እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል አደረሰን!!!
ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቅድስተ ቅዱሳን፣ ከተለዩ የተለየች፣ ከተመረጡ የተመረጠች ክብርት እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በከበረች ቀን ግንቦት አንድ ቀን ተወለደች፡፡ የመወለዷም ነገር እንዲህ ነው፡፡ በጥሪቃና ቴክታ የተባሉ የእግዚአብሔር ሰዎች ነበሩ፤ ባለጸጎች ቢሆንም ልጅ ግን አልነበራቸውም፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ቴክታ ሕልም አለመች፡፡ ለባሏም እንዲህ ስትል ነገረችው «በራእይ ነጭ ዕንቦሳ ከማሕፀኔ ስትወጣ፤ ያችም ዕንቦሳን እየወለደች እስከ ፮ ትውልድ ስትደርስ ፮ኛይቱ ጨረቃን ስትወልድ ጨረቃ ደግሞ ፀሐይን ስትወልድ አየሁ» አለችው፡፡ (ውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ)
ባሏ በጥሪቃም «ራእዩስ ደግ ነው፤ የሚፈታልን የለም እንጂ» አላት፡፡ በማግሥቱ ለሕልም ፈቺ ሔዶ ነገረው፡፡ ሕልም ፈቺውም «እግዚአብሔር በምሕረቱ አይቷችኋል፤ በሣህሉ መግቧችኋል» ብሎ ፮ቱ እንስት ጥጆች መውለዳቸው ፯ ሴቶች ልጆች እንደሚወልዱ፤ ፯ኛይቱ በጨረቃ መመሰሏ ከሰው የበለጠች ከመላእክት የከበረች ደግ ፍጥረት እንደሚወለዱ፤ የፀሐይ ነገር ግን እንደንጉሥ ያለ ይሆናል አልተገለጸልኝም ብሎ ነገረው፡፡ (ነገረ ማርያም)