አሁንም እሞታለሁ፤ ሰው ሞትን ይሸሻል፤ እኔ ግን በደስታ ወደሞት እሄዳለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ህዝብ ታላቅነት ቀድመውኝ መስዋዕት የሆኑትንና አብረውኝ ተነስተው የነበሩትን ጀግኖች ወንድሞቼን ለመገናኝት ናፍቄያለሁ፡፡
የጀመርኩት ስራ ቀላል አይደለም፤ አልተሸነፍኩም፡፡ ወገኔ የሆነው ድሃው የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመርኩለትን ስራ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ፈፅሞ ራሱን በራሱ እንደሚጠቅም አልጠራጠርም፡፡ ከሁሉ በበለጠ የሚያስደስተኝ ለኢትዮጵያ ህዝብ ልሰራለት ካሰብኳቸው ስራዎች አንዱ የኢትዮጵያ ወታደር ዋጋና ክብር ከፍ ማድረግ ሲሆን፤ ይህ ሃሳቤና ፍላጎቴ ህይወቴ ከማለፉ በፊት ሲፈፀም ማየቴ ነው፡፡
ዛሬ መኖራችሁን በማየቴ ነገ መሞታችሁን ረስታችሁ አሜን ብላችሁ ቀናችሁን በማስተላለፍ በመገደዳችሁ፤ በእኔ ላይ ሳትፈርዱ በራሳችሁ ላይ የፈረዳችሁ መሆናችሁን አላስተዋላችሁም፡፡ እኔ የተነሳሁት ከትክክለኛ ህግና ከህሊናችሁ ውጭ ለመፍረድ እንዳትገደዱ ለማድረግ ነበር፡፡ በአጭሩ በእኔ ላይ ለመፍረድ የቸኮላችሁትን ያህል አስርና አስራ አምሰት ዓመት በቀጠሮ የምታጉላሉትን ህዝብ ጉዳይ እንደዚህ አፋጥናችሁ ብትመለከቱለትና ብትሸኙት ኖሮ የእኔ መነሳት ባላስፈለገም ነበር።
ከእናንተ ከዳኞቹ እና የሞት ፍርድ እንድትበይኑብኝ ካዘዛችሁ ሰው ይልቅ፤ እኔ ፍርድ ተቀባይ የዛሬ ወንጀለኛ የነገ ባለታሪክ ነኝ። የኔ ከጓደኞቸ መካከል ለጊዜው በህይወት መቆየትና ለእናንተ ፍርድ መብቃት የዘመኑን ፍርድ ለመጭው ትውልድ የሚያሳይ ይሆናል፡፡
ዋ ! ዋ ! ዋ ! ለእናንተ እና ለገዢአችሁ። የኢትዮጵያ ህዝብ ሃሳቤ በዝርዝር ገብቶት በአንድነት በሚነሳበት ጊዜ የሚወርድባችሁ መዓት አሰቃቂ ይሆናል፡፡
በተለይ የአፄ ኃ/ስላሴ የግፍ መንግስት ባለ አደራዎች ሆነው ድሀውን የኢትዮጵያ ህዝብ ሲገሸልጡት ከነበሩት መኮንን ሀ/ወልድ እና ገ/ወልድ እንግዳወርቅን ከመሳሰሉት በመንፈስ የታሰሩ በስጋ የኮሰሱ መዠገሮች መካከል ጥቂቶቹን ገለል ማድረጌን ሳስታውስና የተረፉትም ፍፃሜያቸውን በሚበድሉት በኢትዮጵያ ህዝብ እጅ ላይ መውደቅ ሲሰማኝ ደስ ይለኛል፡፡