ ሁሉ አስተዋፅኦ ለማድረግ ይታትራል፡፡

በአማራ ትግል ውስጥ አሁን የምናየው ተነፋራ ነገር የብሄርተኛው ቁጥር ከማነሱ የመነጨ ነው፡፡ ብሄርተኝነቱን በየእለቱ እየከተኮትን ስናሳድገው ትግላችን ጥርትና ኩልል እያለ ይመጣል፡፡ ድላችን ይቀርባል፡፡ የተቋማት ባለሀብቶች እንሆናለን፡፡ በሁሉም መስክ አማራ ጀግና ተሟጋቾችን ያገኛል፡፡ ስለሆነም ሀልጊዜም የአማራ ብሄርተኝነትን ማጠናከር ይገባናል፡፡

የአማራ ብሄርተኝነት ይለምልም!!!

Veronica Melaku

14 Oct, 12:37


እርግማን የለብንም!

ለሁሉም ነገር ባህልን ተጠያቂ የማድረግ (cultural determinism) ነገር አለ፡፡ ይህ በተለይ በእኛ ዘንድ በስፋት የሚስተዋል ችግር ነው፡፡ “ተረግመናል፤ አንድ መሆን ያልቻልነው ስለተረገምን ነው፣ የትብብር ባህል ስለሌለን ነው፣ አብሮ መብላት እንጅ አብሮ መስራት አንችልበትም” ወዘተ ይባላል፡፡ ከዚህም አልፎ “መቼም አንድ ልንሆን አንችልም!” እስከማለት ይኬዳል፡፡

መሰረተ-ቢስ አመለካከት ነው፡፡ አንደኛ አላዘመነውም እንጅ ከፍተኛ የሆነ የትብብር ባህል ያለን ህዝብ ነን፡፡ ይህን ለመገንዘብ ብዙሃኑን ህዝባችንን (አርሶ አደሩን) ማየት ነው፡፡ ያለ ደቦ፣ ያለ ወንፈል፣ ያለ ወበራ፣ ያለ ደባይት ወዘተ የሚሰራ አርሶ አደር አለ ወይ? አርሶ አደራችን ከፍተኛ የሆነ የትብብር ባህል ያለው ነው፡፡ በእርስ በርስ መደጋገፍና መረዳዳት የታወቀ ህዝብ ነው፡፡ በየአካባቢው ብዙ ዘመናት ያስቆጠሩ የአብሮ አደግ ማህበራት ያሉ መሆናቸውን መዘንጋት አይገባም፡፡ ስለሆነም ካሳደግነው እርሾው አለ፡፡

በሌላ በኩል፣ በዘመናዊው የድርጅት ግንባታ ታሪካችን ውስጥም ቢሆን፣ እስካሁን ጥሩ የትብብር መንፈስ ፈጥረን ጠንካራ ድርጅቶችን መገንባት አልቻልንም ማለት ዛሬ መገንባት አንችልም ማለት አይደለም፡፡ ትላንት አልተባበርንም ማለት ዛሬ መተባበር አንችልም ማለት አይደለም፡፡ ትላንት ጠንካራ የፖለቲካ፣ የሲቪክና የሚዲያ ተቋማትን መገንባት አልቻልንም ማለት ዛሬ መገንባት አንችልም ማለት አይደለም፡፡ ባህል የሚቀየር ነገር መሆኑ ይግባን፡፡ ባህል የሚሻሻል ነገር መሆኑን እንረዳ፡፡

ስለዚህ ስለ እርግማን የሚወራውን ከንቱ ትንተና እንተወው፡፡ ውሃ አይቋጥርም፡፡ የእንዲህ አይነት አመለካከት እስረኛ አንሁን፡፡ የሚበጀው ለተቋም ግንባታ የሚረዱ እሴቶችን መኮትኮት ነው፡፡ የሚበጀው ከሌሎች ብቻ ሳይሆን ከራሳችንም (ከውድቀታችንም ከስኬታችንም) መማር ነው፡፡ ትምህርት ቀስሞ ወደ ተቋም ግንባታ መግባት ነው፡፡

ጊዜው የስራ ነው!

የአማራ ብሄርተኝነት ይለምልም!!!

Veronica Melaku

14 Oct, 04:14


ያልተማከለ የተማከለ አደረጃጀት!

የታሊባን ታጋዮች በተለያዩ ክፍላተ ሀገራት የሚገኙ ነበሩ፡፡ አንድ ማእከል አልነበራቸውም፡፡ ይህም በአንድ በኩል ለአሜሪካ ሁኔታውን አስቸጋሪ ሲያደርግባት፣ በሌላ በኩል ግን ታሊባኖች ወጥ አመራር ኖሯቸው በተቀናጀ መንገድ እንዳይታገሉ አድርጓቸው ነበር፡፡ ታሊባን ይህን ችግር መቅረፍ የቻለው ያልተማከለ የተማከለ አደረጃጀትን (Decentralized centralization) በመከተል ነው፡፡ ጠላት በሁሉም አካባቢዎች መወጠሩ አስፈላጊ ነበር፡፡ ይሁንና አርበኝነቱን በተቀናጀ አኳኋን ለመምራት በሁሉም አካባቢዎች የሚኖሩ አደረጃጀቶች እንዳሉ ሆነው አንድ የጋራ አደረጃጀት መፍጠር ነበረባቸው፡፡

የአፍጋኒስታን ህዝብ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ነው፡፡ የሚያይዛቸው ቋንቋ ሳይሆን ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ነፃነት ያላቸው ቀናኢነት እንዲሁም እስልምና ሃይማኖታቸው ነው፡፡ ስለሆነም ከቋንቋ፣ ከአካሄድና ታክቲክ ወዘተ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን አቆይተው ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በመስማማት አንድ የጋራ አደረጃጀት መፍጠር ችለዋል፡፡ በትግሉ መነሻና መዳረሻ ላይ፣ በወሳኝ ስትራቴጅክ ጉዳዮች ላይ፣ በሃይሎች አሰላለፍ ላይ፣ ከድል በኋላ በሚመሰረተው መንግስት ወዘተ ዙሪያ ስምምነት አለ፡፡ የጋራ አላማ አለ ማለት ነው፡፡ መግለጫ የሚሰጠው ወጥ በሆነ መንገድ ነው፡፡ አመራር የሚተካበት ስርአት አለ፡፡ ሰራዊቱ የሚመራበት ወጥ የሆነ ጠንካራ መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡ ሰራዊቱ ከህዝቡ ጋር ሊኖረው የሚገባውን መስተጋብር በሚመለከት ግልፅ የሆነ የጋራ ግንዛቤ እና ጥብቅ ዲሲፕሊን አለ፡፡

ታሊባኖች ይህን ካደረጉ በኋላ በሁሉም ቀበሌዎች፣ ወረዳዎች፣ ክፍለ ሀገሮች እና በሀገር ደረጃም ጭምር ትይዩ አስተዳደር መስርተዋል፡፡ አሜሪካኖች ባደራጁት ምስለኔ የወረዳ አስተዳዳሪ ትይዩ ታሊባን በህቡእ የሰየመው አስተዳዳሪ አለ፡፡ ለእያንዳንዱ መስሪያ ቤት ትይዩ ሃላፊ ተመድቦለታል፡፡ በህቡእ፡፡ በዚህ መንገድ ነው የኑውክሌርና የድሮን ጎተራዋን አሜሪካን አዋርደው ያባረሯት!!!

እንዲህ አይነቱን ያልተማከለ የተማከለ አደረጃጀት እስራኤሎችም በስፋት ይጠቀሙበታል፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ የሚንቀሳቀሱትን እስራኤልን የሚደግፉ ወትዋች (ሎቢ) ድርጅቶች ብናይ ቁጥራቸው በጣም ብዙ ነው፡፡ ይሁን እንጅ ሕልውናቸውን ጠብቀው ዣንጥላ አደረጃጀቶችን ይፈጥራሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉት ተሰሚነታቸውን ለማጉላት ነው፤ የሰው ሃይልና የፋይናንስ አቅማቸውን ለማደርጀት ነው፡፡ ሕልውናቸውን የሚጠብቁት ደግሞ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች ስለሚኖሯቸው ነው፡፡ ሁለቱም አዋጭ አካሄድ ነው።

እንዲህ አይነት አደረጃጀት የእርስ በርስ ፍጅትን ያስቀራል፡፡ የዲሞክራሲ ባህልን ያሰርፃል፡፡ ውሳኔዎች ከተቻለ በሙሉ ስምምነት ካልሆነ ደግሞ በአብላጫ ድምፅ ይወሰናሉ፡፡ የብዙሃኑ ውሳኔ ተግባራዊ ይሆናል፤ አነስተኛ ቁጥር ያገኙት ወገኖች መብትም ይከበራል፡፡ መጠፋፋት የለም!

የአማራ አደረጃጀቶችም ከእንዲህ አይነቱ መንገድ ብዙ መማር ይችላሉ፡፡ በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲህ አይነት ዣንጥላ አደረጃጀቶችን መገንባት ይቻላል፡፡ ይገባልም፡፡ የግድ ሁሉም ካልተጨፈለቀ ጠንካራ ድርጅት አይፈጠርም የሚለው አካሄድ መገፋፋትንና መጠፋፋትን እንጅ ጠንካራ ተቋምን ሲያዋልድ አላየንም፡፡ ያልተማከለ የተማከለ አደረጃጀትን እንሞክረው!

የአማራ ብሄርተኝነት ይለምልም!!!

Veronica Melaku

13 Oct, 19:02


updated👇
አብሪ ኮከቧ ወልድያ ከወራሪው ሀይል ነፃ እየወጣች ነው!
ፋኖ 💪

Veronica Melaku

13 Oct, 18:03


የት ላይ ነህ?

ለትግሉ አስተዋጽኦ እያደረክ ነው ወይስ ትግሉን እየጎተትክ? በሚያሰባስብና ህብረት በሚፈጥር ተግባር ላይ ነህ ወይስ በከፋፋይ አጀንዳ ተጠምደሃል? ቤትህ ወይም ካፌ ውስጥ ወይም ቢሮ ተቀምጠህ በማህበራዊ ሚዲያ እያዋጋህ ነው ወይስ ለትግሉ በሚጠቅም ተግባር ላይ ተሰማርተሃል? “የሎጅስቲክ ድጋፍ እንዳናደርግ አልተባበር አሉ! ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት አለኝ ግን መንገዱን አጣሁት” ወዘተ ወዘተ እያልክ ምክንያት እየደረደርክና ራስክን እየሸወድክ ነው ወይስ በምትችለው መንገድ ድጋፍ እያደረክ? “የትግሉ መሰናክሎች የዚህ አካባቢ ሰዎች ናቸው፣ የትግሉ ነቀርሳ እከሌ ነው” ምንትስ ምንትስ እያልክ በማይጠቅም እንቶ ፈንቶ ላይ ተሰማርተሃል ወይስ የምትችለውን እያደረክ ነው? ችግሩ በእኔና በቤተሰቤ ላይ ካልደረሰ ችግር የለም ብለህ ተቀምጠሃል ወይስ የወገኔ ጥቃት ጥቃቴ ነው ብለህ በምትችለው መንገድ ትግሉን እየደገፍክ ነው? ወገናዊነቴ ለህዝቤ ነው ብለህ ትግሉንና ታጋዮችን እየደገፍክ ነው ወይስ የግለሰቦች ጭፍራ ነህ? ሶፋ ላይ ተጋድመህ የድል ዜና እየቃረምክ ነው ወይስ ቲክቶክ ላይ ተጥደህ ከንቱ ወሬ እያግበሰበስክ? የት ላይ ነህ? ምን ላይ ነሽ?

የገባንበትን የሕልውና ትግል ከማሸነፍ ውጪ አማራጭ የለም፡፡ ከዚያው ውጪ ያለው አማራጭ (አማራጭ ከተባለ) ሞት ነው፡፡ ውርደት ነው፡፡ ባርነት ነው!

ስለሆነም ለዚህ ትግል ሁላችንም በምንችለው መንገድ ሁሉ አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን፡፡ ጦርነት በጣም ውድ ተግባር (expensive venture) ነው፡፡ ብዙ ገንዘብ ይጠይቃል፡፡ ብዙ ሀብት ይጠይቃል፡፡ ከፍተኛ ሎጂስቲክስ ያስፈልገዋል፡፡ ጦርነትን በድል ለመወጣት ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ሎጅስቲክስ ነው፡፡ ስለሆነም ሁላችንም የምንችለውን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

ዝም የተሰኙት ብዙሃን (the silenced majority) ትግሉን መቀላቀል አለባቸው፡፡ በሚችሉት መንገድ ሁሉ አስተዋጽኦ ማድረግ አለባቸው፡፡ እነ እከሌ ይሰሩታል ብሎ ነገር የለም፡፡ አንተ ያልሰራኸውን ሌላው እንዲሰራው ለምን ትጠብቃለህ? የእነ እከሌ ወንድሞች ይዋጉ ብሎ ነገር የለም፡፡ የአንተ ወንድም መስዋዕትነት ለመክፈል የፈራውን ሌላው ለምን ይከፍላል? ምክንያት መደርደር አያስፈልግም፡፡ መፍትሄው አንድ ብቻ ነው፡፡ የትግሉ አካል መሆን፡፡ ጨርቄን ማቄንን ማስወገድ፡፡ በፈተና መፅናት!!!

የአማራ ብሄርተኝነት ይለምልም!!!

Veronica Melaku

13 Oct, 04:46


"ወደድንም ጠላንም” እናሰኛቸው!

አንድ የፖለቲካ ሃይል ፖለቲካዊ አቅሙ ከጠነከረ አገዛዞችም ሆኑ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ሳይወዱ በግዳቸው ከምር ሊወስዱት ይገደዳሉ፡፡ ምክንያቱም ሊገፉት የማይችሉት የፖለቲካ እውነታ (political reality) ሆኗልና ነው፡፡ “ወደድንም ጠላንም እነሱን የማሳተፍ ግዴታ አለብን፡፡ እነሱ ካልተሳተፉ ነገሩ አይሰምርም” ማስባል መቻል ትልቅ አቅም ነው፡፡ ሃያልነት ነው፡፡

ብዙዎቻችን አሜሪካ ህወሃትን ትወደዋለች እንላለን፡፡ ፖለቲካ ጠንቅቀው ያውቃሉ የሚባሉት ሰዎች ሳይቀሩ በእንዱህ አይነት ከንቱ ትንተና ሲርመጠመጡ ይታያል፡፡ አሜሪካ ግን ህወሃትን አትወደውም፤ አትጠላውምም፡፡ በአለም አቀፍ ፖለቲካ መዝገበ ቃላት ውስጥ መውደድና መጥላት ብሎ ነገር የለምና፡፡ አሜሪካ “ህወሃት የትግራይ ህዝብ እውነተኛ ወኪል ነው፡፡ የማይነቀነቅ የፖለቲካ እውነታ ነው” ብላ ግን ታምናለች፡፡ ነውም! ህወሃት የትግራይ ህዝብ ወኪል መሆኑን የሚጠራጠር ስለ ትግራይ ፖለቲካ ያልገባው ነው፡፡ ስለ ብሄርተኝነት ያልተገለጠለት ነው፡፡

እኛ እንደ ህዝብ የሀገሪቱ ቀዳሚ ህዝብ ሆነን ሳለ ለምን 2ኛ ናችሁ እንባላለን? ለምን በነህወሃት ደረጃ ትግላችን ትኩረት አላገኘም? መልሱ “የፖለቲካ እውነታ የሆኑ ድርጅቶች ስለሌሉን ነው” የሚል ነው፡፡ መልሱ "ብሄርተኝነታችን ስላልደረ ነው" የሚል ነው። ስለሆነም “ወደድንም ጠላንም አማራ በእውነተኛ ወኪሎቹ ያልተሳተፈበት ለውጥም ይባል ሽግግር ከንቱ ነው” ማስባል መቻል አለብን፡፡ “ወደድንም ጠላንም ከአማራ ጋር ካልሰራን ነገሮች አይሰምሩም” ማሰኘት መቻል አለብን፡፡ ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ ደግሞ የተቀናጁ ስራዎችን መስራት ይገባናል፡፡ የፖለቲካ አቅማችንና አቋማችን ፍንተው ያለና የደረጀ መሆን አለበት፡፡ ወታደራዊ አቅማችን ጠንካራ መሆን አለበት፡፡ የሚዲያ አቅማችን የደረጀ መሆን አለበት፡- በአለም አቀፍ ቋንቋዎች ጭምር በስፋት መጻፍና መዘገብ ይገባናል፡፡ የዲያስፖራውን አቅም ማሰባሰብና ማጠናከር ይገባናል፡፡ ያኔ ነው ሳንፈልጋቸው አጋር እንሁናችሁ እያሉ የሚመጡት፡፡ ያኔ ነው “ወደድንም ጠላንም ከእነሱ ጋር መስራት አለብን” የምንባለው፡፡ ብሄርተኝነታችን በሁሉም መስክ ሲጠነክር ነው ሁሉም አብረውን ሊሰሩ የሚገደዱት፡፡

“ወደድንም ጠላንም” እናሰኛቸው!

የአማራ ብሄርተኝነት ይለምልም!!!

Veronica Melaku

12 Oct, 18:48


ቃላቸውን እንጠብቃለን!

የአማራ ጀግኖች ለህዝባቸው ሕልውናና ነፃነት በየእለቱ ውድ መስዋእትነት እየከፈሉ ነው፡፡ ውድ ዋጋ እየተከፈለልን ነው። የጀግኖቻችን ቃል የመጠበቅ ታሪካዊ ሃላፊነት አለብን፡፡ መስዋእት የሆኑለትን ክቡር አላማ ከዳር የማድረስ ታሪካዊ ተልእኮ አለብን፡፡ የአማራ ሴቶች ለክብራቸው ልዩ ቦታ ስለሚሰጡ አይናገሩትም እንጅ በወራሪው ሰራዊት እየተደፈሩ ነው፡፡ ጌጣቸውን እየተቀሙ ነው፡፡ እየዘረፉ ነው፡፡ አባታቸውን፣ ወንድማቸውንና ልጆቻቸውን እያጡ ነው፡፡ አይናገሩት እንጅ በዝምታቸው አደራ እየሰጡን ነው፡፡ ክብራቸውን የደፈረውን አራዊት አስወግደን አንገታቸውን ቀና እንድናደርገው ሃላፊነት እየሰጡን ነው፡፡ የጀግኖችን እናቶችና እህቶች ክብር የማስመለስና የመጠበቅ ታሪካዊ ሃላፊነት አለብን፡፡ የጀግኖችን ሚስቶች ቃል የመጠበቅ ታሪካዊ ሃላፊነት አለብን፡፡

የአማራ ህዝብ ተዋርዶና አንገቱን ደፍቶ እንዳይኖር፣ ተቅበዝባዥና ሁለተኛ ዜጋ ሆኖ እንዳይኖር ሕልውናውን የማስከበር ታሪካዊ ሃላፊነት አለብን፡፡ የሚሳደደው ህዝባችን አደራ አለብን፡፡ ሁላችንም ለዚህ ክቡር አላማ አስተዋጽኦ ለማበርከት መረባረብ ይገባናል፡፡ ሁላችንም ራሳችን ከቅርብ አዳሪነት ማራቅ ይገባናል፡፡ ሁላችንም በትንሽ ፖለቲካ መርመጥመጡን ትተን በትልቁ ፖለቲካ ላይ፣ ማለትም በሚያሰባስበንና በሚያጠናክረን ጉዳይ ላይ ብቻ እናተኩር፡፡ በሚያሳንሰንና በሚከፋፍለን ላይ ካተኮርን በሰማእታቶች ደም እየቀለድን ነው፡፡ በአማራ ሴቶች መደፈር እየተሳለቅን ነው፡፡ ልብ እንግዛ! ልባሞች እንሁን!!!

የአማራ ብሄርተኝነት ይለምልም!!!

Veronica Melaku

12 Oct, 05:03


የበለጥክ አማራ ሁንባቸው!

በተለያዩ ምክንያቶች ከሌሎች የአማራ ወገኖችህ ጋር ተጋጭተህ ሊሆን ይችላል፡፡ ጥፋት አጥፍተህ ወይም ባላጠፋኸው አጥፍተሃል ብለው እየከሰሱህ ይሆናል፡፡ በማንኛውም ምክንያት ከአማራነት እና ከአማራ ትግል ገፍተው ሊያስወጡህ ሲሞክሩ ይበልጥ አማራ ሆነህ አሸንፋቸው እንጅ ከማንነትህ አትሸሽላቸው፡፡ ሲገፉህ አማራነትን ኖረህ አሳያቸው፤ በተግባርህ አስተምራቸው፡፡ እንጅ አንዳንድ ደካማዎች እንደሚሉት “የአማራ ትግል አልቆለታል፣ አማራ አንድ ሊሆን አይችልም” ወዘተ ወዘተ ብለህ ከማንነትህ አትሽሽ፡፡ አማራነት ዋነኛው ማንነትህ እንጅ ፈተና ሲበረታ የምታወልቀው፣ ነገሮች ሲስተካከሉ የምትለብሰው ማንነት አይደለም፡፡ አማራነትን አጥብቀህ ያዝ፡፡ የአማራን ህዝብ በሚጠቅም ተግባር ላይ አተኩር፡፡ በአላስፈላጊ እልህ ውስጥ ገብተህ ክርር አትበል፡፡ አትመናቸክ!

ትግሉ መራራ ነው፡፡ የሁሉንም አማራ ትብብርና ተሳትፎ ይጠይቃል፡፡ ስለሆነም በሚገባህና በምትችለው ቦታ ተሳትፎ አድርግ፡፡ በጥቂት ወገኖች ላይ ቂም ይዘህ አጠቃላይ አማራን በሚጎዳና በሚያሳንስ ተግባር ላይ አትሰማራ፡፡ መፎካከር ካለብህ፣ የበለጠ አማራ ለመሆን ተፎካከር እንጅ ከአማራነት አታፈግፍግ፡፡ ከአማራነት ማፈግፈግ ከራስ ማፈግፈግ ነው፡፡ ራስን አለመሆን ደግሞ የሞት ሞት ነው፡፡ እንዳትሞት ተጠንቀቅ፡፡ የአማራ ብሄርተኝነትን አጥብቀህ ያዝ፡፡ ሃይማኖትክም ሆነ ሕልውናህ ተከብሮ አንገትክን ቀና አድርገህ መኖር የምትችለው አማራነትህ ሲከበር እንደሆነ ይግባህ፡፡

የአማራ ብሄርተኝነት ይለምልም!!!

Veronica Melaku

11 Oct, 03:56


ቆስሏል?

ስለ ሽምቅ የትጥቅ ትግል በብዙ የስትራቴጂ ጠበብቶች የሚነገር አንድ እጅግ ጠቃሚ መርህ አለ፡፡ በተለይ የቻይናው አብዮታዊ መሪ ማኦ ሴ ቱንግ በተደጋጋሚ ይጠቅሰዋል፡፡ ጥንቸል ዝሆንን አሸንፋለሁ ብላ በተሰበሰቡት እንስሳት ፊት ስትናገር ሁሉም እንስሳት ይሳለቁባታል፡፡ እውነትም ፊት ለፊት ቢገጥሙ ዝሆኑ ጥንቸሏን በቀላሉ ሊደፈጥጣት ይችላል፡፡ ይሁን እንጅ ጥንቸሏ በራሷ ስትራቴጂና ስልት ገጥማ ታሸንፈዋለች፡፡ ጥንቸሏ ግዙፉን ዝሆን በመረጠችው ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ እያደባች ነክሳው ትሮጣለች፡፡ ነክሳው መሮጥ አለባት፡፡ እንዳይደፈጥጣት ያለ አቅሟ ፊት ለፊት አትጋፈጠውም፡፡ እሱ በመረጠው ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ አትገጥመውም፡፡ በዚህ መንገድ ደጋግማ ነክሳ በመሮጥ ሰውነቱ እንዲቆስል ታደርጋለች፡፡ ደጋግማ ቁስሉን ስለምትነክሰው ቁስሉ እያመረቀዘና ሌላ በሽታ እያበቀለ ይሄዳል እንጅ አይድንም፡፡ መጨረሻ ላይ ዝሆኑ የሚሞተው ቁስሉ በሚፈጥርበት በሽታ ነው፡፡

የሽምቅ ተዋጊ ድርጅቶች አምባገነናዊ አገዛዞችን በዚህ መንገድ ነው የሚያሸንፏቸው፡፡ በራሳቸው ስትራቴጂና ታክቲክ፣ በራሳቸው የጊዜ፣ የቦታና የሁኔታ ምርጫ እየገጠሙ ደጋግመው ያቁስሏቸዋል፡፡ ደጋግመው በመንከስ ቁስሉ በሽታ እንዲያበቅል ያደርጉታል፡፡ ያለ አቅማቸው ከጠላት ጋር ፊት ለፊት ጋር በመግጠም አላስፈላጊ መስዋዕትነት አይከፍሉም፡፡ በፍጥነት ያጠቃሉ፡፡ ፈጥነው ሮጠው መደበቂያ ቦታቸውን ይይዛሉ፡፡ ሃይል ይቆጥባሉ፡፡ ምክንያቱም አገዛዙ በሰው ሃይልም፣ በሎጅስቲክና በመሳሪያ አቅምም ከሽምቅ ተዋጊ ድርጅቶች በእጅጉ ይበልጣልና፡፡ጥንቸሏ በአላስፈላጊ ጀብደኝነት ፊት ለፊት ከዝሆኑ ጋር ልጋፈጥ ያለች እንደሆነ የማይድን ቁስል ትቆስላለች ወይም ትደፈጠጣለች፡፡

ሌላ ቦታ ሳንሄድ ወያኔና ህዝባዊ ግንባር ግዙፍ ሰራዊት የነበረውን የደርግ አገዛዝ ያንኮታኮቱት ይህን ስትራቴጅና ታክቲክ በመጠቀም ነው፡፡ ሃይል በመቆጠብ፡፡ በጠላት ሳይሆን በራስ ስትራቴጅና ታክትክ መሰረት በመግጠም፡፡ ጦርነቱን ለአገዛዙ ውድና የማይቻል በማድረግ፡፡ አገዛዙ በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካና ኢኮኖሚ እንዲንኮታኮት በማድረግ፡፡ የተዋጊው ሃይል ሞራል እንዲላሽቅ በማድረግ፡፡ ድርግን የጣላው የህዝባዊ ግንባርና የወያኔ አቅም ሳይሆን ቁስሉ የፈጠረበት በሽታ ወይም ጋንግሪን ነው፡፡

ጦርነቱን በፍጥነት ለማሸነፍ መሯሯጥ ወይም መቸኮል ያለበት አገዛዙ እንጅ የነፃነት ታጋዮች መሆን የለባቸውም፡፡ ጦርነቱ በመቀጠሉ የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ኪሳራ የሚደርስበት አገዛዙ እንጅ የነፃነት ተዋጊዎች አይሆኑም፡፡ ቁስሉ እያመረቀዘ ለሞት የሚዳርገው አገዛዙን እንጅ ሽምቅ ተዋጊዎችን አይደለም፡፡

የፋኖን አርበኝነት በዚህ መነፀር መረዳት ይገባናል፡፡ ተቻኩሎ ጊዜው፣ ቦታውና ሁኔታው በማይፈቅድበት ከዝሆን ጋር ፊት ለፊት እየገጠመ ከፍተኛ ቁስል እንዳይገጥመው ወይም እንዳይደፈጠጥ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ሁልጊዜም እየሰለጠነ፣ ሁልጊዜም የፖለቲካና ወታደራዊ አቅሙን እየገነባ፣ ሁልጊዜም ሃይል እያሰባሰበ ጠላትን ደጋግሞ በመንከስ ማቁሰል እና ቁስሉ በሽታ እንዲያበቅል በማድረግ ገዝግዞ መጣል ይገባዋል፡፡ ታዲያ የራስን ደህንነት እና ጤንነት መጠበቅ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነው!

እስካሁን ባለው ሁኔታ ፋሽስታዊው አገዛዝ የቆሰለ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ “የቁስሉ ደረጃ ምን ያክል ነው? ሌላ በሽታ እያበቀለ ነውን?” የሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙት ግን የራሳችን ሃይል እያሰባሰብንና ተጨማሪ አቅም እየገነባን ያለማቋረጥ ስንነክሰው ነው፡፡

ፍትሃዊነት ያሸንፋል!

የአማራ ብሄርተኝነት ይለምልም!!!