በእንተ ኢሳይያስ 53
ክፍል ሦስት
(በወንድም ሚናስ)
በስመ እግዚአብሔር መሓሪ ወመስተሣህል
ቍጥር 9
“በአፉ ተንኰል ሳይገኝበት፣ ምንም ወንጀል ሳይሠራ፣ #አሟሟቱ ከክፉዎች፣ መቃብሩም ከባለጠጎች ጋር ኾነ።”
וַיִּתֵּן אֶת-רְשָׁעִים קִבְרוֹ, וְאֶת-עָשִׁיר #בְּמֹתָיו; עַל לֹא-חָמָס עָשָׂה, וְלֹא מִרְמָה בְּפִיו.
ይሁዲ ወገኖቻችን በዚህ ክፍል የሚያቀርቡት ሙግት בְּמֹתָיו “ቤሞታው” የሚለው ስም ብዜት ስለኾነ፣ ዕብራይስጡ የሚለን “አሟሟቱ” ሳይኾን “አሟሟታቸው” የሚል ነው፤ ስለዚህ ቊጥሩ ካንድ በላይ ለሚኾኑ አካላት የተነገረ እንጂ ነጠላ አካልን ይኸውም መሲሑን የሚመለከት አይደለም ይሉናል። ኾኖም ግን የይሁዲ ወገኖቻችን ሙግት ተቀባይነት የማያገኝበት ምክንያት፣ በመጽሐፍ ቅዱሳዊው ዕብራይስጥ ኾነ በዘመናዊው ዕብራይስጥ ዘንድ፣ በብዙ ቍጥር የተጻፈ ቃል፣ ዐልፎ ዐልፎ አንድን አካል ብቻ ሊያመለክት የሚችልበት አግባብ አለ፤ ለምሳሌ רחמים “ራሓሚም”፣ הָאֲדֹנִ֑ים “ሃአዶኒም” የሚሉት ቃላት የብዜት ቃላት ቢኾኑም፣ በብዙ ቦታዎች ነጠላ የኾኑ ማጣቀሻዎችን ሲያመለክቱ ይስተዋላል። የሴማዊ ቋንቋዎች ተመራማሪ እና የነገረ መለኮት ጸሓፊ የኾኑት፣ አይሁዳዊው ሊቅ ዶክተር ማይክል ብራውን “የብዜት ቃላት ለነጠላ አካል መጠቀም፣ በቋንቋው ዓለም(በዕብራይስጥ) ዠማሪ ለኾኑ ተማሪዎች እንኳ ሳይቀር እንግዳ ያልኾነ የተለመደ የሰዋስው ሥርዐት ነው” በማለት ይናገራሉ። በማስከተልም ሊቁ “በብሉይ ኪዳን ውስጥ ‛ሞት’ የሚለው ስም በብዙ ቍጥር የተጠቀሰበት ኹለት ጥቅሶች የሚገኙ ሲኾን፤ ይኸውም ኢሳ. 53፥9 እና ሕዝቅኤል 28፥10 ናቸው፤ ታዲያ በሕዝቅኤል 28፥10 ነጠላ ሞትን (תָּמוּת “ታሙት” ) ለማመልከት የብዜት አገላለጽን ( מוֹתֵי “ሞቴይ”) እንደተጠቀመ ማስተዋል ያስፈልጋል።” በማለት בְּמֹתָיו “ቤሞታው” የሚለው የብዜት ቃል ነጠላ አካልን ሊያመልክት እንደሚችል በስፋት ይሞግታሉ[1]
በዘመናችንም ኾነ በጥንት ዘመን በነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራት ደግሞ ይህን ጥቅስ እንዴት እንደተረዱት ጠቅለል ባለ መልኩ ደግሞ እንመልከት፡-
፩.በሙት ባሕር ጥቅሎች(መሲሑ ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት የነበረ) ላይ እንደሚታየው፣ ይህ ጥቅስ የተጻፈው በነጠላ ግስ፣ “አሟሟቱ” (“בומתו”) ተብሎ ነው።
፪.የሰባ ሊቃናት ትርጕም አዘጋጆችም የዕብራይስጡ ምንባብ፣ ስለ አንድ አካል እየተናገረ መኾኑን በመረዳት፣ በነጠላ “አሟሟቱ” ( ἀντὶ τοῦ θανάτου “አንቲ ቱ ታናቱ” ) ብለው ተርጒመው አስቀምጠዋል።
፫.ታርጒም ዮናታን ቤን ዑዝኤል ወደ አረማይክ በተተረጐመው ሥራ አሟሟቱ ብሎ በነጠላ (בְמוֹתָא) ገለጸው እንጂ፣ በብዙ ቊጥር (בְמוֹתָיא) ክፍሉን አላስቀመጠውም።
ይቀጥላል።
1.Michael L. Brown, Answering Jewish Objections to Jesus, Volume Three – Messianic Prophecy Objections: ገጽ. 49-57.
@Who_is_jesus