(February/16/25)
የመልዕክት አቅራቢ: ቄስ መንግስቱ ገ/ሚካኤል
የመልዕክት ክፍል:(2ነገ 2:19-22)
ርዕስ: ከእንግዲህ ወዲያ ሞትና ጭንገፋ አይሆንም
መግቢያ: ኤልያስ እና ኤልሳዕን አሁን ከጠቀስነው ክፍል ከፍ ብለን ስናነብ እናገኛቸዋለን። የኤልያስ ወደ ሰማይ ማረግ ለነብያት ልጆች ተገልጦ ነበር። ለኤልሳዕም ሲነግሩት እናያለን። የመነጠቂያው ሰዓት በደረሰ ጊዜ የእሳት ሰረገላ መጣና ሁለቱን ነጠላቸው። በኤልሳዕም ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ ሁለት እጥፍ ሆኖ ወረደበት።
-የኤልሳዕ አገልግሎት የጀመረው ዮርዳኖስን በመክፈል ነበር። ኤልያስ በአገልግሎቱ መጨረሻ ዮርዳኖስን ከፈለ። ኤልሳዕ ግን በአገልግሎቱ መጀመሪያ ዮርዳኖስን ከፈለ። መንፈሱ በእጥፍ በእርሱ ላይ እንዳለ በዚ እንረዳለን።
-ከዚህም ቀጥሎ ነበር የኢያሪኮ ሕዝብ ወደ ኤልሳዕ ተሰብስበው የመጡት። ከተማዋ መልካም ብትሆንም ውኃዋ ግን ክፉ ነበር። ፍሬዎቿም ይጨነግፋሉ።
ጭንገፋ ምን ማለት ነው?
-ጨነገፈ ማለት የማይጠቅም፣ የማይረባ ሆነ ማለት ነው። ዋጋ የተከፈለበትን ነገር ማጣት ማለት ነው። ይህ ከባድ ነገር ነው።
-የኢያሪኮ ከተማ ከተገነባች በኋላ ሀያ ጊዜ እንደፈረሰች ታሪክ ያመለክተናል። ለምን? ያልተሰበረ መርገም ነበረ። ከተማይቱ በሞት እና ጭንገፋ እርግማን ተቸግራ ነበር።
-ለዚህ እርግማን የመጣባቸው ባለመታዘዝ ምክንያት ነበር። ይህ የሆነው ምድር በአዳም እና ኃጥያት ምክንያት የተረገመች ስለነበር ነው። አለመታዘዝ በእርግማን ስር ይጥላል። ነህምያም ኢያሪኮን የሚገነባ ሰው የተረገመ እንዲሆን በሕዝብ ፊት ተናገሮ ነበር።
ይህ ጭንገፋ እንዴት ቆመ?
የእግዚአብሔር ሰው በመካከላቸው ሲገኝ ጭንገፋ እና ሞት ቆመ።
-አዲስ ማሰሮን አስመጣ፣ ጨውንም አድርጎ ውኃው ወዳለበት ምንጭ ጨመረው። ከዛች ደቂቃ ጀምሮ ውኃው ተፈወሰ፣ ጭንገፋ እና ሞት ቆመ። ምደሪቱም ፍሬዋ ተፈወሰ።
-ለእኛም ሰላም ይሆንልናል። ታሪካችንን ይቀይርልናል፣ ሞት ይሰበርልናል፣ መከራ ይሰበርልናል፣ የድሮ መጠሪያችን ይቀየርልናል፣ አይቶ ማጣት ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ሸክም ተሸክሞ መኖር ያበቃል። እግዚአብሔር ዛሬ በሕይወታችን ጣልቃ ይገባልናል። ባደከመን ነገር፣ ከእንግዲህ ምን ቀረን ባልንበት ጉዳይ እርሱ ጣልቃ ይገባልናል!
ማጠቃለያ
እግዚአብሔር ማንንም ፈፅሞ አይጥልም። በጨነገፈብን ነገር እርሱ ጣልቃ ይገባል። ከእንግዲህ ወዲህ ሞት እና ጭንገፋ አይሆንም! አሜን!