#AddisAbaba #Education
“ በሂሳብና እንግሊዘኛ መፅሐፍት ላይ እጥረት በመታየቱ ተጨማሪ ህትመት እየተካሄደ ነው ” - አ/አ ትምህርት ቢሮ
በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት መሠረት መፅሐፍ ማሳተም ላይ እንደ አገር በተለያዩ ትምህርት ቢሮዎች ክፍተቶች እንዳሉ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያም፣ በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት መሠረት በ2017 የትምህርት ዘመን መፅሐፍትን አሳትሞ ለተማሪዎች ማዳረስ ተቻለ ? ሲል ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጥያቄ አቅርቧል።
የቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በሰጡት ቃል፣ “ በተወሰኑ ትምህርቶች ላይ፤ ሂሳብና እንግሊዘኛ መፅሐፍት እጥረት በመታየቱ ምክንያት ተጨማሪ ህትመት እየተካሄደ ነው። ሪዘርቭም እያደረግን እንገኛለን ” ሲሉ ተናግረዋል።
የመፅሐፍት እጥረቱ በምን ደረጃ ነው ? ሲል ቲክቫህ ላቀረባቸው ጥያቄ በምላሻቸው፣ “ ይህንን ሬሽዎ በተለይ ከግል ትምህርት ቤቶች አካባቢ ላይ ያለ ችግር ነው ” ብለዋል።
“ እነርሱም መፅሐፉን ወስዶ ለማሰራጨት ፍላጎት ማጣት፣ ይሄ ደግሞ የራሳቸው መፅሐጽት አትመው ለመሸጥ ከሚመነጭ ነገር ስለሆነ እሱ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እየወሰድን ትምህርት ቤቶች ወስደው ለተማሪዎቻቸው ተደራሽ እንዲያደርጉ አድርገናል ” ነው ያሉት።
“ ከሁለተኛ ደረጃና ቅድመ አንደኛ ደረጃ በስተቀር ለሁሉም አንድ ለአንድ ተዳርሷል ” ሲሉም ተናግረዋል።
“ ለሁለተኛ ደረጃም ትምህርት ሚኒስቴር አሳትሞ ሰሞኑን ባስገባው መሠረት ለሁሉም ተማሪዎች ማዳረስ ተችሏል" ያሉት ኃላፊው፣ " ባለፉት ሁለት ዓመታት በከፍተኛ ኢንቨስትመንት ተማሪዎቻችን ጋር ተደራሽ ለማድረግ ተሞክሯል” ብለዋል።
በሌላ በኩል፣ ከተማሪዎች ምገባ ጋር በተያያዘ መጋቢ እናቶች ከኑሮ ውድነቱ ጋር በተያያዘ የሚከፈላቸው ገንዘብ አነስተኛ መሆኑን ይገልጻሉ።
ይህንኑ በተመለከተ ምን እየተሰራ እንደሆነ ማብራሪያ የጠየቅናቸው ዘላለም (ዶ/ር)፣ “ በተማሪ 22 ብር የነበረው በዚህ ዓመት ወደ 32 ብር አሳድጎላቸዋል። ስለዚህ ያ ጥያቄ ተመልሷል ማለት ነው ” ብለዋል።
“ በቀን 800 ሺሕ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ ይመገባሉ ” ሲሉ ተናግረዋል።
በተያያዘም በትምህርት ቤት አካባቢዎች ያሉ ሱስን የሚያበረታቱ ቤቶች እንዳሉ፣ ይህም ተማሪዎችን ከዓላማቸው የሚያደናቅፍ ከመሆኑ አንጻር በቂ ትኩረት ተሰጥቷል? ሲልም ቲክቫህ ጥያቄ አቅርቧል።
ዘላለም (ዶ/ር) በምላሻቸው፣ “ትክክል ነው። የተማሪዎችን ሀሳብ፣ ልቦና የሚሰርቁ ጉዳዮች በትምህርት ቤት አካባቢዎች እንዳይኖሩ ባለፉት ዓመታት ጠንካራ እርምጃ ወስደናል” ብለዋል።
“ ከ3000 በላይ የሚደርሱ የተለያዩ መማር ማስተማር ሂደቱን ሊያውኩ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ እርጃ ተወስዷል ” ብለው፣ “ አሁንም እንደዛ አይነት ፍላጎቶች በትምህርት ቤቶች ብቅ ብቅ እንዳይሉ መልሶ ጠንካራ እርምጃና ክትትል ያስፈልጋል ” ሲሉ አስገንዝበዋል።
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia