የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኅብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የሚያከናውናቸው የአካባቢ ልማት ስራዎች በሕዝብ ተሳትፎና እምነት የሚተገበሩ መሆናቸውን የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ፀሐይ ኪባሞ ገልፀዋል::
ኮሚሽኑ በዛሬው ዕለት በኅብረተሰብ ተሳትፎና ሀብት አሰባሰብ ዙሪያ ያተኮረ የፓናል ውይይት መድረክ አካሂዷል። በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ የብሎክ ካውንስል መሪዎች ፣ የወረዳና የክፍለ ከተማ አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። ሕዝብ የለያቸው የልማት ፍላጎቶች በነዋሪው የገንዘብ ፣ የዓይነትና የእውቀት አስተዋፅዖ እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ በሚመድበው የድጎማ በጀት ይከናወናሉ።
ከህዝቡ የሚሰበሰብ ማንኛውም ሀብት በህጋዊ ደረሰኝ ብቻ እንዲሆን ማድረግ የሀብት አጠቃቀም ውጤታማነትን ለማረጋገጥና የብልሹ አሰራር ተጋላጭነትን ለመቀነስ እንደሚያግዝ ምክትል ኮሚሽነሯ አብራርተዋል። ወቅቱን የጠበቀ ኦዲት በማድረግ ግልፅነትን መፍጠር የኅብረተሰቡን ቀጣይነት ያለው ተሳትፎ ለማሳደግ ጥቅም እንዳለው ነው ወ/ሮ ፀሐይ የተናገሩት።
በበጀት ዓመቱ የተያዙ የልማት ስራዎችን በወቅቱ ለማጠናቀቅ ከወዲሁ ሀብት በበቂ ሁኔታ ማሰባሰብ እንደሚገባ በመድረኩ ተገልጿል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በቂ የሀብት መሰብሰቢያ ደረሰኝ በማሰራጨትና ክትትሉን በማጠናከር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን በመጠቆም ለልማት ስራው ውጤታማነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
"ሁሉ አቀፍ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ለዘላቂ ልማት!"