** ** ***
ሴኔቱ በትናንትናውና በዛሬው ዕለት ባካሄደው መደበኛ ስብሳባ የ2017 ዓ.ም የትምህር ዘመን አካዳሚክ ካላንደር ጉዳይን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያየቶ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
በሴኔቱ የውይይት ጊዜ የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጉቼ ጉሌ፤ በዩኒቨርሲቲው የሚሰሩ ማናቸውም ጉዳዮች በመንግስት ህግና ደንብ መሰረት ማለፍ እንዳለባቸው ጠቁመው የመማር ማስተማር፣ የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያግዙ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ሴኔቱ እንዲወስን አቅርበዋል፡፡
በዚሁ መሰረት ሴኔቱ በተከታታይ ትምህርት መርሃ ግብር ለንድፍና ለተግባር እንዲሁም ለላቦራቶሪ ሥራዎች የክፍያ መጠን፣ የዩኒቨርሲቲው መምህራን በታወቁ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ጆርናሎች ላይ ጽሑፍ (Article) ሲያሳትሙ የማበረታቻ ክፍያ እና በዩኒቨርሲቲው በክረምትና በማታ መርሃ ግብር በግል ለሚማሩ ተማሪዎች የመኝታና የምግብ አገልግሎት ለማቅረብ የመኝታና የምግብ አገልግሎት ክፍያ መጠንና የአከፋፈል ሁኔታ የተመለከቱ መመሪያዎችን ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ክፍያዎቹ አገልግሎት ፈላጊውን አቅም ባገዘናዘበ እና ዩኒቨርሲቲውም የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን ማሳለጥ በሚያስችል መልኩ በአጥኚ ቡድን የቀረበ ሲሆን በመመሪያቹ ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ ተወስኖ ለተፈጻሚነት ሁሉም በኃላፊነት መንቀሳቀስ እንዳለበት ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በተለያዩ ኮሌጆች ትምህርታቸውን ጨርሰው ሳይመረቁ የቀሩ ተማሪዎች የምረቃ ጉዳይ፣ የጂኦግራፊያዊ መረጃ ሥርዓት (GIS) እና የሶሻል ወርከር (Social Worker) ትምህርት ስለማስጀመር በተመለከተ ሴኔቱ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
የታሪክ ትምህርት የጋራ ኮርስ (Common Course) ሆኖ በሁሉ ትምህርት ክፍሎች እንዲሰጥ እንዲሁም የ2017 ዓ.ም አካዳሚክ ካላንደር ሴኔቱ ተወያይቶ ያፀደቃቸው አጀንዳዎች መሆናቸውን ከውይይት መድረኩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
➭ «ዕውቀትን በተግባር!!»
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥራ አስፈጻሚ ቢሮ
➤ መስከረም 24/2017 ዓ.ም (ወሶዩ)