ትንትና ማታ አዳማ አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ኖሮኝ ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ ሄድኹኝና እንዳቀርብበት በተሰጠኝ ርእሰ ጉዳይ በጣም በአጭሩ አቀረብኹኝ። አስቀድመው እዚያው እንዳድር አመቻችተውልኝ ስለ ነበር፤ አድሬ ካደርኹበት ቦታ ሌሊት 11፡30 ተነሥቼ ተዘገጃጀኹና ወጣኹኝ። ካደርኹበት ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ የአዲስ አበባ ሚኒ ባሶች ወዳሉበት መናኸሪያ መሄድ ነበረብኝ። ስለዚህም ኹለት ሰው የያዘ ባለ ባጃጅ ታክሲ እየፈለግኹ መሄዴን ገምቶ መናኸሪያ ነህ አለኝ፤ አዎን አልኹኝ። አቆመልኝ አንደኛው ተሳፋሪ ከባጃጁ ወጥቶ በቅርብ ስለምወርድ ብሎ ከመሐል አስገባኝ። መሐል መግባት ባልወድም እሺ ይኹን ብዬ ገባኹኝ።
ጉዞ ወደ መናኸሪያ ተጀመረ። እየሄድን ነው! ትንሽ ሄድ እንዳልን ልወርድን ነው ያለው ሰውዬ 50 ብር አውጥቶ ለባለ ባጃጁ ይሰጠዋል። ባለ ባጃጁም ዘርዝር አልያዝኹም፥ ዝርዝር ብር ያለው ይኖር ይኾን ይለናል እኔንና አንደኛውን ባጃጁን እየነዳ። እኔም ወደ ቲሴ እጄን ከትሁና በይውህና ኾኜ 40 ብር አለኝ፥ መልሱ ስንት ነው? ልስጠውን? አለኹኝ። በዚያን ጊዜ 10 ብር ብቻ ስጠኝ ይበቃል አለኝ። ሰጠኹት። በዚህ ሂደት በቅርብ ወራጅ ነኝ ያለኝ ሰውዬ በእጁ ቦርሳ ይዟል፥ ኪሩን እንደሚፈታትሽ ኾኖ የኔን ስልክ በጣም በእርጋት ከኪሴ ያወጣል። እኔም የኾነ ስሜት ይሰማኛል! የሻሼ አራዳ ነኝና😂 ስቀልድ ነው ገጠሬ ነኝ! ስልኬን ከኪሴ መውጣቷ ገብቶኛል።
ባለ ባጃጁም ወዳት መናኸሪያ ነህ? ወደ አሰላ ወይስ ወደ አዲስ አበባ ሲለኝ፥ ወደ አዲስ አበባ አልኹት ላካስ ወደ ሌላ መስመር እየወሰደኝ ኖሯል! አትነግረኝምን? እዚህ ውረድና ወደዚያ ሄደህ ሌላ ባጃጅ ያዝ ብሎ የሰጠኝን 10 ብር እንዳዛኝ ኾኖ ይሰጠኛል። እኔም ተቀብዬ ልወርድ ስል ኪሴን ቼክ አደረግኹኛ🙄 ስልኳን አጅሬው ከኪሴ አውጥቷታልና፥ ወንበሩም ላይ ቁጭ ብላለች፥ ቶሎ በፍጥነት ብድግ አድርጌያት ወረድኹላቸው! በአራዶች አራዳ ኾንኹባቸው። እየመረራቸው የሄዱ ይመስለኛል። እንዳወጣኸው ወደ ኪስህ አትከተውም ነበርን? ምን አንቀራዘዘህ? የጠዋት አየራችንን አከሰርኸው? ከኪሴ አውጪው ደግሞ ወይኔ! ምን ዓይነት መርዝ ነው😂 እያለኝ ይኾናል።
ስልኬን ቢወስዷት ስልክ ይገዛል በውስጡ ያስቀመጥዃቸው ዶክመንቶች ግን እጅጉን የሚጠቅሙኝ ናቸው። በዚያ ኀዘን ይሰማኝ ነበር። በዚህ አጋጣሚ ስልኮች ግን ሳያዝኑብኝ አይቀርም። በእጄ ብዙ ዓመት የመበርከት አጋጣሚ አግኝተዋልና። ከ5 ዓመት በታች የቆየ ስልክ ትዝ አይለኝም። አኹን የያዝኹት ግን ገና ኹለት ዓመቱ ነበር😁
ይህ ገጣኝ ምን አመለከተኝ መሰላችሁ፥ ንቍ ካልኾንን ሰይጣን እኛ በምንፈልገው መንገድ ወደ እኛ መጥቶ ወደ ምንሄድበትም የሚሄድ መስሎ የሚያጠቃን መኾኑን ነው። ብዙዎቻችንን በኃጢአት ጣዕም አስምጦ የሚያስቀረን እኛ በምንወደውና በምንመርጠው መንገድ መጥቶ ነው። በእርሱ ቍጥጥር ውስጥ ያስገባን ሲመስለው እንኳን በጥንቃቄና በንቃት የምንጓዝ ከኾነ በእግዚአብሔር ቸርነት ወጥመዱን መስበር እንችላለን። ተስፋ መቍረጥ፣ ትክዝ ብሎ መጨነቅ ወደ ጉዳት የሚያደርሰን እንጂ የሚጠቅመን አይደለም። ዐይነ ልቡናችን የሚሰረቀው ባልተገባ ጭንቀት ውስጥ ገብተን ስንዋኝ ነው። ምንም እንኳን አጋንንት እኛን ለመጣልና ወደ ኀዘን ውስጥ ለማስገባት ቢጥሩ፣ የምንወደውንም ነገር በር አድርገው ቢቀርቡን በጥንቃቄና በንቃት የምንኖር ከኾነ አንወድቅም። እግዚአብሔር አምላካችን አጋንንት ከሚያሴሩብን ክፉ ሴራ ይጠብቀን።
ሌላኛው መልእክት። ምንም እንኳን አዳማ በተደጋጋሚ በጉባኤ ምክንያት ብሄድም ብዙም አላቃትም። እነዚህ ሰዎች የበለጠ እናጥቃው ቢሉ የፈለጉበት ወስደው የፈለጉትን ሊያደርጉብኝ ይችሉ ነበር። ያሳደገኝ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ግን በአምላክ ቸርነት በዕለተ ቀኑ ከዚያ ጠበቀኝ። ይህ ማለት እኛ በማናስበው መንገድ ለጥቃት ራሳችንን አጋልጠን ብንሰጥ እንኳን እግዚአብሔር የሚጠብቀን መኾኑን ነው። አላወቅን ይኾናል እንጂ እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ ከክፉ ሴራ ጠላትን እንኳን በእኛ ላይ እንዳይሠለጥኑ ሕሊናቸውን የሚከለክል ቸር አምላክ መኾኑን ልብ እንበል። ክፉ ነገር ከደረሰብን በኋላ ብቻ የሚያድነን ሳይኾን እንዳይደርስብንም አስቀድሞ የሚያድነን አምላክ ኹሌም እናመስግነው። በእምነትና በንጽሕና ኾነንም እርሱ የሚፈልገውን እናድርግ።
https://t.me/phronema