ሐዲሱ አን-ነበዊይ እና ሐዲሱል ቁድሢይ
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ፥ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡
59፥7 *መልክተኛውም የሰጣችሁን ማንኛውንም ነገር ያዙት! ከእርሱም የከለከላችሁን ነገር ተከልከሉ*፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ ቅጣተ ብርቱ ነውና፡፡ وَمَا آتَاكُمُ الرَّسُولُ فَخُذُوهُ وَمَا نَهَاكُمْ عَنْهُ فَانتَهُوا ۚ وَاتَّقُوا اللَّهَ ۖ إِنَّ اللَّهَ شَدِيدُ الْعِقَابِ
“ሐዲስ” حَدِيث የሚለው ቃል “ሐደሰ” حَدَّثَ ማለትም “ተናገረ” ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን “ንግግር” ማለት ነው፥ ነቢያችን”ﷺ” በዐቂዳህ እና በፊቅህ ነጥብ ላይ የሚናገሩት ሐዲስ ሁሉ ወሕይ ነው፦
53፥3 *ከልብ ወለድም አይናገርም*፡፡ وَمَا يَنطِقُ عَنِ الْهَوَىٰ
53፥4 *እርሱ ንግግሩ የሚወረድ ወሕይ እንጅ ሌላ አይደለም*፡፡ إِنْ هُوَ إِلَّا وَحْيٌ يُوحَىٰ
“ወሕይ” وَحْي የሚለው ቃል “አውሓ” أَوْحَىٰٓ ማለትም “ገለጠ” ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን “ግልጠተ-መለኮት” ማለት ነው። “መልክተኛውም የሰጣችሁን ማንኛውንም ነገር ያዙት! ከእርሱም የከለከላችሁን ነገር ተከልከሉ” የሚለው ይህንኑ ሡናህ ዋቢና ታሳቢ ያደረገ ነው፦
59፥7 *መልክተኛውም የሰጣችሁን ማንኛውንም ነገር ያዙት! ከእርሱም የከለከላችሁን ነገር ተከልከሉ*፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ ቅጣተ ብርቱ ነውና፡፡ وَمَا آتَاكُمُ الرَّسُولُ فَخُذُوهُ وَمَا نَهَاكُمْ عَنْهُ فَانتَهُوا ۚ وَاتَّقُوا اللَّهَ ۖ إِنَّ اللَّهَ شَدِيدُ الْعِقَابِ
ታዲያ ቁርኣን እና ሐዲስ ልዩነቱ ምንድን ነው? አዎ! ቁርኣን ለፍዙ ሆነ መዕናው የአላህ ነው፥ ሐዲስ ግን ለፍዙ የነቢያችን”ﷺ” ሲሆን ማዕናው የአላህ ነው። “ለፍዝ” لَفْظ ማለት “ቃል”Verbatim” ማለት ሲሆን “መዕና” مَعْنًى ማለት “መልእክት” “እሳቤ” “አሳብ”notion” ማለት ነው። የቁርኣን ተናጋሪ አላህ ብቻ ነው፥ ቃሉም የወከለው መልእክቱ፣ “እሳቤው፣ አሳቡ የራሱ ነው። ሐዲስ ደግሞ መልእክቱ፣ “እሳቤው፣ አሳቡ የአላህ ሲሆን ቃሉ ግን የራሳቸው የነቢያችን”ﷺ” ነው። አላህ የሐዲስን መልእክት ሲያወርድላቸው እሳቸው በራሳቸው ባህል፣ ወግ፣ ልምድ፣ ክህሎት፣ ትውፊት ያብራሩታል። ይህ ሐዲስ ደግሞ በሁለት ይከፈላል፥ እርሱም ሐዲሱ አን-ነበዊይ እና ሐዲሱል ቁድሢይ ነው።
ነጥብ አንድ
"ሐዲሱ አን-ነበዊይ"
“ነቢይ” نَبِيّ የሚለው ቃል “ነበአ” نَبَّأَ ማለትም “የሩቅ ወሬን አወራ” ከሚል ሥርወ-ቃል የመጣ ሲሆን “የሩቅ ወሬ አውሪ” ማለት ነው፥ የነቢይ ገላጭ መደብ ደግሞ "ነበዊይ" نَبَوِيّ ሲሆን "ነቢያዊ" ማለት ነው። በጥቅሉ "ሐዲሱ አን-ነበዊይ" حَدِيث الْنَبَوِيّ ማለት "ነቢያዊ ሐዲስ" ማለት ነው፥ “የአላህ መልእክተኛም”ﷺ” እንዲህ አሉ" ወይም "ነቢዩም”ﷺ” እንዲህ አሉ" ተብሎ የሚናገሩት ንግግር ሁሉ ሐዲሱ አን-ነበዊይ ይባላል። ለምሳሌ፦
ጃምዒ አት-ቲርሚዚይ መጽሐፍ 27, ሐዲስ 62
አቢ ዘር እንደተረከው፦ “የአላህ መልእክተኛም”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ *”የአንተ ፈገግታ በወንድምህ ፊት ለአንተ ሶደቃህ ነው”*። عَنْ أَبِي ذَرٍّ، قَالَ قَالَ رَسُولُ اللَّهِ صلى الله عليه وسلم “ تَبَسُّمُكَ فِي وَجْهِ أَخِيكَ لَكَ صَدَقَةٌ
ኢማም ቡኻርይ መጽሐፍ 80, ሐዲስ 102
አቢ ሙሣ”ረ.ዐ.” እንደተረከው፦ “ነቢዩም”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ *”ጌታውን የሚዘክር እና የማይዘክር ምሳሌ፥ ልክ እንደ ሕያው እና እንደ ሙታን ነው”*። عَنْ أَبِي مُوسَى ـ رضى الله عنه ـ قَالَ قَالَ النَّبِيُّ صلى الله عليه وسلم “ مَثَلُ الَّذِي يَذْكُرُ رَبَّهُ وَالَّذِي لاَ يَذْكُرُ مَثَلُ الْحَىِّ وَالْمَيِّتِ