ርቱዓ ሃይማኖት (@rituah) Kanalının Son Gönderileri

ርቱዓ ሃይማኖት Telegram Gönderileri

ርቱዓ ሃይማኖት
❖ርቱዓ ሃይማኖት❖

❖ርትዕት ሃይማኖቶሙ ለቅዱሳን አበዊነ❖

"የእግዚአብሔር ሰው ፍፁምና ለበጎ ስራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ይጠቅማልና (፪ጢሞ፫፥፲፯)"

★ በየእለቱ አጥንትን የሚያጠነክሩ መንፈስን የሚያለመልሙ ጽሁፎችን ለማግኘት ይቀላቀሉን


ለአስተያየት @rituaHM
3,710 Abone
36 Fotoğraf
7 Video
Son Güncelleme 01.03.2025 11:07

ርቱዓ ሃይማኖት tarafından Telegram'da paylaşılan en son içerikler


"+"የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት"+"

በጲላጦስ ዘመን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጅ በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት፤ ትንቢቱም ይፈጸም ዘንድ መከራን ተቀበለ፤ ጲላጦስ በ፫ ሰዓት ይሰቅል ዘንድ ሲፈርድበትም፤ ‹‹መስቀሉንም ተሸክሞ በዕብራይስጥ ጎልጎታ ወደ ተባለው ቀራንዮ ወደሚባል ቦታ ወጣ›› (ዮሐ.፲፱፥፲፯) የራስ ቅል ስፍራ ቀራንዮ-ጎልጎታ አዳም ዐጽም የተቀበረበት ቦታ ነበር፡፡ በዚያም የአዳም መቃብር የሆነች ዋሻ አለች፤ የመስቀሉንም እንጨት በዚያ በምድር መካከል አይሁዶች ተከሉት፡፡
የአዳም አጽም ቀድሞ ከአዳም ትውልዶች ሲተላለፍ ከኖኅ ደርሷል፤ ኖኅም ወደ መርከብ እንደታቦት አስገብቶት በኋላ መልከጼዴቅ ቀብሮታል፡፡ ጌታችንም ከአዳም የራስ ቅል በላይ ሊያድነው መስቀል ተሸከሞ ተንገላታ፤ አይሁዶችም የቀራንዮን ዳገት እየገረፉ ከወደ ጫፍ አደረሱት፤ሁለቱንም እንጨት አመሳቅለው ዐይኖቹ እያዩ እጆቹንና እግሮቹን ቸነከሩት፤ በዕለተ ዐርብ ቀትር ፮ ሰዓት ላይም ተሰቀለ፡፡
ጌታችን የተሰቀለበት ሰዓት ፀሐይ በሰማይ መካከል በሆነ ጊዜ የጥላ መታየት በሚጠፋበት፤ ወደ ሰው ተረከዝም በሚገባበት ነበር፡፤ ከ፮ ሰዓት ጀምሮ እስከ ፱ ምድር ጨለመች፤ ፀሐይ፤ ጨረቃ፤ ከዋክብት ብርሃናቸውን ከለከሉ፤ ምክንያቱም የፈጣሪያቸውን ዕርቃኑን ይሸፍኑ ዘንድ ነበር፤ ‹‹ቀትርም በሆነ ጊዜ ፀሐይ ጨለመ፤ምድርም ሁሉ እስከ ፱ ሰዓት ድረስ ጨለማ ሆነ›› ማር.፲፭፥፴፫፡፡
በ፱ ሰዓት በቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ ስለ ጌታችን በሰማይ ፫ት በምድር ፬ት ተአምራትን ሲያደርጉ አይቶ በእውነት አምላክ እንደሆነ አመነ፤ ‹‹አቤቱ በመንግሥት በመጣህ ጊዜ አስበኝ›› ባለ ጊዜ በግራ የተሰቀለው ዳክርስ ግን ‹‹እስቲ አምላክ ከሆነ እራሱን ያድን›› ብሎ ተዘባበተ፡፡ ፍያታዊ ዘየማን ግን ‹‹እኛስ በበደላችን ነው የተሰቀልን፤ እርሱ ግን ምንም ሳይበድል ነው፤ እንዴት በአምላክ ላይ ክፉ ነገርን ትናገራለህ›› ብሎ ገሰጸው ፤ፍያታዊ ዘየማንም ጌታችን በጌትነት መንበረ ጸባዖት(መንግሥት) ሆኖ ታየው፤እርሱንም አይቶ ‹‹ተዘከረኒ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ›› ቢለው ጌታችን ‹‹ዮም ትሄሉ ምስሌየ ውስተ ገነት›› ብሎ ደመ ማኅተሙን ሰጥቶታል፤ በኋላ ገነት ሲገባም መልአኩ አንተ ማነህ፤ አዳም ነህ፤ አብርሃም ወይንስ ይስሐቅ? እያለ ጠይቆታል፡፡
መልአኩ ሳያውቅ የጠየቀ ሆኖ አይደለም፤እንኳን በመጨረሻ የጸደቀ ፍያታዊ ቀርቶ በዘመናቸው የኖሩ ጻድቃንን ያውቃል፤ አዳምን ፤አብርሃምን፤ ይስሐቅን ሳያውቅ ቀርቶም አይደለም፡፡ ነገር ግን ሊቃውንት ሲተረጉሙት ‹‹አዳም ነህ›› ማለቱ የአዳምን ያህል ሥራ አለህን? አብርሃም ነህ ሲለው ደግሞ የአብርሃምን ያህል ሥራ አለህን? ለማለት ነው፡፡ ‹‹በጌታችን ኢየሱስ መስቀል አጠገብም እናቱ፤ የእናቱም እኅት፤ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፤መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር›› (ዮሐ.፲፱፥፳፭) ‹‹እነርሱም ማርያም መግደላዊት፤ የታናሹ ያዕቆብ እና የዮሳ እናት ማርያም፤ የዘብዴዎስም የልጆቹ እናት ሰሎሜም ነበሩ›› (ማር.፲፭፥፵)፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ከተናገራቸው የአደራ ቃላት አንዱ እመቤታችን ለቅዱስ ዮሐንስ መሰጠቷ ነው፤ ለወዳጁ ዮሐንስ ከስጦታ ሁሉ ስጦታ የሆነች እናቱን እናት ትሁንህ ብሎ ሰጠው፤‹‹እነኋት እናትህ፤ እነሆ ልጅሽ›› (ዮሐ.፲፱፥፳፮)፡፡ በኋላ ወደ ቤቱ ወስዷት ፲፭ ዓመት ኖራለች፤ በዚህም የዮሐንስ ቤት በአቢዳራ ቤት ተመስላለች፤እመቤታችንም የሚያጽናናትን ወዳጁ ዮሐንስን ሰጥቷታል፡፡
የእመቤታችን ለዮሐንስ መሰጠት ቀድሞ በሙሴ አንጻር ጽላቷ ለሕዝቡ ሁሉ እንደተሰጠች፤በዮሐንስ አንጻርም እመቤታችን ለሁላችን ለምእመናን ተሰጥታናለች፡፡
፱ ሰዓት በሆነ ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ፤አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ›› ብሎ በታላቅ ቃል ተናገረ፤ (ማር.፲፭፥፴፬)፡፡ በዚያም ቆመው የነበሩት ‹‹ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ፤ ›› የሚለውን ድምጽ የሰሙ ኤልያስን ይጣራል እያሉ አሙት፤ ክህደትንም ተናገሩ፤ ያንጊዜ አንዱ ወታደር ሮጦ ሆምጣጤ የመላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበርና በሰፍነግ መልቶ በሂሶጽም አድርጎ በአፉ ውስጥ ጨመረለት፡፡
በመስቀል ላይ ሳለ ጌታችን ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ሁሉ ተፈጸመ አለ፤ (ማር. ፲፭፥፴፯)፤ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በፈቃዱ ለየ፡፡
አይሁድም እኒህ ሰዎች እንደተሰቀሉ አይደሩ፤ ምክንያቱም ቀጣዩ ቀን ሰንበት ነውና ጭናቸውን ሰብረው ያወርዷቸው ዘንድ ጲላጦስን ጠየቁት፤ እርሱም ፈቀደላቸው፡፡ የሁለቱ ወንበዴዎች፤ ፈያታይ ዘየማንንና ፈያታይ ዘጸጋምን አብረው አወረዷቸው፤ ከጌታችን ዘንድ ቢቀርቡ ፈጽሞ ሞቶ አገኙት፤ በዚህም ጭኑን ሳይሰብሩት ቀሩ፡፡ ሌላው ግን የተመሰለው ምሳሌ ፍጻሜ ሲያገኝ ነው፤ የፋሲካውን በግ ‹‹አጥንቱን ከእርሱ አትስበሩ›› የተባለው አሁን ተፈጸመ፤ (በዘፀ.፲፪፥፲)፡፡ ከጭፍሮቹም አንዱ ቀኝ ጎኑን በጦር ወጋው እንዲል ከወታደሮቹ አንዱ የሆነው ለንጊኖስ የጌታችንን ጎን ቢወጋው ትኩስ ደምና ቀዝቃዛ ውኃ ፈሷል፡፡ ለንጊኖስ ጥንተ ታሪኩ አንድ ዐይኑ የጠፋ ሲሆን ጌታችን በተሰቀለበት ጊዜ ወደ ጫካ ሸሽቶ ርቆ ነበር፤ ምክንያቱም ከዚህ ሰው ሞት አልተባበርም በማለት ነው፡፡ አመሻሹ ላይ የአይሁድ አለቆች ሲመለሱ ከመንገድ አገኘቱ፤ ስለምን ከመሢሑ ሞት አልተባበርክም አሉት? እርሱም ምንም ስላላገኘሁበት አላቸው፡፡ ከዚያም በኋላ እንደሕጋቸው እንደሚቀጡት ቢነግሩት እየሮጠ ሔዶ የጌታችንን ጎን ሲወጋው ደሙ በዐይኑ ላይ ፈሰሰ፤ ያን ጊዜ ዐይኑ በራለት፤ ከጌታችን ጎን የፈሰሰው ደም እንደ ለ ቅርጽ ሆኖ በሁለት ወገን ደምና ውኃ ሆነ፡፡ ከጌታችንም የፈሰሰውን ትኩስ ደም መላእክት በጽዋ ቀድተው በዓለም ላይ ረጩት፤ ይህ መሠረት ሆኖ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን የሚታነጸው የጌታችን ደም የነጠበበት ነው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አሁንም በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ›› ያለው (ሐዋ.፳፥፳፰)፡፡ ከጌታ ጎን የፈሰሰው ውኃ ደግሞ ምእመናን የልጅነት ጥምቀትን ስንጠመቅ ውኃውን ካህኑ ሲባርከው ማየ ገቦ ይሆናል፡፡
ቅዳሜ ከቀድሞው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረችው ቅዳሜ ትባላለች፤ ይህ ቅዳሜ ጌታችን ሥጋው በመቃብር የዋለበት በመሆኑ እኛም እንደ ሐዋርያት የትንሣኤውን ብርሃን ሳናይ እህል አንቀምስም በማለት በጾም ስለምናሳልፈው ነው፡፡
ቄጠማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤው ሌሊት በራሳቸው ላይ ያሰሩታል፤ የቄጠማው አመጣጥና ምሥጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፤ ምድር በጥፋት ውኃ በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሠረችው ቄጠማ ይዛ በመግባት ነው፡፡ ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ኃጢአት ጠፋ፤
በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነፃነት ተሰበከና ታወጀ በማለት ካህናቱ ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበስሩበታል፡፡
በዚህች ቅድስት ቅዳሜ፤ ቅዱስ የሆነ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ፤ በዚህች ዕለት ከሥራው ሁሉ ያረፈባት ዕለት ናት፡፡ ጌታችን የተቀበረበትም ስፍራ ለተሰቀለበት ቦታ አቅራቢያ ነበር፤ ዮሴፍ ከኒቆዲሞስ ጋር ሆኖ ጌታችንን እንደፍጡር
በሐዘንና በልቅሶ ሲገንዙት የጌታችን ዐይኖች ተገለጡ ‹‹እንደፍጡር ትገንዙኛላችሁን? በሉ እንዲህ እያላችሁ ገንዙኝ፤ ቅዱስ እግዚአብሔር፤
ቅዱስ ኃያል፤ ቅዱስ ሕያው›› አላቸው፡፡

ደርሳ አዘነች፤ ተከዘች፤ አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ሞት ከእኔ ይለፍ አልኩ፡፡ ይህም
ሰይጣን እነዚህን የትሕትና ቃሎች ሰምቶ በአሳቡ ይህ እንደማንም ሰው ነው፤ እውጠዋለሁ (እቆራኘዋለሁ) አለ፡፡ አባቶች ነብያትን እነ አብርሃምን፣ ይሥሐቅን፣ ያዕቆብን እንደዋጥኳቸው (እንደተቆራኘኋቸው) ይህንንም እውጠዋለሁ
(እቆራኘዋለሁ) እንደሚፈራ ሰው አየዋለሁና አለ፡፡ እነሆ እንግዲህ እንደ ዕሩቅ ብእሲ መስየው ዋጠኝ (እቆራኘዋለሁ አለ)፤ ቃጣ፤ ግን በሆዱ አምላክ ሆኜ አገኘኝ፡፡ እርሱም እየተገዛ በሥጋ የተሸለመ (ሥጋን የተዋሐደ) መለኰቴን ዋጠ (ሊቆራኝ ቃጣ)፤ ግን የማይጠፋ የመለኰት ፍም ሆኖ አገኘው፤ ነገር ግን ውስጡን አቃጠለው፤ እንደ ተጻፈ ለዓለም እሳት አምጥቻለሁና፡፡
አባት ሆይ ይቺ ጽዋ ሞት ከእኔ ትለፍ ብዬ የተናገርኩት የተሳለ የመለኰትን ሰይፍ
እንደማላሳየው ሆኜ የበግ ጠቦት ያየ ጅብ (ዲያብሎስ) እንዳይሸሽ እንደ በግ ጠቦት ሆንኩለት፡፡ እንደ በግ ጠቦትም ይውጠኛል፤ ሦስት አፍ በሆነ ሰይፍ ከውስጡ ታረደ፤ ተቆረጠ፤ ሰላምን ልሰጥ አልመጣሁምና ሰይፍን እንጂ ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ ያልኩት አነጋገሬ በጠቦት በተመሰለው ሥጋዬ ሁሉን የሚጠብቅ መለኰቴን ሸሸግሁት፤ በምናገረው ጊዜ ጅብ (ዲያብሎስ) እንዳይሸሽ ጠባቂውን መለኰቴን እገልጸው ዘንድ አልወደድኩም፤ ጠባቂ እንደሌለው በግና ረዳት እንደሌለው ሰው ሆንኩ ተብሎ እንደተጻፈ ጠባቂ እንደሌለው በግ ሆንኩ፡፡ እንደ ጠቦት ይውጠኛል፤
ከእረኛውም የተነሣ በውስጡ በመስቀል ፍላጻዎች ይነደፋል፡፡ የሰናፍጭ ቅንጣት ያላምጣል፤ በውስጡም የምታጠርሰውና የምትመረው መለኰታዊ ግብር ሆና አገኛት፡፡ እንደ ዕሩቅ ብእሲ ያላምጠኛል፤ በውስጡም ጥርሶቹን የምትሰብር የጸናሁ ዓለት ሆኜ ያገኘኛል፤ ከዛሬ ጀምሮ ሰውን እንዳያላምጥ ያውቅ ዘንድ፤ አምላክ ጥርሶቹን በአፉ ውስጥ ይሰብራልና ያለውም ጽሑፍ ደረሰ ተፈጸመ፡፡…
በዋጠኝ ጊዜ ወድያውኑ ታውቆኛልና፡፡ ስለ እኔ ባየ ጊዜ ፀሐይ ፈጽሞ ጠፋ፤ ቀኑ ሌሊት ሆነ፡፡ ያን ጊዜም መረረው፤ በበታቹ ሲዖል በተገናኘችው ጊዜ መረረች (ደነገጠች) የሚል ጽሑፍ አለና፡፡…
ደግሞ ይህን ቃል ለሚሰሙ ሁሉ እንደ ደካማ እንደ ሆንኩ ይመስላቸዋል፤ የእግዚአብሔር ድካም ከሰው እንዲበረታ አላወቁምና፡፡ እኔ ጽዋውን በጠጣሁ ጊዜ እርሱ ሰይጣን ሰክሮ እንዲጠወልግ ወገኖች ነቅተው አስተዋዮች እንዲሆን አላስተዋሉም፡፡ የትሕትና ቃሎቼን በሚሰማ ጊዜ ደስ ይሏል፤ በሚውጠኝ ጊዜ ግን አፉ ሲሰነጠቅ፣ መቃብሮች ሲከፈቱ፣ ሙታኖች ሲነሡ ያያል፡፡ ያን ጊዜ በሰማይ ተድላ ደስታ ይሆናል፤ ያን ጊዜ ሰይጣን ያዝናል፤ ስለ እነዚህ የትሕትና ቃሎቼ
በእነርሱ በመጠመዱ ያጸጸታል፤ በአጠመዳት ወጥመድም እንደተጠመደ ያውቃል፡፡ ጕድጓድ ቆፈረ፤ በቆፈረውም ጕድጓድ ይወድቃል፡፡ ደክሞ የሠራው ክፉ ሥራው በራሱ ይመለሳል፤ የሠራትም ዐመፅ በራሱ ላይ ትወርዳለች ተብሎ
እንደተጻፈ፡፡
ለእኔ ያስተከለው መስቀል የሰርግ ቤት እንደ ሆነች፤ ለእርሱ መሰቀያ መጥፊያ እንደሆነው ለእኔ ደስ መሰኛ ለእርሱ መሞቻ እንደሆነው አላወቀም…
አባት ሆይ ሰምተኸኛልና አመሰግነሃለሁ፤ ሁል ጊዜም በየጊዜው እንደምትሰማኝ አውቃለሁ እያልኩ ስናገር ልምሾ የሆነ ሰይጣን በሰማኝ ጊዜ አወቀ፡፡
አሁንም የሞት ጽዋ ታልፍ ዘንድ ጸልያለሁና ይህች ጽዋ ታልፍ ዘንድ ስለ ሞት የተደረገ ጸሎት እንዳይመስልህ፤ ከዚያም ወደ መስቀል መውጣትን ቸል ያልኩእንዳይመስልህ፤ ሞትም እንድትመጣልኝ ስጸልይ አባቴ የእኔ ፈቃድ ያይደለ
የአንተ ፈቃድ ይሁን አልኩ፡፡ ነፍሴን ከሥጋዬ ለይቼ ላኖራት ደግሞም አዋሕጄ ላስነሣት ሥልጣን እያለኝ በሞት ሥልጣን ወደ መያዝ ደረስኩ፡፡ መለኮቴን በነገር ሽፋን ሰውሬ የእኔ ፈቃድ ያይደለ ያንተ ያባቴ ፈቃድ ይሁን ብዬ እንደ ሰው
ተናገርኩ፡፡ ዕውረ ልቡና ሰይጣን ግን የእኔ ፈቃድና የአባቴ ፈቃድ አንድ እንደሆነ አያውቅም፤ የአባቴ የሆነ ሁሉ የእኔ ነው ብዬ እንደተናገርኩ አያውቅም፡፡ ዳግመኛም እኔና አብ አንድ ነን እንዳልኩ፤ እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ
እንዳለ ታውቁ ዘንድ አልኩ ያልኩትን፤ አብ በማንም በማን አይፈርድም ፍርዱን ሁሉ ለልጁ ሰጠው እንጂ ብዬ እንደተናገርኩ፤ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ ይገባል ወልድን የማያከብረው ሁሉ የላከው አብን አያከብረውም እንዳልኩ፤ አባቴ ሁሉን ሰጠኝ እንዳልኩ ረስቶታል፡፡ እኔ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኬ መጣሁ፤ ሙሴ በምድረበዳ የነሐሱን እባብ እንደ ሰቀለው የሰው ልጅ ክርስቶስ እንዲሁ ይሰቀል ዘንድ አለው ያመነበት ሁሉ እንዳይጠፋ ለዘላለም ሕያው ሆኖ ይኖራል እንጂ እንዳልኩ፤ …የስንዴ ቅንጣት ይሰቀላል፤ በሚውጣትም
ጊዜ ትንታ ሆና ያገኛታል ያልኩትን ቃል ረስቶታል፤ እርሱም በዚች ኃይል ታንቆ ይጠፋል ተሳልቄበታለሁና፡፡
”ብጹዕ የሆነው አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “ነገር እንዳናበዛባችሁ ዝንጋዔ ልብንም እንዳናመጣባችሁ እናጠቃልለው” ይልና፡- “ጌታችን በአጋንንቶቹና በሰይጣን ዲያብሎስ ላይ ተሣለቀባቸው፤ ይህም “በችሎታዬ እሠራለሁ፤
በጥበቤም የአሕዛብን ግንብ አፍርሼ ፍጥረቱን ሁሉ እንደ ጫጩቶች እጨብጠዋለሁ፤ እንደ ወደቀ እንቁላልም አንሥቼ እወስደዋለሁ፤ ተከራክሮ የሚነጥቀኝ የለም” በማለት በትዕቢት ቃሉን ከፍ አድርጎ በመናገር የሚታበይ ሰነፍ ሰይጣንን እንቡዝ ልብ ያደርጓል፡፡ ሰይጣንም ከአጋንንቶቹ ጋራ መሣለቅያ ይሆን ዘንድ አለው፤ እንደዚሁ የሚመኩ ሁሉ አአምሮ እንደሌላቸው ሕፃናት ይሆናሉና፡፡ ስለዚህም የሚሠሩትን አያውቁም ነበር፤ አውቀውስ ቢሆን የክብር ባለቤት ክርስቶስን ባልሰቀሉትም ነበር፡፡…
ስለዚህ አስቀድመን እንደነገርናችሁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈራ አይምሰላችሁ፤ ይቺ ጽዋ ሞት ከእርሱ ታልፍ ዘንድ ስለ ጽዋ ሞት አልጸለየም” በማለት ከማር የጣፈጠውን ትምህርቱ ይጨርሳል፡፡
ከአባቱ ጋር ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ለክርስቶስ ምስጋና እናቀርባለን ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

"አባት ሆይ! ቢቻልስ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ"

[ይህ ጽሑፍ የተወሰደው ዓርብ ሌሊት ስድስት ሰዓት ከሚነበበው ከግብረ ሕማማት መጽሐፍ ነው፡፡ የተጻፈውም በጊዜው ለነበሩ መርቅያናውያንና ማኒያውያን ለተባሉ መናፍቃን ምላሽ ሲሆን በእኛ ዘመን ደግሞ በግልጥ
ለሙስሊም፣ ለይሖዋ ምስክሮችና አውቀውም ይሁን ሳያውቁ (ሎቱ ስብሐትና) ክርስቶስን ዝቅ ዝቅ ለሚያደርጉ ለሌሎች መናፍቃን መልስ የሚሆን ድርሳን (Homily) ነው፡፡]
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስቀድሞ “ይህን ረቂቅ ምክርና ጥልቅ ምሥጢር የማያስተውሉ ጌታ እንዲህ በማለቱ ፈርቶ ነው ይሉታል፡፡ ነገር ግን ወዳጆቼ ሆይ! እኛ ደግመን እንነግራችኋለንና አእምሯቸው ስለ ጠፋባቸው ስለ እነርሱ ዘለፋ ዛሬ
በፊታችሁ እንደ ትልልቆች ያይደሉ አእምሮ እንደሌላቸው ሕፃናት ናቸው ብለን
እንተረጕምላችኋለን” በማለት ይጀምራል፡፡ ቀጥሎም እርሱ ይጠይቅና ጌታ የመለሰለትን መልስ ይነግረናል፡፡
ብጹዕ አባታችን እንዲህ በማለት ጥያቄውን ይቀጥላል፡- “አቤቱ ጌታ ሆይ! ስለ
እኛ መከራ ትቀበል ዘንድ ለምን መጣህ? ለምንስ ለመስቀል ደረስክ? ለምን ወደህ በፈቃድህ ፈራህ? ለምን አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ አልክ? የተገዢን ባሕርይ ገንዘብ ታደርግ ዘንድ ያስገደደህ ሳይኖር አንተ በፈቃድህ የተዋሐድክ አይደለምን? አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ የሞት ጽዋ ከእኔ ይለፍ ብለህ ለምን ትማልዳለህ? ይህንንም ጽዋ ትጠጣው ዘንድ አልተጋህምን? አንተ ራስህ የምጠመቀው ጥምቀት አለኝ፤ እፈጽመውም ዘንድ እተጋለሁ፤ እስከምጠጣውም ድረስ እታወካለሁ ያልክ አይደለምን? ትጠጣው ዘንድ የተሰጠህን ዛሬ ስለምን አልተጋህም? ለምንስ እምቢ አልክ? አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ ለምን አልክ? ስለ እኛ ትሞት ዘንድ እንዳለህ
አላወቅህምን? አንተ የሰው ልጅ ክርስቶስን አብዝተው መከራ ያጸኑበታል፤ ይሰቅሉታል፤ ይገድሉታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል ያልክ አይደለምን? ደቀ መዝሙርህ ጴጥሮስን ይህ በአንተ ላይ እንዲህ ይሆን ዘንድ አይገባም ባለህ
ጊዜ፡- ከኋላዬ ወግድ አንተ ባለጋራ እንቅፋት ሁነህብኛልና የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ብለህ የገሰጽከው አይደለምን? እርሱን ጴጥሮስን የከለከልከውን እንግዲህ ለምን አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ
አልክ? የሚታየውንና የማይታየውን የፈጠርክ አንተ አይደለህምን? ድውያንን በእጅህ ዳስሰህ እንዳዳንህ በሞት ሥጋው የፈረሰውን አልዓዛርን በቃልህ አጽንተህ እንዳስነሣህ፤ የደም ምንጭም የሚፈሣትን በልብስህ ዘርፍ እንዳደረቅክ፤ በአምስት እንጀራ አምስት ሺህ ሰውን እንዳጠገብክ፤ ባሕሩን ነፋሱን ገስጸህ ጸጥ እንደ አደረግህ፤ ሞትንም ደምስሰህ እንደ አጠፋኸው
እናውቃለን፡፡ ዛሬ ሞትን እንደምትፈራ ሁነህ አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይቺ የሞት ጸዋ ከእኔ ትለፍ ለምን ትላለህ? ሞትን የምትፈራ ከሆነ ትንሣኤም ሕይወትም እኔ ነኝ ለምን አልክ? ሕይወትም ትንሣኤም ሞትን አይፈራም፡፡ እንግዲህ የሚቻል
ከሆነ ይቺ የሞት ጽዋ ከእኔ ትለፍ ለምን አልክ?
ገና ሳትፈጥረው አስቀድመህ ሁሉን የምታውቅ ሆይ! አላወቅህምን? ይህ የሞት ጽዋ ከአንተ ማለፉ ይቻል እንደሆነ አይቻልም እንደ ሆነ አስቀድመህ አታውቅምን? ከወልድ በቀር አብን የሚያውቀው የለም እንዴት አልክ? ይህም
ጽዋ ማለፉንና አለማለፉን አታውቅምን? አንተስ ጳውሎስ ከእርሱ የተሠወረ ፍጥረት የለም፤ ሁሉም በፊቱ ፈጽሞ የተገለጠ ነው እንዴት አልክ? …አሁንም እኔ አላውቅም የሚቻል ከሆነ እንግዲህ ጽዋ ከእኔ ይለፈ እንዴት አልክ? በዚህ ቃል
ውስጥ ገና ያልተገለጸ ሥውር ምሥጢር ቢኖርበትም ይህ ነገር አቤቱ ላንተ አይገባህም፡፡ አንተ የአምላክ ልጅ አምላክ ነህ፤ የእግዚአብሔር አብ ቃል ነህ፤ ጥበብና ኃይል ነህ፤ ጸዳልና ብርሃን ነህ፤ የእውነት ፀሐይ ነህ፤ በኃጢአት ለሞትን
ለእኛ የትንሣኤያችንና የሕይወታችን ምንጭ ነህ፡፡”
ብጹዕ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህ “አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ” የሚለው ቃል “እንደማይታይና እንደማይመረመር እንደ መለኰትና እንደ ትስብእት ተዋሕዶ ይመስላል፤ ስለዚህም ይህች ምሥጢር ለብዙዎች ጭንቅና
ጠባብ መንገድ ሆነች” በማለት “ኢየሱስ ፈርቶ ይህን ቃል ተናግሮታል” የሚሉትን መናፍቃን ይገስጻል፡፡ ከዚያም ጌታ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ለማስረዳት እርሱ በጌታ ተገብቶ (ለንግግር ያመች ዘንድ) ይመልስልናል፡፡ እንዲህም ይላል፡- “ጥበብ ለራስዋ ቤትን ሠራች ተብሎ እንደተጻፈ ራሴ የተዋሐድኩትን ሥጋ እንደፈጠርኩ፤ በሞት የደከመ ሥጋዬን ሕያው አድርጌ ማሥነሣት እንደምችል፡- አይሁድ እናንተ ግብዞች ሰነፎች ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛው ቀን አነሣዋለሁ ብያቸው ነበርና፤ አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ሞት ከእኔ ይለፍ ያልኩት ሞትን በመፍራትና በመደንገጥ እዳልሆነ ለራስህ እወቅ፤ ተጠንቀቅ፤ ይህ ሥውር የሆነ የምሥጢር ቃል ነው እንጂ፡፡ ይህንንም ልመና እኔ በጥበብ ተናገርኩ፡፡ ይህች ቃል ሰይጣንን ጠብቃ የምታጠምድ ወጥመድ ናት፤ በእነዚህም ቃሎች ሰይጣን አጠምደው ዘንድ አለኝና፡፡
ተአምራትን እንዳደረግሁ፣ በሽተኞችን በእጄ ዳስሼ እንዳዳንኩ፣ አጋንንትም በቃሌ እንዳባረርኩ፣ የሸተተ በድን እንዳስነሣሁ፣ ባሕሩን ነፋሱን እንደገሠፅኩ፣ እነርሱም በመፍራትና በመንቀጥቀጥ እንደታዘዙልኝ ሰይጣን አይቶኝ ነበር፡፡ ያደረግሁትን ይህን ተአምራት አይቶ እኔ የአምላክ ልጅ እንደሆንኩ አውቆ እኔም ብሰቀል እርሱ እንደሚጠፋ ወደ ሲዖልም ብወርድ የብረቱን መቆለፍያ ቀጥቅጬ እንደማጠፋ የብረቱን የናሐሱን መዝጊያ ሰብሬ ሁሉን ወደ ሰማይ እንደማሳርግ ልብ ብሎ አስተውሎ ፈርቶ እንዳሸሽ፣ እንዳይጠፋ፣ በመስቀል የሚደረገው
ምሥጢረ ድኅነት እንዳይቀር እንዳይቋረጥ ምን ላድርግ? አልኩ፡፡ ስለዚህ ራሴን ብልህ እንዳጠመደው ወጥመድ አድርጌ ፈርቶ ከሞት እንደሚደነግጥም አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ከእኔ ይለፍ አልኩ፡፡ በእነዚህም የትሕትና ቃሎቼ ዕሩቅ ብእሲ (ሰው ብቻ) እመስለዋለሁ፤ ምሥጢረ ድኅነት የሚፈጸምበት መስቀል በምድር መካከል ይተከል ዘንድ ይቸኩላል፤ በእኔ ላይ የሚጠበብብኝ እየመሰለው እኔ ግን ለሰው ሁሉ ድኅነት ከእርሱ የሚደረግብኝ ሁሉ እታገሥ ዘንድ
አለኝ፡፡እርሱ የመጀመርያውን ሰው አዳምን ያጠፋው ዘንድ እጅግ ተተንኩሎ ተጠብቦበት ነበር፡፡ በተንኰል አነጋገር አዳምን እንደ ተጠበበበት እንግዲህ እኔ ሁሉን ለማዳን በይበልጥ ለምን አልጠበብበት? እንደዚሁ እኔም እርሱ ባመጣው ተንኰል ላጠምደው ትሕትናን በተመሉ ቃሎች ተጠበብኩበት፡፡ በመለኰታዊ
አነጋገርም ለሰይጣን አልተገለጽኩለትም፤ አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህ ጽዋ ሞት ከእኔ ይለፍ አልኩ እንጂ፡፡
ዓሣ አጥማጅ መቃጥኑን በመብል ሸፍኖ ወደ ባሕር ውስጥ በሚጥለው ጊዜ ሲስበው ለዓሣው እንደሚያስጐመጀው አንድ ጊዜም ሊጐርሰው ጕረሮውን እንደሚከፍት እንዲሁም እኔ መለኰቴን መብል አድርጌ ጣልኩለት፡፡ ለዘላለሙ
በማትመረመር ተዋሕዶ በሥጋዬ ውስጥ ያለ የመለኰት መቃጥንን ጣልኩለት፡፡
በሚያጠምድበት ላይ የተደረገው የሚጐረስ ትል (ወላፍ) ካልተንቀሳቀሰ ዓሣው መንጠቆውን ለመጕረስ አይጐመጅም፡፡ ስለዚህ ሥጋዬን እንደሚጐረስ (ወላፍ) ትል አድርጌ አሳየሁት፡፡ እኔ ሰው ያይደለሁ ትል ነኝ አልኩ፡፡ ይህን ሰምቶ በዚህ
በሥጋዬ ውስጥ ያለችን መቃጥን ሩጦ ሂዶ ይጐርስ ዘንድ፡፡እኔም በመቃጥኔ እስበዋለሁ፤ በኢዮብ መጽሐፍ ከይሲን በወጥመድ ትስበዋለህ ተብሎ የተጻፈውን ይፈጸም ዘንድ፡፡እኔም ፈርቶ እንደሚሸሽ ሰው ሆኜ ነፍሴ እስከ ሞት..

#የሰሙነ_ሕማማት_ዓርብ

ዕለተ ዓርብ በቤተክርስቲያን ልዩ ቀን ነው፡፡ የማይታመመው ታሞ የዋለበት፣ የወደቁ ከተረሱበት ከትቢያ የሚያነሳ እሱ ሲወድቅ ሲነሳ የዋለበት፣ ሕመምተኞችን የሚፈውስ እሱ ሲያቃስት የዋለበት፣ ከሲኦል የዲያብሎስ ግብር ነፃ የሚያወጣ ሲገረፍ የዋለበት፣ ወልደ እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ድኅነት በመስዋዕትነት ሙሽራ የሆነበት የደስታ ቀን፤ አሳዳጅ አሳሪያችን ዲያብሎስ ከነወጥመዱ ድል የተነሳበት ቀን ነው። ከዚህም የተነሳ በቤተክርስቲያን የተለያየ ምስጢራዊ ስያሜዎች ተሰጥቶታል፡፡

#የስቅለት_ዓርብ ይባላል
የዓለም ሁሉ መድኀኒት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ለዓለ ድኅነት መስዋዕት ሆኖ የዋለበት ዕለት በመሆኑ የስቅለት ዓርብ ተብሏል። (ማቴ 27፡35)

#መልካሙ_ዓርብ ይባላል
ይህም የሚያስገነዝበን ከስቅለተ ክርስቶስ በፊት ማንም ሰው ሲያጠፋ በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት ይደረግ ነበር፡፡ በተለይ በሮማውያንና በፈሪሳውያን ሕግ መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ነበረ። በዚህ ዕለት ግን ታሪክን የሚቀይር ነገርን የሚገለብጠው አምላክ የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል በደሙ ቀድሶ የምህረት ምልክት፣ የሕይወት አርአያ፣ የዲያብሎስ ድል መንሻ ፣ የቤተክርስቲያን ጌጥ፣ የገዳማት ዘውድ ስላደረገውና በዕለተ ዓርብ በሞቱ ሕይወትን ስላገኘን መልካሙ ዓርብ ተብሏል፡፡

በዚህ ዕለትም ጌታ ሁሉ ተፈጸመ ብሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ስጋው በራሱ ፈቃድ ከለየ በኋላ አምላክነቱን ለመግለፅ ተአምራት አሳይቷል፦
1. ፀሐይ ጨልማለች
2. ጨረቃ ደም ሆናለች
3. ከዋክብት ረግፈዋል
4. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀዷል
5. ምድር ተናወጣለች (ተንቀጥቅጣለች)
6. መቃብሮች ተከፍተዋል
7. ሙታን ተነስተዋል

በዓመት አንድ ጊዜ የምናገኘው ይህ ዕለት ቀራንዮን የምናስብበት ነገረ መስቀሉን የምናስተውልበት እንጂ ስለምድራዊ ኑሮአችን ስንባክን የምንውልበትና በዋዛ ፈዛዛ ልናሳልፈው አይገባም፡፡

#የሰሙነ_ህማማት_ሐሙስ

#ጸሎተ_ሐሙስ
በቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ስያሜዎች ያሏቸው በርካታ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ዕለት ነውና ጸሎተ ሐሙስ ይባላል፡፡ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋሐደ አምላክ፣ መሆኑን ለመግለጥና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ ያደረበት ነውና ጸሎተ ሐሙስ ተባለ፡፡ (ማቴ. 26፥36-46 ዮሐ.17)

#ሕፅበተ_ሐሙስ_ይባላል፡-
ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀመዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ ይህም የሚያሳየው የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ካህናት በተለይም ሊቃነ ጳጳሳት፣ የደብር አስተዳዳሪዎች፤ «በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝብህን ኃጢአት እጠብ እኛም የአንተን አርአያ አንዘነጋም የሌላውን እግር እናጥባለን፤» ሲሉ በቤተ ክርስቲያን የተገኙትን ምእመናንን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ያጥባሉ፡፡

#የምስጢር_ቀን_ይባላል፡-
ከሰባቱ ምስጢራት አንዱ በዚህ ዕለት ተመሥርቷልና፡፡ ይኸውም «ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው፡፡ እንካችሁ ብሉ» ጽዋውንም አንስቶ አመሰገነ «ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱም ጠጡ» በማለት፤ እኛ ከእርሱ ጋር፣ እርሱ ከእኛ ጋር አንድ የምንሆንበትን ምስጢር ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ፣ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ሥያሜ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል ይዘጋጃል፡፡

#የሐዲስ_ኪዳን_ሐሙስ_ይባላል፡-
ምክንያቱም መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ «ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን ሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ ከእርሱ ጠጡ» በማለቱ ይታወቃል (ሉቃ. 22፥20) ኪዳን ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓለማዊውን ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት ስለሆነ የሐዲስ ኪዳስ ሐሙስ ተባለ፡፡

#የነጻነት_ሐሙስ_ይባላል፡-
ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ፣ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ጌታችን ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር «ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም ባርያ ጌታዉ የሚያደርገውን አያውቅምና ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ» በማለት (ዮሐ. 15፥15)፤ ከባርነት የወጣንበት ልጆች የተባልንበትን ቀን የምናስብበት በመሆኑ ሊቃውንቱ የነጻነት ሐሙስ አሉት፡፡ እያንዳንዱ ክርስቲያንም ከኃጢአት ባርነት ርቆ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወቱን መምራት ይኖርባታል፡፡ ባሮች አልላችሁም ተብለናልና፡፡

#የሰሙነ_ሕማማት_ረቡዕ

#ምክረ_አይሁድ_ይባላል
ምክንያቱም የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚገባቸው ምክር ያጠናቀቁበት ቀን ነውና፡፡ በዚህ ምክራቸው ላይ በጣም ትልቅ ጭንቀት ነበር፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ የፋሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት ቀን የተቃረበ በመሆኑ ብዙው ሕዝብም በጌታችን ትምህርት የተማረኩ ተአምራቱንም የሚያደንቁ ስለ ነበር ሁከት እንዳይፈጠር ነው፡፡ በዚህ ጭንቀት ሳሉ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ በመካከላቸው በመገኘት የምክራቸው ተባባሪ ሆኖ ጭንቀታቸውን አስወግዶላቸዋል፡፡ (ማቴ. 26÷1-14፣ ማር. 14÷1-2፣ ሉቃ. 22÷1-6) የሐዲስ ኪዳን ካህናትና ምእመናን በዚሁ ዕለት በቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው መላ ሰውነታቸውን ለእግዚአብሔር አስገዝተው የሞት ፍርዱን በማሰብና በማልቀስ ሐዋርያት ከጌታችን መያዝ በኋላ በኀዘን በፍርሐት እንደነበሩ እያሰቡ መጻሕፍትን በማንበብ በጾም በጸሎትና በስግደት ተወስነው ይቆዩና ከአሥራ ሁለት ሰዓት በኋላ ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡

#የመልካም_መዓዛ_ቀንም_ይባላል
ምክንያቱም ጌታችን በዚህ ዕለት በቤተ ስምዖን ዘለምጽ ተቀምጦ ሳለ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት (ባለሽቱዋ ማርያም) "ከእንግዲህ ወዲህ በኃጢአት ተበላሽቶ ይኖር የነበረውን ሕይወቴን እንደዚህ መልካም ሽቱ የሚያጣፍጥ ኃጢአትን ይቅር የሚል አምላክ መጣ" ስትል ዋጋው እጅግ በጣም ውድ የሆነ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ የሚያወጣ በአልባስጥሮስ ብልቃጥ የተሞላ ሽቱ ይዛ በመሔድ በጠጉሩ (በራሱ) ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባችው ረቡዕ የመዓዛ ቀን ይባላል፡፡

#የእንባ_ቀንም_ይባላል
ማርያም እንተ እፍረት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ መላ ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት በእንባዋ እግሩን አጥባዋለችና በጠጉሯም በእንባዋ ያጠበችውን እግሩን አብሳዋለችና። (ማቴ. 26÷6-13፣ ማር. 14÷9፣ ዮሐ. 12÷8) ኃጢአትን በማሰብ ማልቀስና ራስን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ማቅረብን ከምታስተምረን ማርያም እንተ እፍረት እንባን ለንስሐ ሕይወት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

የሰሙነ ሕማማት ማክሰኞ

#የጥያቄ_ቀን_ይባላል፡-

ሰኞ ባደረገው አንጽሖተ ቤተመቅደስ ምክንያት፣ ሹመትን ወይም ሥልጣንን ለሰው ልጅ የሰጠ ጌታችን፣ ስለ ሥልጣኑ በጸሐፍት ፈሪሳውያን ተጠይቋልና፤ የጥያቄ ቀን ይባላል፡፡

ጥያቄውም ከምድራውያን ነገሥታት፣ ከሌዋውያን ካህናት ያይደለህ ትምህርት ማስተማር፣ ተዓምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን፣ በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ? የሚል ነበር፡፡ /ማቴ. 21፥23-27፣ ማር. 11፥ 7-35፣ ሉቃ.21፥23-27፣ ማር.11፥27-33፣ ሉቃ. 20፥1-8/፤ እርሱም ሲመልስ፤ «እኔም አንድ ነገር እጠይቃችኋለሁ፣ እናንተም ብትነግሩኝ በማን ሥልጣን እነዚህን እዳደርግ እነግራችኋለሁ፡፡ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረ፣ ከሰማይ ነውን? ወይስ ከሰዉ? በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ ወይስ በሰው ፈቃድ?» አላቸው፡፡ እነርሱም ከሰማይ ብንል ለምን አልተቀበላችሁትም ይለናል፤ ከሰው ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስን እንደ አባት ያከብሩታል፣ እንደ መምህርነቱ ይፈሩታልና ሕዝቡን እንፈራለን፤ ተባብለው ከወዴት እንደሆነ አናውቅም ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም አላቸው» ይህንንም መጠየቃቸው እርሱ የሚያደርጋቸውን ሁሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተዉት አልነበረም፣ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ እንጂ፡፡

#የትምህርት_ቀንም_ይባላል፡-

በማቴ. 21፥28፣ ማቴ. 25፥46፣ ማር.12፥2፣ ማር.13፥37፣ ሉቃ. 20፥9፣ ሉቃ. 21፥38 የሚገኙት ትምህርቶች ሁሉም የማክሰኞ ትምህርት ይባላሉ፡፡ በዚህ ዕለት በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረ፣ የትምህርት ቀን ይባላል፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ከሥጋዊ ነገር ርቆ በዚህ ሰሞን የሃይማኖት ትምህርት ሲማር ሲጠይቅ መሰንበቱም መጽሐፋዊ ሥርዓት ነው፡፡

የሰሙነ ሕማማት ሰኞ፡-

#መርገመ_በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፡

ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሆሣዕና ዕለት ቢታንያ አድሮ በማግሥቱም ከቢታኒያ ሲመጡ ተራበ፡፡ (ማር.11፤11-12) ቅጠል ያላት በለስ ከሩቅ አይቶ ወደ በለሲቱ ቀረበ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር አንዳች ፍሬ አላገኘባትም፡፡ ከአሁን ጀምሮ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ ብሎ ረገማት። በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ናት፤ ፍሬ የተባለች ሃይማኖትና ምግባር ናት፤ ከእስራኤል ፍቅርን፤ ሃይማኖትን፤ ምግባርን ፈለገ አላገኘም፤ እስራኤል (ሕዝበ እግዚአብሔር) መባልን እንጂ፤ ደግ ሰው አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፤ በመርገሙ ምክንያት እርሱ ከለያቸው በስተቀር ደግ ሰው ጠፋባት፡፡

በለስ ኦሪት ናት፤ ኦሪትን በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛት ኦሪትና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ በማለት ፈጸማት፤ ሕገ ኦሪትን ከመፈጸም በቀር በእርሷ ድኅነት አላደረገባትምና፤ ፍሬ በአንቺ አይሁን አላት፤ ደኅነት በአንቺ አይደረግብሽ ብሏታልና እንደመድረቅ ፈጥና አለፈች፡፡

በለስ ኃጢአት ናት፤ የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነች ሁሉ ኃጢአት በዚህ ዓለም ሰፍታ ሰፍና አገኛት፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል፤ ቆይቶ ግን ይመራል፤ ኃጢአትም ሲሰሩት ደስ ደስ ያሰኛል፤ ኋላ ግን ያሳዝናል፤ ወደ እርሷም ሄዶ ማለትም ከኃጥአን ጋር ዋለ፤ ኃጥእ ከመባል በቀር በአንደበቱ ሐሰት፤ በሰውነቱ ክፋት እንዳልተገኘበት ለማመልከት ፍሬ አላገኘባትም አለ፤ በአንቺ ፍሬ አይገኝ የሚለውም፤ በኃጢአት ፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር ለማለት ነው፤ ስትረገም ፈጥና መድረቋም፣ በአዳም ምክንያት ያገኘችን ዕዳ በደል በእርሱ ካሣነት እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው፡፡

#አንጽሆተ_ቤተ_መቅደስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፦

ጌታችን በለስን ከረገማት በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፤ ቤተ መቅደስ፣ ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምስያጥ (የንግድ ቤት) ሆኖ ቢያገኘው ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች፤ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸው፤ ገርፎም አስወጣቸው፤ ይህም የሚያሳየው ማደሪያው ቤቱ የነበርን የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢአታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡

በዚህ በሰሙነ ሕማማት ካህናትና ምእመናን በቤተክርስቲያን ተገኝተው ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ በነግህ፤ በሠለስተ፣ በስድስቱ ሰዓት፤ በተሰዓቱ ሰዓትና በሠርክ መላልሰው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፤ በተለይም ካህናት በማንኛውም አገልግሎት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፤ ምክንያቱም የደረሰብን መከራ ኀዘኑን እና 5ሺ ከ5መቶ ዘመን የሰው ልጅ በጨለማ ይኖር እንደነበረ ለማዘከር ነው፡፡

#ሰሙነ_ሕማማት

ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ሰሙነ ሕማማት የጾመ ሁዳዴ የመጨረሻው ሳምንት፤ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማም የሚታሰብበት፤ ካህናትና ምእመናን በአጸደ ቤተክርስቲያን ተሰብስበው የሕማሙን ነገር የሚያወሳውን ዜማ የሚያዜሙበት፤ ግብረ ሕማም በመባል የሚታወቀውን መጽፍ የሚያነቡበትና የሚሰሙበት፤ በነግህ፣ በሠልስት፣ በስድስት፣ በተሰዓት /ዘጠኝ /ሰዓት፣ በሰርክ /በዐስራ አንድ/ ሰዓት እየመላለሱ የሚሰግዱበትና የሚጸለዩበት ልዩ ሳምንት ነው ከሆሳዕና ማግስት እስከ ትንሳኤ።

በዚህ ሳምንት በተለይ ካህናት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ ምክንያቱም ጌታችን የደረሰበትን መከራና ስቃይ እንዲሁም የሰው ልጅ ፭ ሺ ፭ መቶ ዘመን በጨለማ ግዞት ይኖር እንደነበር ለማዘከርም ጭምር ነው። የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን መከራና ሕማም በጽኑ እንድናስበው ያስተማሩን ሐዋርያት ናቸው። ለእነርሱም የነገራቸው ደግሞ ራሱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

ሰሙነ ሕማማት የጌታችንን ሕማማት ከማሰብ ጋር በየዕለቱ በርካታ ድርጊቶች መፈጸማቸውን የምናስታውስበት ሳምንት ነው፦

#ሰኞ
#መርገመ_በለስ_የተፈጸመበት_ሰኞ_ይባላል፦
በዚህ ዕለት ጌታችን ከቢታኒያ ሲወጣ ተራበ ቅጠል ያለባትን በለስ ተመልክቶ ወደ በለሲቱ ቢቀርብ ከቅጠል በቀር ምንም ነገር ባለማግኘቱ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ምንም ካንቺ ፍሬ አይበላ” ማር ፲፩፥፲፬ በማለት ስለረገማት መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል።

#አንጽሖተ_ቤተ_መቅደስ_ይባላል፡-
ጌታ ወደ ቤተመቅደስ ሄዶ በቤተመቅደሱ የሚሸጡትን እና የሚለውጡትን “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች” ማቴ ፳፩፥፲፫ በማለት ከቤተመቅደስ ገርፎ አስወጥቷቸዋልና።

#ማክሰኞ
#የጥያቄ_ቀን_ይባላል፦
ሰኞ ዕለት በቤተመቅደስ ሲሸጡ እና ሲለውጡ የነበሩትን ሁሉ እየገረፈ በማባረሩ ምክንያት ለሰው ልጅ ሹመትንና ስልጣንን የሰጠ ጌታ “በምን ስልጣን ይህንን ታደርጋለህ?” ማቴ ፳፩፥ ፳፫ ተብሎ በፈሪሳውያን ተጠይቋልና የጥያቄ ቀን ይባላል።

#የትምህርት_ቀን_ይባላል፡-
በዚህ ዕለት በቤተመቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረም የትምህርት ቀን ይባላል። ሉቃ ፳፩ ፥፳፰ ፣ ማር ፲፪፥፪።

#ረቡዕ
#ምክረ_አይሁድ_ይባላል፦
ረቡዕ እለት የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንዳለባቸው የመከሩበትና ውሳኔ ያሳለፉበት ቀን በመሆኑ ምክረ አይሁድ ይባላል። ወቅቱ የፋሲካን በዓል የሚያከብሩበት ቀን በመሆኑ እና ብዙ ህዝብም ጌታን ይከተለው ስለነበር ሁከት እንዳይነሳ ስጋት ነበራቸው ። ነገር ግን ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ስለነገራቸው ሉቃ ፳፪፥፩-፮ ጭንቀታቸው ተወግዶ በጌታ መያዝ ተስማምተዋል።

#የመልካም_መዓዛ_ቀንም_ይባላል፡-
ጌታችን በዚህ ዕለት በለምጻሙ በሰምዖን ቤት ተቀምጦ ሳለ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት/ባለሽቶዋ ማርያም/ ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ የአልባጥሮስ ሽቱ አምጥታ በራሱ ላይ በማርከፍከፍ ስለቀባቸው ማቴ ፳፮፥፮-፯ የመዓዛ ቀን ይባላል።

#የእንባ_ቀን_ይባላል፡-
ባለሽቱዋ ሴት (ማርያም እንተ እፍረት) ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት እየለመነች በእግሩ ስር ተደፍታ በእንባዋ እግሩን አርሳለችና ማር ፲፬፥፱ የእንባ ቀን ይባላል።

#ሐሙስ
#ጸሎተ_ሐሙስ_ይባላል፦
ጌታችን ለአይሁድ ተላልፎ ከመሰጠቱ በፊት በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሲጸልይ በማደሩ ማቴ ፳፮፥፴፮ ጸሎተ ሐሙስ ይባላል።ጌታችን የደቀመዛሙርቱን እግር በፍጹም ትህትና ዝቅ ብሎ ያጠበበት ዕለት በመሆኑም ዮሐ ፲፫፥፫-፲፩ ሕጽበተ ሐሙስ ይባላል።

#የምስጢር_ቀን_ይባላል፡-
ከሰባቱ ምስጢራት አንዱ የቅዱስ ቁርባን ምስጢር ማቴ፳፮፥፳፮-፳፱ በዚህ ዕለት ተፈጽሟልና የምስጢር ቀን ይባላል።

#የሐዲስ_ኪዳን_ሐሙስ_ይባላል፡-
መሥዋዕተ ኦሪት /በእንስሳት ደም የሚቀርብ መሥዋዕት/ቀርቶ ለአለም ድኅነት ራሱን ያቀረበበት ቀን በመሆኑ ሉቃ ፳፪፥፳ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል።

#የነጻነት_ሐሙስ_ይባላል፡-
ለኃጢአትና ለዲያቢሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱን እንዲሁም የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነም ዮሐ ፲፭፥ ፲፭ የነጻነት ሐሙስ ይባላል።

#ዓርብ
#የስቅለት_ዓርብ_ይባላል፦
ጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ የዋለበት ዕለት ነውና ማቴ ፳፯፥፴፭ የስቅለት ዓርብ ይባላል።

#መልካሙ_ዓርብ_ይባላል፡-
ከጌታ ስቅለት በፊት በተለይም በሮማውያን ህግ የወንጀለኛ መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል ጌታችን በደሙ ቀድሶ የምህረት፣ የሕይወት አርማ፣ የዲያቢሎስ ድል መንሻ ስላደረገው፤ በሞቱ መልካሙን ሕይወት ስላገኘን መልካሙ ዓርብ ይባላል።

#ቅዳሜ
#ቀዳም_ስዑር_ትባላለች ፦
ይህች እለት ከድሮ በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል የተሻረች ቅዳሜ ይባላል።

#ለምለም_ቅዳሜ_ይባላል፡-
ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት በመሆኑም ለምለም ቅዳሜ ይባላል። ምዕመናንም ይህንን ለምለም ቀጤማ እስከ ትንሣኤ ለሊት በራሳቸው ላይ ያስሩታል።

#ቅዱስ_ቅዳሜ_ይባላል፡-
ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ያረፈበት ቀን ሲሆን በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ስራውን ሁሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ በነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዶ ሲኦልን በርብሮ ባዶዋን ሲያስቀራት በዚያ የነበሩትን ነፍሳት የዘላለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለሆነ ቅዱስ ቅዳሜ ይባላል።

(ስምዐ ጽድቅ መጋቢት ፳፻፪ ዓ.ም)