በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር ወደ ኢትዮጵያና ጅቡቲ ሊጓዙ እንደኾነ የአገሪቱ ውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል።
አምባሳደር ሐመር በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ቆይታ፣ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች የግጭት ማቆም ስምምነቱን ተግባራዊነት በሚገመግመው የአፍሪካ ኅብረት ኹለተኛ ስብሰባ ላይ እንደሚሳተፉ መስሪያ ቤቱ ገልጧል። የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ፣ አሜሪካ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የኢትዮጵያ መንግሥትንና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን እንደምትደግፍ፣ የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ ለማስፈታት፣ ለመበተንና ከኅብረተሰቡ ጋር መልሶ ለማዋሃድና ለማቋቋም ድጋፍ እንደምታደርግ እንዲኹም የሽግግር ፍትሕና ተጠያቂነት እንዲሰፍንና ተፈናቃዮቹ እንዲመለሱ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቋል። ሐመር፣ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ያለውን ግጭት በንግግር በመፍታት ዙሪያ ከባለሥልጣናት ጋር ይነጋገራሉ ተብሏል። ሐመር መቼ ኢትዮጵያ እንደሚገቡና ስንት ቀን እንደሚቆዩ ግን አልተገለጠም።