ክርስቲያን ንስሐ መግባት አያስፈልገውም ወይም ንስሐ አይገባም የሚል የተሳሳተ ትምህርት አለ።
ሰው አንዴ በክርስቶስ በማመን ከጸደቀ ወዲህ እንደገና ንስሐ ይገባል ማለት ጸድቆ የነበረውን መልሶ ኃጢአተኛ ማድረግ (እንደ ኃጢአተኛ መቁጠር) ነው የሚል ነው ምክንያታቸው።
ነገር ግን፣ ሁለት የንስሐ ዓይነቶች አሉ።
የመጀመሪያው ንስሐ፣ ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት የታረቅንበት (ሮሜ.5፥10)፥ ከሰይጣን አገዛዝ ወደ እግዚአብሔር የዞርንበት፥ ከእግዚአብሔርም ጋር በክርስቶስ ደም አማካኝነት ኪዳን ያደረግንበት ነው።
ጌታ ኢየሱስ ጳውሎስን ሐዋርያ አድርጎ ወደ አሕዛብ የሚልክበትን ምክንያት ሲገልፅለት “የኃጢአትን ስርየት በእኔም በማመን በተቀደሱት መካከል ርስትን ያገኙ ዘንድ፥ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ” አለው (ሐዋ.26፥17-18)።
ይህ የንስሐ ጥሪ ለሰዎች ሁሉ የቀረበ ነው።
“... እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አሁን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤ ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።” (ሐዋ.17፥30-31)
ይኼኛው ንስሐ አንዴ ነው። ሰው አንዴ በክርስቶስ ከሆነ በኋላ በፈረቃ አንዴ በክርስቶስ አንዴ በዓለም መሆን አይችልም።
ነገር ግን፣ ሰው በክርስቶስ ሳለ ኃጢአትን ቢያደርግ ወይም ለክርስቲያን የማይገባ ኑሮ የሚኖር ከሆነ መታረም አለበት። ሁለተኛው የንስሐ ዓይነት እሱ ነው። ይኼኛው ንስሐ የሚደረገው አንድ ጊዜ ብቻ አይደለም። ስላደረግነው ነገር የእግዚአብሔር ቃልና መንፈስ ቅዱስ በሚገስጹን ሕሊናችንም በሚወቅሰን ነገር ሁሉ በማንኛውም ጊዜ ንስሐ መግባት ይኖርብናል።
እዚህ ላይ መረሳት የሌለበት፣ ንስሐ ጸሎት አይደለም። ንስሐ ከተሳሳተ አካሄድ መመለስ ስሕተትን ማረም ነው። “... ንስሐ ግቡ ኃጢአትም ዕንቅፋት እንዳይሆንባችሁ ከኃጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ” ነው የሚለው (ሕዝ.18፥30)።
ንስሐ፣ ሰው በሕሊናው ተወቅሶ ስሕተቱን አምኖ ክፉ ሥራውን ለመተው ሲወስን ነው እንጂ እንዲሁ “እኔ ኃጢአተኛ ነኝ፤ ማረኝ” እያሉ መጸለይን ልማድ ማድረግ አይደለም።
በእርግጥ የንስሐ ጸሎት አለ፤ ሰው ኃጢአቱን ለእግዚአብሔር የሚናዘዝበትና ምሕረትን የሚለምንበት። ነገር ግን፣ ከክፉ ሥራው መመለሱ እንጂ ጸሎቱ አይደለም ንስሐ።
ስለዚህ ንስሐ በግልፅ የሚታይ ተጨባጭ ፍሬ ያለው ነው፤ ምናባዊ አይደለም። ስለ ነነዌ ሰዎች ንስሐ ሲናገር “እግዚአብሔርም ከክፉ መንገዳቸው እንደተመለሱ ሥራቸውን አየ” ይላል (ዮና.3፥10)።
አንድ ክርስቲያን ንስሐ ያስፈልገዋል ማለት ክርስትናው ተሽሯል በክርስቶስ ያለውን ማንነት አጥቷል ማለት አይደለም። ነገር ግን፣ ዓላማውን ስቷል፥ ስለዚህ አካሄዱን ማስተካከል አለበት ማለት ነው።
እግዚአብሔር ያለ ሥራ በጸጋው አድኖናል ማለት ኃጢአት እንድንሠራ ተፈቅዶልናል ማለት አይደለም። ጸጋው ከኵነኔ ነው ነጻ ያወጣን፤ ጽድቅን ከማድረግ ግዴታ ነጻ አላደረገንም። ይልቁን ጽድቅን ማድረግ የተፈጠርንበት ዓላማ እና በምድር እንድንፈጽመው የተሰጠን ተልእኮአችን ነው። “እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን” ነው የሚለው (ኤፌ.2፥10)።
ደግሞም “ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአል፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል” ይላል (ቲቶ.2፥11-14)።
ክርስቲያን ከዚህ ዓላማ አንፃር ነው አካሄዱን መመርመርና መንገዱን ስቶ ሲገኝ መታረም ያለበት። ክርስቲያን ንስሐ አያስፈልገውም ከተባለ ግን ቢሳሳትም አይታረምም ማለት ነው። ይህ ትክክል እንዳልሆነ ግልጥ ነው።
በአዲስ ኪዳን በብዙ ስፍራ ለቤተክርስቲያንና ለምዕመናን ንስሐ እንዲገቡ የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል። ይህም ንስሐ ላልዳኑ ሰዎች ብቻ እንዳልሆነ ነው የሚያሳየው።
ለምሳሌ፣ ሲሞን በፊት ጠንቋይ የነበረ ኋላ ግን በሐዋርያው ፊልጶስ ስብከት በጌታ አምኖ የተጠመቀ አዲስ ክርስቲያን ነበረ። ነገር ግን የእግዚአብሔርን ጸጋ ከሐዋርያት በገንዘብ ለመግዛት በፈለገ ጊዜ ሐዋርያው ጴጥሮስ “የእግዚአብሔርን ስጦታ በገንዘብ እንድታገኝ አስበሃልና ብርህ ከአንተ ጋር ይጥፋ። ልብህ በእግዚአብሔር ፊት የቀና አይደለምና ከዚህ ነገር ዕድል ወይም ፈንታ የለህም” አለውና ንስሐ እንዲገባ መከረው። “እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንስሐ ግባ፥ ምናልባትም የልብህን አሳብ ይቅር ይልህ እንደ ሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን፤ በመራራ መርዝና በዓመፅ እስራት እንዳለህ አይሃለሁና” አለው (ሐዋ.8፥20-23)። ይህ ለክርስቲያን የተነገረ ቃል መሆኑን እናስተውል።
በዮሐንስ ራእይ ደግሞ ከሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት አምስቱን ጌታ ንስሐ እንዲገቡ ሲያስጠነቅቃቸው እናያለን (ራእ.2-3)።
በመሆኑም ክርስቲያን ንስሐ መግባት አያስፈልገውም የሚለው ትምህርት ምዕመኑን ይጎዳዋል። ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር ሥራችንን ሁሉ ወደ ፍርድ ማምጣቱ አይቀርም።
“አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፤ በገዛ ሥጋው የሚዘራ ከሥጋ መበስበስን ያጭዳልና፥ በመንፈስ ግን የሚዘራው ከመንፈስ የዘላለምን ሕይወት ያጭዳል።” (ገላ.6፥7-8)
ራስን መመርመርና ማረም ይጠቅማል፤ “እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” (1ቆሮ.10፥12)፣ ደግሞም “ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብን ነበር” ይላል (1ቆሮ.11፥31)።
* * * መጨረሻ * * *