✥ ጥር ፲፰ ዕለት ለሰማዕቱ "ዝርወተ አጽሙ " ትባላለች:: በቁሙ አጥንቱ የተበተነበት እንደ ማለት ነው።
" ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም ናቁ ስለ መንግሥተ ሠማያትም መራራ ሞትን ታገሡ። " እንደተባለ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዘመናት በብዙ ስቃያት ሲያስጨንቁት ኖረው በጽናቱ አሸነፋቸው:: 70 ነገሥታትን ከነ ሠራዊታቸው ከማሳፈሩ ባሻገርም በርካታ (በመቶ ሺ የሚቆጠሩ) አሕዛብን ማርኮ ለሰማዕትነት አበቃ::
✥ በዚህ የተበሳጨ ዱድያኖስም ኮከበ ፋርስ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲቆራርጡት አዘዘ:: ወታደሮቹም ቅዱሱን ቆራርጠው በብረት ምጣድ ላይ ጠበሱት። ያለ ርሕራሔም አካሉን ኣሳረሩት። ቀጥለውም ፈጭተው ዐመድ አደረጉት። በኣካባቢው ወደ ነበረው ትልቅ ተራራ ጫፍ (ደብረ ይድራስ) ወጥተውም በነፋስ በተኑት:: “ሐረድዎ ወገመድዎ ወዘረዉ ሥጋሁ ከመ ዓመድ” እንዲል:: (ምቅናይ)
✥ እነርሱ ይህንን ፈጽመው ዘወር ሲሉ ግን የቅዱሱ ዐጽም ባረፈባቸው ዛፎች: ቅጠሎችና ድንጋዮች ሁሉ “ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት” የሚል ጽሑፍ ተገኘ:: ስለዚህም ይህቺ ዕለት ቅዱሱ አለቅነትን የተሾመባት ናት ማለት ነው:: ወዲያው ግን ኃያል ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተበተነበት ተነስቶ ወታደሮችን አገኛቸውና “በክርስቶስ እመኑ” ብሎ አስደንቆ ወደ ሕይወት መራቸው፣ ፸ ው ነገሥታት ግን አፈሩ። ሰማዕቱ አባታችን እኛንም በሃይማኖት በምግባር ያጽናን ተራዳኢነቱም አይለየን አሜን። 🙏