በሀገረ እንግሊዝ ግዙፍ የመድረክ ሥራዎች ከሚካሄድባቸው ጥቂት የሙዚቃ ፌስቲቫል ማቅረቢያ ቦታዎች ውስጥ Troxy Music Hall (ትሮክሲ የሙዚቃ አዳራሽ) አንዱ ነው። ይህ ታሪካዊ የጥበብ አዳራሽ ግዙፍ አዳራሾችን በመገንባት በሀገሪቷ ትልቅ እውቅናን ባተረፈው አርክቴክት ጆርጅ ኮልስ እ.ኤ.አ በ1932 ዓመተ ምህረት የተገነባ ነው። Troxy Music Hall (ትሮክሲ የሙዚቃ አዳራሽ) በእንግሊዝ ሎንዶን ከተማ ውስጥ የሚገኝ ግዙፉና እድሜ ጠገብ ዘመናዊ አዳራሾች መካከል አንዱ ነው።
በዚህ ግዙፍና ታሪካዊ የሙዚቃ አዳራሽ ውስጥ የዓለማችን አንጋፋ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ አቀንቃኞች የመድረክ ስራዎቻቸውን አቅርበውበታል። ከነዚህም ውስጥ በእንግሊዝ የሙዚቃ ሰንጠረዥ ላይ በነጠላ ዜማ አንደኛ ደረጃን በመያዝ ቀዳሚዋ ሴት የሆነችው ትውልደ እንግሊዛዊቷ የሶሎ ሙዚቃ አቀንቃኟ ሊታ ሮዛ ተጠቃሽ ስትሆን ሌሎችም ምዕራባውያን እና ነጭ አሜሪካውያን ጥበበኞች ለበርካታ አመታቶች ስራዎቻቸውን አቅርበውበታል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጥቁሮችም በመድረኩ መታየት ጀምረዋል።
እነሆ ከአፍሪካ ኢትዮጵያን በመወከል ለመጀመሪያ ጊዜ እውቁ የኪነጥበብ ባለሙያ የክቡር ዶ/ር አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “ፍቅርን እንጋራ” በሚል መሪ ቃል የሙዚቃ ስራዎቹን February 1/2025 የሚያቀርብ ይሆናል።
የክቡር ዶክተር አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ለመጨረሻ ጊዜ በሎንዶን ከተማ የሙዚቃ ስራውን ያቀረበው እ.ኤ.አ በJuly 25/2015 ነበር። እነሆ ከ10 አመታቶች በኋላ በሚዘጋጀው በዚህ ታላቅ የሙዚቃ ድግስ ላይ ከኢትዮጵያ፣ ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ ግዛቶች የቴዲ አፍሮ አድናቂዎች የሙዚቃ ኮንሰርቱን ለመታደም ይገኛሉ።
✍#ታታ_አፍሮ (ነፃ ብዕር)