Fresenbet G.Y Adhanom

@fresenbett


Fresenbet G.Y Adhanom

12 Oct, 05:57


በልደቴ ቀን የቤተሰብነት ስጦታ ስጡኝ!

ዛሬ ልደቴ ነው። የዚህን ዓመት ልዩ የሚያደርገው ደግሞ ሠላሳ ዓመት መድፈኔ ነው። ከሰሞኑ ጀምሮ "ለመሆኑ እስከ ዛሬ ድረስ በሃያዎቹ እድሜዬ ምን ሠራሁ?" ብዬ መጠየቅ ጀምሬያለሁ። ለራሴ የሰጠሁት መልስ መልካም ነው። መሥራት የምፈልጋቸውን ሁሉ ሠርቻለሁ ባልልም፥ ሃያዎቹ ዓለማዊም ሆነ መንፈሳዊ ትምህርቶችን የተማርኩበት፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት በደንብ የቀረብኩበት፥ ቤተክርስቲያንን ያገለገልኩበት፥ ያገባሁበት እና የወለድኩበት ነው። ሃያዎቹን ከሞላ ጎደል በደንብ እንደተጠቀምኩ ይሠማኛል። በብዙ ቸር የሆነልኝ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይኹን!

አሁን ደግሞ ሠላሳዎቹን 'ሀ' ብዬ ጀምሬያለሁ። በዛሬዋ የልደቴ ቀን አዲሱን የአገልግሎት መሥመሬን ላስተዋውቃችሁ መጥቻለሁ። በአሁን ጊዜ ለብዙዎች ለመድረስ ከሚዲያ የተሻለ አማራጭ የለምና፤ እነሆ 'ቴዎሎጊያ' በተሰኘ ዩቲዩብ ቻናሌ መጥቻለሁ። ይህ ቻናል ጥናትና ምርምር የተደረገባቸውን መንፈሳዊ ቪዲዮዎች የምለቅበት ይሆናል።

በልደቴ ቀን ለወደፊት በብዙ የምትገለገሉበትን ቻናሌን ቤተሰብ ትሆኑኝ ዘንድ ስጦታ ሰጠኋችሁ፤ እናንተም በልደቴ ቀን 'Subscribe' በማድረግ ቤተሰብ የመሆንን ስጦታ ትሰጡኝ ዘንድ በአክብሮት እጠይቃለሁ።

https://youtube.com/@theologiaortho?si=1NXLiOOi2bA37WNy

Fresenbet G.Y Adhanom

14 Sep, 17:08


በእቁብ እናንብብ!

ከጥቂት ጊዜ ወዲህ ሁኔታዬን ሳስተውለው፥ ድሮ መጻሕፍትን በምገዛበት መጠን እየገዛሁ አይደለም። ይህ የሆነው የመጻሕፍት ዋጋ እጅግ እየተወደደ ስለመጣ ነው። መጻሕፍት እጅግ ሲወደዱበትን "ይህንን ነገር ለቤቴ ላሟላ ወይስ መጽሐፉን ልግዛ?" የሚል አጣብቂኝ ውስጥ መግባት ጀመርን። ጉዳዩ እንዲህ መሆኑ ቢያሳዝንም፥ አሪፍ መፍትሔ ይዘው የመጡትን አሪፍ መጻሕፍት ተዋወቋቸው!

አሪፍ መጻሕፍቶች የመጻሕፍት እቁብ ይዘውልን መጥተዋል። ኪሳችን እንዳይጎዳ ደግሞ እንደ አቅማችን በ400 ብር፥ በ700 ብር፥ በ1000 ብር እና በ5000 ብር አማራጭ አቅርበውልናል። እቁቡ በየወሩ የሚጣል ሲሆን፥ በስድስት ወር ውስጥ ይጠናቀቃል። እቁብ ሲወጣልን ደግሞ በቅናሽ መጻሕፍትን ከመግዛት ባሻገር፥ ካለንበት ቦታ በነጻ ዲሊቨሪ ሊያደርሱልን ቃል ገብተዋል።

አኔ ኪሴን የማይጎዳውን አማራጭ በመምረጥ ተመዝግቤያለሁ። እርስዎስ? እስቲ በአዲሱ ዓመት በእቁብም ቢሆን የንባብ ሕይወታችንን እናስቀጥል!

https://forms.gle/8FvLNHsqY1LJ9hzPA ላይ መመዝገብ ይችላሉ።

አሪፍ መጻሕፍት እናመሰግናለን!

🖋 Fresenbet G.Y Adhanom

Fresenbet G.Y Adhanom

11 Sep, 14:37


https://youtu.be/FqLG4hz48sw?si=5WsAJ5Oja_D5l9WY

Fresenbet G.Y Adhanom

11 Sep, 14:36


+ ሀብታም አይጸድቅም? +

ቤተክርስቲያን ለረዥም ዘመናት ሰይፍና ጦርን ብቻ ሳይሆን ሐሰተኛ ትርክቶችንም እየተቋቋመች ዛሬ እስካለንበት ዘመን መዝለቅ ችላለች። ከእነዚህ የሐሰት ክሶች መካከል ቤተክርስቲያን ሥራን ጠልታ ስንፍናን እንደምታገዝፍ፥ ሀብታምን ገፍታ ድሃን ብቻ እንደምታቅፍ፥ ሠርቶ መክበርን ሳይሆን የፈቃድ ድህነትን ብቻ የምትሻ እንደሆነች ተደርጎ የሚነገርባት አንዱ ነው።

ይህንን እና መሠል ጉዳዮችን በተመለከተ ከወንድሜ ዮኒ (Yonas Moh) ጋር ዘለግ ያለ ቆይታ አድርገናል። የአዲስ ዓመት ግብዣ ትሁንልኝ።

እንኳን ለ 2017 ዓ.ም በቸርነቱ አደረሰን!

🖋 Fresenbet G.Y Adhanom

----------

የፌስቡክ ገጽ: https://lnkd.in/e2NNiGH4

ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett

ቲክቶክ: https://lnkd.in/eU7d2X_Q

Fresenbet G.Y Adhanom

08 Sep, 05:45


+• ውሃ የሚያናውጥ መልአክ •+

በጥንት ዘመን በኢየሩሳሌም ውስጥ በሽታ የጸናበት ሰው ሁሉ የሚናፍቃት አንዲት መጠመቂያ ነበረች። ይህቺ መጠመቂያ ጤናማ ሰው ቢመለከታት የተለየ ነገር ላያይባት ይችላል። ታሞ ያያት ሁሉ ግን በውስጧ የመዳን ተስፋን ያይባታል። ስሟ ቤተ-ሳይዳ ይባል ነበር። በዚህች መጠመቂያ ቦታ ደዌ የበረታባቸው ሁሉ በዙሪያዋ ቁጭ ብለው አንዳች ነገር ይጠባበቃሉ።

ይህ የሚጠባበቁት አንዳች ነገር የውሃውን መናወጥ ነበር። ሰላምና የተረጋጋ የነበረው ውሃ ድንገት ከተናወጥ፥ አካባቢው በአንዴ ይረበሻል። ሁሉም ይሯሯጣል። እድል ቀንቶት መጀመሪያ የገባ ካለበት በሽታ ሁሉ በአንዴ ይፈወሳል። የመዳን ሎተሪ እንደማለት ነው። ለአንድ ሰው ብቻ ይወጣል። ሐኪም ቤት ለመታከም ሄደን ቀድሞ የደረሰው ሰው ብቻ ታክሞ ቢድን፥ ሌላው ሁሉ ወደ ቤቱ ቢሸኝ ማለት ነው። ለአንዱ ፈንጠዚያ፥ ለሌላው ግን እንደገና ሌላ የመዳን ጥበቃ።

ውሃው ግን የሚናወጠው በተፈጥሮ ምክንያት አልነበረም። የዮሐንስ ወንጌል "አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ያናውጥ ነበርና" (ዮሐ 5፡4) ይለናል። ለመሆኑ ይህ ውሃውን የሚያናውጥ መልአክ ማነው? በዚህ ዙሪያ ሁለት ምልከታዎች አሉ። አንዱ ወገን መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ነው ሲል ሌላው ደግሞ ቅዱስ ሩፋኤል መሆኑን ይገልጻል።

ከሁለቱ ትውፊቶች ምናልባትም "ቅዱስ ሩፋኤል ነው" የሚለው ቢያመዝን ስንኳ የሚገርም አይሆንም። ቅዱስ ሩፋኤል ብዙ ነገሩ ከፈውስ ጋር የተጣመረ ነው። ሊቃውንት ስሙን ሲተረጉሙት "ደስ የሚያሰኝ፣ ቸር፣ መሐሪ፣ ቅን የዋህ" ብለው ቢሆንም፥ የዕብራይስጡ የስሙ ፍቺ ግን የመልአኩን እውነተኛ ማንነት ይበልጥ አጉልቶ ያሳያል። በዕብራይስጥ ስሙ ራፋኤል (רָפָאֵל‎) ሲሆን፥ የስሙ ዋና ሥር የሆነው ረፈአ (רפא) እንደ ግሥ ስንጠቀመው "ፈውስ" ማለት ነው። በመሆኑም ራፋኤል የሚለው ስም ፍቺ "እግዚአብሔር ፈወሰ" ወይም "እግዚአብሔር ፈውሷል" ማለት ይሆናል።

በአንድ የጥንት የአይሁድ ትውፊት ላይ አብርሃም ከተገረዘ በኋላ እግዚአብሔር ቁስሉን ይፈውስለት ዘንድ ቅዱስ ሩፋኤልን እንደላከለት ያትታል። መጽሐፈ ሄኖክም ስለዚህ መልአክ "በበሽታ ሁሉ ላይ በሰው ልጆችም ቁስል ላይ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው"(ሄኖ 10፡13) በማለት ይገልጻል። ሊቃውንትም ሕሙማንን የሚፈውስ (ፈዋሴ ዱያን) ይሉታል። እንግዲህ "ውሃውን እያናወጸ ሰዎች እንዲፈወሱ ያደርግ የነበረው ቅዱስ ሩፋኤል ነው" ቢባል የማይገርመው ለዚያ ነው፤ እንዲያውም ከስሙም ሆነ ከግብሩ የሚስማማ ይሆናል።

ቅዱስ ሩፋኤል ሆይ፥ የእኛ ደዌ ለሠላሳ ስምንት ዓመት ከተኛው ከመጻጉዕ ይጸናል። በቤተሳይዳ ከተሰበሰቡት ድውዮች ሕመምም ሁሉ ይከፋል። የእነርሱ ደዌስ ለራስና ለአስታማሚ ብቻ ተረፈ። የእኛ ውስጣዊ ደዌ ግን መዘዙ ለሀገር ሁሉ ሆነ። ታላቁ መልአክ ሆይ፥ በተሾምህባት በዚህች ዕለት፥ የተጨነቁትን ነፍሳት ሁሉ አስብ። ደመናቱን አናውጸህ፥ ዝናቡንም ባርከህ በጠበልነቱ ክፉ በሽታችንን ፈውስልን።

🖋 Fresenbet G.Y Adhanom

ሥዕሉን በትውፊቱ መሠረት የሣለው ሠዓሊ Gigar Negusse ነው።

----------

የፌስቡክ ገጽ: https://www.facebook.com/fre.asalib

ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett

ቲክቶክ: https://www.tiktok.com/@fr3senbet?_t=8eAM1NzgeQw&_r=1

Fresenbet G.Y Adhanom

06 Sep, 09:38


+ የክፉ ቀን ‘ተመስገን’ +

አንዱ ሰው “የሰው ልጅ ሕይወት ውጣ ውረድ የበዛው ነው” ሲሉት “የኔ ሕይወት ታዲያ ምነው ውረድ ብቻ ሆነብኝ? ውጣው የታለ?” አለ ይባላል። ይህ ሰው እውነት አለው። አንዳንዴ የሰው ልጅ በመከራ ተወልዶ፥ በመከራ ኖሮ፥ በመከራ ሲያልፍ እንመለከታለን። በሕይወታችን ውስጥ መከራቸው ከመብዛቱ የተነሣ “ምነው ባለፈላቸው” ብለን የምንለምንላቸው ሰዎች አይጠፉም። በዚህ ጊዜ ‘ብርቱ ትግል የሚሰጠው ለብርቱ ወታደር ነው’ የሚለውን እያሰብን እንጽናናለን። በእርግጥ ትግሉ የሚመጣው ከእግዚአብሔር ብቻ አይደለም፤ ይህንን ደግሞ ከኢዮብ ታሪክ በላይ የሚያስረዳ ላይኖር ይችላል።

ጻድቁ ኢዮብ ሰይጣን የሚቀናበት፥ ሰዎች ለመሆን የሚመኙት፥ እግዚአብሔር ደግሞ እጅግ የሚወድደው ሰው ነበር። ሰዎች የሌሎች ሰዎችን ሙገሳ በሚፈልጉበት ዓለም፥ ከፈጣሪው ዘንድ “በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹማና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም” (ኢዮ 1፡8) ተብሎ የተመሰከረለት ነው። ይህ መሆኑ ግን ከመከራ አልሸሸገውም። ከአሥር ሺህ በላይ የሆኑት ከብቶቹ የተወሰኑት ተማርከው፥ የተወሰኑት ተገድለው፥ የተቀሩት ደግሞ ከሰማይ በወረደ እሳት ተበልተው መጥፋታቸው ተነገረው። ሦስቱንም መርዶ የሰማው በተከታታይ ከመሆኑ የተነሳ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ‘እርሱም ገና ሲናገር ሳለ ሌላ መጥቶ እንዲህ አለው’ እያለ ተገልጿል። አንዳንድ መርዶ የቀደመውን መርዶ ሰምተህ እስክትጨርስ ስንኳን አይጠብቅህም። ኢዮብ ይህንን ሁሉ ሰምቶ መጮኽ ሳይጀምር ሌላው ደርሶ ልጆቹ የነበሩበት ቤት በድንገተኛ ነፋስ ተንዶ አሥሩም ልጆቹ እንደሞቱ ነገረው።

ይህ ሁሉ ሆኖበት ኢዮብ ምን አለ? መጎናጸፊያውን ቀድዶ፥ ራሱን ተላጭቶ፥ በምድር ተደፍቶ ሰግዶ “እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔር ነሣ፤ እግዚአብሔርም እንደ ፈቀደ ሆነ፤ የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን” (ኢዮ 1፡21) ብሎ እግዚአብሔርን አመሰገነ። ንብረቱን ሁሉ ያጣው ኢዮብ እግዚአብሔርን አከበረ! አሥር ልጆቹን በአንዴ የተነጠቀው በምድር ላይ ሰግዶ እግዚአብሔርን አመሰገነ!

ልጆቿን ሁሉ በማጣቷ “የወላድ መካን” የሆነችው የኢዮብ ሚስት ወደ ባሏ ስትመጣ ጤናውንም ሳይቀር አጥቶ ከራስ ጸጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ በቁስል ተሸፍኖ አገኘችው። ደህና መካሪ መስላ ‘እግዚአብሔርን ስደብና ሙት’ (ኢዮ 2፡10) አለችው። ብዙዎቻችን ቢሆን “እውነትሽን ነው! በጽድቅ ሆኜ በኖርኩ እንዴት እንዲህ ያደርገኛል!” ብለን ለስድፍ አፋችንን በከፈትን ነበር። ኢዮብ ግን ቀና ብሎ አይቷት “አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ!” ብሎ ገሰጻት። ከዚያም በኋላ ለሁላችንም ምክርና መጽናኛ የሚሆን ነገርን እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፥ ክፉውን ነገርስ አንታገሥምን?” (ኢዮ 2፡10)

ይህ ጥያቄ ለእኛም ነው። ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ከተቀበልን፥ ክፉውን አንታገሥምን? እግዚአብሔርን በሕይወታችን ውስጥ ባሉ ስኬቶች ብቻ መመዘን አይበቃንምን? እግዚአብሔር ቢከፋም ቢለማም፥ ቢደላም ቢጨንቅም የሚመለክ ታላቅ አምላክ አይደለምን?

እግዚአብሔርህ ሆይ፥ ለውጣውም ለውረዱም ተመስገን!

🖋 Fresenbet G.Y Adhanom

----------

የፌስቡክ ገጽ: https://lnkd.in/e2NNiGH4

ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett

ቲክቶክ: https://lnkd.in/eU7d2X_Q

Fresenbet G.Y Adhanom

19 Aug, 15:14


+ በሕጻን ሄቨን ጉዳይ ምን እናድርግ? + (አንዳንድ የመፍትሔ ሃሳቦች)

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጆሮን ጭው የሚያደርጉ፥ ሰውነትን የሚወሩ፥ 'አይ ሰው መሆኔ' የሚያስብሉ፥ በፍትሕ ሥርዓቱ ተስፋን የሚያስቆርጡ ዘግናኝ ወንጀሎች እየተበራከቱ መጥተዋል። የወንጀሎቹ ሰቅጣጭነት ሳያንስ፥ ሁሉም የአንድ ሳምንት አጀንዳ ከመሆን አለመዝለላቸው ደግሞ እጅጉን ያማል። "ፍትሕ" የሚለው ጩኸት ከሳምንት በላይ ሊዘል አለመቻሉ፥ ጥልቅ ማኅበረሰባዊ ልምሻ እያጠቃን መሆኑን አመላካች ነው። የዚህ ልምሻ ክትባትም ሆነ መድኃኒት በቶሎ ካልተገኘ መዘዙ አደገኛ ነው።

ከሰሞኑ የሕጻን ሄቨንን ጉዳይ ሰምቶ ያልታመመ ያለ አይመስለኝም። በግሌ የእናቷን ቃለ መጠይቅ ስንኳ ጨርሼ መስማት አልቻልኩም። ለሚስቴ ባል፥ ለእህቶቼ ወንድም፥ ለልጄ አባት እንደመሆኔ የእናቷን ሕመም ለመጋራት "በእኔስ ቤተሰብ ደርሶ ቢሆን?" ብሎ ራስን መጠየቅ ብቻ በቂ ነው። በእውነቱ ይህንን ማሰብ እስከማልችል ድረስ የሚዘገንን ነው። የሕጻን ሄቨንን ጉዳይ ግን የአንድ አረመኔ ጉዳይ ብቻ አድርገን ካሰብነው ተሳስተናል። ሥልጣንን ለወንጀለኛ ሽፋን መስጫ የሚጠቀሙ ባለሥልጣናትን፥ ማስረጃ ለማጥፋት የሚሞክሩ የጤና ባለሞያዎችን፥ ወንጀልን የሚያደባብሱ የፖሊስ አባላትን፥ ለገዳይ የሚወግኑ ሴቶችን ያየንበት ነው። ይህ ጉዳይ በዳይ እየተዝናና ተበዳይ ሲሳደድ ያየንበት የፍትሕ ሥርዓት እንቆቅልሽ ነው።

በእርግጥ ፍትሕን መጠየቃችን መልካም ነው። ከዚያ ባለፈ ግን “ሌላስ ምን ማድረግ እንችላለን?" ብለንም መጠየቅ ይኖርብናል። በዚህ ደረጃ ሁለት መፍትሔ ይታየኛል። አንድኛው ወንጀለኛው ተገቢውም ቅጣት እንዲያገኝ የማድረጉ ጉዳይ ሲሆን፥ ሁለተኛው ደግሞ የሕጻን ሄቨን እናትን የመደገፉ ጉዳይ ነው።

1) የሕጻን ሄቨን ገዳይ ጉዳይ በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይ ነው። ከዚህ ባለፈ የሴቶች የሕግ ባለሞያዎች ማኅበር እና የሕጻናትና ሴቶች ጉዳይም ያለበትን የሕግ ሁኔታ እየተከታተሉ መሆናቸውን ሰምተናል። ይህ አበረታች ነው። ሆኖም ግን ጉዳዩ እንደሌሎች መሰል ክሶች በሕዝብ ዘንድ ተረሳስቶ እንዳይቀር ከፍተኛ ክትትልን ይጠይቃል። ከዚያ ባለፈ ደግሞ እውነተኛው የፍትሕ ባለቤት እግዚአብሔር ለወንጀሉ ፍትሕን፥ ለሕጻኗ የነፍስ እረፍትን፥ ለእናቷ መጽናናትን ይሰጥ ዘንድ ሁላችንም እንጸልይ። ከዚህ በተጨማሪ ግን ተከሳሹ ከፍተኛውን ቅጣት እንዲያገኝ እየተሰበሰበ ያለ ፐቲሽን ስላለ፥ እርሱን በመፈረም የበኩላችንን ማድረግ እንችላለን። የፕቲሽኑ ሊንክ የሚከተለው ነው፦ https://chng.it/8VRtxHHYZH

2) ሁለተኛው ጉዳይ ለሕጻን ሄቨን እናት የሚደረገውን ድጋፍ በተመለከተ ነው። በማኅበረሰብ ደረጃ በዚህ ጉዳይ ላይ የበለጠ ለውጥ ማምጣት የምንችል ይመስለኛል። በአሁኑ ሰዓት ለእናቷ የሥነ ልቡና እና የገንዘብ ድጋፍ እጅጉን ያስፈልጋል። የሥነ ልቡና ድጋፉን በተመለከተ በተለይም ለሥነ ልቡና ቁስል እና ጥልቅ ሐዘን (Trauma and Grief) በሚሰጥ የሥነልቡና ሕክምና ላይ ልምድ ያላችሁ የሥነ ልቡና ባለሞያዎች አስፈላጊውን የሥነ ልቡና ድጋፍ ብታደርጉላት መልካም ነው። እናትየዋ በግፍ ከሥራዋ ተፈናቅላ ችግር ላይ እንደመሆኗ መጠን ደግሞ፥ የገንዘብ ድጋፉ እጅግ ወሳኝ ነው። ይህንን በተመለከተ ደግሞ ሁላችንም የተቻለንን ድጋፍ በእናቷ የግል አካውንት ማድረግ እንችላለን። የንግድ ባንክ አካውንቷ የሚከተለው ነው፦ Abekyelesh Adeba Kassa – 1000177318934

እግዚአብሔር ፍርዱን ይስጥ!
የሕጻኗንም ነፍስ በግፍ ከተገደሉ ሕጻናት ነፍስ ጋር በገነት ይደምርልን!
ለእናቷም እውነተኛው አጽናኝ መንፈስ መጽናናትን ይስጥልን!

🖋 Fresenbet G.Y Adhanom

----------

የፌስቡክ ገጽ: https://lnkd.in/e2NNiGH4

ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett

ቲክቶክ: https://lnkd.in/eU7d2X_Q

Fresenbet G.Y Adhanom

29 Jul, 11:21


+• ደፋር ሟች እና ፈሪ ገዳይ •+

የብዙ ሰማዕታት አሟሟት የዓለምን ታሪክ ገልብጦ አሳይቶናል። በዓለም ታሪክ የሚታወቀው ሟቾች ሲሸሹ እና በፍርሃት ሲቅበዘበዙ፥ ገዳዮች ደግሞ በድፍረት ሲንጎማለሉ እና ሲኩራሩ ነው። የሰማዕታት ሞት ግን ይለያል። ሟች ሳይፈራ ወደ ሞት ሲገሰግስ፥ ገዳይ ወይም አስገዳይ ደግሞ በሟች ላይ የሚያየው ድፍረት ሲያስፈራው እና ሲያስደነግጠው የምናየው የሰማዕታትን ልዩ ሞት ስንመለከት ነው። አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም “አብ፥ ወልድ፥ መንፈስ ቅዱስ ያስጨክናሉ” የሚለንን በሰማዕታት ድፍረት ውስጥ እናየዋለን። ዛሬ የምናስታውሳቸው ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስም ወደ ሞት ሲገሰግሱ ያልፈሩ ሥላሴ ያስጨከኗቸው ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሰማዕት ናቸው።

ጣሊያን አቡነ ጴጥሮስን ሲከስሳቸው “ሕዝብ ቀስቅሰዋል፥ ራስዎም ዐምጸዋል፥ ሌሎችም እንዲያምጹ አድርገዋል” በማለት ነበረ። ይህንን አስታኮም ብጹዕ አቡነ ቄርሎስ ስንኳ ጣሊያንን ሲቀበሉ እርሳቸው ለምን እንዳመጹ ተጠየቁ። ሰማዕቱ ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስም “አቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን የሚገዳቸው ነገር የለም። እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ። ኃላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ። ስለዚህም ስለ አገሬና ስለ ቤተክርስቲያኔ እቆረቆራለሁ። ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም። ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ። እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ። ግን ተከታዮቼን አትንኩ።” በማለት ተናግረዋል።

ፓጃሌ የተባለ የኮርየሬ ኬላሴራ ጋዜጣ ወኪል ስለ ሰማዕቱ ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ ሲጽፍ፤ ከመሞታቸው በፊት መስቀላቸውን አውጥተው ሕዝቡን እንደባረኩ ይነግረናል። የሞታቸው ሰዓት መድረሱን አውቀው ሰዓታቸውን አውጥተው ሲመለከቱም ሰዓቱ “5፡15” ይል ነበር። ይህ ሁሉ ሲሆን ምንም ፍርሃት እንዳልታየባቸው፤ በተቃራኒው ግን የሞት ፍርዳቸውን ያነብብ የነበረው ጣሊያናዊ ዳኛ ግን ይንቀጠቀጥ እንደነበረ ዘግቧል። የአቡነ ጴጥሮስን የሞት ፍርድ ለማስፈጸም የተኮሱት ወታደሮች በስምንት ጥይት ቢመቷቸውም ስላልሞቱ ሌላ ወታደር የራስ ቅላቸውን በሽጉጥ መትቶ ገድሏቸዋል።

የአባታችን የሰማዕቱ የቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ በረከት በሁላችን ላይ ይደር!


🖋 Fresenbet G.Y Adhanom

----------

የፌስቡክ ገጽ: https://lnkd.in/e2NNiGH4

ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett

ቲክቶክ: https://lnkd.in/eU7d2X_Q

Fresenbet G.Y Adhanom

25 Jul, 06:45


+ ሸክላ ሠሪ +

በድሮ ዘመን ነው - መምህር አልዓዛር የተሰኙ አንድ የአይሁድ መምህር በአህያቸው ላይ ኾነው ከትምህርት ቤታቸው ወደ ሰፈራቸው እየተመለሱ ነው። በእለቱ በዛ ያለ የእግዚአብሔር ቃል ስላጠኑ ቀናቸው ብሩህ ኾኖላቸው ፊታቸው ፈካ ብሏል። በጉዞ ላይ እያሉ ግን አንድ ሰው ቀረበና፡ “መምህር ሆይ፥ ሰላም ለእርስዎ ይኹን!” ብሎ ሰላምታ ሰጣቸው። ከአህያቸው ላይ ሆነው ቁልቁል አዩትና ፊታቸው ጠቆረ። “አንተ የማትረባ! መልክህ ምንድር ነው? ለምንድር ነው እንዲህ መልከ ጥፉ የኾንከው? የአንተ አካባቢ ሰዎች ሁሉ እንዳንተው መልከ ጥፉ ናቸው እንዴ?” አሉት። ይህም ሰው “እርሱን አላውቅም። ባይኾን የሠራኝን ሄደው ‘የሠራኸው ሸክላ እንዴት መልከ ጥፉ ነው!’ ብለው ይንገሩት።” አላቸው።

መምህር አልዓዛርም ሰውየውን በመልኩ ብቻ ክፉ ንግግር እንደተናገሩት አስተዋሉና ከአህያቸው ወረዱ፤ በፊቱም ተደፍተው “እባክህ ይቅር በለኝ” ብለው ለመኑት። እርሱ ግን “እርስዎ ሄደው ለሠራኝ ‘የሠራኸው ሸክላ መልከ ጥፉ ነው!’ ብለው እስካልነገሩት ድረስ ይቅርታ አላደርግልዎትም አላቸው።

መምህር አልዓዛር ሰውየውን እየተከተሉ ይቅርታ እየጠየቁት ከሰፈራቸው ደረሱ። የሰፈሩ ሰው ኹሉም እየወጣ “እንኳን ደህና መጡ፥ መምህር ሆይ” እያሉ ሰላምታ ይሰጡዋቸው ጀመር። ሰውየውም “ማንን ነው መምህር ሆይ የምትሉት?” ብሎ ጠየቀ። ሰዎቹም “እርሳቸውን ነዋ! ታላቅ የኦሪት መምህር ናቸውኮ!” ብለው መለሱለት። እርሱም “እርሳቸው የኦሪት መምህር ከኾኑ፥ እንግዲያውስ ለዘለዓለም በእስራኤል ምድር እንደ እርሳቸው አይነት መምህር አይኑር!” ብሎ ተናገረ። የሰፈራቸው ሰዎችም ደንግጠው ለምን እንዲህ እንዳለ ጠየቁት፤ እርሱም የተፈጠረውን ነገራቸው። ሰዎቹም በማዘን “ቢሆንም ይቅርታ ጠይቀዋል፤ ስለዚህ ይቅር በላቸው። እርሳቸው ታላቅ የኦሪት ምሁር ናቸው።” አሉት። ሰውየውም “ከአሁን በኋላ እንዲህ አይነት ነገር እንደማያደርጉ ቃል ከገቡ፥ ለእናንተ ስል ይቅርታ አደርጋላቸዋለሁ።” በማለት ለመምህሩ ይቅርታ አደረገላቸው።

በእድሜ ዘመናችን ‘ሲያስጠላ፥ ስታስጠላ’ ብለን ያሸማቀቅናቸው ምን ያህል ይኾኑ? ለአንዳንድ ሰው ምርቃት እስኪመስል ድረስ እነዚህ ቃላት ከአንደበቱ አይለዩትም። እግዚአብሔር አስውቦ የሠራውን ሸክላ ለመንቀፍ የበቃነው፥ እኛም ‘ሸክላነታችንን’ ስለምንረሳ ነው። ሸክላነቱን ያልረሳው የዘለሰኛ ገጣሚ፦

‘እዚያ ዳር ያለች ሸክላ ሠሪ፥ ድሃ ናት አሉ ጦም አዳሪ
ማን አስተማራት ጥበቡን፥ ገል ዐፈር መኾኑን!’

… ብሎ አዚሞ ነበር። አንዳንዴ ኹሉ ሲሰምርልን ሥልጣን የሚሻር፥ ሀብት የሚጠፋ፥ መልክ የሚጠወልግ አይመስለንም። አንዳንዶች ጸጉራቸው መመለጥ ሲጀምር ‘ጸጉርኮ ባዳ ነው’ ይላሉ። ጸጉር ብቻ ሳይሆን አሉን የምንላቸው ሁሉ ባዳ ናቸው። በዚህ ሁሉ ውስጥ ጸንቶ የሚቀረው ‘ሸክላነታችን’ ነው፤ እርሱም ወደ መጣንበት ዐፈር እስክንመለስ ድረስ።

ሁላችንም ከአፈር የተሰራን ሸክላ ነንና፤ ሸክላውን በመልኩ ስንሳደብ፥ ሸክላ ሰሪውን እየነቀፍን መኾኑን አንርሳ!

🖋 Fresenbet G.Y Adhanom
---------
የፌስቡክ ገጽ: https://www.facebook.com/fre.asalib

ቴሌግራም: https://t.me/fresenbett

ሊንክድኢን፡ https://www.linkedin.com/in/fresenbet-g-y-adhanom-7b316b312/

ቲክቶክ: https://www.tiktok.com/@fr3senbet?_t=8eAM1NzgeQw&_r=1

Fresenbet G.Y Adhanom

22 Jul, 12:52


በአካባቢው 18 ምእመናን ብቻ የሚኖሩበትን የዋሽወራ ቅዱስ ቂርቆስ እና እናቱ ኢየሉጣ ቤተ ክርስቲያን ታግዙ ዘንድ የበረከት ጥሪ ቀርቦላችኋል።

Fresenbet G.Y Adhanom

22 Jul, 12:50


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!


ውድ የልዑል እግዚአብሔር ቤተሰቦች እንደምን ሰነበታችሁ እንኳን ለአፈ በረከት ለቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ የእረፍት በዓልና ለሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስና የእናቱ የቅድስት ኢየሉጣ ወርሃዊ መታሰቢያ በዓል አደረሳችሁ🙏🙏🙏


ከሥር በምስሉ ላይ የምትመለከቱት ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በጉራጌ ሀገረ ስብከት በምሁርና አክሊል ወረዳ ቤተ ክህነት በአጣጥ ቀበሌ በልዩ ስሙ የዋሽወራ ቅዱስ ቂርቆስ እና የእናቱ የቅድስት ኢየሉጣ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን በአካባቢው 18 ምእመናት ቢቻ ያሉበት አጥቢያ ነው ታዲያ አሁን እየተገለገሉበት ያለው ቤተ መቅደስ ከእርጅናና በክረምት ወቅት ከሚደርስበት የጎርፍ ጥቃት እየተሸረሸረና እየተቦረቦረ ቤተ መቅደሱ ሊፈርስ ከጫፍ ድርሷል ማለት ይቻላል ታዲያ ይህን ታሳቢ በማድረግ በአካባቢው በአሉት ምእመናት ተነሳሽነት ከሥር በምስሉ የምታዩትን ቤተ መቅደስ በአስቸኳይ እየተሰራ ይገኛል ግን በአጥቢያው ያሉት ምእመናት ከአቅማቸው በላይ እያደረጉ ይገኛሉ ግን አሁን ላይ የማቴሪያል እጥረት አጋጥሟቸዋል ይህን ደግሞ ለማድረግ ከአቅማቸው በላይ ስለሆነ የእኛን የሁሉም ኦርቶዶክሳውያን እገዛ ይፈልጋሉ ታዲያ የሁላችንም ግዴታ ነው ይህን ቤተ መቅደስ ማነጽ ምክንያቱም የኃያሉ የልዑል እግዚአብሔር ማደሪያ ስለሆነ የሁላችንም በአርባና በሰማንያ ቀን የሥላሴን ልጅነት የምናገኝበት ስለሆነ ዘወትር በጸሎት በቅዳሴ እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት ስለሆነ ቤተሰብ እንኳን እንመስርት ብንል የጋቢቻ ሥርዓታችን የምንፈጽምበት ስለሆነ በነፍስም በሥጋም ብንታመም የምንፈወስበት ቤት ስለሆነ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን የምንቀበልበት ስለሆነ እንዲሁ ከሥጋ እረፍታችን በምናርፍበት ጊዜ እንኳን ጸሎተ ፍትሐት ተፈጽሞልን የሥጋችን ማርፊያ ስለሆነ ብናዝን ብንደሰት መጽናኛችን ማመስገኛችን ስለሆነ ይህ ሁሉ አገልግሎትና ፀጋ የምናገኘው የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ስናንጽ ነውና ሁላችንም የአቅማችንን በመርዳት ይህን ቤተ መቅደስ እናስፈጽም እግዚአብሔር ዋጋ ሲሰጥ ብዙ የሰጠ ትንሽ የሰጠ አይልም የሁላችንም ዋጋ በሰማይ እኩል ነው ስለዚህ የአቅማችንን እንስጥና ቤቱን እናንጽ እያልን በአምላከ ቅዱስ ቂርቆስና በቅድስት ኢየሉጣ ስም እናሳስባለን🙏🙏🙏


አሁን ላይ የሚያስፈልጉ ማቴሪያሎች

፩, ድንጋይ የውሃ ልኩ ማንሺያ የሚሆን
፪, ሲሚንቶ በጣም ፈተና የሆነ ነገር ነው።
፫, በርና መስኮት
፬, ቀለም እነዚህ ዋንኞችሁ ናቸው በዚህ ሁሉ በረከት መሳተፍ ያስፈልጋል ሌላው ለጸሎትና ለልዩ ልዩ አገልገሎቶች የሚውሉ ንዋየ ቅዱሳት እጣን፣ዘቢብ፣ጧፍና ሻማ ድጋፍ ማድረግ ይቻላል።


👉ድጋፍ የምታድርጉበት አካውንት በቤተ ክርስቲያኑ ስም የተከፈተ ያለው ንብ ባንክ ነው ቁጥሩም፦ 7000028803977 ነው።
ምን አልባት በንግድ ባንክ መላክ የምትፈልጉ የግለሰብ አካውንት አለ እሱም፦ 1000535092797 ዮሐንስ ጌቱ በዚህም ገቢ ማድረግ ይቻላል አደራውን ማድረስ ስለምችል ነው ወገኖቼ ታዲያ ገቢ ከአደረጋችሁ በኋላ እስሊፑን ላኩልን የግድ ለማድረስ ማወቅ ያስፈልጋል ማለት ነው።

ለበለጠ መረጃና ገቢ ማድረጋችሁን ለማሳወቅ፦ 0996990485 ቀሲስ ኃይለ ቂርቆስ የቤተ ክርስቲያኑ አለቃ።

👉0945173873 ዲያቆን በረከት ሞገስ አስተባባሪና አገልጋይ ነው።

👉0937076125፣0912241064 ዮሐንስ ጌቱ በእነዚህ የስልክ አድራሻዎች መረጃ መጠየቅም መስጠትም ትችላላችሁ ማለት ነው።


ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር ይሁን!

5,992

subscribers

93

photos

1

videos