| ጃንደረባው ሚድያ | ግንቦት 6 2016 ዓ.ም.|
አዲስ አበባ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የማኅበራት ማደራጃ መምሪያ የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ በጃን እስጢፋኖስ ላለፉት ሁለት ዓመታት በአዳር የአብነት ትምህርት ያስተማራቸውንና መሥፈርቱን ያሟሉ ዐሥራ ሦስት ተማሪዎች በዛሬው ዕለት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ሄኖክ አንብሮተ ዕድ ማዕረገ ዲቁናን ተቀብለዋል:: የኢጃት ቦርድ ሰብሳቢ ዲ/ን ዶ/ር ዳዊት "ኢጃት ከተመሠረተበት ጊዜ አንሥቶ በጃን ማዕተብ ከሰባ በላይ ንዑሰ ክርስቲያንን ለምሥጢረ ጥምቀት ፣ ብዙኃንን በጃን ዮሐንስ ለምሥጢረ ንስሓና ቁርባን ፣ በጃን ቃና ዘገሊላ ደግሞ ለምሥጢረ ተክሊል ያበቃ ሲሆን አሁን ደግሞ ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርት ለምሥጢረ ክህነት አብቅቶአል" ብለዋል::
"ዲያቆናቱ በአግባቡ የተማሩና ለአገልግሎት ዝግጁ የሆኑ ናቸው" ያሉት የጃን እስጢፋኖስ ሰብሳቢ መምህር ኤፍሬም ሲሳይ ሲሆኑ "ተማሪዎቹ ምንም ዓይነት ትምህርት ሳይኖራቸው ወደ ኢጃት መጥተው በአግባቡ ተምረው ለዚህ በመብቃታቸው እጅግ ደስ ብሎናል:: ትምህርት ሳይጨርሱ ወዴትም እንዳይሔዱ በማስገደድም በአበው ልማድ መሬት ላይ እየተኙ በሌሊት እንዲማሩና ከአብነት ትምህርቱ ጋር መሠረታዊ ነገረ ሃይማኖትም እንዲማሩ ተደርጓል" ብለዋል:: በማያያዝም "በቅርቡ ሱባኤ እስጢፋኖስ የተሰኘ የዲያቆናት ብቻ ሱባኤ ጉባኤ ለማካሔድም ዝግጅታችንን ጨርሰዋል ብለዋል" ዲያቆናቱን አስተምረው ለዚህ ካበቁ መምህራን መካከል አንዱ የሆኑት መምህር ኃይለ ኢየሱስ ተሻለ በበኩላቸው "ወደ አገልግሎት ለመግባት በአግባቡ ደጅ ጸንተውና የአገልግሎቱን ምንነት ተረድተው ለዚህ መብቃታቸው ቤተ ክርስቲያንን የበለጠ ለማገልገል ያስችላቸዋል:: ለዚህ ደርሰው ማየታችን ለኢጃት ትልቅ ደስታ ነው" ብለዋል::