☕️
ጠላን
ተጠላን
:
ወደድን
ተወደድን
:
ቀናን
ቀኑብን
:
እሰይ . . .
እንኳንም ኖርን !
እንኳን ተወለድን
እንኳን ሰው ኾንን ፤
እሰይ . . .
እንኳን አወቅናት ይቺን ውብ መሬት ፤
ማር ነሽ ስንላት
ብትኾንም ሬት ።
እንኳን አልቀረን
ሽል ብቻ ኹነን !
እንኳንም በቀልን ፤
ልክ እንደ አበባ
ልክ እንደ ሀረግ
ልክ እንደ ቅጠል
ምን'ንኳ እሳት ላይ ብንንጠለጠል ፤
እንኳንም ታሰርን በስጋ ገመድ
እንኳን መጣነው ይኽ ኹሉን መንገድ ።
ካልተወለዱት
ደግሞም ከሞቱት ፤
ከመሬት በታች ከተከተቱት
እንኳንም አልኾን !
እንኳን አዬናት የዛሬን ፀሐይ ፤
የዛሬን መሬት
የዛሬን ሰማይ ፤
እንኳን ተያዬን
እንኳንም ቆዬን !
ኣህ ... !
እንጠጣ ነበር . . .
ቡና በቅቤ
በተገናኘን !
እንኳን አፈቀርን
እንኳን ተፈቀርን
እንኳን አኮረፍን
እንኳን ተባበልን
እንኳን ጅል ኾንን
እንኳን ተታለልን በምንወዳቸው ፤
እንኳን ገደሉን
< አሉን ! >ያልናቸው !
እሰይ . . .
ይኸም መኖር ነው ፤
ደግ አደረጉን
ደግ አረግናቸው ።
አፍታ ናት'ና እንደ ዓይን ጥቅሻ ፤
ሕይወት ተወዳጅ
የማምሻ ማምሻ ፣
እንኳን አወቅናት
እንኳን ቀመስናት ።
ጥርስ ነክሰንም
ቡጢ ይዘንም
ለንቦጭ ጥለንም
ተቦጫጨርንም ፤
የዕድሜን ድራማ
እንኳን ተወንናት
እንኳንም ኖርናት !
እሰይ . . . !
Ohhh Teda🖤🤍
╔═════✩˚⋆★⋆˚✩═════╗
⭐️ @astemari_tarikoch
⭐️ @astemari_tarikoch
╚═════✩˚⋆★⋆˚✩═════