የፊልሙ ፕሮዲውሰሮች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለፁት የ 'እጅ አንሰጥም' ፊልም ደራሲና ዳይሬክተር ረዲ በረካ (የሴት ልጅ) ሲሆን ይህ ዘጠነኛ ፊልሙ እንደሆነ ተገልጿል።
ቀደምት ስራዎቹ 'ሱማሌው ቫንዳም' ፣ '50 ሎሚ' ፣ 'ወራጅ አለ' ፣ 'የት ነበርሽ' ፣ 'ዘናጭ' ፣ 'በ17 መርፌ' ፣ 'ሎሌ' የተሰኙ ለተመልካች ያደረሳቸው ፊልሞቹ ናቸው።
የ'እጅ አንሰጥም' ፊልም ፕሮዲዩሰር 'የኔነህ እንግዳወርቅ'ም ከዚህ ቀደም በበርካታ ተመልካቾች ዘንድ ተወዳጅነትን ያገኙትን 'አፋጀሽን' ፣ 'ዘናጭ' ፣ 'ሱማሌው ቫንዳም' ፣ 'በ17 መርፌ' እና 'እንሳሮ' የተሰኙ ፊልሞችን ፕሮዲዩስ በማድረግ ትልቁን ድርሻ ተወጥቷል።
ከየኔነህ እንግዳወርቅ ጋር በጋራ በመሆን 'እጅ አንሰጥም' የተሰኘውን ፊልም 'ኤልቤተር ፊልም ፕሮዳክሽን' በተሰኘው ድርጅቷ በኩል ፕሮዲዩስ ያደረገችው 'ኤልቤተር ዮሴፍ' መሆኗን በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ተገልጿል።
በአደይ ፊልምስ እና በየኔነህ ፊልም ፕሮዳክሽን ተዘጋጅቶ በኤልቤተር ፊልም ፕሮዳክሽን የሚቀርበው 'እጅ አንሰጥም' ፊልም ከነሐሴ 24 ጀምሮ ለተከታታይ 15 ቀናት ብቻ ለእይታ ይቀርባል።
የፊልሙ ፕሮዲዩሰር የኔነህ እንግዳወርቅ ከአመታት በፊት 'እንሳሮ' የተሰኘውን ፊልሙን በብዙ ልፋትና በብዙ ወጪ ሰርቶ ለእይታ ባቀረበበት ወቅት በሀገራችን የፊልም ስራ ውስጥ ተሰንቅረው በገቡ በሰው እንጀራ ላይ አሸዋ መበተንን እንደ እውቀት በሚቆጥሩ ሌቦች ተሰርቆ ከባድ ኪሳራ እንደደረሰበት አስታውሶ 'እጅ አንሰጥም' የተሰኘው ፊልሙ ቢገፉትም እንደማይወድቅ ያሳየበት ፊልሙ መሆኑን በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ገልጿል።
በ'እጅ አንሰጥም' ፊልም ላይ ተዋናይ ሰለሞን ሙሄ ፣ ዳንኤል ተገኝ ፣ እንዲሁም ምህረት ታደሰ (ፒፒሎ) ፣ እዮኤል ባህሩ ተሳትፈውበታል።
'እጅ አንሰጥም' ፊልም ነሐሴ 24 ፣ 25 ፣ 26 እስከ መሥከረም 2 በተመረጡ ሲኒማ ቤቶች ብቻ ለተከታታይ 15 ቀናት መታየት ይጀምራል ።