የኢትዮ ቴሌኮም ሼር መግዛት ያዋጣል/አያዋጣም?
/መላኩ ይርዳው/
የኢትዮ ቴሌኮምን ሼር አዋጭነት በተመለከተ አንዳንድ የተሳሳቱ ትንተናዎች እና የተዛቡ ቁጥራዊ መረጃዎች ሲዘዋወሩ አይቻለሁ!
ኢትዮ ቴሌኮም ባለፈው ዓመት (2016) ገቢው 93.7 ቢሊየን የነበረ ሲሆን ከታክስ በፊት የነበረው ትርፍ 90.7 ቢሊየን ነው። በበጀት ዓመቱ ደግሞ 27.2 ቢሊየን ታክስ ከፍሏል። ከታክስ በኋላ ያለው የተጣራ ትርፍ 63.5 ቢሊየን ነው።
ከ93.7 ቢሊየን ገቢው ውስጥ ወጪው 3 ቢሊየን ብቻ የሆነው ተቋሙ ሸቀጥ አምርቶ ወይም ገዝቶ የሚሸጥ ስላልሆነ እና የሚሸጠው አገልግሎት ከዚህ ቀደም በዘረጋው መሰረተ ልማት፣ ቴክኖሎጂና እውቀት በመሆኑ ነው። ይህ የተቋሙ ውጤታማነት (efficiency) ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል።
***
ለኢንቨስትመንት ውሳኔ የሚረዳውን ስሌት ስናይ -
ዛሬ ላይ ያለው የተቋሙ የተጣራ ሀብት (owner's equity) 113.5 ቢሊየን ነው። ነገር ግን ድርሻውን ለገበያ ሲያቀርብ ተቋሙ ድጋሚ ቢገመት ዋጋው 300 ቢሊየን ይሆናል ብሎ ነው የተነሳው። አንድ ሰው/ድርጅት ንብረቱን ሊሸጥ ገበያ ቢያወጣ ለንብረቱ ዋጋ የሚያወጣው ሻጩ ስለሆነ ኢትዮ ቴሌኮም ራሱ ላይ የፈለገውን ዋጋ የመለጠፍ መብት አለው። ይሄ ዋጋ ተወደደ/አልተወደደም? ዋጋ ያወጠው (የተመነው) በዘፈቀደ ነው ወይስ አስጠንቶ? ያጠናውስ ማን ነው? ያጠናው አካል ሙያዊ መርህን ተከትሎ ነው ወይስ ካይከተል? ... ብሎ መጠየቅ ያለበት ገዢው ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮ ቴሌኮም አሁን ላይ 100.7 ቢሊየን እዳ ስላለበት ሼር ገዢው እዳውንም በድርሻው ልክ አብሮ ይወርሳል ማለት ነው።
ከትርፍ አንጻር
ተቋሙ ለሽያጭ ያቀረበው የሼር ዋጋ የ300 ቢሊየን 10% (30 ቢሊየን) ነው።
ከላይ በገለጽኩት ያለፈው ዓመት ትርፍ መሰረት የሼር ባለቤቶች የሚያገኙት ትርፍ (earning per share) 63.5÷300 = 21.2% ነው። የ1 ሚሊየን ሼር የገዛ ሰው 212,000 ብር ትርፍ (dividend) ያገኛል ማለት ነው። ይህ ትርፍ ለካፒታል ማሳደጊያ ካልዋለ 10% ታክስ ተቆርጦ 190,800 ብር ይከፈለዋል። ትርፍ ከተከፋፈለ 10% ተክስ ስለሚቆረጥበት በባለድርሻው ኪስ የሚገባው ትርፍ ከ21.2% ወደ 19% ዝቅ ይላል። ትርፉ ካልተከፋፈለና ለካፒታል ማሳደጊያ ከዋለ ከሼር ድርሻ የሚገኘው ትርፍ ላይ የሚቆረጠው ታክስ አይቆረጥም።
****
በጥቅሉ ስናየው ከሼር 21.2% ትርፍ ማግነት ትንሽ አይደለም። አንድ ሰው ሳይሰራ ሳይደክም፣ ሳይወጣ ሳይወርድ፣ ቀበሌና ክ/ከተማ ሳይሄድ፣ የሰው ፊት ሳይገርፈው፣ ከሰራተኛ ጋር ሳይጨቃጨቅ በዓመት የኢንቨስትመንቱ 21.2% ትርፍ ካገኘ አዋጭ አይደለም ማለት አይቻልም። ሆኖም በሀገሪቷ ከ35% በላይ ትርፍ የሚያስገኙ ድርጅቶችም አሉ። አንድ ኢንቨስተር 35% ትርፍ የሚያስገኝ ድርጅት እያለ ለምን 21.2% ትርፍ የሚያስገኝ ድርጅት ላይ ኢንቨስት አደርጋለሁ ሊል ይችል።
ነገር ግን ዛሬ 35% ትርፍ የሚያስገኘው ድርጅት የትርፋማነቱ ዘላቂነት እና የህልውናው ቀጣይነት እንዲሁም ዋጋው የማደጉ እድል (appreciation tendency) ከ21.2 ፐርሰንቱ ወይም ከዚያም በታች ከሆነው ድርጅት ሊያንስ ይችላል። ስለዚህ የኢንቨስትመን ውሳኔ ሲወሰን እነዚህ ነገሮች ከግምት ገብተው መሆን አለበት።
ኢትዮ ቴሌኮምን ስናይ ለዘመናት ያካበተው መልካም ስም ያለው ሀገር የምትመካበት ግዙፍ ተቋም ነው። ከቅርብ አመታት ወዲህ በውድድር አልፎ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚችልም አሳይቷል። በቅርብ አመታት ያሳየው የአገልግሎት ጥራት እድገት ተቋሙ ብዙ እምቅ አቅም እንዳለው ማሳያ መሆን የሚችል ነው።ከዚህ አንጻር ይህ ተቋም ላይ የሚፈስ ሀብት ከዓመት ትርፍም ባሻገር እንደ አስተማማኝ ጥሪት ሊወሰድ የሚችል ነው።
እንደ ስጋት ሊቀርብ የሚችለው የተቋሙ 50%+1 ባለድርሻ መንግስት እንደ መሆኑ በተቋሙ ላይ ውሳኔ የሚሰጠው መንግስት ነው። አለም ላይ ባለው ተሞክሮ መንግስት የቢዝነስ ተቋማት የመምራት ስኬቱ አናሳ ነው። ሌላው መንግስት የፖለቲካ ተቋም በመሆኑ በዚህ ተቋም ላይ የሚወስናቸው ውሳኔዎች ከbusiness perspective እና ከባለድርሻዎች ጥቅም አንጻር ብቻ የተቃኙ ላይሆኑ ይችላሉ። መንግስት ለፖለቲካዊ አላማ የተቋሙን ዋጋ ባልተገባ መልኩ appreciate ወይም deppreciate ሊያደርገው ይችላል። የተቋሙ ቢዝነስ ስትራቴጂ መንግስት በተቋሙ ላይ ያለው ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ስለሚሆን ያ ስትራቴጂ ተቋሙን በሚገባው ልክ የማያሳድግ ሊሆን ይችላል። ይህ ባለድርሻዎችን ይጎዳል።
በእኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ከመንግስት ጋር በሽርክና መስራት አዋጭ ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ማድረግስ አበረታች ነው? የሚሉትን ጠያቄዎችም ለኢንቨስተሮቹ ውሳኔና ምርጫ የሚተዉ ናቸው።
Zebidar Tube/ ዘቢዳር ቲዩብ