ልጆቼ! እስኪ ፍቀዱልኝና ዛሬ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡፡ ብዙውን ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ትመላለሳላችሁ፡፡ መልካም ነው፡፡ ግን ምን ለውጥ አመጣችሁ? ምን ፍሬ አፈራችሁ? ታገለግላላችሁን? ከአገልግሎታችሁ ምን ረብሕ አገኛችሁ?
ጥቅምን ካገኛችሁ በእውነት ምልልሳችሁ የጥበበኛ ምልልስ ነበር ማለት ነው፡፡ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ወንጌላውያን እንዲህ እያስተማሩን ሳለ የማንለወጥ ከሆነ ግን የእስከ አሁን ምልልሳችን የአይሁድ ምልልስ ነበር ማለት ነው፡፡ አይሁዳውያን ሕገ ኦሪትን የተሰጠቻቸው ኃጢአታቸውን በእርሷ መስታወትነት አይተው ንስሐ እንዲገቡባት ነበር፡፡ እነርሱ ግን የንስሐ ፍሬ ሳያፈሩባት እንዲሁ ይመኩባት ነበር፡፡ ስለሆነም ለሕይወት የተሰጠቻቸው ሕግ ሞት ሆና አገኟት፡፡ እኛም እንዲህ ለኵነኔ ያይደለ ለጽድቅ የተሰጠችን ወንጌል ፍሬ የማናፈራበት ከሆነ ከአይሁዳውያን የባሰ ቅጣት ትፈርድብናለች፡፡
እስኪ ምሳሌ መስዬ ላስረዳችሁ፡፡ አንድ የሚታገል ሰው (wrestler) በየጊዜው ተጋጣሚውን እንደምን ማሸነፍ እንዳለበት ልምምድ የሚያደርግ ከሆነ ክህሎቱ ይዳብራል፡፡ ተጋጣሚውም በቀላሉ ማሸነፍ ይቻሏል፡፡ በየጊዜው ራሱን የሚያሻሽል (Update) የሚያደርግ ሐኪም ጐበዝ አዋቂና ሕመምተኞችን በአግባቡ የሚረዳ ይሆናል፡፡ በየቀኑ ቃሉ የሚነገረን እኛስ ምን ለውጥ አመጣን? ምን ፍሬ አፈራን?
እየተናገርኩ ያለሁት ለአንድ ዓመት ብቻ በቤተ ክርስቲያን የቆዩትን ምእመናን አይደለም፡፡ እየተናገርኩ ያለሁት ከልጅነታችን አንሥተን በቤቱ ለምንመላለስ እንጂ፡፡ ይህን ያህል ዘመን በቤቱ እየተመላለስን ፍሬ ካላፈራን ቤተ ክርስቲያን ደርሰን ብንመጣ ምን ጥቅም አለው? አባቶቻችን አብያተ ክርስቲያናት ያነጹልን ለምንድነው? ዝም ብለን እንድንሰባሰብ ነውን? እንደዚህማ በገበያ ቦታም መሰባሰብ አንችላለን፡፡ አበው አብያተ ክርስቲያናትን ያነጹለን ቃሉን እንድንማርበት፣ በተማርነው ቃልም የንስሐ ፍሬ እንድናፈራበት፣ ሥጋ ወደሙን እንድንቀበልበተ፣ እርስ በእርሳችን እንድንተራረምበት እንጂ ለሌላ ዓላማ አይደለም፡፡
ታዲያ ምን ፍሬ አፈራን?