እግዚአብሔር ሕዝቡን ከግብጽ ምድር ካወጣ በኋላ በምድረ በዳ ኪዳኑን በቃሉ አጸናላቸው—በዐሥርቱ ትእዛዛት። ይህን ተቀብሎ ለሕዝቡ ያደረሰው ሙሴ ነበር፤ "ሙሴ እህል ሳይበላ፣ ውሃም ሳይጠጣ ከእግዚአብሔር ጋር አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በዚያ ነበር፤ በጽላቶቹ ላይ የቃል ኪዳኑን ቃሎች፣ ዐሥርቱ ትእዛዛትን ጻፈ" (ዘፀ 34፥28)። እግዚአብሔር ለአብርሃም እንደ ገባው ኪዳን ሕዝቡን በታላቅ ክንድ ካስወጣ በኋላ፣ ለኪዳኑ ፍጻሜ የሚጠበቅባቸውን በሕጉ በኩል ገለጠላቸው። ጌታ ኢየሱስ እንዳረጋገጠልንም፣ እነዚህ ትእዛዛት እግዚአብሔርንና ባልነጀራን በመውደድ የሚፈጸሙ ናቸው—ማቴ 22፥40። በ 40 ቀን ቆይታ ይዞ የወረደው ኪዳን፣ በቆይታ—በሕይወት ዘመን—የሚጸና ነው። እግዚአብሔር ፍጹምና የማይለወጥ ስለሆነ ኪዳኑን አያፈርስም፤ በኪዳኑ በመጽናት በርሱ የሚታገዙም እንዲሁ በፍቅር ኪዳኑ ውስጥ ይጸናሉ።