Ethiopian Orthodoxs Daily

@ethiopianorthodoxs


በቤተ ክርስቲያናችን በየቀኑ የሚታሰብ ቅዱሳን፤ የመፅሐፍ ቅዱስ ምንባባት ፤ ብሂለ አበው እና አስተማሪ የሆኑ መንፈሳዊ ፅሁፎች ያገኙበታል::Share https://t.me/ethiopianorthodoxs //like page on facebook fb.me/ethiopianorthodxs ለሀሳብ አስተያየትዎ
@Yakob520

Ethiopian Orthodoxs Daily

21 Jan, 00:26


+  መልአኩ ነው +

       ሰዓቱ ሌሊት ነው ፤ እንደ አጋጣሚ ሆኖ በዚያ ሌሊት መላው የቤተሰባችን አባል አምሽቶ እየተጫወተ ነው፡፡ ከዚህ የቤተሰብ ስብስብ መካከል ሳይገኝ የቀረው አንድ በወኅኒ ቤት የታሰረ ወንድማችን ብቻ ነበር፡፡ ድንገት ግን የጊቢው በር በተደጋጋሚ ተንኳኳና ሁላችንም ጨዋታችንን አቋረጥን፡፡ በሌሊት ደግሞ የሚያንኳኳው ማን ነው ? አልን በልባችን

ሠራተኛችን ሮጣ ሔደች:: ወዲያው ግን በሩን ሳትከፍተው ተመልሳ እየሮጠች መጣች፡፡ በደስታ ሰክራ ‹‹የታሰረው ልጃችን በር ላይ ቆሟል!›› ብላ ተናገረች፡፡ "በድምፁ አወቅኩት!› እያለች ዘለለች፡፡ ከሁኔታዋ የተነሣ ‹አብደሻል እንዴ!?› አላት ቤተሰቡ ሁሉ፡፡

እስዋ ግን በእርግጠኝነት ተናገረች! በቀን የታሰረው ልጅ በሌሊት ተፈቶ መምጣቱ ፈጽሞ ሊታመንን የማይችል ነገር ነው፡፡ ቤተሰቡ ሁሉ የታሰረው ልጅ መጣ ብሎ አላመነም፡፡ ባይሆን የመንግሥት ወታደሮች የቀረነውን ሊወስዱን ይሆን? ማን ሊሆን ይችላል? ብሎ ተብሰለሰለ:: በመጨረሻም የሁሉም ግምት አንድ ነገር ላይ አረፈ:: ሁሉም ሰው በአንድ ድምፅ አንድ ቃል ተናገረ "መልአኩ ነው!"

  መልአኩ የሰው ስም አይደለም:: ቤተሰቡ የተስማማው "ደጅ የቆመው የታሰረው ልጃችን ሳይሆን እሱን ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር የተሠጠው ጠባቂ መልአኩ ይሆናል›› ብሎ ነበር፡፡ የበሩ መንኳኳት አሁንም ስላልቆመ ቤተሰቡ ግር ብሎ ወጣና ተቻኩሎ በሩን ከፈተ፡፡ በደጅ የቆመው ግን እንደተባለው የታሰረው ልጅ ራሱ ነበር፡፡ ሁሉም ተደሰተ!!!

      ይህ ገጠመኝ በአሁን ዘመን የተፈጸመ ነው ብዬ ብናገር ማን ያምነኛል? እውነት በሌሊት የቤታችን በር ሲንኳኳ  መልአክ ነው ብለን እንገምታለን? ይህን የገመተው ቤተሰብ ምን ዓይነት ቤተሰብ ነው?

በሌሊት ሲንኳኳ በብዙዎቻችን አእምሮ ውስጥ መጀመሪያ የሚመጣው ጥርጣሬ ‹ሌባ ሊገባ ይሆን?› የሚል ስለሚሆን ዱላ ፍለጋ እናማትራለን፡፡ ወይ ደግሞ ሌሊቱ ወደ መንጋቱ እየተቃረበ ከሆነ ‹‹የምን መርዶ ሊያረዱኝ ይሆን? የቱ ዘመዴ ሞቶ ይሆን?› የሚል ጭንቀት ይፈጠራል፡፡

‹የሚያንኳኳው የእግዚአብሔርመልአክ ይሆናል› ብሎ የሚጠረጥር ሰው ግን በዚህ ዘመን ለማግኘት ያስቸግራል፡፡ እንዲህ ብሎ ግምቱን የሚናገር ሰው ከቤተሰባችንመካከል ቢገኝ እንኳን እንደ ዕብድ ልንቆጥረው እንችላለን፡፡ ታዲያ ይህን ገጠመኝ ከየት አመጣኸው ትሉኝ ከሆነ መልሱ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚል ነው፡፡

      በሐዋርያት ዘመን ሔሮድስ የተባለው ንጉሥ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስን ወኅኒ ቤት ውስጥ ወርውሮት ነበር፡፡ የቀሩት ደቀመዛሙርትና ክርስቲያኖች በዚያ ሰሞን ሲጸልዩ ከርመዋል፡፡ በአንድ ሌሊት በማርቆስ እናት ቤት ውስጥ ተሰብስበው አምሽተው ነበር፡፡ ድንገት የቤቱ በር ሲንኳኳ ሮዴ የምትባል የቤት ሠራተኛ ደጁን ልትከፍት ወጣች፡፡ ማነው ብላ ስትሰማ የቆመው እስረኛው ቅዱስ ጴጥሮስ መሆኑን በድምፁ አወቀች፡፡ ደስታ ግራ ሲያጋባት በሩን መክፈትን ረስታ ወደ ውስጥ ሮጠችና ጴጥሮስ መምጣቱን ተናገረች፡፡ እነርሱ ግን አላመኑአትም፡፡ ጤንነቷን ተጠራጥረው ‹አብደሻል› አሏት፡፡ እርግጠኛ ሆና ተናገረች፡፡ እነርሱ ግን መልሰው ‹‹የቆመው ጴጥሮስ ሳይሆን መልአኩ ነው፡፡›› አሉ፡፡ ይደንቃል የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች እንዲህ በር ሲንኳኳ ‹መልአክ ነው› ብለው የሚገምቱ መንፈሳዊያን ነበሩ፡፡ (ሐዋ. 12፡12-15)

ክርስትናን ከመላእክት ውጪ አይታሰብም:: ከመጽሐፍ ቅዱስም እንደ ትንቢተ ሐጌና መጽሐፈ አስቴር ያሉ ጥቂት መጻሕፍት በቀር ስለ መላእክት የማይናገር መጽሐፍ የለበትም:: ክርስትና የጀመረው በገብርኤል ብሥራት ነው:: ልደቱ በመላእክት የታጀበ ነው:: ስቅለቱ ትንሣኤውም ከመላእክት ጋር ነው:: የጌታ ምጽአቱም በመላእክት የታጀበ ነው::
     

ቅዱሳንመላእክት እኛ የሰው ልጆች ከመፈጠራችን ቀድመው የተፈጠሩ ታላቅ ወንድሞቻችን ናቸው፡፡ እንዲያውም ምድርና የሰው ልጅ ሲፈጠር ደስ እያላቸው ‹‹እልል›› ይሉ ነበር፡፡ (ኢዮ. 38፡6) ቅዱሳን መላእክትን እግዚአብሔር ለእንዳንዳችን ጠባቂዎች አድርጎ ሠጥቶናል፡፡ መላእክት ለሰው ባልተናነሰ ቁጥር ምድር ላይ አሉ:: እነርሱን ለማየት ግን ቅድስና ይጠይቃል::

ከክርስቶስ እግር ሥር ቁጭ ብለው የተማሩት ቅዱሳን ሐዋርያት ስለ መላእክት ጠባቂነት ጋር ይህን ያህል እምነት ከነበራቸው እኛም የመላእክቱን ጠባቂነት ማመን ለዚህ ዘመን ክርስቲያኖችም ምን ያህል ይገባን ይሆን? ቅዱሳን መላእክት በክርስትና ሕይወት ለሚኖርሰው ሁሉ የመላእክት ረዳትነት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ለሁሉ ብርታት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን በሥጋው ወራት በተያዘባት ምሽት ሲጸልይ ‹‹ከሰማይም መጥቶ የሚያበረታው መልአክ ታየው›› ተብሎ ተጽፏል፡፡ (ሉቃ. 22፡43) ይህም ቀርበው አገለገሉት‹ለከ ኃይል› እያሉ አመሰገኑት ማለት ሲሆን ለእኛም የመላእክት ርዳታ አያስፈልገኝም እንዳንል የሚያስተምረን ነው፡፡

ቅዱሳን መላእክት በምድር የሚሆነውን ያውቃሉ:: (2 ሳሙ 14:20) በበደላችን ስንጸጸት "ኃጢአትህ ተሠረየችልህ" ይላሉ (ኢሳ 6:7) በክፋታችን ጸንተን ከቀጠልን ደግሞ "ይቅር አይሉም" (ዘጸ 23:20)
ስለእኛ በእግዚአብሔር ፊት ቆመው "የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?" ብለው ያማልዳሉ:: (ዘካ 1:12)

አንዳንድ ሰዎች መላእክትን ለረዳትነት ስንጠራ ሲሰሙ እነርሱ በምን ያውቃሉ በሁሉ ቦታ የሉም እኮ ሊሉን ይሞክራሉ:: ሰይጣን "ፈተነኝ" ስንል ግን "እሱ በሁሉ ቦታ የለም ምን ያውቃል አይሉም:: እኛ ግን መላእክት በሁሉ ባይሞሉም ለትንሽዋ ፕላኔት ምድር ግን እንደማያንሱና አንዱ መልአክ ብቻ ለምድር እንደሚበቃ እናምናለን:: (ራእ 18:1)
ለመላእክት ስንዘምር የሚቃወሙ ሰዎች "ጠላቴ ሆይ" ብለው ስለ ሰይጣን ክፉነት እያነሱ ብዙ መዝሙር ሲዘምሩ ስንሰማ ግራ እንጋባለን::

እኛ ግን በመላእክቱ ረዳትነትና ምልጃ እናምናለን:: ባለንበት ዘመን በየሆስፒታሉ በዓለም ሁሉ በበሽታ የሚሠቃየው ብዙ ነው::  በሕመም ለሚሠቃየው ሁሉ

"መልአክ ቢገኝለት እየራራለት [ለእግዚአብሔር] ፡— ቤዛ አግኝቻለሁና ወደ ጕድጓድ እንዳይወርድ አድነው፡ ቢለው፥ ሥጋው እንደ ሕፃን ሥጋ ይለመልማል፤ ወደ ጕብዝናውም ዘመን ይመለሳል" ኢዮ 33:23-25

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ሰኔ ሚካኤል - 2007 ዓ ም የተጻፈ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ዘንድ ጸልዩ! ሌሎች እንዲያነቡትም የሚከተሉት አድራሻዎች Like እና Share ያድርጉ
FB: https://www.facebook.com/officialHenokhaile/
Telegram: https://t.me/deaconhenokhaile
Instagram: https://www.instagram.com/p/CBnMF0nnhcQ/?igshid=549jvl607bv4
Youtube: https://www.youtube.com/channel/UCOaVsWC05aUjeqIEW3fWj7g

Ethiopian Orthodoxs Daily

21 Jan, 00:16


አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥቅምት አምስት በዚህች ቀን ተአምራቱና ትሩፋቱ እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ የእግዚአብሔር ማደርያ የሆነ ቅዱስ አባት ተጋዳይ የአባ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የመታሰቢያ ቀኑ ነው::

ይህ ጻድቅ ዕረፍቱ በመጋቢት ሲሆን ቃል-ኪዳን የተቀበሉበት ቀን በጥቅምት ነው:: በመጋቢት ወር በስፋት እና በጥልቀት መልእክቱን ልኬ ክብር ይግባውና ከቃል-ኪዳኑ በረከት ተካፋይ ሆነናል::

ገድለ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን በማንበብ በረከትና ቃል-ኪዳኑን በእምነት መቀበል ነው:: ይባረኩበታል:: ይቀደሱበታል::

ገድለ ገብረ መንፈስ ቅዱስን በማንበቦ ወይ ሲነበብ በመስማቶ: በስማቸው የታነጸ ቤተ ክርስቲያን ሔደው በመሳለሞ: ማኅሌቱን ቆመው: ቅዳሴ አስቀድሰው: ቃለ ወንጌሉን ሰምተው: ዕጣን ጧፍ ሰጥተው: ለነዳያን እንደ አቅሞ መጽውተው ጻድቁ የተሰጣቸው ቃል-ኪዳን በእምነት ይቀበላሉ::

በዛሬው ቀን ጥቅምት አምስት ቀን እንድናከብረው መምህራነ ቤተ ክርስቲያን ያዘዙን በመጋቢት ወር ዐቢይ ጾም ምክንያት ወደዚህ የዞረ ባዓል ነው:: ለበረከት ያህል ግን እንሆ......
            ++++ ለበረከት +++++

ይህም ቅዱስ አባት በተወለደበት ቀን ድንቅ የሆነ ሥራን ሠራ:: እንደተወለደ ተነሥቶ ከእናቱ እቅፍ ወርዶ ከጨለማ ወደ ብርሃን ላወጣኽኝ ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን እያለ ለሥላሴ ሰግዷል ምስጋናም አቅርቧልና::

በበረሀም ብዙ ዘመናት ሲኖር:: ነፍሱን ነፍስ ሆይ ዕወቂ በእግዚአብሔር ፊት ራቁትሽን ትቆሚ ዘንድ እንዳለሽ እንግዲህስ ጽኚ በርቺ ታገሺ ይላት ነበር::

ከብዙ ዘመናት በኋላም ለአባታችን ለገብረ መንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር እንዲህ አለው:: ከእንግዲህ በዓለም ካሉ ሰዎች ከካህናት ከመነኰሳት ወይም ከምእመናን ሕዝባውያን እንዳያውቁህ አደርግሃለሁ:: እንዳንተ ካሉ በቀረ አንተ ራስህ ብትፈቅድ እንጂ መላእክትም ይጎበኙሃል::

የብርሃን ሠረገላም ይሁንል መድረስ ወደምትሻበት ሁሉ ብረር:: እኔንም ማየት በምትፈልግበት ጊዜ አባቴን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በሦስትነቴ ታየኛለህ::

ስልሳ አንበሶች ስልሳ ነብሮች በፊት በኋላ አጅበውት ወደ ኢትዮጵያ ምድር ተጓዙ:: የእግዚአብሔር መልእክተኛ ቅዱስ ገብርኤልም ከአንበሶችና ከነብሮች ጋር በነፋስ ሠረገላ አሳፍሮ ይመራው ነበር:: ወደ ምድረ ከብድም አደረሰው ከዚያም ወደ ልዩ ተራራ ወደ ደብረ ዝቋላ ወሰደው::

አባታችን መላው ኢትዮጵያን ያስማረ ፈጣሪም አብዝቶ ቃል ኪዳን የሰጠው ነው:: ስለ ሕዝቡ ምሕረት ልመና መቶ ዓመት በባሕር ኖረ::

በሽተኞችን እንዲፈውስ ሙታንን እንዲያስነሳ አምላካችን ሥልጣን ሰጥቶታል:: ስሙን ለሚጠራና መታሰቢያውን ለሚያደርግ እስከ አሥራ አምስት ትውልድ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጠው::

የጸሎቱ ኃይል ሁላችንን የክርስቲያን ወገኖች ይጠብቀን ለዘለዓለሙ አሜን::

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን የአባታችንም የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ምልጃ ቃል ኪዳንና በረከት አይለየን ለዘላለሙ አሜን::
🇪🇹@ethiopianorthodoxs⛪️⛪️

Ethiopian Orthodoxs Daily

21 Jan, 00:03


🌻እንኳን ለፆመ ፅጌ በሰላም አደረሰን!
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ሃያ ስድስት በዚህች ቀን እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ገብርኤልን ወደ በራክዩ ልጅ ዘካርያስ ልኮት መጥምቁ ዮሐንስ ከእርሱ ስለ መወለዱ አበሠረው::

ስሙ የተመሰገነ እግዚአብሔር ልጅን ይሰጠው ዘንድ አስቀድሞ ሁል ጊዜ በመጸለይ ወደ እግዚአብሔር ይማልድ ነበር::

ልጅ ያልወለደውን እግዚአብሔር ብዙ ተባዙ ምድርን ምሉዋት ያለውን በረከት ያጣ ነው በማለት እስራኤል ይገዳደሩት ነበርና::

ልመናውንም ሰማ በቤተ መቅደስ ቁሞ ዕጣንን ሲያሳርግ  መልአኩን ላከለት በከበረ ወንጌልም እንደተባለ መንገዱን ይጠርግ ዘንድ በንጉሥ ክርስቶስ ፊት እንደሚሔድ የተነገረለት ታላቅ ነቢይ ዮሐንስ ከእርሱ መወለዱን አበሠረው::

ዘካሪያስም የሰውነቱን መድከም የመወለጃውም ዘመን እንዳለፈና ፈጽሞ እንዳረጀ የሚስቱም እንዲሁ ዘመኗ እንዳለፈና ፈጽሞ እንዳረጀች መካንም እንደሆነች ያውቃልና ስለዚህ ይህ ነገር እንዴት  ይሆንልኛል እኔ ያረጀሁ ሽማግሌ ነኝ ሚስቴም እንዲሁ ዘመኗ አልፎ መካን ሁናለች  ብሎ የእግዚአብሔር መልአክ ተከራከረው::

መልአኩም እኔ ልንገርህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ወዳንተ ተልኬ ነበር ልትጠራጠር ባልተገባህም  ነበር አሁንም ይህ በጊዜው እስቲፈጸም ዲዳ ሁነህ መናገር ይሳንሃል ብሎ ገሠጸው::

ዘካርያስም የወልደ እግዚአብሔርን መንገድ የሚጠርግ ዮሐንስ እስከሚመለድበት ጊዜ ድረስ ዲዳ ሆነ::

በሚገረዝበትም ቀን የሕፃኑን ስም ምን ብለው እንደሚሰይሙት ጠየቁት እርሱም ብራና ለምኖ ስሙ ዮሐንስ ነው ብሎ ጻፈ በዚያም ጊዜ አንደበቱ ተፈትቶ እግዚአብሔርን አመሰገነው::

ስለ ልጁ ዮሐንስም እርሱ የልዑል ነቢይ እንዲባል መንገዱንም ይጠርግ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት እንደሚሔድ ትንቢት ተናገረ::

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዘካርያስና በኤልሳቤጥ በልጃቸው በዮሐንስም ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን::
🇪🇹@ethiopianorthodoxs⛪️⛪️

Ethiopian Orthodoxs Daily

21 Jan, 00:00


ማኅሌተ ጽጌ፤ ምንጩ ትርጉሙና መልእክቱ

በዲያቆን ያረጋል አበጋዝ

Ethiopian Orthodoxs Daily

20 Jan, 23:53


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ዐሥራ ዘጠኝ በዚችም ቀን ደግሞ የከበረ መስቀል የበዓሉ መታሰቢያ ነው::

በተገኘ ጊዜ ሦስት ቀኖች ያህል በፍጹም ደስታ በዓልን አድርገውለት ነበርና::

እኛም እንዲሁ በታላቅ ደስታ የበዓሉን መታሰቢያ ልናደርግ ይገባል:: ከጠላታችን እጅ ድኅነታችን በእርሱ ተደርጎልና::

ከጠላታችን ያዳነን በፍጹም ፍቅሩ ነው:: መስቀልን ስናከብር ታዲያ በጠላት መንገድ በፌሽታ በጭፈራ በዝሙት በስካር አብዝቶም በመብላት መሆን የለበትም:: ይህ የጥፋትና የጠላት መንገድ ነውና::

የመስቀሉ መንገድ ጸጥታ÷ ፍቅር÷ ሰላም÷ መከራ÷ ሰማዕትነት÷ ጾም÷ ጸሎት÷ ስግደት÷ ያጡትን መርዳትና መጎብኘት መልካም መሥራትና መፈጸም ነው::

በመስቀሉ ለአዳነን ለእግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና ይሁን::

ሁላችን የሐዋርያት የሆነች የከበረች የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ስለ እኛ የተቀበለውን መከራውን የምናምንና የምናስበውን በባለሟልነትና በፍቅሩ ወደ እርሱ ያቅርበን ለዘላለሙ አሜን::

የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱስ ገብርኤል ረዳትነት አይለየን ለዘላለሙ አሜን::
🇪🇹@ethiopianorthodoxs⛪️⛪️

Ethiopian Orthodoxs Daily

20 Jan, 23:51


መስቀል

ነደ እሳትን የተሸከመ የኪሩቤልም ባልንጀራ የሆነ እንደ ድንግል ማርያም ስም አራት ፊደል ያለው ነበልባላዊ የእሳት መንበር።

✣✣✣ አዳምን ከሞት ያወጣው የሕይወት ዛፍ።

✥✥✥ የኃጢአትን ቀላይ የገታ መርከብ።

❖❖❖ ባሕረ እሳትን ያሻገረ የድኅነት ትርክዛ።

✞✟✟ነፍሳት የሕይወት እንጀራን የጠገቡበት ማዕድ!

✟✟✟ክርስቶስና ቤተክረስተያን የተሞሸሩበት የሠርግ ቦታ።

✝️✝️✝️ምእመናን የተጸነሱበት መካነ ክርስትና።

🔸🔸🔸 ቤተክርስቲያን የጸናችበት መሠረተ ሃይማኖት።

🔹🔹🔹የፍስሐ ኩሉዓለም ክርስቶስ ደም የፈለቀበት ሙሐዘ ትፍሥሕት!

🔶🔶🔶 ከሕይወት ውኃ ከክርስቶስ የተተከለ ሁል ጊዜ የሚያፈራ የሕይወት ዛፍ።

🔷🔷🔷 የንጉሥ ልጅ በአባቱ ኅልቀተ ወርቅ ማኅተም እንዲመካ፥ የንጉሠ ነገሥት ክርስቶስ ልጆች የምንለይበት የምንመካበት ትእምርተ ድኂን።

✔️ የጨለማውን አበጋዞችን ድቅድቅ የምንገፍበት
ጸዳለ ኩሉ ዓለም።

✔️ የሚወረወረውን ፍላጻ የምንሰብርበት ልብሰ ሃይማኖት ጥሩር።

✟✟✟✔️ጦር ከነቀነቀ ጋሻ ከታጠቀ ከቀን ወራሪ ከሌሊት ሰባሪ የምንመክትበት ንዋየ ሐቅል።

ቢዋጉ ማሸነፊያ ቢሸሹ መጠጊያ ጸወነ ሥጋ ወነፍስ ወልታ የጽድቅ።
መስቀል መልእልተ ኲሉ ነገር

Ethiopian Orthodoxs Daily

20 Jan, 23:49


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ዐሥራ ስድስት በዚህች ቀን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ላይ ቤተ ክርስቲያን የታነጸችበትና የተቀደሰችበት ቀን ነው::

ይህም እንዲህ ነው ቅድስት ዕሌኒ ልጇ ቊስጥንጥንዮስ በነገሠ በሃያ ዓመት ቅዱሳን የሆኑ 318 አባቶችን  በኒቂያ ከተማ ከሰበሰበ በኋላ ቅድስ እናቱ ዕሌኒ እንዲህ አለችው ልጄ ሆይ እኔ ወደ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም በመሔድ የክብር ንጉሥ የሆነ የክርስቶስን ዕፀ መስቀል ፈልጌ አወጣ ዘንድ ለእግዚአብሔር ስዕለትን ተስያለሁ አለችው::

ቈስጠንጢኖስም ሰምቶ በዚህ ነገር ደስ አለው ከብዙ ሠራዊት ጋር ገንዘብ ሰጥቶ የከበሩ የግምጃ ልብሶችንም ሰጥቶ ላካት እርሷም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰች ጊዜ ከከበሩ ቦታዎች ተባረከች::

ከዚህም በኋላ ስለ ከበረና አዳኝ ስለሆነ ዕፀ መስቀል መረመረች በታላቅ ድካምም አገኘችውና ታላቅ ክብርም አከበረችው በታላቅ ምስጋናም አመሰገነችው:: (ስለዚህ ቦታ ታሪክ ስለ መስቀሉ አወጣጥ በነገው ዕለት ከብዙ በጥቂቱ ለበረከት እጽፋለሁና ይከታተሉኝ::)

በኢየሩሳሌምም ስሙ መቃርስ የሚባል ኤጴስ ቆጶስ ንግሥት ዕሌናኒን ስለምታንጸው ቤተ መቅደስ እንዲህ ብሎ መከራት ጠንካራ የሆነ የማይናወጽና የማይፈርስ ጥሩ ሕንፃ ልታሠሪ ይገባል ከዚህ የሚተርፈውንም ለድሆችና ለችግረኞች ስጪአቸው አላት::

ከዚህም በኋላ በጎሎጎልታ በቤተ ልሔምም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ዋሻ ደግሞ በጽርሐ ጽዮን የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ በተቀበረበት በጌቴሴማኒ በደብረ  ዘይትም በከበሩ ቦታዎች ሁሉ የቤተ መቅደስ መሠዊያ እንዲሠሩ አዘዘች::

ንጉሥ ቈስጠንጢኖስም በነገሠ በ30 ዓመቱ የከበረ ቦታዎች ሕንፃቸው በተፈጸመ ጊዜ ንዋየ ቅድሳትን ላከ::

በየአህጉራት ያሉ ኤጴስ ቆጶሳቶቹን ሰብስቦ አቢያተ ክርስቲያናቱን በዛሬው ቀን አከበራቸው ቅዳሴም ተቀድሶ ሁሉም ሥጋወ ደሙን ተቀበሉ በዚያ ቀን ታላቅ ደስታ ሆነ:: 

የከበረ መስቀልንም በመሸከም በነዚያ በከበሩ ቦታዎች ዞሩ በውስጣቸውም ለእግዚአብሔር ሰገዱ አመሰገኑትም መስቀሉንም አከበሩት ወደ ሀገሮቻቸውም በሰላም በፍቅር ተመልሰው ገቡ::

በዛሬው ዕለት የመስቀልን ደመራ ደምረን በአደባባይ በተለያዩ አብያተ ክርስቲያን በየሰፈራችንም ተሰብስበን የምናከብርበት ዕለት ነው::

በዚህ ዕለት የሚከበረው ደመራ በየሰፈራ ሰፈሩና በየመንደራ መንደሩ የተለየ መንፈሳዊ ያልሆነ አከባበር እየተደረገ ሲከበር እየተመለከትን ነውና መንፈሣዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር የቤተ ክርስቲያን ልጆች በያለንበት ቦታ ልንቆጣጠረው ይገባል::

መንፈሣዊ ይዘት እንዲኖረው በያለንበት ቦታ ለበዓሉ የሚዘጋጁትን ነገሮች መንፈሣዊ ይዘት እንዲኖራቸው በማድረግ ኃላፊነት ወስደን መሥራት ይጠበቅብናል::

በመዝሙር ተጀምሮ በመዝሙር እንዲያልቅ በመንፈሣዊ ተጀምሮ በሥጋዊ እንዳያልቅ ማስተማርና መምከር ከእኛ ይጠበቃል::

መልካም የደመራና የመስቀል በዓል ይሁንልን አሜን!

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በመስቀሉ ኃይልም ሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን ይጠብቀን ለዘላለሙ አሜን::
🇪🇹@ethiopianorthodoxs⛪️⛪️

Ethiopian Orthodoxs Daily

20 Jan, 23:47


(የሉቃስ ወንጌል ምዕ. 16)
----------
19፤ ቀይ ልብስና ቀጭን የተልባ እግር የለበሰ አንድ ባለ ጠጋ ሰው ነበረ፥ ዕለት ዕለትም እየተመቸው በደስታ ይኖር ነበር።

20፤ አልዓዛርም የሚባል አንድ ድሀ በቍስል ተወርሶ በደጁ ተኝቶ ነበር፥

21፤ ከባለ ጠጋውም ማዕድ ከሚወድቀው ፍርፋሪ ሊጠግብ ይመኝ ነበር፤ ውሾች እንኳ መጥተው ቍስሎቹን ይልሱ ነበር።

22፤ ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደ አብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ባለ ጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ።

23፤ በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ።

24፤ እርሱም እየጮኸ። አብርሃም አባት ሆይ፥ ማረኝ፥ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ አለ።

25፤ አብርሃም ግን። ልጄ ሆይ፥ አንተ በሕይወትህ ሳለህ መልካም እንደ ተቀበልህ አስብ አልዓዛርም እንዲሁ ክፉ፤ አሁን ግን እርሱ በዚህ ይጽናናል አንተም ትሣቀያለህ።

26፤ ከዚህም ሁሉ ጋር ከዚህ ወደ እናንተ ሊያልፉ የሚፈልጉ እንዳይችሉ፥ ወዲያ ያሉ ደግሞ ወደ እኛ እንዳይሻገሩ በእኛና በእናንተ መካከል ታላቅ ገደል ተደርጎአል አለ።

27፤ እርሱም። እንኪያስ፥ አባት ሆይ፥ ወደ አባቴ ቤት እንድትሰደው እለምንሃለሁ፤ አምስት ወንድሞች አሉኝና፤

28፤ እነርሱ ደግሞ ወደዚህ ሥቃይ ስፍራ እንዳይመጡ ይመስክርላቸው አለ።

29፤ አብርሃም ግን። ሙሴና ነቢያት አሉአቸው፤ እነርሱን ይስሙ አለው።

30፤ እርሱም። አይደለም፥ አብርሃም አባት ሆይ፥ ነገር ግን ከሙታን አንዱ ቢሄድላቸው ንስሐ ይገባሉ አለ።

31፤ ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ፥ ከሙታንም እንኳ አንድ ቢነሣ አያምኑም አለው።
🇪🇹@ethiopianorthodoxs⛪️⛪️

Ethiopian Orthodoxs Daily

20 Jan, 23:43


የቅዱስ ሚካኤል ተአምር:-
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ዘጠኝ በዚህች ቀን በሮም አገር ፍሩምያ በምትባል ከተማ ቅዱስ ሚካኤል ላደረገው ተአምር መታሰቢያ ሆነ::

ነገሩም እንዲህ ነው የሰማይ ሠራዊት አለቃ በሆነ በከበረ መልአክ በቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚታዩ ድንቆችና ተአምራቶች ምክንያት ዮናናውያን ሰዎች ሰይጣናዊ ቅናት አደረባቸው::

ከመቅናታቸውም ብዛት የተነሣ በዚያ አካባቢ የሚወርደውን የወንዝ ውኃ በዚያች ቤተ ክርስቲያን ላይ አቅጣጫውን አስቀይረው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሊመልሱትና ከሚጠብቃት መጋቢዋ ጋር በውኃ ስጥመት ሊአጠፋት አሰቡ::

የሰማያዊያን ሠራዊት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም ለቤተ ክርስቲያኑ መጋቢ ለናርጢኖስ ተገለጠለት ወደ ርሱም ቀርቦ ጽና አትፍራ አለው ይህንን ብሎ በእጁ ውስጥ ባለ በትር ወንዙ ሊመጣ ባለበት አቅጣጫ አለቱን መታው አለቱም ተሰንጥቆ እንደ በር ሆነ የዚያ ወንዝ ውኃው በውስጡም አልፎ ሔደ::

ይህንንም ያዩ ምንም ማድረግ የማይሳነውን ምስጉን እግዚአብሔርን አመሰገኑት የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልንም አከበሩት::

ከዚያች ቀን እስከ ዛሬ የወንዙን ውኃ በዚያች በተሠነጠቀች አለት ውስጥ አልፎ ሲሔድ ያዩታል ወደ መላእክት አለቃ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከቶ አይቀርብም::

እንግዲህ እናስተውል የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ እንመልከት በእምነታችን ፀንተን ከታመንን መልአኩን ልኮ ሊመጣብን ከታቀደው ፈተናና መከራ ፈጥኖ ያድነናል!

እንግዲህ ማናቸውንም አንፍራ ከሁሉ ነገር እርሱ ያድነናልና።

ዘወትር ወደ ቤተ ክርስቲያን መመላለስን አናቋርጥ በጎ ሥራንም አንተው ከክፉ ሥራ እንራቅ በእምነታችን ጸንተን ከሚመጣው መከራ እንዲጠብቀን በጾም በጸሎት እንታጋ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት ይማረን ይጠብቀን ለዘላለሙ አሜን::
🇪🇹@ethiopianorthodoxs⛪️⛪️

Ethiopian Orthodoxs Daily

20 Jan, 23:34


ነብዩ ኢሳያስ:-
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም 6 በዚህች ቀን ታላቅ ነቢይ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ አረፈ::

ይህም ነቢይ ለይሁዳ በነገሡ 5 ነገሥታት ዘመን አስተማረ እኒህም ኢዮአታም: አካዝ: ሕዝቅያስና ምናሴ ናቸው::

በአካዝ ዘመን እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ::

እንሆ ስለዚህ እግዚአብሔር ምልክት ይሰጣችኋል:: እንሆ ድንግል ፀንሳ ወንድ ልጅን ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች:: ትርጎሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደሆነ ማለት ነው:: እርሱም በኃጢአታቸው ከሚመጣባቸው ፍዳ ወገኖቹን የሚያድናቻው ወደ ሃይማኖቱም የሚአስገባቸው እንደሆነ የእስራኤልም ልጆች መስዋዕታቸውንና ክህነታቸውን እንደሚሽር ከሐዲስ ወገኖችም የሚያመሰግኑት ካህናት እንደሚሾሙ ተናገረ::

የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬምም ኢየሩሳሌምን ከቦ የስድብ ቃልን በክብር ባለቤት እግዚአብሔር ላይ በተናገረ ጊዜ የፋርስ ንጉሥ ሰናክሬም ያጠፋው ዘንድ እግዚአብሔር እንዳለው ለሕዝቅያስ ትንቢትን ተናገረ::

በዚያች ሌሊትም እግዚአብሔር የላከው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደ ሠናክሬም ሰፈር መጥቶ ከፋርስ ሠራዊት 185ሺ አርበኞችን ገደለ::

ሕዝቅያስም ታሞ ለሞት በተቃረበ ጊዜ ኢሳይያስ ወደርሱ መጥቶ እግዚአብሔር ትሞታለህ እንጂ አትድንም ብሏልና ቤትህን አዘጋጅ አለው።

እሱም ፊቱን ወደ ግድግዳው መልሶ ወደ እግዚአብሔር ለመነ ፈጽሞ ጽኑ ልቅሶንም አለቀሰ:: ልቅሶው ተሰማለት የአባትህ የዳዊት ፈጣሪ ጸሎትህን ሰማሁ ዕንባህንም አየሁ እንሆ በዘመንህ ላይ ዐሥራ አምስ ዓመት ጨመርኩልህ አለው::

እዚህ ጋር ስናስተውል ንስሐ መግባት በዕድሜ ላይ ዕድሜ እንደሚጨምር ነው ስለዚህ ስለሠራነው በደልና ኃጢአት ንስሐ ገብተን ፊታችንን ወደ እግዚአብሔር ልንመልስ ይገባል።

ምናሴም ኢሳይያስን በመጋዝ ሰንጥቆ ገደለው::

ከክ.ል.በ 910 ዓመት አስተማረ ትንቢት እየተናገረም ሰባ ዓመት ከዚህም በላይ ይሆናል::

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከሁላችን ጋር ትኑር አሜን::
🇪🇹@ethiopianorthodoxs⛪️⛪️

Ethiopian Orthodoxs Daily

20 Jan, 23:27


ቀሪ ዘመናችንን  ሁሉ እንደ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት የእግዚአብሔርን አሳብ በመፈጸም የምንባረክበት ዘመን እንዲሆንልን፤ ዘመን ለፍስሐ ዕድሜ ለንሰሐ እንዲያድለን፤ 2017 ዓ.ም የሰላም የፍቅር የአንድነት እንዲሁም የመተሳሰብ እንዲያደርግልን መልካም ምኞቴን እገልፃለሁ። መልካም አዲስ ዓመት🌼

Ethiopian Orthodoxs Daily

20 Jan, 23:22


የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሩፋኤል:-
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጳጒሜ ሦስት በዚህች ቀን የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ የሩፋኤል የበዓሉ መታሰቢያ ነው::

እርሱም ከመላእክት አለቆች ሦስተኛ የሆነ ነው::

ሩፋኤል ማለት ደስ የሚያሰኝ ቸር መሐሪ ቅን የዋህ ማለት ነው::

እኔ ሩፋኤል ኃጢአተኛችን በእግዚአብሔር ዘንድ አልከሳቸውም ከኃጢአታቸው በንስሐ እስኪመለሱ ስለ ቅንነቴ በእነርሱ ላይ እታገሳለሁ::

ሩፋኤል ራሱ በሃያ ሦስት የመላእክት ነገድ ሠራዊት ላይ እግዚአብሔር የሾመኝ እኔ ሩፋኤል ነኝ::

እግዚአብሔር አብን ይቅር ባይ ልጁን አጽናኝ አዳኝ የሆነ መንፈስ ቅዱስን እናመሰግነው ዘንድ::

በደብረ ጽዮን በሚደረገው የሺ ዓመት ተድላ ደስታ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የክብር ጽዋን በሚሰጣቸው ጊዜ ለቅዱሳኖቹ በጎ ነገርን እንደ ሰጣቸው እግዚአብሔር ያዘዘኝ ሩፋኤል እኔ ነኝ::

ደግሞም በዚህች ቀን ከዕፀ ሕይወት ዐጽቅ ወስጄ ለተመረጡ ክርስቲያኖች በእጄ እንድሰጣቸው ያዘዘኝ እኔ ሩፋኤል ነኝ::

የሰማይ መዛግብት ከእጄ በታች ተጠብቀው የሚኖሩ እኔ ሩፋኤል ነኝ::

እግዚዚአብሔር እንዳዘዘኝ እከፍታቸዋለው እዘጋቸዋለሁ::

በምድር ሰው ለባልንጀራው ስለ ስሜ በጎ ነገር ቢያደርግ እኔ በመከራው በችግሩ እረደዋለሁ ወይም የሹመቴን ነገር የሚጽፍ ወይም ከቅዱሳን ጋር ስሜን የሚያስብ ወይም በስሜ ለቊርባን የሚሆነውን የሚሰጥ ይኸውም እግዚአብሔር በሊቃነ መላእክት ክብር የሾመኝና ያከበረኝ ጳጒሚን ሦስት ቀን ነው::

ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት እስከሚገባ በብርሃን ሠረገላ እኔ እሸከመዋለሁ::

በምድር ላይ ከቶ እንደርሱ ያለ የማይገኝ መዐዛው እጅግ ጣፋጭ በሆነ ሽቱ ነፍሶቻቸው እርሱን በማሽተት ደስ እንዲላቸው አደርጋለሁ::

ሐዋርያት ሆይ በእግዚአብሔር ፊት እስከምትቆሙ እጠብቃቹ ዘንድ ከእኔ ርዳታን ሹ::

የዚህ መልአክ ሩፋኤል ታምራቶቹ ብዙ ናቸው ስለ እኛም ይማልዳል::

በዛሬው ዕለት አፍላጋት ወንዞች ውቅያኖሶች ሁሉ ይባረካሉ ከሰማይ የእግዚአብሔር መልአክ በመስቀል ሁሉንም ውኃ ይባርካል ምእመናንም በመጠመቅ በረከትን ይወስዳሉ::

ምእመናንም ይህን ስለሚያውቁ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ጀምረው በየአጥቢያቸው ወዳሉ መጠመቂያ ሔደው ይጠመቃሉ ከሰማይ በሚወርደውም ዝናብ ይጠመቃሉ::

በዚህ ዕለት መምህረ ንስሐቸውን ወደ ቤት ጠርተው ጸበል ያስረጫሉ:: በቤታቸው ያሉትን ዕቃዎች ሁሉ እደጅ አውጥተው ጠበል ያስረጫሉ::

በዚህች ቀን የበረታ የዳዊትን መዝሙር በሙሉ ይጸልያል አባታችን ሆይ እና ሰላም ለኪንም በጥሞና በዓመቲቱ ልክ ሦስት መቶ ስሳ ስድስት ጊዜ ይጸልያሉ::

ይህ ለመላኩ ለቅዱስ ኡራኤል የተሰጠው ቃል ኪዳን ነውና::

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ መልአክ አማላጅነት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን::
🇪🇹@ethiopianorthodoxs⛪️⛪️

Ethiopian Orthodoxs Daily

20 Jan, 23:15


ፈረስ የሚጋልብ ሰው ልጓሙን በአግባቡ ካልያዘው በቀር ፈረሱም ጋላቢውም ይጎዳሉ፡፡ አንድ እባብ የነደፈው ሰው ባለመድኃኒቶችን አግኝቶ መርዙ ወደ ሰውነቱ ኹሉ እንዳይሰራጭ ካላደረገ በቀር ወደ ሞት ሊደርስ ይችላል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ አንድ ትንሽ ቁስል በጊዜው ጊዜ ካልታከሙት በቀር ሰፍቶና ተስፋፍቶ ትልቅ ቁስል ወደ መኾን ያድጋል፡፡

በእኛ በክርስቲያኖች ዘንድም እንደዚህ ነው፡፡ የኃጢአት ቁስል የሚሰፋው ችላ ሲባል ነው፡፡ ገና ትንሽ ነው በሚባልበት ደረጃ ካላራቅነው በቀር ነገ ከነገ ወዲያ ትልቅ ቁስለ ነፍስ ይኾናል፡፡

ተመልከቱ! ዛሬ ላለመቈጣት የሚታገል ሰው ነገ ሰዎችን የሚጎዳበት ዘዴን አይዘይድም፡፡ ሰዎችን የሚጎዳበት ዘዴ ካልዘየደም ብዙ ባልንጀሮች ይኖሩታል፡፡ ብዙ ባልንጀሮች ካሉት የሚጠላቸውም የሚጠሉትም ሰዎች አይኖሩም፡፡ ባልንጀራ እንጂ ጠላት የሌለው ሰውም የምግባር ኹሉ ፍጻሜ የኾነውን ፍቅር ገንዘብ ያደርጋል፡፡

ስለዚህ ተወዳጅ ሆይ! ወደዚህ ምግባር ታድግ ዘንድ ወደዚህ እንዳታድግ የሚያደርጉህን ጥቃቅን ኃጢአቶችን ከአንተ አርቅ፡፡ ሰፍቶ ተስፋፍቶ ነገ እንዳይቸግርህ ዛሬ በእንጭጩ እያለ ችላ አትበለው፡፡

ይሁዳ ገና የገንዘብ ፍቅር ደረጃ ላይ እያለ ራሱን ቢመረምርና ይህን ለማራቅ ቢጥር ኖሮ በኋላ ከተሰበሰበው ገንዘብ ወደ መስረቅ ባላደገ ነበር፡፡ ገና ከመጀመሪያው ደረጃ እያለ ችላ ባይል ኖሮ የኃጢአት ኹሉ ራስ የኾነው ኃጢአት ወደ መፈጸም ባልደረሰ ነበር፡፡

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እንደዚህ ልናደርግ እንደሚገባን ሲያስተምረን ከዝሙት ብቻ እንድርቅ ሳይኾን የእርሱ ሥር የኾነውንና አይቶ መመኘትን ችላ ልንለው እንደማይገባን ነገረን (ማቴ.5፡28)፡፡ ኃጢአት ሥር ሰዳና ሰፍታ ከመቸገራችን በፊት በችግኝ ደረጃ ላይ እያለች ነቅለን መጣል ቀላል ነውና፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ

Ethiopian Orthodoxs Daily

20 Jan, 23:09


መድኃኒታችንም እንዲህ አለው ወዳጄ ሆይ አንተ በመከራዬ መሰልከኝ እኔም በመንግሥቴ

ከእኔ ጋራ እንድትመስለኝ አደርግሃለሁ::

እነሆ የዚህ ዓለም ድካምህ ተፈጸመልህ በእኔ ዘንድም የምቀበለው ሆነ ከእንግዲህስ መንግሥተ ሰማያትን ትወርስ ዘንድ ና::

እንሆ ስምህን ለሚጠራ መታሰቢያህን ለሚያደርግ ገድልህን ለሚጽፈው ለሚያነበውና ለሚሰማውም ቤተ ክርስቲያንህን ለሚሰራ በስምህ መባ ለሚሰጥ ለድኆችም በስምህ ለሚመጸውት በመታሰቢያህ ቀን ለሚቆርብ ስለ አንተ በጎ ሥራ ለሚሠራ ሁሉ እኔ እስከ ዐሥር ትውልድ እምርልሃለሁ::

አባታችንም እጅግ ደስ አለው ለጌታችንም ሰገደ ጌታችንም ከእርሱ ዘንድ በታላቅ ክብር ወደ ሰማይ ዐረገ::

ከዚህም በኋላ አባታችን በንዳድ በሽታ ጥቂት ታመመ ዕድሜውም ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከስምንት ወር ከአንድ ቀን ሆኖት በለመለመ ዕርግና አረፈ::

በመዘመርና በማመስገን አክብረው ገንዘው በዋሻው ውስጥ ቀበሩት::

ይህንን በማሰብ ከዋዜማው ጀምሮ ታላቅ በዓል እናደርጋለን በተክለ ሃይማኖት ስም በተሰራች ቤተ ክርስቲያን በገዳማት ተሰባስበን እግዚአብሔርን እናመልካለን::

እግዚአብሔር ሆይ በፃድቁ ስም ተሰባስበን ስናመሰግንህ በፃድቁ ስም መልካም ስንሰራ ቃል ኪዳንህን አታስቀርብን ና ባርከን ፈውሰን አሜን እንላለን::

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባታችን ተክለ ሃይማኖት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከሁላችን የክርስቲያን ወገኖች ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን::
🇪🇹@ethiopianorthodoxs⛪️⛪️

Ethiopian Orthodoxs Daily

20 Jan, 23:09


አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነሐሴ ሃያ አራት በዚህች ታላቅ ዕለት የከበረ ሐዲስ ሐዋርያ የትሩፋትም መምህር የሆነ አባታችን ተክለ ሃይማኖት አረፈ::

የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ጸጋ ዘአብ የእናቱ ስም እግዚእ ኀርያ ነው::

እሊህም ቅዱሱን ለኢትዮጵያ የሃይማኖት ብርሃንን ላበሩ ካህናት ከወገኖቻቸው የሆኑ ናቸው::

እግዚእ ኀረያም መካን ስለሆነች ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር እያዘኑ ሲጸልዩ ኖረ::

በዚህም ነገር እያሉ የዳሞት ገዥ ሞተለሚን ሰይጣን አነሣሣው የሸዋን አውራጃዎች እስከ ጅማ እስከ ገዛ ድረስ::

የየሀገሩ መኳንንቶችም በየተራቸው ሚስቶቻቸውን ይሰጡታል:: ከማረከውም ደምግባት ያላቸውን ሴቶች ያገኘ እንደሆነ ቁባቶቹ ያደርጋቸዋል::

በዚያ ወራት ወደ ጽላልሽ ደርሶ ብዙ ክርስቲያኖችን ገደለ ከእርሳቸውም የሚበዙትን ማረከ ጸጋ ዘአብም ከግድያ ፍርሃት የተነሳ ሸሸ::

አንድ ወታደርም ተከተለው እርሱም ወደ ባሕር ተወርውሮ ገባ በእግዚአብሔርም ፈቃድ በባሕሩ ውስጥ ተሸሸገ::

ሚስቱን እግዚእ ኀረያንም ወታደሮቹ ማረኳት ወደ ሞተለሚም አደረሷት በአያትም ጊዜ ውበቷንና ላህይዋን አደነቀ::

በልቡም እጅግ ደስ ብሎት ብዙ ሽልማትን ጌጥን ሰጥቷት በሽልማትና በጌጥ ሁሉ ሸለማት አስጌጣትም የጋብቻ ሥርዓትንም ማዘጋጀት ጀመረ:: ለሠርጉም እንዲሰበሰቡ ወደ መኳንቶቹ ሁሉ ላከ::

እግዚእ ኀርያም ይህን በሰማች ጊዜ ከአረሚ ጋር አንድ ከመሆን ያድናት ዘንድ በብዙ ልቅሶ ወደ እግዚአብሔር ጸሎትን አደረገች::

ያን ጊዜ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል በብርሃናዊ ክንፉ ተሸክሞ ከዳሞት አገር ወደ ምድረ ዞረሬ አድርሶ ወዲያውኑ ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ በሴቶች መቆሚያ አቆማት::

ባሏ ጸጋ ዘአብም ከማዕጠንት ጋራ በወጣ ጊዜ እንደተሸለመች ቁማ አያት አድንቆ በልቡ ይቺ ሴት ምንድ ናት ወደዚህስ ማን አመጣት አለ::

የማዕጠንቱንም ሥራ ጨርሶ ወጣ በጠየቃትና በመረመራት ጊዜ እርሷ ሚስቱ እግዚእ ኀርያ እንደሆነች አገኛት:: እርሷም ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው እግዚአብሔር ያደረገላትን ነገረችው::

ከዚህም በኃላ የእግዚአብሔር መልአክ በአንዲት ሌሊት ተገለጠላቸው::

የዜናው መሰማት በዓለም ሁሉ የሚደርስ የተባረከ ልጅ ይወልዱ ዘንድ እንዳላቸው ነገራቸው አበሠራቸው::

ከጥቂት ቀኖች በኋላ ይህ ቅዱስ ተፀንሶ በታኅሣሥ ወር በሃያ አራት ተወለደ::

በጸጋ ዘአብና በእግዚእ ኀረያ በቤታቸው ታላቅ ደስታ ሆነ ከዘመዶቻቸው ጋራ ደስ አላቸው:: ለክርስትና ጥምቀት ባስገቡት ጊዜ ፍስሐ ጽዮን ብለው ሰየሙት::

ሕፃኑም አደገ ድንቅ ተአምራትንም እያደረገ ዕውቀትንና ኃይልንም ተመልቶ በመንፈስ ቅዱስ ጸና::

ከዚህም በኋላ ዲቁና ይሾም ዘንድ አባ ጌርሎስ ወደ ተባለ ጳጳስ ወሰዱት ::

በዚያ ዘመን በዛጔ መንግሥት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ አባ ቢንያሚ ነበር:: ወደ ጳጳሱ ባደረሱት ጊዜ ይህ ልጅ የተመረጠ ዕቃ ይሆናል ብሎ ትንቢት ተናገረለት::

የዲቁና ሹመትን ተቀብሎ ወደ ሀገሩ ተመለሰ ጎልማሳም በሆነ ጊዜ አራዊትን ሊያድን ወደ ዱር ሔደ::

ቀትር ሲሆንም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልኩ በሚያምር ጎልማሳ አምሳሎ በቅዱስ ሚካኤል ክንፍ ላይ ተገለጠለትና እንዲህ አለው::

ወዳጄ አትፍራ እንግዲህስ የኃጢአተኞችን ነፍስ ወደ ሕይወት የምታጠምድ ትሆናለህ እንጂ አራዊትን የምታድን አትሆንም ስምህም ተክለ ሃይማኖት ይሁን::

እንደ ኤርሚያስና አጥማቂው ዮሐንስ እኔ ከእናትህ ማኅፀን መርጬ አክብሬሃለውና::

እንሆ በሽተኞችን ትፈውስ ዘንድ ሙታንንም ታሥነሣ ዘንድ ሥልጣንን ሰጠሁህ ርኵሳን አጋንንትንም ከሁሉ ቦታ ታሳድዳቸዋለህ::

ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ ገንዘቡን ሁሉ ለድሆችና ለምስኪኖች በተነ:: ዓለሙንም ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጠፋ ለሰው ምን ይጠቅመዋል እያለ ቤቱን እንደተከፈተ ትቶ ምርጒዙን ይዞ በሌሊት ወጣ::

ከዚህም በኋላ ወደ ጳጳስ ሒዶ የቅስና ሹመት ተቀብሎ ለሸዋ አገር ሁሉ ወንጌልን መስበክ ጀመረ::

ዐሥራ ሁለት ሽህ ሦስት መቶ ነፍስ ያህል አጠመቀ:: ለጣዖት የሚሰዉበትን ሁሉ ሻረ:: በውስጡ የሚኖሩ አጋንንትን እስኪሸሹ ድረስ ዐፀዶቻቸውን ሁሉ ቆረጠ::

ሁለተኛም ወደ ዳሞት ምድር ሒዶ ብዙ ሟርተኞችንና አስማተኞችን ጠንቋዮችን አሳመነ::

ከሀዲ ሞተለሚም ብዙ ወራት ተቃወመው:: በጉማሬ ማጥመጃ ውስጥ በመጨመር ብዙ ጊዜ ወደ ገደል ወረወረው::

እርሱ ግን በደኅና ይመላለሳል ደግሞ ሊወጋው ጦር ወረወረ ጦሩም ተመልሶ እጁን ወግቶ ተጠመጠመበት በተሰቃየም ጊዜ አባታችንን ለመነው እርሱም የክብር ባለቤት በሆነ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አሳምኖ አዳነው የተጠመጠመበትን ጦርም ፈታለት ቀናውን መንገድ የሚያጣምሙ ሟርተኞችንም አጠፋቸው::

ከዚህ በኋላ በክብር ባለቤት ጌታችን ስም ያደረገውን ድንቅ ተአምራቱን አይተው የአገር ሰዎች ሁሉም ከንጉሣቸው ጋራ አመኑ::

የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው:: ቤተ ክርስቲያንም ሠርቶላቸው የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት አስተማራቸው:: በቀናች ሃይማኖትም አጸናቸው ከዚህም ሁሉ ጋራ በጾም በጸሎት በስግደት ሁል ጊዜ ያለ ማቋረጥ ተጠምዶ ይጋደል ነበር::

ዜናውንም ሰምተው ወደርሱ የሚመጡትን የነፍሳቸውን ድኅነት ያስተምራቸዋል የክብር ባለቤት የሆነ ጌታችን ኢየሱስ በማመንም ያጸናቸዋል::

ከዚህም በኋላ በኤልያስ ሠረገላ ተቀምጦ ወደ አምሐራ ሀገር ሔደ:: በገድል ተጸምዶ ወደ ሚኖር መነኰስ ወደ አባ በጸሎተ ሚካኤል በአንዲት ቀን ደርሶ በዚያ እንደ ባሪያ ሲያገለግል ኖረ::

በአንድነት የሚኖሩ መነኮሳትንም ያገለግላቸው ነበር የሞተውንም እስከማንሳት ድረስ ከደዌያቸው ይፈውሳቸው ነበር:: 

በዚያም ዐሥራ ሁለት ዓመት ከሆነው በኋላ ሐይቅ በሚባል ቦታ ወደ ሚኖረው ወደ ኢየሱስ ሞዓ የእግዚአብሔር መልአክ እንዳዘዘው ሔደ:: ከእርሱም የምንኩስና ልብስ ቀሚስና ቅናትን ተቀበለ::

ሁለተኛም ወደ ኢየሩሳሌም ሔዶ ከከበሩ ቦታዎችና ከሊቀ ጳጳሳቱ ቡራኬን ተቀበለ::

ከዚያም ወደ ሸዋ ምድር ተመልሶ የአባቱ ወንድም ልጅ የሆነ አባ ዜና ማርቆስን አገኘው በወግዳ በረሀም በአንድነት ኖሩ::

ከዚያም ግራርያ ወደሚባል አገር ሒዶ በኮረብታ መካከል ዋሻ አዘጋጅቶ ተቀመጠ:: በቀንም በሌሊትም ከዚያ አይወጣም ነበር ከጥቂት ቅጠልም በቀር እህልን አይቀምስም መጠጡም ጥቂት ውኃ ነው::

ብዙ ወንዶችና ሴቶች ወደርሱ መጥተው መነኮሳቶች ሆኑ በአንድ ቤት ውስጥ በአንድ መኝታ ላይ ተኝተው ያድራሉ እርስ በእርሳቸውም አይተዋወቁም::

እነርሱም እንደ ሕፃናት ናቸው: በጸሎትና በቅዳሴ ጊዜም በአንድነት ይቆማሉ በዘመኑ ሰይጣን ስለ ታሠረ ወንዱ ሴቷን ሴት እንደሆነች አያውቅም እንዲሁም ሴቷ ወንዱን ወንድ እንደሆነ አታውቅም::

ከዚህ በኋላ መጠጊያ ሠርቶ በፊቱ በኋላም በቀኙ በግራው የተሳሉ ፍላጻዎችን ተከለ ይህንንም ማድረጉ በመደገፍና በመተኛት እንዳያርፍ ነው በዚያም እግሩ ከቅልጥሙ እስቲሰበር ሰባት ዓመት ቆመ::

በዚያም ወራት ምንም የዕንጨት ፍሬ ወይም ቅጠል ሳይቀምስ ውኃም ሳይጠጣው ኖረ::

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደርሱ መጣ ከእርሱም ጋራ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ደግሞ የከበሩ ነቢያትና ሐዋርያት ሁሉም ሰማዕታትና ጻድቃን የጳጳሳት አለቆች የመላእክት አለቆችም ከሠራዊቶቻቸው ጋራ አሉ::

Ethiopian Orthodoxs Daily

20 Jan, 23:07


(የማቴዎስ ወንጌል ምዕ. 21)
----------
18፤ በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ።

19፤ በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርስዋ መጣ፤ ከቅጠልም ብቻ በቀር ምንም አላገኘባትምና። ለዘላለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት። በለሲቱም ያንጊዜውን ደረቀች።

20፤ ደቀ መዛሙርቱም ይህን አይተው። በለሲቱ ያንጊዜውን እንዴት ደረቀች? ብለው ተደነቁ።

21፤ ኢየሱስም መልሶ። እውነት እላችኋለሁ፥ እምነት ቢኖራችሁ ባትጠራጠሩም፥ በበለሲቱ እንደ ሆነባት ብቻ አታደርጉም፤ ነገር ግን ይህን ተራራ እንኳ። ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር ብትሉት ይሆናል፤

22፤ አምናችሁም በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ ትቀበላላችሁ አላቸው።
https://t.me/ethiopianorthodoxs

Ethiopian Orthodoxs Daily

20 Jan, 23:02


የነሐሴ ፩፱ ቅዳሴ ምንባብ 📖
(1ኛ የጴጥሮስ መልእክት ምዕ. 3)
----------
8፤ በመጨረሻው ሁላችሁ በአንድ ልብ ሁኑ፥ የሌላው መከራ ለእናንተ እንደሚሆን አድርጉ፥ እንደወንድሞች ተዋደዱ፥ ርኅሩኆችና ትሑታን ሁኑ፤

9፤ ክፉን በክፉ ፈንታ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ በዚህ ፈንታ ባርኩ እንጂ፥ በረከትን ልትወርሱ ለዚህ ተጠርታችኋልና።

10፤ ሕይወትን ሊወድ መልካሞችንም ቀኖች ሊያይ የሚፈልግ ሰው፥ መላሱን ከክፉ ከንፈሮቹንም ተንኰልን ከመናገር ይከልክል፤

11፤ ከክፉ ፈቀቅ ይበል፥ መልካምንም ያድርግ፥ ሰላምን ይሻ ይከተለውም፤

12፤ የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን ናቸውና፥ ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው ተከፍተዋል፥ የጌታ ፊት ግን ክፉ ነገርን በሚያደርጉ ላይ ነው።

13፤ በጎንም ለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማን ነው?

14፤ ነገር ግን ስለ ጽድቅ እንኳ መከራን ብትቀበሉ ብፁዓን ናችሁ። ማስፈራራታቸውንም አትፍሩ አትናወጡም፥

15፤ ዳሩ ግን ጌታን እርሱም ክርስቶስ በልባችሁ ቀድሱት። በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን።
🇪🇹@ethiopianorthodoxs⛪️⛪️

Ethiopian Orthodoxs Daily

20 Jan, 22:58


አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅ ዱስ ስም የተወደዳቹ የዚህ ጹሑፍ ቤተሰቦች እንኳን አደረሳችሁ ሰባኤውን በሰላም አስፈጽሞ ለዚህ ታላቅ ቀን ያደረሰን አምላክ ይክበር ይመስገን።

የዛሬን መልዕክት ከብዙ በጥቂቱ በሦስት ክፍል ከፍዬ አቅርቢዋለሁና በረከቷ ረድኤቷ ይድረሰን አሜን!

ነሐሴ 16 በዚህች ቀን አምላክን የወለደች የእመቤታችን ድንግል ማርያም ሥጋዋ ያረገበት መታሰቢያዋ ሆነ::

ከዕረፍቷም በኋላ ከእርሳቸው ስለመለየቷ ሐዋርያት ፈጽሞ እያዘኑ ነበር::

ከዚህም በኋላ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ተገለጠላቸው እርሷን በሥጋ ያዩ ዘንድ እንዳላቸውም ተስፋ ሰጣቸው::

ወንጌላዊ ዮሐንስም እስያ በሚባል አገር እያስተማረ ሳለ በነሐሴ ወር 16 ቀን ተድላ ደስታ ወዳለበት ገነት በመንፈስ ቅዱስ ተነጠቀ::

የክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ካለበት ከዕፀ ሕይወት ሥር ተቀምጦ አየው::

የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጣ ዘንድ ምድርን እንዲጠሩዋት ሰባቱን የመላእክት አለቆች አዘዛቸው::

እነርሱም የንጽሕት እናቱን ሥጋ ታወጪ ዘንድ እግዚአብሔር አዞሻል አሏት::

ያን ጊዜም ከዕፀ ሕይወት በታች ካለ መቃብር የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ ወጣ::

የክብር ባለቤት ጌታችንም እንዲህ እያለ አረጋጋት የተወደድሽ የወለድሽኝ እናቴ ሆይ ዘላለማዊ ወደ ሆነ መንግሥተ ሰማያት አሳርግሽ ዘንድ ነዪ::

ያን ጊዜም በገነት ያሉ ዕፅዋት ሁሉ አዘነበሉ መላእክት የመላእክት አለቆች ጻድቃን ሰማዕታትም እየሰገዱላትና ፈጽሞ እያመሰገኗት አሳረጓት::

አባቷ ዳዊትም ንግሥት እመቤታችን ወርቀ ዘቦ ለብሳ ደርባ ደራርባ በቀኝህ ትቀመጣለች እያለ በበገና አመሰገናት::

በኪሮቤል ሠረገላ ተቀምጣ ከዐረገች በኋላ በልጅዋና በፈጣሪዋ ቀኝ በታላቅ ክብር ተቀመጠች::

2...ወንጌላዌ ዮሐንስ ከእርሷ በረከትን ተቀብሎ ሰግዶላት ተመልሶ ወረደ።

ሐዋርያትን ተሰብስበው ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ ፈጽመው ሲያዝኑና ሲተክዙ አገኛቸው::

እርሱም እንዳየ እንደሰማ ሥጋዋንም በታላቅ ክብር በምስጋና እንዳሳረጓት ነገራቸው::

ሐዋርያትም በሰሙ ጊዜ ዮሐንስ እንዳየና እንደሰማ ባለማየታቸውና ባለመስማታቸው እጅግ አዘኑ::

ከዚህ በኋላ እያዘኑ ሳለ እንሆ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠላቸውና የፍቅር አንድነት ልጆች ሰላም ይሁንላቹ ስለ እናቴ ማርያም ሥጋ ለምን ታዝናላችሁ::

እንሆ እርሷን በሥጋ ላሳያችሁ ልባችሁም ደስ ሊለው ይገባዋል አላቸው ይህንንም ብሎ ከእርሳቸው ዘንድ ወደ ሰማያት ዐረገ::

ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆዩ የነሐሴ ወር በባተ ቀን ለሐዋርያት ዮሐንስ እንዲህ አላቸው አምላክን የወለደች የእመቤታችንን ሥጋዋን ለማየት የተዘጋጀን አድርጎ ያሳየን ዘንድ ኑ ይህን ሁለት ሱባዔ በመጾም የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንለምነው በልጅዋ በወዳጅዋ ቀኝ ተቀምጣ አይተን በእርሷ ደስ እንዲለን::

በዚያን ጊዜም ዮሐንስ እንዳላቸው በጾም በጸሎት ሱባዔ ያዙ የነሐሴ ወር እንደ ዛሬ ዐሥራ ስድስተኛ ቀን በሆነ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉኑም ሐዋርያት ወደ ሰማይ አወጣቸው በታላቅ ክብር በተወደደ ልጅዋ ቀኝ ተቀምጣ ከሥጋዋ ተዋሕዶ ተነሥታ እመቤታችን ማርያምን አዩዋት::

እጆቿንም ዘርግታ የከበሩ ሐዋርያትን እየአንዳንዳቸውን ባረከቻቸው በልባቸውም እጅግ ደስ አላቸው::

የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስም በከበረ ሥጋውና ደሙ ላይ ሠራዔ ካህን ሆነ::

እስጢፋኖስም አዘጋጀ ዮሐንስም በመፍራት ቁሙ አለ::

ሁሉም ሐዋርያት በመሠዊያው ዙሪያ ቆሙ በዚያን ጊዜ ከቶ እንደርሱ ሁኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታ ሆነ::

3.....ጌታችንም የቅዳሴውን ሥርዓት በፈጸመ ጊዜ ሥጋ ውንና ደሙን አቀበላቸው::

ከዚያም በኪሩቤልና በሱራፌል ሠረገላ ተቀምጣ በምታርግ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ እመቤታችን ማርያምን እንዲህ ብሎ ተናገራት::

በዚህች ቀን የሆነ የዕርገትሽን መታሰቢያ በዓለም ውስጥ እንዲሰብኩ ልጆችሽ ሐዋርያትን እዘዣቸው::

መታሰቢያሽን የሚያደርገውን ሁሉ ተጠብቆም በዚህች ቀን ቅዱስ ቁርባንን የሚቀበለውን ኃጢአቱን እደመስስለታለሁ::

የእሳትን ሥቃይ ከቶ አያያትም መታሰቢያሽን ለሚያደርጉ ሁሉ በዚህች ቀን ለድኆች በስምሽ ለሚመጸውቱ ቸርነቴ ትገናኘዋለች ይህም ሥጋሽ ወደ ሰማይ ያረገበት ነው::

እመቤታችንም ድንግል ማርያምም ክብር ይግባውና ጌታችንን እንዲህ አለችው።

ልጄ ሆይ እንሆ በዐይኖቻቸው አዩ በጆሮቻቸው ሰሙ በእጆቻቸውም ያዙ ሌሎችም ታላላቅ ድንቆች ሥራዋችን አዩ::

እመቤታችንም ይህንን ስትናገር በታላቅ ደስታ ወደ ደብረ ዘይት ተመለሱ::

የተወደዳቹ ወንድሞች ሆይ በፍጹም ደስታ መታሰቢያዋን እናደርግ ዘንድ ይገባናል እርሷ ስለ እኛ ወደተወደደ ልጅዋ ሁል ጊዜ ትማልዳለችና::

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይማረን በረከቷም ሐዋርያት ከሰበሰቧት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ከሁላችን ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን::
@ethiopianorthodoxs