ህዝባዊ በዓላት የፖለቲካ መድረክ ሊሆኑ አይገባም!
ፓርቲያችን #ኢዜማ በመርኆዎቹ ካስቀመጣቸው መሠረታዊ ሐሳቦች መካከል አንዱ “ኢትዮጵያ ልንንከባከበው የሚገባን ባለ ብዙ ባሕል፣ ታሪክ እና ቅርስ ባለቤት የሆነች ሀገር መሆኗን ከልብ እናምናለን” የሚል ነው። እነዚሕን ባሕል፣ ታሪክ እና ቅርሶች በተሻለ ደረጃ ለመጠበቅ ለማቆየት እና ለማጎልበት የመንግሥት፣ የማኅበረሠቡ እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት መሆኑን እና እነዚህም የጋራ ማንነት ለመፍጠር ያላቸውን አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ አንዳች ጥርጥር የለውም።
እነዚህ የጋራ ማንነትን በመፍጠር ሚናቸው ከፍተኛ የሆኑ ባሕሎችን በእኩል መንከባከብ እና ማሳደግ ተገቢ እና የሚበረታታ ነው። ነገር ግን ሀገራችን ባላት ስሁት ፌደራላዊ የመንግሥት ስሪትን በመንተራስ መሠል ባህሎችን የጋራ ማንነት ማጠንከሪያ ምሰሶዎች ከማድረግ ይልቅ የፖለቲካ ውግንና እና ትርፍ መሸቀጫነት ለማድረግ ሲሞከሩ ማየት የሚያሳዝን ነው፡፡ ልንከባከባቸው ልናሣድጋቸው እና በደማቅ ሁኔታ ልናከብራቸው ከሚገቡ ባሕሎች መካከል አንዱ በቅርብ ቀን የሚከበረው ኢሬቻ መሆኑን ኢዜማ ያምናል።
መንግሥት ከባሕል፣ ታሪክ እና ቅርሶች ጉዳይ ጋር በተያያዘ ዋነኛ ኃላፊነቱ የሆነውን እነኚህን ለማሳደግ፣ ለመጠበቅ እና ለማጎልበት የሚረዱ የሕግ ማዕቀፎችን እና ፖሊሲዎችን ማውጣትና መተግበር፣ ግንዛቤ መፍጠር እና ለቅርሶቹ አስፈላጊውን ጥበቃ ማድረግ እንዲሁም ባሕሎቹ ሲከበሩ ያለምንም ስጋት ተከብረው እንዲጠናቀቁ የጸጥታ እና ደኅንነት ሥራን መሥራት ብቻ ነው። ሆኖም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይም ኢሬቻን በማክበር ሒደት በመንግሥት መዋቅሮች እና በመንግሥታዊ ኃላፊነት ቦታ ላይ የተቀመጡ ባለሥልጣናት ባሕሉ ካለው ሕዝባዊ እሴት ባፈነገጠ መልኩ ባሕሉን ከሕዝቡ ባለቤትነት ነጥቆ ፖለቲከኞቹ ዋነኛ አጋፋሪ ሆነው መምጣታቸው በሌሎች ዘንድ የመገለል እና የስጋት ስሜት ይፈጥራል። ገዢው ፓርቲም በዚህ መልኩ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በሚመስል መልኩ መንቀሳቀሱ ተገቢ አይደለም ብለን እናምናለን።
በተለይ ለባሕሉ ተብሎ በተለያዩ አካባቢዎች ከተቋማት እና ከንግዱ ማኅበረሠብ በድጋፍ ስም በመንግስት መስሪያ ቤቶች ደብዳቤ የንግድ ማኅበረሠቡን በሚያስጨንቅ እና ከአቅም በላይ የሆነ ከፍተኛ አስገዳጅ የገንዘብ መዋጮ መጠየቅ ማኅበረሠቡን ከፍተኛ ምሬት ውስጥ በመክተት ባሕሉን በስጋት እንዲመለከተው እያደረገ ይገኛል።
የባሕሉ ባለቤት የሆነው ሕዝብም ተቋማትን እና ግለሰቦችን አስጨንቃችሁ መዋጮ በመሰብሰብ በዓሉን አድምቁልኝ አይልም፤ ይህንንም ሕገወጥ ተግባር የሚጠየፈው መሆኑን አንዳች ጥርጥር የለንም። በመሆኑም የየትኛውንም ማኅበረሠብ ባሕላዊም ሆነ ሃይማኖታዊ በዓል ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል ባሕሉን መበረዝ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። ይህን መሰል የአደባባይ ክብረ በዓላት ለየትኛውም አይነት የፖለቲካ አጀንዳ ማራመጃነት መጠቀምን ፓርቲያችን ፍፁም የሚያወግዘው ነው።
በመሆኑም በንግዱ ማኅበረሠብ ላይ እየተደረገ ያለውን ተጠያቂነት የሌለበት ሕገወጥ ጫናን ጨምሮ ሌሎች አስገዳጅ ድርጊቶችን መንግሥት በቶሎ እንዲያቆም እያሳሰብን መንግሥት ባሕሎችን ጠንቅቆ ለሚያውቀው ማኅበረሠብ በመመለስ መሠረታዊ ስንል ከላይ የጠቀስናቸውን ኃላፊነቶቹን ብቻ በቅጡ እንዲወጣ እንጠይቃለን።
መስከረም 22/2017 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ