---------------------------
(ዜና ፓርላማ) ጥቅምት 13 ቀን ፣2017 ዓ.ም፤ ሱሉልታ፤ ኢትዮጵያ የፀጥታ እና የደህንነት ተቋማትን እምርታ በማምጣት ላይ መሆኗን ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አመላከቱ።
ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ የፀጥታ እና የደህንነት ተቋማትን በመገንባት ረገድ የረጅም ጊዜ ባለ ታሪክ መሆኗንም ገልፀዋል።
የዛሬው የሥልጠና ርዕሰ ጉዳይ "የፀጥታና ደህንነት እመርታ" የሚል ሲሆን በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለኢፌድሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራርና አባላት እንዲሁም ለሕዝብ ተወካዮች እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የጽህፈት ቤቶች አመራሮች የሥልጠናው ገለፃ በክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ቀርቧል።
ክቡር ም/ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ተመስገን ባቀረቡት ገለፃ ሀገራችን የፀጥታና የደህንነት ተቋማትን በመገንባት ረጅም አመታትን ማስቆጠር ብቻ ሳይሆን እነዚህ ተቋማት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ አልፈው እንደ ኮሪያ፣ ኮንጎ እና በሌሎች ሀገራት በመሰማራት ሰላም የማስከበር ሀገራዊ ሀላፊነታቸውን መወጣት የቻሉ ናቸው ብለዋል።
ተቋማቱ የየራሳቸው ጥንካሬ ቢኖራቸውም የነበረባቸው ክፍተት ሊያርም በሚችል መልኩ አሁን ላይ በክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ አነሳሽነት ወቅቱን በሚመጥን ደረጃ የሪፎርም ሥራ በመሠራቱ ከፍተኛ አቅም ለመፍጠር ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል።
ዘመኑ የኢኮኖሚ፣ የቴክኖሎጂ የበላይነት ፉክክር የሚታይበት ብቻ ሳይሆን የጦርነትም በመሆኑ ኢትዮጵያም ከየትኛውም አካል የሚሰነዘርባትን ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል የራሷን የፀጥታና ደህንነት ተቋማትን የመገንባትና በሪፎርም የማጠናከር ሥራ ሠርታለች፤ ትሰራለችም፤ ሲሉ አስገንዝበዋል።
በመሆኑም መከላከያን ጨምሮ በፀጥታ ተቋማት፣ በኢትዮጵያ የመረጃና ደህንነት፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት እና በፋይናንስ ደህንነት የተጠናከረ የሪፎርም ሥራ መሰራቱንም ነው ክቡር ም/ጠቅላይ ሚንስትር ተመስገን ጥሩነህ ያብራሩት።
የክቡር ም/ጠቅላይ ሚንስትሩ ገለፃ ዛሬ 6ኛ ቀን ባስቆጠረው ሥልጠና ላይ ቀጥሏል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament
በዩቲዩብ
https://www.youtube.com/@FDREHOPR
በቴሌግራም
https://t.me/ParlamaNews
በትዊተር
http://twitter.com/fdrehopr
በዌብሳይት
www.hopr.gov.et ይከታተሉ።