* * *
ከብዙ ወንዶች ጋር ትወጣለች። "ሴሰኛ" ልትባል የምትችል ናት። ወንድ እየቀያየራች ጭኗን ትከፍትላቸዋለች። ገና በአበባነት ዘመኗ ከብዙዎች ጋር አንሶላ ተጋፋለች። ለፀፀት የሚዳርግ አይነት የወሲብ ህይወት አላት።
ይህች ወጣት እንዲህ ሂያጅ ከመሆኗ በፊት ክብሯት የገረሰሰው የገዛ ወንድሟ ነው። የአባትና የእናቷ ልጅ አስገድዶ አነወራት። ታላቅ ወንድሟ "ያደረግነውን ብትናገሪ እገድልሻለሁ" ብሎ እየዛተ ደጋግሞ ተገናኝቷታል። ብዙ ጊዜ ደፍሯታል።
ልጅት ከዚህ በኋላ ባከነች። ካገኘችው የምትተኛ ሆነች።
ሌላ ታሪክ
ባለትዳር ናት። ከባሏ ጋር ወሲብ ልትፈፅም ስትሞክር መቀመጫዋ አከባቢ ያማታል። ከወገብ በታች ህመም ይሰማታል። ህመሙ ሲባባስባት ወደ ሀኪም ሄደች። ከምርመራ በኋላ "ህመም የለብሽም" ይሏታል። ሀኪሞች በሽታ የለብሽም ቢሏትም ሁሌም ወሲብ ልትፈፅም ስትል ያማታል።
በመጨረሻም አንድ ሃኪም የስነልቦና ባለሞያ ጋር እንድትሄድ መከራት። ያኔ የህመሟ መንስኤ ታወቀ።
ልጅ እያለች በአያቷ ፆታዊ ጥቃት ተፈፅሞባታል። አያቷ በመቀመጫዋ በኩል ፆታዊ ጥቃት አድርሶባታል። ያ ክስተት የአእምሮ ጠባሳ ፈጠረባት። ወሲብ ስትፈፅም የሚያማት ጥቃቱ ባደረሰበት የስነልቦና ህመም የተነሳ ነበር።
ሁለቱ እውነተኛ ታሪኮች "ምን ሆኛለሁ?" በሚለው መፅሐፍ ላይ የሰፈሩ ናቸው።
ሁለቱ ታሪኮች ብዙ ይነግሩናል።
ተጠቂዎቹ ጥቃት የደረሰባቸው በቤተሰባቸው አባል ነው። መከታ እና ከለላ ሊሆኗቸው ከሚገባ ሰው ፆታዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ጉዳቱ ዘመን ዘለል አእምሯዊ ጠባሳ እና ስነልቦናዊ ጉዳት አደርሶባቸዋል።
ሴቶች ሲደፈሩ የሚደርስባቸው ስነልቦናዊ መቃወስ ሳይታከም መቅረቱ ጉዳቱ ለማህበረሰቡ ጭምር ነው። ስነልቦናቸው የተጎዳ ሴቶች እናት ሲሆን ልጆቻቸውን እንዴት ያሳድጉታል?
ሴትን ከጥቃት መጠበቅ ማህበረሰብን መጠበቅ ነው።
አርቲስት እግቱ የጥቃት ሙከራ ከተደረገባት በኋላ በርካታ ሰዎች ተሳልቀውባታል። አንዳንዶች "ይቺን መልከ ጥፉ ማን ይነካታል" የሚል ከነውረኛ አእምሮ የሚፈልቅ መከራከሪያ አቅርበዋል።
ይህ የሚነግረን ነገር አለ።
ሴት ተገዳ እንድትደፈር ቆንጆ መሆን አይጠበቅባትም። ሴት በመሆኗ ብቻ ለጥቃት ተጋላጭ ናት።
ቆንጆ ሚስታቸውን አስቀምጠው የቤት ሰራተኛ የሚደፍሩ አሉ። የጎዳና ተዳዳሪዎች ይደፈራሉ። በልመና የተሰማሩ ይደፈራሉ። የአእምሮ ህሙማን ይደፈራሉ።
ሻሸመኔ የማውቃት የአእምሮ ህመምተኛ ነበረች። አንድ ወቅት አርግዛ አየኋት። ማነው ያስረገዛት? መልሱ ግልፅ ነው።
በዙሪያችሁ ያሉ ሴቶችን ስለፆታዊ ጥቃት ብትጠይቁ ልባችሁ ይሰበራል። ብዙ ሴቶች በተለያየ አጋጣሚ ለጥቃት ተጋልጠዋል።
ህፃናት በአዋቂዎች ይደፈራሉ። ሰራተኞች ከአሰሪዎች ትንኮሳ ይደርስባቸዋል። ደግሞም በቤተሰብ አባል የሚሰነዘር ጥቃትም አለ።
ሐገር የሚወድ ሴትን ከጥቃት ይጠብቅ።
ማህበረሰብን የሚወድ ሴትን ከጥቃት ይጠብቅ።
ራሱን የሚያከብር ወንድ ሴትን ከጥቃት ይጠብቅ።
https://t.me/+9k2KYUWaftM2OGRk