በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ብቃት ያለው መምህርና የትምህርት ቤት አመራር መፍጠር ላይ በማተኮር እየተሰራ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ ተናገሩ።
የተማሪዎች ውጤት ማሻሻል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እና ከሆሳዕና ትምህርት ኮሌጅ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አቶ አንተነህ ገልጸዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ በቅድመ 1ኛ እና በ1ኛ ደረጃ የዕጩ መምህራን መመልመያና መረጣ መመሪያ እና በማጠናከሪያ ትምህርት አሰጣጥ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል።
በምክክር መድረኩ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በክልሉ ብቃት ያለው መምህርና የትምህርት ቤት አመራር ለመፍጠር በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል።
ይሁንና በክልሉ በቅድመ 1ኛ እና በ1ኛ ደረጃ ያለው የመምህራን አቅርቦት ከፍላጎት ጋር ሲስተያይ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም በቅድመ 1ኛ ያለው የመምህራን ቁጥር 27 በመቶ ብቻ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ይህን ችግር ለመቅረፍ እየተሰራ ነው ያሉት ኃላፊው በዘንድሮው ዓመት 760 ዕጩ መምህራን በሆሳዕና ትምህርት ኮሌጅ ለማሰልጠን ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
መምህራን ከማብቃት አንጻር ባለፈው ዓመት ለ2ኛ ደረጃ መምህራን ከክልሉ በተጨማሪ በትምህርት ሚንስቴርም ጭምር የአቅም ግምባታ ስልጠና መሰጠቱን አንስተዋል።
በዘንድሮው ዓመት በተለየ መልኩ በ1ኛ ደረጃ ላይ ላሉ በተለይም ለ7ኛ እና 8ኛ ክፍል መምህራንን የአቅም ግምባታ ስልጠና ለመስጠት ይሰራል ብለዋል።
በክልሉ ባለፈው ዓመት ከዩኒቨርሲቲዎች እና ከሆሳዕና ትምህርት ኮሌጅ ጋር በመተባበር ለ12ኛ እና ለ8ኛ ክፍል የተሰጠው የማጠናከሪያ ትምህርት በተማሪዎች ውጤት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል።
ይህንንም በዘንድሮ ዓመት በማስቀጠል 7ኛ እና 11 ክፍል ጨምሮ የማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት ይሰራል ብለዋል።
በክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እና ትምህርት ኮሌጅ ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እና ለመምህራን የአቅም ግምባታ ስልጠና በመስጠት ብሎም በክልሉ የትምህርት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮች በጥናት የተደገፈ ምርምር በማድረግ የመፍትሔ ሀሳቦች በማቅረብ እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።