EOTC ቤተ መጻሕፍት

@eotclibilery


ይህ Channel የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን የሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍት፤ ስብከትች እንዲሁም የተለያዩ ለአብነት ትምህርት የሚሆኑ በድምፅ ፤ይሁን በጹሁፍ እንዲሁም በ Video ሚለቀቅበት Channl new
ተጨማሪ ወይም ሚፈልጉትን መፃህፍት

ብለው ይጠይቁን
ማስታወቂያም እንሰራለን በውስጥ መስመር ይጠይቁን
የሰማነዉን እንናገራለን!
ያየነዉን እንመሰክራለን!

EOTC ቤተ መጻሕፍት

22 Oct, 14:17


ስለጠባይና ስለቅንነቱ እጅግ አድርጐ ወደደው፡፡ ከዚያም አስኬማው ወይም ቆቡ ላይ ወደ እግዚአብሔር ጸልዮ አመነኰሰው፤ ስሙንም ዘሚካኤል ብሎ ጠራው፤ በዚህ ጊዜ እድሜው 14 ዓመት ነበር፡፡
አባ ዘሚካኤል አስኬማ ካደረገ በኋላም በታላቅ ትጋቱ በጸሎቱና በጾሙ አባ ጳኵሚስ ተደነቀ፡፡ ስለሱም ዝናው በየሀገሩ ሁሉ እስከ አባቱ አገር ሮም ድረስ ተሰማ፡፡ አባ ዘሚካኤል ገና በሕፃንነቱ የምንኵስና ማዕረግ መቀበሉን ከሰሙ በኋላ ወደ እሱም 8 ቅዱሳን የመጡ ነበሩ፡፡ እነሱም፦ አባ ሊቃኖስ ከቁስጥንጥንያ፣ አባ ይምዓታ ከሀገረ ቁስያ፣ አባ ገሪማ ከሮም፣ ከአንፆኪያ አባ ድሕማ፣ ከቂልቅያ አባ ጉባ፣ ከእስያ አባ አፍጼ፣ ከሮሚያ አባ ጴንጠሌዎን፣ ከቂሳርያ አባ አሌፍ ነበሩ፡፡ እነሱም አባ ጳኵሚስ የምንኵስናውን አፅፍ አጐናፀፏቸውና አመነኮሷቸው፡፡ ለእያንዳንዳቸውም ስማቸውን ሰየሟቸው፡፡ እኒህም አባቶች ስለትዕግስት፣ አርምሞ፣ ትህትና፣ ስለሥርዐተ ማኀበር አመሠራረት ከአባ ጳኵሚስ ዘንድ ተማሩ፡፡
    ከዚህ በኋላ በዚያ ገዳም ለብዙ ዓመታት በፍቅር በአንድነት ከአባ ቴዎድሮስ ጋር ተቀመጡ፡፡ በዚህን ጊዜ ግን አባ ጳኩሚስ አርፈው አባ ቴዎድሮስ ተተክተው ነበር፡፡ እነዚህም አባቶች ወደየሃገራቸው ሄደው ማስተማርና ሃይማኖትን ማስፋፋት እንዳለባቸው ተስማምተው ወደየሀገራቸው ተመለሡ፡፡ አባ ዘሚካኤል ግን በዚያው ቆየ፡፡ እሱ ልቡን የነካችዉ ዜናዋንም የሰማላት ሃገር ነበረችና፡፡ ይህቺውም ሃገራችን ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ እሱም ማንም ሰው ሳያውቅና ሳያየው ከሁለቱ ደቀመዛሙርቱ ጋር ቅዱስ ሚካኤል እየመራቸው መጥተው ጐብኝተዋታል፡፡ ያለመምህራንና ያለአስተማሪ ያመነች የዚህችን ሀገረ እምነቷንና ሥነስርዐቷን ተመልክቶ ተደነቀ፡፡ እነዚያን 8 መነኰሳትም ከያሉበት ስለሃገሪቷ እየነገረ ጠራቸው የሚገርመው ግን እነሱም ስለዚህች ሀገር እንደሰሙ ያለምንም ማመንታት መጥተዋል፡፡ እነሱም ሕዝቡን እንደሰሙት አገኙት፡፡ አባ ዘሚካኤል አቡነ አረጋዊ የሚለውን ስያሜ ያገኙት ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ ትህትናቸውና ታዛዥነታቸው እሳቸው ሲመነኩሱ ገና ሕፃን ነበሩ ስራቸው ግን የአረጋውያን ነበርና አንተስ ሐፃን አይደለህም የልጅ አዋቂ ነህ ሲሉ አረጋዊ አሏቸው፡፡
አቡነ አረጋዊ በኢትዮጵያ ሲኖሩ በሄዱበት ስፍራ ብቻቸውን የሚፀልዩበትን ቦታ ሁል ጊዜ ይፈልጉ ነበር፡፡ አንድ ቀንም በመንገድ እየሄዱ ሳሉ ትልቅ ተራራን (ደብረ ዳሞን) ተመለከቱ፤ ከሦስተኛው ቀን በኃላም የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ሚካኤል መጥቶ ‹‹አንተ እግዚአብሔር ያከበረህ ቅዱስ ሆይ ምን ያስጨንቀሃል›› አለው፡፡ አባታችንም አቡነ አረጋዊም ‹‹ከዚህች ተራራ ላይ ወጥቼ ስለኃጥያቴ እናዘዝና እለማመን ስለበደሌም ይቅርታን እጠይቅ ዘንድ እወዳለሁ›› አለው፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም እንዲፀልይና ታላቅ ዘንዶም ወደርሱ እንደሚላክለት ነገረው፡፡ በሦስት ሰዓትም ዘንዶው መጣ፤ አባታችንም የዘንዶውን ጅራት ይዘው ወደላይ ወጡ ብቻቸውን አልነበሩም፡፡ ዘንዶው እንዳያስደነግጣቸውና እንዳይጐዳቸው ሰይፍን ይዞ ቅዱስ ሚካኤል ይጠብቃቸው ነበር እንጂ፡፡
አባታችን አቡነ አረጋዊም የእርጅና ዘመናቸው በደረሠ ጊዜ እግዚአብሔር ወደእርሱ በመንፈቀሌሊት ተገልጾ ቃልኪዳን ሰጣቸው፡፡ ይኸውም ‹‹መታሰቢያህን ያደርግ በጸሎትህም የተማመነውን ሁሉ እኔ በመላእክት ፊት ሞገስን ቧለሟልነትን እሰጠዋለሁ፤ በእውነተኛ ሀይማኖት ሁሉ የገድልህን መጽሐፍ የጻፈ፤ ያጻፈ፤ የተረጐመ እኔ ስሙን በሕይወት መጽሐፍ እጽፈዋለሁ፤ ይህ ሁሉ ላደረገም እስከ 14 ትውልድ ድረስ እምርልሀለሁ›› አላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ አባታችን አልሞተም በዓመቱ "ሞትን የማይቀምሱ አሉ፡፡" ብሎ እንደተናገረው /ማቴ 16 ፥ 28/ ጥቅምት 14 ቀን 558 ዓ/ም ተሠውረዋል፡፡ ከጻድቁ አባት በረከት ይክፈለን፤ በቃልኪዳናቸው ይጠብቀን፤ አሜን፡፡

**#ቅዱስ_ሙሴ_ብእሴ_እግዚአብሔር_በዓለ_ዕረፍታቸው_፡፡
ታሪኩ ከሙሽራው ቅዱስ ገብረ ክርስቶስና ከቅዱስ ቶማስ ዘቶርማቅ ጋር ተመሳሳይ የሆነው የእግዚአብሔር ሰው የተባለ የቅዱስ ሙሴ ዕረፍቱ ነው፡፡
@Nigatu5
@Nigatu5
@Nigatu5

EOTC ቤተ መጻሕፍት

22 Oct, 14:16


#ጥቅምት_14፤ ** #ቅዱስ_ገብረክርሰቶስ_(#አብደል_መሲህ_) #በዓለ_እረፍቱ_፤

በጎ ሥራን ከሚሠሩ፤ እግዚአብሔርን ከሚፈሩ  ከቊስጥንጥንያው ንጉሥ ቴዎዶስዮስና ከመርኬዛ ልጅ የላቸውም ነበርና ኢየሩሳሌም ድረስ ሂደው በስዕለት ያገኙት ታላቅ አባት ነው፡፡ ስሙንም ቤተሰቡ አብደል መሲህ ብለው ሰየሙት፤ (አብደል ማለት አገልጋይ ማለት ሲሆን መሲህ ማለት ክርስቶስ ማለት ነው፡፡ የስሙ ትርጓሜውም ገብረ ክርስቶስ (የክርስቶስ ሥራ) ማለት ነው፡፡
      እድሜውም ለትምህርት ሲደርስ የቤተክርስቲያንንና ሥጋዊ ትምህርትን አስተማሩት፤ አድጎም በጎለመሰ ጊዜ የሮሜውን ንጉስ ልጅ አጭተው እንደሥርዓቱ አጋቡት። እሱ ግን በምድራዊ ሕይወት ከመደሰት ይልቅ በሰማይ ስለሚያገኘው ነገር አብዝቶ ይናፍቅ ነበርና በጋብቻ ከመኖር ይልቅ ምንኵስናን ይወድ ነበርና በሰርጉ ዕለትም እኩለ ሌሊት በሆነ ጊዜ  ሙሽራው ገብረክርስቶስ ተነስቶ ወደ ሙሽራይቱ ሔዶ እጇንም ይዞ ከእርሷ ጋር ቃልኪዳን አደረገ፤ ከዚያም የሃይማኖት ጸሎትን አድርሶ ለእርሷም ምን አይነት ሕይወት መኖር እንደሚፈልግ አስረድቷት የተሞሸረበትን ልብስ ከላዩ አውልቆ የግምጃ ልብስን ለብሶ ለመሄድ ተነሳ፡፡ ሙሽራይቱም ‹‹እኔን ለማን ትተወኛለህ?›› ብላ አልቅሳ ጠየቀችው፡፡ እርሱም ‹‹በእግዚአብሔር ዘንድ እተውሻለሁ፤ እኔም ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን ልከተለው እሄዳለሁ፤ የአባቴ መንግስት ኃላፊ ነውና፡፡ አንቺም መሀላሽን አስቢ፡፡›› አላት፡፡ ያን ጊዜ መሃላዋን አስባ ዝም አለች።
      ከቤቱ ተነስቶ ወጣ፤ በመርከብ ከሚጓዙ መንገደኞች ጋር ያመት መንገድም ወደሚሆን አርመንያም ተጓዘ።
     በነጋም ሰዓት አባትና እናቱ ሙሽራው ልጃቸውን ለማግኘት ወደ ሰርጉ አዳራሽ ገቡ፤ እንዳሰቡት ግን ሙሽራው ልጃቸውን አላገኙትም፤ ይልቁንም ሙሽሪቷን እያለቀሰች አገኟት እንጂ፡፡ እነሱም አጥብቀው በጠየቋት ሰዓት መሐላን አስምሏት በሌሊት እንደሄደ ነገረቻቸው፤ ታላቅ ለቅሶን አለቀሱ። ይፈልጉት ዘንድም ንጉሥ አባቱ አምስት መቶ አገልጋዮችን ላከ፡፡ ለድሆችና ለምስኪኖችም ምጽዋት ያደርጉ ዘንድ ብዙ ገንዘብን ሰጣቸው ገብረክርስቶስ ግን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም በተሰራች አርመንያ ሀገር በምትገኝ በአንዲት ቤተክርስቲያን ደጅ መኖር ጀምሮ ነበር፡፡      
አባቱ የላካቸው ሁለቱ አገልጋዮችም ከዚያ ደርሰው ስለርሱ መርምረው ነበር፤ ወሬውን ግን ማግኘት ተሳናቸው፡፡ ለድሆችም ምጽዋትን ተቀብሏል ግን እንደማንኛውም የኔቢጤ ስለመሰላቸው ማወቅ ተስኗቸው ነበር፡፡ በዚህችም ቦታ ማንም እሱ የንጉሥ ልጅ፤ ቅዱስ መሆኑን ሳያውቅ 15 ዓመት ኖረ፡፡                           
      እመቤታችን ለአንድ ቄስ ተገልጻ ገብረ ክርስቶስን ወደ ቤ/ን ያስገባው ዘንድ አዘዘች፤ ገብረክ ርስቶስም ይህን ባወቀ ጊዜ በሌሊት ተነስቶ በእመቤታችን ስዕል ፊት ‹‹እመቤቴ ሆይ የተሰወረ ሥራዬን አንቺ ለምን ገለጥሽ አሁንም ወደ ሚሻለኝ ምሪኝ›› ብሎ ስዕሏን ተሳልሞ በሌሊት ወጥቶ ወደ ባህሩ ወደብ ደረሰ፡፡
    ወደሌላ ሃገርም ሊሄድ ወዶ በመርከብ ተሳፈረ ግን በእግዚአብሔር ፈቃድ ከአባቱ አገር ደረሰ እሱም እናትና አባቴ ለኔ የፈለጉትን እየሰጡኝ ለነሱ ምጽዋት ይሆንላቸው ዘንድ በደጃቸው ልኑር ብሎ በፈቃዱ ወደ እነርሱ ሄደ፡፡ የእነርሱን መዳን ሽቷልና ፊቱ በጣም ተለውጧልና ከቤተሰቦቹም ይሁን ከገረዶቻቸው መሃል ማንም ያወቀው አልነበረም ከውሾቹ በቀር፡፡ ለአባቱም እኔ መጻተኛ ነኝና በቤተ መንገሥትህ ደጅ ፊት ለፊት እንዳትረሳኝ ጎጆ ሥራልኝና ልኑር አለው፤ አባቱም የልጁን ኹኔታ አስቦ እኔም ልጄ እንዲሁ አይደል ብሎ ፈቀደለትና መኖር ጀመረ፡፡ የቤተ መንግሥቱ ባለሟሎችና እንዲንከባከቡት የታዘዙት ሠራተኞች ግን ሲገቡና ሲወጡ ሽታው እንዳያስጨንቀን ይህን ምስኪን አስውግዱልን እያሉ ወጭትና ድስትም እያጠቡ በላዩ ይደፉበት ነበር፡፡ ውሾችም እንዲናከሱበትና እንዲበሉት የሥጋ ትርፍራፊ ይጥሉበት ነበር፡፡ ውሾች ግን ቁስሉን ይልሱለት ነበር፡፡
ቅዱስ አባ ገብረ ክርስቶስም ጊዜ እየረዘመ በሄደ ጊዜ የባሮቹ በደል እየበዛ ሲመጣ (መቋቋም ስላቃተው ሳይሆን ለእነሱ በደል እንዳይሆንባቸው ሲል) ወደ እግዚአብሔር ይወስደው ዘንድ ለመነ፡፡ ከዚያም ታሪኩን ከመጀመሪያ እስከመጨረሻው ጽፎ በእጁ ይዟት አረፈ፤ የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትን የማይነሳ ፈጣሪም እንደፈለገ ነፍሱን ከሥጋው ለየለት፡፡ ለሱም ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውንም ለሚያደርግ ቃልኪዳን ሰጠው፡፡ የዕረፍት ቀኑም እሑድ ነበርና ሕዝቡ ሁሉና ካህናቱ ከሊቀጳጳሳቱ ጋር በቅዳሴ ጊዜ በቤተክርስቲያን ውስጥ ሳሉ ‹የእግዚአብሔርን ሰው በንጉሡ በቴዎዶስዮስ ቤት ፈልጉት› የሚል ቃል ከሰማይ ሰሙ በዚያን ጊዜ ሂደው በአረፈበት ቦታ አገኙት፡፡ በእጁም ውስጥ የተጨበጠ ክርታስን አዩ፡፡ ሊወስዷትም ሽተው መውሰድ ተሳናቸው በአንድነትም በጸለዩ ጊዜ እጁ ተፈትታ ወስደው አነበቧት፡፡ አባትና እናቱም ልጃቸው እንደሆነ አወቁ ታላቅ ጩኸትም ሆነ መሪር ልቅሶንም አለቀሱ አክብረውም በጥምቀት 14 በእረፍቱ ቀን ቀበሩት መቃብሩም በሽተኞችን ሁሉ በመፈወስ ድንቅ የሆኑ ብዙ ተዓምራቶችን የሚያደርግ ሆነ ከጻድቁ ረድኤት በረከት ያሳትፈን፡፡

፠*፠ #አቡነ_አረጋዊ ፠*፠ (#ዘሚካኤል)#ወቅዱስ_ሙሴ_ብእሴ_እግዚአብሔር
#አቡነ_አረጋዊ (#ዘሚካኤል)

ትውልዳቸው ሮም ሲሆን እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ከአባታቸው ይስሐቅና ከእናቸው እድና  የተገኙ የቅዱሳን ፍሬ ናቸው፤ ወንድሞቹም ቴዎድሮስ እና ገብረ አምላክ ይባላሉ፡፡ የቀድሞው ስማቸው ዘሚካኤል ነበር፡፡ “አረጋዊ” የተባሉት ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ ነው፡፡ በእድሜ ልጅ ሲሆኑ በመንፈሳዊ ሕይወታቸውና ሥራቸው አዋቂ ስለነበሩ አረጋዊ ብለዋቸዋል፡፡
ወላጆቻቸው ቅዱሳት መጻሕፍትን እያስተማሩ አሳደጉት፤ እሱም በመንፈስ ቅዱስ ኀይል እየጸናና እየበረታ ሄደ፡፡ ዕለት ዕለት ጧትና ማታም ወደቤተክርስቲያን እየሄደ ጸሎት ከመጸለይ አያቋርጥም ነበር፡፡
እድሜውም ለጋብቻ ሲደርስ አባትና አናቱ ያገባ ዘንድ ሚስት አጩለት፡፡ እሱ ግን ፈጽሞ እምቢ አለ፤ ከሕፃንነቱ ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ እየተቃኘ የምንኵስና ሕይወትን ለመኖር ፈልጓልና፡፡ ከብዙ ዘመንም በኋላ የምንኵንስና ሕይወትን ለመኖር ወደ አባ ጳኩሚስ ዘንድ ሄደ፤ ወደ ገዳሙም በገባ ጊዜ አንድ መነኵሴ አገኙትና ‹‹ልጄ ሆይ ከወዴት መጥተሃል እነሆ አንተ ሕፃን እንደሆንክ እመለከታለሁና›› አሉት፡፡ እሱም አመጣጡ ከሮም እንደሆነና ከአባ ጳኵሚስ ዘንድ የሚፈልገው ነገር እንዳለ ነገራቸው፡፡ እሳቸውም ነገሩን ከሰሙ በኋላ ወደ አባ ጳኩሚስ ዘንድ ወሰዱት፡፡
አባ ጳኩሚስም በአየው ጊዜ ከመንበሩ ተነስቶ  በፍፁም ፍቅር አቅፎ ሳመው የእግዚአብሔር ጸጋ በእሱ ላይ አድሯልና፡፡ ከዚያም ቀጥሎ ስለምን ጉዳይ ወደ እሱ እንደመጣ ጠየቀው፡፡ አባ ዘሚካኤልም ‹‹እንደአንተ እንደ አባቴ መነኵሴ እሆን ዘንድ መጥቻለሁ›› አለው፡፡ አባ ጳኩሚስም ‹‹ልጄ ሆይ አንተ የንጉሥ ልጅ እንደመሆንህ መጠን የመንግሥቱ ወራሽ ነህና መንኵሰህ ለመኖር እንደምን ይቻልሃል?›› ሲል መለሰለት፡፡ አባ ዘሚካኤል ግን የምድር መንግሥት ኀላፊ ጠፊ እንደሆነ ያውቃልና ከዓለም ንግሥና ይልቅ ዘለዓለማዊ መንግሥትን ይወርስ ዘንድ እንደሚሻ ያመነኵሰውም ዘንድ አጥብቆ ጠየቀው፡፡ አባ ጳኩሚስም ፈተናን ፈትኖት መቋቋም የሚችል ከሆነ እንደሚያስገባው ነግሮ የተለያዩ ፈተናዎችን ፈትነው፡፡ አባ ዘሚካኤልም የተባለውን የታዘዘውን ሁሉ በትጋት ፈጸመ፡፡ አባ ጳኵሚስም ስለሃይማኖቱ ጽናት

EOTC ቤተ መጻሕፍት

22 Oct, 12:31


የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አጀንዳ አርቃቂ ብፁዓን አባቶችን ሰየመ።

ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም (ተ.ሚ.ማ/አዲስአበባ)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የጥቅምት 2017 ዓ.ም ምልዓተ ጉባኤ አጀንዳ አርቃቂ ብፁዓን አባቶችን ሰይሟል።

ምልዓተ ጉባኤው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የመክፈቻ መልዕክት ዛሬ ጠዋት መጀመሩ የሚታወቅ ሲሆን ከቅዱስነታቸው የመክፈቻ መልእክት በኋላም የመወያያ አጀንዳ ቀርጸው የሚያቀርቡ ሰባት ሊቃነ ጳጳሳትን ነው የሰየመው።

በዚህም መሰረት

1.ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ
2.ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ
3.ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ
4.ብፁዕ አቡነ ማርቆስ (ዘስያትል)
5.ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ
6.ብፁዕ አቡነ  ኤጲፋንዮስ
7.ብፁዕ አቡነ ኤልሣዕ የተመረጡ ሲሆን አጀንዳ የማርቀቅ ተግባራቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ የሚያቀርቡትን ረቂቅ አጀንዳ ከመረመረና ማስተካከያ ካደረገበት በኋላ የጸደቀውን አጀንዳ መሰረት በማድረግ በቅደም ተከተል እየተወያየ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።
@Nigatu5
@Nigatu5
@Nigatu5