በቤተ ክርስቲያን የተሐድሶ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ የነበረው ጀርመናዊው ማርቲን ሉተር (Nov.10, 1483 - Feb.18, 1546)፣ "ጻድቅ በእምነት ይኖራል" (ሮሜ 1፡17) የሚለውን ቃል መሠረት በማድረግ፣ በወቅቱ የነበረውን የሮም ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ፣ በተለይም በድነት፣ በአማኝና በቤተ ክርስቲያን ማንነት ዙሪያ ፊት ለፊት በመቃወም የጀመረው ታላቅ የተሐድሶ ንቅናቄ በቅርቡ አምስት መቶ ዓመት አልፎታል። ይህን ታሪካዊ ቀን ለማስታወስ በዓለም ዙሪያ፣ በተለይም በትውልድ ሀገሩ በጀርመን ዝግጅት ተደረጎ ነበር። ሉተር የወቅቷን የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ስሁት አስተምህሮና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በቀጥታ የሚጋጭ ተልኳዊ የራስ-ግንዛቤ የተቃወመበት 95 ጭብጥ ሀሳብ የያዘ ጽሑፍ "thesis" በቪተንበርግ ከተማ ቤተ ክርስቲያን (Wittenberg Castle Church) በር ላይ የለጠፈው ጥቅምት 31፣ 1517 ነበር። ይህቺ ቀን፣ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከፍታለች፤ የታሪክም መገንጠያ ሆና ትታሰባለች።
ሉተር ማንም ሊደፍረው የማይችለውን የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስትያንን የተሳሳተ መሠረት፣ በነፍሱ በመወራርድ አናውጧል። April 18, 1521 በንጉሥ ቻርልስ አምስተኛ (የስፔንና የሮማ ካቶሊካዊ ግዛት ንጉሥ) በተሰየመው የቤተ ክህነት ፍርድ ቤት፣ አስተምህሮውን እንዲሽር (recant) በተጠየቀ ጊዜ፡- በታሪክ "እነሆ እዚህ ቆሜለሁ" (Here I stand) በመባል በሚታወሰው የሙግት ንግግሩ እንዲህ ብሎ ነበር፦
"የተከበሩትን ፓፓ ጨምሮ፣ ማንም ግለሰብ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማስረጃነት በመጥቀስ ስህተቴን ካሳየኝ፣ ጽሁፌን በአደባባይ አቃጥላለሁ። ሆኖም ኅሊናዬ የቅዱሳት መጻሕፍት እውነት እስረኛ ሆኗል፤ ስለዚህ ከበራልኝ የእውነት ብርሃን ፈቀቅ ለማለት ኅሊናዬ አይፈቅድም፤ አያዋጣኝምም!"
May 8, 1521፣ ፍርድ ቤቱ "ኑፋቄ" በማለት ከቤተ ክርስቲያን አባልነት በሞት ፍርድ አገደው። ሥራዎቹም ታገዱ፤ ማንበብም ሆነ ማሰራጨት ሕገ ወጥ ድርጊት መሆኑ ታወጀ። ይሁን እንጂ፣ ሉተር እስከሞተበት ጊዜ ድረስ በታማኝት፣ በሞት ጥላ ውስጥ እያለፈ አገልግሏል።
ሉተር በብዙ መከራ ውስጥም እያለፈ፣ ውሎው ከእግዚአብሔር ቃል ጋር፣ ልቡም በመንግሥቱ ንጹህ የወንጌል ሥራ ላይ ያተኮረ ነበር። ትጉህ፣ የማይለጉም፣ ለጠራው እግዚአብሔርና ለበራለት እውነት ታማኝ ነበር። በዓመት ሁለት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ከጥግ እስከ ጥግ ያነብ ነበር። በሙሉ ጊዜ ፕሮፌሰርነት እያገለገለ፣ መጽሐፍ ቅዱስን በጀርመንኛ ተርጉሞ፣ ለገዛ ሕዝቡ የማይጠፋ ርስት አድርጎ አውርሷል። የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ሕይወቱ እስትንፋስ አድርጎ ነበር የሚይስበው። የዘወትር የውስጥ ጩኸቱም;፟ "ዓይኖቼን ክፈት፥ ከሕግህም ተኣምራትህን አያለሁ።" (መዝ 119፡18) የሚል ነበር። እንዲህም ብሎ ጽፏል፦ "መጽሐፍ ቅዱስ ዛፍ፣ በውስጡም የተጻፉት ቃላት ቅርንጫፎች ቢሆኑ፣ እያንዳንዱን ቅርንጫፍ ደጋግሜ ወጥቼ ወርጄበታለሁ።" (What Luther Says: An Anthology, Vol. 1, p. 83)። ይኽም ለቃሉ የነበርው ረሃብ ያሳየናል። ከርስቶስን ያማከለ ታላቅ የቃሉም ሰባኪ ነበር። ከ1510-1546 ሦስት ሺህ ጊዜ ያህል ሰብኳል። ያም ማለት በአንድ ቀን ተኩል፣ አንድ የወንጌል ስብከት ማለት ነው። ምንም እንኳን፣ የቀድሞ አባቶችን ሥራዎች ጠንቅቆ ቢያጠናም፣ የስብከቱ ዋና ምንጭ ቅዱስ ቃሉ ነበር። የጸሎት ሰው ነበር - ከልቡ! ከከንቱ ኀይማኖተኝነት የመነጫ ሙት ልምምድ ሳይሆን፣ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል የተደገፈና ሕያውነት የተሞላ ጸሎት ነበር። የተሃድሶውም ጩኸት መሠርቱ፣ የእግዚብሔር ቃልና የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ነበር። የእኛስ የስብከታች መካከለኛ ምን ይሆን?
መዝሙር 46 ብዙ አጽናንቶታል። ልጅ ሞቶበታል፤ ከስሜት መርበሽ ጋር ታግሏል። እድሜውን በሙሉ በሞት ዐዋጅ ጥላ ውስጥ ነበር የኖረው። ማንም ሰው ቢያገኘው፣ እንዲገድለው ሕጋዊ ፈቃድ የሰጠው የቻርልስ አምስተኛ የሞት ዐዋጅ እንዲህ ይል ነበር፡-"ሥጋዬ፣ ነፍሴ፣ ደሜ፣ በመንግሥቴ ግዛት ያለ አስተዳደርና ዜጋ ሁሉ ሉተርን ከምድር ገጽ እንዲያጠፋው አዝዣለሁ" (Heiko A. Oberman, Luther: Man Between God and the Devil, 29.)። በኩላሊት ህመምና የራስ ምታት (ማይግሬን)፤ በሆድ ድርቀት፤ በጆሮ ቁስልና የትኩሳት ንዳድ ይሰቃይ ነበር። በአጋንት መንፈስ ነው የሚመራው፤ ሀሰተኛ ነብይም ተብሏል። August 2, 1527 የጻፈው ማስታወሻ እንዲህ ይላል፦
"ከሳምንት በላይ በሞትና በሲዖል ጥላ ውስጥ ተመላልሻለሁ። በክርስቶስ ላይ ያለኘ መታመን እስኪፈተን ድረስ መላው አካሌና መጋጣጠሚያዎቼ ሁሉ ታመዋል። የመከራ ጎርፍና ማዕበል ተባብረው፣ እምነትን የሚፈትን ድቅድቅ የቀን ጨለማ ውስጥ ከተውኛል። ተስፋ መቁረጥ ልቤን አድክሞታል። ይሁን እንጂ በቅዱሳን ምልጃ ተርፈኩኝ፤ እግዚአብሔርም በምህረቱ አሰበኝ፤ ከመከራዬም አሳረፈኝ። " (Man Between God and the Devil, 323.)
እናም ከዳዊት ጋር፦ "አምላካችን መጠጊያችንና ኀይላችን፣ በሚደርስብን መከራ ሁሉ የቅርብ ረዳታችን ነው። ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ እንኳ፣ ተራሮችም ወደ ባሕር ጥልቅ ቢሰምጡ አንፈራም። ውሆች ቢያስገመግሙ፣ ዐረፋ ቢደፍቁም፣ ተራሮችም ከውሆቹ ሙላት የተነሣ ቢንቀጠቀጡም አንደናገጥም።" (መዝ 46:1-3) በማለት ዘምሮ፣ በጸጋው ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ ሠርቶ አለፈ።
ጌታ ተሃድሶውን ይስደድልን፣ ዘመንን መረዳት እንደአባቶች ይለግሰን! አሜን!
(በዶ/ር Girma Bekele )
#ተሐድሶው
#ማርቲን_ሉተር