ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት

@finottebiirhan


የአቃቂ መንበረ ሕይወት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት ለማንኛውም ጥያቄ
@Finotebrhan

ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት

22 Oct, 10:28


የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አጀንዳ አርቃቂ ብፁዓን አባቶችን ሰየመ።


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የጥቅምት 2017 ዓ.ም ምልዓተ ጉባኤ አጀንዳ አርቃቂ ብፁዓን አባቶችን ሰይሟል።

ምልዓተ ጉባኤው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የመክፈቻ መልዕክት ዛሬ ጠዋት መጀመሩ የሚታወቅ ሲሆን ከቅዱስነታቸው የመክፈቻ መልእክት በኋላም የመወያያ አጀንዳ ቀርጸው የሚያቀርቡ ሰባት ሊቃነ ጳጳሳትን ነው የሰየመው።

በዚህም መሰረት

1.ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ
2.ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ
3.ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ
4.ብፁዕ አቡነ ማርቆስ (ዘስያትል)
5.ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ
6.ብፁዕ አቡነ  ኤጲፋንዮስ
7.ብፁዕ አቡነ ኤልሣዕ የተመረጡ ሲሆን አጀንዳ የማርቀቅ ተግባራቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ የሚያቀርቡትን ረቂቅ አጀንዳ ከመረመረና ማስተካከያ ካደረገበት በኋላ የጸደቀውን አጀንዳ መሰረት በማድረግ በቅደም ተከተል እየተወያየ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።

ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት

22 Oct, 07:44


"እኛም በዚህ ዓለም የእግዚአብሔር ወኪሎች ስለሆንን ቢሰሙንም ባይሰሙንም ዓለማውያን ሹማምንትን  የማስተማርና የመምከር ኃላፊነት አለብን" ቅዱስ ፓትርያርኩ


የ2017 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመጀመሪያ መደበኛ ጉባኤውን በዛሬው ዕለት በመንበረ ፓትርያርክ የቅዱስ ሲኖዶስ መሰብሰቢያ አዳራሽ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት መልእክት ተከፍቷል።

ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው በዛሬው ዕለት መደበኛና አመታዊ ጉባኤው መጀመሩን ያበሠሩ ሲሆን አክለውም ይህ ጉባኤ በሀገር ውስጥና በውጭ ለሚገኙና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን መሪና ጠባቂ ነው፤ ከዚያም ባሻገር እንደ ቃሉ እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ቃሉን በመስበክ ፍጥረተ ሰብእን በሙሉ የመጥራት ተልእኮ ለእኛ የተሰጠ የቤት ስራ ነው ብለዋል።

ሁላችን እንደምንገነዘበው አሁን የምንገኝበት ዘመን የጸላኤ ሠናያት መንፈስ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ከምንም ጊዜ በበለጠ ጦሩን ሰብቆ የተነሣበት ጊዜ ነው፤ አሁን ያለው ዓለም በሀገራችንም ሆነ በሌላው ክፍለ ዓለም ላሉ ኦርቶዶክሳውያን ከባድ ፈተና ተደቅኖብናል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው አክለው ምንም ቢሆን የተቀበልነው ኃላፊነት የእግዚአብሔር ነውና በሚሰራው ሁሉ በሿሚው አምላክ ከመጠየቅ አያመልጥ ፤ እኛም በዚህ ዓለም የእግዚአብሔር ወኪሎች ስለሆንን ቢሰሙንም ባይሰሙንም ዓለማውያን ሹማምንትን  የማስተማርና የመምከር ኃላፊነት አለብን፡፡ ይህ የሁለታችን ኃላፊነት እንደ እግዚብሔር ፈቃድ ስንፈጽም የሕዝብ ሰላምና በረከት፣ ፍቅና አንድነት፣ ዕድገትና ልማት በአስተማማኝ ሁኔታ ይረጋገጣል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ በሀገራችንም ሆነ በአካባቢያችን እየሆነ ያለው ይህ አይደለም፤ አለመግባባት በዝቶአል፣ ማኵረፍና መቀያየም ሰፍቶአል፤ ነገሩ ሁሉ ግራ የሚያጋባና የተመሰቃቀለ ሆኖ ይታያል፡፡ ችግሩ ከሕዝብ አልፎ የአምልኮ ስፍራዎችንና የአምልኮው ፈጻሚዎችን ዒላማ ያደረገ እግዚአብሔርን መዳፈር እየተለመደ መጥቶአል፤ ይህ ለአንድ ሀገር ወይም ሕዝብ የውድቀት ምክንያት ከሚሆን በቀር ከቶውኑም የዕድገት ምልክት ሊሆን አይችልም ብለዋል።

ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ ይህ ክፉ ድርጊት እየተፈጸመ ያለው በእኛው ልጆች በኢትዮጵያውያን መሆኑ ነው፤ ስለሆነም በከተማም፣ በጫካም፣ በገጠርም በየትኛውም ስፍራ የምትገኙ ልጆቻችን ምንም ይሁን ምን ሀገርንና ሕዝብን ከመጉዳት ተቆጠቡ፡፡ በተለይም ከቤተ ክርስቲያንና ከሀገር እንደዚሁም ሕዝቡን ከሚያገለግሉ ካህናትና ሲቪል ሰራተኞች እባካችሁ እጃችሁን አንሡ፤ ቤተ ክርስቲያን እኮ የእናንተና የሕዝቡ ሁሉ እናት ናት፤ በእናታችሁ ላይ መጨከንን እንዴት ተለማመዳችሁት? አሁንም ንስሐ ግቡ ያለፈው ይበቃል በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመጨረሻም በእግዚአብሔር ስም ለመላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንና ልጆቻችን የምናስተላፈው ወቅታዊ መልእክታችን ይህ ነው፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ አገልግሎትና የስራ አፈጻጸም ላይ ለመምከርና ለመወሰን ኃላፊነት ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ በዛሬው ዕለት መደበኛና ዓመታዊ ጉባኤውን የጀመረ መሆኑን ለሕዝበ ክርስቲያኑ እናበስራለን በማለት የጉባኤውን መጀመር አስታውቀዋል።

ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት

21 Oct, 09:01


የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በነገው ዕለት ይጀመራል !

ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የጥቅምት 2017 ዓ.ም  ምልዓተ ጉባኤ በነገው ዕለት በጽርሐ መንበረ ፓትርያርክ ይጀመራል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜ ጥቅምት 12 እና በዓለ ትንሣኤ በዋለ በ25ተኛው ቀን ምልዓተ ጉባኤውን የሚያከናውን መሆኑ ይታወቃል።

ምልዓተ ጉባኤው በዛሬው ዕለት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በሚደረገው የጸሎት መርሐግብር የሚከፈት ሲሆን ከነገ ጀምሮ ቅዱስ ሲኖዶስ በልዩ ልዩ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያንና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ  እንደሚወያይ ይጠበቃል።

ፍኖተ ብርሃን ሰንበት ትምህርት ቤት

21 Oct, 07:40


አጣሪ ኮሚቴው ሪፖርቱን ለቋሚ ሲኖዶስ አቀረበ።

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተከስተዋል የተባሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በተመለከተ በዝርዝር በማጣራት ከመፍትሔ ሐሳብ ጭምር እንደያቀርብ የተሰየመው አጣሪ ኮሚቴ ባለፉት አሥራ አምስት ቀናት ሲያከናውናቸው የሰነበተውን የማጣራት ሥራዎች በማስመልከት ያዘጋጀውን ሪፖርት ዛሬ ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻ ፲ወ፯ ዓ.ም ለቋሚ ሲኖዶስ አቅርቧል።

አጣሪ ኮሚቴው አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአካል ተገኝቶ ማጣራት እንዳይችል።የተከለከለ መሆኑን በመጥቀስ መረጃውን ለሣሰባሰብ ይቻል ዘንድ ተበዳዮች በስልክ፣በቴሌጌራምና በዋትስ አፕ መልዕክቶች፣በአካል በመቅረብ፣በሰነድ ማስረጃ በማስደገፍ፣በድምጽና 3:30 ርዝማኔ ባለው በቪዲዮ በተቀረጸ ማስረጃ ጭምር መረጃዎችን ማሰባሰቡን፣መተንተኑን፣
ማደራጀቱንና ጥቅም ላይ ማዋሉን ገልጿል።

በሪፖርቱም ከመልካም አስተዳደርና ከብልሹ አሰራር ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች በማስረጃ ተደግፈው የቀረቡ ሲሆን በማጣራት ስራው የተረጋገጡ ጉድለቶችንና ጥፋቶችን መሰረት በማድረግም በጊዜያዊነትና በቋሚነት ችግሮቹን ለመፍታትና የካህናትና የአገልጋዮችን ቅሬታ ዘላቂነት ሊፈቱ ይችላሉ ተብለው የቀረቡ  በሰባት ነጥቦች የተተነተኑ  የመፍትሔ ሐሳቦችና በዘጠኝ ነጥቦች የተተነተኑ ችግሮቹን በዘላቂነት ሊፈቱ ይችላሉ ተብሎ የታመነባቸው የመፍትሔ ሐሳቦችን አቅርቧል።ይኸው የጥናት
ሰነድ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ቀርቦ ውሳኔ የሚሰጥበት ይሆናል።