ጋሜል Media

@gamel_media


✍️ "ጋሜል" ማለት "እግዚአብሔር ሊመረመር የማይቻል ግሩም ድንቅ ነው።" ማለት ነው። ✍️
✍️ "ጋሜል ብሂል ግሩም እግዚአብሔር።" ✍️
✍️ "Gamel" means "God is wonderful beyond measure." ✍️
መዝሙረ ዳዊት (Psalm) 118÷7

Youtube - https://www.youtube.com/channel/UCHxwszkxLPFCFKAOf1WtaDw

ጋሜል Media

22 Oct, 03:11


በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል፤ ሕዝብም ከሆነ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያልሆነ የመከራ ዘመን ይሆናል፤ በዚያም ዘመን በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ እያንዳንዱ ይድናል

ዳንኤል 12፥1

በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም፥”

ራእይ 12፥7

ከዚህ በኋላ ታላቅ ስልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁከክብሩም የተነሣ ምድር በራች

ራእይ 18፥1

እንኳን ለሊቀ መልአኩ ለቅዱስ ሚካኤል ወርኃዊ መታሰቢያ በዓል አደረሳችሁ!

@Gamel_Media

ጋሜል Media

16 Oct, 14:56


ማንም፦
እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው።

ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?

እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን።

1ኛ ዮሐንስ 4÷20

@Gamel_Media

ጋሜል Media

11 Oct, 20:19


#የያዕቆብ_ሌሊት ያድርግልን ማለት ምን ማለት ነው?
            
    በመጀመሪያ ያዕቆብ ማነው?

ቅዱስ ያዕቆብ የይስሐቅ ልጅ ማለትም የአባታችን የአብርሃም የልጅ ልጅ ነው።

የአብርሃም ልጅ ይስሐቅ ርብቃን አገባ ርብቃም መካን ስለነበረች ልጅ አልነበራትምና አባታችን ይስሐቅ ስለ ሚስቱ እግዚአብሔርን ለመነ እግዚአብሔርም ተለመነው ርብቃ ሚስቱም ፀነሰች።

ልጆቹም በሆዷ ውስጥ ይገፋፉ ነበር ርሷም እንዲህ ከሆነ ይህ ለእኔ ምኔ ነው አለች። ከእግዚአብሔርም ትጠይቅ ዘንድ ሄደች።

እግዚአብሔርም እንዲህ አላት ሁለት ወገኖች በማህፀንሽ ናቸው ሁለቱም ሕዝብ ከሆድሽ ይከፈላሉ ሕዝብም ከሕዝብ ይበረታል ታላቁም ለታናሹ ይገዛል።

ትወልድ ዘንድ ዘመኗ በተፈፀመ ጊዜም እነሆ በማህፀኗ #መንታ ነበሩ።

በፊትም የወጣው ቀይ ነበረ ሁለንተናውም ጠጉር ለብሶ ነበር ስሙም #ዔሳው ተባለ።

ከዚያም በኋላ ወንድሙ ወጣ በእጁም የዔሳውን ተረከዝ ይዞ ነበር ስሙም #ያዕቆብ ተባለ።

አባታቸው ይስሐቅም ዔሳውን ይወድደው ነበር
እናታቸው ርብቃ ግን ያዕቆብን አብልጣ ትወደው ነበር።

ስለዚህም አባታቸው ይስሐቅ በሸመገለ ጊዜ በጣም አርጅቶ ነበርና ለሚወደው ልጁ ሊባርከው (ሊመርቀው) አሰበ።
ነገር ግን እናታቸው ርብቃ የዔሳውን ምርቃን ለያዕቆብ በመምከር የዔሳውን በረከት አስወሰደችበት።

ዔሳውም በጣም ተናዶ ወንድሙ ያዕቆብን ለመግደል ወሰነ በረከቱን ወስዶበታልና።

እናቱ ርብቃም ይህ የታላቁ ልጇ የዔሳውን ቃል ደረሰላት ታናሹንም ልጇን ያዕቆብንም አስጠርታ እነሆ ወንድምህ ዔሳው ሊገድልህ ይፈቅዳል።

ልጄ ሆይ ቃሌን ስማ ተነስና ወደ ካራን ምድር ወደ ወንድሜ ወደ ላባ ሂድ የወንድምህ ቁጣ እስኪበርድለት ጥቂት ቀናት በዚያው ተቀመጥ ብላ አሳመነችው።
ያዕቆብም እሺ ብሎ መንገዱን ጀመረ።

ያዕቆብም ከቤርሳቤህ ወደ ካራን ሄደ።

ወደ አንድ ስፍራም ደረሰ ፀሐይም ጠልቃ ነበርና ከዚያ አደረ በዚያም ስፍራ ድንጋይ አነሳ ከእርሱም በታች ተንተርሶ በዚያ ስፍራ ተኛ።

ሕልምም አለመ እነሆም መሰላል በምድር ላይ ተተክሎ ራሱም ወደ ሰማይ ደረሰ እነሆም የእግዚአብሔር መላእክት ይወጡበት ይወርዱበት ነበርና።

እነሆም እግዚአብሔር በላይ ቆሞበት ነበር እንዲህም አለ የአባትህ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ይህችን አንተ የተኛህባትን ምድር ለአንተም ለዘርህም እሰጥሃለሁ።

ዘርህም እንደ ምድር አሸዋ ይሆናል እስከ ምዕራብና እስከ ምስራቅ እስከ ሰሜንና እስከ ደቡብ ትስፋፋለህ የምድርም አህዛብ ሁሉ ባንተ በዘርህም ይባረካሉ።

እነሆም እኔ ከአንተ ጋራ ነኝ በምትሄድበትም መንገድ ሁሉ እጠብቅሃለሁ ወደዚችም ምድር እመልስልሃለሁ የነገርሁህን ሁሉ እስካደርግልህ ድረስ አልተውህምና።

ያዕቆብም ከእንቅልፉ ተነስቶ በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ነው እኔ አላወቅሁም ነበር አለ።

ፈራ እንዲህም አለ "ይህ ስፍራ እንዴት ያስፈራ ይህ ስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም ይህም የሰማይ ደጅ ነው።"

ያዕቆብም ማልዶ ተነሳ ተንተርሶት የነበረውንም ድንጋይ ወስዶ ሐውልት አድርጎ አቆመው በበላዩም ዘይትን አፈሰሰበት።

ያዕቆብም ያንን ስፍራ ቤቴል ብሎ ጠራው አስቀድሞ ግን የዚያች ቦታ ስም ሎዛ ነበረ።

ያዕቆብም እንዲህ ብሎ ስእለት ተሳለ።

"እግዚአብሔር ከእኔ ጋራ ቢሆን በምሄድበትም በዚች መንገድ ቢጠብቀኝ የምበላውንም እንጀራ የምለብሰውንም ልብስ ቢሰጠኝ፥

ወደ አባቴ ቤትም በጤና ብመለስ እግዚአብሔር አምላኬ ይሆንልኛል።

ለሐውልት የተከልሁት ይህም ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ይሆናል ከሰጠኸኝም ሁሉ ለአንተ ከአስር እጅ አነዱን እሰጥሃለሁ።" ብሎ ቃል ገባ።

✝️ ስለዚህም እኛም #የያዕቆብ_ሌሊት ያድርግልን የምንባባለው

👉 እግዚአብሔር አምላክ ከቅዱሳን መላእክቱ ጋር ከእኛ ጋር እንዲያድርና ጥሩ የሰላም እንቅልፍ እንዲያስተኛን ቅዱሳን መላእክትን በሕልማችን እንዲያሳየን ከመጥፎ ህልም እንዲጠብቀን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንዲሆን ከመጥፎ አጋንንት እንዲጠብቀን #የያዕቆብ_ሌሊት ይሁንልን እንላለን።

              ወስብሐት ለእግዚአብሔር ይቆየን!!!
         ለበለጠ ኦሪት ዘፍጥረት (26-30) አንብቡት
ምንጭ: - Mule Ze Kdst Ldeta

ጋሜል Media

10 Oct, 03:39


ትመጫለሽ_አይደል?

ቤተመቅደስሽን ከበን አለን - መቅደስ ገላችን ቢረክስም

በሕንጻ መቅደስሽ ከትመናል - ሕንጻ ሥላሴን ብናፈርስም

በልማድና በእምነት መሐል – በተወጠረ መንፈሳችን

በጎጥ በጎሳ በታጠረ - በተፍረከረከ አንድነታችን

ስቀለው ስቀለው እንጂ – ምን በድሎ? በማይል ልሳናችን

ለክፋት ባደገደገ - በጎ ግብር በራቀው

ኃጢአት ባጠራቀመ – የጽድቅ መንገድ በናፈቀው

ነውርን መግለጥ እንጂ - ከባቴ አበሳነት በማያውቀው

በረከሰ ማንነት ነው – ንዒ ማርያም የምንልሽ

ከልዑሉ ሚካኤል ጋ ከደስተኛው ገብርኤል ጋ

            ጽጌ ጸዐዳ ልጅሽን ይዘሽ
            ነይ ርግባችን የምንልሽ

በሚገባ ንጽህና – ሆነን አይደለም ድንግል

ግን ነይ ስንልሽ አትቀሪም.... ትመጫለሽ አይደል?

ልባችን ቂምን ቋጥሮ በአፍ ዜማ ብቻ - ብንጠራሽም ንዒ ብንልም ድንግል

ርሕርሕተ ሕሊና እመ ትሕትና.....

ትመጫለሽ አይደል?

ስለተጠራው ስምሽ
ድንግል ትመጫለሽ አይደል?

ስለኪዳንሽ
ድንግል ትመጫለሽ አይደል?

አልቦ ምግባር ብንሆንም - እንደ ቃና ማድጋ
ማርያም አትቅሪ እኛ ጋ

ንዒ ስንል
አዛኝቱ ድንግል
ትመጫለሽ አይደል?

@Gamel_Media

ጋሜል Media

06 Oct, 18:02


እንኳን አደረሳችሁ!

ጋሜል Media

26 Sep, 20:11


የመስቀል በዓል በረቢ መካነ ጎልጎታ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን።

ጋሜል Media

26 Sep, 16:58


ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ።

ገላትያ 6፥14

እንኳን አደረሳችሁ! 🙏🙏🙏

ጋሜል Media

25 Sep, 02:42


እንኳን ለቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት እና ለአቡነ ገብረ ማርያም ዘሐንታ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት ወቀዳሜ ሰማዕት

በሕገ ወንጌል (ክርስትና) የመጀመሪያው ሊቀ ዲያቆናትና ቀዳሚው ሰማዕት ይህ ቅዱስ ነው:: ቅዱሱ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን አስገራሚ ማንነት ከነበራቸው እሥራኤላውያን አንዱ ነበር::

ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- የቅዱስ እስጢፋኖስ ወላጆቹ ስምዖንና ማርያም ይባላሉ:: (ሌሎች ናቸው የሚሉም አሉ) ገና ከልጅነቱ ቁም ነገር ወዳድ የነበረው ቅዱስ በሥርዓተ ኦሪት አድጐ እድሜው ሲደርስ ወደ ት/ቤት ገባ:: የወቅቱ ታላቅ መምሕር ገማልያል ይባል ነበር:: ይህ ሰው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 5:33 ላይ ተጠቅሷል::

በትውፊት ትምሕርት ደግሞ ይህ ደግ (ትልቅ) ሰው በርካታ ቅዱሳንን (እስጢፋኖስን: ዻውሎስን: ናትናኤልን: ኒቆዲሞስን . ..) አስተምሯል:: በጌታችን መዋዕለ ስብከት ጊዜም ከፈጣሪያችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እየቀረበ ይጨዋወት ነበር:: በፍጻሜውም አምኗል::

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ እስጢፋኖስ ከዚህ ምሑር ዘንድ ተምሮ: ኦሪቱን ነቢያቱን ጠንቅቆ ወጣ:: ወቅቱ አስቸጋሪና ለኃጢአት ሕይወት የተመቸ ቢሆንም ቅዱሱ ግን የመሲህን መምጣት በጸሎትና በተስፋ ይጠባበቅ ነበር::

በወቅቱ ደግሞ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ የንስሃ ጥምቀትን እየሰበከ መምጣቱን የተመለከተ ቅዱስ እስጢፋኖስ ነገሩን መረመረ:: ከእግዚአብሔር ሆኖ ቢያገኘው የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆነ:: ለ6 ወራትም በትጋት ቅዱስ ዮሐንስን አገለገለ:: ለ6 ወራት ከቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ ከተማረ በኋላ ለስም አጠራሩ ስግደት ይድረሰውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠመቀ:: በወቅቱ የተደረገውን ታላቅ ተአምር ልብ ያለው ቅዱስ እስጢፋኖስ መምሕሩን ቅዱስ ዮሐንስን እንዲያስረዳው ጠየቀው::
"ከእኔ ይልቅ ከፈጣሪው አንደበት ይስማው" በሚል ላከው:: ቅዱሱም ከጌታ ዘንድ ሔዶ: እጅ ነስቶ ተማረ:: (ሉቃ. 7:18) በዚያውም የጌታ ደቀ መዝሙር ሆኖ ቀረ:: ጌታም ከ72ቱ አርድእት አንዱ አድርጐት ለአገልግሎት ላከው:: አጋንንትም ተገዙለት:: (ሉቃ. 10:17)

ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌታችን መድኃኔ ዓለም ከዋለበት እየዋለ: ካደረበት እያደረ ወንጌልን ተማረ:: ምሥጢር አስተረጐመ:: ጌታ በፈቃዱ ስለ እኛ ሙቶ ከተነሳ በኋላ ሲያርግ ደቀ መዛሙርቱን በአንብሮ እድ ባርኳል:: በዚህ ጊዜም ቅዱሱ እንደ ወንድሞቹ ሐዋርያት ቅስናን (ዽዽስናን) ተሹሟል:: በበዓለ ሃምሳም መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከ72ቱ አርድእት የእርሱን ያህል ልሳን የበዛለት: ምሥጢርም የተገለጠለት የለም:: በፍጹም ድፍረትም ወንጌልን ይሰብክ ገባ::

በመጀመሪያይቱ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ከማዕድ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ፈተና ሲመጣ በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ 7 ዲያቆናት ሲመረጡ አንዱ እርሱ ነበር:: አልፎም የ6ቱ ዲያቆናት አለቃ እና የ8ሺው ማሕበር መሪ (አስተዳዳሪ) ሆኗል:: 8ሺ ሰውን ከአጋንንት ፈተና መጠበቅ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለማወቅ አባቶቻችንን መጠየቅ ነው:: አንድን ሰው ተቆጣጥሮ ለድኅነት ማብቃት እንኳ እጅግ ፈተና ነው:: መጽሐፍ እንደሚል ግን 'መንፈስ ቅዱስ የሞላበት: ማሕደረ እግዚአብሔር' ነውና ለእርሱ ተቻለው:: (ሐዋ. 6:5)

አንዳንዶቻችን ቅዱስ እስጢፋኖስ 'ሊቀ ዲያቆናት' ሲባል እንደዘመኑ ይመስለን ይሆናል:: እርሱ በመጀመሪያ ሐዋርያና ካህን ነው:: ዲቁናው ለእርሱ 'በራት ላይ ዳረጐት' ነው እንጂ እንዲሁ ዲያቆን ብቻ አይደለም::

ቅዱስ እስጢፋኖስ ከጌታ ዕርገት በኋላ ለ 1 ዓመት ያህል 8ሺውን ማሕበር እየመራ: ወንጌልን እየሰበከ ቢጋደል ኦሪት 'እጠፋ እጠፋ': ወንጌል ደግሞ 'እሰፋ እሰፋ' አለች:: በዚህ ጊዜ 'ክርስትናን ለማጥፋት መፍትሔው ቅዱስ እስጢፋኖስን መግደል ነው' ብለው አይሁድ በማመናቸው ሊገልድሉት አስበውም አልቀሩ ገደሉት::

እርሱ ግን ፊቱ እንደ እግዚአብሔር መልአክ እያበራ ፈጣሪውን በብዙ ነገር መሰለው:: በመጨረሻውም ስለ እነሱ ምሕረትን እየለመነ በድንጋይ ወገሩት:: ደቀ መዛሙርቱም ታላቅ ለቅሶን እያለቀሱ ቀበሩት::

ቅዱስ እስጢፋኖስ ካረፈ ከ300 ዓመታት በኋላ በኢየሩሳሌም የሚኖር አንድ ደግ ሰው ነበር:: ስሙም ሉክያኖስ ይባል ነበር:: በተደጋጋሚ በራዕይ ቅዱሱ እየተገለጠ "ሥጋየን አውጣ" ይለው ነበርና ሒዶ ለዻዻሱ ነገረው:: ዻዻሱም ደስ ብሎት ካህናትና ምዕመናንን ሰብስቦ ወደ አጸደ ገማልያል (የመምሕሩ ርስት ነው) ሔደ:: ቦታውንም በቆፈሩ ጊዜ ታላቅ መነዋወጥ ሆነ:: መላእክት ሲያጥኑ በጐ መዓዛ ሸተተ:: ዝማሬ መላእክትም ተሰማ:: ሕዝቡና ዻዻሱም በቅዱስ እስጢፋኖስ ፊት ሰግደው: በታላቅ ዝማሬና በሐሴት ዐጽሙን ከዚያ አውጥተው: በጽርሐ ጽዮን (በተቀደሰችው ቤት) አኖሩት:: እለ እስክንድሮስ የተባለ ደግ ሰውም ቤተ ክርስቲያን አንጾለት ወደዚያ አገቡት:: ከ5 ዓመታት በኋላም እለ እስክንድሮስ ሲያርፍ በሳጥን አድርገው በቅዱሱ ጐን ስለ ፍቅሩ አኖሩት:: ሚስቱ ወደ ሃገሯ ቁስጥንጥንያ ስትመለስ የባሏን ሥጋ መስሏት የቅዱስ እስጢፋኖስን ቅዱስ ሥጋ በመርከብ ጭና ወሰደችው:: መንገድ ላይ ከሳጥኑ ውስጥ ዝማሬ ሰምታ ብታየው ያመጣችው የቅዱሱን ሥጋ ነው:: እጅግ ደስ አላት: አምላክ ለዚህ አድሏታልና:: እርሷም ወስዳ ለታላቁ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ አስረከበች:: በከተማውም ታላቅ ሐሴት ተደረገ::

ሥጋውን ሊያኖሩት በበቅሎ ጭነው ሲወስዱትም በቅሎዋ በሰው ልሳን ተናግራ ማረፊያውን አሳወቀች:: በዚያም ላይ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ታንጾለታል:: ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲመቱ ጥቅምት 17: ዕረፍቱ ጥር 1: ፍልሠቱ ደግሞ መስከረም 15 ቀን ነው::

††† @Gamel_Media †††

ጋሜል Media

11 Sep, 18:40


2017 ዓ.ም

ጋሜል Media

10 Sep, 18:31


የባሕሩን ጥልቀት የሞገድንም ጩኸት ታናውጣለህ።

ከተአምራትህ የተነሣ አሕዛብ ይደነግጣሉ

በምድር ዳርቻም የሚኖሩ ይፈራሉ

የጥዋትን እና የማታን መውጫ ደስ ታሰኛቸዋለህ።

ምድርን ጐበኘሃት አጠጣሃትም
ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ

የእግዚአብሔር ወንዝ ውኃን የተመላ ነው

ምግባቸውን አዘጋጀህ
እንዲሁ ታሰናዳለህና።

ትልምዋን ታረካለህ
ቦይዋንም ታስተካክላለህ
በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ
ቡቃያዋንም ትባርካለህ።

በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ
ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል።

የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ
ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ።

ማሰማርያዎች መንጎችን ለበሱ
ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ
በደስታ ይጮኻሉ ይዘምራሉም።

መዝሙር 65÷7

እንኳን ከ2016 ዓ.ም ወደ 2017 ዓ.ም በሠላም አሸጋገረን!

@Gamel_Media

ጋሜል Media

21 Aug, 19:26


ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ
አንተ ወታቦተ መቅደስከ።

“አቤቱ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት።”
መዝሙር 131፥8

ታቦት ማደርያ ማለት ሲሆን
መቅደስ የሚባለው ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ነው።

“ኢየሱስም መልሶ፦ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው።......... እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር።”

ዮሐንስ 2፥19-21

የመቅደስህ ታቦት ማለት ደግሞ የሥጋህ ማደርያ ማለት ነው 9 ወር ከ 5 ቀን አድሮባታልና።

ስለዚህ ቅዱስ ዳዊት በትንቢት መነጽር ተመልክቶ በተናገረው መሠረት እርሷም እንደ ልጇ ተነስታለችና

"አቤቱ፥ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት።” እያልን እንደ ቅዱስ ዳዊት እናመሰግናለን።

እንኳን ለእናታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የእርገት መታሰቢያ በዓል በሠላም አደረሳችሁ።

@Gamel_Media

ጋሜል Media

19 Aug, 01:09


+ የሐዲስ ኪዳን ደብረ ሲና +

አይሁድ ‘እኛ የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንደተናገረው እኛ እናውቃለን ይህ ሰው ግን  ከወዴት እንደሆነ አናውቅም’ ብለው ክርስቶስን ሊያቃልሉ ሞክረው ነበር፡፡

ዛሬ በደብረ ታቦር የተከናወነውን ቢያውቁ ምን ይሉ ይሆን? እነርሱ ሕጉን እንጠብቃለን ብለው የሚመኩበትና የእርሱን ሕግ እየጠቀሱ ክርስቶስን ሊነቅፉ የሚሞክሩበት ሙሴ ዛሬ በታቦር ተራራ ከጌታ ፊት በፍርሃት ቆመ፡፡ አይሁድ ይህንን ቢያዩ ምን ይሉ ይሆን? ፈሪሳውያን ሆይ ወደ ደብረ ታቦር ብቅ ብትሉ የእርሱ ደቀ መዛሙርት ነን ብላችሁ የምትመኩበት ሙሴን የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ሆኖ ታገኙታላችሁ፡፡ የሕግ ፍጻሜ ክርስቶስ የሕጉን ተቀባይ ሙሴን ጠርቶ እያነጋገረው ነው፡፡ ሙሴም በሲና ተራራ በዛፍ ላይ ሲነድ ካየው እሳት ጋር እየተነጋገረ ነው፡፡

አይሁድ ሆይ በጌታ ፊት በትሕትና ብትቀርቡ ኖሮ የት እንደተቀበረ እንኳን የማታውቁትን ሙሴ ለማየት በታደላችሁ ነበር፡፡ የሙሴን መጻሕፍት በቃላችሁ የምታውቁ ሕግ አዋቂዎች ሆይ እናንተ ቁጭ ብላችሁ ክርስቶስ ለሦስት ትሑታን ዓሣ አጥማጆች ሙሴን እያሳያቸው ነው፡፡ ‘ኤልያስ ይመጣል’ የምትሉ ጻፎች ሆይ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ብትሆኑ ኖሮ ኤልያስን በታቦር ተራራ ባያችሁት ነበር፡፡ ደብረ ታቦር ብትገኙና ኤልያስን ብታዩት ኖሮ መስቀሉ ሥር ቆማችሁ ኤሎሔ ሲል ስትሰሙ ‘ኤልያስን ይጠራል ያድነው ከሆነ እናያለን’ ብላችሁ ባልሰማ ጆሮአችሁ ከፈጣሪ ጋር አትጣሉም ነበር፡፡

ደብረ ታቦር የሐዲስ ኪዳን ደብረ ሲና ሆነች፡፡ ሙሴ ሕዝቡን ከተራራ በታች ትቶ ከኢያሱና ከወንድማማቾቹ አብዩድና ናዳብ ጋር ወደ ሲና ተራራ ይወጣ እንደነበር ክርስቶስም ከጴጥሮስና ከወንድማማቾቹ ያዕቆብና ዮሐንስ ጋር ወደ ታቦር ተራራ ወጣ፡፡ ሙሴ በሲና በደመና መካከል የእግዚአብሔርን ድምፅ እንደሰማ በታቦርም የአብ ቃል ተሰማ፡፡ የታቦር ድምፅ ግን እንደ ሲና ‘ባሪያዬ ሙሴ’ የሚል ሳይሆን ‘የምወደው ልጄ’ የሚል ነበር፡፡ ሙሴ በሲና ተራራ ባየው የእግዚአብሔር ክብር ምክንያት ፊቱ እስራኤል ተሸፈንልን እስኪሉት ድረስ አበራ፡፡ የታቦር ተራራው ግን የተለየ ነበር ፤ ብርሃኑ ከውስጡ የፈለቀው ጌታ ፊቱ ከሙሴ ይልቅ አበራ በልብሱ እንዳይሸፍነው ልብሱም ብርሃን ነበረና ተማሪዎቹ ወደቁ፡፡

ታቦር እንዴት ያለች ‘እግዚአብሔር የወደዳት’ ተራራ ናት? [ደብር ዘሠምሮ እንዲል] ሐዋርያትና ነቢያት በአንድነት ቆመው የሚተያዩባት ፤ ብሉይና ሐዲስ የተዋወቁባት ፤ ጥላና አካል የተጋጠሙባት ይህች ተራራ እንዴት የተመረጠች ናት? ‘ታቦርና አርሞናዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል’ እንደተባለ ነቢያትና ሐዋርያትን በግራ በቀኙ አድርጎ በሰማያዊ አባቱ ‘የምወደው ልጄ’ ተብሎ ሲጠራ ስሙን ሰምታ ታቦር ምንኛ ደስ ይላት ይሆን? የሰናፍጭ ቅንጣት ታህል እምነት አጣን እንጂ ነቅለን ወደ ሀገራችን ከምናስገባቸው ተራሮች አንዱ ታቦር በሆነ ነበር፡፡

በታቦር ተራራ ሐዋርያትና ነቢያት በአንድ ወንበር ከሊቀ ሊቃውንት ክርስቶስ ትምህርት ተምረው ተመለሱ፡፡ ሐዋርያቱ የነቢያት ጌታ መሆኑን ሲማሩ ነቢያቱ ደግሞ የሐዋርያት አምላክ መሆኑን አወቁ፡፡ ነቢያት ደክመው የዘሩትን ከሚያጭዱ አጫጆች ሐዋርያት ጋር ተዋወቁ፡፡
ነቢያት አምላክነቱን ያውቃሉ ፤ ሐዋርያት ደግሞ ሰውነቱን ያውቃሉ፡፡ በታቦር ተራራ ግን  አዲስ ትምህርት ተማሩ፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም እንዲህ ይላል ፦ ‘‘ነቢያቱ አይተውት የማያውቁትን ሰውነቱን አይተው ተደሰቱ ፤ ሐዋርያቱ አምላክነቱን አይተው ተደሰቱ’’

       ሐዋርያት ደነገጡ ፤ እነርሱ ባልነበሩበት በዮርዳኖስ የተናገረውን የእግዚአብሔር አብን ድምፅ በታቦር ተራራ ሰሙ ፤ ጴጥሮስ ‘አንተ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ’ ያለው በሰማይ ያለው አብ ገልጦለት ነበረ ፤ አሁን በልቡ ያንን ቃል ያስቀመጠውን የአብን ድምፅ ሰምቶ ዓለቱ ስምዖን በፍርሃት ወደቀ፡፡ የጌታን ፊት አብርቶ ሲያይ ሳያይ ያመነውን አምላክነቱን አወቀ፡፡ ‘ሐዋርያት በአንድ ቀን ሁለት ፀሐይ ወጥቶ አዩ ፤ አንደኛው የተለመደችው ፀሐይ ስትሆን ሁለተኛው ደግሞ የሚያበራው የጌታ ፊት ነበር’ ይላል ቅዱስ ኤፍሬም፡፡ እውነትም ስሙን ለሚፈሩ ሐዋርያት የጽድቅ ፀሐይ ክርስቶስ በታቦር ተራራ ላይ ወጣላቸው፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም በታቦር ተራራ ነቢያትና ሐዋርያት መገናኘታቸውን እንዲህ ሲል ያደንቃል ፦
‘የብሉይ ኪዳን ጸሐፊዎች የሐዲስ ኪዳን ጸሐፊዎችን አዩ ፤ ቅዱሱ ሙሴ ቅዱስ ጴጥሮስን አየው የአብ እንደራሴ የወልድን አገልጋይ ተመለከተው፡፡ የብሉይ ኪዳኑ ድንግል ኤልያስ የሐዲስ ኪዳኑን ድንግል ዮሐንስን አየው፡፡ በእሳት ሰረገላ ላይ የተሳፈረው ኤልያስ ወደ እሳታዊው ክርስቶስ ደረት የተጠጋውን ዮሐንስን አየው፡፡ የታቦር ተራራ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ሆነ ፤ ክርስቶስም ሁለቱን ኪዳናት አዋሐዳቸው!’

ሐዋርያት ወድቀው ‘የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት’ የሚል ቃል ከሰሙ በኋላ ሲነሡ ከክርስቶስ ብቻ በቀር ማንንም አላዩም፡፡ በእርግጥም ‘የምወደው ልጄ ይህ ነው’ ተብለው ማሳሰቢያ ከተሠጣቸው በኋላ ቀና ሲሉ ማግኘት ያለባቸው ‘የሚወደው ልጁን’ ክርስቶስን ብቻ ካልሆነ አዋጁ ስለማን እንደሆነ ግራ ይገባቸው ነበር ይላል ማር ኤፍሬም፡፡

    ሐዋርያት ቀና ሲሉ ሙሴ የለም ፤ ኤልያስም የለም፡፡ ለነገሩ ከሙሴም ከኤልያስም የሚልቀው ጌታ ከእነርሱ ጋር ካለ ምን ይፈልጋሉ? ባልወለደው ፈርኦን የልጅ ልጅ ተብሎ ከተጠራው ሙሴ ይልቅ ባልወለደው ዮሴፍ የዮሴፍ ልጅ ተብሎ የተጠራው ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር ነው፡፡ ከፈርኦን ሰይፍ ተርፎ እስራኤልን ነጻ ካወጣው ሙሴ የሚበልጠው ከሔሮድስ ሰይፍ ተርፎ ዓለምን ነጻ ያወጣው ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር አለ፡፡ እናቱ ሞግዚቱ ሆና ካሳደገችው ሙሴ በላይ ‘እናትና ገረድ ማርያም ደስ’ ብሏት ያሳደገችው ክርስቶስ አይሻላቸውም? ግብፃዊውን ገድሎ ለማንም አትናገሩ ከሚለው ሙሴ ይልቅ ዕውራንን አብርቶ ለምፃምን አንጽቶ ፊቱ እንደ ፀሐይ አብርቶ ለማንም አትናገሩብኝ የሚለው ክርስቶስ አብሮአቸው ካለ ምን ይፈልጋሉ፡፡ ‘የቆምህበት ሥፍራ የተቀደሰች ናትና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ’ ተብሎ ከተነገረው ሙሴ ይልቅ ‘የጌታ እግር በሚቆምበት እንሰግዳለን’  ‘የጫማህን ጠፍር እንኳን ልፈታ አይገባኝም’ እየተባለ የተዘመረለት ክርስቶስ ከእነርሱ ጋር ነውና ለሦስቱ ደቀ መዛሙርት የሙሴ መሔድ አላስደነቃቸውም፡፡

ኤልያስንም ስላላዩ አላዘኑም ፤ በእሳት ሰረገላ ከሔደው ኤልያስ በላይ ልብሱ እሳት ቀሚሱ እሳት የሆነው አምላክ ከእነርሱ ጋር ነው፡፡ ኤልያስ ለደቀ መዝሙሩ ወደ ሰማይ ሲሔድ መጎናጸፊያውን ትቶለት ሔዶ ነበር፡፡ የሐዋርያት መምህር ክርስቶስ ግን ሲያርግ ልብሱን አልወረወረላቸውም፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳለ እርሱ ሲያርግ ለደቀ መዛሙርቱ የተወላቸው ልብሱን ሳይሆን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ነው፡፡ ስለዚህ ኤልያስ ቢሔድ ሙሴም ቢሰወር ደቀ መዛሙርቱ ጌታችንን ከብበው ከታቦር ተራራ በደስታ ወረዱ፡፡

እንኳን አደረሳችሁ!

@Gamel_Media